አክሎግ ቢራራ (ዶር)
ጽሁፎቸን ለምትከታተሉ ለማስታወስ ከዚህ በፊት “አንድነት፤ አንድነት ስንል ከአርባ ዓመታት በላይ አሳልፈናል” በሚል ርእስ፤ ሰፊ ትንተናና ምክሮችን አቅርቤ ነበር። ያ ስላልተሰራበት፤ የኢትዮጵያ ህልውና ደግሞ እንቅልፍ የሚነሳ ስለሆነና እድል ሲገኝ ቶሎ ብሎ ማስተጋባት ስለሚያስፈልግ ይህንን ሃተታ ለመጻፍ ተገድጃለሁ።
እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ ኢትዮጵያ ሁሉም በየዘውጉና በየጎጡ “ነጻ አውጭ ግንባር” የተፈለፈለባት አገር ሆናለች። ሂሳብ ማወራረድ አልቻልንም እንጂ ለኢትዮጵያ ሃገራችን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዓላዊነት፤ ክብርና ልማት የታገሉና መስዋት የከፈሉ ልጆቿ ብዙ ናቸው። በዚያው ልክ ደግሞ በተከታታይ የፈረንጆች ተቀጣሪ፤ ከሃዲ፤ ለሆዳቸው ብቻ ቆመው አገራቸውን ለድርድር እንደ ሸቀጥ የተዋዋሉባት ብዙ ናቸው። ዛሬም ቢሆን በአገር ውስጥም በውጭም ሆነው፤ ልክ እንደ እሥስት እየተለዋወጡ ኢትዮጵያን ያጋለጧት አሉ። ለፈረንጆቹ የሚሉት ሌላ፤ ለኢትዮጵያዊያን የሚሉት ሌላ!
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነትና ስር ነቀል አፍራሽ ትርክት የሚካሄደው በማንና በማን መካከል ነው? የሚለውን ጥያቄ ከእኔ ጥናትና ምርምር አንጻር በማያሻማ ደረጃ ልመልስ። መሰረቱ (The root cause) የዘውግ ወይንም የእምነት ልዩነት አይደለም። የሞት የሽረት ትግሉ በአንድ በኩል ኢትዮጵያን እንደ ሃገረ ግዛት (አገር/ Ethiopia as a state) እንድትቀጥል በቆረጡና በሚታገሉ አገር ወዳዶችና በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትበታተን/እንዳትቀጥል በሚፈልጉ የውስጥ የዘውግ ጽንፈኞች፤ የብሄር ነጻ አውጭ ግንባሮችና የውጭ ደጋፊዎቻቸው መካከል ነው።
በማንኛውም መስፈርት ሲገመገም፤ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር ድህነትና ኋላ ቀርነት ነው። ይህንን ግዙፍ ተግዳሮት ለመቅረፍና ኢትዮጵያ ተገቢውን ቦታዋን እንድትይዝ ለማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ ከማንኛውም መስፈርት በበለጠ ደረጃ እንደ ሃገር መቀጠል አለባት። ሰላም፤ እርጋታ፤ ብሄራዊና ህዝባዊ አንድነት፤ መላውን ሕዝብ በቅንነት፤ በቅልጥፍና፤ በፍትህ፤ ያለ ምንም ጉቦና ሙስና የሚያገለግላት መንግሥት ያስፈልጋታል።
የነጻ አውጭ ግንባሮች፤ ጅሃዲስቶች፤ ጠባብ ብሄርተኞች ጽንፈኞች፤ የብሄር አክራሪዎች፤ በተተኪነት ብቻ የሚያምኑ ኃይሎች፤ የፈረንጆች አምልኮ የበከላቸው ግለሰቦችና ስብስቦች፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባዮች፤ ወዘተ ሊዋጥላቸው ያልቻለው አስኳል ጉዳይ ኢትዮጵያ ብትወድም ወይንም ብትበታተን ማንም የዘውግ ወይንም የእምነት አባል በሰላም ለመኖር የሚቻልባት አገር እንደማትሆን አለማወቃቸው ነው። አለማወቅን ማወቅ ትልቅ መሰናክል ስለሆነ ሰከን ብሎ ለማሰብ ቢቻል የተሻለ ይሆናል።
“ነጻ አውጭ ግንባሮች” ራሳችሁን ከየትኛው ጠላት ነጻ ለማውጣት ነው የምትዋጉት? እናንተ የጀመራችሁት ጦርነት ራሳችሁንና ንጹሁን ሕዝባችሁን ጭምር አይጎዳም ወይ? ትኩረታችሁ ድህነትን ከመቅረፉ ላይ ቢሆን የሚያስከትለውን እውነታዊ ውጤት አስባችሁበታል? የሚሉ ራስን ከመፈተሽ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥያቄዎችን አቀርባለሁ።
ፈረንጆች እና አረቦች ወዳጆቻችሁ የሚለግሱትን ምክር እየሰማችሁ ከሆነ በዩጎስላቭያ፤ በሊብያ፤ በኢራክ፤ በሶርያ፤ በየመን፤ በሶማልያ፤ በአፍጋኒስታን የደረሰውን እልቂትና ሰብአዊ ግፍ ለምን አላጤናችሁም? የሚሉ ጥያቄዎችንም አቀርብላቸዋለሁ።
ወደ ዋናው ትንተናየ ስገባ ኢትዮጵያን እነደ አንዲት ቤት ብናያት ቤቷ እንዳትፈርስ በቤቱ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ–እናት፤ አባት፤ አያት፤ ልጅ ወዘተ ቤቷ እንዳትፈርስ ቀን ከሌት ይንከባከቧታል። ጣራው ቢፈርስ በዝናብና በብርድ እንደሚሰቃዩ ያውቃሉ። ኢትዮጵያን ቤታችን ናት ካልን፤ ችግሩ ከዚህ ላይም ብሄራዊ መግባባባት ገና ስር አልሰደደም/አልሰረጸም።
ኢትዮጵያ የወጣት ትውልድ አገር ናት። እድሜው ከሰላሳ ዓመት በታች የሆነው 70 በመቶ ነው። ይህ ግዙፍ ትውልድ ወታደር ለመመልመል እድል ይሰጣል፤ ልማት ስፋት እንዲኖረው ለማድረግ እድል ይሰጣል። የስራ እድል ከሌለው ደግሞ ለነጻ አውጭ ግንባሮች፤ ለጀሃዲስቶችና ለሌሎች መሳቢያ ይሆናል። ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት በቆራጥነት እንዲሰበሰብ፤እንዲደራጅና እንዲሰራ ለማድረግ ብሄራዊ ወይንም አገራዊ ትኩረት ይጠይቃል። ሕዝብ ለሕዝብ ውይይት ያስፈልጋል፤ ለምሳሌ በየኮሌጁና በየ ዩንቨርስቲው።
የወጣቱ ትውልድ፤ የባለሥልጣናት፤ የምሁራን፤ የልሂቃን፤ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች፤ የመንፈሳዊ አባቶችና እናቶች ወዘተ የመጀመሪያው ትኩረታችን ኢትዮጵያ እንዳትፈራርስ መረባረብ ነው። ለመረባረብ ደግሞ የጠላትነትን ሰው ሰራሽ ትርክት፤ ቂም በቀልን፤ ጥላቻን ማስወገድ ግዴታችን ነው። ኢትዮጵያ እንዳትፈራርስ ማሰብ ያለብን ላለመፈራረስ ብሄራዊ ተቋማትና በአገር ወዳድነታቸው እንከን የሌላቸው መሪዎች በየ እርከኑ ያስፈልጓታል። ፈረንጆች ኢትዮጵያዊ ተቋማትንና አገር ወዳድ መሪዎችን እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ በድርጊት አሳይተዋል። ነግረውናል፤ ሴራዎችን አካሂደውብናል፤ አሁንም እያካሄዱብን ነው። ዛሬ አንዳንድ ታዛቢዎች፤ ቲንክ ታንኮችና ባለሞያዎች በኢትዮጵያ “መፈንቅለ መንግሥት” የማይቀር ነው ይሉናል። ይህ ሂደት የሚነግረኝ አንድ ነገር አለ። በደርግ መንግሥት ወቅት በተከታታይ ሃያ ሰባት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች መካሄዳቸውን ነው። ሙከራዎቹን ያደረጉት ፈረንጆች አይደሉም፤ የአገር ውስጥ የስልጣን ጥመኞች፤ ራስ ወዳዶችና “ቅጥረኞች” ጭምር ናቸው፤ የውጭ ድጋፍ ግን ነበራቸው። ይህ ሁኔታ አሁንም ይታያል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጀርባ ለኔ የሚያሳስበኝ ግን የቤቷ ወይንም የኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ለመታደግ፤
- ጠንካራና የማይበገር ብሄራዊ መከላከያያስፈልጋታል፤ ይህ ተቋም ተገዢነቱ ለሕዝብ፤ ታዛዥነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ መሆን አለበት፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ፤ ከአንድ ግለሰብ በላይ፤
- ይህንን ተቋም የሚደግፍ ብሄራዊ የደህነት፤ የመረጃና የመገናኛ መረብና ሰንሰለት ያስፈልጋታል፤
- ከፓርቲ በላይ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነትእሴቶች የቆሙ፤ ችሎታ ያላቸው፤ አገር ወዳድ የሆኑ፤ የሌላውን ሃሳብና ምክር ለማዳመጥና ለማስተናገድ የሚችሉ፤ በሕዝቡ በኩል ተቀባይነት ያላቸው፤ በጉቦና በሙስና የማይጠረጡሩ፤ ለቆሙበት አላማ ቆራጥነት የሚያሳዩና መስዋእት ለመሆን የተዘጋጁ፤ እየተናበቡ ለመስራት የሚችሉ መሪዎች በእየ እርከኑ ያስፈልጋታል።
በሃሰት ትርክት የተቀናጀ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ አለ።
“ገሃነም ገብተንም ቢሆን ኢትዮጵያን ከማፈራረስ ወደ ኋላ አንልም” ብሎ የሚፎክረው ህወሓት፤ በቅርቡ የተዋቀረው የትግራይ መከላከያ ኃይል የሚባለው እንዴት ሊያንሰራራ ቻለ? የሚለው ጥያቄ ብዙ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል። ይህ “ሞተ፤ አለቀለት፤ እንድ ዱቂት በነነ” የተባለው ኃይል ማንሰራራቱ ግን ሊካድ አይችልም። ወደ ሱዳን ኮሪዶር (መናኸሪያ) ለመፍጠር ሞክሮ አልቻለም። ሌላ አማራጭ ወደ አፋር ክልል ለምን ፈለገና የጦር አውድማውን ወደዚህ አካባቢ አደረገ? የሚለውን ባጭሩ ላስቀምጠው።
የኢትዮጵያ የባህር በር ስለተዘጋ 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ የሚካሄደው በጅቡቲ ወደብ ነው። የማጓጓዣው ሃዲድ የተዘረጋው በዚህ አካባቢ ነው። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በሆነ ደረጃ ማውደም አለብን። ሕዝቡ በመንግሥቱ ላይ የሚነሳው ጉረሮው ሲታነቅ ነው ወዘተ ብሎ የሚንቀሳቀሰው ኃይል፤ እንደ ግብጽ ካሉ የውጭ ጠላቶች ጋር እየተናበበ የኢኮኖሚና የንግድ ሁከትና ውድመት (Economic and trade chaos and crisis) እያካሄደ ነው። ይህንን ሁከት “የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ” አለ ከሚለው ጋር ብናያይዘው ኢኮኖሚውና የኑሮው ውድነት ህዝቡን ሲያማርረው የአዲስ አበባውን መንግሥት ለመገልበጥ አመች ሁኔታ ይገኛል የሚል እሳቤ እንዳለ እገምታለሁ። አለያ፤ ለምንድን ነው የምእራብ አገሮች ኤምባሲዎች በተጠንቀቅ ላይ ያሉት? ብለን የመጠየቅና ዝግጅት የማድረግ ሃላፊነት አለብን። ይሆናል ብሎ መዘጋጀትና ጠላትን ከስሩ መከላከል ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ነው።
