February 22, 2021
129 mins read

የአገር ወዳድነት ስሜት በጠፋበትና ክህደት በበዛበት አገር ጠንካራ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ መገንባት አይቻልም!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
የካቲት 22፣ 2021ዓ.ም

መግቢያ

ከሞላ ጎደል የአገራችንንም ሆነ የሌሎችን አገሮች የወጣ ውረድ ትግልና እዚህ ደረጃ ላይ በመድረስ እንደማህበረሰብ የመኖርን ሁኔታ ስንመለከት በሁሉም አገሮች ውስጥ አንዳች ዐይነት ስሜት መዳበር ችሎ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም አንዳንድ ከሌሎች አገሮች የተሻልን ነን፣ ግዛታችንንም ማስፋፋትና ህዝቦቻቸውንም ተገዢ ማድረግ አለብን ብለው ወረራ ያካሄዱ ኃይሎችን ተከላክሎ ለመመለስና ተገዢ ላለመሆን የተደረገውን አስቸጋሪ ትግል ስንመለከት በአብዛኛዎች አገሮች ውስጥ አንዳች ዐይነት የአገር ወዳድነት ስሜት መዳበር እንደቻለ እንመለከታለን። ይህ ዐይነቱ የአገር ወዳድነት ስሜት ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን በአንዳንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እንደማህበረሰብ መኖር ሲጀምሩና የአንድነትና የሚያስተሳሰር ስሜት ያላቸው መሆኑን እየተረዱ ሲመጡ ነው።

እንደሚባለው አንድ ማህበረሰብና አገር ዱቄት ተቦክቶና ከተነሳ በኋላ እንደዳቦ በአንድ ቀን ተጠፍጥፎ የሚጋገርና እንደሚበላ ሳይሆን የብዙ ጊዜ ውጣ ውረድ ትግል ውጤት ነው። በአንድ አገር ከሚኖር ህዝብ ውስጥ ሻል ብሎ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ህዝቡን አንድ ላይ እንዲሰባሰብና በስራ-ክፍፍል እንዲደራጅ በማድረግ አውቆም ሆነ ሳያውቅ ለጠቅላላው ህዝብ የሚሆን የአንድነት ስሜት ብቻ ሳይሆን፣ የሞራልና የስነ-ምግባር መሰረትም ይዘረጋል። ማንኛውም ህብረተሰብም ሆነ ህዝብ ቀድሞውን በተደራጀ ስርዓት ውስጥ እንዲኖር ከላይ ወደ ታች በአንዳች ኃይል የተወረወረ ሳይሆን በዚያው ህብረተሰብ ውስጥ በተደረገ ትግልና አንዳንድ በተገለጸላቸው ሰዎች አማካይነት ብቻ ነው እንደማህበረሰብ እንዲኖር ከዝቅተኛ  የኑሮ ወይም ካልተደራጀና ተሰበጣጥሮ ከመኖር ሁኔታ ወደ ተሻለ ሊሸጋገር የቻለው። እንደሚባለውና አንዳንድ መጽሀፍትንም እንዳነበብነውና በደንብ ተገንዝበን ከሆነ ማንኛውም ማህበረሰብ በመደብ ትግል ወይም በጨቋኝና በተጨቋኝ ስርዓት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። በእነዚህ ነገሮች ብቻ የሚገለጽ ቢሆን ኖሮ አንድ ማህበረሰብ ከአዳኝነት ሙያ በመላቀቅ ተሰባስቦ በመኖር በእርሻ ተግባር ላይ በመሰማራት የተሻለ ኑሮ መኖር ባልቻለ ነበር። ከዚያም አልፎ ልዩ ልዩ የማምረቻ መሳሪያዎችን በመስራትና የተለያዩ የሰብል ዐይነቶችን በማምረት የንግድ ልውውጥን ማካሄድ ባልቻለ ነበር። ከዚያም በማለፍ ለስነ ጽሁፍ የሚያገለግሉ ፊደላትን በመቅረጽ ለአንድ ቋንቋ በስነ-ስርዓት መነገርና መጻፍ የሚያስችልን ሰዋስውን ማዳበር ባልቻለ ነበር። ከዚያም በማለፍ ሙዚቃንና ሌሎች ነገሮችን በመፍጠርና በመስራት ከእንስሳ የተሻለ መሆኑን ማረጋገጥ ባልቻለ ነበር።

በአጠቃላይ ሲታይ ከዚህና ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ የመሸጋገርን ሁኔታ ስንመለከት ይህ ይነቱ ዕድገት በተራ የመደብ ትግልና የጨቋኝና የተጨቋኝ ስርዓት ሊገለጽ ወይም ዝቅ ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። በሌላ ወገን ግን የመደብ ተግል የሚባለውና የጨቋኝና የተጨቋኝ ስርዓት የሚባሉት ጽንሰ-ሃሳቦች እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ትክክል ቢሆኑም ስልጣንን የጨበጠው ኃይል በሚያስተዳድረው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከፈለገ በመበዝበዝ ብቻ የራሱን ማንነት ሊያሳይና የበላይነቱን ሊያረጋግጥ በፍጹም አይችልም። ከዚህም በላይ ሁለቱ ጽንሰ-ሃሳቦች በጊዜው ከሚኖረው የማቴሪያልና የንቃተ-ህሊና ሁኔታ በመነሳት ብቻ ነው ሚዛናዊነት ያለው ፍርድ መስጠት የሚቻለው። የንቃተ-ህሊና መዳበርና የማቴሪያል ሁኔታዎች መሻሻል ደግሞ ከገዢ መደብ ውስጥ ብቻ የሚፈልቁ ሳይሆን በገዢው መደብ ውስጥ ካልተካተተውና የህብረተሰብን ሂደት ትችታዊ በሆነ መልክ በሚመለከትና በተገለጸለት ኃይል በሚደረጉ የተጣመረና የማያቋርጥ ትግል አማካይነት ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ በአንድ በኩል ከገዢው መደብ ውስጥ የሚደረግ የቀስ በቀስ ለውጥና፣ ንቃተ-ህሊናው ከፍ ካለው የህብረተሰብ ክፍል የሚደረግ ግፊትና የተቀናጀ ትግል የግዴታ ለአገር ወዳድነት ስሜት መዳበር የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል።

ይህ ዐይነቱ ከዝቅተኛ ወደ ተሻለ የኑሮ ሁኔታ መሸጋገርንና መንግስት የሚባለውን ሁሉንም መልክ የሚያሲዝና የሚያስተሳሰር ነገር ማደግና የመፍጠርን ሁኔታ ስንመለከት ይህ በራሱ በተለይም ስልጣንን በያዙ ኃይሎች መሀከል የተወሰነ የሞራል ብቃትነትንና የአገር ወዳድነት ስሜትነትን ማሳደር ችሏል ማለት ይቻላል። ስልጣንን የያዙ የገዢ መደቦች ከውስጥ ህብረተሰቡን መያዝ ብቻ ሳይሆን ከውጭ የሚመጣባቸውን ቀጥተኛ ወራሪ ኃይል ለመከላከል ሲሉ ወደ ጦርነት ውስጥ የገቡበትን ሁነታ ስንመለከት ከውጭ የሚመጣባቸውን ወራሪ ኃይል መክተው ለመመለስ የሚችሉት ከድርጅታዊ ብቃት ባሻገር የአገር ወዳድነትና በጋራ የመኖርን ስሜት ለማዳበር በመቻላቸው ነው። በዚህ መልክ ከውጭ እየተደጋገመ ወራሪ ኃይል በሚመጣበት ጊዜ ላለመወረርና ተገዢ ላለመሆን የሚፈልገው የገዢ መደብ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው ህብረተሰብም ቀስ በቀስ የአገር ወዳድነት ስሜት መንፈስን በማዳበር አገሩን ይከላከላል ማለት ነው።

የእያንዳንዱ አገር ታሪክ የራሱ የሆነ ልዩ ዐይነት መለዮች ቢኖሩትም አገራችንም ይህንን ዐይነቱን የውጣ ውረድ ጉዞ በመጓዝ ነው ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራት አገር ልትገነባና የሁላችንም መለያ ለመሆን የበቃችው። ይሁንና ግን የታሪክን ውጣ ውረድነት ወይም አስቸጋሪ የሆነውን ጉዞ ለመረዳት የማይችሉ ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ዝቅ ያሉ ኃይሎች ዛሬ ኢትዮጵያ ተብላ የምትጠራው አገር በመስፋፋትና አንደኛው የህብረተሰብ  ክፍል ወይም ብሄረሰብ ሌላውን በማስገደድና ባህሉን በማውደም ብቻ ነው ለመገንባት የተቻለው በማለትና በህብረተሰብ ሳይንስ የማይረጋገጥ ነገር ያወራሉ። ስለሆነም ስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠር የአገር ወዳድነት ስሜት እንዲሽረሸር የማያደርጉት መወራገጥ በጥቂት ቃላት የሚገለጽ አይደለም። ያም ሆነ ይህ በአጠቃላይ ሲታይ የአገር ወዳድነት ስሜት የሚለውን ከባህላዊ ወይም ከትራዲሽናልና ከዘመናዊ ወይም ከንቃተ-ህሊና መዳበር አንፃር በማየት ለመመርመር እንሞክር። ይህ ዐይነቱ ማነፃፀር በተለይም በከፍተኛ ዕውቀት በታነፀና በዝቅተኛ ዕውቀት የተሞረደን ጭንቅላት በአገር ወዳድ ስሜት መዳበር ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ተጽዕኖ የበለጠ ለመረዳት ያስችለናል።

 

ባህላዊ ወይም ትራዲሽናል የአገር ወዳድነት ስሜት!

በእኛ ምሁራን በምንባለው ኢትዮጵያውያን መሀከል ያለው አስቸጋሪ ነገር አንድ ህብረተሰብና አስተሳስቡም ቆመው እንደሚቀሩ እንጂ በየጊዜው እንደሚለወጡና እንደሚሻሻሉ፣ አሊያም ደግሞ በተበላሸ ፖሊሲ አማካይነት የማቴሪያል ሁኔታዎችና የሰውም ንቃተ-ህሊና ሊበላሽ ወይም እየተሸረሸረ ሊመጣ እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባት ነው። ይህ ዐይነቱ የነገሮችን ሂደት በአንድ ቦታ ላይ ረግተው  እንደሚቀሩ አድርጎ መውሰድና ማሰብ ፍሪያማ ለሆነ ምሁራዊ ክርክርና ጥናት እንቅፋት ለመሆን በቅቷል ብል የምሳሳት አይመስለኝም። በሌላ ወገን ደግሞ የመወረርንና የመጨቆንን ነገሮች አጥብቀው የሚያነሱና ከንቃተ-ህሊና ማነስ የተነሳ በጥላቻ መንፈስ በመታገዝ የመረረ ትግል የሚያደርጉትንና የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን አገርን ብቻ ሳይሆን ስንትና ስንት ሺህ ዐመታት እየዳበረ የመጣን ታሪክንና ባህልን ለማፈራረስ የሚሯሯጡትን ኃይሎች ስንመለከት በሁላችንም ዘንድ የቱን ያህል የዕውቀትና የንቃተ-ህሊና ማነስ እንዳለ ለመገንዘብ ይቻላል። ስለሆነም ካለብዙ ምርምርና የጭንቅላት ስራና ማብላላት የሚወረወሩ ቃላቶችና የሚጻፉ ነገሮች በአጠቃላይ ሲታይ ለህብረተሰባችን ዕድገት፣ እንዲያም ሲል ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መፈጠረና መዳበር በጣም ጠንቆች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት ከአርቆ ማሰብ እጥረት የተነሳ የአገራችንን ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና የተጓዘበትን ጠመዝማዛ መንገድ ሳይጠናና ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ የሚደረጉ ትግሎችና የሚወረወሩ ኢ-ሳይንሳዊ ቃላቶች  የአገራችንን ዕድገት ወደ ኋላ የሚጎትቱና ህዝባችንንም  የድህነት ሰለባ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርጉ ናቸው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።

ለማንኛውም ለመግባባትና ወደፊት በመተባበር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊያስተናግድ የሚችል አገር እንድንመሰርት ከተፈለገ የነገሮችን አመጣጥና ዕድገት የግዴታ መረዳት አለብን። በሌላ አነጋገር፣ የአገራችንን የህብረተሰብ አወቃቀርና የዛሬው ደረጃ ላይ መድረስ የግዴታ በሳይንስ መነጽር ማየትና መመርመር መቻል አለብን። ይህ ብቻ ሳይሆን የዓለምን የተወሳሰበ ሁኔታና በተለያየ መልክ የሚደረግብንን ጫናና እንደማህበረሰብ እንዳንኖርና ለተከታታዩ ትውልድ የሚሆን የተረጋጋና መሰረት ያለው ነገር ጥለን እንዳናልፍ የሚሸረብንን ሴራ ጠጋ ብለን ማጥናትና መክተንም ለመመለስ እስካልቻልን ድረስ በታሪክ ፊት ተጠያቂ መሆናችን የማይቀር ጉዳይ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የአገር ወዳድነት ስሜት መዳበርን ከሁለት አንፃር  ማየቱ በአንድ በኩል በተለያዩ ጊዜያት በተለይም የስሜኑን ግዛት ያስተዳድሩት በነበረው የተለያዩ ነገስታት፣ እናቶቻችንና አባቶቻችን ኢትዮጵያ ለምትባለው አገር መሰረት መጣል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ቀስ በቀስ ዘመናዊነት የሚባለው ትምህርትና ከሱ ጋር የተያያዙ በአጠቃላይ ሲታይ ቴክኖሎጂ ነክ ነገሮች ወደ አገራችን መግባት ወደድንም ጠላንም ሁላችንንም የአንድ ሀብረተሰብ አካል እንድንሆን ማስተሳሰር መቻል እስከተወሰነ ደረጃ የጋራ የሆነ መለያ ወይም ስሜት ሊሰጡን በቅተዋል ብል የምሳሳት አይመስለኝም።

ለምንድ ነው ለመሆኑ የአገር ወዳድነት ስሜት የመዳበርን ጉዳይ ከሁለት አንፃር ማየቱ የሚያስፈልገው? አንዳንዶች ይህንን ዐይነቱን አከፋፈልና ትንተና ምናልባት የማያስፈልግ የምሁራን ፀጉር ፈለጣ አድርገው ሊቆጥሩት ይችሉ ይሆናል።  በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም ነገር በዲያሌክቲካል ክንዋኔ ከትንሽ ሁኔታ በመነሳት በውስጣዊ ቅራኔ መሰረት እየተወሳሰበና እየተሳሰረ የሚመጣና የሚዳብር በመሆኑ የአገር ወዳድነት ስሜትም መዳበር በዚህ መልክ ብቻ ነው መታየትና መመርመር የሚችለው።  ስለሆነም የንቃተ-ህሊና ጉዳይ በውስን ደረጃና ከፍ ብሎ ማደግ በአንድ አገርና ማህበረሰብ ዕድገትና የአገር ወዳድነት ስሜት ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው። ስለሆነም የአገር ወዳድነት ስሜትን ጉዳይ ከሁለት አንፃር ማየቱ የችግራችንን ጥልቀትና ውስብስብነት እንድንረዳና መፍትሄም እንድንፈልግ ሊረዳን ይችላል።

በመግቢያው ላይ እንዳልኩት አንድ ህዝብ ከተዘዋዋሪነት፣ ማለትም ከአዳኝነትና ከከብት አርቢነትና ለከብቶች ግጦሽና ውሃ ለመፈለግ ሲባል እየተዘዋውሩ ከመኖር ይልቅ አንድ ላይ ተሰባስቦ መኖር ሲጀምርና የስራ-ክፍፍል ማዳበር ሲችል እንደማህበረሰብ ይተሳሰራል፤ በልዩ ልዩ ነገሮች የሚገለጹ የሚያስተሳስሩትን ነገሮችንም ያዳብራል። እነዚህ ነገሮች አንድ ላይ በመጣመር የጋራ የሆነ መለያ(Collective Identity)  ይሰጡታል። ነገሩን ይበልጥ ለመረዳት፣ አንድ ህዝብ የአንድነትንም ሆነ የአገር ወዳድነት ስሜትን ሊያዳብር የሚችለውና ከውጭ የሚመጣበትን ጥቃት ሊከላከል የሚችለው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የማቴሪያል ሁኔታዎች ሲያድጉና የሚያግባባው ቁንቋ ሲኖረውና ሃሳቡንም ከንግግር አልፎ በጽሁፍ መልክ ሲገልጽ ብቻ ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ባህላዊ ለውጦች፣ ማለትም የሃይማኖት መዳበርና የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ዕምነትና መለያ መሆን፣ የሙዚቃ መሳሪያዎች መዳበርና መዝሙርና ዘፈን ነክ ነገሮች መፈጠር፣ የምግብ አስራር ባህልን ማዳበርና፣ ከአንድ የተወሰነ የምግብ ዐይነት ይልቅ የተለያዩ የምግብ ዐይነቶችን ማዘጋጀትና በስነ-ስርዓት መመገብ…ወዘተ. ከዚህ ጋር ተያይዘው አንድን ማህበረሰብ እንደማህበረሰብ ይኖር ዘንድ የሚንቀሳቀስባቸው ሞራላዊና የስነ-ምግባር ሁኔታዎች መዳብር፣ እንዲሁም በጋርዮሽ አንድን ነገር መስራትና አብሮ መብላትና መጠጣት ወይም ደግሞ ማህበርን መመስረትና በዓላትን በጋርዮሽ ማክበር፣ እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ በመጣመር ወይም በመተሳሰር ለአንድ ህዝብ የጋራ የሆነ የአገር ወዳድነት ስሜት ይሰጡታል። በዚህ መልክ የሚገለጽ የአገር ወዳድነት ስሜት በአንድ በኩል ግብታዊ በሆነ መልክ ሲዳብር፣ በሌላው ወገን ደግሞ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በንቃተ-ህሊና በመታገዝ የሚዳብር ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የማቴሪያል ሁኔታዎችንም ዕድገትና መዳበር፣ እንዲሁም የአገር ወዳድነት ስሜትነት መኖር ከሰው ልጅ ውስጣዊ የመኖር ፍላጎት(Out of Necessity) የሚፈጠሩና ከዝቅተኛ ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር የሚችሉ ናቸው። የሰውንም ልጅ ሰው የሚያሰኘው በዚህ መልክ ከአንድ የኑሮ ደረጃ ከሞራልና ከስነ-ምግባር ጋር በማያያዝ ማደግ የቻለ ከሆነና ለተከታታዩም ትውልድ መሰረት ለመጣል የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። ስለሆነም በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ ከዝቅተኛ የኑሮና የአመራረት ሁኔታ ወደ ተሻለና ወደ ተወሳሰበ ሁኔታ በተለያዩ ህብረተሰቡን በሚያገናኙ ለምሳሌ በንግድ እንቅስቃሴና ገንዘብ፣ እንዲሁም በገበያ አማካይነት መተሳሰር የሰው ልጅ የዕድገት መለያዎች ናቸው። በዚህ መልክ ከታች ወደ ላይ እየተሻሻለ የሚመጣ ማህበረሰብ በተሻለ መልክ ማሰብ ይችላል፤ ተፈጥሮን የመቃኘት ችሎታውም ከፍ እያለ ይመጣል።  ማህበራዊ ባህርይም (Social Being)  ይይዛል ማለት ነው።

የአገራችንን ዕድገት ሁኔታ ስንመለከት ወደድንም ጠላንም ከሞላ ጎደል ይህንን ዐይነቱን ከዝቅተኛ የህብረተሰብ የዕድገት ደረጃ በመነሳት ነው ወደ ሚቀጥለውና ወደ ተሻሻለው መሸጋገር የተቻለው። በሰሜኑ ክፍል ከዳማት እስከ አክሱም ነገስታት አገዛዝና፣ ከዛጉዌ ዲይናስቲና እስከ ሰለሞናዊት ዲይናስቲ ድረስ የነበረውን አገዛዝና ስርዓት ስንመለከት ሁሉም በየፊናቸው በጊዜው በነበራቸው የንቃተ-ህሊና በመታገዝ በተለያየ መልክ የሚገለጽ የማቴሪያልና የመንፈሳዊ ዕድገት መሰረት ጥለው ማለፍ ችለዋል። ካለነሱ ታታሪነትና የግዛት መስፋፋትና ሌላውን ማስገበርና ማስልጠን ባይቻል ኖሮ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብን ማስተናገድ የሚችል አገርና ሁሉንም ሊያስተሳስር የሚችል በተለያየ መልክ የሚገለጽ ባህል ማዳበር ባልተቻለ ነበር። ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ዕድገት ሄገል የሚባለው ፈላስፋ ፌኖሚኖሊጂ ኦፍ ዘ ስፒሪት በሚለው ትልቁ ስራው ውስጥ በደንብ ያሳያል። በእሱ ሀተታም መሰረት ማንኛውም ህይወት ያለው ፍጡር፣ አዕፅዋትንም ጨምሮ በውስጣቸው ባለው ራስን በራስ የማደራጀት ኃይል በመታገዝ ከትንሽ ነገር በመነሳት በውስጠ-ሃይላቸው እንቅስቃሴ ከውጭ በሚመጣ እንደ ፀሀይና ሚኔራሎች በመታገዝ ቅርጻቸውንና መልካቸውን በመለወጥ ያድጋሉ፤ ይባዛሉም። ይህ ዐይነቱ የዕድገት አካሄድ በሰው ልጅም ከመጸነስ ጀምሮ እስከመረገዝ ድረስና፣ ተወልዶ ቀስ በቀስ ማደግና እስከ አቅመ-አዳም ድረስ መድረስ ያለውን ሁኔታ የሚያመለክትና፣ አንድ ህብረተሰብም በዚህ ዐይነቱ የዕድገት አካሄድ እንደሚገለጽ ነው።

ይህንን ሀቅ ስንመረምርና በሌላ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችን የዕድገት ደረጃና የጋራ አስተሳሰብ ሁኔታ ከእኛው ጋር ማወዳደር ስንችልና ሚዛናዊ ፍርድ ስንሰጥ ብቻ ነው እኛም ራሳችን በተሻለ የአገር ወዳድነት ስሜት መታገል የምንችለው። የለም እንደዚህ ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በጨቋኝና በተጨቋኝ፣ በማሰገበርና በመገበር ብቻ ነው የሚገለጸው ብለን የማያስፈልግ ግብግብ ውስጥ የምንገባ ከሆነ ወደፊት ማየትና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገት ማምጣት በፍጹም አንችልም። በየጊዜው በተለያዩ አገዛዞች ወይም ነገስታት የተሰሩትን ስህተቶች ወይም ጥፋቶች መለካት የምንችለው በጊዜው ከነበረው የንቃተ-ህሊና ሁኔታ በመነሳትና ይህንን መመርመር የቻልን እንደሆነ ብቻ ነው። ይህንን ሁኔታ ደግሞ ከሌሎች አገሮች ዕድገትና የግዛት መስፋፋት ጋር ስናያይዘውና ስናወዳድረው የተሻለ ስዕል ይሰጠናል፤ ፍርዳችንም ሚዛናዊ ይሆናል። ጥናታችንና አተናተናችንም ሳይንሳዊ ይሆናል ማለት ነው። በሌላ ወገን ግን ወደ ኋላ በመጓዝ ታሪካችን እንደዚህ ነበር፣ በዚህም ምክንያት ነው ሊበላሽ የቻለው እያሉ የማያስፈልግ ንትርክ ውስጥ መግባት ዛሬ የሚታዩትን ችግሮች በደንብ እንዳናጠናና መፍትሄም እንዳንፈልግ ያግደናል።

በዚህ ላይ ስምምነት ካለን ወደድንም ጠላንም አፄ ምኒልክ ስልጣንን ከያዙና የዘመናዊነትን ፖሊሲ ማካሄድ እስከጀመሩ ድረስ በጊዜው በነገስታቱም ሆነ በህዝቡ ዘንድ የነበረው የአገር ወዳድነት ስሜት የበለጠ ስሜታዊነት የነበረው፣ በአርቆ የማየት መነፅር መታየት የማይችልና፣ ከሃምሳና ከመቶ ዐመት በኋላ ሊከሰት የሚችለውን ሁኔታ ማየት የማይችል ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። በተለይም ከውጭ የሚመጣን ጠላት በጋራ መታገል በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደገሞ ከውጭ የሚመጣ ወራሪ ኃይል በሌለበት ጊዜ እርስ በርስ መሻኮትና መወጋጋት በጊዜው የሰፈነውን በባህላዊ መልክ የሚገለጸውን ንቃተ-ህሊና የሚያሳይ ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ በውስጥ የሚከሰት የእርስ በርስ ጦርነት ኃይልን ጨራሽ በመሆን ለፈጠራ ስራና ለማሰብ የሚያመች ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ በቅቷል። ለዚህ ዐይነቱ የአስተሳሰብ ጉድለትና የበለጠ በስሜታዊ መንፈስ መታገልና የአገር ወዳድነት ስሜትም ይበልጥ በባህላዊ መልክ መገለጽ ዋናው ምክንያት ደግሞ የነበርን ዕውቀት እየተወሳሰበ መምጣት ከጀመረው ችግርና ማህበረሰባዊ አወቃቀር ጋር ሊጓዙ ወይም ለመሻሻል ባለመቻሉ ነው። እንደሚታወቀው ከማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መግቢያ ድረስ ዕውቀት የሚባለው ነገር ከቤተክርስቲያን የሚፈልቅና ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ስለነበር አንድን ህብረተሰብ እንደ ማህበረሰብ ለማደራጀት የሚያስችሉ ፍልስፍናዊና ኢኮኖሚያዊ ቲዎሪዎች ሆነ ሌሎች ዕውቀቶች አልነበሩም፤ ወይም ከውስጥ ሊፈልቁ አልቻሉም። ሰፋ ያለ የዕውቀት መሰረትም ባለመኖሩ ህብረተሰቡን በአዲስ ዐይነት የስራ-ክፍፍልና የአኗኗር ስልት ማደራጀትና ምርታማነትን ማሻሻል አልተቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ወደ ተሻለና ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ወዳለ የህብረተሰብ አወቃቀር ማሸጋገር አልተቻለም። በተለይም ደግሞ ከውጭው ዓለም ጋር የነበረን ግኑኝነት በጣም የላላ ስለነበር እንደፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሶስዮሎጂና ማቲማቲክስ፣ የህንፃ አገነባብ ጥበብና የስነ-ልቦና ዕውቀቶች ጋር መተዋወቅ ባለመቻላችን የማሰብ አድማስና የመፍጠር ችሎታ ለመዳበር አልቻሉም። ይህም በራሱ በጊዜው የነበረውን ባህላዊ አስተሳሰብ፣ ነገሮች ቆመው እንደሚቀሩ አድርጎ ከመገንዘብ ጋር የተያያዘ አስተሳሰብ ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ወደድንም ጠላንም ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ከፊዩዳላዊ የግብዝነትና ስሜታዊ አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ ግብዝነት የተሞላበት አስተሳሰብ እስከዛሬም ድረስ እንዳለ ነው። የትም ኖርን የትም ይህ ዐይነቱ ግብዛዊና ስሜታዊ አስተሳሰብ ከደማችን ጋር የተዋሃደና በቀላሉ መፍትሄም የማይገኝለት ነው። ይህ በራሱ ደግሞ ሳይንሳዊ፣ፍልስፍናዊና በሶስይሎጂ መልክ እንዳናስብ ሊያግደን በቅቷል።

ከዚህ ስንነሳ ከውጭ የመጡትን ወረራዎች በሙሉ መክቶ መመለስ የተቻለውና፣ በአንድ በኩል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተፈጠረውና የዳበረው ባህላዊና ማህበራዊ አኗኗር ስላገዘንና፣ በዚህ ላይ በመነሳት የአልሸነፍነት ባህርይ በማዳበራችን የተነሳ ነው። በተጨማሪም የአገራችን የምድር አቀማመጥ በቀላሉ በውጭ ኃይል እንዳንወረር በራሱ የበኩሉን አስተዋፅዖ ለማድረግ በቅቷል። ይህም ማለት የተሻለ ድርጅታዊ ብቃትነት ስለነበረና፣ በተሻለ የጦር መሳሪያ በመታገዝ ሳይሆን የውጭ ጠላትን እየመከቱ መመለስ የተቻለው፣ በስሜታዊነት ላይ በተመሰረተ፣ ይሁንና አስፈላጊና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ በጊዜው በነበረው ንቃተ-ህሊናና የአንድነት ስሜት በመታገዝ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ ቆራጥነትና የአገር ወዳድነት ስሜት ሊዳብር የቻለው በየጊዜው የተሰነዘረብንን ጠላት መክቶ ለመመለስ የሚያስችል ውስን የሆነ የባህል ዕድገትና በየጊዜው የነበሩ መሪዎች በአልበገርም ባይነት ባደረጉት ታሪካዊ አስተዋፅዖ ምክንያት የተነሳ ነው። በጊዜው የነበሩ ነገስታት በዚህ መልክ ባይታገሉ ኖሮ ለመሆኑ  ዕጣችን ምን ይሆን ነበር? ዕጣችን እንደ ህዝብና እንደማህበረሰብ፣ እንዲያም ሲል እንደ አገር አለመኖር ነበር የሚሆነው። ስለሆነም በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን የገዙትን ነገስታት ስም እያነሱ በጨካኝነት መፈረጅ በአንድ በኩል በጊዜው የነበረውን የንቃተ-ህሊና ደረጃ ስሌት ውስጥ አለማስገባት ነው፣ በሌላ ወገን ደግሞ የራስን አረመኔያዊና አገር አፍራሽ ድርጊት እንዳለ በመካድ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የታሪክንና የህብረተሰብን አገነባብ ሁኔታም በቅጡ ለመገንዘብ ካለመቻል የተነሳ የሚሰነዘር ኢ-ምሁራዊ አባባል ነው።

ያም ሆነ ይህ የሰው ልጅ ከአንድ የኑሮ ሁኔታ ወደ ተሻለ የመሄድ ፍላጎት አለው፤ በዚያው መጠንም የማሰብ ኃይሉም መዳበር ይችላል በሚለው የምንስማማ ከሆነ፣ መጠየቅ ያለብን የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ውጣ ውረዶችን ካሳለፈና እርስ በርሱ የሚያተሳስሩት ብዙ ነገሮችን ከሰራና እንደ ማህበረሰብም የተወሰነ ጥንካሬ ካገኘ በኋላ ከዚህ አልፎ በመሄድ ለምን ድርጅታዊ ብቃትነቱን አላሻሻለም? ለምንስ የተሻሉ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት አልቻለም? ለምንስ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን መፍጠርና ማዳበር አልቻለም? ብለን መጠየቅ አለብን። ለዚህ መልስ ስናገኝ ብቻ ነው የአገር ወዳድነት ስሜታችን መዳበሩንና አለመዳበሩን፣ እንዲሁም ድርጅታዊ ጥንካሬ ይኖረን ወይም አይኖረን እንደሆነ ለማወቅ የምንችለው። በሌላው ወገን ግን ዘመናዊ የሚባለው በተለያየ መልክ የሚገለጸውና የሚተረጎመው የቱን ያህል በተሻለ መልክ እንድናስብና ይበልጥ የአገር ወዳድነት ስሜትም ማደበር አስችሎን እንደሆነ መገንዘብ የምንችለው ዘመናዊነት የሚባለው ነገር አገራችን ውስጥ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለዕድገታችን ያደረገውን አስተዋፅዖ ለመመርመር ይቻልን እንደሆን ብቻ ነው።

ከዚህ በመነሳት ወደ አፄ ምኒልክ የአገዛዝ ዘመን ጋ ስንመጣ የአገር ወዳድነት ስሜታችን ከሞላ ጎደል መዳበር የቻለው በአደዋ ላይ ከተደረገው ድልና በንጉሰ-ነገስታችን ፍላጎትና አርቆ አሳቢነት በገባው የዘመናዊነት ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው። የአደዋ ድልና የዘመናዊነት ፖሊሲ የባህል ዕምርታን ሰጥቶናል ማለት ይቻላል። በዚህ አማካይነትና በአንድ ባንዲራ ስር መጠቃለላችንና በንግድ አማካይነትና በተሻለ የአመራረት ዘዴና በገንዘብ አማካይነት መተሳሰራችን የጋራ አስተሳሰብ አዳብሮልናል ማለት ይቻላል። በዚያው መጠንም እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ የማሰብ ኃይላችን ለማደግ ችሏል። ይሁንና የዘመናዊነት ፖሊሲው በፍልስፍና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በስነ-ጽሁፍ፣ በልዩ ልዩ የአመራርትና የዕደ-ጥበብ ሙያዎች፣ በመንደሮችና በከተማዎች ግንባታና ዕድገት ለመታገዝ ባለመቻሉ የአገር ወዳድነት ስሜታችንም ከበርቴያዊና ምሁራዊ ከመሆን ይልቅ ፊዩዳላዊ ወይም ባህላዊ ሆኖ ለመቅረት ችሏል ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይሁንና ግን በዚህ የሚገለጸው አስተሳሰባችንና የዘመናዊ ፖሊሲ ውስንነት በአፄ ምኒልክ የሚሳበብ ሳይሆን በጊዜው የነበረው በአገሪቱ ውስጥ ይታይ የነበረው የአለማደግ ሁኔታ ነው። በሌላ አነጋገር፣ አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን በአንድ አገዛዝ ስር ለማጠቃለል ሲነሱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ በስራ-ክፍፍልና በንግድ የሚገለጽ የአኗኗር ስልት አልነበረውም። ከተማዎችና መንደሮች አለተሰሩም ወይም አልተዘጋጁም ነበር። በየክልሉ ውስጠ-ኃይል ያለውና ከክልሉ ወጥቶ ሊያስብና ህብረተሰባዊ ለውጥ ለማምጣት የሚችል የህብረተሰብ ኃይል አልነበረም። ዘመናዊ ተቋማትም አልነበሩም። ይህም ማለት አፄ ምኒልክ ህዝባችንን ከዘመናዊ ስልጣኔ ጋር ለማስተዋወቅ ሙክራ ሲያደርጉና አንዳንድ ነገሮችንም ሲያስገቡ ከዜሮ መነሳት ነበረባቸው። በዚህ ምክንያትና፣ ወደ ዋናው ከተማ ስንመጣ ደግሞ የሳቸውን የዘመናዊነት ፖሊሲ የሚደግፍና የሚያራምድ ህብረተሰባዊና ምሁራዊ ኃይል ባለመኖሩ የዘመናዊነት ፖሊሲው ውስን ሊሆን ቻለ።

 

ዘመናዊ የሆነ የአገር ወዳድነት ስሜት !

ዛሬ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት የሆኑቱን፣ ከተማዎችንና መንደሮችን በመገንባት በተለያዩ የመመላለሻና የመገናኛ ዘዴዎች ማስተሳሰር ወይም ማገናኘት የቻሉትን፣ ዘመናዊ ተቋማትን በመገንባት ለህዝቦቻቸው ልዩ ልዩ ግልጋሎቶችን ለመስጠት የቻሉትንና፣ ህዝቦቻቸውን ከድህነትና ከረሃብ በማላቀቅ በማቴሪያልም ሆነ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የመንፈስ ደስታን እንዲጎናጸፉ ያደረጉ አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት ለዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ የአገር ወዳድነት ስሜት ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል።

ተቀበልንም አልተቀበልንም ዛሬ የካፒታሊስት አገሮች በመባል የሚታወቁትና የዓለምን ማህበረሰብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል የሚወስኑትን፣ እንዲሁም ደግሞ እንደኛ የመሳሰሉትን በአስተሳሰብ ደካማ የሆኑ አገሮችን ለመቆጣጠር የቻሉትን  አገሮችን ሁኔታ ስንመረምር እነሱም ከሁለትና ከሶስት መቶ ዓመታት በፊት እንደኛ ወደ ኋላ የቀሩ ነበሩ። ከሁለት መቶና ከሶስት መቶ ዓመታትም በፊት የእነዚህ አገሮች ህዝቦች ዕጣ መሰደድ፣ መራብና መጠማት፣ እንዲሁም በተለያዩ የወረርሽኝ በሽታዎች የሚሰቃዩ ነበሩ ማለት ይቻላል፤ ጦርነትም ዕጣቸው ነበር። ከዚህም በላይ በተለይም የተገለጸላቸው ምሁራን የሚገደሉበት፣ የሚቃጠሉበት፣ ለእስር ቤት የሚዳረጉበትና የሚሰደዱበት ሁኔታ እንደነበርም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። እንደዛሬው እንደኛ አገርና እንደሌሎች የአፍሪካና የላቲንና የማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች አገዛዞች ያልተገለጸላቸው ኃይሎች ስልጣን ላይ የተቀመጡ ስለነበሩ አዳዲስና ሳይንሳዊ አስተሳሰቦችን ይጠሉና ይዋጉ ነበር፤ ከእነሱ አስተሳሰብ ውጭ የሚፈልቅ ማንኛውም ዐይነት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ለስልጣናችን አደገኛ ነው ብለው ያስቡ ስለነበር በሳይንስ የተረጋገጡና ችግርን ፈቺ ሃሳቦችን የመቀበል ፍላጎት አልነበራቸውም። ስለሆነም የተገለጸላቸውን ምሁራዊ ኃይሎችን ይገድሉና ከአገር እንዲሰደዱ ያደርጉ ነበር። ይሁንና የተቀሩት ከውጭም ሆነ ከውስጥ ባለማቋረጥ በመታገላቸው የኋላ ኋላ ብዙ ደቀ-መዝሙሮችን ሊያፈሩና ተቀባይነትም ሊያገኙ ችለዋል። ይህ ዐይነቱ ያልተቋረጠ ትግል የግዴታ ለአዳዲስና ብሄራዊ ስሜት ላላቸው ኃይሎች አመቺን ሁኔታ ሊፈጥር ችሏል።

ስለሆነም ከ14ኛው-19ኛው ክፈለ-ዘመን ድረስ የተካሄደውን የባህላዊ ዕድገት ለውጥና የየግለሰቦችን አስተዋፅዖ በቁጥር በማስገባት፣ የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ለመምጣት የቻሉትና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የበቁት በአገር ወዳድነት  ስሜት በመነሳትና ጭንቅላታቸውን በየጊዜው በመኮትኮታቸውና አርቆ የማሰብ ኃይላቸውን በማዳበር ብቻ ነው። እንደ ጀርመን የመሳሰሉት አገሮች ወደ አንድ አጋዛዝ ከመሸጋገራቸው በፊት በየጊዜው በተለያዩ ኃይሎች የሚጠቁና የሚወረሩ ነበሩ። በመሀከላቸው የነበረው የትናንሽ ግዛት መንፈስና በክልል ብቻ ተወስኖ መቅረት በውጭ ኃይሎች ለመጠቃትና ለመወረር አመቺ ነበር። ይህንን የተረዱት የፕረሺያ አገዛዞችና ነገስታት ከእንደዚህ ዐይነቱ ውርደትና በተደጋጋሚ በውጭ ኃይሎች መጠቃት መቋረጥ የሚችለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው የሚል ዕምነት ስላደረባቸው በዚህ ዙሪያ አጥብቀው መስራት ጀመሩ። ከዚህም በላይ ከውስጥ የመንፈስ ጥንካሬ እንዳይኖርና በኢንዱስትሪ አብዮት የሚገለጽ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን አግዶ የያዘውን የትናንሽ መሳፍንቶች አገዛዝ በመስበር ብቻ ነው የአገር ወዳድነት ስሜትን ማዳበርና ከውርደት መላቀቅ የሚቻለው ብለው የተነሱት የፕረሺያ የፍጹም ሞናርኪዎች በጦርነትም ሆነ በማባበል አንድ አህዳዊ አገዛዝ መመስረትና መገንባት ቀዳሚ ተግባራቸው ነበር። ስለሆነም ከውስጥ የአንድነት መንፈስ ሲዳብርና፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለ-ገብ የጥገና ለውጥ ሲካሄድ፣ በዚህ መልክ ብቻ የህዝቡን የመፍጠር ችሎታ በማዳበር ልዩ ልዩ ዐይነት የማምረቻ መሳሪያዎችን መስራትና የተለያዩ ምርቶችን ማምረት ይቻላል። በተለይም በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የተካሄደውን አጠቃላይ የአገር ግንባታና በዚያን ጊዜ የተሰሩ የሚያማምሩ ቤቶችንና ህንፃዎችን ስንመለከት የአገር ወዳድነት ስሜት ሊዳብር የሚችለው ከአፍ ወደ እጅ በሚካሄድ የእርሻ ተግባርና በቀጨጨ ኢኮኖሚ አማካይነት ሳይሆን፣ በተወሳሰበ መልክ በማሰብና አጠቃላይ የአገር ግንባታ ሲካሄድ ብቻ ነው። የከተማዎች ዕድገት፣ የተለያዩ ከተማዎች በተለያዩ የመመላለሻ ዘዴዎች መያያዝ፣ በስነ-ጽሁፍና በቲአትር የሚገለጽ ባህል ሲዳብር የዚያን ጊዜም የአገር ወዳድነት ስሜት መዳበሩ ብቻ ሳይሆን አንድ ህዝብም በውጭ ኃይሎች ተከብሮ የመኖር ኃይሉ ከፍ ይላል። በተለይም ፍሪድሪሽ ሊስት የሚባለው ለጀርመን የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረገው ታላቅ የብሄራዊ ኢኮኖሚክስ ምሁር የሚያስተምረን ይህንን ነው። አንድ በጥሬ-ሀብትና በእርሻ ላይ የተመሰረተ የአመራረት ዘዴ ያለው አገር ሰፋ ያለና የተወሳሰበ ባህል ሊያዳብር አይችልም። ሃሳቡም የቀጨጨ ስለሚሆን ሻል ብለው በሚገኙ የውጭ ኃይሎች የመታለልና የመወረር ኃይሉ ክፍ ያለ ነው ይለናል። ስለሆነም አንድ አገር እንደ ህብረተሰብ እንድታድግ ከተፈለገና ከውስጥ ህብረተሰባዊ ጥንካሬ ይመጣ ይችል ዘንድ የግዴታ ሁለ-ገብ የሆነ የማኑፋክቱር አብዮት ማካሄድ አለበት ይላል። ይህም ጉዳይ የግዴታ በፍልስፍና፣ በማቲማቲክስና በተፈጥሮ ሳይንስ መደገፍ አለበት በማለት ያስተምራል። በአጭሩ ማቴሪያላዊ ዕድገትና የመንፈሳዊ ዕድገት አንድ ላይ ተያይዘው ሲሄዱ የአገር ወዳድነት ስሜትም የበለጠ ይዳብራል።

