ከዶ/ር በቀለ ገሠሠ ([email protected])
1ኛ/ መንደርደሪያ፤
የአማራና የትግራይ ክልሎችን በተመለከተ ሃቀኛ ታሪኮች እየተዛቡ ይገኛሉ። ሱዳን ድንበራችንን ስትደፍር ምንም እርምጃ ሲወሰድ አይታይም። ግብፅና ሱዳን የሕዳሴ ግድባችን ግንባታ እንዳይሳካ በዓለም አቀፍ ዙሪያ የማይሸርቡት ሸር የለም። ይባስ ብላ ሱዳን ከነጭራሹም ግድቡ ያለበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኔ ነዉ ማለት ጀምራለች። መገንጠልን የሚደግፍ የአሁኑ መርዘኛ ሕገ መንግሥት ምንም ዋስትና ሊሰጠን አይችልም። በዚህ ላይ ጠንካራ ዉስጣዊ አንድነትና ሰላም አይታይም። እነዚህን አንገብጋቢና አሳሳቢ ችግሮች ለመቅረፍ የሚከተሉትን እርምጃዎች ቶሎ መዉሰድ ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ። የሁሉንም ቅን ዜጋ አስተዋጽኦ የሚጠይቅ ስለሆነ እናስብበት ዘንድ ደጋግሜ አደራ እላለሁ።
2ኛ/ የጠንካራ ዲፕሎማሲ አስፈላጊነት
ደጋግመን እንደምንጠቅሰዉ፤ የምዕራብ ሀገሮች አፍሪቃን በባርነት፤ በቅኝ ገዥነትና በእጅ አዙር አስተዳደር ከፍተኛ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደኖሩ ግልፅ ነዉ። ኢትዮጵያ ግን ነፃነትዋን አስከብራ ከመቆየትዋም በላይ ሌሎች የአፍሪቃ ሀገሮች ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግዋ ምክንያት ለምዕራባዉያን ቅኝ ገዢዎች የጉሮሮ አጥንት ሆናለች። በዚህም ምክንያት ቂም ተይዞባታል። መሪዎቻቸዉና የዜና አዉታሮቻቸዉ ሃቆችን ያዛባሉ፤ ህዝቦቻቸዉን ያታልላሉ። የአካባቢዉም የቀይ ባህር፤ የህንድ ዉቅያኖስና የአረቦች ፖሊቲካ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ መዘዞች አሏቸዉ። ስለዚህ በተለይ የሚከተሉት ሃቆቹ ወደ ህብረተሰቦቹ እንዲደርሱ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅብናል።
ሀ) አንድ ጠንካራ የልዑካን ቡድን ቶሎ እንዲቋቋ እጠይቃሉ።ቡድኑም የድፕሎማሲ፤ የታሪክ፤ የጂኦግራፊ፤ የፖሊቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ ወዘተ ችሎታና ጥሩ ልምድ ያሏቸዉንና ከተለያዩ የህብረተሰባችን ክፍሎች የተዉጣጡ ሃቀኛ ዜጎችነ ቢያጠቃልል ይመረጣል። ይሄም ቡድን በተለያዩ የዓለማቀፍ ክፍሎች እየዞረ ለዉጪ መንግሥታት ያሉትን ሀቆች በመረጃ በማስደገፍ ደጋግሞ መግለፅ ይጠበቅበታል። በየሚሄዱባቸዉም ሀገሮች ያሉትን የዜና አዉታር ዕድሎች በሙሉ በመጠቀም መልዕክቶቹ ወደህዝቦች እንዲደርሱ ማድረግ ይገባል። በዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ዉስጥ የነቃ ዜጋ (ግብር ከፋይ) ለዉጥ ሊያመጣ ስለሚችል ሃቆቹን በሙሉ ለዓለም ህብረተሰቦች ማዳረስ በጣም ጠቃሚ ይሆናል። ለጊዜዉ መልእክቶቹ በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነዉ ብዬ አምናለሁ።
ለ) የአማራና የትግራይ ክልሎች እዉነተኛ ድንበሮች በግልፅ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ለዚህም ብዙ መረጃዎች ያሉ ስለሆነ አንዳችም ችግር ይኖራል ብዬ አላምንም። በምዕራብ በኩል በወልቃይት፤ በጠገዴ፤ በጠለምት፤ ወዘተ፤ አካባቢዎች አላስፈላጊ ግጭቶች ከተነሱ ሰንብተዋል። በምሥራቅም በራያ አካባቢ ተመሳሳይ አላስፈላጊ ገጭቶች ከተቀሰቀሱ ሰንብተዋል። መሬት እየቀሙ ወደሌላ በጉልበት ሲያካልሉ ቆይተዋል።ህዝብ በፊት እንደለመደዉ በሰላምና በፍቅር አብሮ እንዳይኖር ተከለከለ።ይሄ ችግር ላንዴም ሆነ ለመጨረሻ ጊዜ ቶሎ እልባት ማግኘት ይኖርበታል።
ሐ) ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ለቅቃ ቶሎ መዉጣት ይኖርባታል። ግድባችን ያለበትም የኢትዮጵያ ክልል አፍ አዉጥታ የኔ ነዉ ማለትም ጀምራለች። ድርጊቶችዋ የዓለማቀፍ ድንጋጌዎችን በግልፅ የጣሱ ናቸዉ። የዓለማቀፍ ህብረተሰብ ይህን እያየ ዝም ማለት አይኖርበትም። ካለበለዚያ አላስፈላጊ ከባድ ግጭት ቶሎ ሊቀሰቀስ ይችላል። የህዝብ በገፍ መፈናቀልና መሰደድ ደግሞ ለዓለማቀፉም ህብረተሰብ ጭምር ብዙ አላስፈላጊ መዘዞች ይኖራቸዋልና ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ደጋግሞ ማስታወስ ያስፈልጋል።
መ) በታችኞቹን የዓባይ ተፋሰስ ሀጎሮች (በሱዳንና በግብፅ ላይ) ከባድ ጉዳት በማያስከትል መንገድ ኢትዮጵያ ወንዟን በመገደብና ኃይል በማመንጨት ህዝብዋን ከጭለማ የማዉጣት ሙሉ መብት እንዳላት መታወቅ ይኖርበታል። ይሄ በኢትዮጵያ አልተጀመረም። ሁሉም ሀገር የሚያደርገዉ ነዉ። ሱዳን በተለይ ለግብፅ ለማጎብደድ ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያ ግድብ ትጠቀም እንደሆነ እንጂ አንዳችም ጉዳት ሊደርስባት እንደማይችል ግልፅ ነዉ። የዓለማቀፍ ህብረተሰብ ለሰላምና ዕድገት የሚቆረቆር ከሆነ የነግብፅን ከንቱ ማስፈራሪያ እየሰማ ዝም ማለት አይጠበቅበትም። ድርቅ ሲገባ ዉሃ ሊቀነስብን ይችላል ይላሉ። ታዲያ ድርቅ እንዳይገባ መተባበር ይኖርባቸዋላ። ድርቅ የሚገባዉና የሚባባሰዉ የአየር ንብረት ሲናወጥ (Climate Change) ነዉ። ይሄ ደግሞ ዓለምን በሙሉ እያሳሰበ የሚገኝ ከባድ ጥያቄ ስለሆነ መፍትሄዉ በአፈርና በአካባቢ አየር ጥበቃ ላይ ብርቱ ትብብር ማድረግ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ በዉሃ ኃይል መብራት ማመንጨት ከቻለች እኮ የዛፍ ጭፍጨፋ ይቀነሳል። የዛፍና የዕፅዋት ሽፋን ሲበዛ ደግሞ ዉሃ በብዛት ይጠራቀማል። ስለዚህ ብልሆች ብንሆን ይሻላል።
ሠ) ከዉስጥም ብዙ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል። እላይ እንደተጠቀሰዉ ያለዉ ሕገ መንግሥት ህዝብን የሚከፋፍልና የሚያጋጭ እንደሆነ ሁሉም የሚያዉቀዉ ሃቅ ነዉና ቶሎ መለወጥ ይኖርበታል። ነገ ቤኒሻንጉል በቀላሉ የሚገነጠል ወይንም በጠላት ኃይሎች የሚነጠቅ ከሆነ የታላቁ ሕዳሴ ግንባታ ጥረት እምኑ ላይ ነዉ? በሀገሪቷ ዉስጥ አንድነትና ሰላም መስፈን ይኖርባቸዋል። ካለዚያ እንናቃለን፤ ለከፍተኛ ጉዳት እንዳረጋለን። አንድነት ኃይል ነዉና። ስለዚህ ብዙም ሳንዘገይ አስፈላጊ እርምጃዎችን መዉሰድ ይጠበቅብናል። የድሆች አምላክ ይጨመርበት።