ማተቡን ከቆረጠ (ዘ-ጌርሣም)

ክሯን ሳይሆን
ቃሉንና የማይታየውን
በድምፅ የማይሰማውን
በእጅ የማይዳሰስውን
ህሊና ብቻ የሚያውቀውን
ለሰው ልጅ የተሰጠውን
ግዑዙን ቃል ነው
ማተብ መታመን ነው የምንለው
ማንም ማተቡን ከቆረጠ
ከሃዲነቱን በአደባባይ ከገለጠ
በራሱ ባልሆነ ለመክበር ቋምጦ
ሰብዕናውን ለነዋይ ሽጦ
ደፋ ቀና ከሚል
ቢያውቅ መልካም ነበር ቢያስተውል
ይህን መረዳት አቅቶት በጥፋቱ ከቀጠለ
አይሻልም ከቆሻሻ ከተጣለ
ሁለንተናውም ይሟጠጣል
ከአራዊት ዘር ይመደባል
የሰው ልጅ ክቡር መሆኑ ተረስቶ
በጊዜ ዋቢነት ተዳኝቶ
እርቃኑን ይቀራል ተራቁቶ
ድሮ በደጋጎቹ ዘመን
ሰው ይረከብ ነበር አደራን
በሕይወት እስካለ የድርሻውን
ምላሱን ላያጥፍ ላይከዳ ህሊናውን
ያኔ ማተብ ሲባል
ፊርማ ሳይኖረው በቃል
የአብሮነት ህግ ነበር
እምነትን በቃል የሚያስከብር
ቃል በሰማይ ቃል በምድር አስብሎ
ማተቡን በልብ ዳኝነት አስምሎ
ይረከብ ነበር አደራውን
በሕይወት እስካለ የድርሻውን
አይቀሬው ሞት እንኳን ሲመጣ
ቃሉን ለማጠፍ ሳይቃጣ
ያወርስ ነበር አደራውን
በቃል የተረከበውን
ለባለቤቱ እንዲያስረክብ
እምነት በቃሏ እንድታብብ
አደራ ተረካቢም በበኩሉ
ይታመን ነበር ለቃሉ
ቃል እምነት መሆኗን
ይረዳ ነበር ሐቁን
በዚህ መልኩ ትውልድ ይቀጥል ነበር
ዛሬ እንዲህ ላይኖር
ተረት ተረት ሆኖ ሊቀር
ማንም ማተቡን ከቆረጠ
ከሃዲነቱን ከገለጠ
በራሱ ባልሆነ ቋምጦ
ሰብዕናውን ለነዋይ ሽጦ
ደፋ ቀና ከሚል
ይነገረው እንዲያስተውል
መታመንን ቃሌ ነው ይበል
ትውልድም በሕግጋቱ ይቀጥል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.