“ጁንታው ቡድን በክልላችንና በሀገራችን ላይ እየፈፀመ ያለውን የወረራና የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ በቂ ምላሽና የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል”

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት

4444

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ባስተላለፉት መልዕክት የተጀመረው ትግል ለህልውናችን የምናደርገው ትግል በመሆኑ መላው ኢትዮጵያዊያን፣ የክልላችንና በውጭ የሚኖሩ ወገኖቻችን ሁሉ እየተሳተፉበት ነው ብለዋል። በግንባር በአውደ ዉጊያው እየተሳተፉ ያሉት ጀግኖች የልዩ ኃይል ፖሊሶቻችንና ሚሊሻዎቻችን አሸባሪውን የትህነግ ቡድን እየተፋለሙ ድል እየተቀናጁ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በግንባር እየተፋለመ ያለውን ኃይል ለመቀላቀል አዳዲስ የልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ምልስ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የመደበኛ የፓሊስ አባላትም በፈቃዳቸው ትግሉን እየተቀላቀሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። አብዛኛው ወጣትም በትግሉ ለመሳተፍ በሁሉም የክልሉ አከባቢዎች ወታደራዊ ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

“ህልውናችን ላይ የተቃጣብንን አደጋ ለመፋለም የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ መላው ሕዝባችን እያሳዬ ያለው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው። በክልላችን በመንግሥትና በግል ተቋማት በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማራችሁ ሠራተኞችም ለትግሉ የወር ደሞዛችሁን ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በትግሉ ለመሳተፍ ከፍተኛ ጥያቄ እያቀረባችሁ እንደሆነ ተረድተናል። በዚህም መንግሥትና በግል ተቋማት የተሰማራችሁ ሠራተኞች የኑሮ ውድነቱ ሳይበግራችሁ ከህልውና በላይ አይሆንም ብላችሁ የወር ደሞዛችሁን ለትግሉ ድጋፍ በማድረጋችሁ መንግሥት ለእናንተ ያለውን ክብርና ምስጋና ይገልፅላችኋል” ብለዋል።

በአውደ ዉጊያው ለመሳተፍ ያቀረባችሁት ጥያቄም ጠቀባይነት ያለውና ፍላጎታችሁም ከፍተኛ በመሆኑ በየአላችሁበት ተመዝግባችሁ ስልጠና ወስዳችሁ እንድትሳተፉ ሁኔታዎችን የምናመቻችና የምንቀበላችሁ መሆኑን እንገጽላችኋለን ነው ያሉት።

የነጋዴው ማኅበረሰብ፣ የከተማና የገጠር ነዋሪዎቻችንም በዉጊያው ” እምቢ ለሀገሬ” ብላችሁ በግንባር ከመሳተፍ ባሻገር ገንዘብ በማዋጣት ለታጋዩ የኋላ ደጀን ሁናችሁ ስንቅ እያዘጋጃችሁ ቦታው ድረስ በመሄድ ስንቅ በማድረስ የምታደርጉት ታጋዩን የማበረታታት ሥራ በጣም ከፍ ያለ ነው እና የክልሉ መንግሥት እውቅና ይሰጣል ብለዋል።

“ምስጋናችንም ከያላችሁበት ይድረሻችሁ እንላለን። ከክልሉ ውጭና በውጭ የምትኖሩ የክልላችን ነዋሪዎችም ሀሳብና ገንዘብ በማዋጣት ትግሉን በመቀላቀላችሁ ከፍ ያለ ምስጋና ይድረሳችሁ። ለእውነት የቆማችሁ ለህልውናችን ትግሉን የተቀላቀላችሁ ሀቀኛ የማኅበረሰብ አንቂዎቻችንና ሚዲያዎቻችን ትክክለኛ መረጃ ለሕዝባችንና ለአለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማድረስት አሸባሪውን በመታገል ሂደቱ የበኩላችሁን እየተወጣችሁ እንደሆነ እንገነዘባለን። ስለሆነም ለምታደርጉት ሁሉ እውቅና የሰጠናችሁ ሲሆን በክልሉ ሕዝብ ስም ምስጋናችን ይድረሳችሁ” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በአጠቃላይ በህልውና ዘመቻው በተለያዬ መንገድ እየተሳተፋችሁ ያላችሁ መላ ኢትዮጵያዊያን፣ የክልላችን ነዋሪዎች ወራሪውንና አሸባሪውን ትህነግ ለመፋለም እያደረጋችሁት ያላችሁት ትግል ፍሬ እያፈራ ድል እያጎናፀፈን ሲሆን በቀጣይም ትህነግን ካላጠፋን ሰላም የለምና የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪያችን ይድረሳችሁ በማለትም መልዕክት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስተላልፈዋል።

አሚኮ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.