ለተከበራቹህ ወገኖች
የኮሮና ልምድ ከጀርመን – 3ኛው ማዕበል የከረርው ፍጹም ሎክዳውን
23.03.2021
ካለፈው በመቀጠል በ22.03.2021 እስከ እኩለ ሌሊት ከተደረጉ ውይይቶች በኋላ የፌዴራል እና የሪጅናል ስቴት (ክልል) መንግስታት አዲስ የተከሰተውን 3ኛውን ዙር ማዕበል ለመስበር ለጥቂት ቀናት የሚቆይ ፍፁም ሎክዳውን በመጣል እና በተጨማሪም ከዚህ በፊት የነበረው እስከ ሚያዚያ 18/ 2021 እንዲቀጥል አጽድቀዋል።
በጀርመን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትም በዚህ ሳምንት እንደ ዥዋዥዌ ተቀይሮ በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ወደ 3ኛው ዙር ገብቷል። በሰባት ቀናት ውስጥ ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል የተገኘው ኢንፌክሽን በአማካይ በቁጥር 13 ጽሁፌ ከገለጽኩት 65 ወደ 108 ጨምሯል። የሟቾቹ ቁጥር በቀን አሁንም ቢሆን ከ200 በላይ ነው። ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በጀርመን 2.6 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 2.4 ሚሊዮን አገግመዋል። ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር 74,964 ደርሷል። የታማሚዎችም ሰነ ዕድሜ በእድሜ ከገፉት ወደ ወጣቶች እየተቀየረ ነው። ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው በእድሜ የገፉት አስቀድመው እየተከተቡ በመሆኑ እና ከእንግሊዝ ሀገር የመጣው የተቀየረው የቫይረሱ አይነት ከባድ አጥቂነት አለው ስለሚባል ነው።
- ማህበርዊ ግንኙነት በምዕራብያውያን ፋሲካ ወቅት – ከ01.04.2021 ጀምሮ ለአምስት ቀናት
ከመጪው ሓሙስ ሚያዚያ 1 እስከ ሰኞ ሚያዚያ 5 ድረስ ውስን በነበሩት የማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ ተመልሶ የጠበቀ ገደቦች ተጥለዋል። በዚህ ወቅትም በአምስት ተከታታይ ቀናት ውስጥ “በቤት ውስጥ እንቆያለን” (Wir bleiben zu Hause) የሚለው መርህ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ከገዛ ቤተሰብ በተጨማሪም ከሌላ አንድ ቤተሰብ ጋር የሚደረጉ ማህበራዊ ግንኙነቶች ሲፈቀዱ፣ ግን ይህ ከአምስት ሰዎች በላይ ማለፍ የለበትም። እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ከዚህ ነፃ ናቸው።
ለሰባት ቀናት በተከታታይ ከ100 አዳዲስ ኢንፌክሽኖች በላይ በሚከሰትባቸው ወረዳዎች ውስጥ ጠንካራ ገደብ እስከ ሰዓት እላፊ እና ከአካባቢ ወይም ከቤት የመራቅ ገደቦች ይጣላል።
- የእምነት ቦታዎች
በአብያተ-ክርስቲያናት በተለይም የካቶሊክ አውሮፓውያን ፋሲካ በዓል በአካል በመገኘት የሚደረጉ አገልግሎቶች አይኖርም። በአማራጭነት የኦንላይን የቤተክርስቲያን ግልጋሎት ይመከራል።
- ጉዞ
ከውጭ ለእረፍት የሄዱ ተመላሾች ያለአስቀድሞ ኒጌቲቭ የናሙና ምርመራ ወደ ጀርመን መግባት እንደማይችሉ ቅድመ ሁኔታ ይቀመጣል፡፡ የፌዴራል መንግስቱ እና የፌዴራል ክልሎች በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚደረግ ጉዞን እጅግ ፍጹም አስቸኳይ ወይም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር እንዳይደርግ ይመክራሉ።
- የዕለታዊ ፍጆታ ጅምላ ሻጮች እና ቸርቻሪዎች
ሁሉም ሱቆችና የገበያ ቦታዎች ከሚያዚያ 1 ቀን 2021 እስከ ሚያዚያ 5 ድረስ ዝግ ሆነው ይቆያሉ። የምግብ ቸርቻሪዎች፣ ሳምንታዊ ገበያ እና አካፋፍዮች፣ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች፣ የፖስታ እና የእቃ የመሰብሰብ እና የማደል አገልግሎቶች፣ የመጠጥ ገበያዎች፣ ቅዳሜ ሚያዚያ 3 ብቻ በተወሰነ መልኩ ክፍት ናቸው።
- ትምህርት ቤቶች
ለትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለመዋዕለ ሕጻናት ሰራተኞች የኮሮና ናሙና ምርመራዎችን “በተቻለ ፍጥነት በሳምንት ሁለት ምርመራዎችን” ለማድረግ እየተሰራበት ነው። አተግባበሩ እንደ ሪጅናል ስቴቱ ይለያያል። ለምሳሌ በበርሊን ትምህርት ቤቶች ውስጥ 10 የናሙና ኪቶችን ለተማሪዎች በማከፋፈል በሳምንት ሁለት ምርመራዎችን እንዲያደርጉ ተጀምሯል።
- ቀጣይ ውሳኔዎች
ከ18 ሚያዚያ 2021 ቀጣዩ የመክፈቻ እርምጃዎች የሚወሰኑት ሚያዚያ 12/ 2021 በሚደረግ ጉባኤ ይሆናል።
- ክትባት
እስከዛሬ ወደ 7.7 ሚሊዮን ሰዎች አንድ ጊዜ ያህል ሲከተቡ 3.4 ሚሊዮን ሰዎች ደግመው ተከትበዋል። አሁንም ቢሆን ይህ ዝግተኛ አካሄድ እንደተጠበቀው ሊፈጥን አልቻለም። የAstraZeneca ክትባት የደም መርጋትን ሊያመጣ ይችላል በሚለው ክስተት የተነሳ ለጊዜው ተቋርጦ የነበር ሲሆን አሁን ግን እንዲቀጥል ተወስኖ ክትባቶች ቀጥለዋል። ቢሆንም ሰው አሁንም ቢሆን AstraZeneca የመከተብ ፍላጎቱ ዝቅተኛ ነው።
- ከኮሮና ጋር የተያያዘ ሙስና
የፓርላማ አባል የሆኑ እና ሌሎች የጀርመን ፖለቲከኞች ከኮሮና የማስክ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ስልጣናቸውን በመጠቀም ጥቅም ያስገኙ እና ጥቅም አግኝተዋል በሚለው የሙስና መጠርጠር ላይ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን የጀርመኑ የጤና ሚኒስተር ስልጣናቸው እየተነቃነቅ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቀዋል።
- ኢኮኖሚ
በአለፈው እንደገለጽኩት የጀርመን ኢኮኖሚ ሁለተኛውን ወረርሽኝ የሚያስከትለው አደጋን ተቋቁሟል። ከአምስት ወራት ጀምሮ ሎክዳውን ቢሰፍንም፣ የተለያዩ የጀርመን የኢኮኖሚ ጥናት ተቋማት የጀርመን ኢኮኖሚ እድገት ላይ የበለጠ ተስፋ እንዳላቸው ይገልፃሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት በጥሩ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ በተተነበየው መንቃቃት ላይ የተመረኮዘው የኢንዱስትሪ ሴክተር መልካም አዝማሚያ በማሳየቱ ነው። ለዚህም ምክንያት የክትባት መከላከያ መጨመሩ፣ የፈጣን የናሙና ምርመራ እና የመግበየት ጠንካራ ፍላጎት በመጨመሩ ነው። በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት በ2021 በ3.7 በመቶ (ከዚህ በፊት 3.1 በመቶ) እና በ 2022 ደግሞ በ4.8 በመቶ (4.5 በመቶ) ያድጋል በማለት የኢኮኖሚ ትንበያውን ወደላይ አሻሽሎታል። የአሜሪካ ኢኮኖሚ መጠናከር የዓለም ኢኮኖሚን ያጠነክራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የወረርሽኙ መጨመሩ እጅግ የሚያሳዝን ነው። በተከታታይ በአቀርብኳቸው ፅሁፎች ላይ መዘናጋት ሊያስከትል የሚችለውን ችግር የገለጽኩ መሆኑ ይታወሳል። ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ወደአሉ መስሪያ ቤቶች ለመገናኘት ለሚጻፉ ኢሚይሎች መልስ ማግኘት፣ ሲደወሉ ሊመልሱ የሚችሉ ስልክ ቁጥሮችን እና አመርቂ መልስ ሰጪዎችን ማግኘት፣ ስለራስ ድርጊት ከሚገልጹ ፊስ ቡክ ይልቅ ወቅታዊ መርጃ የሚሰጡ ድህረ ገጽ ያላቸው መስሪያ ቤቶችን ማግኘት እጅግ ብርቅ በሆነበት ሁኔታ የጤና ሚኒስቴር ይህንን በማሟላቱ ተደራሽነት ያለው መስሪያ ቤት መሆኑን አሳይቷል ብዬ እገምታልሁ። ስለኮሮና መከላከል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚያደርገውን ጥረት እያመስገንኩ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ያሉት መረጃዎችን እና ምክሮችን፣ ፖስተሮችን እንዳይሰለቹ/እንዳይረሱ በየጊዜው መቀያየር ያስፈልጋል፣ ለምሳሌ ስልክ ላይ ሲደወል አስቀድሞ የሚመጣውን መልዕክት „ከኮሮና ራስዎን ይጠብቁ የሚለው…“ ጥሩ ነው። እኛ ከውጭ ስንደውል እንኳን ራሳችንን እንድንጠብቅ የሚያስታውስን እና ምስል የሚፈጥር ነው። ቢሆንም የተለመደ ምክር እንደመዘናጋት ይሆናል እና መልእክት በየሳምንቱ ያለውን ሁኔታ እንዲገልጽ ማሻሻል፣ ከፍተኛ ቁጥጥሮችን እና የኮሙዩኒክሽን ራዎችን መስራት፣ በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችም እንዲሳተፉበት ማስቻል እና አዳዲስ የተሻሻለ የመከላከል እቅድ ማቅረብም አስፈላጊ ይመስለኛል። ወረርሽኙ በከፍተኛ ቦታ በተሰራጨባቸው ከተማዎች/ ወረዳዎች ላይ ቁጥጥር ማጥበቅ እና ከዲዛይን ማስክ ይልቅ በተቻለ መጠን በህክምና ሰርቲፋይድ የሆነ ማስክ መጠቀም እና በወረርሽኙ ተይዞ ቢዳንም ወይም ክትባት ቢወሰድም እንኳ ማስክ መጠቀምን አለማቋርጥ ይመከራል።
አንድን ሕይወት የሚያድን ሁሉ ዓለምንም ያድናል።
– ታልሙድ
ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)
——-
Dr. Tsegaye Degineh
Berlin, Germany
——
Email: mail@degineh.de,