ሰው መሆን ሰውነት አይደለም!  – አገሬ አዲስ

ታህሳስ 07 ቀን 2014 ዓም (16-12-2021)

በዚህ ትልቅና ሰፊ እርእስ ላይ ለመጻፍ ብቃቱ ባይኖረኝም ካገኘሁት አጠቃላይ ግንዛቤ ስነሳ ይህን አጭር የመቀስቀሻ ወይም የመነሻ ትንታኔ ለመሰንዘር ደፍሬአለሁ።በዚህ ዕርእስ ላይ የውጭ አገር ሊቃውንት ብዙ ያሉት ቢኖርም በአገራችን ምሁራን በኩል ግን የተባለ ነገር አላገኘሁም።ከቤተ እምነቱ ብቻ ስለሰው ልጅ አመጣጥና   ስለበጎ ተግባር የሚሰበክና የሚነገር ቀደም ሲልም  በትምህርት ቤት ደረጃ በግብረገብ ክፍለጊዜ እንደ አንዱ የትምህርት አይነት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ ከዚያ ባሻገር እራሱን የቻለ ምርምርና ጥናት የተካሄደበት ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም።በአሁኑ ጊዜ በተለይም ከሃምሳ ዓመታት ወዲህ ግብረገብ እንኳንስ በትምህርት ቤት ውስጥ ክፍለጊዜ ተሰጥቶት ይቅርና  በጽሁፍ ቀርቦ ለማንበብም ዕድሉ የመነመነ ሆኗል።አብዘሃኛው የእምነት አባቶችም ሳይቀሩ በእራሱ ስሜትና የግል ፍላጎትና ጥቅም ላይ ያነጣጠረ እንጂ ስለሚኖርበት ማህበረሰብና ስለሚኖረው አበርክቶ(ድርሻ) የሚጨነቅና የሚያስብ፣አልሆነም።

እንደ ወል መጠሪያው ሰው ማለት በእምነት ተቋማት አገላለጽ በፈጣሪ ፈቃድና ፍላጎት በራሱ አምሳል የተፈጠረ ሲሆን በሳይንሳዊ  ዕይታ ደግሞ የእንስሳ የዝንጀሮነት ደረጃውን በጊዜ ብዛት እዬለወጠ የመጣ ዘመናዊ ወይም የተሻለ እንስሳ፣ በእንግሊዝኛውም ሆሞ ሳፒያን ሬስ(Homo sapien race) ነው ይላሉ።ይህ የሰው መንጋ በአንድ ከባቢ ወይም የተወሰነ ቦታ ላይ ተከማችቶ ሲኖር አገር ፈጠረ ይላሉ።የአገር መፈጠርም ጋር ተያይዞ ሕዝብ የሚለውን የጋራ ማንነት እንደያዘ ይገልጻሉ።በዓለም ዙሪያ ተበትኖ የሚኖረው የዓለም ሕዝብ ሲባል፣በዬጊዜውና በዬምክንያቱ ተለያይቶ የየራሱን ድንበር ከልሎ ለሚኖርበት ቦታ ስም አውጥቶ መኖር ሲጀምር እሱም ባዋጣው አገር ስም ለመታወቅ መቻሉን የታሪኩን  አመጣጥ ያጠኑ ይዘረዝሩታል።እኛም የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለመባል ያበቃን የቀድሞ ትውልዶቻችን በኖሩበት መሬት ወይም በመሰረቱት አገር ባወጡት ስምና ማንነት ነው።ሌላው የምንገለጽበትንም የጋራ እሴቶች ወርሰናል።ቋንቋ፣ባህል፣እምነት…ወዘተ የዚያ ትሩፋቶች ናቸው።

በሕዝብ፣ወይም ሰው በተባለው ፍጡር መካከል ደግሞ የተለያዬ መለያ መኖሩን ማወቅ መልካም ነው። ከቋንቋው፣ከባህሉና እምነቱ በተጨማሪ ከቁመቱ፣ከጾታውና ከቆዳው ቀለም ባሻገር ሌሎች ለመለያ የሚያበቁት ገጸ ባህሪው፣ስነምግባሩና አስተሳሰቦቹ ናቸው።ስለሆነም ነው ሰው ፣ሰብአዊና ኢሰብአዊ ተብሎ የሚመደበው።በሰውነት ደረጃ ደግ፣እሩህሩህ፣አዛኝ፣ለጋራ ጥቅም የሚቆም፣ታማኝ… ወዘተ የሚሉት ገላጭ ማንነቶቹ ሲሆኑ በኢሰብአዊነት ደረጃ ደግሞ የሚመደቡት ዘረኛ፣ጎሰኛ፣ጨካኝ፣አረመኔ፣ገዳይ፣ቀማኛ፣ውሸታም፣ከሃዲ፣እራስ ወዳድ፣…ወዘተ የመሰሉትን እኩይ ጸባያት የሚያንጸባርቁት ናቸው።እነዚህን ሁለት ተጻራሪ ጸባያት ምሁራን በእንግሊዝኛው እንዲህ ሲሉ በአጭሩ ይገልጿቸዋል። “Human is a noun that describes someone who has Human qualities But Humane is an adjuctive that describes specific human qualities like COMPASSION and KINDNESS”A humane person is one who shows great compassion and caring for others including animals and plants.Who tries whenever possible to alievate anothers sufferings, while the word is derived from the word human, the sad fact is that a person can be human without being humane”እውነት ነው! የሰው ልጅ በቁመናው ብቻ አይለካም፣አይመዘንም።በምግባሩ እንጂ! ምግባረቢስ የሆነ ሰው የተሟላ ሰውነት አይኖረውም።ሰው መሳይ አውሬ ነው።

ኢሰብአዊነት ከመልካም ባህሪያት ውጭ ያሉትን የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን እንደሰው በሌላው የሚታዘዙና የሚንቀሳቀሱትንም መኪናዎችና ሮቦቶችንም (Machines and Robots) ያጠቃልላል፣ያም ማለት በሰው የሚታዘዙና የሚነዱ፣በራሳቸው ህሊና የማይመሩትም  ሰዎች የነዚሁ እቃዎች ቤተሰቦች መሆናቸውን ግብራቸው ያስተሳስራቸዋል ማለት ነው።

የሰው ልጅ በተፈጥሮ የመጥፎና የደግ ባህሪያትን የሚረጩ ህዋሳት ወይም አካላትን ተሸክሞ የተወለደ አይደለም፣የንፁህ አይምሮ ባለቤት ሆኖ የተፈጠረ ነው፤ፈረንጆቹ የተፈጥሮ ሰው ወይም ናቹራል ፕርሰን(Natural Person)ይሉታል። በግእዙም ቃል ሰብ ማለት ሰው ማለት ሲሆን ኢሰብ ደግሞ ሰው ያልሆነ ግን በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስ ማለት ነው።ሰውን የተሟላ ሰው የሚያደርገው ተጨማሪ ባህሪያት ሲኖሩትና ሲያሟላ ነው። የዃላ ዃላ ከሚቀላቀለው ህብረተሰብና ከአስተዳደጉ ለሚወርሰው ባህሪያት የተጋለጠና የነዚያ ባህሪያት ተሸካሚ የሆነ ፍጡር ነው።የእኩይ ባህሪያት ቀሳሚ ብቻ ሳይሆን በውስጡም እዬጎለመሰ ሲሄድ የመረዳት፣አመዛዝኖ የመቀበልና የመጣል ችሎታም በማዳበር ክፉና ደጉን፣መጥፎና ጥሩውን ለመለዬት የሚያስችልና የሚያመዛዝን ችሎታና አእምሮ ባለቤት ነው።ግን የመጠቀሙና የፈለገውን የመሆን ውሳኔ፣ ምርጫ ና ፈቃድ የራሱ ነው።

እውቁ ቻይናዊ  ፈላስፋ ከክርስቶስ በፊት በ28-10-551 ቢሲ ተወልዶ በ11-04-479 ያለፈው ኮንፊሸስ  (ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ዘመን አቆጣጠር ከላይ ወደታች መሆኑን ልብ ይሏል) ቻይና በልዩነት ቀውስ ውስጥ ገብታ፣መረጋጋት ባጣችበት ጊዜ የኖረና የታዘበ ሲሆን የሁኔታውን መነሻ ምክንያት  በጥልቀት ተመልክቶ መፍትሄ ሃሳቦችን ያፈለቀ ሰው ነው። “ የሰው ልጅ በስነምግባር፣እርስ በርሱ በመዋደድና አንዱ ለሌላው አስቦ ከኖረ ማህበረሰብ ሰላማዊ፣የቆመለትን ዓላማ በሚገባ ፈጻሚና ከግቡ የሚያደርስ  ይሆናል።ሁሉም ተግባር በትክክሉ ከተፈጸመ ሕግ፣ሃይልና መንግሥትም አስፈላጊ አይሆኑም፣ምክንያቱም ሰዎች በስነሥርዓት ስለሚተዳደሩ ነው። በዚህ መንገድ ህይወቱን የሚመራ ሰው የሰውነትን ጸጋ የተላበሰ ነው።አለያ ግን ሙሉ ሰው አይሆንም።” ሌላው የሚታወቅበት ትምህርቱ ደግሞ “በራስህ ላይ ሊደረግ የማትሻውን በሌሎች ላይ አታድርግ” የሚለው ነው።በዚህ መንገድ ህይወቱን የሚመራ ሰው የሰውነትን ጸጋ የተላበሰ ነው አለያ ግን ሙሉ ሰው አይሆንም።ሲል  በሰውና ሰውነት መካከል ያለውን ልዩነት ገልጾታል።በቻይናዎች ዘንድ የሚታዬው ለቤተሰብ፣ለልጆች፣ለሴቶች፣ለአዛውንት ክብርና ትህትና ከዚያ አስተምሮ የተገኘ መሆኑ ይነገርለታል።

በአገራችን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት ያለውም ሕዝብ ስለሰብአዊነትና ኢሰብአዊነት ቢጻፍለትም ለማንበብ ፍላጎት ያለው በጣም ጥቂቱ ነው፤ከነጭራሹም የለም ለማለት ያስደፍራል።በአብዛኛውም እይታ ሰብአዊነት ኻላቀርና መሃይምነት፣ኢሰብአዊነት ግን ዘመናዊነትና እውቀት ተደርጎ ከሚታይበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

በጥልቀት ቢሠራበት ኖሮማ በሕዝቡ፣በተለይም በዘመኑ ትውልድ አይምሮ ውስጥ የጥፋትና የክፋት ፣የጥላቻና የበቀል ስሜት አይኖርም ነበር።የተሻለ አመለካከትና ምግባር ጎልቶ በታዬ ነበር፤አሁን ለተከሰተው አውሬነት መጋለጥ ባልመጣም ነበር።አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአገራችን በኢትዮጵያ የሰውነት ድባቡ እዬጠፋ ኢሰብአዊነት እያበበና እዬጎመራ መምጣቱ ከምን የተነሳ ይሆን?

የሰውን ልጅ ወደ አውሬነት የለወጠው ዋናው ምክንያት በዋሻ እዬኖረ ምግቡን በአደን በሚሰበስብበት ወቅት ሌላው ነጥቄ ልብላ ሲል ያደረገው የመከላከል ግብግብ ለአሁኑ የብላ ተባላ ዘመን ትውልድ ለግጭት መንደርደሪያው እንደሆነ የተደረጉ ጥናቶችና መላ ምቶች ያስረዳሉ።ይህ ማለት የቅራኔውና የእርስ በርስ ግብግቡ ምክንያት የእኔ ነው ባይነት ስሜት በማደሩ ሲሆን አሁን ለዓለማችን ውዝግብና የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያቱ ቅጥ ያጣ እራስ ወዳድነት፣(በተወሰነ ደረጃ ለእራስ ማሰብ ተገቢ ቢሆንም)፣የስግብግብነት መንፈስ ማሳደሩና ያንንም በውድም ሆነ በግድ ለማረጋገጥ የመፈለጉ አባዜ ነው።ይህንን አጠር ባለ አገላለጽ ገደብ የሌለው የግል ንብረትና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ግለኝነት የቅርሾና የንትርክ መነሻ ነው ይሉታል(uncontrolled  private ownership and incorrectly managed individualism are  the root causes or seeds of human conflicts and wars)

ከላይ ከመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያም እንደሌሎቹ አገራት የሰው መንጋ የሰፈረባት መሬት ስትሆን፣ሁሉንም ጸባይ የተሸከመ የሰው ዝርያ የኖረባትና የሚኖርባት አገር ነች።ከላይ የሰው ልጅን አመዳደብ እንዳዬነው ሁሉ የኢትዮጵያም ሕዝብ በተጠቀሱት ምድቦች ውስጥ ይካተታል።ሰብአዊና ኢሰብአዊ በሚባሉት ምድቦች ውስጥ ይሰለፋል።ታዲያ የሕብረተሰቡን ስነምግባርና አድራጎት ስናዬው ጥቂቱ ሰብአዊ ብዙሃኑ ኢሰብአዊ ሆኖ እናገኘዋለን።የአንድ አገር ሕዝብ በጎሳና በዘር፣በእምነትና በጎጥ ተከፋፍሎ፣ክልል የሚባል አጥር ገንብቶ የመባላቱ፣የመሬት ነጠቃውና የንብረት ዘረፋው፣የጥላቻውና የጨካኝነቱ፣አገሩን የማፍረሱ አዝማሚያ፣እራስ ወዳድነቱና ከሃዲነቱ ሲጨመርበት ከዚያ ከኢሰብአዊነት ማንነቱ የተቀዳ  መርዛማ ፈሳሽ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ጎን ለጎንም ጥቂቶቹ በሰብአዊነት ደረጃ ላይ ሆነው ከነዚህ አጥፊ ድርጊቶች የራቁና ድርጊቶቹን ተቃውመው የሚታገሉ  መኖራቸው ሊረሳና ሊካድ አይገባም።ዓለማችንም ሆነች አገራችን እዬተንገዳገደችም ቢሆን እስከአሁን ድረስ የዘለቀችው በነዚህ በጥቂቶቹ ተጋድሎ ነው።ታዲያ ኢትዮጵያ የብዙ ኢሰብአውያን የጥቂት ሰብአውያን አገር ነች ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም።

በኢትዮጵያ አገራችን የሚሆነውን አስመልክቶ ለማውቃቸው አንዳንድ ሰዎች ኧ ረ ምን ነካችሁ፣ አገራችን ወዴት እዬሄደች ነው?ስላቸው “አይ ያንተ ነገር! ምን ሰው አለ ብለህ ነው?ሁሉም እኮ አውሬ ሆኗል” የሚለውን ምላሽ ስሰማ  እኔም አገር ያለው ሕዝብ፣ ሰው የሌላት አገር ለማለት ዳዳሁ። ኢትዮጵያን የመሰለ ለሁሉም በቂ የሆነች  አገር ያለው ሕዝብ  ግን ኢትዮጵያን የሚመጥን ሰብአዊነት ያለው ዜጋ የላትም ቢኖርም ጥቂቱ ነው ለማለት ነው።ኢትዮጵያም ብቻ ሳትሆን ዓለም የኢሰብአዊያን መድረክነቷን በግልጽ እያሳዬች መጥታለች።ጥቂት ሰብአውያንም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞት የሽረት ትግል እያደረጉ ነው።የሰውን ልጅ ከጥፋት ለማዳን ከኢሰብአውያኑ ጋር ግብ ግብ ገጥመዋል።የፖለቲካውም ሆነ የኤኮኖሚው ብሎም የማህበረሰቡ መመሪያ የሚነደፈው ብዙሃኑን በሚያሽከረክሩት፣ለእኩይ ተግባራቸው መከላከያ ሃይል በገነቡት ኢሰብአዊያን በመሆኑ ትግሉ ቀላል አይሆንም።እነሱ የሚረጩት መርዝ ማህበረሰቡን በክሎታል።በግድም በውድም ተከታይ አድርገውታል።

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላውም አገር ብዙሃኑ በጥቂቶች ኢሰብአውያን ትዕዛዝና ፍላጎት የሚንቀሳቀስ የሰው መኪና ወይም ሮቦት ሆኖ እራሱንም አገሩንም እያጠቃ ነው።የማመዛዘኛ ውስጣዊ አቅሙን ካልተጠቀመና በያዘው ከቀጠለበት እራሱም አብሮ ከመጥፋት አይድንም።የያዘው መንገድ የአጥፍቶ የመጥፋት ጉዞ ነው።

የተነሳሁበት እርዕስ ሰው፣ሕዝብ፣ሰብአዊነትና ኢሰብአዊነት የሚለው ስያሜና ሃረግ ብዙ ጥናትና ምርምር  እንዲደረግበት የሚሻ ነው።ለጊዜው ግን መነሻ ይሆን ዘንድ በዚህ መልኩ በአጭሩ ለማቅረብ ሞክሬለሁ።ሌላው ይቀጥልበታል የሚል ተስፋ አለኝ ፣ ሰፋ ያለ ጥናት ካለም ለሰፊው ሕዝብ  ይቅረብለት። በጦር ሜዳ ከማንበርከክ የበለጠ በአስተሳሰብ ላይ ዘምቶ ማሸነፍ ዘለቄታ ላለው ድል ያበቃል። በዓለም ላይ ያለውን ምስቅልቅል ሁኔታ፣ግጭትና ውድመት መቀነስ ብቻ ሳይሆን ያጠፋል። ኢሰብአዊነቱን ቀንሶ ሰብአዊነቱን ሊያበረክትበት ይችላል።አስተዋይ ልሂቃንም “ትልቁ ቁምነገርና ችሎታ  ዓለምን ማወቅ ብቻ ሳይሆን መለወጥም ነው” ይላሉ።ስለሆነም እኛም ዓለምን ለመለወጥ በመጀመሪያ  እራሳችንን መለወጥ ከዚያም አገራችን ያለችበትን ደረጃና ሁኔታ አውቀን  በመለወጡ ሥራ ላይ እንሰማራ።የኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ትንሳኤ፣በኢሰባውያን ላይ ሰብአውያን የሚጎናጸፉት ድል ለሌላው አፍሪካዊ ብሎም ለሚጨቆኑትና ለሚበዘበዙት አገራት ፋና ወጊ ይሆናል።የአድዋን ታሪክ እንድገመው!! የእኛ ከኢሰብአዊነት ሰልፍ ወጥተን በሰብአዊነት ሰልፍ ውስጥ መግባት ለሌላው ምሳሌ ይሆናል።ከአገር አፍራሽ የጎሳ ትንቅንቅ ውስጥ ወጥተን በአገራዊ ቁመና ላይ መዋል ለሌላው አገር ህልውና ምልክትና ፈር ቀዳጅ ይሆናል።ሙሉ ሰው የመሆኑም ትርጉም ይኸው ነው።

አትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ የሰብአዊያን አገር ትሁንልን!!

ኢሰብአውያንን ይቀንስልን፣ያድክምልን! ያጥፋልንም!!!

አገሬ አዲስ

 

2 Comments

  1. በቅድሚያ ፈጣሪን እንዲህ አርግልን የሚሉ ሁሉ ጤነኛ ጭንቅላት ያላቸው ሰዎች አይደሉም። የሚሰማ፤ የሚያይ፤ ነገርን የሚለውጥ አምላክ ቢኖር ኑሮ 6 ሚሊዪን አይሁዶች ሲጨፈጨፉ፤ የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚፍገመገሙ ሃበሾች በመርዝ ጋዝ በጣሊያን ባልተጨፈጨፉም ነበር። በዓለም ላይ የምናየው ችግሩ ሁሉ ምንጩ እኛ ሰዎች መፍትሄውም እኛው ነን። እልፍ አማልክት ቢጠሩት በምድር ላይ ያለውን እውነት አይቀይረውም። ዛሬም ትላንትም ከመገዳደል ያዳነን አንድም ሰማያዊ ሃይል የለም። ወደፊትም አይኖርም። ሰለጠንኩ የሚለን የነጩ ዓለም ከሩቅና በቅርብ ሃገርን እየናደ፤ በመንግስታትና በህዝቦች ላይ ጫና እያደረገ እምቢኝ ያሉትን መሪዎችም መቃብር እያወረደ ለራሱ የሚጠቅመውን ብቻ በመያዝ እርስ በእርሳችን ሲያናቁረን እንደኖረና እንዳለ የማይታየው ሰው በቁሙ የሞተ ነው። በህዝባችን ላይ የሚሰራ ሥራ ከምንሰማውና ከምናየው የላቀ ነው። እንደ ተባለውም ” ሰው መሆነ ሰውነት አይደለም”። እንዲያውም በእኔው እይታ ሰው ከዝንጀሮ መጣ የሚባለው ቢያወዛግበኝም ወደ አራዊትነት እየተለወጥን እንደሆነ ግን በሌሎችም ላይ የምናደርሰው ሰቆቃና መከራ መስካሪ ነው። ለዚህ ሰው ወደ እንስሳነት ተቀየረ ለሚለው እይታዬ በሰዎች ላይ የተንጠለጠለ ጅራትና አራት እግር ማሳየት አይጠበቅብኝም። ለገንዘብ ወላጆቹን የሚገድል፤ እህቱን ገቢያ ላይ አውጥቶ የሚሸጥ፤ አደራ የተቀበለውን የሚበላ፤ የቆመን የሚያፈርስና የሚዘርፍ፤ ሰውን አሰልፎ የሚረሽን፤ በዘሩ ተሰልፎ ቱልቱላ የሚነፋ የጎጥ ፓለቲካ አራማጅ ሁሉ በጅምላ ለእኔ ጅራታም አውሬ ነው።
    ምጡቅ ነኝ ተምሬአለሁ እናውቃለን የሚሉን እነዚህ የቁም ሙታኖች ፊደል መቁጠር መማር አለመሆኑ ተግባራቸው በግልጽ ያሳያል። የሰው ልጅ የመማሩ መለኪያ አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያን ተቀብሎ ድምጽ ለሌላቸው ዘሩን፤ ወንዝ የማያሻግር ቋንቋውን፤ የማይኖርበትን የይስሙላ ሃይማኖቱን በመተው ግፈኞችን ተፋልሞ ማለፉ ብቻ ነው። ያካበትከው እውቀት፤ ያከማቸኸው ሃብት የሚሰፈረው ለሌላው በምታረገውና በምትኖርበት ዘመንና ጊዜ ነው። ዛሬ ላይ ተቀምጠው አጼ ዮሃንስ፤ አጼ ሚኒሊክ ይህን ሰሩ የሚሉን ጅቦች ሰው የሚመዘነው በኖረበት የጊዜ ዘመን መሆኑ ትዝ አይላቸውም። ድሮ የሰው መድሃኒቱ ሰው ነው ሲባል የሰው ልብ በይቅርታ ነገሮችን ለቀቅ አርጎ ሰላምን ለማስፈን በዚህም በዚያም ሽማግሌ ተደምጦ ይኖር ነበር። አሁን ስለጠን በማለት ሰይጣን የሆነው ይህ ትውልድ ከመራኮትና ራሱን ለመከራ አዘጋጅቶ ሌላው ላይ መከራ ከማዝነብ በስተቀር ሌላ ሙያ የለውም። ሲመከሩ የማይሰሙ የበሉበትን ወጭት ሰባሪዎች አሁን ደግሞ ያጎረሰውን እጅም በጥይት የሚደበድቡ የእብድ ክምችቶች ያፈራች ሃገር ናት። የዚህ እብደት ዋና ማሳያው ኦነግ ሸኔ ከወያኔ ጎን ተሰልፎ መፋለሙ ነው። እልፍ የኦሮሞ ልጆች በ 27 ዓመት የገደላቸው፤ አካለ ጎደሎ ያደረጋቸው ይህ የትግራይ ስብስብ መሆኑ እየታወቀ አሁን የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በማለት በኦሮሞ ህዝብ ስም አብረው ተሰልፈው የሚፈጽሙት ግፍ ከሰው ባህሪ የወጣ ነው። በአማራ ራሱን የቅማት ነጻ አውጪ በማለት በአይከልና በዙሪያዋ የፈጸመው ግፍ የወያኔ ቋሚ ተላላኪ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል። እነዚህ ነጠላ ሃሳብና ጡሊዎች ሁልጊዜም የሚያስቡት ዘርፎ መክበርን ነው። ወያኔ ለዘመናት ያሳያቸው በአፈ ሙዝ ገንዘብ እንደሚገኝ እንጂ ሰርቶ መኖርን አይደለም። ለዚያ ይሁን French writer Balzac ” Behind every great fortune there’s a crime” ያለን። የተመድ የድግግሞሽ ስብሰባና በዙሪያቸው ያሰፈሰፉት ተከፋይና ዋሾ የዜና አውታሮች ዛሬም ትላንትም ወደፊትም ውሸትን እንደሚለፈልፉ እንዴት ሰው አይረዳም። ግን በኑሮ ክብደት፤ በእጽ፤ በልዪ ልዪ ሃኪም ባዘዘው መድሃኒት የደነዘዘ ህዝብ እውነትን ለመረዳት አይፈልግም ቢፈልግም ትንሽ ተመልክቶ ይህስ ይደብራል ብሎ ነው የሚያልፈው። በራፉ ላይ ደርሶ የራሱ ቤት ውስጥ ሲገባ ግን ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል። ባጭሩ የሰው ሰውነት መሰፈሪያው ተዛብቷል።
    በቅርቡ አንድ መስፍን ጉቱ የሚባል ለሰማይ ያደረ ሰው ነኝ ባይ ለደረጀ ከበደ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው አዳመጥኩ። ወቸው ጉድ ያሰኛል። አንተ እዛ ሆነህ በርገርህን እየበላህ፤ ከአሁን በህዋላ ያንተ ጠላቶች እኛ ነን፤ ወንድ ከሆነክ ለምን ከዚህ አትመጣም እያለ ሲለፈልፍ እንዴ እንዲህ አለሙ ሁሉ ገምቷል እንዴ አልኩ። ወሬው ተያያዥ በመሆኑ ሶፊያም ሌሎችም ወንጌላዊ፤ ነብይ፤ ነብያት፤ ሃዋሪያ፤ አገልጋይ የተባሉት የሰጡትን ሁሉ ካዳመጥኩ በህዋላ አንድ ነገር ወደ ልቤ መጣ። እነዚህ በሃይማኖት ስም ራሳቸውን ያከበሩና ከሰማይ መንገድ እጅግ የራቁ ቱልቱላዎች ሰው የራሱን አቋም ተናገረ ብሎ መለፍለፍ ምን ይባላል። ተያይዞ ማበድ ይሉሃል እንዲህ ነው። ያበድነው ሁላችንም ነን። የለበሰ ሁሉ ያላበደ የመሰላችሁ ሁሉ ስታቹሃል። የለበሰም ይበጭጫል። እስኪያወልቅ አትጠብቁ። ባጭሩ የሃገሪቱ መከራ አዝናቢዎች በሩቅም በቅርብም ያለን ሰው መሳይ አውሬዎች እኛው ነን። ችግሩን ሌላ ላይ ለማሳበብ ያ ነው እነዚያ ናቸው ከማለት ይልቅ ራስን ማየት አስፈላጊ ነው። አሁን በሰሜን በኩል ያለው ችግር ቢረግብም በሌላ በኩል አፈትልኮ እንደገና እንዘጥ እንዘጥ አይቀሬ ነው። በዚህ ላይ የአሜሪካዊያንና የአውሮፓ ሴራ ሸፋፋ በመሆኑ ሳናውቀው ጠልፎ ሊያጠላልፈን እንደሚችል ይታየኛል። ወያኔ የሰሜን ጦርን ሲመታ ከአሜሪካ ጋር ተነጋግረው እንደሆነ ጭራሽ አልጠራጠርም። የሱዳን የኢትዮጵያን መሬት መውረር የአሜሪካ ግፊት እንዳለበት የታወቀ ነው። አሁን በቱርክ፤ በግብጽ በዪኤኢ በመጓዝ ነገሮችን እያማታ ያለው የአሜሪካው ዲፕሎማት የሞት መልዕክተኛ እንጂ የሰላም ሰው እንዳልሆነ ያለፈ ታሪካቸው ያሳያል። ነጭ የጥቁር ህዝቦችን የበላይነት አይፈልግም። በሰውኛ አስተሳሰብ ለመኖርና ሰው ተብሎ ለመጠራት ከሃይማኖት፤ ከዘርና ከቋንቋ የተሻገረ ሃገር አቀፍ፤ አህጉራዊ እይታ ያስፈልጋል። የክልል ፓለቲካው አጥር ማጠር ለሚችሉ ጭፍኖች ይሁን። አንድ ነገር ልጨምርና ይብቃኝ። በቅርቡ አንድ በሃገር ስለሆነው ሊያጽናናኝ ፈልጎ አይዞህ እንደመሸ አይቀርም አለኝ። ካበቃን በህዋላ ይህችን ስንኝ ጻፍኩ። እንሆ።
    እንደ መሸ አይቀርም ይነጋል ያላችሁ
    መንጋቱን አሳዪን መምሸቱን ትታችሁ። በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.