አምጣ ወልዳቸው ዘጠኝ ወር አርግዛ፣
ልሳ አሳድጋቸው ጡቶቿን አጥብታ፣
ጥጆቿ ለቅርጫ በካራ አረዷታ!
ተከብት ባህሪ ከተፈጥሮ ወጥተው፣
የጅብ አቀንጣጤ መንጋጋን አብቅለው፣
ገነጣጥለው በሏት ልጆቿ አውሬ ሆነው!
ተጅብ ተጥንብ አንሳ ተጆፌ ተማክረው፣
አንጀቷን አወጡት ሆድ እቃ ዘክዝከው፣
በወላዲተ አምላክ ተገላዋ አንሳቸው!
ኮርማ አሳዳጊዋ የወይፈኖች እናት፣
ግዜ ጣላትና የጥጃ አውሬ በላት፡፡
እንደ ፍየል መንጋ እየለፈለፉ፣
እንደ ሜዳ አህያ እየተራገጡ፣
እንደ ኖህም ቁራ ከንፈው እየካዱ፣
እርግቧን ላም በዓለም እርኩም አስመሰሉ፡፡
እባክህ አምላክ ሆይ እምቧ ስትል ስማት፣
ተጡት ነካሽ ጥጃ በኃይልህ ገላግላት!
እባክህ መለኮት ላሚቱን ታደጋት፣
እናት የሚያስከብር ኮርማ ፍጠርላት!
እባክህ እግዚአብሔር ላሚቱን ተመልከት፣
ሥጋዋን ዘንችረው ጥጆቿ ሲበሏት፡፡
በላይነህ አባተ abatebelai@yahoo.com
መጋቢት ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ. ም.