March 21, 2021
10 mins read

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ተቋማቱን ሪፎርም በማድረግ ፤ በአዲስ መልክ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ የህዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችል ብቃት ያለው ኃይል እየገነባም ይገኛል፡፡

ባለፉት ዓመታትም ሆነ በቅርቡ በተደረገው የህግ ማስከበር የህልውና ዘመቻ ላይ የክልላችን የፀጥታ መዋቅር በህዝባችን ላይ የተቃጣውን ጥቃት በመመከት ፣ በማጥቃትና በማክሸፍ አኩሪ ገድል ፈጽሟል፡፡

በዚህም ምክንያት ከምንጊዜውም በላይ ክልላችን የተቃጡበትን ጥቃቶች በአኩሪ ድል መክቶ ህዝባችን በሰላም ተረጋግቶ የሚኖርበትና ሰላማዊ የሆኑ ዜጎች ሁሉ በነጻነት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት ሰላማዊ ክልል እንዲሆን አድርጓል፡፡

በክልላችን ውስጥ አልፎ አልፎ በአንዳንድ እኩያን ተንኳሽነት የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት በህዝባችን ውስጥ ለዘመናት አብሮ በኖረው ሰላማዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ እንዲፈቱ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ከወጣቱና ከመንግሥት መዋቅር ጋር በጋራ በመሆን የሚፈታበት ሥርዓትም ያለ ነው፡፡

በመሆኑም በህዝቡ ፣ በአመራሩና በጸጥታ መዋቅሩ ጥምረት የትህነግ ቅሪቶች እንዲሁም የትህነግ ተላላኪ የሆኑ ኦነግ ሸኔና መሰሎቹ በየቦታው የሚፈጥሩትን ትንኮሳዎች ሁሉ በአስተውሎትና በሰከነ የትግል ሥልት እያሸነፍን ህዝባችን የሰላም አየር እየተነፈሰ ከድህነት ለመውጣትና ኑሮውን ለማሻሻል መደበኛ ህይወቱ ላይ አተኩሮ የሚሰራበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

የአሁኑ ግጭት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች የተፈጠረ ሲሆን ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ጅሌ ጥሙጋ ላይ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት አንድ ሰው ህይወት ህልፈትን ምክንያት በማድረግ የተቀሰቀሰ ነው፡፡ በግለሰቦች መካከል የነበረውን ግጭትና የደረሰውን ሞት ምክንያት በማድረግም በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቅ ተፈጽሞ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የሆኑ አካላት በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ ከዓርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም. ጀምሮ አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡

የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ህዝቦች ለዘመናት በሰላም የኖሩና እየኖሩ ያሉ መሆኑ እየታወቀ ሀገር በሰላም ውላ እንዳታድር የሚፈልጉት አንዳንድ ተላላኪዎች በንጹሐን ላይ የፈፀሙት ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው፡፡

በዚህ ጥቃት እጅግ ክቡር የሆነው የዜጎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረትም ወድሟል፡፡ ለጠፋው ህይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመትም የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡

ይህ ጥቃት የተፈጸመው የክልላችን የፀጥታ መዋቅር ህግ በማስከበር የህልውና ዘመቻው ላይ ትኩረት እድርጎ እየተንቀሳቀሰ በሚገኝበት ወቅት ላይ ነው። በተለይም ክልላችን ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ተቋርጦ የቀረው የትህነግ ርዝራዥ የሚተነኩሰውን ግጭት ለመከላከል እቅስቃሴ እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ነው።

ይህን ምክንያት በማድረግ በአጣየና አካባቢው ፀረ ኢትዮጵያ እና ሀገር አፍራሽ የሆኑ ኃይሎች ከዚህም ከዚያም ተቀናጅተው የክልላችን ህዝብ እረፍት ለመንሳትና ሀገር ለማተራመስ እያደረጉት ያለ አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን የክልሉ መንግሥት በሚገባ ይገነዘባል፡፡

በመሆኑም የክልሉ መንግሥት ይህ ወንጀለኛ ቡድን በንጹሃን ላይ እየፈፀመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ጥቃቱ ከጀመረበት ሰዓት ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠርና ንጹሐን ዜጎችን ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ እየሠራ ይገኛል፡፡

በአጣየና በአካባቢው የተፈጸመውን ዝርዝር ጥቃት፣ የደረሰውን ሰብአዊና የንብረት ጉዳት መንግሥት በፍጥነት መረጃውን አጣርቶ ለህዝቡ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

የክልሉ መንግሥት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በንጹሐን ላይ ለደረሰው የህይወት መስዋእትነትና የንብረት ውድመት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በድጋሜ እየገለጸ አጥፊ የወንጀለኞችን ቡድንና በድርጊቱ የተሳተፉት ተባባሪ አካላትን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለህግ የሚያቀርብ መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ይህ ጥቃት በተፈጸመበት አካባቢም ሆነ በሌሎች የክልላችን አካባቢዎች የትህነግ ርዝራዦችም ሆኑ የትህነግ ቅሪት ተልእኮ አስፈጻሚና ፈጻሚ የሆኑ ኃይሎች የፈጸሙትንና የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመመከት ህዝባችን ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል፡፡

እነዚህ ኃይሎች እድሉን ካገኙ ኢትዮጵያን ለማፍረስም ሆነ ለማተራመስ በክልላችንና ከክልላችን ውጭ በሚኖረው ህዝባችን ላይ አሰቃቂ ጥቃቶችን ለመፈጸም እንደማያመነቱ ደጋግመን ተመለክተናል፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች የተፈጠረውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በክልላችን ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ግጭቱን ለማባባስ ጥረት ሲያደርጉ ታዝበናል። እነኝህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የክልሉ መንግሥት በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።

ስለሆነም መላው ህዝባችን ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንድነት ለሰላማችን በጋራ የምንቆምበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ተገንዝቦ በየትኛውም አካባቢ ለፀጥታው ስጋት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥመው ለሚመለከተው የመንግሥት አመራርና የፀጥታ መዋቅር መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም

ባሕር ዳር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop