“አሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽመው የሰብዓዊ ድጋፍ የማደናቀፍ ድርጊት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊወገዝ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

“አሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽመው የሰብዓዊ ድጋፍ የማደናቀፍ ድርጊት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊወገዝ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው ሕወሓት የሚፈጽመው የሰብዓዊ ድጋፍ በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ጥረት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ጽሕፈት ቤቱ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ የሚገኝበትን ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት አርሶ አደሩ እንዲያርስና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀላጠፍ በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማድረጉን ተከትሎ የአሸባሪው ሕወሓት ትርፍራፊዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደቱን ችግር ውስጥ እንደከተቱት አመልክቷል።

የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው ከተላለፈበትና የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ከመቀሌና ሌሎች የክልሉ ከተሞች እንዲወጡ ከተደረገበት ከሰኔ 21 /2013 ዓ.ም በፊት በነበረው ሁኔታ የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ኮሚቴ በሦስት ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሷል።

ከዚህ በተጨማሪም ለሥርጭት የተዘጋጀ 400 ሺህ ኩንታል ስንዴ እና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ተከማችቶ እንደነበርም አመላክቷል።

በተጨማሪም 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ሕዝቡ እንዲጠቀምበት በሚል በክልሉ ዲፖዎች ውስጥ ተከማችቶ እንደነበርም ጠቅሷል።

አጋሮችና ዓለም ዓቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በክልሉ ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ በመንግሥት መፈጠሩን የገለጸው መግለጫው፤ መንግሥት አሁንም ቢሆን ለሕዝቡ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የብሔራዊ ደኅንነትን ለአደጋ በማያጋልጥ መንገድ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስታውቋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ በረራ ፈቃድ መሰጠቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ በአዲስ አበባ በኩል የማለፍ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው የማይጣስና የሚከበረውን የሀገር ደኅንነትን ለመጠበቅ በማሰብ እንደሆነ አመላክቷል።

ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሁለት በረራ ማድረጉንም ገልጿል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአፋር ክልል ወጣቶች ለውትድርና በግዴታ እየታፈሱ ነው

በተሽከርካሪ የሰብዓዊ ድጋፍ በአፋር ክልል በኩል እንዲጓጓዝ እየተደረገ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ መዘግየትን ለማስቀረትና የተቀላጠፈ የፍተሻ ሥራ እንዲከናወን ለማድረግም ጥረቶች እንዳሉ ጠቅሷል።

ከቀናት በፊት የሰብዓዊ ድጋፍ ከሰመራ አባላ መስመር ሲያጓጉዙ የነበሩ መኪናዎች ላይ በአሸባሪው ሕወሓት አማካኝነት የተፈጸመውን ጥቃት በድጋሚ ያወገዘው መግለጫው፤ በቡድኑ አማካኝነት እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍን በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው ገልጿል።

አሸባሪው ሕወሓት ሕጻናት ወታደሮችና የታጠቁ ሲቪሎችን በመጠቀም በሀገር መከላከያ ላይ ትንኮሳ እየፈጸመ መንግሥትን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ያልተገባ ንትርክ ውስጥ ለመጨመር እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአጋሮች ጋር ያለመታከት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጾ፤ ምግብና መድኃኒት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሠራ አረጋግጧል።

ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎች ጋርም በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share