ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ሰኞ፣ ኅዳር 21፣ ፪ሺ ፲፫ ዓ.ም. (Nov. 30, 2020) ቅጽ ፯ ቁጥር ፳፫
ዐማራ ላይ አሁንም አደጋው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ያልተደራጀና ያልታጠቀ ሕዝብ ለጥቃት ስለመጋለጡ ለዐማራ ሕዝብ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል። ምክንያቱም በወያኔ ማኒፌስቶና በኢህአዴግ ወያኔ አገዛዝ ለ30 ዓመት ጥቃት ሲፈፀምበት ኖሯል። ለውጥ ተብየው ከመጣ በኋላ ወያኔን ገለል በማድረግ በወያኔ ማኒፌስቶ የሚተዳደረው የብልፅግና ኦሮሙማ አገዛዝም በዐማራ ሕዝብ ላይ ጥቃቱን አጠናክሮ ጭፍጨፋውና መፈናቀሉ ተባብሶ ቀጥሏል። በዐማራ ላይ የሚፈፅመው ጭፍጨፋ፣ ከቤትና ንብረት ማፈናቀል፣ ከተማ የማውደምና ዐማራን የማፅዳቱ የጥፋት ተልዕኮዎች ተግባር መንግስታዊ መዋቅር ሰራሽና ወታደራዊ ድጋፍ ያለው የዘር ማጥፋትና ማፅዳት ወንጀል ለመሆኑ አሌ አይባልም። ይህንንም የዘር ማጥፋትና ማፅዳት ወንጀል ለአንዴና ለሁሌዬ ለማስቆም የግድ በበለጠ መደራጀት፣ መታጠቅ፣ መመከት፣ በአጭሩ ሊያጠፋ በመጣ ጠላት ላይ ክንድ ማንሳት የወቅቱ ጥሪ ነው።
ስልጣን በተቆጣጠረው የኢህአዴግ መራሽ ብልፅግናና ከስልጣን በተወገደው ትሕነግ (ወያኔ) ኢህአዴግ መካከል የተነሳው እሰጥ አገባ ወደከፋ ደረጃ ተሸጋገረ። የፋሽስቱ ወያኔ ታጣቂ ኃይሎች በሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ዘግናኝ ጥቃት ፈፀሙ፤ የሰሜን ዕዝ ወታደሮችን ገደሉ፤ ልብሳቸውን አውልቀው፤ አስከሬናቸውን አንድ ላይ ከምረው መኪና ነዱበት፤ ወያኔዎች በዚህ አፀያፊ ተግባራቸውም ሌሊቱን ሲጨፍሩ አደሩ፤ የሟቾቹ አስከሬን አሞራና ጅብ እየበላው ነው ሲል አምልጠው በሕይወት የተረፉት የመከላከያ ሠራዊ አባላት የድረሱልኝ ጥሪ አቀረቡ። ወያኔና ግብረአበሮቹም በማይካድራ ከ700 በላይ ዐማራ በግፍ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲጨፈጭፉ፣ ሕግና መንግሥት ወዳድ የሆነው የዐማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ የአገሩን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር፣ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ የመከላከያ ሠራዊትን ከመታደጉም በላይ በግፈኛወና አረመኔው ወያኔ ቅኝ አገዛዝ ሥር ለ30 ዓመታት ሲጨፈጨፍ፣ ሲፈናቀልና የምድር ሲዖል ሲያይ የነበረውን የወልቃይት፣ የጠለምት እና የራያ ሕዝብ እንደማይካድራ ከመጨፍጨፉ በፊት ደርሶ ነፃ አውጥቷል።
ወያኔ እንዴት እንደተደመሰሰ በተደጋጋሚ ሲነግረን የነበረው የብልፅግና መንግሥት፣ ዛሬ ደግሞ ወያኔ ነፋስ ላይ እንደተበተነ ዱቄት ነው ባለበት አፉ፣ ወደ ጦርነት ከገባ ከ 7 ወራት በኋላ የተናጠል የተኩስ ማቆም እርምጃ በመውሰድ የመከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ እንደወጣና ወያኔ መቀሌን መቆጣጠሩን አበሰረን። የአገር መከላከላከያ ሠራዊት በመንግሥት ትእዛዝ ትግራይን ለወያኔ አስረክቦ ሲወጣ በትግራይ ያለው ሰላማዊ ሕዝብ፣ የመንግሥት ሰራተኛና በተለይም ከተለያዩ ክልሎች የመጡ በትግራይ በሚገኙ የተለያየ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ጉዳይ እንደ መንግሥት በጭራሽ አላሳሰበውም።
የወያኔው ጀኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳይና አፈቀላጤው ጌታቸው ረዳ ጠላቴ በሚሉት የዐማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን በማለት እየዛቱ ነው። እንደ ወያኔ አባባል ከሆነ አስፈላጊ ከሆነ ተከዜን ተሻግረው ዐማራን እንደሚያጠቁ አሳውቀዋል። ስሙን የሚቀያይረውና ለዐማራ መከራ ተጠያቂ የሆነው ብአዴን/አዴፓ/ዐማራ ብልፅግናም ወደ ሞቀበት ዘንጠፍ እንደሚል እሙን ነው። ብአዴን/አዴፓ ትናንት ዐማራ በየእለቱ በጅምላ ሲታረድ እያየ፣ ዐማራን በመናቅና በማንአለብኝነት ለሽመልስ አብዲሳና ለአሻድሊ ሀሰን ካባ እንዳለበሰው ሁሉ ነገ ለወያኔ አድሮ በድጋሚ ዐማራን ሊሸጥ እንደሚችል ታሪካቸው ምስክር ነው።
በትግራይ ወያኔና በአብይ መራሹ የኦሮሙማ መንግሥት ያለው ቅራኔ የሥልጣን ግብግብ እንጂ ስትራቴጅያዊ ግባቸው አንድ ነው። ይህም ዐማራን በጠላትነት ያስቀመጠውንና ዜግነትን የገሰሰውን የአፓርታይድ ሕገ መንግሥትና የአገዛዝ መዋቅርን ማስቀጠል ነው። ይኸም በጋራ እየገፉት ያለው ኢትዮጵያን የማፍረስ ሂደት ነው። ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚጎዳ ቢሆንም በተለይ ዐማራውን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለዋል። በአፉ ኢትዮጵያ አትፈርስም ማለት የማይቦዝነው አብይ አህመድ አሊ ባለፉት አጭር 3 ዓመታት ግን በተግባር ቁልጭ አድርጎ ያሳየን ሀቅ ቢኖር ነውጥን የመንግሥት መሳርያ አድርጎ ዐማራውን በመላው ሀገሪቱ የሚወርበት፣ የሚገልበትና የሚያሳድድበት ዋናው ግብ የኢትዮጵያ ነገዶችን ኅልውናና ማንነትን አጥፍቶ፤ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ታላቋ ኦሮሚያን የመፍጠሩ ትልቅ የኦሮሙማ ሕልም አካል ነው።
ታጋሹና አስተዋዩ የዐማራ ሕዝብ ሆይ! “የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም” እንዲሉ በራስህ በልጆችህ እንጅ በኢሕአዴግ/ብልፅግና እንዳትተማመን፤ በተደጋጋሚ ክህደት ተፈፅሞብሀል። ስለዚህ በአምላክህ ቸርነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እየተናበብክ በቆራጥነትና በፅናት የተደገሰልህን መከራ ተቋቁመህ ኅልውናህን እና ማንነትህን የማስቀጠል ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት ወድቆብሀል። ስለሆነም ሁሉም ዐማራ ፋኖ በመሆን ከዐማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር በመናበብ፤ በጋራ በመቆም በማንኛውም ሰዓት፣ ከየትኛውም አካባቢ ሊመጣ የሚችል ጥቃት እንደሚኖር ተረድተህ፤ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ፤ ራስህን ከፈፅሞ ጥቃት ለመከላከልና ለመመከት በተጠናከረና በተደራጀ መልክ አመራር የሚሰጥ ሕዝባዊ ትግሉ በሂደት የሚወልደው መሪ ድርጅት በመፍጠር ዐማራው ይህን አስከፊ ዘመን በድል አድራጊነት እንዲሻገር እንዲሆ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ከታላቅ ሕዝባዊ አደራ ጋር ጥሪውን ያስተላልፋል።
አንድ ዐማራ ለሁሉም ዐማራ፤ ሁሉም ዐማራ ለዐንድ ዐማራ!
ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!