መልዕክተ 2014 ዓ/ም – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

” Therefore, one who becomes a prince through the favor of the people ought to keep them friendly, and this he can easily do seeing they only ask not to be oppressed by him. But one who, in opposition to the people, becomes a prince by the favor of the nobles, ought, above everything, to seek to win the people over to himself, and this he may easily do if he takes them under his protection. Because men, when they receive good from him of whom they were expecting evil, are bound more closely to their benefactor; thus the people quickly become more devoted to him than if he had been raised to the principality by their favors; and the prince can win their affections in many ways, but as these vary according to the circumstances one cannot give fixed rules, so I omit them; but, I repeat, it is necessary for a prince to have the people friendly, otherwise he has no security in adversity… ”

( ” THE PRINCE ” Nicolo machiavelli page 78 )

በህዝብ ይሁንታ ለሥልጣን የበቃ የአገር መሪ ( ልኡል ) የሚጠበቅበት የህዝብ ፍቅር ግለቱን ሳይቀንስ እንዲቀጥል ፣ ከህዝብ ጋር ያለው ወዳጅነት የበለጠ እየጠበቀ እንዲሄድ ማድረግ ይኖርበታል ። ይህንን ማድረግ ደግሞ ቀላል ነው ። ህዝብ ጭቋኝ መንግስትን ስለሚጠላ የጭቆናን ቀምበር በህዝብ ትከሻ ላይ ለመጫን መቃጣት ፈፅሞ የለበትም ። በህዝብ ይሁንታ ወደ ሥልጣን የመጣ መሪ ከህዝብ ፍቃድ ውጪ እርምጃውን ካደረገ ከህዝብ ሥለሚነጠል ሥልጣኑንን በቀላሉ ያጣልና ማንኛውንም አርምጃውን ከህዝብ ፍላጎት ጋር ማድረግ ይጠበቅበታል ።

ከህዝብ ይሁንታ ውጪ ፣ በሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ( መሣፍንቶች ) ድጋፍ ለሥልጣን የበቃ የአገር መሪ ( ልዑል ) ቢሆን እንኳን ፣ በሥልጣን ለመሰንበት ከፈለገ ፤ በአሸናፊነት በትረ ሥልጣኑንን እንደያዘ ፣ ፍቅደውም ሆነ ተገደው ከተሸናፊው መንግሥት ጎን ተሠልፈው ለነበሩት ሁሉ ምህረት ና ይቅርታ በማድረግ ፍቅራቸውን ማትረፍ ይኖርበታል ። ህዝቡ ከቀደመው ሥርዓት በተሻለ ነፃነት ኑሮውን እንዲመራና ህይወትን እንዲኖራት የማድረግ ድጋፉን በግልጽ መስጠት አለበት ። ህዝብ ጭቆና የሌለበትን ህይወት መሪ እንዲሆን ደግሞ የቀደመውን በኃይልና በፍርደ ገምድልነት የሚመራውን ቢሮክራሲ በመቀየር ተጨባጭ የሆነ የህዝብ ቅቡልነት ያለው ቢሮክራሲ በመላ አገሩ መዘርጋት ተቀዳሚ ሥራው መሆን አለበት ። ሽንገላ የሌለበት ፤ ያልተቀባባ ፤ አግላይ ያልሆነ የፖለቲካ ሥርዓትን ፤የሞራል ልልና ባላቸው ባለስልጣናቱ በአገሩ ካላሰፈነ ግን ፤ አልጋው ሊረጋለት አይችልም ። አልጋው የማይረጋለትም በመላ አገሩ “ በቢሮክራሲ ሥም “ በየቀያቸው እውነተኛ ፍትህን ሥለሚነፈጉ ፣ እውነተኛ ፍትህን አጥተው በባርነት ከሚኖሩ ለክብራቸውና ለነፃነታቸው ሲሉ በሥርዓቱ ላይ ማመፅ ስለሚጀምሩ ነው ። … “

እዚህ ላይ ፣ህዝብ በጭቆና ሲሰቃይ ድንገት ደርሶለት ፣ ጨቋኝን ላሶገደለት ጉልበታም ልዑል (የፖለቲካ ፖርታ ና መሪ ) ሁሉ ፣ ድጋፉን በዩሉንታ እንደሚሰጥ ማሥተዋል መልካም ነው ። ግፉአን የተፈፀመባቸውን ግፍ ባይረሱትም ፣ ከአሰቃያቸው ገዢ ነፃ ያወጣቸውን ገዢ በውለታ ዕዳ ተይዘው ንግሥናውን በይሁንታ ይቀበላሉ ። ይኽ ደጋፋቸው የሚቀጥለው ግን አገዛዙ ጨቆኝ ያለመሆኑንን በየዕለቱ በተግባር እያረጋገጠ እስከሄደ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው። ይለናል ማኬቬሊ ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፣ ማክቬሊ የፖለቲካ ሊቅነቱን በዛ ዘመን ባስመሰከረበት ልዑል በተሰኘ መፅሐፉ ፣ ለአገር መሪዎች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል ።

አንድ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘ መሪ ( ልዑል ) በህዝብ ተወዳጅ ሆኖ ለመዝለቅ የሚችልበት የተለያዩ የአገዛዝ መንገዶች እንዳሉ ቢታወቅም ፤ ከህዝብ ላይ ጭቆናንን አስወግዶ ፣ ጠንካራ ተቋማትን ገንብቶ ፣ ፍትህን በመላው አገር እንዳሰፈነ አይነት ሥርዓተ መንግሥት ቅቡልነት ያለው በዓለም አይገኝም ። በአገዛዙ ሥርዓት ፍትሃዊነት ሰበብ ፣ የአጠቃላይ ህዝቡን ቅቡልነት ያገኘ መሪ ደግሞ ፤ የተደላደለ መንበር ይኖረዋል ። በጭቆና ፣ በኃይል ና በያዘው በትር ፣ ተቀናቃኙን ባሶገደበት መንገድ ህዝብን ቀጥቅጦ ና አንቀጥቅጦ ፤ በጭቆና ቀንበር ውስጥ አስገብቶ ፣ እየበዘበዘ ለመግዛት ቆርጦ የተነሳ መሪ ግን በመንበሩ ላይ አይሰነብትም ፡፡ በማለት ፡፡…

ኒኮሎ ማኪያቬሊ ፣ ወደ ኢጣላዊዋ ፣ፍሎራንሥ ምድር የመጣው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 3 / 1969 /ም ሲሆን ፤ ነፍሱ ከሥጋው የተለየችው ደግሞ ሰኔ 21/ 1527 ( እኤአ ) እንደሆነ ዊኪፒዲያ ላይ ከተፃፈው የህይወት ታሪኩ መረዳት ይቻላል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከኖርዲክና ስካንዲኔቭያ ሃገሮች ዴሞክራሲ ምን እንማራለን? - በ.ከ.

ሰውየው የተዋጣለት ጦረኛ ጀነራል ፣ ሥመጥር ዲፕሎማት ፣ የታሪክ አዋቂ ፣ ፈላስፋ ና የህዝብ አሥተዳደር ሊቅ ነበር ።

በዘመኑ ከሚታወቁ ሥመ ጥር ምሁራን ተርታ የሚሰለፈው ማኪያቬሊ፣ በጥልቅ አሳቢዎቹ በነ ሩሶ ና ስፔኖዛ የሚደናቅ የፖለቲካ አመለካከት ነበረው ።

በገሃዱ ዓለም የፖለቲካ እንቅሥቃሴ ውሥጥ የመንግሥት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ከማኬቬሌ በላይ ያብራራ ሊቅ በዛን ዘመን አልነበረም ።

የጠንካራ መንግሥትን አወቃቀርና ሚናንን በተመለከተ ሉዑል ( The prince ) በተሰኘ መፀሐፉ በጥልቀት አብራርቷል ። ለሥልጣን ሲባል በሴራ መግደልን ና የአገዳደሉን መንገድ የተለያዩ ልኡላን ወደ ሥልጣን የመጡበትን ታሪክ በመፀሐፉ በመጥቀስ ካሮትብቻ ሳይሆን በትርም አገር ለመግዛት እጅግ አሥፈላጊ ነው ። በማለቱ በጥቂት ምሁራን ውግዘት ና የእርኩሰት መምህር ( Teacher of evil ) እሥከመባል ቢደርሥም ፤ አውሮፓውያኑ ይኽ ከንቱ ወቀሳ ነው ፡፡ በማለት የእኛ የዘመናዊ፣ ፖለቲካ ፍልሥፍና እና የፖለቲካ ሳይንሥ አባት ማኬቬሊ ነው ፡፡ ( The father of modern political philosophy and political science. ) ” በማለት በአስተምህሮቱ ዛሬም ድረስ ፣ከዘመኑ ጋር እየበረዙ ይጠቀሙበታል ፡፡

ማኬቬሊ በአርሱ ዘመን በልዩ፣ልዩ ግዛት በተከፋፈለችው ኢጣሊያ የፍሎረንሥ ግዛት ከፍተኛ ባለሥልጣን ከመሆኑም በላይ ወታደራዊውን ጉዳይ በበላይነት የሚመራ የጦር ጀነራልም ነበር ።

ማኬቬሊ ፣ የመንግሥት ሥልጣንን በቅጡ ለመጠቀም የግለሰብን የግል ሞራል ና የቡድንን ሞራል በሚገባ ማወቅ እንደሚያሥፈልግ ይመክራል ፡፡ በህዝብ መሐል ዝነኛ እና ቅቡልነት ያለው መሪ ለመሆን የአጠቃላይ ህዝቡን ሞራል እንጂ የግለሰቦችን ሞራል ለመጠበቀ መባዘን የለበትም ፡፡ ዜጎችን ሁሉ ድርጊት በመፈፀም ተወዳጅነቱን የሚጨምር ተግባር ሁሌም ለመከወን መጣር እንጂ በጥቂት ግለሰቦች ሞራል ግንባታ ላይ በማተኮር የብዙኃኑን ሞራል መጨፍለቅ ፣የራስን ውድቀት ያፋጥናል ባይ ነው ፡፡

ሥለሞራል አብዝቶ በመጨነቅ ፣ ፊት ለፊት የተደቀነን አውዳሚ አደጋን ችላ ማለት ና መሰናክሉን ገለል ከማድረግ መዘግየት ፤ ወይም መዘናጋት የኋላ ፣ ኋላ የማይቀለበስ አደጋ ሊያሥከትል እንደሚችል አጥብቆ ይመክራል ።

ሥህተት ቢሆንም ቀድሞ የኃይል እርምጃ በመውሰድ አደጋ አዋላጁን ከማሶገድ መቆጠብ የሚያሥከፍለው አደጋ የማይቀለበስ ይሆናል ፡፡ ፊት ለፊት የመጣብህን አደጋ ሥለሞራል በመጨነቅ ልትመክተው ካቅማማህ የአደጋው ሰለባ ትሆናለህ ። በማለት ፣ ልዑላን ግልፅና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የማይቀለበሥ አደጋ ከፊታቸው ተደቅኖ በሞራል አመካኝተው እጃቸውን አጣምረው ቁጭ ካሉ ፣ ቁጭ ባሉበት እንደሚቀበሩ ፣ በበዙ ምሳሌዎች ያሳስባል ።

( አንባቢ ሆይ ፣ በዚኽ የማኬቬሊ ፍልስፍና መሠረት ኃያሏን ጃፖን በአንድ ጊዜ አቅመ ቢስ ያደረጋት የአሜሪካ አቶሚክ ቦንብ መሆኑንን አትዘንጋ ። ሄሮሽማና ናጋሳኪ የተባሉ ሁለት ከተሟችን እሥከነ ህዝባቸው እምሽክ ያደረገውን አውቶሚክ ቦንብ ፤ ግዙፉን እና ጀግናውን የጃፖን ጦር ከግዛት ማስፋፋት አላማው እንዳቀበውም አትዘንጋ !! የጀፓን ህዝብ በዚህ ሥቃይን በሚያበዛ ፣ ሰቅጣጭ ሞትን አሥከታይ አቶሚክ ቦንብ ከሚያልቅ ጦርነቱን ለማቆም መወሰኑ ተገቢ ነው ። …. )

በማኬቬሊ እምነት ፤ ማንኛውም አገዛዝ የበዛና የሠለጠነ ሠራዊት ኖሮት ፤ የሚያሥተዳድረውን ህዝብ በተደጋጋሚ ፣ ቅቡልነት የሌለው ሞራለ ቢስ ተግባር በመፈጸም የሚያሳዝነው ከሆነ ፤ የልኡሉ ወታደሮቹም ሥርዓት የሌላቸው ና ቀምቶ በይዎች ከሆኑ ፤ በጉልበተኛ ና በቀማኛ ወታደራዊ ኃይሉ መከታነት ብቻ በሥልጣን ላይ ለመሰንበት ከቶም አይችልም ። …”

እውነት ነው ። የአንድ አገር መንግሥት በሥልጣን ለመሰንበት ከፈለገ ፣ የሚያስተዳድረውን ህዝብ ልባዊ ፍቅር ማግኘት ይኖርበታል ። ከሚያስተዳድረው ህዝብ ፍቅር ለማግኘትም ዜጎች አለአድሎ እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ቅቡልነት ያለው ፍትሐዊ ሥርዓት መዘርጋት አለበት ።

ይህ ፍትሐዊ ሥርዓትም ለእያንዳንዱ ዜጋ እኩል አገልጋይነቱን በኢኮኖሚያዊ ፣ በሶሻል እና በፖለቲካዊ ሥርዓተ መዋቅሩ በተግባር የሚያረጋግጥ ሆኖ መቀረፅ ይኖርበታል ።

መንግሥታዊ ሥርዓቱም ፣ ዜጎችን በአንድ ዐይን በሚመለከት የሶሾ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት ካልቀረፀ በስተቀር ህዝቡ የተረጋጋ ፤ አገርም ሰላም የሰፈነበት አይሆንም ።

መንግሥት በግጭት ላይ ያልተመሠረተ ቅብብሎሽ ፤ ህዝብም የሰከነ እና የጣመ ህይወት የሚኖረው መላው ዜጋ የሚተዳደርበት ሥርዓተ መንግሥት ለጠበበ የቡድን መብት ያላደለና ከፋፋይ የሆነ ህገ መንግሥትም ከሌለው ብቻ ነው ።

አንድ አገርን እና ዜጎቿን ለመጠበቅ ና ለማሥተዳደር የመሪው ወንበር ላይ የተቀመጠ መንግሥት እጅግ በመጥበበ ፤ በአይጠረቄነት በመስገብገብ ፤ በገዳይ በትር ፤ አንዳንዴም በሽንገላ እየደለልኩ ለረዢም ዓመት ሥልጣን ላይ እቆያለሁ ብሎ ካሰበ ፣ ማሥተዋልና ጥበብ በአይምሮው ስሌለለው ሥልጣኑን ከማሳጠር ውጪ የሚያተርፈው አንዳች ነገር የለም ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕዝብን ሊያፋጁ የተነሱ የጉግ ማንጉጉ መንግስታት ተላላኪዎች!! - ተዘራ አሰጉ

ከዚህ ትንታኔ አንፃር ፤ ከመስከረም 24 ቀን 2014 /ም በኋላ የብልጽግናን ፓርቲ አገር አበልጻጊነትን መገምገም እንጀምራለን ፡፡

በኢትዮጵያ ከመስከረም 24 ቀን / 2014 /ም በኋላ በብልፅግና ፓርቲ የሚመሰረተው መንግስት ካድሬ መር እንደማይሆንም ተስፋ እናደርጋለን ፡፡ የፓርቲና የመንግስት አሰራርም በግልፅ እንደሚለይና ዜጎች በሰለጠነ መንገድ መንግስታዊ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚስችል ዘመናዊ አስተዳደር ገዢው ፓርቲ በሁሉም የአገሪቱ ቀበሌዎች እንደሚዘረጋም እናልማለን ፡፡ እርግጥ ነው ፤ ማስተዋል ያለው መንግስት ከመስከረም 24 ቀን 2014 /ም በኋላ እንደሚኖረን ተስፋ ያደረግን ዜጎች ሚሊዮኖች ነን ፡፡ ብልፅግና የቀደመውን የመንግስት ሽግግር ታሪካችንን በቅጡ በማስታወስ መጥፎ ታሪካችንን ይደግማል ብዬ … አላስብም ፡፡ ይሁን እንጂ ለትውስታ መልካም እንዲሆነው በማሰብ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የቅርብ ግዜ የኢትዮጵያን መንግስት የሥልጣን ሽግግር ሣንካ እና የሤራ ጥልፍልፍ እኩይ ተግባራት ፤ መለስ ብለው እንዲቃኙ ግን አጥብቄ አሳስባለሁ ፡፡

የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያን መንግሥታት የስልጣን ሽግግርን ስናስተውል ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል አሥተዋይ ና ብልህ እንደነበር ፤በአንፃሩ የመንግስትን ቁንጮ ሥልጣን የተቆጣጠሩት አንዳንድ ግለሰቦችና እና ግብረአበሮቻቸው ፤ ምን ያህል ግትርና ነገን ማስተዋል የተሳናቸው እንደነበሩ ከታሪካቸው መገንዘብ እንችላለን ።

. ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለስላሴ

ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ ፤በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጪ ነባራዊ እውነታዎች ገፊ ምክንያት ምሁራዊ ጸረ ፈውዳሊዝም ንቅናቄ በዙሪያቸው መጋጋሉን በመገንዘብና በየጊዜው እየነቃ የአገዛዝ ሥርዓቱ እንዲቀየር እየወተወተ ና እያመጸ የመጣውን የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት በመረዳት ፤ እነደ እንጊሊዝ ዓይነት ንጉሣዊ ሥርዓተ መንግስት ገንብተው… ፤ በክብር በቤተ መንግስታቸው እንደመቀመጥ ፤ የዓለምን ፖለቲካ ባለማስተዋል ፤ በመለኮታዊ ሥልጣን እያሥፈራሩ ፤እኔ ከአምላክ ( ከፈጣሪ ) የተቀባሁ ነኝ ፡፡ ማንም ኃይማኖተኛ ጫፊን አይነካም ፡፡ በማለት ፤ የአገሪቱን ሀብት ጠቅልለው በመያዝ ሰጪ ና ነሺ ፤ መሐሪ ና ገዳይ ! ” ንጉሡ ብቻ መሆናቸውን ፤ ዜጋው አምኖ እንዲኖር ቢፈልጉም ፤ቀስ በቀስ እየተቀጣጠለ የመጣውን የህዝብ የቁጣ እሳት ለማጥፋት ባለመቻላቸው የካቲትት 1966 የጀመረው ግብታዊውው ዓብዮት ወታደራዊውን ደርግ አዋልዶ መሥከረም 2/1967 /ም ከ54 ዓመታት ገዢነታቸው ከዛ በክብር ከተቀመጡበት ዙፋን አውርዶ ፣ በቮልስ ዎገን ውሥጥ ከቶ ከቤተ መንግስት በማስወጣት ፣ የቁም እሥረኛ በሆኑበት ሚጢጢ ቪላ ቤት ውሥጥ ለጥቂት ወራት አሥቀምጦ የኋላ ኋላ ገድሏቸዋል ።

. ” ደርግ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት በኋላ ደግሞ ኢሠፓ

ግብታዊው አብዮት ፤ከመስከረም 2 ቀን / 1967 /ም ጀምሮ ራሱን ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት አድርጎ ሾመ ። የመንግሥት መሪነቱንም ለጀነራል አማን አምዶም በመስጠት አገር መምራትን ብሎ ጀመረ ። እሳቸውንም ብዙም ሳይሰነብቱ ከሻአብያ ጋር አብረዋል በማለት በሴራ ፖለቲካ ገደላቸው ። በእግራቸውም ጀነራል ተፈሪ ዋና ሊቀመንበር ፤ ሻለቃ መንግሥቱ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ፤ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ሆነው ተመራረጡ ። በርጋዴር ጀነራል ተፈሪ ባንቲም ለሁለት ዓመት ከሁለት ወር ( 28 November 1974 – 3 February 1977 ) አገርን ሲመሩ ቆይተው ፤ ከደርግ የግራ ፖለተካ ከመቆም ይልቅ በተቃራኒ ከቆሙት ቀኞች ጋር አብረዋል በማለት ( ከካፒታሊስቱ ጎራ ጋር ) ደርግ ገደላቸው ና አብዮቱ የራሱን ልጆች መብላት መጀመሯን አበሰረ ። ቀጥሎም ምክትል ሊቀመንበሩ ሌ/ኮ አጥናፉን በግልፅ አቋማቸው እና ከኮ/ሌ መግሥቱ የቀደመ ተራማጅ አሥተሣሠብ ሥለነበራቸው ፤ ለመንግሥቱ ሥልጣን መደላድል እንቅፋት በመሆናቸው በሴራ ፖለቲካ ተገደሉ ።

/ሌ መንግሥቱ ኃ/ማርያም እና ወታደራዊው የሴራ ቡድናቸው ፤ አገርን በሰለጠኑበት እና በሚያቁት ሙያ ከመጠበቅ ይልቅ ለሥልጣን በመቋመጣቸው ፤ የወቅቱ የሶሻሊሥት ና የኢምፔሪያሊዝም ሹክቻ መደረክ አገሪቱ እንድትሆን ባለማወቅ ፈቀዱ ፡፡ እናም ፣ ኢትዮጵያ በቀኃሥ ዘመን ከነበራት ዝና ፣ ሀብት ና የብልፅግና ጉዞ ገቷት ፡፡ በአፍሪካ ና በዓለም ከተጎናፀፈችው ክብር ና የኢኮኖሚ የበላይነትም በአጭር ጊዜ ቁልቁል ወርዳ የደሃ ፣ ደሃ እንድትሆን አደረጎት ።

ለኢትዮጵያ የቁልቁለት ጉዞ አሥተዋፆ ያደረጉት ደርጎች ብቻ አልነበሩም ። የሰሜኑ የአገራችን ክፍል የነፃ አውጪ ደርጅቶች ( ጀብሐ ፣ ሻብያና ህውሓት ) በግብፅ ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ሲደገፉ የነበሩ ፣ የኢትዮጵያ ድህነት ሰበቦች ነበሩ ። ደርግ በእነዚህ በኢትዮጵያ ጠላቶች በሚደገፉ ተገንጣይ ቡድኖች 17 ዓመታት አገር አላስገነጥልም ብሎ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጎኑ አሰልፎ ሲዋጋ መኖሩ ይታወቃል ፡፡ይኽ ጦርነት የአገሪቱን ኢኮኖሚ መብለቱን ማንም ለማሥተባበል አይችልም ። እናም ደርግ አሥተውሎት ያጣው ከጅምሩ ሥልጣን ፈላጊ በሆኑ ሴረኞች በመጠለፉ የተነሳ ፣ በእጁ የገባውን ዕድል ለአገር ጥቅም ለማዋል አቅቶታል ፡፡ ችግሮችን በውይይት እና በሰጥቶ መቀበል ለመፍታት ቀናነት ብቻ ሳይሆን የወቅቱም ሁኔታ አልፈቀደለትም ነበር ። ዋናዋ ሶሻሊስት እና የኃይል ሚዛን ጠባቂዋ ታላቋ ሶቬት ህብረት ፣ በጉርቫቾቭና በየልሲን የዋህነት እና በአሜሪካ ሴራ መጠለፍ የተነሳ ደርግ እጀ ሰባራ ሆኖ ነበር ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኦነግ ምክንያት የታሰሩ የኦሮሞ ወጣቶችም ይፈቱ | ቡልቻ ደመቅሳ

1983 /ም ብቸኛ ልዕለ ኃያል መንግስት በሆነችው በኢፔሪያሊሥቷ አሜሪካ አማካኝነት ደርግን ከሥልጣኑ ያሶገደው ወያኔም ፣ ባልሰራው ገድል እና ነፃ የማውጣት ጀብዱ የተወጣጠረ ግብዝ በመሆኑ ፣ የነፃ አውጪ ካባውን ሳያወልቅ በዓፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ዘው ብሎ በመግባት ፣ ታላቅ የሆነችውን አገር አኮስሶ በዘውግ ሸንሽኖ ፣ በቋንቋ ፖለቲካ 27 ዓመት ገዛ ። በ27 ዓመት ያገዛዝ ዘመኑ ግን ከህዝብ ጥላቻን እንጂ ፍቅርን አላተረፈም ።

ሲጀመር ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በቋንቋ ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ እንዳይግባባ ና እንዳይጋባ ፣ ከሰው ባህሪ እና ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ህዝብ እንዲፈጠር ፤ ከቶም የማይቻለውን የፆታን ፍቅር ፈፅሞ ለመደምሰስ በብርቱ በማሴር የቋንቋን አጥር አጥሮ ከቶ እንዴት በዜጎች ሊወደድ ይችላል ?

ከሰው ማህበራዊነት ና ተፈጥሯዊነት ያፈነገጠ የዘውግ ፣ የጎሣ እና የመንደር ፖለቲካ እያራገቡ ፣ እንዴት በተደላደለ መንበር ላይ ለመቀመጥስ ይቻላል ?

ዛሬ በቀቢፀ ተስፋ ሳይሆን አጥፍቶ በመጥፋት ሃሰብ ( እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በማለት ) የትግራይን ህዝብ በማያምንበት ጦርነት በግድ ያሰለፈው ወያኔ ከ27 ዓመት በኋላ ፣ ከመንበሩ ሰውነትን እና ክብርን በሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ከሥልጣን ተወግዷል ፡፡ከስልጣኑ ከተወገደ በኋላ ፣ ከወያኔ / ኢህአዴግ ውሥጥ በወጡ ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በሚያከብሩ ኢህአዲጋዊያን የለውጥ መሪዎች መንበሩ መተካቱም ይታወቃል ። በለውጡ ውስጥ የበለፀገ አእምሮ ያላቸውና የቀጨጨ አእምሮ ያላቸው ተፋልመው የበለፀገ አእምሮ ያላቸው አሸንፈዋል ፡፡ ነገም እንደሚያሸንፉ አስባለሁ ፡፡

. ብልፅግና ፓርቲ

ከመስከረም በኋላ የሚመሰረተው መንግስት ፤ የኢትዮጵያን ዜጎች ሥሜት እና ፍላጎት ተከትሎ የሚጎዝ እንጂ ፤80 ብሔረሰቦችን ንቆ ለጥቂቶቹ ሞገስን ሰጥቶ ፣ እንደ ዘመነ ወያኔ በጠበበ የዘረኝነት መንገድ መጎዝን እንደማይመርጥም ብዙዎቻችን ተስፋ አድረገናል ፡፡ የዜጎችን ፣ የሥራ ና የኑሮ ዋሥትና የሚያሳጡ በተለይም የኢትዮጵያን ወጣት የሚከፋፍሉ ህገመግስታዊ ሽፋን ያላቸው የአፓርታይድ አሰራሮች በፍጥነት ታርመው ፤ በየክልሉ ከተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች ዓላማ ጋር የማይሄዱ ፤ ከዜግነት መርህ ጭራሽ ያፈነገጡ የሥራ ቅጥሮችንም በአፋጣኝ በማረም በየቤታቸው የሚያለቅሱትን ምሩቃን እንባ እንደሚያብስም አልመናል ፡፡ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እናት ናት ። በማለት ልጆቿ በእኩል ደረጃ አገልጋይዋና በመሰቧ ዙርያም በክብር ተቀምጠው በእኩልነት ተመጋቢ እንደሚሆኑም አምናለሁ ፡፡

ከዩኒቨርስቲ በሚመረቁ ወጣቶቻችን ላይ እሥከአሁን አፓርታይዳዊ መድሎ እየተፈፀመባቸው እንደሆነም በመገንዘብ አዲሱ መንግስት አስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰውድም ተስፋ እናደርጋለን ። ነገ ይኽቺን አገር የሚረከቧት እነዚህ የተማሩ ወጣቶች ፤ በሥራ እጦት ሳብያ እርስ በራሳቸው የሚቃረኑበትን መንገድ ወያኔ ፈጥሮልን ላይመለስ መሄዱን መቼም የሚዘነጋ አይመስለንም ፡፡ አንዱ በልቶ አዳሪ ሌላውን ተመፅዎች በማድረግም በአንድ አገር ዜጎች መካከል ጥላቻን ዘርቷል ፡፡ ይኽንን ወላፈንድ ፣ ካለሶገድን በስተቀር ፣ በእንዲህ ዓይነት ከፋፋይነትን በሚያደምቅ የሥራ ቅጥር ወደፊት ሥለኢትዮጵያ አንድነትና ብልፅግና ማውራት አንችልምና ፡፡ ዛሬ ና አሁን የተፈጠረውንም የአንድነት ፣ የፍቅርና የወድማማችነት መንፈስ ወደ በጎ ለመቀየር ከተፈለገ ፣ አዲሱ መንግስት ይኽ ወቅት መልካም አጋጣሚ መሆኑን በውል እንደሚገነዘብ እናምናለን ፡፡

በነገሬ ላይ ፤ በማሥተማር ሙያ ከየዩኒቨርስታዎቻችን የተመረቀ ወጣትን በትልልቅ ከተሞች ውሥጥ ባሉ ህብረ ብሔራዊ ገፅታ ባላቸው ት/ቤቶች ውሥጥ ፣የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አፋን ኦሮሞ ካልቻልክ አልቀጥርህም ካለ ፣ ( የህንድ ፤ የአውሮፓ ና የአሜሪካ ዜጎችን ኦሮምኛ ሳያውቁ ዜጎቻችንን እንዲያሥተምሩ በግልፅ በአደባባይ እየቀጠርን ) ፤ አማራ ፣ ትግራይ ፣ ሱማሌ፣ ሲዳማ ፣ ወላይታ ፤ ወዘተ ፡፡ የኦሮሚያን መንገድ ይዘው በዘር ፣ በዘውግ ና በወንዜ ልጅነት የተማረን ወጣት በመቅጠር ፣ በዜጎች መካከል ልዩነትን እያጎሉ ከመጡ ዛሬ እየገነባን ያለነውን ህብረት ፣ አንድነት እና የአገር ፍቅር ሥሜት ከንቱ ያደርጉብናል ፡፡ …

በመጨረሻም ፣ አሻጋሪው መንግስት ፣ ሽግግሩን ጨርሶ ሥልጣኑን በሠላም እንዲረከብ ፈጣሪ ያብቃው ፡፡ ፈጣሪ ከምድራችን ላይ ሴጣናትን አጥፍቶ ዘመኑን ጠሠላምና የብልፅግና ያድርግልን ! አሜን ! ” በማለት የ2014 /ም መልክቴን እቋጫለሁ ፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share