እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ/አደረሰን!!

ባህልና ታሪክ

243038886 4760836177282518 3750432096373717473 n

የመስቀል በዓል!

የመስቀል በዓል ስናከብር ልናጤነው የሚገባን ዐቢይ ቁም ነገር አይሁድ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ በመቅበር እንዲረሳ ለማድረግ ቢሞክሩም በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት እንዴት እንደተገኘና የቀኝ እጁ የተቸነገረበት ክፋይ ወይም ግማድ እንዴት ወደ ሀገራችን እንደመጣ እንቃኛለን፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ይሁንላችሁ!
የመስቀል በዓል ታሪካዊ አመጣጥ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑና ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ፡፡

በ326 ዓ.ም. የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቀድ ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትንና የተጣለበትን አካባቢ ያውቅ ዘንድ ጠየቀችው፡፡ ሽማግሌውም “አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ እጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ” አላት እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። እንጨት ደምራ በዚያ ላይም ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡ ይህ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪርያኮስ ተብሏል፡፡

በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ. ም. ነበር፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶን እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ፡፡ ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት፡፡ በኋላም በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ዕብነ መሠረት ወይም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ለመሰቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ ተመርቆ የገባው (ቅዳሴ ቤቱ) የተከበረው መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም. ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት 10 ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረው መስከረም 17 በመሆኑ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

ይህ ዕለት ከ300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የምንዘክርበት በዚህም ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ደመራ በመደመር የመስቀል በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ይከበራል፡፡

የደመራ ትርጉም
ደመራ የሚለው ቃል – ደመረ፣ ጨመረ፣ አንድ አደረገ፤ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን መቀላቀልን፣ መገናኘትን፣ መሰብሰብን፣ መጣመርን፣ መዋሐድን በአጠቃላይ ሱታፌን፣ አንድነትን እና ኅብረትን ያመለክታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ቦታም ስለሆነም ደመራ እንጨቶች የሚደመሩበት የበዓለ መስቀል ዋዜማ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ በዓል ነው፡፡ መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።

በሀገራችን በኢትዮጵያ የመስቀልን በዓል ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት፥ ቅዳሴ በመቀደስና ማኅሌት በመቆም የምናከብረው ለዚህ ነው። በዚሁም ላይ ይህን ታላቅ ዕፀ መስቀል በወቅቱ የነበሩ ታላላቅ ነገሥታት የሚያደርጋቸውን ተዓምራት በማየት ለእያንዳንዳቸው ይደርሳቸው ዘንድ ከአራት ክፍል ሲከፍሉት ከአራቱ አንዱ የቀኝ እጁ ያረፈበት ግማድ /ክፋይ/ ብቻ በደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም ሲገኝ ሌሎች ሦስቱ ግን የት እንደደረሱ አይታወቅም።

መስቀሉ እንዴት ወደ ሀገራችን መጣ?
የጌታችን ቅዱስ መስቀል ወደ ሀገራችን ሊመጣ የቻለበት 1394 ዓ.ም. ሁለተኛ በነገሡ በ29ኛ ዓመታቸው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል 47ኛ በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ መኖር በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከታሰረበት ዝዋይ እስር ቤት የለም መባሉ ቤተሰቦቹን ግራ አጋብቷል

አፄ ዳዊት “ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት” ብለው አዋጅ በማወጅ ጦርነት ለማካሔድ ወስነው ወደ ካርቱም ጦራቸውን አዘመቱ፡፡ ካርቱም ደርሰው ሁኔታውን ሲያዩ ጦርነት ከማካሔድ ለምን የዐባይን ወንዝ አልገድብም ብለው ወሰኑ፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ፡፡
ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው፡፡

የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው፡፡ በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን የተቀጸል ጽጌ /የዐፄ መስቀል/ እየተባለ የሚከበረው ይህን መነሻ በማድረግ ነው፡፡

የታላቋን ንግሥት ዕሌኒን ታሪክ በማስታወስ መስከረም 17 የመስቀል በዓልን ካከበሩ በኋላ “መስቀልየ ይነብር በዲበ መስቀል /መስቀሌ በመስቀል ላይ ይኖራል/” የሚል ራእይ ታያቸው፡፡ “ይሔ ነገር ምሥጢሩ ምንድን ነው?” እያሉ በድንገት ሲናር ላይ አረፈው አጽማቸው ዳጋ እስጢፋኖስ አርፏል፡፡

በእሳቸው እግር የተተኩት ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል /መስቀሌን በመስቀልያ ስፍራ አስቀምጥ/” የሚል ራእይ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር አሳያቸው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት መልከዐ ምድር ውስጥ የመስቀል ቅርጽ ያለው የቀራንዮ አምሳል የሆነ ቦታ ከፈለጉትና ካጠኑ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል አሁን ግሼ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ደብረ ከርቤ አሁን እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ቦታ ላይ እንዲያርፍ አደረጉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ አየር መንገድ CNN ያሰራጨዉን ዘገባ እንዲያርም ጠየቀ

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም
የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም ወሎ ክፍለ ሃገር፣ አምባሰል ወረዳ ውስጥ ግሸን ተራራ አናት ላይ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት። ለዚች ቤተ ክርስቲያን መግቢያ አንድ መንገድ ብቻ ነው። እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይህች ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያየ ስያሜን አግኝታለች።
የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም መጠሪያ ስሞች

ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም መጠሪያ ስሞች በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል፡፡
• ከዐፄ ድልናአድ ዘመን /866 ዓ.ም/ እስከ 11ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ /ደብረ ከርቤ/ ትታወቅ ነበር።

• በ11ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔር አብ የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሰሩ ደብረ እግዚአብሔር በሚል ስም ታወቀች። ብዙ ሳይቆይ ግን ደብረ ነገሥት ተባለች።

• በ1446 ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን በዚህ ስፍራ ሲያርፍ ደብረ ነገሥት መባሏ ቀርቶ ደብረ ከርቤ ተባለች።
ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ “ገሰ” ወይም በአማርኛው “ገሰገሰ” የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተቀየረ። አካባቢው በዚህ ስም እንደተጠራ የግሸን ደብረ ከርቤ ገዳም ታሪክ የጻፉት የመሪጌታ የማነ ብርሃን አዲሴ መጽሐፍ በስፋት ይነግረናል፡፡

(አምደ ተዋህዶ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share