ለቸኮለ! ዐርብ ነሐሴ 28/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

ethiopian inflation

1፤ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ከመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ ላልተወሰነ ጊዜ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ እንደተነሳ የገንዘብ ሚንስትር ደዔታ እዮብ ተካልኝ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ከውጭ የሚገባ ስንዴ፣ በሀገር ውስጥ ግብይት የሚደረግበት ወይም ከውጭ የሚገባ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ፣ ፓስታ፣ መኮሮኒና ስኳር ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ነጻ የተደረጉ ሲሆን፣ የዶሮ እንቁላል ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ተደርጓል፡፡ ለ6 ወራት ተፈቅዶ የነበረው ያለ ውጭ ምንዛሬ ሸቀጦችን የማስገባት አሠራር ለቀጣዮቹ 6 ወራት ተራዝሟል፡፡ መንግሥት ወደፊት ተጨማሪ የገንዘብና የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚያደርግ እዮብ ተናግረዋል፡፡

2፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት ለዋጋ ንረት አስተዋጽዖ እንዳደረገ የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ፍቃዱ ደግፌ ለብሉምበርግ ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ መፈናቀል ባስከተለባቸው አካባቢዎች ምርት እንደቆመና ተፈናቃዮችን ለመርዳት ከገበያ የሚገዛው የምግብ ዕርዳታ ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ለመከሰቱ ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረገው የምርት አቅርቦት ዕጥረት መሆኑን የጠቀሱት ፍቃዱ፣ የገንዘብ አቅርቦትና ሥርጭትም የራሱን ሚና እንደተጫወተ ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉት የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች ዋጋ ንረቱን ያወርዱታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሃላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡

3፤ መንግሥት ቀደም ብሎ የወሰዳቸው ርምጃዎች የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ከባድ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር እንዳስቻሉ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል፡፡ ሕዝቡ ከፍተኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ ወጭውን እየተጋራ መሆኑን የጠቀሰው ጽሕፈት ቤቱ፣ በነሐሴ ወር ብቻ መንግሥት ለአስቸኳይ ዕርዳታ 9 ቢሊዮን ብር ወጭ ማድረጉን ገልጧል፡፡

4፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች የዋግ ኽምራ ዞን ዋና ከተማ ሰቆጣን ከሕወሃት ተዋጊዎች እንዳስለቀቁ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በፌስቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡ የሕወሃት ተዋጊዎች ሰቆጣ ከተማን ለቀናት ተቆጣጥረው እንደቆዩ አገኘሁ ገልጸዋል።

5፤ ትናንት ወደ ሐርጌሳ ያቀኑት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ ሬድዋን ሁሴን ዛሬ ከሱማሌላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር እንደተወያዩ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል። ሬድዋን ከፕሬዝዳንቱ ቢሂ ጋር በድንበር ጸጥታና ኢምግሬሽን ጉዳዮች ዙሪያ እንደተነጋገሩ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል።

6፤ ለግጭት ተጎጅዎች በታሰበ ሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ የሚፈጸምን ጣልቃ ገብነትና ስርቆት አጥብቆ እንደሚያወግዝ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡ ኢምባሲው በሰሜን አማራ ክልል 3 የዕርዳታ መጋዘን ዝርፊያዎች ስለመፈጸማቸው መረጃ ደርሶኛል ያለ ሲሆን፣ ዝርፊያው መቼ፣ የትና በማን እንደተፈጸመ ግን አላብራራም፡፡ ዋናው ችግር የዕርዳታ ተደራሽነት አለመኖር እንደሆነ በመጠቆም፣ መንግሥት ለዕርዳታ ፈላጊዎች ዕርዳታ እንዲደርስ እንዲያደርግ ኢምባሲው ጠይቋል፡፡

7፤ የትግራይ ክልል ተረጅዎች ለከፍተኛ የእርዳታ እጥረት ሊዳረጉ ይችላሉ ሲሉ በኢትዮጵያ የተመድ ዕርዳታ ተጠባባቂ አስተባባሪ ግራንት ለይቲ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል፡፡ በክልሉ የዕርዳታ ምግብ ክምችት ከ10 ቀናት በፊት መሟጠጡን የጠቀሱት ሃላፊው፣ የጥሬ ገንዘብና ነዳጅ እጥረትም እንደተባባሰ ጠቁመዋል፡፡ በግጭቱና በቢሮክራሲያዊ ማናቆ ሳቢያ ካለፉት 10 ቀናት ወዲህ የዕርዳታ ካሚዮኖች ወደ ክልል እንዳልገቡ ሃላፊው አክለው ተናግረዋል። የአፍሪካ ኅብረት ሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነርም ዕርዳታ በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ መንግሥት ተጨማሪ ርምጃዎችን እንዲወስድ ዛሬ ለውጭ ዜና ወኪሎች በሰጡት ቃል ጠይቀዋል፡፡

8፤ አንጋፋው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ዓለማየሁ ለሕልፈት የተዳረገው በድንገተኛ ሕመም እንደሆነ ታውቋል፡፡ ድምጻዊው ከ1960ዎቹ ጀምሮ በተጫወታቸው ሙዚቃዎቹ በርካታ አድናቂዎችን ያተረፈ ታዋቂ ድምጻዊ ነው፡፡

9፤ በሱማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ከቀጣዩ ጥር በኋላ ቆይታውን ለማራዘም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው አፍሪካ ኅብረት መናገሩን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡ ተልዕኮው ለተጨማሪ 6 ዓመታት እንዲራዘምና ተመድ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ኅብረቱ ጥሪ ማድረጉን የኅብረቱ ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር ዛሬ ለጋዜጠኞች የተናገሩ ሲሆን፣ የሞቃዲሹ ባለሥልጣናት ግን ተመድ በተልዕኮው እጁን እንዲያስገባ አይፈልጉም ብለዋል [ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.