ዋሽንግተን ዲሲ
ሰሜን አሜሪካ
ግንቦት 4, 2013 ዓ/ም
በሰሞኑ የኢትዬጵያ ሳታላይት ቴሌቭዥን ( ኢሳት ) በማህበራዊ ሚዲያ ዙሪያ ያስተላለፈውን ዘገባ አስመልክቶ ከኢትዬጵያ አገር አድን ግብረኃይ የተሰጠ መግለጫ!
የነቃ፣ መረጃ ያለውና የተደራጀ ማህበረሰብ ለአምባገነንነት አይመችም፡፡ በመሆኑም አምባገነን መንግስታት በስልጣን ኮርቻዎቻቸው ለመቀጠል፣ የሚገዙትን ሕዝብ ማዳከም ፣ መብቱን እንዳይጠይቅና መረጃ እንዳያገኝ ማድረግ ዋና መሳሪያዎቻቸው ናቸው፡፡
ህወሃት የነጻ ፕሬስ ጠላት እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡ የመንግስት ሜዲያዎች፣ ገዢዎች ሕዝቡ እንዲሰማ የሚፈልጉትን እንጂ ፣ ሕዝቡ መስማት ያለበትን አልነበረም የሚዘግቡለት፡፡ የተለያዩ የኦንልያን ሜዲያዎች ብሎክ ይደረጉ ነበር፡፡ እንደ ኢሳት (የኢትዮጵያ ሳይተላይት ቴሌቪዥን) ያሉ፣ ከውጭ በሳተላይት መረጃዎችን ለሕዝብ የሚያቀርቡ ተቋማት፣ በህወሃት ዘንድ እንደ ጠላት ነበር የሚቆጠሩት፡፡ እነ ኢሳትን ከአየር ላይ ለማውረድ ያልተደረገ ጥረት፣ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም፡፡ የኢሳት ስርጭቶችን ለማስተጓጎል ጃሚንግ ሲጠቀሙ እንደነበረም የሚታወስ ነው፡፡
ኢሳት በወቅቱ እስከነ ድክመቱ ፣ ኢትዮጵያዉያን ነጻና አስፈላጊ መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ዙሪያ ትልቅ ሚና የተጫወተ ተቋም ነው፡፡ ለዚህም ነው ከአስር አመታት በላይ ኢትዮጵያዊያን ኢሳትን ሲደግፉና ሲረዱ የነበሩት፡፡
ኢሳት ብቻ አይደለም፣ ሶሻል ሜዲያ የህወሃት አገዛዝንና ግፎችን በማጋለጥ፣ ሕዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ዙሪያ የራሱ የሆነ ጉልህና ቁልፍ ሚና እንደነበረው፣ አሁንም እንዳለው ለማወቅ ረጅም ረቀት መሄድ አያስፈልግም፡፡
በሕዝብ ትግል ህወሃት ከአራት ኪሎ ተወገዶ፣ ሌሎች ፣ እራሳቸውን የ”ለውጥ ኃይል ነን” ብለው የሚጠሩ በቦታው ተተክተዋል፡፡
ሆኖም ግን አዲሶቹ ገዢዎች ከቀድሞ ህወሃቶች የተሻሉ ሆነው አልተገኙም፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙዎች የፍትህ፣ የሰላምና የዜጎች ደህንነት ጉዳይ ግድ ብሏቸው፣ አሁን በስልጣን ላይ ያሉትን ገዢዎች መጠየቅ፣ ቻሌንጅ ማድረግ ብሎም መቃወም የደረሱበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ትላንት በሕወሃት ካድሬዎች ኢላማ ውስጥ ገብተው ፣ ጃም ሲደረጉ፣ ከአየር ላይ እንዲወርዱ ጫና ሲፈጽምባቸው የነበሩ ኢሳቶች፣ ትላንት በህወሃት ጊዜ ሲጠይቋቸው የነበሩ፣ የሰላም የፍትህና የዜጎች በአገራቸው የመኖር ጥያቄዎች፣ አሁን እንዳልተመለሱ እያወቁ፣ አሁንም ዜጎች በዉሸትና በፈጠራ ክስ እየታሰሩ ባለበት ሁኔታ፣ የሕዝብ ጆሮና አይን ከመሆን የገዢው ፓርቲ የኦህዴድ/ብልጽግና አፈቀላጤዎች መሆናቸው እጅግ በጣም አሳዝኖናል፡፡
ያ ብቻ አይደለም ፣ አሁን እነርሱ ተገልብጠው፣ የሜዲያ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወሰድና ሶሻል ሜዲያ በኢትዮጵያ እስከ ምርጫው እንዲታገድ ሲጠይቁ መስማታችን እጅግ በጣም አስደንግጦናል፡፡ በዚህ ልክ በውጭ አገር ያሉ የኢሳት ጋዜጠኞች፣ የትላንቶቹን እነ አይጋ ፎረምን በመተካት፣ ከጋዜጠኝነት ስነ መግባር እጅግ ማፈንገጣቸው፣ተቋሙ ለረጅም አመታት ያበረከተውን ትልቅ አስተዋጾ ገድል ውስጥ የሚከት ብቻ ሳይሆን ኢሳትን ለአስርተ አመታት ሲደገፉና ሲረዱ በነበሩትና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ትልቅ ክህደት ነው፡፡
አሁንም ኢሳት እንደ ተቋም ለዚህ ድርጊቱ በአስቸኳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅ እያሳሰብን፣ ፌስቡክ እንዲዘጋ፣ ቲቪ ጣቢያዎች እንዲታገዱ በይፋ ጥሪ ያቀረቡ ጋዜጠኞችን በማሰናበት አስቸኳይ መስረታዊ እርማት እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡
ኢሳት የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት በሚጎዳ መልኩ እያደረገ ያለው ድርጅቱን የበለጠ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለውና በታሪክም ተጠያቂ እንደሚያደርገው ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
የኢትዮጵያ አገር አንድ ግብረ ኃይል
” ኢትዬጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር ”
የኢትዮጵያ አገር አድን ግብረኃይል በሰሜን አሜሪካ
——————————————————————————————————–
Email- [email protected]