በእኔ ጥናትና ምርምር ህወሓት ከእነ አስተሳሰቡ፤ ከእነ መዋቅሩ፤ ከነ ስርአቱ፤ ከእነ ግዙፍ ንብረቱ ካልጠፋ በስተቀር በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው ሴራ ይቀጥላል። ህወሓት ህክምና የሌለው ካንሠር (malignant and incurable) ብቻ አይደለም፤ወንፊት ነው። ከሃዲ ነው። የውጭ ኃይሎች አገልጋይ ነው። ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ነው።
ህወሓት/ትህነግ በፈጠረውና በጀመረው ዘውጋዊ፤ ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ጦርነት ዓላማ ያደረገውና ሂሳብ እወራረድበታለሁ ብሎ የተነሳው የአማራውን፤ በተለይ የጎንደር/ቤጌምድርን ሕዝብ ነው። ልሂቃን የሚለው ሽፋን እንጅ ኢላማው ግልጽ ነው። ማኒፌስቶውን ዘመናዊ ለማድረግ ነው የሞክረው። “ዶሮን ሲያታልሉ” እንዲሉ ይህ የከፋፍለህ ግዛውና ምታው ዘዴ ነው። ማሰብ ያለብን ግን፤ ዋናው ኢላማ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንዳትቀጥል ለማድረግ መሆኑን ነው።
ማንኛውም የእርስ በእርስ ጦርነት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያየለ ነው። ሆኖም፤ ጦርነት ሲካሄድ እድሎችም ይፈጠራሉ። የኔ አጭር ትንተናና ምክር እድሉን በሚመለከት ነው። ምን እድል?
የአማራው ክልል አመራር በአስቸኳይ ድረሱልኝ የሚል ጥሪ ለሁሉም የክልል ወገኖቹ አቀረበ። ውጭ ሆነን ለምንከታተለው ማን አወንታዊ መልስ ይሰጥ ይሆን? ኢላማው አማራ ስለሆነና ህወሓት ትርኩትን ዓለም አቀፍ በሆነ ደረጃ ስር እንዲሰድ ስላደረገው የክልል አመራሮች የዚህ ስለባ ሆነው ይሆን? የሚለው ጥያቄ ሲብላላ ነበር።
በመሬት ላይ የሆነው ግን እመርታዊ ለውጥ ያሳያል። የሲዳማ፤ የደቡብ፤ የኦሮሞ፤ የሶማሌ፤ የቢኒ ሻንጉ ጉሙዝ ወዘተ ልዩ ኃይሎች የአማራውን ኃይል ተቀላቀሉ። በከሃዲው ህወሓት ላይ የሚደረገው እርብርብሮሽ ኢትዮጵያዊ ሆነ። በባህር ዳር በሌሎች አካቢዎች አባላቱ የተናገሩት ኢትዮጵያዊያንን ከማስደሰቱና ከማበራታቱ በተጨማሪ የምእራብ አገሮችን፤ ግብጽን፤ ሱዳንን አስደንግጧል። መልእክቱ ኢትዮጵያን አትንኳት የሚል ነው።
በዚህ ወር ይህ ብቻ አይደለም “እልል በሉ” የሚል መፈክር እንድንከተል የምንገደደው። የህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ሙሌት ወደ ጦርነት ያመራል የሚሉ ታዛቢዎችንም አንርሳ። ግብጽና ሱዳን ወደ ተባባሩት ደህንነት ተቋም (United Nations Security Council) በተደጋጋሚ ሄደው ተቋሙ ይህ የአፍሪካ ጉዳይ መፈታት ያለበት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካይነት ነው የሚለው መርህ ስኬታማ ሆኗል። ይህ ስኬት ደግሞ የኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጥበባዊ ስልት ውጤት ነው። ይህ ከፍተኛ ድል ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፍ አድርጎታል።
ሁለተኛው የሚያኮራ የፖለቲካ ሂደት ውጤት ህወሓትና ኦነግ ሽኔ እንደሚሉት ሳይሆን፤ ትህነግና አጋሮቹ የጀመሩት አዲስ ጦርነት ኢላማ ያደረገው አማራውን ብቻ አይደለም፤ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብና ኢትዮጵያን ነው የሚለው ነው። ጦርነቱ የኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ሆነ። ይህንን ነው እድል ተፈጥሯልና እድሉን አናባክነው ያልኩበት ምክንያት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ከተነሳና የአድዋን መንፈስ ከተከተለ ኢትዮጵያ አትፈራርስም። የሚከፈለው ዋጋ ግን ቀላል አይሆንም። ከዚህ ላይ እኔን የሚያስጨንቀይ መሰረታዊ ጉዳይ እኛ ኢትዮጵያዊያን ሆዳችን ቆስሏል፤ ልባችን ሸፍቷል እያልን ስንገዳደልና የሰራነውን ስናወድም ልንኖር እንችልም። ኢትዮጵያ በሁከትና በጦርነት ስትደማ ቆይታለች፤ አሁንም እየደማች ነው። ለጋስ መንግሥታትና አበዳሪ ድርጅቶች ተጨማሪ የመዋእለንዋይ እቀባ ቢያደርጉ ምን ሁኔታ ሊከሰት ይችል ይሆን ብለን መጠየቅ አለብን።
ለማጠቃለል፤
- እኛ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ የተቀነባበረ አደጋ ለማዳን ቆርጠን መነሳት አለብን፤ በአንድ ድምጽ መናገር አለብን፤ በቁሳቁስ ሆነ በሌላ የመረባረብ ግዴታ አለብን።
- የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያመቻች፤ ከባድ መሳሪያዎች ከትግራይ መከላከያ አካላት ነጻ ሳያደርግ፤ ስልታዊ እቅድ ሳያወጣ፤ የአንድ ወገን የጦር አቁም (unilateral ceasefire) የፖለቲካ ውሳኔ ቀድሞ ማድረጉ አሁን ለተከሰተው የሚዘገንንና አላስፈላጊ እልቂትና ውርደት ግብዓት አድርጓል። ሃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል። ህወሓት እንዴት ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊያንሰራራ ቻለ? እንዴት ታንክና ሌላ ከባድ መሳሪያ አገኘ? እንዴት የጦርነቱን አውድማ ከላይ እንደ ጠቀስኩት ወደ አማራውና ወደ አፋሩ ክልል ለማስፋፋት ቻለ? ህወሓት ወደ ጂቡቲየሚወስደውን የሃዲድና ሌላ የመገናኛ መዋቅር ከተቆጣጠረው የኢትዮጵያን መንግሥት ለመገልበጥ ያለው እድል ከፍ እንደሚል እገምታለሁ። የጦር አቁም አዋጅ ሁለቱም አካላት የሚስማሙበት ሁኔታ ካልተገመገመ እንዴት ይህንን አይነት አደገኛ የፖለቲካ እርምጃ ለመውሰድ ተቻለ? ማን አደረገው? ማን አስገድዶት? ለምን አላማ?
- አከራካሪውና አወዛጋቢው የጦርነት መሰረቱ ከክህደትና ከእልቂት ወደ መሬት ይግባኛልነት ተሸጋግሯል። የትግራይ መከላከያ ኃይል በጋራ የሚፈልጉትን ግልጽ አድርገዋል። የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት፤ በተለይ አንቶኒ ብሊክን የተከተለው መርህ ከህወሓት ጋር ተመሳሳይ ነው። አማራው ከራሱ መሬት “ከምእራብ ትግራይ” ይውጣ የሚል። የትግራይ ወሰን ተከዜ መሆኑን አያውቁም ለማለት አልችልም፤ ያውቃሉ። ግን፤ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትም ቢሆን ግልጽ አቋም አልወሰደም። ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ ከአማራው ክልልናሕዝብ የተነጠቁት በኃይል ነው። ነዋሪው ሕዝብ ተጠይቆና መርጦ አይደለም። በሌላ አነጋገር ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ለተነጠቁት መሬቶች ወደ ትግራይ መጠቃለል እውቅና የሰጠው በበላይ በሚመራው በህወሓት የፖለቲካ ትእዛዝ ነው። የፖለቲካ ውሳኔ የሚፈታው በፖለቲካ እንጅ ሕዝብ ድምጽ ይስጥበት በሚል መንገድ አይደለም። የሕዝቡን ስርጭት በዘዴና በኃይል ቀይሮታል። የፌደራሉ መንግሥት ሃላፊነት ዛሬ ያለውን የነዋሪውን ሕዝብ ምኞትና ፍላጎት አወንታዊ ማድረግ ነው። ለውጭ መንግሥታት ደግሞ የአካባቢውን ታሪክ የመግለጽ ሃላፊነት አለበት። ሊሸሸው አይችልም። ጉዳዩ የመሬት ብቻ ሳይሆን የማንነት ጥያቄ ነው።
- የትግራይ ወሰን የተከዜ ወንዝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በዘላቂነት ስመለከተው ግን፤ በወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ራያና ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት በሚኖሩበት ሁሉ መከበር አለበት። ሕገ መንግሥቱ የዜግነት መብትን መሰረት ካደረገ ይኼ ሁኔታ ይቻላል። ለዚህ የሚረዳው ቅድመ ሁኔታ ለጦርነት በለው፤ በለው፤ ከምንል ይልቅ፤ ለሰላም፤ ለወንድማማች/እህትማማችነት፤ ለውይይትና ለድርድር፤ ለፍትህ-ርትእ፤ ለርቅና ለብሄራው መግባባት ትኩረት ብንሰጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚጠቀሙበት እንድል ይፈጠራል። አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ሆኗል። ጦርነት በራሱ መፍትሄ ሊሆን አይችልም።
- ህወሓት ወጣት ወታደሮችን በገፍ እያሰገደደና እየመለመለ ለእልቂት እንደ ዳረጋቸው መረጃዎች ያሳያሉ። እኔ የምጠይቀው የምእራብ አገሮች፤ በተለይ የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ አንቶኒ ብሊንከን፤ ሴማንታ ፓወርስ፤ ጀፍ ፌልትማን ወዘተ ይህ ህገ ወጥ ተግባር የትግራይን መሪዎች በሃላፊነት በፍርድ እንደሚያስጠይቃቸው ለምን አይናገሩም? በኔ ግምት፤ የማይናገሩበት ዋና ምክንያት ህወሓት/ትህነግና ሌሎች አጋሮች የሚሰሩት ወንጀል ሁሉ ችላ የሚባለው ከአሜሪካ እቅድ ጋር አብሮ የሚሄድ ስለሆነ ነው። ዋናው ትኩረታቸው ለተራው የትግራይ ወጣት፤ ህጻናት፤ እናቶችና ወጣት ሴቶች ደህንነት ሳይሆን ጦርነቱ የራሳቸውን አላማ ስኬታማ ያደርገዋል ለሚል ነው። ህወሓት ለሃያ ሰባት አመታት የፈጸመውን ወንጀል ያውቃሉ፤ ግን ህወሓት የአሜሪካኖቾ ታዛዥና አገልጋይ ቡድን ስለነበረ አቤቱታ አያሰሙም ነበር። ይህ ሃቅ እንዳለ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ወንጀል በሜድያ ማጋለጥ አለበት፤ እኛም እንዲሁ። የኢትዮጵያ ወዳጅ ጀፍ ፒርስ ያደረገውን ህወሓትንና የምእራብ ሜድያዎችን የማጋለጥ ስራ እኛም በጋራ ማድረግ አለብን። አንድ ቀን አማራ፤ ሌላ ቀን ኦሮሞ፤ ሌላ ቀን ትግሬ ወዘተ ከሆነ ግን ኢትዮጵያን የሚወክላት ማነው? የሚለው ማነቆ ይቀጥላል።
