የኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ የ2014 ፡ ዓ.ም. ፡ መልካም ፡ ምኞት ፡ መልእክት ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ

መስከረም ፡ 1 ፡ ቀን ፡ 2014 ፡ ዓ.ም. ።
ገ_ዐዓ_20140101_ዐማርኛ
 የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.)
፡የ2014 ፡ ዓ.ም. ፡ መልካም ፡ ምኞት ፡ መልእክት ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ
የሙት ፡ ይዘት ፡ ትድገት ፥ የለም ፡ በዐዲስ ፡ ዓመት !
_______
ለንደን፥ መስከረም ፡ 1 ፡ ቀን ፥ 2014 ፡ ዓ.ም.።
የኢትዮጵያ ፡ ሕዝብ ፡ ሆይ!
ላለፉት ፡ ሠላሳ ፡ ዓመታት ፦
• ላልሠራኸው፡”ሕገ፡መንግሥት” ፣ ለሕገ ፡ ውንብድና ፡ ካልተገዛኽ ፡ እያለ ፡ ሲጨቍንኽ፥
• የኢትዮጵያ ፡ አንድያ ፡ ባለቤትነትኽን ፡ በመካድ ፡ “ሕዝቦች” ፡ እያለ ፡ እየመነዘረኽ ፡ ሀገርኽ ፡ ኢትዮጵያን ፡ ባለቤት ፡ አልባ ፡ ሲያደርግብኽ ፥
• እንደ ፡ እንስሳ ፡ በ”ክልል” ፡ ሲያግድኽ ፥
• ከታሪካውያን ፡ ጠላቶችኽ ፡ ጋራ ፡ ለጥፋትኽ ፡ ሲዶልትብኽና ፡ ባለቤት ፡ አልባ ፡ ሀገርኽን ፡ ሲቈራርስብኽና ፡ ሲያስበዘብዝብኽ ፡
የኖረውን ፡ ከሓዲውንና ፡ ንኅለተኛውን ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ይዘት ፥ እንሆ ፥ በአንድነት ፡ ክንድኽ ፡ ዐናቱን ፡ ወያኔ-ሕ.ወ.ሐ.ት.ን ፡ ቀልተኽ ፡ ብታሽቀነጥርበትም ፥ ቅሬታ ፡ አካሉ ፡ “ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.-ብልጽግና፡ፓርቲ-ሸኔ” ፡ ባፈሰሰለት ፡ የመሰንበቻ ፡ ዐቅም ፡ አንሰራርቶ ፥ አረመኔያዊ ፡ የፈሪ ፡ በትሩን ፡ ዳግም ፡ ሲያሳርፍብኽ ፡ ከርሟል ። አንተም ፡ ልትመክተውና ፡ ፈጽመኽ ፡ ልትደመስሰው ፡ ቈርጠኽ ፡ በመነሣት ፥ የተቀላ፟ ፡ ራሱ ፡ ወደወደቀበት ፡ ወደ ፡ ሰሜን ፡ ኢትዮጵያ ፡ እንሆ ፡ ተመ፟ኻል ።
“የዐዞ ፡ ክፋቱ ፥ ፊት ፥ ጥርሱ ፤ ዃላ ፥ ጅራቱ ።”
ነውና ፥ ዐዲስ ፡ አበባ ፡ ተቈርጦ ፡ እና ፡ አድብቶ ፡ የቈየ ፡ ቅሬታ ፡ አ���ሉን ፡ ፈጥነኽ ፡ ካላስወገድከውና ፡ መላ፟ ፡ ሀገርኽ ፡ ኢትዮጵያን ፡ መልሰኽ ፡ እእጅኽ ፡ ካላገባኻት ፡ በቀር ፥ አኹንም ፡ ከዠርባኽ ፡ ተከድተኽ ፡ መሥዋዕትኽ ፡ ዅሉ ፡ አላንዳች ፡ ጥርጥር ፡ ከንቱ ፡ ይኾንብኻል ።
