September 26, 2021
14 mins read

የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ ወቅታዊ ሁኔታ እና ትንበያ  –  ዋዜማው

ለተከበራቹህ ወገኖች                                                                           

olafscholz spd annalenabaerbock green arminlaschet cdu

እ.ኤ.አ September 26. 2021 መስከረም 16፣ 2014 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ የዓለምን የማራቶን ክብረ ወሰን ለማሻሻል በጀርመን ዋና ከተማ በበርሊን የሚሮጥበት ቀን ነው። ከሁሉም በላይ የዓለምን ትኩረት የሳበው ደግሞ 709 መቀመጫዎች (ወንበሮች) ያለው የጀርመን ብሔራዊ ምርጫ የሚደረግበት ዕለት መሆኑ ነው።  ልዩ የሚያደርገውም ከፍተኛ ተሰሚነት እና ተወዳጅነት ያላቸው የክርስቲያን ዲሞክራቷ መራሒተ መንግሥት አንጄላ ሜርክል Angela Merkel ከ16 ዓመታት ቻንስለረነት በኋላ በገዛ ፈቃደቸው በምርጫው አልወዳደርም በማለታቸው ማን እሳቸውን ይተካል? የሚለው ነው። በአሁኑ ምርጫ በእጩ ቻንስለርነት ክርስቲያን ዲሞክራቶች (CDU / CSU)  የፓርቲውን ሊቀመንበርን አርመን ላሼትን Armin Laschet ሲያቀርቡ፣ ሶሻል ዲሞክራቶቹ (SPD) ደግሞ የፋይናንስ ሚንስትር እና የቀድሞው የሐምቡርግ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ የነበሩትን ኦላፍ ሾልዝን Olaf Scholz፣  የአረንጓዴ ፓርቲ (Bündnis90 / Die Grünen) ደግሞ ሊቀመንበሩዋን አናሊና ቤይርቦክን Annalena Baerbock በእጩነት አቅርበዋል። ቢሆኑም በሕዝብ አስተያየት መመዘኛ ከፍተኛ የማሸነፍ ዕድል ያላቸው ሶሻል ዲሞክራቶቹ  ወይም ከእነሱ በ3 ፐርሰንት ዝቅ ብለው እየተከተሉ ያሉት የክርስትያን ዲሞክራቶች ናቸው።

የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ በአብላጫው እንደሚያሳየው ለቻንስለርነት የሚመኙት የሶሻል ዲሞክራቱን ሊቀመንበር፣ ኦላፍ ሾልዝን ነው። ቢሆንም በጣም በተቀራረበው አስተያየት መመዘኛ የተንሣ ውጤቱ ክፍት ነው። በምርጫ ጊዜ የነበሩት መወዳደሪያ ነጥቦች በጥቂቱ ከተመለከትን ስለአየር ንብረት ጥበቃ ፣ የጡረታ አበል ክፍያ፣ የገቢ ታክስ እና የኮሮና ወረርሽኝ ስላስከተለው ቀውስ  የመሳሰሉት ናቸው። ፕሮግራሞቻቸው የሚመሳሰል እንዳለበት ሁሉ ልዩነቶቹም ከፍተኛ ናቸው።  አንዳንድ ጊዜ ‹የመንግሥት ፕሮግራም› ፣ ‹የወደፊት ፕሮግራም› ብለው ያቀርቧቸዋል። የቻንስለር እጩዎች ሦስቱን የምርጫ ክርክሮች እና በፓርላማ ውስጥ ያሉትን ፓርቲዎች ክርክር እንዳየሁት እና የአንዳንዶቹን ፓርቲዎች አቋማቸውን እና ግቦቻቸውን ያቀረቡበት እስከ 200 ገጾች ፕሮግራሞቻቸውን  በገረፍታ እንደተረዳሁት አስተያየቴን እንደሚከተለው በጥቂቱ አቀርባልሁ።

  • ለምሳሌ ሶሻል ዲሞክራቶቹ ከድንጋይ ከሰል ኢነርጂ ለመውጣት ኢንዱስትሪውን ለአየር ንብረት ገለልተኛ የማድረጊያ ጊዜ ገደብ እ.ኤ.አ እስከ 2045  ሲያስቀምጡ፣ ሊበራሎቹ FDP ደግሞ የመውጫውን ገደብ እስከ 2050 ያደርሱታል። አረንጓዴዎች ደግሞ ከዚህ በአነስ ጊዜ ፓሪስ በተደረገው የአየር ንብረት ስምምነት መሠረት ኃላፊነትን መወጣት አለብን ይላሉ (በፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዓለም ሙቀት መጠን መጨመርን ከተቻለ ከሁለት ዲግሪ በታች ወደ 1.5 ዲግሪ ለመገደብ መስማማቱ አይዘነጋም። ይህንን ተከትሎ ብዙ ለውጦች ሲካሄዱ ለምሳሌ አንዳንድ መኪና አምራቾች በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን ብቻ ለማምረት የወሰኑ አሉ)። ክርስትያን ዲሞክራቶቹ የጊዜ ገደብ ማቅረብን ሳይሆን በምርምር እና በቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት በማድረግ ለአየር ንብረት ገለልተኛነት አዳዲስ ቴክኖሎጂ እንሥራ ይላሉ። የግራ ዘመም ፓርቲዎቹ Die LINKE ከናቶ (NATO) አባልነት በረዥም ጊዜ „መውጣት“፣ ለጦር መሣሪያ የሚውለውን በጀት ለዘላቂ ልማት አንዲውል እናደርጋለን ሲሉ፣ አማራጭ ለጀርመን AFD በመባል የሚታወቀው እና ከቀኝ አክራሪነት እስከ ዘረኝነት የሚፈርጁትን ያያዘው ፓርቲ ለውጭ አገር እርዳታ እና ለስደተኞች የሚወጣውን በጀት ለአገር ውስጥ እናውል ሲል የአየር ንብረት ፕሮግራማቸውም አይደለም።
  • በግብር/ በታክስ ፖሊሲ ውስጥም በፓርቲዎች መካከል ልዩነቶች አሉ። የኮሮና ቀውስ እና ባለፈው ሐምሌ ወር በተከሠተው የጎርፍ አደጋ በጀርመን ኢኮኖሜ እና በፋይናንስ ውስጥ ከፍተኛ ልዩነቶችን ፈጥሯል። ስለዚህ ሶሻል ዲሞክራቶቹ፣ አረንጓዴ እና ግራ ፓርቲ ሀብታሞች የበለጠ እንዲሸከሙ እና መረዳዳት እንዲፈጠር በማለት ለምሳሌ ሶሻል ዲሞክራቶቹ ከመቶ ሺ ዩሮ በላይ በዓመት ለሚያገኙት የገቢ ግብር/ታክስን ለመጨመር በተጓዳኙ ደግሞ በሰዓት የሚከፈለውን የደሞዝ ክፍያ ወደ 12.50 ዩሮ ለማሳደግ ይፈልጋሉ። የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ እና ሊበራሎቹ ደግሞ በሀብታሞች ላይ ታክስ መጨመር በሥራ ፈጣሪዎች ላይ ማነቆ ነው፣ የገንዘብ ነጻነት ሲኖር እና እፎይታ ኢንቨስትመንትን ይጨምራል በማለት የገቢ ታክስን መጨመር የሚለውን አይቀበሉትም።
  • የቤት ኪራይ የመጨመሪያ ወለልን ማስቀመጥ፣ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ከ67 ዓመት እንዳይበልጥ፣ የኮሮና ሎክዳውን በተመሳሳይ ሁኔት ተመልሶ እንዳይመጥ በሚለው የመከራከሪያ ነጥብ ላይ አብዛኞቹ ፓርቲዎቹ ይስማማሉ።
  • የሶሻል ዲሞክራቶቹ እና አረንጓዴዎቹ ልዩ ጥቅሞች የሚገኙበትን የግል ጤና ኢንሹራንስ ከመደበኛ የጤና ኢንሹራንስ ጋር ተዋሕዶ ለሁሉም ተመሳሳይ የሆነ “የዜጎች ኢንሹራንስን” ለመፍጠር እንደሚሠሩ አስቀምጠዋል።  የኮሮና ክትባትን በተመለከተ  ጀርመን ላይ የመከተብ ግዴታ እስከ አሁን ድረስ የለም። ቢሆንም በተለይም በተለያዩ የፌደራል ስቴቶች ያሉ ፖለቲከኞች ለመከተብ ለማይፈልጉት ጥቅም አስቀሪ መመሪያዎችን ለማውጣት ማዘጋጀታቸውን ብዙዎቹ ፓርቲዎች ይስማማሉ።

የምርጫ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ እንደሚያሳየው ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ታሪክ ሁለት ፓርቲዎች የሚፈጥሩት ጥምረት መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ከ50% በላይ መቀመጫ ስለማያስገኝ የግድ ሦስትዮሽ ጥምረት ያስፈልጋል። ባለፉት 4 ዓመታት በአንጄላ ሜርክል ሥር በጥምረት የመሩት የክርስትያን ዲሞክራቶች እና ሶሻል ዲሞክራቶቹ የፌደራሉን መንግሥት በጥምረት ለመምራት አብረው እንደማይቀጥሉ አስታውቀዋል።

የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ ከሊበራሎቹ እና ከአረንጓዴ ፓርቲ ጋር የጥምረት መንግሥት መመሥረትን ሲመኙ ብዙ የአረንጓዴ ፓርቲ አባላት ግን ይህንን አይቀበሉም። የሶሻል ዲሞክራቶቹ ከአረንጓዴዎቹ እና ሊበራሎች ወይም ከግራዎች ጋር ለመጣመር ይመርጣሉ። በኦላፍ ሾልዝ የሚመራው የሶሻል ዲሞክራቶቹ እና የአረንጓዴዎቹ መንግሥት (ሦስተኛ ፓርቲ ተጨምሮበት)  አሁን ካለው ወይም በአርሚን ላሼት በሚመራው የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ እና ሊበራሎቹ ጥምረት (ሦስተኛ ፓርቲ ተጨምሮበት) በአፍሪካ ወይም የተለየ ፖሊሲ እንደማይኖረው ይጠበቃል። ወግ አጥባቂዎቹ የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ በታሪካቸው ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሲኖራቸው ሶሻል ዲሞክራቶቹ ከአሜሪካ ጋር መልካም ግንኙነት ቢኖራቸውም በአለፈው የኢራቅ ጦርነት ጊዜ የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ጌርሃርድ ሽሯይደር ወታደሮችን አልክም ብለው መቃቃራቸው አይዘነጋም።

የጀርመን መሪዎች ለኢትዮጵያ ጥሩ አመለካከት ያላቸው ሲሆን አንጄላ ሜርከል አፍሪካን የሚወዱ እንደ ሶሻል ዲሞክራቱ ጌርሃርድ ሽሯይደር ወደ ኢትዮጵያ ሄደው አገሪቱን መጎብኘታቸው ይታወቃል። የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በተመለከተ የጀርመን ፖለቲከኞች የአፍሪካ ኅብረትን የመፍትሔ ሐሳብ እንደሚደግፉ ማስታወቃቸው አይረሳም። ለኢትዮጵያ ልዩ ቅርበት የነበራቸው የኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትሩ ጌርድ ሙለር ፓርቲያቸው የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ ቢያሸነፉ እንኳ ተመልሰው አይቀጥሉም ምክንያቱም የUNIDO ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ተሾመዋልና።

ከብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሰማው አዲሱ የመንግሥት ምሥረታ ድርድር ከምርጫው በኋላ በርካታ ወራትን ሊፈጅ እንደሚችል ይተነብያሉ።

የተመጣጠነ የጀርመን የምርጫ ስራዓት ለኢትዮጵያ ተመክሮ ሊሆን ይችላል። ያሸነፈ ሁሉን ይወስዳል በሚለው ብቻ ሳይሆን በቀጥታ የሚያሸንፈው ተወዳዳሪ እና ከ5% በላይ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎች የሚያቀርቡት እጩዎች እንደየፐርስንታቸው ፓርላማ ይገባሉ።

መልካም የብረሃነ የመስቀል በዓል እና ሰላማዊ ምርጫ በጀርመን!
                                   

ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

——-

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop