ኩሽ፣ ሴም፣ ኑቢያ፣ አበሻ እና ኢትዮጵያ (በግል የቀረበ ዳሰሳ/ ደረጀ ተፈራ)

 

መግቢያ፣

የቋንቋ አፈጣጠር (ባጭሩ)፣

ስለ ቋንቋ አፈጣጠር በተመለከተ የሃይማኖት ሰዎች ፈጣሪ ለሰው ልጅ (ለአዳም) የሰጠው መለኮታዊ ስጦታ ነው ይላሉ። መጀመሪያ አዳምና ቤተሰቡ ይናገሩት የነበረው ቋንቋ አንድ ብቻ እንደነበርና ከጊዜ በኋላ የሰዉ ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱና በፈጣሪውም ላይ በማመጽ የባቢሎንን (የሰናኦርን) ግንብ በሚገነባበት ጊዜ ፈጣሪ የሰውን ቋንቋ በመለያየቱ በርካታ ልሳኖች መፈጠራቸውን መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ የሃይማኖት ሰዎች ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የቋንቋ ምሁራን (Linguist) የሰው ልጅ በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት (evolution) ባሳየው የአዕምሮና የአካል ቅርፅ ለውጥ እንዲሁም ድምፅ ለመፍጠር የሚያገለግሉ የሰውነት ክፍሎች (Organs) ለንግግር አመቺ እየሆኑ መምጣታቸውና ከአእምሮ እድገት ጋር በተያያዘ የሰው የመናገር ችሎታው ቀስ በቀስ እየዳበረ እንደመጣ ይገልፃሉ። ብልሁ ሰው (Homo sapiens) እየተባለ የሚታወቀው የሰው ዘር እንጨት፣ ድንጋይ፣ አጥንት እና የመሳሰሉ በአካባቢው የሚያገኛቸውን ቁሶች በመጠቀም ለአደን እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች እንዲሆኑት ቀላል የእጅ መገልገያ መሳሪያዎችን ቆርጦና አስተካክሎ በመስራት መገልገል መጀመሩ በአዕምሮው የሚገኘውን የቋንቋ ክፍል እንዲነቃቃ እንዳደረገው ይገለጻል። በዚህም ምክንያት የሰው አዕምሮው እየዳበረና እየተነቃቃ በመምጣቱ የንግግር ቋንቋ ለመፍጠር እንደቻለ ምሁራኑ ያስረዳሉ። ባጠቃላይ የቋንቋ ምሁራኑም ሆኑ የሃይማኖት ሰዎች ስለቋንቋ አፈጣጠር በተመለከተ በየራሳቸው መንገድ የገለጹት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ጽሁፍ በዋናነት ለመዳሰስ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ላምራ።

ኩሽ (Kush) ባጭሩ፣

“ኩሽ” ለሚለውን ቃል የሃይማኖት ሰዎች፣ የታሪክ ፀሃፊዎች፣ የቋንቋ ምሁራን እና ፓለቲከኞች በየራሳቸው መንገድ የተለያየ ትርጉምና ፍቺ ይሰጡታል። ኩሽ ተብለው የሚጠሩ ህዝቦች መኖሪያ ስፍራቸው፣ የሚናገሩት የቋንቋ ዓይነትና የመሳሰለው እንደ ፀሃፊው የእውቀት ደረጃና የጥናት ውጤት፣ እንደ ፓለቲካ ዝንባሌው ልዩነት ሊኖረው ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ (Biblical History) ስለ ኩሽ የዘር ሃረግ የሚከተለውን ይላል። ኖህ የሚባል አንድ ፃድቅ ሰው ሴም፣ ካም እና ያፌት የሚባሉ ልጆች ወለደ። ካም በተራው ኩሽ፣ ምስር (ምጽራይም)፣ ፉጥ እና ከነዓን የሚባሉ አራት ልጆችን ይወልዳል። ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖህ ልጆች ለኑሮ በሚያመቻቸው ቦታ ቤተሰባቸውን እየያዙ በተለያየ አቅጣጫ በመሰደድ መኖር ጀመሩ። ኩሽ የሚለውን ቃል ፍቺ ስንመለከት ደግሞ አንዳንድ ሰዎች በእብራይስጥ ቋንቋ ኩሽ ማለት ጥቁር ማለት ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ጥቁር ቆዳ ያላቸውን ህዝቦች ዝቅ ለማድረግ የተጠቀሙበት የስድብ ቃል (derogatory word) ነው፣ ቃሉም “ኩሺ ወይም ኩሺም” (kushi or kushim) ከሚለው ከእብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው ይላሉ። በአሁኑ ጊዜ የነጭ የበላይነትን የሚያቀነቅኑ ዘረኛ አመለካከት ያላቸው አንዳንድ ነጭ እስራኤላውያን የኢትዮጵያ ቤተእስራኤላውያንን ኩሺ (ኩሺም) በማለት የዘር እና የቀለም መድልዎ ያደርጉባቸዋል ሲባል ይሰማል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩሽ የሚለው ቃል ቀጥታ ገጸ ንባቡን (Literally) ከመጽሃፍ ቅዱስ አንጻር ቃል በቃል እንደወረደ ብንመለከት አጀማመሩ ከካም (Ham) ልጅ ከሆነው ከኩሽ ዘር መገኘትን እንጂ ከቋንቋ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና እንዳልነበረው መረዳት ይቻላል። ሴም፣ ካም እና ያፌት አንድ ላይ ያደጉ፣ የአንድ አባትና እናት ልጆች የሆኑ ወንድማማቾች ስለነበሩ ተመሳሳይ ቋንቋ እየተናገሩ ስለማደጋቸው ለማንም ግልጽ ነው። ይሁንና እነዚህ የኖህ ልጆች ለኑሮ በሚያመቻቸው ቦታ ቤተሰባቸውን እየያዙ በየአቅጣጫው በመጓዝ መኖር ጀመሩ፣ ከብዙ ትውልድ በኋላም የባህል፣ የአኗኗር፣ የቋንቋና የመሳሰለው ልዩነት እያሳዩ መጡ።

በመሆኑም በጊዜ ሂደት ኩሽ የሚለው መጠሪያ (ቃል) ከአንድ በላይ ትርጉም እየያዘ መጣ። አንደኛው በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው የዘር ሃረጉ ከኩሽ በደም የሚወለድ ማንኛውም ጥቁር የሰው ዘር የሚገልጽ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ የቋንቋዎችን ምደባ (Language Classification) ያደረጉት የቅኝ ገዢ መንግስታት ሚሲዮናውያን ኩሽ በማለት ስም የሰጡት የቋንቋ ቤተሰብ ነው። ሶስተኛው የኩሽ ትርጉም ደግሞ የታሪክ ምሁራን በሰሜናዊ ሱዳን በአባይ ሸለቆ የነበረን የጥቁር ህዝብ ስልጣኔ የሚገልጹበት ነው። ሚሲዮናውያኑ የአፍሪካ የቋንቋዎችን ምደባ ባደረጉ ጊዜ የፈጸሙት መሰረታዊ ስህተት አለ፣ ይኸውም ኩሽ ብለው ለሰየሙት የቋንቋ ቤተሰብ ሌላ አግባብነት ያለውን ስም መስጠት (መጠቀም) ሲችሉ ለጥቁር ህዝብ ሁሉ በጋራ መጠሪያነት ያገለግል የነበረውን የመጽሃፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን “ኩሽ” የሚለውን ጥቅል ቃል (generic term) ለአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ብቻ ነጥለው መስጠታቸው ነው። በሌላ አነጋገር ለምሳሌ አፍሪካ የሚለው ቃል ለጥቂት ነገዶችን (ጎሳዎችን) ቋንቋ ብቻ ነጥሎ በመስጠት የአፍሪካ ቋንቋ ብለው እንደመሰየም ነው። Traditional Linguist ተብለው የሚታወቁት እነዚህ የአውሮፓ ሚሲዮናውያን የሰሩትን ስህተት ሳያርሙ ከእነሱ ቀጥሎ የአፍሪካ ቋንቋዎችን ምደባ የሰሩ የቋንቋ ምሁራን (Linguist) በዛው መቀጠላቸው ችግሩን ይበልጥ አወሳሰበው። ባጠቃላይ “ኩሽ” ለሚለው ቃል የሃይማኖት ሰዎች፣ የታሪክ ፀሃፊዎች፣ የቋንቋ ምሁራንና ፓለቲከኞች ጥርት ያለ ፍች ከመስጠት ይልቅ ሁሉም በተረዳውና ለራሱ በሚያመቸው መንገድ ሲገለገልበት ይታያል። ስለዚህ በመጽሃፍ ቅዱስ ላይ ያለው የካም ልጅ ኩሽ እና በታሪክ፣ በቋንቋ ምሁራን ወይም በሃገራችን ፖለቶከኞች ኩሽ ብለው የሚጠሩት ቃል ከስም አጠራሩ መመሳሰል በስተቀር የአጠቃቀም (የይዘት) ልዩነት እንዳላቸው መረዳት ያስስፈልጋል።

ኑቢያ (Nubia) ባጭሩ፣

በቅድመ ታሪክ ኑቢያ (Nubia) የሚባለው በሰሜን ሱዳን ውስጥ በአባይ ወንዝ ዳርቻዎች የሚገኝ አካባቢ (Geographical Region) ሲሆን ከደቡብ ግብጽ ከሚገኘው ኤሌፋንቲን ተብሎ ከሚጠራው ከአስዋን ግድብ ጀምሮ እስከ ጥቁርና ነጭ የአባይ ወንዝ (Nile River) መገናኛ እስከሆነው ካርቱም ከተማ ድረስ የሚያካልል ነበር። ኑብያ የሚለው ቃል ከዛሬ ከ8ሺህ ዓመት ጀምሮ የሚታወቅ ሲሆን ነገር ግን ኩሽ የሚለው መጠሪያ ግን መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ከተገለጸበት ከኖህ ቤተሰብ ታሪክ ጀምሮም ሆነ የኩሽ ስልጣኔን በተመለከተ በድንጋይ እና በፓፒረስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙ መረጃዎች የሚያሳዩት ኩሽ የሚለው መጠሪያ ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ከዛሬ ከ2ሺህ 5መቶ ዓመት አካባቢ እንደሆነ ነው። ስለዚህ ኩሽ ከኑብያ ጋር ሲነፃፀር የቅርብ ጊዜ ስያሜ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች በልምድ ኩሽና ኑቢያን እየለዋወጡ ሲጠቀሙባቸው ይታያል። ቀደም ባለው ጊዜ በኑብያ ውስጥ ስልጣኔዎች ሳይመሰረቱ በፊት በአባይ ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ በቀስት ተዋጊ የነበሩ ህዝቦች ስለበሩ አካባቢው ታሴቲ (Ta-Seti) በመባል ይታወቅ ነበር፣ ትርጉሙም የቀስተኞች ምድር (Land of the bow) ማለት ነው። እነዚህ ማህበረሰቦች የመጡት የአባይን ወንዝ ተፋሰስ ተከትለው ከአባይ ምንጭ ከሚገኝ ተራራማ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል። የታሪክ ተመራማሪ፣ አንትሮፖሎጂስት እና ፊዚስት የሆኑት ሴኔጋላዊው ዶ/ር ሼክ አንታ ዲዮፕ (Dr. Cheikh Anta Diop) የህዝቡን ዝምድና እና አመጣጥ በተመለከተ ባደረጉት የዘረ መል (DNA) ጥናት ይህንኑ አረጋግጠዋል።

በቅድመ ታሪክ በኑቢያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ጥቁር የሃገሩ ነባር ህዝቦች በአረብ እና በበርበር ህዝቦች በወረራና በጦርነት ተሸንፈው በተፅእኖ ሥር በመውደቃቸው ስማቸው፣ ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ እምነታቸውና የማንነት መገለጫዎቻቸው እንዲቀይሩ በመደረጉ ጥንታዊ መጠሪያ ስማቸው ቀርቶ አረቦች ባወጡላቸው “ሱዳን” በሚባል አዲስ ስም ይጠራሉ። ከምስራቅ አፍሪካ የቀይ ባህር ወደብ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ድረስ የአረብ የባሪያ እና የሸቀጥ ነጋዴዎች አቋርተው የሚያልፉበት የጥቁር ህዝብ መኖሪያ ሃገር አረቦች በቋንቋቸው “Bilad al Sudan” በማለት ይጠሩት ነበር። በአረብኛ ቋንቋ “Bilad al Sudan” ማለት የጥቁሮች ሃገር ማለት ነው። ይሁን እንጂ ከኑቢያ ደቡባዊ አቅጣጫ የሚገኙት የኢትዮጵያ ነገስታት ግን በየዘመኑ በአረቦች፣ በግብጾች፣ በቱርኮች እና በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች በህዝባቸውና በሃገራቸው ላይ የሚቃጣውን ተደጋጋሚ ወረራ ህዝባቸውን እያስተባበሩ፣ እነሱም በግንባር በየጦሩነቱ ላይ እየተሰለፉ የህይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈል የህዝባቸውን እና የሃገራቸውን ነጻነት፣ ባህል፣ ቋንቋ እና ኢትዮጵያዊ ብዝሃነት ሳይበረዝ አስጠብቀው መዝለቅ ችለዋል። ባህላችንን፣ ቋንቋችንን፣ ነጻነታችንን፣ ማንነታችንን ጠብቀው ላቆዩልን አባቶቻችን ዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ይሁን!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሕብር ሬዲዮ ፕሮግራም - ድብቁ የእነ ዶ/ር አብይ ጦርነት በምዕራብ ኦሮሚያ

ኢትዮጵያ (Ethiopia) ባጭሩ፣

ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፣ የግዮን መፍለቂያ፣ በቅዱሳን መፃህፍት የተገለፀች፣ የዳአ’ማት እና የአክሱም ስልጣኔ፣ የአይሁድ፣ የክርስትና፣ የእስልምና (የአብርሃም እምነቶች) እንዲሁም ባህላዊ አምልኮቶች የሚገኙባት ታላቅ ሃገር ናት። የኢትዮጵያ አመሠራረቷም ሆነ ታሪኳ ከአሜሪካ፣ ከቻይናም ሆነ ከሌሎች ሃገራት የተለየ የራሷን መንገድ ይዛ የመጣች፣ የማንም ኮፒ ያልሆነች፣ የራሷ አሻራና ማንነት ያላት ጥንታዊትና ቀዳሚት ሃገር ናት። ህዝቧም ከአፈሯ ላይ ተፈጥሮ፣ በዘመናት ሂደት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቱን/ ትስስሩን አዳብሮለመንግስትነትየበቃ ህዝብነው።ኢትዮጵያ በነጻ የተገኘች ሳትሆን አርበኛ ልጆቿ የደም ዋጋ የከፈሉላት ናት።ስለዚህ ኢትዮጵያበአንድበኩልየሰውልጅመገኛበሌላበኩልደግሞየውህደትሃገር ናት። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ትርጉምና አመጣጡን ስንመለከት ደግሞ በአብዛኛው የሃገራችን ምሁራን ተቀባይነት ያገኙሁለት ትንታኔዎች አሉ። የመጀመሪያው የቆዳ ጥቁረትን ለማመልከት በጥንታዊ የግሪክቋንቋ በጸሃይ የተቃጠለ ፊት የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ስም ደግሞ የንግስትሳባ(ማክዳ) አባትየሆነውየአጋቦስአምስተኛየልጅልጅ ከሆነው”ኢትዮፒስ” ከሚባል የኢትዮጵያ ንጉስ ስም እንደሆነ ይነገራል። ሁለቱም ታሪካችንን እና ማንነታችንን የሚገልጹ መልካም ታሪክና ትርጉም ያላቸው ትንታኔዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያ የሚለው ስም ተቀባይነት ያለው የተቀደሰ ቃል ነው።

ኢትዮጵያ ብዙ ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ናት። ታሪኳም ጥልቅና ውስብስብ ነው። በ1974 በአፋር ስምጥ ሸለቆ ልዩ ስሙ ሃዳር በተባለ ቦታ እድሜው ወደ 3.2 ሚሊዮን አመት የሚሆን የሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል መገኘቱ የሰው ልጅ በኢትዮጵያ ምድር መፈጠሩን የሚያሳይ ሲሆን በ1967 በደቡብ ኢትዮጵያ “ኪቢሽ” ተብሎ በሚጠራ ከኦሞ ወንዝ አካባቢ እድሜው ወደ 200 ሺህ ዓመት የሚሆነው እድገቱን ያጠናቀቀ የዘመናዊ የሰው የራስ ቅል በቁፋሮ መገኘቱና ይህ የራስ ቅል ብልሁ ሰው (Homo sapiens) ተብሎ የሚታወቀው የሰው ዘር እንደሆነ በሳይንስ መረጋገጡ ኢትዮጵያን በሰው ልጅ አፈጣጠር እና የአዝጋሚ ለውጥ ሂደት አንጻር ከፍ ያለ ስፍራ አሰጥቷታል። በመሆኑም ከዛሬ 200ሺህ ዓመታት አካባቢ በአዝጋሚ ለውጥ እድገቱን ያጠናቀቀ ዘመናዊ ሰው በሁለት እግሩ ቆሞ በኢትዮጵያ ምድር መሄድ መጀመሩን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ከኢትዮጵያ ምድር (ማህጸን) ተነስቶ ወንዝና ልምላኔን ተከትሎ በዙሪያው በአፍሪካ ምድር እና የኤደንን ባህረ ሰላጤን በኩል ባል አል ማንዳብ (Bal-al-Mandab) ተብሎ የሚጠራውን የባህር ሰርጥ በማቋረጥ ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መሰራጨቱ ይገለጻል። ከዛሬ አንድ መቶ ሺህ ዓመታት አካባቢ አጠቃላይ በዓለማችን ላይ ማለትም በምሥራቅ አፍሪካ በኢትዮጵያ ምድር ይኖር የነበረው ህዝብ ብዛቱ ከአስር (10) ሺህ ያልበለጠ (“ኢትዮጵያዊ”) እንደነበረና ይህ ህዝብ ተዋልዶና ተሰራጭቶ አሁን በዓለማችን ላይ የሚገኘውን 7 ቢሊየን ህዝብ አስገኝቷል።

ፑንት/Punt፣

ፑንት/Punt በሰሜን ኢትዮጵያ ይገኝ የነበረ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ አካባቢ ሲሆን በግብጻዊያን ጥንታዊ ቋንቋ ፑንት/Punt ማለት “የአምላክ ምድር ወይም የአምላክ መኖሪያ” ማለት ነው። ከዛሬ 3ሺህ 5መቶ ዓመት አካባቢ ሃሻፕሱት (Hathepsut) የተባለች የግብጽ ፈርዖን (ንግስት) ግብጽን በምትገዛበት ጊዜ የግብጽ ነጋዴዎች እጣን፣ ከርቤ፣ የዱር እንስሣት ቆዳ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ወርቅ እና የመሳሰሉትን የሚገበያዩት ወደዚሁ ፑንት ወደሚባለው አካባቢ በመምጣት ነበር። የግብጽ ነጋዴዎች ወደ ፑንት የሚመጡት በሁለት አቅጣጫ ሲሆን የመጀመሪያው የዓባይን ወንዝ ተከትለው የኑቢያን በረሃን በእግር ጉዞ አቋርጠው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከግብጽ ተነስተው በቀይ ባህር ላይ በመርከብ ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመጓዝ በአዱሊስ ጥንታዊ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ የባህር ወደብ በኩል በማድረግ ወደ ውስጥ ዘልቀው በእግር ጉዞ በመጓዝ ነበር። ስለ ፑንት በግብጽ ሃውልቶች ላይ የተፃፉ የጽሁፍ መረጃዎች እና የፑንት ነዋሪዎች መኖሪያ ተብለው በቤተ መቅደስ ግንቦች ላይ የተሳሉ የጎጆ ቤት ምስሎች አሰራር በሰሜኑ የሃገራችን አካባቢ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ Periplus of the Erythraean Sea የተባለ የመርከበኞች የጉዞ ካርታ የግብጽ ነጋዴዎች ወደ ፑንት ሲጓዙ የሚጠቀሙበት አዱሊስን ወደብ የሚያስይ በመሆኑ ፑንት በሰሜን ኢትዮጵያ ይገኝ የነበረ አካባቢ መሆኑ ተረጋግጧል። ሌላው ፑንት በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኝ እንደነበር የሚያሳየው በግብፅ ፈርኦኖች መቃብር ውስጥ አብረው ከጌቶቻቸው ጋር ተቀብረው የተገኙ በመሚ የደረቁ የዝንጀሮዎች አካል ላይ በተወሰደ ናሙና ላይ በተደረገ የDNA የላቦራቶሪ የፍተሻ ነው። የDNA የፍተሻ ውጤት የሚያሳየው በመሚ የደረቁ ዝንጀሮዎች ዝርያቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ መሆናቸው ነው።

አበሻ ማነው?

አበሻ(ሐበሻ) የሚለውቃልዘርን፣ጎሳን፣ነገድን፣ ሃይማኖትንወይምየትኛውንምማህበረሰብ በተናጠል የማይወክል፣ ውህድ ማንነት ሲሆንበባህል፣በኑሮ፣በባህሪናበአስተሳሰብ (Mindset)የሚገለጽ ነው።ለምሳሌየአበሻመድሃኒት፣የአበሻልብስ፣የአበሻዶሮ፣የአበሻጎመን፣የአበሻ ቃሪያ፣እንዲሁምከባህሪና ከስነ ምግባርአንፃርደግሞየአበሻጀብዱ፣ የአበሻኩራት፣የአበሻይሉኝታ፣የአበሻጀግንነትወዘተ እየተባለ ይገለጻል። ስለዚህ አበሻነት በኢትዮጵያምድርበቅሎ ያደገ፣ በሚታይና በሚጨበጥ፣ በኑሮ፣ በባህል፣ በባህሪ፣ በምግብ፣ በልብስእና በመሳሰሉት የሚገለጽ በመሆኑ ብሔርና ቋንቋ ሳይገድበው የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ሃብት መሆን ችሏል።

አበሻ የሚባል የተለየ ጎሳ፣ ብሔር፣ ህዝብ ወይም ክልል በኢትዮጵያ ምድር የለም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ቋንቋው ግዕዝ የሆነ አበሻ (ሐበሻ)የሚባልነገድበጥንትጊዜኢትዮጵያውስጥ ይኖርነበር ሲሉ ይሰማል፣ ሌሎቹ በተለይ ሃገሪቷን በዘር፣ በጎሳና በየምክንያቱ የመከፋፈል ልክፍት ያለባቸው ጠባብ ብሔርተኞች ደግሞ አበሻ የሰሜን ኢትዮጵያ ነዋሪዎችን የሚወክል ነው ይላሉ። እውነቱ ግን በሰሜን ኢትዮጵያ የሚኖረው ህዝብ የሴም፣ የኩሽ እና የናይሎቲክ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ እንጂ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የተለየ አይደለም። ህዝቡ የየራሱ ባህል ቢኖረውም በጋራ የሚጋራው ከአለባበሱ እና ከአመጋገቡ ጀምሮ በርካታ ተመሳሳይባህልና ስነልቦና ያለው ህዝብ ነው። ለምሳሌ የአገው ትውልድ የሚመዘዘው ከንጉስ ዳዊት የልጁ ልጅ ነው። ቀዳማዊ ምኒሊክ የዳዊት የልጅ ልጅ የንጉስ ሰሎሞን ልጅ ነው። ስለዚህ የአገው እና የአማራ ነገስታት የአጎት ልጆች(cousin)ወይም ወንድማማቾች ናቸው። እንደሚታወቀው ንጉስ ዳዊት የእስራኤል ዘር በመሆኑ ሴማዊ ነው። ስለዚህ የአገው ነገድ የነብዩ የንጉስ ዳዊት ዘር ስለሆነ በቋንቋው የኩሽ ቤተሰብ ቢባልም በደሙ ግን የሴም ዘር ነው። በመሆኑም አማራ እና አገው በታሪክም፣ በባህልም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሆኑ ከአንድ የዘር ግንድ የተገኙ በደም የተሳሰሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው።

ባጠቃላይ አሁንያለውነባራዊሁኔታየሚያሳየን መነሻው የትም ይሁን የትአበሻነት በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ እንደጨው ሟሙቶና እንደ ቅቤ ቀልጦ በአለባበስ፣ በአመጋገብ፣ በአኗኗር፣ በአስተሰብ፣ በባህሪበሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚንጸባረቅ፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ጎሳና ነገዶች የሚጋሩት ቋንቋ፣ ብሔር እና ሃይማኖት የማይገድበው ውህድ ማንነት እንጂ በተናጠል የእገሌ ብቻ ነው የሚባል አይደለም።አበሻነትየኢትዮጵያህዝብአብሮለዘመናትበጋራበመኖሩ የገነባው የጋራእሴት ነው።አበሻየሚለውአገላለጽ የሃገርበቀልየሆነውንእፅዋት፣እንስሳ፣ሰውን እና አስተሳሰቡን ጭምር የሚመለከት፣ ኢትዮጵያዊውንከውጭከመጣውከባዕዱለመለየትየሚያገለግል ስለሆነ አበሻለሃገሩነባር(Native) መሆንንያመለክታል።

ምንም እንኳን አቢሲኒያ የሚለው መጠሪያ አበሻ ከሚለው ቃል የተገኘ ቢመስልም በአማርኛም ሆነ በግዕዝ የቋንቋ ስርዓት (ሰዋሰው) ከአበሻ ከሚለው ቃል አበሾች፣ የአበሻ ሃገር ወዘተ ተብሎ ቃል ሊራባ (ሊገኝ) ይቻላል እንጂ “አቢሲንያ” ተብሎ አይጻፍም። “አቢሲኒያ (Abyssinia)” የሚለውን ቃል እንደ ሃገር ወይም እንደ ቦታ መጠሪያነት ለመጀመሪያ ጊዜ የፃፉት በመካከለኛው ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ የፖርቹጋል ሚሲዮናውያን (እየሱሳውያን) ናቸው። “Abyssinia”, የላቲን ቋንቋ ስርዓት ነው። በላቲን “ia” ማለት መሬት ወይም ሃገር ማለት ነው። እንደሚታወቀው በጥንት ጊዜ የነበሩ የሃገራችን ንጉሶች እኔ የኢትዮጵያ ንጉስ ነኝ ይላሉ እንጂ ሃገሬ አበሻ ወይም አቢሲኒያ ናት ብለው አያውቁም። ከውጭ መንግስታት ጋር ሲፃፃፉም የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት እያሉ ነበር ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት። ለምሳሌ በ4ኛው ክ/ዘ የነገሰው ንጉስ ኢዛናም ሆነ ከሺህ ዓመት በኋላ በ14ኛው ክ/ዘ የነገሰው አፄ ዓምደ ጽዮን እራሳቸውን የሚጠሩት እኔ “ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” እያሉ ነበር። ይሁን እንጂ የ60ዎቹ ግራ ዘመም ፓለቲከኞች ህዝቡን በንጉሳዊ መንግስት ላይ ለአመፅ ለማነሳሳት አበሻ የሚለውን ቃል ትርጉሙን በማዛባት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተጠቅመውበታል። በዚህ ክፉ ስራቸው የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል መሬቷን እንደ አኬል ዳማ የደም መሬት አድርገዋታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንደ ታደሰ ወረደ ስለ ጥምር ጦሩ ብርታት የተናገረ የመንግስት አካልም የለም

የአባይ ሸለቆ ስልጣኔ (Nile valley Civilization)፣

እንደሚታወቀው ውሃ ለህይወት መሰረት ነው። በመሆኑም በአባይ ወንዝ ዳርቻ ከሚገኙት ከኑብያና ከግብፅ እስከ ሜሴፖታሚያ ድረስ የተገነቡ አብዛኛዎቹ ጥንታዊ ስልጣኔዎች በወንዝ (በውሃ) ዳር የተገነቡ ናቸው። አንድ አካባቢ ሰፍረው፣ መንደር መስርተው ይኖሩ የነበሩ ጥንታዊ ማህበረሰቦች በተለያዩ የገቢ ምንጭ ባላቸው ስራዎች ተሰማርተው እየሰሩ ለመኖር በሚያደርጉት ጥረት በጊዜ ሂደት እየተደራጁ በመሄድ ከትንሽ ሰፈራ (Settlement) ተነስተው ከፍ ወዳለና ወደ ተሻለ ስልጣኔ እንደሚሸጋገሩ ይታወቃል። በመሆኑም የኑብያን በረሃ መሃል ለመሃል ሰንጥቆ በሚያልፈው በአባይ ወንዝ ዳርቻ የበረሃው ንዳድ ገፍቶ፣ የዓባይ ልምላሜ እንደ ማግኔት ስቦ ያሰባሰባቸው፣ በለምለሙ የአባይ ሸለቆ (Nile Valley) እዚህም እዛም የሰፈሩ ጥንታዊ ማህበረሰቦች በአነስተኛ ግብርና፣ በአደን፣ በአሳ ማጥመድ፣ በከብት ማርባት፣ በሸክላ ስራ፣ በንግድ ስራ እና በመሳሰሉት ስራዎች ተሰማርተው ይኖሩ ነበር። እነዚህ ማህበረሰቦች በሂደት ከሰፈራ (Settlement) ወደ አነስተኛ ስልጣኔ በመሸጋገር በአባይ ወንዝ ዳርቻ ከዛሬ 5 ሺህ 5 መቶ ዓመት አካባቢ ከርማ ወይም ኑብ (Kerma/ Pnubs) በተባለ ቦታ የመጀመሪያውን የጥቁር ህዝብ ስልጣኔ (Civilization) መሰረቱ። ከከርማ ቀጥሎ ናፓታ (Napata)፣ ሜሮኤ (Meroe’)፣ ማኩሪያ (Makuria)፣ አሎዲያ (Alodia)፣ ኑባቲያ (Nobatia) እና የመሳሰሉት የጥቁር ህዝብ መኖሪያ መንደሮችና ስልጣኔዎች በናይል ሸለቆ በአባይ ወንዝ ዳርቻዎች እየተስፋፉ ሄዱ።

የግሪክ ታሪክ ጸሃፊና ጂኦግራፈር የሆነው ሄሮዱተስ “Egypt is a gift of Nile.” እንዳለው የዓባይ ወንዝ ባይኖር የግብጽም ሆነ የኑብያ ስልጣኔዎች አይታሰቡም ነበር። በአባይ ዳርቻ ከተከሰቱ ስልጣኔዎች እንደ ምሳሌ በደቡብ ኑብያ የሚገኘው የሜሮኤ (Meroe’) ስልጣኔን ብንመለከት በወቅቱ የዓባይን ወንዝ በመጥለፍ በመስኖ እርሻ ስራ የታወቁ ነበሩ። ከሜሮኤ በፊት ከርማ፣ ናፓታና የመሳሰሉት በሰሜንና በማዕከላዊ ኑብያ ይገኙ የነበሩ የጥቁር ህዝብ ስልጣኔዎች በግብፅ የፈርዖን ጦር የወደሙት በአካባቢው የበላይ ገዥ ለመሆን በነበረ የጠላትነት ስሜት ነበር። በተለይ በ25ኛው ስርወ መንግሥት ኑቢያውያን ናፓታን ዋና ከተማቸው በማድረግ ከግብጽ እስከ ሶሪያ ድረስ ይገዙ ስለነበር ሳምቲክ 2ኛ (Psamtic II) የተባለ ፈርኦን በ592 ዓ/ዓለም ናፓታ ዳግም ግብጽን መግዛት እንዳትችል አድርጎ በበቀል ከተማዋን ያለ ምህረት እና ያለምልክት ከምድረገጽ አጠፋት። ይሁንና ከሞትና ከምርኮ የተረፉት የናፓታ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ወደ ደቡብ ኑቢያ እርቀው በመሰደድ የሜሮኤ መንግስትን (Meroe’ Kingdoom) በመመስረት ንግስናቸውን ቀጠሉ። ይህ የሜሮኤ መንግስት የኩሳ (ኩሽ) መንግስት እየተባለ በጥንት የኢትዮጵያ ታሪክ ይገለጻል።

ምንም እንኳን የሜሮኤ (የኩሳ) ስልጣኔ ከግብጽ የራቀ በመሆኑ ለጊዜው የተረጋጉ ቢመለሱም በሌላ በኩል ደግሞ ለአክሱም ከነበራቸው ቀረቤታ አንጻር የአካባቢውን የንግድ መስመር ለመቆጣጠር ከአክሱም መንግስት ጋር አዲስ ፉክክር ውስጥ ገቡ። በመሆኑም የሜሮኤና የአክሱም መንግስታት ትከሻ ለትከሻ ይለካኩ ጀመር። በወቅቱ የሜሮኤ መንግስት ከአባይ ወንዝ በተጠለፈ ውሃ በመስኖ የእርሻ ልማት በተጨማሪ በብረት ማቅለጥ ጥበብ (ቴክኖሎጂ) ስራም የተካኑ ስለነበሩ ከብረት የተሰሩ ጦር፣ ጎራዴ፣ ቢለዋ፣ ማረሻ እና የመሳሰሉ የእጅ መሳሪያዎችን በማምረት ለገበያ በማቅረብ ከፍታኛ ገቢ ያገኙ ነበር። ይሁንና ብረት የማቅለጡን ስራ የሚያከናውኑበት መንገድ እጅግ አድካሚና ከፍተኛ የእንጨት ፍጆታ የሚያስፈልገው አባካኝ ስለነበረ ለዚሁ ስራ የሚጠቀሙበት የአካባቢው ደን ተጨፍጭፎ በማለቁ (Deforestation) ምክንያት ከፍተኛ የእንጨት እጥረት አጋጠማቸው። ከዚህም በተጨማሪ መሬቱ በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ በመስኖ ይታረስ ስለነበር የአፈሩ የተፈጥሮ ለምነቱን በማጣቱ በቂ ምርት መስጠት አቆመ። ባጠቃላይ ባጋጠማቸው ተደራራቢ ችግር የሜሮኤ ኢኮኖሚ እየወደቀ፣ መንግስቱም ጥንካሬውን እያጣ ሄደ። ከዚህ በተጨማሪ ከአባይ ወንዝ እስከ ቀይ ባህር ዳርቻ በዑደት ከቦታ ቦታ በመዟዟር የሚኖሩ ቤጃ የሚባሉ ተንቀሳቃሽ ከብት አርቢ (Pastoral Nomadic) በሜሮኤ ከተማ እና በአካባቢው በሚገኙ መንደሮች ላይ ድንገተኛ ወረራ በመፈፀም በነዋሪው ላይ በተደጋጋሚ ዝርፊያና ጥቃት ፈጽመው የመሸሽ ክፉ ልማድ ነበራቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ/ ኤርትራ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የአክሱም መንግስት አካል የነበሩ (Bareya)፣ ሳሊም (Salim)፣ ኩናማ (kunama) የሚባሉ ማህበረሰቦች ነበሩ። ኢኮኖሚው የተዳከመው የሜሮኤ (የኩሳ) መንግስት ወደ አክሱም ግዛት ውስጥ ጥሶ በመግባት እነዚህን የባርያ፣ የሳሊም እና የኩነማ ማህበረሰቦችን ለመፈንገል ጥቃት ይፈጽምባቸው ጀመር (ባርያ በወቅቱ የአንድ ማህበረሰብ ስም የነበረ ሲሆን ከአዲያቦ በስተሰሜን የሚኖሩ ማህበረሰቦች ናቸው።) የባርያ ማህበረሰቦች መልዕክተኛ አክሱም ከተማ ድረስ በመላክ የደረሰባቸውን ጥቃት ለመንግስታቸው በማሳወቃቸው በወቅቱ የአክሱም ንጉስ የነበረው ንጉስ ኢዛና ከሜሮኤ መንግስት ጋር የአትባራ (ተከዜ) ወንዝ ወደ ዓባይ ወንዝ በሚቀላቀልበት አካባቢ በ350 ላይ ጦርነት አድርገው በንጉስ ኢዛና የሚመራው የአክሱም ሰራዊት ድል በማድረግ ብዛታቸው ከ6መቶ በላይ የሚሆኑ የሜሮኤ (ኩሳ) ምርኮኞችን ይዞ ወደ አክሱም በድል ተመለሰ። ንጉስ ኢዛና ከድል በኋላ አንዱን በአክሱም ሌላውን ደግሞ በሜሮኤ ከተማ ባቆመው በድንጋይ (Tablet) ሃውልት ላይ በግዕዝ፣ በሳባውያን እና በጥንታዊ የግሪክ ቋንቋዎች (TriLingual) ባጻፈው የድል ሃውልት ላይ እኔ ንጉሰ ነገስት ኢዛና የኢላ አሚድ ልጅ በሰማይ እና በምድር አምላክ ረዳትነት የኖባ (የኩሳ) ህዝቦች በአመጽ ተነሳስተው የባርያ እና የሶባ (ጥቁር እና ቀይ ህዝቦችን) በግፍ በማጥቃታቸው ጦርነት ገጥሜያቸው አሸንፌያለሁ ይላል። በመቀጠልም በዚሁ የድል ሃውልት ላይ እኔ የኩሳ (የሜሮኤ)፣ የቤጃ፣ የሳባ፣ የኢትዮጵያ ንጉስ ነኝ በማለት በማያሻማ ሁኔታ ንጉሰ ነገስት መሆኑን ገልጿል።

ቋንቋ ምደባ እናየህዝብ ፍልሰት፣

እንደሚታወቀው የሰው ልጅ በዓለማችን ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲፈልስ፣ ሲሰደድ፣ ሲሰራጭ ኖሯል። በተለይ በኢትዮጵያ የተደረጉ የህዝብ ፍልሰቶችን እና ስርጭቶችን የተመለከትን እንደሆነ በሦስት አቅጣጫ የተደረጉ ሆነው እናገኛቸዋለን። አንደኛው ከኢትዮጵያ ተነስቶ ድንበር አቋርጦ ወደ ውጭ የተደረገ ፍልሰት፣ ሁለተኛው ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የተደረገ፣ ሶስተኛው ደግሞ ከአንደኛው የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ሌላኛው የኢትዮጵያ ክፍል የተደረጉ የሃገር ውስጥ ፍልሰቶች እና መስፋፋቶች ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ብቻ ሳትሆን የቋንቋና የባህል መፈጠሪያና መዋሃጃ ጭምርም ናት። በተለያዩ ዘመናት ሰዎች ከኢትዮጵያ ምድር ተነስተው ወደ ቀረው ዓለም በተሰራጩ (በተሰደዱ) ጊዜ ባህልና ቋንቋቸውም አብሯቸው እንደሚሰራጭ ይታወቃል። ከብዙ ዘመናት ቆይታ በኋላ በዳግም ፍልሰት (Back migration) ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ወይም በንግድና በመሳሰሉት ከህዝቡ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በተሰደዱበት ቦታ ያዳበሩትን ባህልና ቋንቋ ይዘው በመመለስ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በፈጠሩት መስተጋብር አዲስ ውህድ ማንነት (አበሻነትን)አስገኝተዋል።

እንደሚታወቀው በሃገራችን ቁጥራቸው ከ85 ያላነሱ ነገዶች/ ብሔሮች ይገኛሉ። በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሞ ሸለቆና በአካባቢው ሃይቆችና ወንዞች ዳርቻዎች ብቻ ከ40 በላይ ሲሆን ከቋንቋ ብዛት አንፃር ስንመለከት ደግሞ በኢትዮጵያ ከ83 በላይ ቋንቋዎች (Languages) እና ከ200 በላይ ዘዬዎች (dialects) መኖራቸው ተረጋግጧል። የቋንቋ ምደባ (Languages Classification) ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ ውስጥ የተካሄደው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከቅኝ ግዛት ማስፋፋት ጋር በተያያዘ ወደ አፍሪካ በመጡ የአውሮፓ ሚሲዮናውያን፣ በቅኝ ግዛቶቹ ሹመኞች፣ በሰላዮቻቸው እና በመሳሰሉት ነበር። ምናልባት ስራውን እስከሰሩ ድረስ የፓለቲካ አቋማቸው ወይም እምነታቸው ምንድነው ችግሩ የሚል ገራገር ሃሳብ ሊነሳ ይችል ይሆናል። ከፍተኛ የቋንቋ ብዝሃነት (high linguistic diversity) ባለበበት እና ከ2000 ያላነሰ ቋንቋዎች በሚነገርበት በአፍሪካ አህጉር የቋንቋውን ተናጋሪ ማህበረሰቦችን በያሉበት በማግኘት ለስራው አጋዥ የሆነ በቂ መረጃ አሰባስበው ስለመስራታቸው እና ከሞያ ብቃታቸው ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዋናነት በቅኝ ገዢ መንግስቶቻቸው እንዲያሳኩ የተሰጣቸው ዓላማና ተልዕኮ በውጤቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዳለው አያጠያይቅም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለቸኮለ! ሰኞ ታኅሳስ 25/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

ከሰባኪ ሚሲዮናውያኑና ፓስተሮች በመቀጠል የአፍሪካ ቋንቋዎችን ምደባ (Language Classification) የተደረገው በ1963 ላይ በአሜሪካዊው የስነ ልሳን ሊቅ በሆነው በፕ/ር ጆሴፍ ግሪንበርግ ሲሆን ከእሱ በፊት Friedrich Müller እና Diedrich Westermann የተባሉ ሚሲዮናውያን (Traditional Linguist) የአፍሪካ የቋንቋ ቤተሰብ በማለት አዘጋጅተውት የነበረውን መሰረት ባደረገ ሁኔታ የራሱን “Mass Comparison Method” ብሎ የሰየመውን የቃላቶችን ዝምድና ማነጻጸሪያ ዘዴ (Tabulation) በመጠቀምና አንዳንድ የስም ለውጦችን እና የምደባ ማሻሻያዎችን በማድረግ አጠቃላይ በአፍሪካ አህጉር እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚነገሩ ቋንቋዎችን 1) አፍሮ-ኤሽያ (Afro-Asiatic)፣ 2) ናይሎ-ሳህራ (Nilo-Saharan)፣ 3) ኒጀር-ኮንጎ (Niger-Congo) እና 4) ካሆሲያን (Khoisan) የቋንቋ ቤተሰብ በማለት በአራት ትላልቅ (ዓብይ) የቋንቋ ቤተሰቦች መደባቸው። እያንዳንዱ ዓብይ የቋንቋ ቤተሰብ በስሩ ንኡሳን የቋንቋ ቤተሰቦችን ያቀፈ ነው። ለምሳሌ በተራ ቁ 1 ላይ አፍሮ-ኤሽያ (Afro-Asiatic) ተብሎ በሚጠራው ዓብይ የቋንቋ ቤተሰብ ስር ኩሻዊ፣ ሴማዊ፣ ኦማዊ፣ በርበር፣ ቻዳዊ፣ ኮፕት/ Egyptian በማለት ይዘረዝራቸዋል።

ይሁን እንጂ እንደ Lionel Bender (2000), Harold Fleming (1976), Lyle Campbell (2008) እና የመሳሰሉ የቋንቋ ልሂቃን (linguists) የፕ/ር ጆሴፍ ግሪንበርግ በጅምላ ንጽጽር ዘዴ (Mass Comparison Method) መሰረት ያዘጋጀው የቋንቋ ምደባ የማይዛመዱ ቋንቋዎች አንድ ላይ ደበላልቆ መያዙን በመጠቆም፣ አመዳደቡ የሃሳብ እና የመዋቅር (conceptual and structural) ችግሮች እንዳሉበት ሙያዊ ትችቶችን በመስጠት ማሻሻያ እንዲደረግበት ሂስ አቀረቡ። የጅምላ ንጽጽር ዘዴው በአፍሪካ ቋንቋዎች ምደባ ላይ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የአሜሪካ ነባር ህዝቦች በሆኑት በቀይ ህንዶች ቋንቋ ምደባ ላይም ተመሳሳይ ህጸጽ ነበረበት።

የጆሴፍ ግሪንበርግ የጅምላ ንጽጽር ዘዴ በአፍሪካ የቋንቋ ምደባ ላይ ያሳየውን ውስንነት አንድ ሁለት ምሳሌዎችን በማንሳት ለማየት እንሞክር። እንደሚታወቀው የኑብያ ስልጣኔ ከጀመረበት በአባይ ወንዝ ዳር በሰሜን ኑብያ ከሚገኘው ከርማ ከሚባለው ጀምሮ ናፓታ፣ ማኩሪያ፣ አሎዲያ፣ ኑባሺያ፣ ዶንጋላን አልፎ እስከ ደቡባዊ ኑብያ እስከ ሆነችው ሜሮኤ ድረስ አሁኑ በአካባቢው የሚኖረው ህዝብ የሚናገረው የቋንቋ ቤተሰብ የተመደበው የኩሽ ቋንቋ በሚባለው ሳይሆን በናይሎ ሳህራ (Nilo-Saharan) የቋንቋ ቤተሰብ ስር ነው። እዚህ ላይ የተጣረሰ ነገር ያለ ይመስላል። በአሁኑ ጊዜ ሃውልቶቹና ቤተ መቅደሱ ፈራርሰው በሚታዩበት በመሬቱ/ በአካባቢው ላይ የሚኖረው ህዝብ የሚናገረው ቋንቋ “ናይሎሳህራ” ነው እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣኔው ግን የኩሽ ስልጣኔ ነው ማለታቸው ግልጽ አይደለም። ችግሩ በዚህ ብቻ አያበቃም አሁንበዘመናችንበተለይምበእኛሃገር”የኩሽ” ቋንቋተናጋሪተብለውየተሰየሙትህዝቦችወይምነገዶች”በኩሽ” ስም ከመጠራታቸውውጪበጥንትጊዜኑብያውስጥ በታሪክየኩሽስልጣኔና ህዝብተብለውከሚታወቁት ህዝቦች ጋር በቋንቋ፣በባህል፣በአምልኮትናበመሳሰለውየሚጋሩትአንዳች ነገር ለመኖሩ የቀረበ ማስረጃ የለም። በሌላአነጋገር ባሁን ጊዜ በአካባቢው በመኖር ላይ የሚገኙ የኑብያህዝቦችንበናይሎሳህራየቋንቋቤተሰብሲመደቡ፣ ከኑብያ የግዛት ክልል ውጪ የሚገኙለኩሽስልጣኔየነበራቸው ታሪካዊ ግንኙነት የሚያሳይ አንዳችም መረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ በሺ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩ ህዝቦች ግን የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ተብለው መመደባቸው ነገሩን እንቆቅልሽ ያደርገዋል። ሌላው ደግሞ የአገው ህዝብ የዘር ትውልድ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከትውፊት አንጻር ስንመለከት በደሙ ሴማዊ ሆኖ እናገኘዋለን ነው። በአገው ማለትም በላስታ ማህበረሰብ ትውፊት እንደሚነገረው የአገው ትውልድ የሚመዘዘው ከንጉስ ዳዊት የልጁ ልጅ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ምኒሊክ ጋር አብረው እንደመጡ ይነገራል። ቀዳማዊ ምኒሊክ የዳዊት የልጅ ልጅ የንጉስ ሰሎሞን ልጅ በመሆኑ ከአገው አባቶች ጋር የአጎት ልጆች ወይም ወንድማማቾች ናቸው ማለት ነው። እንደሚታወቀው ንጉስ ዳዊት ደግሞ የእስራኤል ዘር ሴማዊ ነው። ስለዚህ የአገው ነገድ የነብዩ የንጉስ ዳዊት ዘር ስለሆነ በቋንቋው የኩሽ ቤተሰብ ቢባልም በደሙ ግን የሴም ዘር ነው።

የኩሽ ቋንቋና የኩሽ ስልጣኔ፣ (ባጭሩ)

የኩሽ ስልጣኔ እና የኩሽ ቋንቋ የተለያዩ ናቸው። የኩሽ ስልጣኔ ሲባል በኑብያ ውስጥ በአባይ ዳርቻ የነበረውን ጥንታዊ የጥቁር ህዝብ ስልጣኔ ለማለት እንጂ በወቅቱ ህዝቡ ይናገረው የነበረው ቋንቋ አሁን በሃገራችን “የኩሽ  ቋንቋ” ተብሎ ከሚገለፀው ጋር አንድ ነው ለማለት ዓይደለም። በቅድመ ታሪክ በኩሽ ህዝብ ተብለው በሚጠሩት ማህበረሰቦች የነበራቸው ባህል፣ ልማድ፣ የአምልኮ ስርዓት፣ የቤተመቅደስና የቤተመንግስት ህንጻ የአሰራራ ጥበባቸው፣ የንጉሶች የመቃብር ሃውልቶች አሰራር፣ የአምላኮቻቸው መጠሪያ ስሞች አሁን የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪ ተብለው በሚጠሩት ህዝቦች ዘንድ አንዱም አይገኝም። የጥንቱ የኩሽ ቋንቋ (ቋንቋዎች) ምን ዓይነት እንደነበር(ሩ) አይታወቅም። በድንጋይ ላይም ሆነ በፓፒረስ ላይ የኩሽ ነገስታት ስለራሳቸው ነገድና ጎሳ፣ በግዛታቸው ስለ ነበሩ ማህበረሰቦች ብዛትና ዓይነት ወይም ይናገሩት የነበረውን ቋንቋ በተመለከተ ያስቀመጡት ምንም ዓይነት መረጃ አልተገኘም። የኩሽ ቋንቋ (የኩሽ ቋንቋ ቤተሰብ) መባል የተጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ሃገራችን እና አህጉራችን በመጡ ሚሲዮናውያን (“ነጭ ደብተራዎች”) ነው። ሚሲዮናውያኑ የፈለጉትን ሌላ ገላጭ የሆነ ስም መጠቀም (መስጠት) ሲችሉ በምንቸገረኝነት ከጥንት ጀምሮ ለጥቁር ህዝብ ሁሉ በጋራ መጠሪያነት ያገለግል የነበረውን “ኩሽ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል (Generic Term) ለአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ብቻ ነጥለው መስጠታቸው የቃሉን ትርጉምና ታሪካዊ አመጣጡን በማዛባት በብዙ ሰዎች ዘንድ ኩሽ በሚለው ቃል አጠቃቀም ላይ መደናገርን ፈጠረ።

የመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለፀው ኩሽ እና በታሪክ የኩሽ ስልጣኔ የሚባሉት የተለያዩ መሆናቸውን “ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው ዶ/ር ግርማ አውግቸው በሰፊው አብራርተው ስለጻፉት መፅሃፉን ማንበብ የተሻለ ይሆናል። ከሞላ ጎደል በመጽሃፉ ላይ የሚከተሉት ፍሬ ሃሳቦች ይገኛሉ፡ በዘመናችን ኩሽ እየተባሉ የሚገለጹትን የቋንቋ ቤተሰቦችም ሆኑ እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሕዝቦች ጥንት በቅድመ ክርስቶስ ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ጀምሮ በነበረው ኩሽ በሚባለው አገር (ስልጣኔ) ከሚኖሩ ነገዶች ወይም ሕዝቦች በቀጥታ የወረዱ ናቸው ማለት አይደለም። በዘመናችን ኩሽ የሚባሉት ህዝቦች በስማቸው ከመመሳሰል ውጭ “ከጥንቱ የኩሽ ስልጣኔ” ጋር ግንኙነት የላቸውም። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱሱ ላይ ኩሽ ተብሎ የተገለፀው የካም ልጅ (የኖህ የልጅ ልጅ) እና አሁን በሥነ ልሳን ጥናት ኩሽ የሚባለው የቋንቋ ቤተሰብ ከስማችው መመሳሰል በስተቀር የታሪክ ግንኙነት የላቸውም። —//—

እውነት መዳኛችን ነው!

ደረጀ ተፈራ

ምንጭ፣

“ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ” (ዶ/ር ግርማ አውግቸው )
“በረራ – ቀዳሚት አዲስ አበባ (1400 – 1887). .” ዶ/ር ሃብታሙ መንግስቴ ተገኝ – 2020
“The origin of Amharic” (Girma Awgichew Demeke)
“The Ethiopian Borderlands” (Richard Pankhurst)

—///—

3 Comments

  1. The original Jews are African people from Suthern
    Egypt that had been relocated or carried out to the
    land of Canaan by one Egyptian pharoh in his war
    with the Achamenid dynasty persian king called
    xerxes.The light skinnned black Africans settled
    in the then empty land called canaan . When the
    bible was written this history got somewhat distorted
    in later times to change the narrative that human
    civilization originated in Africa or Egypt .

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share