ዐዲሱ ፡ ዓመት ፡ 2014 ፡ ዓ.ም. ፥ የፍጹም ፡ ድል ፡ ዓመት ፡ እንዲኾንልኽ ፥ ሕዝባዊ ፡ አንድነታዊ ፡ ውጥን ፡ አካልኽ ፡ የኾነው ፡ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.) ፡ ከልብ ፡ ይመኝልኻል ።
ጥንተ ፡ ጠላትኽን ፡ ፋሺስት ፡ ኢጣልያን ፡ ሚያዝያ ፡ 27 ፡ ቀን ፡ 1933 ፡ ዓ.ም. ፡ በዐርበኞችኽ ፡ ተጋድሎ ፡ ድል ፡ ብታደርጋትም ፥ ፍጹም ፡ ድል ፡ የተገኘው ፡ ግን ፥ ከመንፈቅ ፡ በዃላ ፥ ኅዳር ፡ 18 ፡ ቀን ፡ 1934 ፡ ዓ.ም. ፥ እጥንተ ፡ መዲናኽ ፡ ጐንደር ፡ ላይ ፡ መሽጎ ፡ የነበረው ፡ ቅሬታ ፡ አካሏ ፡ በዐርበኞችኽ ፡ ክንድ ፡ የተደመሰሰ ፡ ዕለት ፡ ነበር ። ዛሬም ፥ በሰማንያኛ ፡ ዓመቱ ፥ ባዲሱ ፡ ዓመት ፡ መባቻ ፥ ፈጽመኽ ፡ በምትተማመንበት ፡ አምላክኽ ፡ በእግዚአብሔር ፡ ኀይል ፡ ጸንተኽና ፥ ሀገራዊ ፡ ሰራዊትኽን ፡ በጠራ፟ ፡ አመራር ፡ እፊትኽ ፡ አስሰልፈኽ ፦
1) ወያኔ-ሕ.ወ.ሐ.ት.ን ፡ ፈጽመኽ ፡ የምትደመስስበትና ፥ አለቆቹን ፡ ለፍርድ ፡ የምታቀርብበት ፥
2) የወያኔ-ሕ.ወ.ሐ.ት. ፡ ቅሬታ ፡ አካል ፡ የኾነውን ፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፡ ቅሬታ ፡ ይዘት ፡ ገርስሰኽ ፡ በመጣል ፥ ከዛሬዋ ፡ መዲናኽ ፡ ዐዲስ ፡ አበባ ፡ ፈጽመኽ ፡ የምታስወግድበት ፥
3) መላ፟ ፡ ሀገርኽን ፡ ተቈጣጥረኽ ፥ ዳር ፡ ድንበሯን ፡ የምታስከብርበት ፥
4) በግፍ ፡ የታሰሩ ፡ ልጆችኽን ፡ የምታስፈታበትና ፡ የምትክስበት ፥
5) ሀገር ፡ ኢትዮጵያን ፡ የከዱና ፡ ያስበዘበዙ ፣ በደም ፡ የታጠቡ ፡ መንደር ፡ ገነኖችንና ፡ ሆድኛ ፡ ዐዳሪዎች ፡ ግብር ፡ ዐበሮቻቸውን ፡ ለፍርድ ፡ የምታቀርብበት ፥
6) ሀገራዊ ፡ እግዚእናኽን ፡ በማስከበር ፥ ሥልጡንሕዝባዊት ፡ ኢትዮጵያን ፡ ባዲስ ፡ ሕገ ፡ መንግሥት ፡ (ባዲስ ፡ ክዋኔ) ፡ ዳግም ፡ የምትከውንበት ፥
7) አንድነትን ፣ ነጻነትን ፣ ፍትሕን ፣ ሰላምንና ፡ ልማትን ፡ የምታገኝበት ፡
ዓመት ፡ እንዲኾንልኽ ፡ የኢትዮጵያውያን ፡ ሀገራዊ ፡ ሥልጡንሕዝባዊ ፡ አንድነት ፡ (ኢ.ሀ.ሥ.አ.) ፡ ከልብ ፡ ይመኝልኻል ፤ በምትፈጽመው ፡ ተጋድሎኽም ፡ ዅሉ ፡ ኢ.ሀ.ሥ.አ. ፡ ከጐንኽ ፡ አይለ፟ይ፟ም ፨
ትሑት፡አገልጋይኽ፦
ኢ.ሀ.ሥ.አ.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.