July 14, 2021
6 mins read

አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በከፈተው ዳግም ወረራ የአማራ ክልል መንግሥት ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገሩን አስታወቀ

4444

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሴራ ተወልዶ በሴራ ያደገው አሸባሪው ትህነግ ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ከተጣለ ቆይቷል፡፡ እኔ ያልዘረፍኳት እና እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች በሚል ትዕቢት በመከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ሕዝብ ላይ በቃጣው ትንኮሳ ላለፉት ስምንት ወራት ጉድጓድ ውስጥ እንዲወሸቅ ተገዶ ቆይቷል፡፡
የፌዴራል መንግሥት ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተከትሎ አሸባሪው ትህነግ ከስህተቱ ተምሮ ሕዝብን ከከፋ ስቃይ መታደግ ሲገባው በአማራ ክልል ግዛቶች ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ መክፈቱን የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሸባሪው ቡድን በራያ አካባቢ አላማጣ፣ ኮረም እና ባላ፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጅ፣ ዛታ እና አበርገሌ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ እና ማይጠብሪ ዳግም ወረራ ከፍቶብናል ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ተገዥ አለመሆኑን አረጋግጧል ያሉት አቶ ግዛቸው በወረራው ካህናትን፣ አዛውንቶችን፣ ሴቶችን እና ሕጻናትን ከፊት በማሰለፍ ነውረኝነቱን አሳይቷል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት የአሸባሪውን ወረራ ስልታዊ በሆነ መንገድ ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው “ከዚህ በላይ ትዕግስት የከፋ ዋጋ ስለሚያስከፍል ከዛሬ ጀምሮ ከመከላከል አልፈን ግልጽ ማጥቃት ጀምረናል” ነው ያሉት፡፡
አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው የክልሉ መንግሥት የአሸባሪውን አቅም በሚገባ እንደሚያውቀው ጠቁመው በአጭር ቀን ወደ መጣበት ይመለሳልም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ እስካለ ድረስ ለአማራ ሕዝብ እና ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የህልውና ዘመቻው የተራዘመ ጊዜን ስለሚጠይቅ አስፈላጊው ዝግጅት ጎን ለጎን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ክልሎች የሕልውና ዘመቻውን ጥሪ በአዎንታ ተቀብለው ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ለዘመናት በዘረፈው ገንዘብ በዓለም አቀፍ ተቋማት እና ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ውስጥ ተላላኪዎቹን ገዝቶ መጠነ ሰፊ ጫና እየፈጠረ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው ሕዝቡ ይህንን ተረድቶ ድጋፍ ማድረግ እና በአንድ መቆም እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች የወር ደመወዛቸውን ድጋፍ አድርገዋል፣ የነጋዴው ማኅበረሰብ በአደረጃጀቱ የሚመጥን ድጋፍ እያደረጉ ነው፣ እናቶች እና ሴቶች ስንቅ በማዘጋጀት ታሪካዊ ኀላፊነቶቻውን እየተወጡ መሆኑም የሚመሰገን መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
“የተከፈተብን መጠነ ሰፊ ወረራ የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ የክልሉ መንግሥት የትኛውንም አይነት አፍራሽ ግብ ያላቸውን አካላት እኩይ ሴራ አይታገስም” ብለዋል፡፡
ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት ይቻል ነበር፤ ነገር ግን በዚህ ሰዓት የሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ለኦፕሬሽኑ ስኬት ሲባል መልስ የማይሰጥባቸው ስለሚሆኑ በትዕግስት መጠበቅ ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡ በየዕለቱ ለሚፈጠሩ ለውጦች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ርእሰ መሥተዳድሩ፣ የሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ቢሮ ወይም የክልሉ መንግሥት ቃል ዐቀባይ መግለጫዎችን ይሰጣሉም ተብሏል፡፡
ወጣቶች ከማኅበራዊ ሚዲያ ብሽሽቅ እና የተዛባ መረጃ ወጥተው አካባቢያቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ የክልሉ መንግሥት ጥሪ ሲያቀርብም አስፈላጊውን ምልመላ እና ስልጠና ወስደው የሕልውና ዘመቻው ይቀላቀላሉ ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
AMC

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop