የኦነግ ሥልጣን የመያዣ ስልቶችና ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅዱ – ከሚክያስ

ኦነግ ማነውኦነግ – በጀግናው፣ ታታሪውና ሃገር ወዳዱ ኦሮሞ ሕዝብ ስም አዲስ አበባን ፊንፊኔ ካደረገ በኃላ ኢትዮጵያ መፍረሷን ለማወጅ የሚጠባበቅ ኃይል ነው። ኦነግ የብዙ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ማዕከላዊ ኃይል ሲሆን – ሸኔ ደግሞ ድርጅቶቹ ባንድነት ደምመላሽ” የሚሉት ተዋጊ ኃይላቸው ነው። ኦነግ – ስልቱ – ጠንካራዋን ኢትዮጵያ አዳክሞ አዳክሞ በለስ ከቀናው እሚኒልክ ሃውልት ሥር ተሰባስቦ ነፍጠኛ ይውደም” “- ራስ ጎበና ይውደም” – ካለ በኋላ መርካቶን አገምሳ፣ ፒያሳን ቢርቢሮስ ጎሮ፣ ካዛንቺዝን ቀርሳ፣ ሰንጋ ተራን ገርቢ፣ እንጦጦን ድልድላ፣ አራት ኪሎን ጨፌ አካራ፣ ሽሮ ሜዳን ሙጃ፣ ወዘተ፣ ለማለት ነጋ ጠባ የሚያልም ድርጅት ነው ። 

የለሚ ስልት

ኦነጎች የለሚ ስልት” የሚሉት የኦሮሞና አማራ ህብረት የነበረውን – ኦሮማራን –  ነው። ኦሮማራ ወያኔን ለመጣል አማራን ጊዜአዊ ወዳጅ አድርጎ የመያዝ ስልት እንደነበር የታወቀው ዶክተር ለማ ከአደባባይ ሲርቁ፣ ከመደመር ዓላማ ጋር ሲጋጩና የብልጽግናን መመስረት ሲቃወሙ ነበር። ታጋይ ለማ ብዙዎች ሸወዱን” እያሉ ሲያሟቸው ቆፍጠን ያለ መልስ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያን ለኔ ቀብድ የሠጠኝ አለ እንዴ?” በማለት ነበር ተሰብሳቢውን ያሳቁት። አቶ ሽመልስ እዚህ የደረስነው አወዛግበን ወይም አሳምነን ነው” ያሉ ዕለት የኦሮማራ ድብቅ አካሄድ ገሃድ ወጣ። በርካቶች የጥንቃቄ እርምጃ የወሰዱት በግልጽ ከሚናገሩት ካቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር በኋላ ነው። አቶ ሽመልስ ወድያና ወዲህ አይሉም። እውነቱን ፍርጥ አድርገው ይናገራሉ። የሠበሩንን ሠብረናቸው ሬቻን ፊንፊኔ ላይ አክብረናል” በማለት ቁርጡን ሲናገሩ የአዲስ አበባ ልጆች ይህች ባቄላ ያደረች እንደሆን አትቆረጠምም” ብለው እስኬውን የሙጥኝ አሉ። አብዛኛዎቹ የቀድሞ ኦሆዴዶች የዛሬዎቹ ኦዴፓ ብልጽግናዎች የፕሮቴስታንት ኃይማኖት ተከታዮች ናቸው። አዲሱን የሬቻንና ፕሮቴስታንታዊነት ውሁድ ቀኖና ግን እስካሁን አላስረዱንም።

ዶክተር አብይን ደካማ ማድረግ

ኦነግ ቀዳሚ ስልቱ ዶክተር አብይን ደካማ ማድረግና የመምራት አቅመ አሳጥቶ እንዲቀመጡ ማድረግ ነው” ይላሉ አንዳንድ የፖለቲካ አዋቂዎች። ኦነግ ጥቂት የማይባሉ አባሎች በብልጽግና ውስጥ አሉት። ብዙ ጨዋና ሥራውን አክባሪ ቢኖርም በብላክ ሌብል ውስኪ እጆችን መታጠብና ከትናንሽ ልጃገረዶች ጋር አሼሼ ገዳሜ የሚያስጨፍረውን ወያኔያዊ እርኩስ ባህልን እየተጋቱ ካደጉ ከሕወሃት ዘመን ኦህዴዶች አዕምሮ ውስጥ ሙስናንና መዝናናትን በቶሎ ማስቀረት አይቻልም። ሙስና፣ ራስ ወዳድነትና አሸሼ ገዳሜ – አስተዳደርን ያቆሽሻሉ። አስተዳደሩ ሲቆሽሽ ዶክተር አብይ ይደክማሉ።

