ስለ ዶክተር ዝናቡ እርገጤማ አለመናገር አይቻልም! – አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

ወደን የማንስቅባቸው ብዙ አጋጣሚዎች መኖራቸውን “ወደው አይስቁ” የሚለው ፈሊጥ ያረጋግጥልናል፡፡ አዎ፣ አንዳንዴ ተገደንም ቢሆን እንስቃለን፡፡ አንገቱ የተቆረጠ ሰው – አሉ ነው – ከሰውነቱ የሚለዬው ጭንቅላት በሣቅ እየተንከተከተ ለተወሰነ ጊዜ ራሱን ችሎ ይንቀሳቀሳል ይባላል፡፡ ይህ ግን የውዴታ ሳቅ አይደለም፡፡ እናም ሆዳችን እያረረ የምንስቅባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ – ልክ እንደማሽላዋ፡፡

ዶ/ር ዝናቡ እርገጤ ሕዝበ አዳምን በሣቅ ጦሽ ማድረጉን እንደቀጠለ ነው፤ ግሩም ተዋናይ እኮ ነው! በዚህ የሣቅና ስላቅ ሂደት የሚያሳዝኑኝ አንዳች ድግምት የተዞረባቸው የሚመስሉት ጭፍንና ምናልባትም የዋህ ደጋፊዎቹና ተከፋይ አክቲቪስቶቹ በነሀብታሙ አገላለጽ ውታፍ ነቃዮቹ ናቸው፡፡ “አውቆ የተደበቀ ቢጠሩት አይሰማም” – ትክክል ነው፡፡ ውታፍ ነቃዮቹ መተዳደሪያቸው ኅሊናን ሸጦ በሚገኝ ሶልዲ በመሆኑ የተፈለገውን ያህል እውነት ቢነገርና ቢለፈፍ ጆሮ የላቸውም፡፡ በቆረቡበት ውሸትን የማራገብ የሆድ አደርነት ተግባር እንደተሰለፉ እስከህቅታቸው ማብቂያ ይዘልቃሉ፡፡ በገንዘብ የተለወጠ ኅሊና ወደ ሆድ ወርዶ ስለሚሸጎጥ ሰውን መግደልና ማረድም ለነሱ ጽድቅ እንጂ ኩነኔ አይደለም፡፡

ዶ/ር እርገጤ ማነው ዝናቡ እርገጤ “በጎጃምና በሰሜን ሸዋ ዝናብ ያዘነብኩት እኔ ነኝ” እያለ ነው – ይህ ልጅ ጊዜ ካገኘ እንደ ሊቀ ሣጥናኤል እኛን ጭምር “አነ ፈጠርክክሙ በአምሳሊየ ወበአርአያየ” ሳይለን ይቀራል ብላችሁ ነው? እንዲያውም ይህን ዝናብ የማዝነብ ጥበቡን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ መሆኑንም “አብሥሮናል” – አሃ! ግን ቴሌ ባለአራት ጂቢ ብሮባንድን በኦሮሚያ ሲያስጀምር “ዝናብ” በሚል ኮድ ባላጡት ሥፍራ በአማራ ክልል የተጀመረው ዝናብን የማዝነብ የመንዝ ደብተራ ድግምት “አልጋ እንዲረጋ ለሰይጣን ግብር የሰው ደም ማፍሰስ” ለማለት እንደሆነስ ቅኔው እንዴት ሊገባን ይችላል? ለማንኛውም ጆሯችን ጤንነቱን አይጣ እንጂ እርገጤ ገና ብዙ ጉድ ያሰማናል፡፡ ታስታውሱ እንደሆነ ወደሥልጣን እንደመጣ ሰሞን በቲቪ መስኮት ብቅ ብሎ በሀገራችን የነዳጅ ድፍድፍ መገኘቱንና ወደምርት ልንገባ ጫፍ ላይ መድረሳችንን ነገረንና በነዳጅ አምሮት የተቃጠለውን ምላሳችንን ምራቅ በምራቅ አደረገው፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ወፍ የለም፡፡ እንዲያውም ያን ጊዜ የነበረው የነዳጅ ዋጋ አሁን ዕጥፍ ድርብ አድጎ በነዳጅ ውድነትና እርሱን ተከትሎ መጣ በተባለው የኑሮ ውድነት ሀገር ምድሩ እየታመሰ ነው፡፡ ታሪክ ከታቢዎች የእርገጤን የየዕለት ውሸት ዘግቡና ለታሪክ አቆዩት እባካችሁን፡፡ ወደፊት በታሪካችን “እንዴ! እንዲህ ዓይነት መሪም ኢትዮጵያ ነበራት?” ተብሎ ትውልዱ እንዲማርና በነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ሳይሆን በስሜት ከሚነዳ ወፈፌ መሪ እንዲጠነቀቅ ሀገርን እንርዳ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይቺ ያንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት ዋጋዋ ስንት ቢሆን ነው ፓርላማው የቆጠባት? - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ወደሌላ ወቅታዊ ጉዳይ ከማምራቴ በፊት ስለዝናብ ማዝነብ ትንሽ ነገር ልጨምር፡፡ ዝናብን ማዝነብም ሆነ እንዳይዘንብ ማድረግ በመተታዊ ድግምት ይቻላል፡፡ በሽናሻዎች ለምሣሌ ዝናብ እንዲዘንብም እንዳይዘንብም ማድረግ የሚቻላቸው ባህላዊ ጠቢባን እንዳሉ እዚያው አካባቢ በሄድኩ ጊዜ ሰምቻለሁ፡፡ ከሰይጣን ጋር ጉድኝት ያላቸው ደባትርም ይህንና ሌላም አንደርባዊ መተት ያከናውናሉ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ሆኖ የዶክተር እርገጤን የዝናብ ማዝነብ ሣይንስ እውነት ነው ብለን ብንቀበል እንኳን አሁን ወቅቱ ነው ወይ? እግሬን በሰላ ጎራዴ እየጨረገደኝ “ስወድህ እኮ!” በሚል መደለያ ራሴን ቢያክልኝ ምኑን ፍቅር ሆነው? ጎጃምና ሰሜን ሸዋስ እንዴት ለዝናብ ሊመረጡ ቻሉ? አማራን በዚህ መልክ ማነሁለል ይቻላል ብሎስ አስቦ ይሆን? ጎጃም መተከልና ሸዋ አጣዬ ሰሞኑን ምን እንደተፈጠረ ይታወቃል፡፡ ይህ ዶክተር እርገጤ በምን ሒሣብ ነው ዝናብን ከነዚህ ሥፍራዎች ጋር ሊያያይዝ የቻለው? የሀገራችን የወቅቱ ራስ ምታትስ የዝናብ ዕጥረት ነው ወይ? ከሁሉ በፊት ሰው አራጆችንና ዘረኛ ኬኛዎችን አደብ ማስገዛት አይቀድምም ነበር? በንግዱ ሠርገው ገብተው የአንድ ሊትር ዘይት ዋጋ እስከ ብር 140 እያደረሱ ያሉ የኑሮ ውድነት ጁንታዎችን አደብ ማስገዛት አይሻልም? የግንባታ ግብኣቶችን ዋጋ ሰማይ እየሰቀሉ የቤት ሠሪዎችን ኪስ የሚያጥቡና ገበያውን በሲዖላዊ ነበልባል የሚያጋዩ ዜጎች ከመንግሥት ዕይታ ውጭ ሆነው ነው?  ወዘተ. ብለን ስንጠይቅ የሰውዬው ድርጊትና የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አራምባና ቆቦ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የፌዴራል መንግሥት ተብዬው አልጋውን ላለማስነጠቅ ሌት ተቀን የሚለፋ እንጂ ለህዝብ ኑሮ የሚጨነቅ አልሆነም፤ አፈር ደቼ ብንበላ ግድ የለውም፡፡ እንጂ እውነት ከሆነና እንደሌላ ጊዜው ሁሉ ሰውዬው የውሸት ቱማታውን ካልለቀቀብን ዝናብ በተፈለገ ጊዜ እንዲዘንብ የሚያደርግ ጥበብን የሚጠላ ጤናማ ዜጋ የለም፡፡ የዚህ የአሁኑ ዝናብ ዓላማ ግን ፖለቲካዊ ግብን ያነገበና ምናልባትም በሣይንስ ወለድ ፊሲክሣዊ “ትሪክ” አማራን ለመደለል ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ከዝናብ በፊት በመንግሥት ተንቀባርረው ተይዘው በህዝብ አንደኛ ደረጃ አውቶቡስ የትም ቦታ በነፃነት በመንቀሳቀስ አማራውን እየጨፈጨፉ የሚገኙ ኦህዲድ-ሠራሽ ኦነግ-ሸኔዎችን ሃይ ይባሉልን፡፡ ዝናባችን እሱ ይሁን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በደም የተከበረ የዓለም ሠራተኞች ቀን፤ ሜይ ዴይ

ሰሞነኛውን የኦነግ/ኦህዲድ በአማራ ሕዝብ ላይ የተካሄደውና አሁን ድረስ ያልቆመው ጦርነት መንስኤው የአማራ አልጠግብ ባይነትና በኦሮሞ ላይ ያለው ጥላቻ የወለደው እንደሆነ በብጥለው ገለበጠኝ ከኦነጋውያን እየሰማን ነው፡፡ አለማፈርን ከሸጡ አይቀር እንደዚህ ነው፡፡ የአጣዬና ማጀቴ ሕዝብ ነቅሎ ወጥቶ ሆሮ ጉድሩ ላይ የሚገኝን ኦሮሞ ሲጨፈጭፍ የተገኘ አስመሰሉት፡፡ ይሉኝታንና ሀፍረትን መሸጥ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ የለም፡፡ ዶ/ር ኮሎኔል ሎሬት እርገጤም ተደርቦ “አማራና ኦሮሞ ድብድባችሁን አቁሙ” ዓይነት ንግግር በአሻንጉሊት ፓርላማው ፊት ሲናገር ተደምጧል አሉ፡፡ ማን ተንኳሽ ማን ጥፋተኛ እንደሆነ ልቦናው እያወቀ ጥፋትን ለንጹሓን ጭምር ማጋራት ወይም ማከፋፈል የተንኮለኞችና የሤረኞች ጠባይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አማራን በደለኛ ለማስባል የሚሄዱበት ርቀት እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኦነግ/ኦህዲድ በቀቀኖች ያጠኑትን ንግግር በፓርላማ ተብዬው የኦህዲድ ብልግና ፓርቲ የባለጌዎች ሠርግ ዳስ ውስጥ ሲዘላብዱ የሰማቸው ሁሉ ተደንቋል፡፡ ካበዱ አይቀር እንዲህ ነው፡፡

ዶ/ር ዝናቡ እርገጤ የዚህ ሁሉ ድራማ ደራሲ መሆኑን ለመረዳት በቅርቡ የተከበረውን 125ኛ የዐድዋ ዝክረ በዓል ማስታወስ በቂ ነው፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ አክራሪ ኦሮሞዎች ያሳዩት ነውር የተሞላበትና የደጃች ባልቻ አባነፍሶ ቤተሰብ ማኅበርም አጥብቆ የተቃወመው የበዓል አከባበር ለዚህ ለሰሞኑ ዕልቂት የዋዜማ ዝግጅት ጠቋሚ ነበር፡፡ ያን አንዳችም ኢትዮጵያዊነት ያልተንጸባረቀበት በዓል የታዘበ ሰው እነዚህ ሰዎች የሽመልስ አብዲሣን ንግግር ተግባራዊ ለማድረግ ቀን ከሌት እየተራወጡ እንደሆነ መረዳት አይከብደውም፡፡ ሕዝበ አዳም ግን የተደገሰለትን ያወቀ አይመስልም፡፡ አብዛኛውን ሕዝብ ስታዘበው በአገር አማን ምንም ሳይመስለው እየተንጠራወዘም ቢሆን ኑሮውን ይገፋል፡፡ ግርምቲ አዲ!

ካለፈው ተነስቼ መጪውን እያወቅሁት “እገሌ እንዲህ በል፤ እነገሌ እንዲህ አድርጉ” ማለት አልፈልግም፡፡ ለነገሩ ምን ጥልቅ አደረገኝ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የለውጡ ተግዳሮቶች በኔ ዕይታ - ይነጋል በላቸው (ከአዲስ አበባ)

1 Comment

  1. ወቸው ጉድ ዝናብ በሰው ሰራሽ ብልሃት እንደ ዶፍም ባይወረድም ጠብ ጠብ እንደሚል ሳይንሱ ይናገራል። እኛ ሃገር በሰው ሰራሽ የዘነበው ዝናብ መጠኑና የት ቦታ እንደዘነበ ለምን ሚስጢር እንደሆነ አልገባኝም። አይ ሃበሻ የቁልቁለት ድምር ሲጠፋበት አበድረኝ ብሎ ያው ስሌቱም ተማቶበት ከነብድሩ የሚጠፋ ትውልድ! በአፍሪቃ ሁኔታ ልቤ መድማት ከጀመረ ዘመን ተቆጠረ። የሚገርመው ያኔ የነበረው እና አሁንም ያለው ተግባሩ አንድ መሆኑ ነው። በሞት ያለፉትን አንዳንድ የሃገሬን ልጆች ሳስብ ይች ሃገር የጉድ ሃገር ናት እላለሁ። ጉዳዪ እንዲህ ነው። ለፓለቲካ አሻጥር እውቁን የኦሮምኛ ዘፈን አቀንቃኝና የመብት ተሟጋች ሃጫሉን ሁንዴሳን፤ ከትግርኛ ዘፋኝ ኢያሱ በርሄን፤ ኪሮስ ዓለማየሁን፤ የማነ ባሪያን ሳስብ ምድሪቱ የሽንኮች መናህሪያ ናት እላለሁ። ያለ ተንኮልና ያዘው አባረው ግደለው ብቻ ነው ድንፋታችን። በአሜሪካን ሃገር አንድ የትግርኛ ቤ/ክ ቄስ መስቀሉ ደረቱ ላይ አርጎ በሰልፉ መካከል በመቆም ያስተላልፍ የነበረውን የፓለቲካ ቅስቀሳና የዘር ጥላቻ ለሰማ ሰው እውነትም ጨርቁን ጥሏል ያሰኛል። ግን አይገርመኝም። ወያኔ ከጫማ ጠራጊ እስከ ሴተኛ አዳሪ፤ ከዘበኛ እስከ መ/ቤት ሚኒስቴር፤ ከተራው ወታደር እስከ ከፍተኛ መኮንኖች ድረስ በስለላ መረቡ በጥቅማ ጥቅም ወጥሮ የያዛቸው የያኔው ጄሌዎቹ አሁንም ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ነው። ያልታያቸው እንወድሃለን የሚሉት የትግራይ ህዝብ የእነርሱ መነገጃ መሆኑ ነው። ትላንትም ዛሬን ሲመስል እንዲህ ነው። ወያኔና ወያኔ አፍቃሪዎች ዘርና የክልል ፓለቲካን ገፍተር አድርገው እውነቱን ቢፈትሹ ለ 46 ዓመታት መከራ ያየው ህዝብ ነጻ እናወጣሃለን፤ ነጻ ወጥተሃል እያሉ የቀለድበት ህዝብ ዛሬም ያው የትግራይ መከረኛ ህዝብ መሆኑ ይሰቀጥጣል። ችግሩ ግን የሁሉም ነው። ገና ከጅምሩ ሰው እንደ ከብት ሲያርዱ፤እኛም ለመኖርና ፍርፋሪ ለመልቀም ሰው በመላ ሃገሪቱ ሰቆቃ ሲያይ እኔ ላይ ካልደረሰ ምን አገባኝ እያልን የጠገበው ወርዶ ሌላ በላተኛ በስፍራው ተተክቷል። ይህ አያሳዝንም የሚል ልበ ድንጋይ ነው። አቶ ዝናቡ ከዚሁ ወራጅ ውሃ የተቀዳ ነው። ተንከባላይ ፓለቲከኛ!
    እውቁ ኢትዮጵያዊ ጀኔራል በረታ ገሞራው በወያኔ እጅ ሲወድቁ ሲቀልድባቸውና ሲዘልፋቸው የነበረው አቶ ታምራት ላይኔ ነበር። ያው በህዋላ ወያኔም እሱን አኝኮ ተፋውና እንደሚሆን ሆነ። ይህ ጄኔራል ወያኔን እንደጠላ ከአንድ የእስር ጉድጓድ ወደ ሌላ ወስደው ሲያሰቃዬት ሁላችንም ወደ እማይቀርልን ቦታ ተሰናበተ። ሃገሪቱ ሌባ አስተናጋጅ ናት። የገደላትን የምታበላ የሞቱላትን የምትረሳ። የዛሬውም እንገጭ እንገጭ ፓለቲካ ካለፈው ተምሮ፤ ሃገርን አረጋግቶ፤ ህዝባችን የጎሳና የፓለቲካ ክልልን ረስቶ በሰላም በአንድነት እንድንኖር ህግጋትን ሽሮ ሌላ ካላወጣ ዛሬ በየደብሩና በየጎዳናው የአማራን ቤትና ንብረት እያቃጠሉ አንገት የሚቀሉት የውስጥና የውጭ ተቀጣሪ ሃይሎች የቤ/መንግሥት አለቆቻችንም አይለቋቸውም። በልመና በጸሎት የሚሆን ነገር ቢሆን በምድሪቱ ተጽሞ ክራራይሶ ተብሏል። ፈጣሪ በሃበሻ ፓለቲካ ላይገባ ርቆ ተቀምጧል። ትንቢትና ስብከቱ ሁሉ የውሸት ነው። የደነዘዘ ህዝብ ማንቂያ ዲወል የለውም። ያው አዚም እንደተደረገበት ሲያንቀላፋ ነው ወደ ሙታን ምድር የሚወርደው። ለሁሉ ማብቂያ አለው። የሃገር ሰራዊት ገደሉ ዘረፉ በማለት በየጊዜው ያሰለቸን የዶ/ር አብይ መንግስት በስማቸው የቆሙ ቤቶችን፤ ንግድ ቤቶችን፤ በውጭና በውስጥ በእጅ አዙር በዘመዶቻቸው የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን፤ በኢምባሲና በካውንስለር ጽ/ቤቶች ተሰግስገው የኢትዮጵያን ፓስፓርት የሚሸጡትን፤ ህዝብ በመከፋፈል ሰውን ያዘው ግደለው ፍጨው የሚሉትን ለቅሞ በድህነንቱ ሰንሰልት አልከተታቸውም። ዝም ብሎ ጡሩንባ መንፋት አደከመን። ስራ በልብ በተግባር ነው። የሚገርመው አሁን ራሱ ትግራይ በረሃ ውስጥ ገብተው የሚዋጉት ጡረተኛ ጄኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች የጡረታ ሁሉ እንደሚከፈላቸው ነው። አይገርምም። እስቲ ወያኔ ያንሰራራና ሲምራችሁ እናያለን። ለነገሩ እልፍ የትግራይ የገበሬ ልጆችን ያስጨረሱትን እነ አቦይ ስብሃትን በቃሬዛ ስትሸከሙ ነው ነገሩ የተበላሽው። ያን የድሃ ልጅ ማን ያንሳው? ትላንትም ሟች ዛሬም ሟች። የዶ/ር አብይ መንግሥት ጉዳይ ግራ እያጋባኝ መጥቷል። የሃገሬ ሰዎች ሲተርቱ ” ያሳምራል ያሉት ኩል ዓይን ያጠፋል ይላሉ” ጉዳዪ እንዲዚያ ይሆን? እነ ዶ/ር ዝናቡንና መሰሎቻቸውን ጮቤ እያስረገጠ የሚያስጨፍራቸው እውነት ሞታ በተቀበረችበት ምድር ላይ መሆኑ ረስተው ነው? አይደለም። እኔ ብሎ ለሚያስብ ሰው የሚታየው የራሱ መኖር ብቻ ነው። ገጣሚው ባለው ስንኝ እገታለሁ።
    እያረረ ሆዴ ጥርሴ ሲስቅ አይተው
    ድልቶታል ይላሉ የማሽላን ማረር መፍካቷን ረስተው።
    ልብ ይስጠን … በቃኝ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share