ለቸኮለ! ማክሰኞ መስከረም 18/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

addis ababa city cousil members

1፤ በቀጣዩ ሰኞ የሚመሠረተው አዲሱ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት 21 ካቢኔዎች እንደሚኖሩት የዋዜማ ምንጮች ዘግበዋል። አንዳንድ ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች የአደረጃጀት ለውጥ እንደተደረገባቸው ምንጮች የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፍትህ ሚንስቴር ተብሎ በሚንስቴር ደረጃ እንደገና እንደሚዋቀር እና ፕላን ኮሚሽን ደሞ ፕላን እና ልማት ሚንስቴር ተብሎ እንደሚቋቋም ተሰምቷል። ሰላም ሚንስቴር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር በሚል ስያሜ ይዋቀራል ተብሏል። ዝርዝሩን ያንብቡት

2፤ የኢትዮጵያ ኮምንኬሽን ባለሥልጣን ለሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ጨረታ ዓለማቀፍ ተጫራች ኩባንያዎች የጨረታ ሰነዳቸውን እስከ ታኅሳስ አጋማሽ እንዲያስገቡ በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ ጠይቋል። ሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ የሞባይል ገንዘብ ግብይትን እና ማስተላለፍን የሚጨምር ነው። በርካታ ተጫራች ኩባንያዎችን ለማሳተፍ ሲባል ባለሥልጣኑ የጨረታ ተሳትፎ መስፈርቶችን እንዳሻሻለ ባለሥልጣኑ አክሎ ገልጧል።

3፤ አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከተማዋን በምክትል ከንቲባነት በማገልገል ላይ ያሉትን አዳነች አቤቤን ከንቲባ አድርጎ በሙሉ ድምጽ እንደመረጠ የከተማዋ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ጃንጥራር አባይ ደሞ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል። የከተማዋ ሥራ አስኪያጅ ጥራቱ ከበደ በሃላፊነታቸው ይቀጥላሉ። የባሕል እና ቱሪዝም ሚንስትር ደዔታ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት ቡዜና አልቃድር፣ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ሆነዋል።

4፤ አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማዋን ሥራ አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ እንዳጸደቀ የከተማዋ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። አዋጁ የሥራ አስፈጻሚ አካላቱን ብዛት ከ61 ወደ 46 ዝቅ አድርጓል። መከላከያ ሚንስትር ቀንዓ ያዴታ የከተማዋን የጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የባሕልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ኂሩት ጣሰው የባሕልና ቱሪዝም ቢሮን፣ የተቃዋሚው ኢዜማ አባል ግርማ ሠይፉ የኢንቨስትመንት ቢሮን፣ የአብን አመራር የሱፍ ኢብራሂም የመንግሥት ንብረት አስተደርን ቢሮን እንዲመሩ በዕጩነት ቀርበዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  No to "Grand Coalition" with the EPRDF

5፤ ኢትዮጵያ በግብጽ እና አየርላንድ የሚገኙ ኢምባሲዎቿን ለጊዜው እንደምትዘጋ የተለያዩ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከ3 እስከ 6 ወራት ለሚዘልቅ ጊዜ እንደሚዘጋ በካይሮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ለዓረብኛው ቢቢሲ መናገራቸውን የግብጽ ጋዜጦች ዘግበዋል። መንግሥት ኢምባሲዎቹን ለመዝጋት የተገደደው ሀገሪቱ ባጋጠማት የገንዘብ እጥረት ሳቢያ እንደሆነ ተገልጧል።

6፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሱዳን ባሁኑ ወቅት የገጠሟትን ችግሮች በራሷ አቅም ብቻ ትፈታቸዋለች ብለው እንደሚያምኑ በዓረብኛ ቋንቋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በጻፉት መግለጫ መግለጻቸውን የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ እና ሱዳን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ተግዳሮቶች እየገጠሙት እና የውጭ ኃይሎችም በሁለቱ ሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ የጠቀሱት ዐቢይ፣ ሱዳናዊያን የፖለቲካ ኃይሎች አሁን የገጠማቸውን ችግር ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት ራሳቸው ይፈቱታል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። የሱዳን ሽግግር መንግሥት ባለፈው ሳምንት የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ እንደተደረገበት ይታወሳል።

7፤ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት ሰሞኑን በጎሳ አመጽ የተዘጉ የነዳጅ ማመላለሻ መስመሮች እንዲከፈቱ ከተቃዋሚው የምሥራቃዊ ሱዳኑ ቤጃ ጎሳ መሪዎች ጋር ስምምነት ላይ እንደደረሱ የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ቤጃዎች ደቡብ ሱዳን ነዳጇን ለዓለማቀፍ ገበያ ወደምታስወጣበት የሰሜን ሱዳኗ ባሻዬር ወደብ የተዘረጉ የነዳጅ መስመሮችን ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የዘጉት፣ በሱዳን ሽግግር መንግሥት በቂ ፖለቲካዊ ውክልና እንዳላገኙ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ በመጥቀስ ነው።

8፤ ከባድ ኪሳራ ላይ ያሉት የኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች የፓን አፍሪካ አየር መንገድን በጋራ ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ስምምነት እንደፈጠሩ ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል። የአየር መንገዶቹ ጥምረት የመንገደኞች እና ጭነት መጓጓዣዎችን በጋራ ለማቀናጀትና የሙያተኛ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላቸዋል ተብሏል። ሁለቱ አየር መንገዶች ከስረው ለዓመታት በመንግሥት ሲደጎሙ የቆዩ ሲሆኑ፣ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ደሞ በረራ ካቆመ ዓመት ከመንፈቅ ሆኖታል። [ዋዜማ ራዲዮ]

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትህነግ ስትራቴጂ -መፅሐፍ- ቅኝት {መስፍን ማሞ ተሰማ - ሲድኒ አውስትራሊያ}

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share