- በአሁኑ ወቅት የሚታየው ዋና ተግዳሮት የኢትዮጵያ ሕልውና ጉዳይ ስለሆነ የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል እንዲጠናከር ድርሻችን መወጣት አለብን። በዚህ አጋጣሚ በዘላቂነት የኢትዮጵያን መንትግሥት የምመክረው “የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የደቡብ፤ የሲዳማ፤ የሶማሌ፤ የትግራይ ወዘተ” ልዩ ኃይል የሚባሉ ተቋማት እንዲፈርሱና ፍላጎትና ችሎታ ያላቸው ወደ ኢትዮጵያ መከላከያ እንዲቀላቀሉ ነው። በተጨማሪ፤ በየአካባቢው ፖሊስ ሆነው ለማገልገል የሚፈልጉትና የሚችሉት ወደ ፖሊስ ስራ እንዲሰማሩ ነው። መንግሥት ለሌሎቹ የስራ እድል የመፍጠር ግዴታ አለበት።
- በዘላቂነት ስመራመረው ግን ኢትዮጵያን ለከታታይ ጥቃትና ድክመት የዳረጋት ህወሓትና አጋሮቹ የፈጠሩት ስርዓት ስለሆነ፤ ሕገ መንግሥቱና የአስተዳደሩ መዋቅር እንዲቅየሩ ያልተቆጠበ ጥረት የማድረግ ግዴታ አለብን። የአስተዳደር መዋቅሩ ስል ፌደራላዊ አይሁን ማለቴ አይደለም። ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ያስፈልጋታል። መሰረቱ ግን የእያንዳዱ ዜጋ/ግለሰብ መብት መከበር ነው። የመገንጠል መብት ህጋዊ አድርጎ ህወሓትን ትክክል አይደለህም ለማለት አይቻልም። ብሊንከን ኢትዮጵያዊያን የመሰረቱትን ሕገ መንግሥት አክብሩ እያለን ነው።
- ለኔ ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል አለመኖሩ ነው። ይህ ሁኔታ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። እርግጥ ነው፤ ወጣቱ ትውልድ እመርታዊ የባህል፤ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖረው ሁሉም ባለድርሻዎች በማህበረሰባዊ ትምህርት፤ በውይይት፤ በብሄራዊና አገራዊ ተቋም ግንባታ ስራ ግንባታ ላይ ትኩረት እንዲደረግ እኛም የድርሻችንን መወጣት አለብን። ወጣቱ ትውልድ መታገልና ማስወገድ ያለበት አንዱ አስኳል ጉዳይ የጉቦንና የሙስናን ባህል ማጥፋት ነው። ምክንያቱም፤ ጉቦና ሙስና ስር ከሰደደ (ስር እየሰደዱ ነው) ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት አይቻልም። ሰላምና እርጋታ አይቻልም። ወጣቱ ያጥፊዎች ሰለባ ይሆናል።
- ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይ የፖለቲካ ልሂቃንና ምሁራን “የመንግሥት” ትሩግም ምን እንደሆነ ማስተማር አለባቸው። በኢትዮጵያ መንግሥት የሚለው ዋጋው ዝቅ ብሏል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት የሚለይበት ምንድን ነው? የሚለውን እናሳስብበት፤ እንመራመር፤ አማራጭ እናቅርብ። አካባቢን ማስተዳደር እና ኢትዮጵያን እንደ አንዲት ሉዓላዊ አገር በመንግሥት ሚና መምራት የተለያዩ ናቸው።
- ለኢትዮጵያ በዘላቄነት የሚያስፈልጋት ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሄራዊ ውይይት፤ ብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም መሆኑን በተደጋጋሚ አሳስቤአለሁ፤ አሁንም አሰምርበታለሁ።
- በመጨረሻ፤ ከላይ የጠቅስኳቸውን ሃሳቦችና ምክሮች ለማድረግ የምንችልበት እድል አለን። የደቡብ፤ የሲዳማ፤ የሶማሌ. የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ የኦሮሞና ሌሎች ልዩ ኃይሎች የአማራው ጦርነት የኔም ጦርነት ነው፤ ህወሓት አማራውን “እወራረድህላሁ” ሲል መፈክርህ እኛንም ይመለከታል ብለው ኢትዮጵያን ከመፈራረስ አደጋ ለማዳን ተባበረው ሲሰለፉ ይህንን እንደ እድል እቆጠረዋለሁ። እድሉን እንዳናባክነው አደራ እላለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
July 21, 2021