March 20, 2021
22 mins read

ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ የኢትዮጵያና የህዝቧ ዋና ጠላቶች ናቸው!!! – መሰረት ተስፉ

supporter

ፍትሃዊ በሆነ ህግ የተከለከለ እስካልሆነ ድረስ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃሳብ ብሎም ተግባር የመደገፍ ካልሆነም የመቃወም መብት አለው። ቢፈልግ ቅዱሳንን ካልፈለገ ደግሞ ሃጥዓንን የመደገፍና የመቃወም ብቻ ሳይሆን የማምለክ ወይም የመከተል መብቱ ተፈጥሯዊ ነው። ስለዚህ ማንም ሰው የፈለገውን  ሃሳብ የማወደስ ሳይፈልግ ሲቀር ደግሞ የመንቀፍ ፍላጎቱን እውን ማድረግ ይችላል። ይህ መብት ውጤታማ ይሆን ዘንድ ግን ከጭፍንነት መራቅ አስፈላጊ ይሆናል። ጭፍንነት ደግሞ በድጋፍም በተቃውሞም ሊገለፅ ይችላል።

ጭፍን ድጋፍም ይሁን ጭፍን ተቃውሞ የሚነሱት ከአመክንዮ (Logic) ሳይሆን ከስሜት (Emotion) ነው። በስሜት የሚነዱ ሰዎች ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ግምት ውስጥ የሚያስገቡት ሃሳብን፣ ርዕዮተ-ዓለምን፣ የማስፈፀም ብቃትን ወይም ክህሎትን አይደለም። እንደዚህ አይነት ሰዎች የድጋፋቸውም ይሁን የተቃውሟቸው ማጠንጠኛ ሃሳብ ወይም ተግባር ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ለምደገፍም ሆነ ለመቃወም ሃሳቡን ያመነጨው/የተናገረው ወይም ተግባሩን የፈፀመው ማነው በሚለው ጉዳይ ላይ ያተኩራሉ። የሚደግፉትን ወይም የሚቃወሙትን ሰው መለኪያዎቻቸው ደግሞ ዘር/ብሄር፣ ቋንቋ፣ ተክለ ሰውነት፣ ጎጥ፣ መንደር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ወግ፣ልምድ እና ሌሎችም መመዘኛዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ባጠቃላይም በስሜት የሚነዳ ሰው የሚደግፈውም ይሁን የሚቃወመው በራሱ አእምሮ አገናዝቦ፣ አውጥቶና አውርዶ ሳይሆን ሃሳቡን ያነሳውና ተግባሩን የፈፀመው ማነው የሚለውን ሰምቶ ወይም አይቶ ነው። የዚህ አይነት ሰዎች የሚቀላቸው እንደ “መንጋ” መንጎድ ነው። በስሜትና በመንጋ የመንጎድ ዝንባሌና ባህሪ በግልፅ የሚያሳየው ደግሞ ሰው በተፈጥሮ የተቸረውን የማመዛዘኛ አእምሮ በሚገባ ሊጠቀምበት አለመፈለጉን ነው። እንዲህ አይነት ባህሪ እዛው ሳለም በራስ አለመቆምንና ለራስ ክብር ማጣትን ቁልጭ አድርጎ ሊያሳይ ይችላል።

