September 28, 2021
7 mins read

በቀጣዩ ሳምንት የሚመሰረተው መንግሥት 21 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይኖሩታል [ዋዜማ ራዲዮ]

file photo: ethiopia's prime minister abiy ahmed addresses the members of parliament inside the house of peoples' representatives in addis ababa

ሰኞ፣ መስከረም 24 ቀን 2014 በተወካዮች ምክር ቤት የሚቋቋመው አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ አወቃቀርና ስያሜ ላይ መጠነኛ ለውጥ እንደሚያደርግ ዋዜማ ሰምታለች። በሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 ቁጥራቸው 19 የሆኑት መሥሪያ ቤቶች አዲስ በሚቋቋመው ካቢኔ ወደ 21 ከፍ ይላሉ። ከተጣመሩትና የአደረጃጀት ለውጥ ከሚያደርጉት ውጭ፣ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትነት የመጡት ሁለት ተቋማት ፍትሕ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ናቸው።

የፌደራል መንግሥቱን የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ገምግሞ የመከለሱን ሥራ በዋናነት የመራው የፕላንና ልማት ኮሚሽን ነው። ከዓመት በላይ ፈጀ በተባለው ሒደት፣ የኮሚሽኑ ባለሞያዎች የሁሉንም አስፈጻሚ ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊዎች ማነጋገራቸውን፣ ክርክሮች መካሄዳቸውን በሂደቱ የተካፈሉ ገልጸውልናል። ሒደቱ ሲጀመር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል የገመቱ ቢኖሩም ውጤቱ በአመዛኙ የስራ ግንኙነቶቹን ለማሻሻል በመሞከር አትኩሯል።

ስምንት ቁልፍ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን የመምራትና የመቆጠጠር ስልጣን የተሰጠው “ሰላም ሚኒስቴር” ስሙ “የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር” ተብሎ እንዲቀየር ሐሳብ ቀርቧል። በ2011 የተቋቋመው ‘ሰላም ሚኒስቴር’ የሚያስተዳድራቸው ተቋማት የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የውጭ ግ ንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ፣ የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ናቸው። ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በቦታቸው ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

“የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር” ስያሜውን “የሥርዓተ ፆታና ማኅበራዊ ጉዳይ” በሚል ይቀይራል። ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ በዚሁ ሰሞን የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይፈርሳል/ይታጠፋል የሚል መረጃ ቢሰራጭም፣ የዋዜማ ዘጋቢዎች ያሰባሰቡት መረጃ መሥሪያ ቤቱ ከውስጣዊ የአደረጃጀት ለውጥ በቀር ባለበት እንደሚቀጥል የሚያረጋግጥ ነው።

በ2008 (አዋጅ 943) ቀድሞ ሲጠራበት የነበረውን ስሙን ቀይሮ “የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ” ተብሎ የነበረው መሥሪያ ቤት፣ በድጋሚ የፍትሕ ሚኒስቴር ይባላል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በሚኒስትር ማዕረግ በሹመታቸው እንደሚቀጥሉ የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። አሁን በኮሚሽንነት ያለው ፕላንና ልማት፣ ወደ ሚኒስቴርነት ከፍ ሲል፣ በቅርብ የጸደቀውን የ10 ዓመት መሪ እቅድ በማዘጋጅት የመሪነት ሚና የተጫወቱት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ባሉበት እንደሚቀጥሉ ተገምቷል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን “የቱሪዝም፣ ስነ ጥበብና ባህል ሚኒስቴር” (Ministry of Tourism, Creative Arts and Culture ) በሚል የሚያዋቅረው ለውጥ፣ “ንግድና ኢንዱስትሪን” “የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር” ወደሚል አገር ዘለል ሚና ወዳለው ተቋም አሳድጎ ኢንዱስትሪን ከኢንተርፕራይዝ ጋራ አጣምሮታል። የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ገጠርንም እንዲያካትት ተደርጎ “የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር” ተብሎ ይዋቀራል ተብሏል።

ለውጡን ተከትሎ የፈረሰው የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ በድጋሚ ሊቋቋም ይችላል የሚል የቀደመ ግምት ቢሰጥም፣ አዲሱ ዕቅድ ሳያካትተው ቀርቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ በፓርላማው ፊት ያቀርቡታል ተብሎ የሚጠበቀው ቀዳሚ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶቻቸው ዝርዝር የሚከተለው ነው።

  1. የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር (የሰላም ሚኒስቴር)
  2. የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
  3. የግብርና ሚኒስቴር
  4. የመከላከያ ሚኒስቴር
  5. የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
  6. የፕላንና ልማት ሚኒስቴር
  7. የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
  8. የቱሪዝም፣ ስነ ጥበብና ባህል ሚኒስቴር
  9. የማዕድን ሚኒስቴር
  10. የሠራተኛ፣ ሥራ ፈጠራና ክህሎት ልማት ሚኒስቴር
  11. የገንዘብ ሚኒስቴር
  12. የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ
  13. የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር
  14. የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር
  15. የከተማ-ገጠር ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር
  16. የውሃ፣ አካባቢና ኢነርጂ ሚኒስቴር
  17. የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር
  18. የትምህርት ሚኒስቴር
  19. የጤና ሚኒስቴር
  20. የሥርዓተ ፆታና ማሕበራዊ ጉዳይ
  21. የፍትህ ሚኒስቴር

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ቁጥር በ1995 (አዋጅ ቁጥር 471) ሃያ የነበረ ሲሆን በ2008 (አዋጅ ቁጥር 916) 25 ደርሶ ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop