የባልደራስ አመራሮች ባስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል! (ጌታቸው ሺፈራው)

የባልደራስ ሊቀመንበር እስክንድር ነጋን ጨምሮ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ አስካለ ደምሴ የታሰሩት፣ የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ ብዙ ወንጀል እንዲሰራ ላደረጉት ሌሎች አካላት ማመጣጠኛ ነው። እነ እስክንድር ምንም ሳያደርጉ ታስረው ብዙ ወንጀል የሰሩ ግን አሁንም የሽግርር መንግስት በማቋቋም ላይ ናቸው። ዋናው ነገር እነ እስክንድር ምንም አይነት ወንጀል አልሰሩም ነው። ብዙ ንፁሃንን አስፈጅተው ለታሰሩት ማመጣጠኛ ተብለው የታሰሩት እነ እስክንድር ምንም ወንጀል ሳይሰሩ ነው የታሰሩትና ይፈቱ ስንለው ከከረምነው አሁን ተጨማሪ ምክንያቶች አሉን።

1) በዚህ ሀገር ምርጫ ያለው ጫና እየታወቀ፣ ከእስር ቤት ውጭ ያሉትና ቀስቅሰው ምርጫ ማድረግ የሚችሉትም ምርጫውን አንፈልግም ብለው፣ ኢትዮጵያን እየጎተቱ ላሉት የውጫ አካላት በየቀኑ መረጃ እያቀበሉ፣ አሁን ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደር ቅብጥርጥስ ሲሉ በእስር ቤት ብዙ በደል እየደረሰባቸው ያሉት የባልደራስ አመራሮች ግን ምርጫውን እንሳተፋለን አሉ። ተሳተፉ። ከእነ ችግሩ ለተደረገ ምርጫ “ለመረጣችሁንም ላልመረጣችሁንም እናመሰግናለን” ነው ያሉት። እስር ቤት ለብሶት የሚዳርግ ብዙ ነገር ስላለ ምርጫው አያስፈልግም አላሉም። ምርጫውን አላሸነፍንም ብለው አላንገረገሩም። ችግር ስላልነበረበት አይደለም። ከራሳቸውም ከፓርቲያቸውም በላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ዙርያ ገባውን አይተው ነው። ይሄ የባልደራስ አመራሮች አካሄድ የሞራል የበላይነታቸውን፣ የአሳሪዎችን ባሕሪ በደንብ ያጋለጠ ነው። የብልፅግና ካድሬዎች “ኢትዮጵያ አሸንፋለች” ይላሉ። ይህ አባባል እውነት ቢሆን ኖሮ የባልደራስ አመራሮች ነበር ማለት የነበረባቸው። ያለ አግባብ ታስረው፣ እስር ቤት ውስጥ ብዙ ጫና ችለው፣ መወዳደር አትችሉም ሲባሉ የፍርድ ሂደቱ ላይ እምነት አድርገው እስከመጨረሻው ተከራክረው፣ እስር ቤት ያሉ አካል እንደሚለው “ምርጫው አይጠቅምም” ሳይሉ ተሳትፈው፣ ከዛም ለመረጣቸውም ላልመረጣቸውም አመስግነዋል። ከዚህ በላይ ለዲሞክራሲ ሞዴል የት ይገኛል? ከዚህ በላይ ሀገር እንዲያሸንፍ የሚፈልግ ማን ነው? ከዚህ በላይ የራሱን በደል ችሎ ለሂደት የሚጨነቅ ማን አለ? ከእነዚህ እስረኞች የተሻለ በዚህ ወቅት ምስቅልቅል ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያ በአሳቢነት ማን ሊጠቀስ ይችላል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምዕራብ ጎጃም የተጠለሉ ተፈናቃዮች አቤቱታ

2) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምርጫው ለተሳተፉ ፓርቲዎች እንደ ተሰትፏቸው ስልጣን እንደሚያጋሩ ተናግረዋል። በሂደት የሚታይ ይሆናል። የሆነ ሆኖ በምርጫ ለተሳተፉት አጋራለሁ ያሉት ምንም ይሁን ምን በሂደቱ አምነው ስለተሳተፉ ነው። ባልደራስ በሂደቱ ተሳትፏል። እስር ላይ ያሉ አመራሮች ከእስር ቤት ውጭ ያሉትን ጓዶቻቸውን “እኛን እስር ቤት ጥላችሁ እንዴት ምርጫ ላይ ጊዜያችሁን ታጠፋላችሁ?” አላሉም። እነሱም ምንም ይሁን ብለው በሂደቱ ተሳትፈዋል። በምርጫው ከተሳተፉት ሁሉ የመጀመርያው እውቅናም ምስጋናም ሊሰጥ የሚገባው እስር ቤት ሆነው ለተሳተፉት ነበር። ከእስር ቤት ውጭ ካሉት በባሰ በከፋ ሁኔታ ሆነው ነው ለምርጫ የቀረቡት። መንግስት መጋራቱ እስር ቤት ላሉት የባልደራስ አመራሮች ቅንጦት ነው። መጀመርያ ያለ አግባብ ከታጎሩበት መለቀቅ አለባቸው። ከዛ መንግስት ማጋራት የሚለው የሚታይ ይሆናል። በምርጫ የተሳተፉትን የባልደራስ አመራሮች እስር ቤት አጉሮ፣ ውጭ ሆኖ የተሳተፈውን አጋራለሁ ማለት ለጊዜያዊ ድጋፍ ማግኛ ነው የሚሆነው። የምር፣ የመርህ ከሆነ የባልደራስ አመራሮች ሊፈቱ ይገባል። ድሮም ተፈትተው ነበር ምርጫውን መሳተፍ የነበረባቸው።

3) መንግስት ከተሞችን በሮኬት ከደበደበው፣ ሰራዊቱን በተኛበት ካረደው፣ ሀገርን ለመበተን እየሰራ ካለው፣ በምክር ቤት ከተፈረጀውን ትህነግ ጋር እደራደራለሁ ብሏል። በአንፃሩ በምርጫ ሂደት አምነው የተሳተፉ፣ ሲሸነፉም “እናመሰግናለን” ያሉ የዲሞክራሲ ቀንዲሎችን በእስር አጉሯል። ይህ አካሄድ ክፉ ባህል ነው የሚያስለምደው። በቀል ካልሆነ በስተቀር እነዚህን ለሀገር አሳቢዎች እስር ቤት የሚያቆያቸው ጉዳይ የለም። ጥላቻ፣ መርህ አልባነት፣ መልካምነታቸውን መጥላት ከልሆነ በስተቀር እነዚህን ተምሳሌቶች እስር ቤት ማቆየት ለማንም አይጠቅምም።

ከእነ በርካታ ችግሩ የተካሄደን ምርጫ እስር ቤት ሆኖ የተሳተፈን አጉረህ፣ ጫካ ሆኖ ሀገር አፈርሳለሁ የሚል ጋር ሰላም እፈጥራለሁ ስትል ለሕዝብ እየነገርከው ያለኸው መሳርያ አንስቶ ለሚታገል ቦታ እንደምትሰጥ ነው። የመሳርያ አቅም ከሌለህ፣ የፈለገ ለሀገር ቀናኢ ብትሆን ጉዳዬ አይደለም ነው እያልከው ያለኸው። ሰራዊት እየከዳ፣ ሕዝብ እያረደ፣ ከውጭ ጠላት ጋር እየተሞዳሞደ ያለው ይመቸኛል፣ ከእሱ ጋር ነው የምግባባው ነው እያልክ ያለኸው። ምርጫውን ከእነ ችግሩ ችሎ የተሳተፈውን እንቀዋለሁ፣ እውቅና አልሰጠውም፣ አላበረታታም ነው እያልክ ያለኸው። ለዲሞክራሲ ከሚታትር ይልቅ ሽብርን መንገዱ ያደረገውን እመርጣለሁ እያልክ ነው። ይህ መንገድ አጥፊ ነው። ለኢትዮጵያ የሚበጁት እስር ቤት ሆነው በምርጫ የተሳተፉት፣ የመረጣቸውንም ያልመረጣቸውንም ያመሰገኑት፣ ለሂደቱ፣ ለሀገራቸው ሲሉ በሂደቱ የገጠመውን ሁሉ ከሀገር አይበልጥም ብለው ያለፉት ናቸው። እነ እስክንድር በማናጆነት ስለመታሰረቸው እነ ጃዋር ሳይቀር በፍርድ ቤት ተናግረዋል። ሕዝብ ቀርቶ ተቀናቃኞቻቸው፣ በብዙ አመለካከት የማይስማሟቸው፣ በእኛ ምክንያት ነው የታሰሩት ብለው ታዝበዋል። የባልደራስ አመራሮች በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል። መፈታተቸው ለሀገር ይጠቅማል። ብዙ ያስተምራል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከኦህዴድ ብልጽግና አስር ክፍለጦር፣ የምሁራን አንድ ብዕር!!! መብረቅ ጋዜጠኞች፣ ቌጥኝ ምሁራን!!! ወርካ ፍለጋ!!!

 

 

2 Comments

  1. በማንኛውም መልክ በወንጀል ተጠርጥሮ እስር ቤት ያለ ሰው አገር ለመምራት እስር ቤት እያለ ጠበቃ ይዞ እየተከራከረ የፍርድ ውሳኔ እየጠበቀ ሀገረ ለመመራት የምርጫ ውድድር እንዲያደርግ መፈቀዱ መንግሥትን ያስመሰግናል እንጂ አያስወቅስም። ለመሆኑ በየትኛው ሀገር ነው በወንጀል ተጥርጥሮ በእስር ላለ ስው ሀገር እንዲመራ ወይም እንዲያስተዳድር የምርጫ ውድድር የተፈቀደበት የት ነው? ህዝቡ የሚበጀውን መርጦአል የህዝብ ድምጽም መከበር አለበት ።የህዝብን ድምጽ እና መበት ነፍጎ እስክንድር የባልደራስ አመራሮች ይፈቱ ብሎ መንጨርጨሩ በአሁኑ ሰዓት ዋጋ የለውም።ደግሞም በልደራስ የሚባለው በተወሰን አካባቢ በምርጫ ውድድሩ ተሳትፎአል ሆኖም ምን ያህል እንዳሸነፈ ባላውቅም የወደቀ ይመስለኛል።ከሆነም ራሱን ማጥናት አለበት እላለሁ።

  2. ለህሊናና ለአነት መቆም ዛሬም ዋጋ ያስከፍላል።እነእስክንድር ዋጋ የሚከፍሉትም ለዚህ ነው።ፍትህ ለሂሊና ሠዎች አሁኑኑ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share