ከላይ ከተቀመጡት ቁምነገሮች አንፃር ሲታይ አንድ በጭፍን የሚደግፍ ሰው የተፈፀመው ድርጊት የቱንም ያህል አስከፊ ገፅታ ቢኖረው ምክንያት አፈላልጎ ከመደገፍ ወደኋላ የማይል መሆኑን ነው። ጭፍን ደጋፊ የሆነ ሰው የሚደግፈው ተራ ጥፋትን ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ከባድ የሆነን ወንጀል ሳይቀር ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ ፕሬዚደንት ትራምፕ በመጀመሪያው ምርጫ ውድድር ላይ በነበሩበት ወቅት “I could stand in the middle of 5th Avenue and shoot somebody, and I wouldn’t lose voters.” ብለው ነበር።  ይህ የትራምፕ አባባል በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲተረጎም “አምስተኛ ጎዳና መሃል ላይ ሆኘ ሰው ላይ ብተኩስ ድምፅ የሚሰጡኝ መራጮቸ እኔን ከመምረጥ ወደኋላ አይሉም” የሚል ነው። ከዚህ የትራምፕ ንግግር ጭፍን ድጋፍ ምን ያህል ምክንያት የለሽ፣ አደገኛና አጥፊ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። ከዚሁ ጋ ተያይዞም ወ/ሮ መላና ትራምፕ በባለቤታቸው በዓለ ሲመት ላይ ያደረጉት ንግግር ከወ/ሮ ሚሸል ኦባማ የተኮረጀ ነው የሚል በማስረጃ የተደገፈ ክስ ሲቀርብ ድርጊቱን አውግዞ ከመቆም ይልቅ እነዚሁ የትራምፕ “ጭፍን ደጋፊዎች” ክሱን ለማጣጣልና ለመካድ ያልፈነቀሉት ደንጋይና ያላቀረቡት ምክንያት እንዳልነበረ ሰምተናል፤ አንብበናልም።

በጭፍን የሚቃወም ሰውም እንዲሁ የሚቃወመውን ሰው ሃሳብ ወይም ስራ ማጣጣሉ አይቀርም። በጭፍን የሚቃወም ሰው ልክ እንደጭፍን ደጋፊ ሁሉ ተቃውሞውን የሚያቀርበው የሃሳቡን ምንነት ተገንዝቦና አውቆ ሳይሆን እሱ የሚቃወመው ሰው ወይም አካል በመሆኑ ብቻ ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች የሆነ ያልሆነ ምክንያት በመደርደር ሊሰራ የታሰበው ስራ እንዳይከናወን ወይም የተሰራው ስራ እንዲቀለበስ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የፈለቀው ሃሳብ ወይም የተሰራው ስራ በማንኛውም መመዘኛ የተሟላ እያለም ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ስንመጣም በጭፍን የመደገፍና የመቃወም ዝንባሌዎች በስፋት አሉ ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ብዙዎቻችን ገዥውን ፓርቲ ወይም መንግስትን የምንደግፈው መልካም ነገር ሲሰራ ብቻ ሳይሆን መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ሲፈፅምም ጭምር ነው። ለምሳሌ ባለፉት ሶስት አመታት መንግስትና ገዥው ፓርቲ በርካታ ስህተቶች እንደፈፀሙ መንግስት ራሱ የሚክደው አይመስለኝም። ጭፍን የሆኑ ደጋፊዎች ግን አሁንም መንግስትን ብፁዕ ነው ብለው ሲከራከሩ ይደመጣሉ።

ገዥውን ፓርቲ ወይም መንገስትን የምንቃወም ከሆነ ደግሞ የሚታየን መልካም ያልሆነው ብቻ ነው። ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት የፈፀማቸው ስህተቶች በርካታ ቢሆኑም ያከናወናቸው በጎ ተግባራት እንዳሉም መካድ አይቻልም። በጭፍን መቃወም የተጠናወታቸው ሰዎች ግን የመንግስትን በጎ ተግባራት ሊደግፉ ቀርቶ አቃቂር እያወጡ ሊያጣጥሉ ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ነው።

የጭፍንነትን መርህ አልባነት ከተወሰኑ ጉዳዮች ጋ አያይዠ ለምሳየት እሞክራለሁ። አደኛው አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመ ነው።  ይህ  ጉዳይ የተፈፀመው ከአንድ አመት በላይ ቢሆነውም ስህተቱ ጉልህ ስለሆነ የጭፍን ደጋፊዎችን አይን ያወጣ ስህተት ለማሳየት ልጠቀምበት ወድጃለሁ። እንደሚታወቀው ቡራዩ ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋና መፈናቀል ተከትሎ ቡራዩና አዲስ አበባ ላይ በርካታ ሰዎች ታሰረው እንደነበር በተለያዩ መንገዶች ሰምተናል። በተለይ አዲስ አበባ ላይ ወጣቶች እየታፈሱ ለፀባይ ማረሚያ ስልጠና ጦላይ ወታደራዊ ካምፕ እንደገቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በልበ ሙልነት ገልፀዋል። ይህ አሰራር በየትኛውም የህግ መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይደለም። በኢትዮጵያ ህግ በማንኛውም ሰው ላይ የእስር፣ የማህበራዊ ግልጋሎት ብሎም የፀባይ ማረምያ ስልጠናና የመሳሰሉ ቅጣቶች እንዲሁም የእርምት እርምጃዎች ሊወሰኑ የሚችሉት በፍርድ ቤትና በፍርድ ቤት ብቻ ነው። በዚህ ሂደት ፖሊስ የተሰጠው አንዱ ስልጣን የፍርድ ቤት ትእዛዝ በማውጣት እስር መፈፀምና በ48 ሰዓታት ውስጥ የወንጀል ሁኔታውን አጣርቶ ፍርድ ቤት ማቅረብ ነው። ሌላው የፖሊስ ህጋዊ ስልጣን የፍርድ ቤት ትእዛዝ ባይኖረውም ወንጀል ለመከላከል አስፈላጊ ነው ብሎ በተጠራጠረበት ወቅት ተጠርጣሪውን በእስር ማቆየት ነው። ፖሊስ በዚህ ሁኔታ ያሰረውን ተጠርጣሪ አሁንም በ48 ሰአት ውስጥ ፍርድ ቤት ማቅረብ ግዴታ አለበት። ከዚህ ውጭ ፖሊስ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ካልሆነ በስተቀር ሰውን ከ48 ሰዓት በላይ ለሆነ ጊዜ የፀባይ ማረሚያ ስልጠና እሰጣለሁ ብሎ መንቀሳቀስ ህግመንግስታዊዉን የሰዎች በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ከመጣሱም አልፎ ህገወጥነቱን በግልፅ ያሳየበት ድርጊት ነው።

ይህን ጉዳይ እዚህ ላይ ያነሳሁት ፖሊስ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የፈፀመውን በጅምላ የማጎርና ብሎም የፀባይ ማረሚያ ስልጠና እሰጣለሁ የሚል እንቅስቃሴ ኢህገመንግስታዊነት ለመግለፅ ሳይሆን ይህን ህገመንግስት የጣሰ ድርጊት በርካታ ሰዎች በጭፍን ሲደግፉ እንደነበር ለማሳየት ነው። በዚህም መሰረት እገታው ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ በነበሩት ተከታታይ ጊዚያት የአዲስ አበባ ፖሊስ የሄደበት መንገድ ትክክል ነው ብለው የጮሁ ደጋፊዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አልነበረም። ይህ የመገናኛ ብዙሃንንም በተለይ የመንግስት የሆኑትን  ይጨምራል። ምክንያቱም ብዙዎቹ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት የወጣቶቹን ያለአግባብ መታሰር ሳይሆን ከእገታው የተለቀቁበትን ሂደት ነበር። እነዚህ በጭፍን የሚደግፉ ሰዎች ድርጊቱ ህገመንግስቱን የጣሰ መሆኑን ቢቀበሉም አሁን ያለውን ስርዓት በጭፍን ስለሚደግፉ ብቻ ህገመንግስታዊ ጥሰቱ በለውጥ ሂደት ላይ የተፈፀመ ስለሆነ ተቃውሞ ሊገጥመው አይገባም ብለው እስከመከራከር ደርሰው ነበር።  ለነዚህ ጭፍን ደጋፊዎች ያስጨነቃቸው በአንድ ወይም በሌላ መንገድ  የህግ ልዕልና ባለመከበሩ ምክንያት በህዝብና በሃገር ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ሳይሆን እንደግፈዋለን የሚሉት ስርዓት ትችት ላይ መውደው ነው።

ጭፍንነት በሃገር ደህንነት ጉዳይ ላይ ሳይቀር ሚዛናዊ አስተዋፅዖ  እንዳይኖር ያደርጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሃገርን ደህንነትና ፀጥታ የሚመለከቱ ጉዳዮች ተቋማዊ መልክ በያዘ መልኩ እንደማይከናወኑ የሚያመላክቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ። ለምሳሌ በኤርትራና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ያለውን ስምምንት በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ያለው የተወካዮች ም/ ቤት እንኳ የሚያውቀው አይመስልም። ትግራይ ውስጥ ችግር ከመፈጠሩ ቀደም ብሎና ከዚያ በኋላ ከሱዳን ጋ የነበረውን ስምምነትም ተወካዮች ም/ቤትም ሆነ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነው ህዝቡ የሚያውቁት ነገር እንዳላቸው እስካሁን ማስረጃ የለኝም። እኒህን የመሳሰሉ ተቋማዊ ያልሆኑ አሰራሮች ያሳሰባቸው አንዳንድ ሰዎች ስጋታቸውን ሲገልፁ የመንግስት ጭፍን ደጋፊፊዎች በበኩላቸው ስጋት ያደረባቸውን ቅን ሰዎች አፍ ለመለጎም የማያደርጉት ዘመቻ እንደሌለ እየታዘብን ነው።

በሌላ በኩል አሁን ያለውን መንግስትና ገዥ ፓርቲ በጭፍን የሚቃወሙ ሰዎች ሃገሪቱ ውስጥ የሚሰሩትን መናፈሻዎችና የቱሪዝም መስህቦች ሲነቅፉ ማየት የተለመደ ሆኗል። በእርግጥ ሃገሪቷ ካሉባት ውስብስብ የሆኑ ችግሮች በመነሳት የመናፈሻ ቦታዎች ግንባታ ቅድሚያ ሊሰጣቸው አይገባም ብሎ መተቸት ችግር ነው ብየ አላስብም። ነገር ግን መናፈሻዎችን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በጥቅሉ መንቀፍ ግን በጭፍን ከመቃውም አባዜ የሚነሳ ጭራቃዊ የሆነ አስተሳሰብ ነው የሚል እምንት አለኝ።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የጭፍንነት ሰለባ ከመሆን አልዳኑም። ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚያራምዱት ርዕዮተ-አለምና አስተሳሰብ መዝኖ ድምፅን መስጠት ወይም መንፈግ ሲቻል ከጭፍን ተቃውሞ በመነሳት  ማዋከብና ጉዳት ማድረስ ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ነው። ለምሳሌ ኢዜማና አብን ኦሮሚያ ውስጥ ገብተው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እየተቸገሩ እንዳሉ የሚገልፁባቸው ሁኔታዎች በርካታ መሆናቸውን እየታዘብን ነው። በተለይ ኢዜማ ኦሮሚያ ውስጥ በደረሱበት ችግሮች ምክንያት እጩዎችን እንደማያስመሰግብ የገለፀው በቅርቡ ነበር። አማራ ክልልም ኢዜማ ይገባና ወዮለት የሚሉ አፋኝ ሰዎች እንዳሉ በተለያየ መንገድ እየሰማን ነው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው ሌላው የጭፍንነት አስከፊ ገፅታ ጭፍን ተቃውሞንና ጭፍን ድጋፍን የሚቃወሙ ቅን፣ ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊና ገለልተኛ የሆኑ ሰዎችን ጭምር የሚያቀጭጭ አረመኔያዊ ባህሪ መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ አቶ ልደቱ አያሌው ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። እንደሚታወቀው አቶ ልደቱ የተቀዋሚ ፓርቲ መሪ ሆነው ለረጅም አመታት ሰርተዋል። በነዚህ ጊዚያት ሊተቹባቸው የሚችሉ በርካታ ባህሪያት እንዳሏቸው ብገነዘብም የኢህአዴግን ጥፋቶች ያለምንም መደራደርና ርህራሄ እያብጠረጠሩ እያወጡ በአደባባይ አሳይተዋል። በአንፃሩ ኢህአዴግ ጥሩ ሰርቷል ብለው ባመኑባቸው ሁኔታዎች ላይ ደግሞ ግልፅ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። አሁንም ያላቸው ፖለቲካዊ አቀራረብ ከቀድሞው ጋ ተመሳሳይ ነው። ይህ የአቶ ልደቱ አካሄድ በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ ስልጡን የፖለቲካ ሂደቶች የሚመደብ ነው ብሎ መናገር አያሳፍርም። ይሁንና የአቶ ልደቱ ምክንያታዊ አካሄድ ያስከፋቸው ጭፍን ተቀዋሚዎች ረቂቅ በሆነ መንገድ በመዶለት አቶ ልደቱ ከፖለቲካ እንዲርቁ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ከዚህ ሁሉ እንደሰው የሚያሳዝነው ግን አቶ ልደቱ በተለያየ መንገድ ፍትህ ሲጓደልባቸውና በባሰ ሁኔታ ደግሞ ውጭ ሄደው ህክምና እንዳይከታተሉ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ኢሰብዓዊ የሆነ ክልከላ ሲፈፀምባቸው ከመቃወም ይልቅ በጭፍን ጥላቻ ምክንያት በአቶ ልደቱ ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ግፎች ደግፈው የቆሙ ሰዎች መኖራቸው ነው። በዚህ መንገድ የሚገለፅ ጭፍንነት መርህን ያጓድላል ብቻ ሳይሆን በአቶ ልደቱ ላይ እየተፈፀሙ ያሉት ግፎች ነገ ከነገ ወዲያ በራሳችን ላይ ሊመጡ እንደሚችሉ እንኳ ለመረዳት የማያስችል መሆኑ ነው።

በአጠቃላይ ጭፍን ድጋፎችና ተቃውሞዎች ምክንያታዊ ያልሆኑና በስሜት የሚነዱ ዝንባሌዎች ናቸው። መመሪያቸው የሚያመዛዝን አእምሮ ሳይሆን ልቅ የሆነ የመንጋ (Mob) ህግ ነው። መለኪያዎቻቸውም የሃሳቦችና የተግባራት ልህቀት ሳይሆን ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጎጥ፣ ዝምድናና የመሳሰሉት መመዘኛዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር ጭፍን ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች የሚደግፉትና የሚቃወሙት ሃሳቡን ማን አነሳውና ከየት ተነሳ ብለው እንጅ የተነሳው ሃሳብ ወይም የተሰራው ስራ መጥፎ ወይም ጥሩ መሆንና አለመሆኑን አመዛዝነው አይደለም። እነዚህ ጭፍን የሆኑ ድጋፎችና ተቃውሞዎች እጂግ በጣም ሲበዛ ክብረ ነክ ብቻ ሳይሆኑ አገርንና ህዝብን የሚያመሰቃቅሉ አጥፊ መንገዶች በመሆንቸው የሚያስከትሉትን አደጋ ተረድተን ተዋናዮቹ የተጠናወታቸውን የአስተሳሰብ ጉብጠት ለማቃናት ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል የሚል ሃሳብ አለኝ።

 

ከመሰረት ተስፉ (Meserettesfu4@gmail.com)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Previous Story

አሜሪቃ ሄይቲና ጦቢያ – መስፍን አረጋ

pp 3
Next Story

የኦነግ ሥልጣን የመያዣ ስልቶችና ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅዱ – ከሚክያስ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop