ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (Global Alliance for the Rights of Ethiopians) ቦርድ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሃምሌ 3 እና 4፤ 2013 ዓ.ም. የሁለት ቀናት ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ግንዛቤዎች ያቀርባል።
- ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (Global Alliance for the Rights of Ethiopians) በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ለይ ያንዣበበውን አደጋ በማጤን አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ግምገማዎችን አካሂዷል።
በመጀመሪያ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ግብፅና ሱዳን ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ውይይት አድርጎ ጉዳዩ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካይነት በሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር ፍትሃዊና ሚዛናዊ መፍትሄ እንዲያገኝ መስማማቱ አግባብ ያለው መሆኑን አምነንበታል። በዚህ ጉዳይ ድርጅታችን የኢትዮጵያ መንግስት፤ በተለይ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ባለሞያዎችና አገር ወዳድ
ግለሰቦች ያደረጉትን አስተዋጽዖ ያደንቃል። በዚህ ብሄራዊ ተግባር ላይ ያለው መተባበር እንዲቀጥል ምኞታችንን እየገለጽን ህዝባዊው አስተዋጽዖ የግድቡ ስራ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን።
- ድርጅታችን ኢትዮጵያ በቅርቡ ያካሄደችው ብሄራዊ ምርጫ ብዙ ድክመቶችና ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም በአብዛኛው በሰላም መካሄዱ የሚመሰገን መሆኑን ይቀበላል። ምርጫ መከናወኑ ብቻ የኢትዮጵያን አንገብጋቢ ችግሮች በዘላቂነት ስለማይፈታ ከምርጫው በኋላ ምን ይደረግ? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ከተወያየን በኋላ ኢትዮጵያን ከተከታታይ አደጋ ለመታደግ የሚቻለው፤ የችግሮቹ ዋና ምንጭ የሆነው ሕገ-መንግስቱንና የአስተዳደር መዋቅሩን ለማሻሻል ሲቻል ብቻ ነው ወደሚለው ድምዳሜ መድረሳችንን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመግለጽ እንፈልጋለን። ከምርጫው በኋላ የሚቋቋመው መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተቀዳሚ ተግባሩ እንዲያደርገው በአጽንዖት እናሳስባለን።
- ድርጅታችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ስኬታማ ለማድረግ የሚቻልባቸው እድሎች አሉ፤ የሚለውን አመለካከት ይቀበላል። ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ስኬታማ ለማድረግ ግን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለድርሻዎችና ተወካዮች፤ በተለይ ዜጎቿ፤ የብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም፤ ውይይትና ምክክር ማካሄድ ይኖርባቸዋል። አገራችንን ከጥቃት ለመታደግ ቅድሚያ የሚሰጠው አገራዊ ውይይትና ስምምነት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር እንዲካሄድ ማድረግ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ሂደቱን በሚመለከት ግን አገር ቤትና ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በፅሞናና በብልሃት የባለሞያዎች ጥበብ ታክሎበት እንዲታቀድና ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲዘጋጅ አደራ እያልን ድርጅታችን ለዚህ የተቀደሰ ሂደት ድርሻውን እንደሚወጣ ቃል ይገባል።
- በመጨረሻም ከላይ የቀረቡት ማሳሰቢያዎች ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙና ለባለድርሻ አካላት ትብብር ውወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ በተለይ የማኅበረሰብዓዊ ድርጅቶችና የሕዝብ መገናኛ አውታሮች ቀጣይነት ያለው የሥነ-ዜጋ ቅስቀሳእንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ በቆራጥ ዜጎቿ ትብብር አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ለዘላለም ትኑር።