ትግራይ ውስጥ በተመራቂ ተማሪዎች በተፈፀመ ጥቃት፣ 35 ያህል ተማሪዎች ሆስፒታል መጥተዋል። 12 ጉዳት ደርሶባቸዋል

ተመራቂ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አሳፍሮ ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ በነበረ አውቶብስ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ስድስቱ ሲገደሉ ሌሎች መቁሰላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ የአይን እማኞች እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገለፁ።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 11/2013 ዓ.ም አርባ አንድ ወጣት ሴቶችና ወንዶችን አሳፍሮ ይጓዝ በነበረው አውቶቡስ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው አዲ መስኖ በምትባል ቦታ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
ይህንን በተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ አስካሁን የተሰጠ ማብራሪያም ሆነ ስለጥቃቱ ፈጻሚዎች በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
በአውቶብሱ ውስጥ ተሳፍሮ የነበረና ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ትምህርት ተመራቂ ተማሪ፤ በጥቃቱ ስድስት ተማሪዎች ሞተው መመልከቱን እና በሰባት ተማሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ ገልጿል።
ተማሪው ጨምሮም በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል መሆኑን በመግለጽ “እኔም ውስጥ እግሬ ላይ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞኛል” ብሏል።
ቢያንስ ለስድስት ሰዎች መሞትና ከ10 በላይ በሚሆኑት ላይ ለደረሰው ጉዳት ምክንያት የሆነው ጥቃት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ገደማ በትግራይ ክልል ሒዋነ ከተማ፤ ልዩ ስሙ አዲ መስኖ የሚባል አካባቢ መድረሱን በአውቶብሱ ተሳፍረው የነበሩ ተማሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ፕሬዚደንት እና የአገር አቀፍ የተማሪዎች ሕብረት ምክትል ፕሬዚደንት አብረሃለይ አረፋይኔ ከተማሪዎቹ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ለቢቢሲ እንደገለጸው ሒዋነ ከተማ አካባቢ የሰባት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉንና ከ10 በላይ የሚሆኑት ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጧል።
በጥቃቱ ተማሪዎቹን አጅበው ሲጓዙ የነበሩ ሁለት የመከላከያ ሠራዊት አባላትም መገደላቸውን መስማቱን አብረሃለይ ጠቅሶ፤ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ወደ ወልዲያ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ጨምሮ ተናግሯል።
ከጥቃቱ የተረፉ ተማሪዎች ለህክምና ከተወሰዱባቸው ሆስፒታሎች አንዱ የሆነው የቆቦ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን አዲሱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አርብ ምሽት 35 ተማሪዎች ወደ ሆስፒታላቸው መምጣታቸውን አመልክተው ከመካከላቸው 12ቱ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ።
በጥቃቱ ከተጎዱት መካከል ሴቶችም እንደሚገኙበት የገለፁት አቶ ካሳሁን፤ እጃቸው፣ ጭናቸው እና መቀመጫቸው ላይ በጥይት የተመቱ ተማሪዎች መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ነገር ግን የደረሰባቸው ጉዳት ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ብለዋል።
ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታሉ ሕክምና የተደርጎላቸው ተማሪዎች ትናንት እሁድ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሸኘት እንደተወሰዱ ጨምረው ተናግረዋል።
አቶ ካሳሁን በጥቃቱ ህይወታቸው አልፏል ከተባሉት መካከል አስከሬናቸው ወደ ሆስፒታላቸው የገባ፤ አሊያም ጉዳት ደርሶባቸው ከመጡት ውስጥ በሕክምና ላይ ሕይወቱ ያለፈ ሰው አለመኖሩን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ተማሪዎች ከሳምንት በፊት በመቀለ ከተማ በተከናወነው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተሳትፈው ወደ የመጡባቸው አካባቢዎች እተመለሱ የነበሩ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈንቅል የተባለው ስብስብ የሆነውና ህወሓትን በመቃወም የሚታወቀው ቡድን አመራር የነበረው አቶ የማነ ንጉሠ በተመሳሳይ ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈጸመበት ጥቃት ቅዳሜ ዕለት ተገድሏል።
መንግሥት ለአቶ የማነ ግድያ “የህወሓት ርዝራዥ” ያላቸውን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፤ ከግድያው ጋር ተያያዘ ኃላፊነት የወሰደም ሆነ በቁጥጥር ስር የዋለ ተጠርጣሪ ስለመኖሩ ተባለ ነገር የለም።
በአውቶብሱ ላይ ምን ነበር የተፈጸመው?
በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ተስተጓጉሎ በነበረው ትምህርት ምክንያት ሳይመረቁ የቆዩ ተማሪዎች ከሳምንት በፊት በመቀለ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት መመረቃቸው ይታወሳል።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነውና በአውቶብሱ ተሳፍሮ ነበረው ተማሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው እሱና ሌሎች ተማሪዎች ከምረቃቸው በኋላ አስከ ረቡዕ ዕለት ባሉት ቀናት የትምህርት ማስረጃቸውን ተቀብለው ነበር ወደየመጡበት ለመመለስ ጉዞ የጀመሩት።
ሐሙስ ዕለት ጉዟቸውን ሲጀምሩ በሁለት መከላከያ ሠራዊት አባላት ታጅበው የነበረ ሲሆን፤ በመንገዳቸው ላይ ‘አዲጉዶም’ የተባለ ቦታ ሲደርሱ መንገድ ዝግ ነው የሚል ወሬ መሰማቱን ተማሪው ያስታውሳል።
ወደ ሥፍራው ሲደርሱም ወጣቶች መንገድ ዘግተው እንዳገኙና የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ መንገዱን አስከፍተው ጉዟቸውን እንደቀጠሉ ይናገራል።
ተማሪው ጨምሮ እንደሚለው ዕለቱ የየካቲት 11 በዓል ስለነበር በአካባቢው ብዙም እንቅስቃሴ አይታይም ነበር።
ከዚያ በኋላም ከቀኑ 7 ሰዓት ገደማ ‘አዲ መስኖ’ የተባለች ቦታ ላይ ታጣቂዎች እንዳስቆሟቸውና የመከላከያ ሠራዊት አባላቱም ሊያነጋግሯቸው ከአውቶብሱ ሲወርዱ ተኩስ መከፈቱን ገልጿል።
“ጥይቱ ከብዙ አቅጣጫ ነው የሚመጣው፤ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፤ ብቻ ዝቅ በሉ ነው የተባልነው” ይላል።
“በጥቃቱ ዓይናችን እያየ ስድስት ተማሪ ነው ሕይወቱ ያለፈው” የሚለው ተማሪው፤ በአውቶብሱና በሌሎች የተማሪዎቹ መረጃዎችና ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱንም ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ የታጣቂዎች ቁጥር ከ30 እስከ 50 ይደርሳል የሚለው ከጥቃቱ የተረፈው ተማሪ፤ ታጣቂዎቹ “የተረፍነውን ተማሪዎች ናቸሁ” በሚል እንደለቀቋቸው ጠቅሷል።
ከጥቃቱ በኋላም ሌላ መኪና ተሳፍረው ወደ አላማጣ መሄዳቸውንና ከዚያም በመከላካያ ሠራዊት እርዳታ ወደ ቆቦ ሆስፒታል መሄድ መቻላቸውን ተማሪው ለቢቢሲ አስረድቷል።
ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ላይ ክልሉ እንዳይረጋጋ ለማድረግ የሚሞክሩ “የተበተኑ የህወሓት ኃይሎችን” መኖራቸውን መጥቀሱ የሚታወስ ሲሆን ሕዝቡም መጠጊያ እንዳይሰጣቸው ጥሪ አቅርቦ ነበር። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጨምሮም “የተበተኑ” ያላቸው የህወሓት ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ መሸሸጋቸውን ገልጾ “የጥፋት ኃይሎች በመንደሮች እና በከተሞች ውስጥ ተሰማርተው የሕዝቡን ሠላም በማናጋት ወደ ሌላ የከፋ ቀውስ እንዲገባ እየሰሩ ነው” ብሏል።በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ላይ በቀረበውና ከጊዜያዊው አስተዳደር የወጣው ይህ መግለጫ እንዳስጠነቀቀው ፣ ሊወሰድ በሚችለው እርምጃ ሕዝቡ እንዳይጎዳ “የጥፋት ኃይሎቹን አሳልፎ እንዲሰጥ ወይም ለደኅንነቱ ሲል ራሱን ከእነዚህ ኃይሎች እንዲያርቅ” አሳስቧል።በተጨማሪ የክልሉ ነዋሪዎች ከምሽት 12:00 ሰዓት እስከ ንጋት 12:00 ሰዓት የተደነገገውን ሰዓት እላፊ ጨምሮ ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውሳኔዎችን እንዲያከብሩም አሳስቧል።
ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 09/2013 ዓ.ም ለትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል በሚያስተላልፉ መስመሮች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በመላው የትግራይ ክልል የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዳግም መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መስታወቁ ይታወሳል።
ድርጅቱ በክልሉ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የተቋረጠው “የህወሓት ርዝራዦች” ያላቸው ኃይሎች በክልሉ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በፈፀሙት ጥቃት መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የፌደራል መንግሥት በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረው የህወሓት አመራሮችን ከስልጣን መወገዳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የተበታተኑ የሚላቸውን የቡድኑን ታጣቂዎች ተጠያቂ ያደርጋል።
ቢቢሲ
ተጨማሪ ያንብቡ:  እናንተ ደጀን በመሆን ከጀርባችን ሁኑልን እንጂ ወታደራዊ ጥበቡን ለእኛ ተውልን!! ጄነራል አበባው ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share