ወደትግራይ ክልል፤ የመገስገስ አስፈላጊነት!! – ቴዎድሮስ ጌታቸው|ድሬዳዋ

መነሻ!

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት የሚመራው ‹‹ጥምር ኃይል›› ወደትግራይ ክልል /መቀሌ/ እየገሰገሰ ይገኛል፤ ይህን ግስጋሴ በሚያደርግበት በዚህ ወቅት፣ በዚህ እለት እና ሰዓት፤ እኛ ደግሞ ‹‹ትግራይ ክልል የማን ናት?›› የሚል ጥያቄ እናነሳለን፤ ይህን መነሻ አድርገንም፤ ትግራይ! የኩናማ፣ የኢሮብ፣ የሳሆ፣ የአንደርቴዎች ወይስ የትግሬ (ተጋሩ) ማሕበረሰብ? እያልን አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ ምክንያቱም! ይህን ጥያቄ መመለስ ወደትግራይ ክልል የሚደረገውን ግስጋሴ፤ ከግስጋሴውም በዃላ በክልሉ ለሚከናወነው ‹‹ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ››፤ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት በመኖሩ ነው፡፡

ትግራይን ምናልባት ‹‹በትግራይ የሚኖሩ ማሕበረሰቦች ክልል ናት›› በማለት! ቀለል አድርገን ለመመለስ እንሞክር ይሆናል፤ ነገር ግን! በትግራይ ክልል እጣ-ፈንታ የሚወስነው፣ እንዳሻው የሚያዘው፣ የሚፈልጠው፣ የሚቆርጠው፣ በዕብሪት የሚያብደውና የሚቦርቀው! ማን ነው? ብለን ‹‹በማስተዋል እና በብርቱ›› መጠየቅ ስንጀምር፤ ቀደም ሲል እንደዘበት የሰጠነውን መልሳችንን እንደገለባ ቀልሎ የሚያሳይብን ያደርገዋል፡፡ ምን ማለት ነው?

ያልተገባ ውክልና!

ባለፉት 27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን! በህ.ወ.ሓ.ት. አማካኝነት የትግራይ ክልልን ለትግሬዎች (ተጋሩ) ሙሉ ውክልናና ኃላፊነት ለመስጠት የተደረገውን ሙከራ! እንደሕዝብ በዝምታ መመልከታችን፤ ከባድ ስህት ውስጥ ጥሎናል፡፡ በርግጥ! ይህ ሊሆን የቻለው ህ.ወ.ሓ.ት. የነበረውን የክልል እና የፌዴራል ሥልጣን መከታ በማድረግ! በፈጠረው ‹‹ግርግር እና ወከባ›› ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ‹‹ያለፈው አልፏል›› ብለን ብንተው እንኳ! ከዚህ በዃላ በትግራይ ክልል የሚገኙ ማሕበረሰቦች ውስጥ! ማንኛውም ‹‹ያልተገባ ውክልና›› እንዲኖር መፍቀድ! በቀጣይ ለብዙ ዘመናት ‹‹ያልተገባ ዋጋ›› እንደሚያስከፍለን መረዳት ተገቢ ነው፡፡

ከዚህ በዃላ የምንፈፅመው ስህተት! ‹‹ያልተገባ ዋጋ›› ከማስከፈሉ ባለፈ፤ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን፤ ጥንታዊ ባለታሪኮችና ክልልሉን የቆረቆሩ፤ በክልሉ የሚገኙና የራሳቸው ማንነት ያላቸውን ማሕበበረሰቦች፤ እውቅና መንፈግ ጭምር ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ ‹‹ብርቱ ስህተት›› ሆኖ! የታሪክ ተወቃሽነትን ይወልዳል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሱዳን ስደተኛ ካምፕ የትህነግ ወታደራዊ ምልመላ ቀጥሏል! (በጌታቸው ሽፈራው)

ስለዚህ! በትግራይ ክልል የሚገኙትን ብሔር ብሄረሰቦች፤ በትግራይ ክልል እና በኢትዮጵያ ጉዳይ፤ ከሌሎች ማሕበረሰቦች ጋር በጋራ የሚጎናፀፉትን መብቶቻቸውንና የመወሰን አቅማቸውን፤ አፅድቀንና ወስነን፤ ማለትም በትግራይ ክልል ውስጥ አሁን የሚገኘውን፤ ‹‹ያልተገባ ክልላዊ የሕዝብ ውክልና›› በተገቢ ውክልና በመተካት፤ የውስጥ ጦርነቱን ማጠናቀቅ ይኖርብናል፡፡

ይህ ተጠባቂና ተገቢ ተግባር! አሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት. ‹‹ለተጋሩዎች እና ለትግራይ ክልል ብቸኛ ተወካይ ነኝ›› በሚል፤ በተቀሩት የክልሉ አባላት ላይ የሚያደርሰውን ጭቆና ከማስቀረቱ ባሻገር፤ በቀጣይ በፅንፈኛውና አሸባሪው ቡድን አማካኝነት፤ በክልሎች ላይ የሚፈፀመውን የሽብርና የጦርነት ትንኮሳን ማስቀረት ያስችላል፡፡ በመሆኑም! በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት የሚመራውና ወደትግራይ እየገሰገሰ የሚገኘው የጦር ኃይል፤ መቀሌን ከመቆጣጠሩ አስቀድሞ! መንግስት በትግራይ ክልል የሚፈፅማቸውን ‹‹ተጠባቂ ግቦች››፤ ከወዲሁ ግልፅ ያደርጋል /ያስተዋውቃል/ ተብሎ ይታመናል፡፡

 

ተጠባቂ ግቦች!

የህ.ወ.ሓ.ት. የሽብር ቡድን! በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት በአሸባሪነት የተፈረጀና በወንጀኛነቱም የሚፈለግ ቡድን እንደመሆኑ፤ በሀምሌ 7/2013 በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር በድጋሚ የቀረበው ሀገራዊ ህልውናን የመታደግ ጥሪ፤ አሸባሪውን ህ.ወ.ሓ.ት. ጨምሮ ተባባሪ የሽብር ቡድኖቹን፤ በቁጥጥር ስር የማድረግና ሕግ ፊት የማቅብ፤ እንዲሁም የሽብር ቡድኑን እስከማክሰም ድረስ የዘለቀ ኦፕሬሽን ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማስቻል፡፡

በጫጫታ፣ በወከባና በተለያዩ መንገዶች፤ የትግራይ ክልል የአሸባሪው ህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን እና የትግሬዎች ክልል ብቻ እንደሆነ ተደርጎ፤ የሰረፀውን ‹‹የተሳሳተ ትርክት›› ለማስቆም፤ በማይቋረጥና ተከታታይነት ባለው ፕሮፓጋንዳ፤ ትግራይ ክልል የሳሆ፣ የኢሮብ፣ የኩናማ፣ የአጋመ፤ እንዲሁም ሌላ ማንነት ያላቸው ማሕበረሰቦች ክልል መሆኗን ተቀባይነት ማስገኘት፡፡

መንግስት በትግራይ ክልል ሕጋዊነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ፤ በክልሉም ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የያዘውን አቋሙንና ግፊቱን በማጠናከር፤ የክልሉ ባለቤት የሆኑትን ማለትም የሳሆ፣ የኢሮብ፣ የኩናማ፣ የአጋመና ሌላ ማንነት ያላቸውን ብሄር ብሄረሰቦች፤ በክልሉ ምክር ቤት ተገቢውን ውክልና እንዲያገኙ ማደራጀት፤ እንዲሁም እነዚህ ብሄረሰቦች ጥምረት ፈጥረው ክልሉን፤ ከትግሬዎች /ተጋሩዎች/ ጋር በእኩልነት ማስተዳደር እንዲችሉ፤ ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ ክትትልና እገዛ ማድረግ፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት በትግራይ ክልል እውን የሚያደርጋቸው! ‹‹ተጠባቂ ግቦች›› ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሁለት ዙር የሰለጠኑ 235 የድረ ገፅ መረጃ ማዛባት የሚችሉ ፕሮፓጋንዲስቶች በስራ ላይ መሆናቸው ታወቀ፡፡

ቀጭን መጠቅለያ!

ልብ እንበል! ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግስት እና ከቁርጥ ቀን ልጆቻችን የሚጠበቁ፤ እነዚህ ቁልፍ ተግባሮች!! የዛሬ 125 ዓመታት ማለትም በ1888፤ ዓለም ላይ በኃይል ሰፍኖ የነበረውን የነጭ የበላይነት መንፈስ ለማስቆም፤ አያት ቅድመ-አያቶቻችን በአድዋ የፈፀሙትን አፍሪካዊ ጀብድ፤ እኛ የልጅ ልጆቻቸው ‹‹በተጋድሎ ቦታቸው አድዋ ተገኝተን ለማሰብ››፤ ቪዛ ለመጠየቅ እንድንገደድ የሚያደርገውን እና በኢትዮጵያ ቀጣይ ትውልድ ላይ የተቃጣውን! ‹‹አደገኛውን ስውር ሤራ›› የሚያከሽፉ ናቸው፡፡ እንዲሁም አሸባሪውን ቡድን! የውጭ ኃይሎችን እኩይ ስትራቴጂ ከማስፈፀም ጉዞው የሚያናጥቡት ይሆናሉ፡፡

ወደትግራይ ክልል የመገስገስ አስፈላጊነት! አሸባሪውን የህ.ወ.ሓ.ት. ቡድን ትጥቅ የማስፈታት ጭምር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ትጥቅ ማስፈታት! ቀጣይ አይቀሬ በሆነው ከጋላቢው ጋር የመፋጠጥ ጉዞ፤ ወይም ‹‹ቀጣዩን ተጋላቢ ለማንበርከክ›› በሚደረገው የህልውና ትንቅንቅ ላይ! ‹‹የውስጥ እንቅፋት›› እንዳይፈጠር፤ የጀርባ ወጊዎችን /Back Stabbers/ የማፅዳት ግስጋሴ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹ጥንቃቄ ይጠብቅሀል፤ ማስተዋልም ይጋርድሀል›› የሚለው ቃል! ተገቢ የሚሆነውም እዚህ ላይ ነው!! ጤና ይስጥልኝ፡፡

ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለአፍሪካ

 

tewedros getachew
             ቴዎድሮስ ጌታቸው

 /ደራሲና የፖለቲካ ተመልካች/

ድሬዳዋ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share