የኦነግ የዳቦ ስም

ኦነግ – ግማሽ ምዕት ዓመት ያስቆጠረ ድርጅት ነው። እንደ እድሜው ብዛት ሥራ አልሠራም። ገና ትላንት ነው መላ የዘየደው። ፖለቲከኞቹ ሠላማዊ ታጋይ መስለው ፊንፊኔ እሚሏት አዲስ አበባ ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ሲዝናኑ፣ ሲሰበሰቡ፣ የተጣሉ እየመሰሉ ሲሻሻሩ – የተዋደዱ እየመሰሉ ሲሿሿሙ – ፎቶ ሲነሱ – ሥራውን የሚሰሩላቸው ሁለት ኃይሎች ናቸው። አንደኞቹ ብልጽግና ውስጥ ያሉ ኦህዴድኦነጎች ከአራት ኪሎ ሲሆን ሌላኛው እጫካ ያለው እነግሸኔ ነው። አባ ቶርቤና ቄሮ በአራት ኪሎና ጫካው መሃል ያሉ ተወርዋሪ ኃይሎች ናቸው። ሸኔ – የኦነግ የዳቦ ስም ነው። ከሃምሳ ዓመት መዋተት በኋላ ይህን መላ ያገኙት ከኤርትራ ሲመለሱ መቀሌ ላይ ጠብቆ ካነጋገራቸው ስብሃት ነጋ ነው። የትህነግ ወላጅ አባት የሆነው ስብሃት ከአስመራ ሲመለሱ ኦነግን በጉዲፈቻ ልጅነት አቅፎ ያዘው። ከአብራኩ የወለደው ወያኔም ሆነ የጉዲፈቻ ልጁ ኦነግ ግን በመከራው ጊዜ አልደረሱለትም። በመከራው ጊዜ እስከ ባለቤቱና እህቱ ተሸክመው አውርደው የታደጓቸው የአማራ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት ናቸው።

ተረኝነት

ኦነግ – ፊንፊኔ ብሎ አውጆ ሥልጣን ከመያዙ በፊት ሥራ ላይ እያዋለ ያለው ቀዳሚው ስልት ወይም የሥራ ልምምድ ተረኝነት” ይባላል። አማራ ሶስት ሺህ ዓመት ገዝቷል፣ ትግሬ ሃያ ስምንት ዓመት ገዝቷል፣ ተራው የእኛ ነው” የሚለው የተረኝነት ቦለቲካ ከየት እንደመጣ አይታወቅም። ግን መሬትን በመቸብቸብ፣ ገንዘብ በመዝረፍ፣ ሥልጣን ካለችሎታ በመያዝ – የሚተገበረው ተረኝነት ለነገ የሚቀመጥ አበሳ ነው። በኃይለሥላሴ ዘመን እኮ ሥልጣን በትምህርት ችሎታ ነበር የሚለካው። በደርግ ዘመን የነበሩት እውቅ የኦሮሞ ልጆች ከፍተኛ ቦታ የያዙት በእውቀታቸው ነበር። በንጉሡም በደርግም ዘመን ቁልፍ ቦታ ላይ የነበሩት የኦሮሞ ምሁራን ለዕይታ እኮ አልነበረም ወንበሩን የያዙት በእምቅ ችሎታቸውን አስተዳደርን ሊተገብሯት እንጂ።

የአማራን ሥነልቦና መጉዳት

ኦነግ አንዱ ስልቱ ብልጽግና ውስጥ ያሉ ተረኞችን እየተጠቀመ የአማራን ሥነልቦና መጉዳት ነው። አማሮች ሲፈናቀሉና ሲገደሉ ዝም የሚሉት ብልጽግናዎች ይባስ ብለው የሞቱትን እንኳን ክብር ነስተው ከባህል ውጭ በግሬደር እያፋፈሱ ጉድጓድ ጥለዋል። ኦነግ አማራን አሳዝኖ ለማሸማቀቅ ይፈልጋል። ይህ ስልት ግን አይሰራም። ነገ ዋጋ ያስከፍላል። ግልጽ ወረራ፣ ልጃገረዶችን ማገትና ደብዛ ማጥፋት፣ ጅምላ ግድያና ማፈናቀል፤ ወዘተ፣ – ፍርድ ከላይ የመጣ ዕለት መደበቅያም መከለያም የለውም።

ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ ስትደፈር ዝም ማለት

የኦነግ ሌላኛው ስልቱ ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷ ሲደፈር ብልጽግና ውስጥ ባሉ አባሎቹ እየታገዘ እርምጃ እንዳይወሰድ ማድረግ ነው። ኢጣልያ ለወረራ ስትመጣ አሁን ግን በእግዚአብሄር ረዳትነት አልምረውም” ብለው ነው ሚኒሊክ ሕዝቡን ክተት ያሉት። ሶማልያ ምስራቅ ኢትዮጵያን ለመያዝ ስትጣደፍ ታፍራና ተከብራ የኖረች እናት አገር በአዲሱ ትውልድ መዳፍ ሥር ሆና አትደፈርም” ብለው ነው ኮሎኔል መንግሥቱ ሶስት መቶ ሺህ ሚሊሽያ እንዲሰለጥንና እንዲከት ያደረጉት። ዛሬስ የግብጽ ግመል የሆነችው አቅመ ቢሷ ሱዳን ድንበር ተሻግራ የጎንደርን መሬት ስትይዝ ብልጽግናዎች ለምን ይሆን አመራር መስጠት የተሳናቸው? “ተነስ ሃገርህ ተደፍራለች” ማለት አቅቶ ነው ወይንስ የአማራን ሥነልቦና ለመጉዳት?

ኢትዮጵያን የነካ ዋ!

ኦነግሸኔ በበርካታ አካባቢዎች ጥቃት እያደረሰ ነው። ይባስ ብሎ ትላንት ከደብረብርሃን ከተማ በማትርቀው አጣዬ ላይ ወረራ ፈጽሞ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል። ሸኔ ከባድ መሳርያ ይዞ አጣዬን የከበበው የአማራ ልዩ ኃይል ቦታውን መልቀቁን መረጃ ከደረሰው በኋላ ነው። ወያኔ በተደመሰሰበት ሃገር ሸኔ ይህን ያህል አገር ማስጨነቁ አስገራሚ ነው። ለመሆኑ ወያኔን የደመሰሰው ያ – ትልቅ ኃይል – ኦነግሸኔ አቅቶት ነው ወይንስ ከላይ የጠቀስኳቸው ምክንያቶች በብርቱ እየተተገበሩ?

በኢትዮጵያ ላይ መቀለድ ወይንም መቆመር እጅግ ዋጋ ያስከፍላል። ኦነጎችም ሆነ በብልጽግና ውስጥ የመሸጋችሁ ተረኞች፣ አባ ቶርቤም ሆነ ኦነግሸኔ – ኢትዮጵያ ቀና ያለች እንደሆነ ማምለጫ የላችሁም። ብልሹ አስተዳደር ያሳመማትንና ያዳከማትን ኢትዮጵያን መናቅ አይበጅም። ኢትዮጵያ ጠላትዋን በቆፈረው ጉድጓድ መልሳ እንደምትቀብር ደጋግማ – ደጋግማ አሳይታለች። ብዙ መናገር ሳያስፈልግ በወያኔው አባት በስብሃት ላይ የደረሰው ውርደትና ውድቀት እግዚአብሄር ፈቅዶ ለትምህርታችን ያደረገው ነው። አምላክ ቢፈልግ ኖሮ እሱም እንደ ወለደው ልጁ፣ ስዩም መስፍን፣ አባይ ጸሃዬና አስመላሽ ሞቶ በድኑ እንዲታይ ያደርግ ነበር። ስብሃትን እንዲያዝ ያደረገው ፈጣሪ እንድናስተውል ነው። ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በነሱ ላይ የደረሰው በማንም አይድረስ” በማለት – ከሮም አወዳደቅ ሺህ ጊዜ የገዘፈውን የወያኔን ውድቀትና ውርደት – ባጭር ቃል ገልጸውታል። በርካታ ሮኬቶችና ከባድባድ መሳርያዎች የታጠቀ፣ ለሶስት አስርት ዓመታት ስንቅና ትጥቅ ያከማቸ፣ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ግዙፍ ምሽጎች የቆፈረ፣ በመገናኛ መስመሮች ላይ ሻጥር እንዲሁም የሳይበር ጥቃት መፈጸም የቻለ፣ እንደ ተራራ የተቆለለ ገንዘቦች ያሉት፣ መከላከያ ሠራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት በማድረግ የኃይል ሚዛን ያካበተ፣ ወዘተ፣ – ወያኔ – በሶስት ሳምንት ውጊያ መደመሰሱ ከእግዚአብሄር አይደለም ትላላችሁየትላንት ቅንጡዎች መጮህ አንሶባቸው አስፋልት ለአስፋልት ቢንከባለሉ ትህነግ እስከ ወድያኛው አሸልባለች። ትህነግ ትቢያ እንጂ ታሪክ አይደለችም።

ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የምትዳክሩ ሁሉ – እዚያ ማዶ – ተመልከቱ – ፊት ለፊት – ይታያል። ያን እየለበለበ፣ እየፈጀ፣ እያቃጠለ የሚገሰግሰውን ሰደድ እሳት መቋቋም አትችሉትም። እባካችሁ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የወጠናችሁትን ሴራ እርግፍ አድርጋችሁ ትታችሁ ዛሬውን ንሥሃ ግቡ። ኢትዮጵያ መሃሪ ነች። እኔ ነግሪአችኋለሁ፣ የምችለውን አድርጌአለሁ፣ ከዚህ በኋላ ውርድ ከራሴ – አይቆጨኝም።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop