❝ባለቤቴን ማክሰኞ ገድለውት እስከ ቅዳሜ አልጋ ላይ አስተኝቼ ሰነበትኩ❞

ባለቤታቸውና ልጃቸው በአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን የተገደሉባቸው እናት

564

የከፋው በደል ሁሉ ተፈፅሟል፤ የደም ጎርፍ ፈስሷል፤ አዱኛ ፈርሷል፤ መንደሩ በሐዘን ተሞልቷል፤ እናቶች ያለ ማቋረጥ ያነባሉ፤ ልጆች በስስት ያለቅሳሉ፤ ሳቃቸውን ተቀምተዋል፤ ፍቅራቸውን ተነጥቀዋል፤ ደስታቸውን አጥተዋል። ደሰታ የሞላበት፣ የፍቅር ዥረት የፈሰሰበት ታላቁ መንደር ደም ሲፈስበት፣ ጀንበር ሲጠልቅበት በመንደሩ ዋይታ ተተካበት። በዚያ መንደር ክረምት ከበጋ ጥጆች ይቦርቁበት፣ ኮርማዎች ያገሱበት፣ ላሞች ወተት ይሰጡበት፣ ወይዛዝርቱ ይዋቡበት፣ ጎበዛዝቱ ጎፈሬያቸውን እያስተካከሉ፣ ወገብ ሙሉ ትጥቃቸውን እያሳመሩ፣ ለአደን የሚወጡበት ነበር። ችግር ብሎ የማያውቀው፣ ደስታና ፍቅር የማይርቀው፣ ጎተራውን ነጭና ጥቁር የሚያስጨንቀው ነበር።

አሁን በመንደሩ ጥጆች እንዳሻቸው አይቦርቁም፤ እረኞች ዋሽንታቸውን ይዘው ከብቶቻቸውን እየነዱ ከበረት አያወጡም፤ ለጨዋታ በአንድ ላይ አይቀመጡም፤ ኮርማዎች አያገሱም፤ ላሞች አይታለቡም፤ወተት አይሰጡም። የደመቀው መንደር ቀዝቅዟል፤ የሞቀው ቤት ፈዝዟል፤ ክፉዎች የመንደሩን ሰዎች ገድለዋቸው በሜዳው የሚፈነጥዙትን ጥጆች፣ የሚያገሱትን ኮርማዎች፣ ወተት የሚሰጡትን ላሞች አርደዋቸው፣ ቤቱን ያለ ሰው፣ ሜዳውን ያለ ከብት፣ ማሳውን ያለ አዝዕርት አስቀርተውታል፡፡

መንደሩ ጭር ብሏል፤ ቀድሞ በድግሱ እና በቡናው እየተጠራሩ ይደሰቱ የነበሩት ብዙዎቹ ሞተዋል፤ ብዙቹም ጠፍተዋል፤ ሌሎቹም በሐዘን ታስረዋልና መንደሩ ጭር ብሏል። ደስታ የለመደው፣ መከፋት የማይወደው መንደር ጭር ብሎ ሲያዩት እና የደረሰውን በደል ሲመለከቱት ያሳዝናልአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ቡድን ግፍ የፈፀመበት ጭና።

ትዳር ከመሰረቱ እና ሦስት ጉልቻ ከጎለቱ ጊዜ ጀምሮ ቤታቸውን ችግር አይቶት፣ ማጣት ጎብኝቶት አያውቅም። ጮማና ወተት፣ ጠጅና ጠላ አይታጣበትም። በላም ልጅ በሬ፣ በልጅ ገበሬ፣ እያሳረሱ፣ በሰፊ አውድማ እያሳፈሱ፣ ጎተራቸውን እያስጨነቁ ነጭና ጤፍ አማርጠው ይበላሉ። ታዲያ የተከበረውን ቤታቸውን ጠላት ገባበት እና ደስታቸውን ነጠቃቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ ሞት አይቀርም ፤ ሥም አይቀበርም ። “ እና  ለሥማችሁ ሥትሉ ፤ ተመሥገን ደሣልኝን እና ታዲዎስ ታንቱን ፍቷቸው

ሐምሌ ነሐሴ ሲርበው ሀገር

ጎተራ ከፍቶ ይሰጠው ነበር❞ የሚባል ጀግና አርሶአደር ባለቤት ነበራቸውና ለተቸገረ እያጎረሱ፣ ለታረዘ እያለበሱ ነበር የሚኖሩት። አሁን ሁሉም እንደ ድንገት አልፏል፣ ከንቱ ሆኗል፣ የሚኮሩበት ባለቤታቸው፣ የሚወዱት ልጃቸው በግፍ አልፈው ልባቸው በሐዘን ተሞልቶ መኖር ጀምረዋልና።

ወይዘሮ የዝባለም ጫኔ ይባላሉ፤ ከባለቤታቸው ንጉሤ ወንድይራድ ሰባት ልጆችን ወልደዋል። በጭና የደረሰውን ግፍ የተመለከቱ፣ በደል የደረሰባቸው እናት ናቸው። ባለቤታቸውን እና ጥላሁን የተሰኘውን ልጃቸውን በግፍ ተነጥቀዋል። ያን ጊዜ ሲያስታውሱት “ሌት ነው ጥይት የተተኮሰ፤ ሳንነሳ ደረሱ። እኔ ቀድሜ ወጣሁ፤ አንተ ጦሩ ዋጠነ አልኩት፤ ‘ወደ የት ሄደ’ ሲል ኧረ ከደጃፋችን መጥቷል። ስለው እኔን ተከትሎ ሲወጣ መጥተው ከደጃፋችን ደረሱ። እርሱም ‘ምንድን ነው ደጃፋችንን የምትይዙት’ አላቸው፤ ‘ምን ሆነህ ነው የምታፈጥ በለው’ አለው፤ በጥይት ራሱን መታው፤ ፈክሮ በርከክ ሲል ‘ድገመው’ አለው። እግሩን ደገመው። ከዚያማ ወደቀ።”

የልጆቻቸውን አባት፣ ግማሽ አካላቸውን፣ ትዳርና ማዕረጋቸውን ድንገት አጡ። ዋይታውን ቢያቀልጡት፣ ባለቤታቸውን ቢያንከላብሷቸው ነብሳቸው ከስጋቸው ተለይታለች እና መልስ አልነበረም። ያለ ኑዛዜ፣ ያለ ስንብት ድንገት ተለያዩ።

ገድለው ጥለውት ወደታች ወረዱ፤ ልጄ ነበርና ሬሳውን ከድነን ተቀመጥን፤ እንደዚያ ብለን አደርን፤ በበነጋታው ልጄ በጎችንና ፍየሎችን ፈትቶ ይዞ ወጣ፤ ይመጣል እያልኩ ባይ ባይ በዚያው ቅልጥ ብሎ ቀረ፤ ሬሳ ብቻዬን ይዤ አዎይ ጅቡ በላኝ፣ እዝጎ ስል፣ የልጄ ሚስት ከልጆቿ ጋር ሆና ቤት ተደበቀች፤ እኔም በጨለማ እየዳበስኩ ሄጄ የልጄ ልጅ አንዲት ጨቅላ አለች እሷን ይዤ መጣሁና ከሬሳው ጋር ቁጭ አልን❞ ተጨነቁ የሚደርስላቸው አልነበረም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደማችን እንደተከዜ ወንዝ ይፈሳል እንጂ የሰማዕታት አደራ አይታጠፍም!

ቀናት ተተካኩ፣ መብላትም ሆነ መጠጣት የለም፤ ጦርነቱ ግሏል። የወገን ጦር ክንዱ በርትቶ ጠላትን እየደመሰሰ ደረሰላቸው። ከተዋጊው ጦረኛ ጋር አንድ ልጃቸው ሲዋጋ ነበርና ሲበር ደረሰ። ልጃቸው ደርሶ መኖራቸውን አረጋገጠ። አባቱ የት እንደሄዱ ጠየቀ። ወይዘሮ የዝባለም ሞቷል ብለው ለመናገር ድፍረት አልነበራቸውም እና እንባቸውን እያፈሰሱ ዝም አሉት። አጥብቆ ጠየቃቸው። የማይቀረውን እውነት ነገሩት። ለቅሶው በረታ። ከማክሰኞ እስከ ቅዳሜ ድረስ በጭንቅ ውስጥ ከሬሳ ጋር ሰንብተዋልና እሳቸው ሐዘኑን መቋቋም አቅቷቸዋል። ❝ባለቤቴን ማክሰኞ ገድለውት እስከ ቅዳሜ አልጋ ላይ አስተኝቼ ሰነበትኩ” ብለዋል፡፡

ባለቤታቸው በሞቱ በአምስተኛው ቀን ወደ ቀብር ተወሰዱ። አፈር አልብሰው እያለቀሱ ተመለሱ። በጎችንና ፍየሎችን ይዞ እንደወጣ የቀረው ልጅ ጉዳይ ሌላ ጭንቅ ሆነ። በማግስቱ ልጃቸውን ይፈልጉ ጀመር። እርሱም እንደ አባቱ ሁሉ ላይመለስ አሸልቧል። ተገድሎ አገኙት። የከፋ በደል፤ ጨለማው ዋጣቸው፤ ቅዳሜ ባለቤታቸውን እሁድ ልጃቸውን ቀበሩተጎራብቷቸው ወግና ማዕረግ ያሳያቸውን ልጅ። ❝ከቤታችን ገብተው እህሉን ይዘው ይሄዳሉ፤ ጎታውን ይሰብራሉ፤ ሰንበቴ ልከፍል ድግስ ደግሼ ነበርና ጠላውን ይዘውት ሄዱ❞ ነው ያሉኝ። ያላደረሱባቸው ስቃይ እንደሌለም ነግረውኛል። ሰንበቴውን የሚከፍሉት ልጃቸው በተቀበረበት ቀን ነበር። መከራው ባይመጣ ኖሮ።

ከባለቤታቸው ጋር ሲኖሩ የነበረውን ዘመን ሲያስታውሱ ❝አይ እናቴ ሀብታም፣ በጣም ሀብታም ነበርን፤ ችግርና ረሃብ አናውቅም፤ ባለቤቴ ታታሪ አርሶአደር ነው። የሁለት ዓመታት የሦስት ዓመታት ጤፍ ነው የምንበላው። ያለ ሥራ ሌላ አያውቅም። ቤተክርስቲያን መሳም፣ ማረስ ማፈስ ነው ሥራው❞ ነው ያሉት። ያን አዱኛ ስላፈረሰባቸው፣ ደስታቸውን እና ማዕረጋቸውን ስለነጠቀባቸው ሐዘናቸው ከባድ ሆኗል። ❝ከቆረብን 25 ዓመት ሆኖናል። ለነፍሳችን ያደርን ነበር፤ ግብረ ሰላም ስናበላ የሚታረደው ሙከት ግሩም ነበር። አሁን ሁሉን ነገር ቀሙኝ፤ እኔ ሐሰት አልናገርም፤ ሀብታችንን ዘርፈውናል፤ ዶሮዎችን ሳይቀር ከፊቴ ላይ ነው እየመለጡ የበሏቸው።” ነው ያሉኝ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መንግሥት መንገደኞች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመግባት መብታቸውን እንዲያስከብር - ኢሰመጉ

እማማ የዝባለም ሐዘኑ በርትቶባቸዋል፤ የሚገቡት ቤት አልተውላቸውም፤ አፈራርሰውባቸዋል። በጭንቅ ሆነው፣ ሬሳ ታቅፈው ለእነዚያ ወራሪዎች እና ዘራፊዎች እውነታውን ከመናገር አላረፉም ነበር።

እንጀራ እያበላን፣ ጠላ እያጠጣን፣ የእኛ እህል እየተጫነ እናንተን ከችግር ሲያወጣ ነበር፣ አልኳቸው፤ ‘አንቺ ዝም በይ’ አሉኝ። ተው ምርትና ቃል ኪዳን ይክዳችኋል፤ አልኳቸው” ነው ያሉኝ። የልባቸውን እውነት ነግረዋቸዋል፤ ትናንትን እንዲያዩ አመላክተዋቸዋል።

ባለቤታቸው ከጣልያን ዘማቹ አባታቸው የወረሱትን ማስታወሻ ዘራፊዎቹ አንድ ሳያስቀሩ ወስደውታል። ያጌጡበት፣ ቤተክርስቲያን ይስሙበት የነበረውን ጋቢና ኩታም አልተውት ሳንዱቅ ከፍተው ሙልጭ አድርገው ወሰዱት እንጂ። እማማ የዝባለም ያ ሁሉ ሃብትና ንብረት አልፎ ዛሬ ላይ ምንም እንዳልነበራቸው ሆነዋል።

እማማ የዝባለምን ፈጣሪ ከሐዘናቸው ያበረታቸው ዘንድ ተመኝቼ፣ አመስግኛቸው ተሰናበትኳቸው። ሐዘናቸው ግን ተከትሎኛል።

በታርቆ ክንዴ

መስከረም 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share