ዐብይ አህመድ ባማራ ሕዝብና ባማራ ልዩ ኃይል ላይ የከፈተው የማጠልሸት ዘመቻና ምክኒያቱ – መስፍን አረጋ

‹‹ያማራ ብሔርተኝነት ለኢትዮጵያ ስጋት ነው‹‹ (ዐብይ አህመድ፣ በድብቅ ከተቀረጸ ቪዲዮ)

”Faild coup in #Ethiopia’s Amhara state was an attempt by ethnic nationalists to restore Amhara hegemony over all of Ethiopia that existed for several centuries prior to 1991.  That dream is now permanently dead.” (ባማራ ክልል ውስጥ የተካሄደው ያልተሳካው የመንግሥት ግልበጣ (ወያኔ ጦቢያን እስከተቆጣጠረበት) እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ለምዕተ ዓመታት ሰፍኖ የነበረውን ያማራ የበላይነት ለማስመለስ ያማራ ብሔርተኞች ያደረጉት ሙከራ ነበር፡፡  ይህ ህልማቸው ለዘለዓለም አሸለበ፡፡) ኸርማን ኮኸን (Herman Cohen) በትዊተር (twitter)

The numerous tribes who inhabit the Ethiopian state are being forcibly kept from European colonialism by Abyssinian rulers whose aim is to act as champions of all black people so as to attack and destroy Western culture. (የጦቢያን አያሌ ብሔረሰቦች የነጭ ባርያ የመሆን ምርጫቸውን የነፈጓቸው፣ ዓላማቸው በነጭ የባህል  (እና የሐይማኖት) መቃብር ላይ የጥቁርን ልዕልና መገንባት የሆነው የሐበሻ መሪወች ናቸው፡፡)  Roman Prochaska (Abyssinia: The Powder Barrel, Vienna, 1935)

ዐብይ አህመድ ባማራ ልዩ ኃይል ላይ በዚሁ አስታኮ ደግሞ  በጠቅላላው ባማራ ሕዝብ  ላይ የማያቋርጥ የስም የማጠልሸት (vilification) ዘመቻ የከፈተው የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ስልጣን ባማራ ፖለቲከኞች ወሳኝ ድጋፍ በጁ ካስገባ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነው፡፡

በመጀመርያ ያማራ ብሔርተኝነት የኢትዮጵያ ስጋት ነው ሲል በድብቅ በተቀረጸ ቪዲዮ ተደመጠ፡፡  ይህ የአማራ ብሔርተኝነት ግን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በዙርያው በማሰባሰብ የአውሮጳ ቅኝ ገዥወችን አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያረጋገጠ፣ ቅኝ ገዥወችን ካፍሪቃ አህጉር ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ ለማስወጣት በር የከፈተ፣ በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች የማንነት ኩራት (black pride) እና የጥቁር ብሔርተኝነት (black nationalism) መሠረት የሆነ፣ ያማራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ጦቢያውያን ጦቢያዊ ብሔርተኝነት ነው፡፡  የኢትዮጵያ ስጋቶች ጎጠኝነት የተጠናወታቸው አግላዮቹ የኦሮሞና የትግሬ ብሔርተኝነቶች እንጅ፣ ጦቢያዊነትን የሚያስቀድመው አሳታፊው ያማራ (የጦቢያ) ብሔርተኝነት አይደለም፡፡

ቀጥሎ ደግሞ ያማራ ክልል መሠረተ ልማት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እጅግ በከፋ ሁኔታ ቆርቋዛ የሆነው፣ የወያኔ መንግሥት ሥራየ ብሎ ይከተለው በነበረው ፀራማራ ፖሊሲ ሳቢያ ሳይሆን፣ ክልሉ ያለችውን ሐብት በልዩ ኃይሉ ላይ ስለሚያጠፋ ነው የሚል የማይመስል ነገር ተናገረ፡፡  ይህን የተናገረው ደግሞ ያማራ ክልል ልዩ ኃይል (ባንድ ዙር ብቻ የሰለጠኑ) ጥቂት ሺ ወታደሮችን ብቻ ያቀፈ አነስተኛ ኃይል መሆኑ ሳይጠፋውና፣ የሱ የራሱ የሆነው የኦሮምያ ክልል ግን ያማራ ክልልን ልዩ ኃይል ካስር እጥፍ በላይ የሚበልጥ ልዩ ኃይል (ከሠላሳ በሚበልጡ ዙሮች) ለማሰልጠንና ለማስታጠቅ በመቶ ሚሊዮኖች (ምናልባትም በቢሊዮኖች) የሚቆጠር ያሜሪቃ ዶላር ማፍሰሱን እያወቀ ነው፡፡  ይህን ባለ በሳምንቱ ደግሞ፣ እራሱ ዐብይ አህመድ ዋናው ተጠርጣሪ በሆነበት እጀግ አጠራጣሪ ክስተት፣ ያማራ ክልል ዋና ዋና ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች፣ ሥራየ ብሎ የተቀወጠ በሚመስል ከጥቂት ሰዓታት ባልዘለገ ውስን ቀውጥ (controlled chaos) ተረሽነው አለቁ፡፡  ያማራ ክልል ዋና ዋና አመራሮች መረሸናቸውን እንዳረጋገጠ ደግሞ፣ ባሜሪቃ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያፍሪካ ወንበር ኃላፊ የነበረው፣ የሮማን ፕሮቻዝካን (Roman Prochaska) ፀራማራ አጀንዳ አራማጅ እንደሆነ የሚገመተው፣ በወያኔ አፍቃሪነቱ የሚታወቀው፣ ፀራማራው ኸርማን ኮኸን (Herman Cohen) በርሸናው መደሰቱን በሚያሳብቅበት ሁኔታ ያማራ የበላይነት ሙቶ ተቀበረ (Amhara hegemony … is now permanetly dead) በማለት በትዊተር (twitter) ገጹ ተሸቀዳድሞ አወጀ፡፡

በመጨረሻ ደግሞ በራሱ ባብይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ፣ ያማራ ልዩ ኃይል በራሱ ባማራ ክልል ውስጥ ዘር ማጽዳት (ethnic cleansing) ፈጽሟል የሚል ውንጀላ መጋቢት 6(2013) ላይ በመግለጫ መልክ በማውጣት ባማራ ልዩ ኃይልና ባማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተውን የማጠልሸት ዘመቻ ከፍተኛው ደረጃ ላይ አደረሰው፡፡  በማግስቱ ደግሞ ይሄው የኦነጋውያን የውንጀላ መግለጫ ባብይ አህመድ የይስሙላ ፓርላማ ውስጥ ቃል በቃል እንዲነበብና ለመላው የኦትዮጵያ ሕዘብ በቀጥታ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡

ያማራ ሕዝብ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር የተጋባ፣ የተዋለደና የተዛመደ፣ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን በላይ አቃፊና ደጋፊ የሆነ፣ ሲርበው የማይቧግት ሲጠግብ የማይተብት፣ ሁሉን በልኩ የሚይዝ ሆደ ሰፊ ሕዝብ ነው፡፡  ያማራ ልዩ ኃይል ደግሞ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ ሊሳተፍበት የሚችልበት፣ በራሷ በኢትዮጵያ አምሳል የተዋቀረ ሕብረ ብሔራዊ ኃይል ነው፡፡ ሕብረ ብሔራዊነቱ ደግሞ ጠቅላይ አዛዡ ራሱ አብይ አህመድ፣ ኢታማዦር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ፣ አየር ኃይል አዛዡ ይልማ መርዳሳ የሆኑበት፣ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በኦሮሞወች ብቻ የሚመራው፣ በስሙ የኦትዮጵያ በግብሩ ግን የኦሮሙማ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት ካለው ሕብረ ብሔራዊነት እጅጉን የላቀ ነው፡፡  በዘረኝነት ለመወቀስና ለመከሰስ ከሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች የመጨረሻው የሚሆነው ያማራ ክልል ልዩ ኃይል ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህዝብ መስዋዕትነት -በወያኔ መስመር እንዳይስት - ይገረም አለሙ

ጎሰኝነት ላማራ ሕዝብ ባዕድ ነው፡፡  ይልቁንም ደግሞ ያማራን ሕዝብ የጎሰኞች ሰለባ ያደረገው ትልቁ ድክመቱ ጎሰኞ ጭራቆች እንደ አሸን በፈሉባት ጦቢያ ውስጥ በበቂ ደረጃ ጎሰኛ አለመሆኑና በብሔሩ አለመደራጀቱ ነው፡፡  በመጠኑም ቢሆን የተደራጀን አማራ ማንም ጎሰኛ ሊያጠቃው ቀርቶ ሊደፍረው አይችልም፡፡  ለዚህ ማረጋገጫ ደግሞ በሮኬት፣ በታንክና ባዳፍኔ ይታገዝ የነበረው የወያኔ ጦር፣ ነፍስ ወከፍ ነፍጥ ባነፈጡ ነፍጠኞች ድባቅ መመታቱን መጥቀስ ብቻ በቂ ነው፡፡  ኦሮሙማውያን አጥብቀው የሚፈሩት ደግሞ ይህን የአማራን እምቅ ነፍጠኝነት ነው፡፡  እስካፍንጫቸው ቢታጠቁም፣ የመሣርያ ጋጋታ ለወያኔም እንዳልጠቀመው ባይናቸው በብሌኑ አይተዋል፡፡  ያላቸው አንድ አማራጭ አማራን በሌላ ሶስተኛ ወገን ማስመታት ብቻ ነው፡፡  ያማራን ልዩ ኃይልና ያማራን ሕዝብ በዘር ማጽደት ወንጀል አስወንጅው በምዕራባውያን ቦምቦች ሊያስቀጠቅጡት የተነሳሱበትም ምክኒያት ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡

ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት፣ ያማራ ሕዝብ አስገድዶ መድፈርንና መሀን ማድረግን (rape and forced sterlization) የሚጨምር፣ ባያሌ መረጃወች የተደገፈና ለሰላሳ ዓመታት የዘለቀ መጠነ ሰፊና እጅግ አስከፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞበታል፡፡  ይህን ወንጀል የፈጸመበት ደግሞ ዋናውና መሠረታዊው ጠላቱ ያማራ ሕዝብ መሆኑን በማንፌስቶው ላይ በይፋ በገለጸው በጎሰኛው የወያኔ መንግሥት ነበር፡፡

ባማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እጅግ አስከፊ እንደነበር ለመመስከር ደግሞ ከወልቃይትና ራያ የበለጠ ምስክር የለም፡፡  በነዚህ ቦታወች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሕዝቡን አሰፋፈር (demographis) በከፍተኛ ደረጃ ስለቀየረው (እነዚህን የአማራ ቦታወች በግድ ወደ ትግራይ የቀላቀለው ወያኔ ከተወገደ በኃላ እንኳን) የትግራይ ብሔርተኞች የሕዝብ ብዛትን እየጣቀሱ እነዚህን ቦታወች የምዕራብና የደቡብ ትግራይ ክፍሎች ናቸው ማለታቸውን ቀጥለውበታል፡፡

የዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ደግሞ ያማራን ሰቆቃ መስቀጠል ብቻ ሳይሆን እጅግ የከፋ አደረገው፡፡  ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ፣ የራሱ ያብይ አህመድ ክልል በሆነው በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ በሺወች (ምናልባትም ባስር ሺወች) የሚቆጠሩ አማሮች በሚዘገንን ሁኔታ እንደ ከብት ታርደዋል፣  በመቶሺወች (ምናልባትም በሚሊዮኖች) የሚቆጠሩ አማሮች ደግሞ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ፣ ያፈሩትን ሐብትና ንብረት ባለበት ጥለው እየተባረሩ ከክልሉ ሸሽተው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡  ይህን ሁሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚፈጽመው ደግሞ ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር እየተመጋገበ ተቀናጅቶ የሚንቀሳቀሰው፣ ኤርትራ በነበረ ጊዜ አብይ አህመድ መረጃ ያቀብለው የነበረው፣ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ደግሞ ከነ ሙሉ ትጥቁ እንዲገባ የተደረገው፣ የኦሮሙማ ወታደራዊ ክንፍ የሆነው፣ በዳቦ ስሙ ኦነግ ሸኔ የሚባለው ኦነግ ነው፡፡

ዐብይ አህመድ ባንድም በሌላም መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሆነ ደረስ፣  ጠቅላይ ሚንስትርነቱ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን አማራን ጨምሮ ለሁሉም ጦቢያውያን ነው፣ ጠቅላይ የተባለው ሁሉንም እንዲያጠቃልል ነውና፡፡  በመሆኑም  በኦሮምያ፣ በመተከልና በሲዳማ ክልሎች ባማራ ሕዝብ ላይ በሱ የስልጣን ዘመን ለተፈጸሙትና እየተፈጸሙ ላሉት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በቀጥታና በተዛዋሪ ተጠያቂ ነው፡፡  ለተፈጸሙትና እየተፈጸሙ ላሉት ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት ሊፈጸሙ ለታሰቡትም ተጠያቂ ነው፣ ሳይፈጸሙ በፊት አስፈላጊውን ጥንቃቄና ርምጃ አስቀድሞ እንዲወስድ ይጠበቅበታልና፡፡

ዐብይ አህመድ ግን ያማራን ጩኸት ቀምቶ እራሱ ገርፎ ራሱ እየጮኸ፣ አማሮች በኦነግ በተጨፈጨፉበት አጣየ ላይ ኦሮሞወች ባማራ ልዩ ኃይል ተጨፈጨፉ አስብሎ ያማራን ልዩ ኃይል በዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስወንጀል ተነሳሳ፡፡  ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጣ፣ የኔ ነው የሚለውን ኦሮሞን ጨምሮ ከማንም ሕዝብ በላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የደገፈው ያማራ ሕዝብ ሆኖ ሳለ፣  ያማራ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የደገፈው ደግሞ እሱ ያማራ ብሔርተኝነት የሚለውን የጦቢያን ብሔርተኝነት ባሞገሰበት ዲስኩሩ ብቻ ሆኖ ሳለ፣ ያማራን ሕዝብና ያማራን (የጦቢያን) ብሔርተኝነት እንደ እናቱ ገዳይ ነክሶ የያዘበት ምክኒያት ምንድን ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ገዳይ ደስ አይበልህ፤ ሟችም ብዙ አይክፋህ - ግርማ በላይ

ዐብይ አህመድ የጭቆናን ምንነት በቅጡ በማያውቅበት እድሜው “ያማራ ጨቋኞችን” ለመታገል ጫካ ገብቶ የወያኔን ጡት እየጠባ ባማራ ጥላቻ ተመርዞና ተሰቅዞ ያደገ፣ አማራዊ ናት የሚላትን ጦቢያን አፈራርሶ በሷ መቃብር ላይ የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) ለመመሥረት ቆርጦ የተነሳ አክራሪ ኦነጋዊ ነው፡፡  በሌላ አነጋገር ዐብይ አህመድ ማለት፣ በቀንደኛው ኦነጋዊ በለማ መገርሳ አማካኝነት ኦነጋውያን ቆጥረው ያስረከቡትን ጥያቄወች በመመለስ የኦሮሙማን አጀንዳ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚያስፈጽም የዘመናችን ሉባ ነው፡፡  እሱ ራሱ በግልጽ እንደሚናገረው ደግሞ ራሱን የሚመለከተው እንደ ሉባ (ንጉሥ) ነው፡፡  የለየለት ፀራማራና ፀረጦቢያ ለመሆኑ ደግሞ ከዲስኩሮቹ ጋር ገማዘንጋዊ ተቀራኒ (diametrically opposite) የሆኑት ተግባሮቹ ሊስተባበሉ የማይችሉ ማረጋገጫወች ናቸው፡፡  ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ፣ አፉና ምግባሩ ሓራምባና ቆቦ፡፡

ዐብይ አህመድ ጦቢያን አፈራርሶ የኦሮሞ አጼጌ በመመሥረት የኦሮሙማ ሕልሙን ማሳካት የሚችለው ግን ባንድ በኩል ወያኔን በሌላ በኩል ደግሞ ያማራን ልዩ ኃይል ተራ በተራ ድባቅ ከመታቸው (ይልቁንም ደግሞ ካስመታቸው) ብቻና ብቻ ነው፡፡  ወያኔና ኦነግ ጦቢያን ለማፈራረስ እጅና ጓንት ቢሆኑም፣ የፈራረሰችውን ጦቢያን ሲከፋፈሉ ግን ዓይንና ናጫ እንደሚሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው::  በመሆናቸውም (ባብይ አህመድ እቅድ መሠረት) ጦቢያ ከመፈራረስ አፋፍ ላይ እስከምትደረስ ድረስ ከወያኔ ጋር መመሳጠሩንና መተባበሩን ይቀጥልበትና፣ ጦቢያ ልክ ልትንኮታኮት ስትል ግን በእንኩትኳቹ ክፍፍል ላይ ጦርነት እንዳያነሳ ራሱን ወያኔን ባፋጥኝ ያንኮታኩተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ያማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ላማራ ሕዝብ የተሰዋውን ጀነራል አሳምነው ጽጌን በመሰለ በሚታፈርና በሚከበር ጠንካራ መሪ እስከተመራ ድረስ ያብይ አህመድ የኦሮሙማ ኃይል (ማለትም የኦሮምያን ልዩ ኃይል፣ የኦነግን ኃይልና በስሙ የጦቢያ የሚባለውን በግብሩ ግን የኦሮሙማ የሆነውን ያገር የመከላከያ ኃይል የሚያጠቃልል ኃይል) ያማራን ልዩ ኃይል ሊያሸንፍ ቀርቶ በቅጡ ሊገዳደር እንደማይችል ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው፡፡  ይህን ሐቅ ይበልጥ የሚያጠናክረው ደግሞ ወልቃይትና ራያ ወደ ቀድሞ ቤታቸው ወደ አማራ ክልል ተመልሰው ተቀላቅለው፣ ክልሉን በሕዝብ ብዛትና በተፈጥሮ ሐብት ጨምሮ በሁሉም ረገዶች የሁሉም ክልሎቸ የበላይ ማድረጋቸው ነው፡፡  ስለዚህም (የአብይ አህመድ የኦሮሙማ ሕልም ይሳካ ዘንድ) ወልቃይትና ራያ በምንም ዓይነት ያማራን ክልል መቀላቀል የለባቸውም፣ ያማራ ክልል ልዩ ኃይል ደግሞ ባመችው ጊዜና ቦታ፣ ባመችው ዘዴ ድባቅ መመታት አለበት፡፡

ያማራ ክልል ልዩ ኃይል ድባቅ መመታት ያለበት ግን ወያኔን ድባቅ እንዲመታ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡  ለዚህ ምክኒያቱ ደግሞ የኦነግ ሠራዊት ብዛቱ እንደጤፍ፣ መሣርያው በገፍ ቢሆንም፣ የወያኔን ጦር ማጥፋት ቀርቶ መግፋት ስለማይችል ነው፡፡  የኦነግን ውስጠ ሚስጥር አብጠርጥሮ የሚያውቀው የወያኔው ሰየ አብርሃ፣ ኦነግን ካምስት ሳንቲም አንቆጥረውም ያለው፣ ለማዋረድ ሲል ሳይሆን፣ ባለመታጠቃቸው ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰላማዊ ሰወችን ጨለማን ተገን አድርጎ ከማረድና ከማወራረድ የዘለለ፣ ሊጠቀስ የሚችል የውጊያ ችሎታም ሆነ ጀግንነት የሌለው፣ በባሩድ ጭስ በርግጎ በገደል የሚንኮታኮት አንኩቶ ሠራዊት መሆኑን ስለሚያውቅ ነበር፡፡

የኦነግ ሠራዊት ዕድሜው ከግማሽ ምዕተ ዓመት ያለፈ አዛውንት ሠራዊት ቢሆንም፣ በዚህ ረዥም እድሜው ግን፣ ፖሊስ ወይም ቀበሌ ጠባቂ የሌለባቸውን የገጠር ቀበሌወችና አናሳ ከተሞች በድንገት አጥቅቶ፣ የደም ጥማቱን ለማርካት የሚያርደውን አርዶ ባፋጣኝ ከመሸሽ ባሻገር፣ ጓንዴ ከታጠቀ ባላጋራ ጋር እንኳን ፊት ለፊት ገጥሞም ሆነ አሸንፎ አያውቅም፡፡  አሁን ላይ ደግሞ ዐብይ አህመድ ይህን ቱሪናፋ የኦሮሙማ ሠራዊት (በቀጥታና በተዛዋሪ) እስካፍንጫው ቢያስታጥቀውም፣ ወያኔን ወይም ያማራን ልዩ ኃይል ፊት ለፊት ልግጠም ካለ ግን ትርፉ መሣርያውን ማስረከብ ብቻ እንደሚሆን ራሱ አብይ አህመድ ያውቃል፡፡

በማታለል ጥበብ እጅጉን የተካነው ሸፍጠኛው ዐብይ አህመድ፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ እያንዳንዱንና ሁሉን የጦበያ ነገር በኬኛ ፖለቲካ አማካኝነት የኦሮሞ፣ በኦሮሞ፣ ለኦሮሞ በማድረግ ጦቢያን ከመፈራረስ አፋፍ አድርሷታል፡፡  ይህ ማለት ደግሞ ጦቢያን ለማፈራረስ እስካሁን ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋሪ ዐብይ አህመድን በከፍተኛ ደረጃ ያግዝ የነበረው ወያኔ፣ በፍርስራሹ ክፍፍል ላይ ጦርነት እንዳያነሳ ባፋጣኝ የመወገጃው ጊዜ አሁን ነው ማለት ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከመጨነቅ የመፍትሄ አካል መሆን - ሽመልስ ወርቅነህ

ወያኔ ደግሞ ድፍን ጦቢያን እንደገና ቢገዛ ደስታውን አይችለውም፣ በመጀመርያ ወደ ስልጣን ሲመጣ እንዳደረገው አሁንም እንደገና ባማራ ክልል ላይ ተረማምዶ ድፍን ጦቢያን ለመቆጣጠር እቅድ ቢያወጣም አያስገርምም፡፡  ጥቅምት 2(2013 ዓ.ም) ላይ ግን (ምናልባትም ራሱ ዐብይ አህመድ በተዛዋሪ መንገድ ገፋፍቶትና አደፋፍሮት ሳይሆን አይቀርም) እቅዱን ለማሳካት አስቦ ማዕከላዊ እዝን በድንገት በማጥቃትና አማራ መኮንኖችን እየመረጠ በማረድ፣ ባማራ ሕዘብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ፣ ዐብይ አህመድ ካጠመደለት ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ፡፡  ከዚያም (ዐብይ አህመድ በትክክል እንደገመተው) በቁጭት የተነሳሳው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ ወያኔን ከተወለደበትና ፀራማራ ማንፌስቶውን ካረቀቀበት ከደደቢት አቅራቢያ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በመቅበር ያማራን ሕዝብ መታደግ ብቻ ሳይሆን፣ ያብይ አህመድንም መንግሥት ከመገርሰስ አዳነው፡፡

ዐብይ አህመድ ግን ከውድቀት ያዳነውን ድለኛውን (victorious) ያማራ ክልል ልዩ ኃይል የተመለከተው፣ ወሮታውን ሊከፍለው እንደሚገባው ኃይል ሳይሆን፣ ከወያኔ የባሰ ለመንግስቱ አደገኛ የሆነ ኃይል አድርጎ ነው፡፡  ባብይ አህመድ እቅድ መሠረት ያማራ ልዩ ኃይል ወያኔን ድባቅ እንደመታ ተልእኮውን ስለጨረሰ (mission acomplished)፣ ወደ ኦሮሞ አጼጌ የሚያመራውን መንገድ ክፍትና ግልጽ ለማድረግ ባፋጣኝ ድባቅ መመታት አለበት፡፡

የዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ኃይል ግን የአማራን ልዩ ኃይል ፊት ለፊት ገጥሞ ድባቅ መምታት ቀርቶ ዝንቡን እሽ ሊለው አይችልም፡፡  ያማራ ልዩ ኃይል (ትጥቁ ነፍስ ወከፍ ብቻ ቢሆንም እንኳን) ዐብይ አህመድ ሊያሰማራው የሚችለውን አስካፍንጫው የታጠቀን ማናቸውንም የኦሮሙማ ኃይል በቀላሉ መመከት እንደሚችል እሙን ነው፡፡  ስለዚህም ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ሕልሙን እንዳያውን (realize) የሚያደርገውን ይህን ያማራ ልዩ ኃይል ማስወገድ የሚችለው፣ በዘር ማጥፋት ወንጅል አስከስሶ ምዕራባውያን ባለ በሌለ መሣርያቸው እንዲረባረቡት ካደረገ ብቻና ብቻ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ደግሞ ዐብይ አህመድ ችግር አይኖርበትም፡፡  ሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochaska) በትክክል እንዳስቀመጠው አማራወች ኩሩ ጥቁሮች (“champions of all black people”) በመሆናቸው፣ ያማራ (የጦቢያ) ብሔርተኝነት ያውሮጳ ቅኝ ገዥነትን አድዋ ላይ ስለገታው (“forcibly kept European colonialism”)፣ በተጨማሪ ደግሞ አማራወች ማናቸውንም ነጭ የሚመለከቱት በሰውነቱ ብቻ እንጅ አንረውም አኮስሰውም ባለመሆኑ፣ አማራወችን አምርረው የሚጠሉ ኸርማን ኮኸንን (Herman Cohen) የመሳሰሉ ፀራማራ ከፍተኛ የመንግስት ሹሞች በምዕራባውያን መንግስታት ውስጥ በብዛት ይገኛሉ፡፡  እነዚህ ፀራማራ ሹሞች ደግሞ በስማበለው (hearsay) ብቻ ተመርኩዘው፣ ያማራን ልዩ ኃይል በዘር ማጽዳት (ethnic cleansing) ወንጅለው፣ የዘመናዊ መሣርያወቻቸው መፈተሻ እያደረጉ ያማራን ልዩ ኃይል አስታከውም ያማራን ሕዝብ ድምጥማጡን ቢያጠፉት ደስታውን አይችሉትም፡፡

ዐብይ አህመድ ባማራ ክልል ላይ ያሰማራቸውን ኦነጋዊ እንደራሴወቹን በመጠቀም ያማራ ልዩ ኃይልን በዘር ማጥፋት ወንጀል በሐሰት የወነጀለበትም ዋና ምክኒያት ይሄውና ይሄው ብቻ ነው፡፡  ውንጀላውን ለማቅረብ የይስሙላ ፓርላማውን የመረጠበት ምክኒያት ደግሞ፣ ለውንጀላው ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት፣ ይልቁንም ደግሞ ምዕራባዊ ያልሆኑ የጦር ወንጀለኞን አዳኝ አድርገው ራሳቸውን የሾሙት ምዕራባውያን (በተለይም ደግሞ አሜሪቃኖች፣ እንግሊዞችና ፈረንሳዮች) በግልጽና በደንብ እንዲሰሙት በማሰብ ነው፡፡

በመጨረሻም የሚሰሙ ከሆነ ለብአዴኖች ምክር ቢጤ፡፡

ደመቀ መኮንን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አገኘኹ ተሻገር … ጨው ለራስህ ጣፍጥ ነውና፣ ላማራ ሕዝብ ብላችሁ ሳይሆን ለራሳችሁ ብላችሁ አጭበርባሪው አብይ አህመድ እናንተን እንደሚያጭበረብረው ሊያጭበረብራቸው ለማይችል ዓይነ-ንሥር ልበ-ነብር ወጣት አመራሮች ስልጣናችሁን ባስቸኳይ አስረክቡ፡፡  አለበለዚያ የፊጥኝ ታስራችሁ፣ ወደ ሄግ (Hague) ተግዛችሁ፣ የምዕራባውያንን ጥቅም ለማስከበር በተቋቋመው ፍርድቤት (International Criminal Court) ቀርባችሁ፣ ባማራነታችሁ ብቻ በሚጠሏችሁ ነጭ ላዕልተኛ (white supremacist) ዳኞች ፊት ቁማችሁ፣ ያለጥፋታችሁ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተወንጅላችሁና በሙሉ ድምጽ ተፈርዶባችሁ፣ ዘብጥያ የምትወርዱበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፣ ለዚያውም ደግሞ ይሙት በቃ ተበይኖባችሁ በስቅላት ካልተቀጣችሁ፡፡  በተለይም ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቅፈህ ቆጥ የሰቀልከው ዐብይ አህመድ ዘሎ ሳይከመርብህ በፊት ገሸሽ ብለህ እንዲፈጠፈጥ ብታደርገው፣ ራስህንና አማራን ብቻ ሳይሆን ድፍን ጦቢያን በልቶ ከማይጠረቃው ከስግብግቡ የኦሮሙማ ጅብ አድነህ፣ የጦቢያና የጦቢያውያን ዘላለማዊ ባለውለታ ትሆናለህ፡፡

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

6 Comments

  1. ምንም ፍሬ ነገር የሌለው መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁናቴ የማይገናኝ በመረጃ ያልተደገፈ እንቶ ፈንቶ ሃሜት የመንደር የቡና አጣጭ ጽንፈኛ ትርክት ነው። ጊዜየን በከንቱ አቃጠልኩ።

    • ተባረክ ሀሳቤን ቁልጭ አድርገህ ከትበሀል:: ይህ ፅሁፍ ጥበበኛው ወያኔ ኢትዮጵያን ከሚያፈራርስበት ዘዴ ለይቼ አላየውም:: እኔ እንደ አማራ በኢትዮጵያ ጉዳይ ብርሀኑ ጁላንና አበባው ታደሰን ለይቼ አላያቸውም:: የኦሮሞም ሆነ አማራ ፅንፈኞች የሚጋብዙት ወያኔ የሚፈልገውን civil war ነው:: ይህ አይሆንም

  2. It is so realistic, straightforward and powerful !! This is the way we need to be courageous and patriotic enough if we are truly concerned about the deadly ethno-centric politicians of EPRDF, now Prosperity of Abyi Ahmed should be dealt appropriately and effectively before it totally destroys the very existence of the country.

  3. በዚህ ገጽ ላይ አዘውትረው የጦር አውርድ ወይም ቆሻሻ ፅሁፍ ከሚያቀርቡት መካካል አንዱ ይህኛው ናቸው፡፡ በርግጥ መግቢያውን እና መደምደሚያውን በወፍ በረር ከማየት ውጭ ማንም ሰው በቁም ነገር ያንበዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share