ቀደም ብሎ በእንግሊዝ አገር የተጀመረውንና የተካሄደውን የኢንዱስትሪ አብዮት መሰረት ስንመለከት መሰረቱ የአገር ወዳድነት ስሜት ነበር። እንግሊዝ ከጣሊያን ጋር ስትወዳደር ወደ ኋላ የቀረችና የጥሬ-ሀብትም ወደ ጣሊያን፣ በተለይም ወደ ፍሎሬንስ የምትልክ ስለነበር፣ በጊዜው ስልጣን ላይ የነበረው ሃይንሪሽ ስምንተኛው የሚባለው ንጉስ እንግሊዝ በየጊዜው የሚደርስባትን የንግድ ሚዛን መዛባት ምክንያቱ እንዲጠና በማድረግና ሰላዮችን በመላክ በጊዜው ጣሊያን የተሻለ ቴክኖሎጂና የአመራረት ስልት እንደነበራት ስለተገነዘበ ቴክኖሎጂውን በመኮረጅ የጥሬ-ሀብትን ከመላክ ይልቅ አገር ውስጥ እንዲመረትና የአገር ውስጥ ገበያ እንዲያድግና እንዲስፋፋ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል። ይህ ዐይነቱ ወደ ውስጥ ያተኮረ ፖሊሲና ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ምሁራኖች ከውስጡ ጋር በመዋሃድ ለእንግሊዙ ሁለ-ገብ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። በዚህም አማካይነት አዲስና በራሱ የሚተማመን ከኋላ-ቀር አስተሳሰብ የተላቀቀ ወደፊት መራመድን የሚፈልግ የከበርቴው መደብ ብቅ ይላል። ቀስ በቀስም የፊዩዳሉን አስተሳሰብና ተቋማት በመሰባበር ለካፒታሊዝም ዕድገት የሚሆኑ መሰረቶችን ይጥላል።

በዚህ መልክ ቀደም ብሎ በሆላንድ፣ በኋላ ደግሞ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይና አሜሪካ ቀጥሎ ደግሞ በጀርመንና የኋላ ኋላ ደግሞ በጃፓን አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ዕድገትና ህብረተሰቡን የሚያስተሳስሩ ተቋማት ይሰራሉ። በተለይም ፕሮፈሰር ግሪንፊልድ ሊያህ የካፒታሊዝም መንፈስ(Greenfeld, Liah, The Spirit of Capitalism: Nationalism and Economic Growth, London, 2001) በሚለው በጣም ግሩም መጽሀፋቸው ለአንድ አገር ዕድገት በንቃተ-ህሊና ላይ የተመሰረተ የአገር ወዳድነት ስሜት አስፈላጊ እንደሆነ ነው የሚያረጋግጡት። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አያሌ የፍልስፍና፣ የግጥምና የድራማ ስራዎችን ፈጠራ ስንመለከት ለአንድ አገር ጥንካሬና በውጭ ኃይሎች ላለመጠቃት የግዴታ ፊዩዳላዊ ከሆነ የጀግንነት አስተሳሰብ መላቀቅ እንደሚያስፈልግ ነው። ፍሪድሪሽ ሽለር ስለአንድ አገር እንደ አገር ሆኖ መጠራትና ህዝባዊ መተሳሰር የግዴታ አገር አቀፋዊ ወይም ብሄራዊ ቲአትር መደረስና ተግባራዊ መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው። ምክንያቱም ትናንሽ አስተሳሰብና ትናንሽና የተዝረከረኩ የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች በተስፋፉበት አገር ብሄራዊ ስሜትን ማዳበርና ከውጭ የሚመጣውን ማንኛውንም ግፊት መከላከል ስለማይቻል ነው። በከፍተኛ የጭንቅላት ስራና ዕውቀት ብቻ ነው ከውጭ የሚመጣ የተሳሳተ ዕውቀትንና በመዋዕለ-ነዋይ ስም የሚካሄደውን ዘረፋ መረዳት የሚቻለው። በተለይም በዘመነ ግሎባላይዜሽን በፓወር ፖይንትና በኤክስል ተዘጋጅተው የሚቀርቡ አቀራረቦች የተወሳሰበ ዕውቀት የሌለውን የማሳሳት ኃይላቸው ከፍ ያለ ስለሆነ የግዴታ በፍስልፍና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በሶስዮሎጂና በተለያዩ የኢኮኖሚ ዕውቀት ዘርፎች መታጠቅን ይጠይቃል።

ስለሆነም የካፒታሊስት አገሮችን የዕድገት ታሪክ በምናጠናበት ጊዜ የአገር ወዳድነት ስሜትና ዕድገት አንድ ላይ የተያያዙና እነዚህም ነገሮች የግዴታ በትክክለኛ ዕውቀትና በምሁራዊ እንቅስቃሴ መታገዝ እንዳለባቸው ነው። በተለያዩ ጊዜያት ለማሳየት እንደሞከርኩት በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከሬሳንስ ወይም ከመንፈስ ተሃድሶ እስከ ኢንላይተንሜንት ተብሎ እስከሚጠራው የምሁራዊ እንቅስቃሴ ድረስ የተካሄደው ጭንቅላትን አዳሽና ገንቢ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በተለይም ምሁራንን ሰብአዊ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ እንደረዳቸውና በዚህም አማካይነት በሌላው ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ብሄራዊ ስሜትን ማሳደር እንደቻሉ እንረዳለን። ይሁንና ይህ ዐይነቱ ሰብአዊ አስተሳሰብ በካፒታሊዝም ማደግና በኃይል አሰላለፍ መለወጥ የተነሳ የኋላ ኋላ እየተሸረሸረም እንደመጣ መረዳት ይቻላል። በሌላ ወገን ግን በዚያን ጊዜ የተጣለው የሰብአዊነት መሰረት በየጊዜው በመነሳትና ክርክር በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከብዙ ነገሮች ጋር መያያዝ እንዳለበት ለማሳየት ይሞክራሉ። ይሁንና ግን በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የተፈጠረው  የዘረኝነት አስተሳሰብ ናሺናሊዝም ለሚባለው ሌላ ቀለም ወይም ዘር አላቸው የሚባሉትን አግላይ በመሆን የፋሺዝም መሰረት እንደተጣለ መረዳት እንችላለን። ይህም ማለት በሰብአዊነትና በከፍተኛ ምሁራዊ ንቃተ-ህሊና ላይ በተመሰረተው የአገር ወዳድነት ስሜትና በናሺናሊዝም መሀከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለም መገንዘብ ያስፈልጋል።

ከዚህ ለየት ባለመልክና ሌላ የህብረተሰብ ታሪክ ያላቸውን አገሮች እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን፣ ቻይናንና ሰሜን ኮሪያን፣ እንዲሁም ሩሲያን፣ ኋላ ደግሞ ሶቭየት ህብረት ተብላ በመጠራት ትታወቅ የነበረችውን አገር ታሪክ ስንመለከት እነዚህ ሁሉ አገሮች ከርዕዮተ-ዓለም ባሻገር ለኢኮኖሚ ዕድገትና እንዲያም ሲል ለውስጥ ጥንካሬ የሰጣቸው እያደገና እየዳበረ የመጣው የአገር ወዳድነት ስሜታቸው ነው። ከውጭ ይደረግባቸው የነበረውን የወረራ ሙከራና ጫና ለመቋቋምና ላለመዋረድ የነበራቸው አማራጭ ወደውስጥ ኃይላቸውን ሰብሰብ በማድረግ ነው አገራቸውን መገንባትና ራሳቸውን ማስከበር የቻሉት። በሆነው ባልሆነው አስተሳሰብ ጭንቅላታቸውን በመያዝና በመጨቃጨቅ አይደለም እንደቻይናና ሩሲያ ታላላቅ አገሮች ለመሆን የበቁት። ይህንን ሁኔታ ስንመለከትና የራሳችንን አገር ከእነዚህ አገሮች ምሁራንና  አገዛዞች ጋር ስናወዳድረው በአሰተሳሰብ ረገድ በእነሱና በእኛ መሀከል የሰማይና የምድርን ያህል ልዩነት አለ ብሎ መናገር ይቻላል። ይህ ጉዳይ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

 

የዘመናዊ ትምህርትና ዘመናዊነት ያመጡት አሉታዊ ነገሮች!

ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ እንዳላት ይታወቃል። በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ንጉሳዊ አገዛዞችና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምክንያት የተነሳ ህዝባዊ መተሳሰርና ባህላዊ ዕድገቶች ሊዳብሩ እንደቻሉ በታሪክ የተመዘገበ ነው። ቋንቋና ጽሁፍም ሊዳብሩና መልክ መያዝ የቻሉት በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቀሳውስት ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ አማካይነት ነው። ብዙም ሳንመራመር የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደ አገር እስከዚህ ደረጃ ድረስ ለመዝለቅ የቻለችውና በብዙ መልኮች የሚገለጹ ባህላዊ ነገሮችን ማዳበር የተቻለው በተለይም ከ1940ዎቹ በኋላ የተፈጠረው ትውልድ ለዕድገት የሚሆን አስተዋፅዖ በማበርከቱ ሳይሆን በፊዩዳሉ ስርዓትና በንጉሳዊ አገዛዞች ምክንያት ነው። ይህ ዐይነቱ በፊዩዳሉ ስርዓት የዳበረው ባህል፣ መጠነኛ የከተማ ግንባታ፣ የዕደ-ጥበብ ሙያተኞችን መሰብሰባና ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን ማሰራት መጀመር፣ እንዲሁም ደግሞ በረራ በሚባለው የቀድሞው ከተማ ውስጥ መዳበር የቻለው የንግድ እንቅስቃሴ፣ የቤተ-መንግስትና የቤተ-ክርስቲያናት ስራ እነዚህ ነገሮች በሙሉ በ16ኛው ክፍለ-ዘመን በተነሳው የግራኝ ወራሪ ኃይል እንዳለ ድምጥማጣቸው ይጠፋል። ይህ ሁኔታ ለአሮሞዎች መስፋፋት ቀዳዳ በመስጠት በዚህ ዐይነቱ ወረራ የተነሳ ከውድመት የዳኑት ወይም ሙሉ በሙሉ ያልወደሙት እንዳሉ ይወድማሉ። እንደዚህ ዐይነቱን ቀደም ብለው የተሰሩ ነገሮችን የማውደም ጉዳይ በአውሮፓ ምድርም ውስጥ የተለመደ ነበር። የጀርመን ወራሪዎች በአምስተኛው ክፍለ-ዘመንና ከዚያም በኋላ ሮማውያን በሰፈሩበት ቦታ ሁሉ የገነቧቸውን ከተማዎች በማፈራረስ የኋሊት ጉዞ እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው። እንደዚሁም ቪኪንገር የሚባሉት ከተለያዩ ስካንዲኔቢያን አገሮች የተሰባሰቡት የዘላንነት ባህርይ የነበራቸው በዘረፋና በጦርነት የሚታወቁና የሚፈሩ ነበሩ። ከተማዎችንና ግንቦችን ሲያዩ የማፈራረስ ባህርይ እንደነበራቸው ይነገራል። ይህም ማለት ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣም ኢትዮጵያ በፊዩዳሉ ዘመን ወደፊት ለመገስገስ ያልቻለችው አንደኛውና ዋናው ምክንያት ከውስጥ ወራሪዎች ባደረጉት የጥፋት ድርጊት የተነሳ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን ሀቅ ስንቀበል ብቻ ነው የአገራችንን ኋላ-መቅረትና የአገር ወዳድነት ስሜት በዘመናዊ መልክ አለመዳበር መረዳት የምንችለው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ሀሰተኛ ትረካ ወደ ኋላ እንድንጓዝ ከማድረግና ለማኝ ሆነን ከማስቀረት በስተቀር መንፈሳዊ ተሃድሶና ጥንካሬ በፍጹም ሊሰጠን አይችልም።

የዘመናዊነት ትምህርትንና የዘመናዊነትን አስተሳሰብ በሚመለከት ብዙም ሳይታሰብ ጉድ የሰራን ዘመናዊ አስተሳሰብ ነው እየተባለ ይነገራል። በተለይም ይህ ዐይነቱ አባባል በአሁኑ ጊዜ እንደ ግሽበት በመናፈስ አንዳንድ ወጣቶችና ጋዜጠኞች ዘመናዊነትን እንዳለ በማውገዝ ላይ ይገኛሉ። ሀቁ ግን ዘመናዊነት ወይም ከአንድ ኑሮ ደረጃ ወደ ሌላው መሸጋገር ያለና የሚኖርም ነው። የሰው ልጅም የግዴታ በኑሮው መሻሻል አለበት፤ ይፈልጋልም። ዘለዓለሙን በጎጆ ቤት ውስጥ ለመኖር የሚፈልግ የለም፤ በመቶ ኪሎ ሜትሮችም የሚቆጠር ርቀትም በእግሩ ለመጓዝ የሚመኝ የለም። ንጹህ ውሃ ቤቱ በራፍ ድረሰ ወይም ቤቱ ውስጥ በቧንቧ መልክ ቢቀርብለትና ቢፈስለት ደስ የማይለው የለም። እንደዚሁም ከኩራዝና በጭስ እየታፈኑ ከመኖር ይልቅ በኤሌክትሪክ ኃይል እየተጠቀመ ኑሮን ማቃለልን የሚጠላ አይኖርም።  ይህን ዐይነቱን ድካምና ችግርን ማቃለል የሚቻለው በዘመናዊነት ወይም በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው። ስለዚህም ነው ይህን ዐይነቱን በቴክኖሎጂ መራቀቅና እርስ በርስ መገናኘት የምናየው። ይሁንና ግን ዘመናዊ የሚባለውን አስተሳሰብና በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮችና በአገራችንም ተግባራዊ የሆነውን ፖሊሲ ስንመለከት የተዛባ አስተሳሰብ እንመለከታለን። በአገራችን ምድር በዘመናዊነት ስም የተካሄዱት ከውጭ የመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ሳይጠኑና ሳይመረመሩ ነው በጭፍን ተግባራዊ ለመሆን የበቁት። ይህ ጉዳይ ለኋላ ቀርነታችንና ለተበላሽ አስተሳሰባችን እንደዋና ምክንያት ሊቆጠር ይችላል። እንደዚህ ዐይነት ሁኔታ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በብዙ የአፍሪካ አገሮችና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮችም አፍጦ አግጦ ያለ ሃቅ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የካፒታሊዝም ማደግና ካለቅጥ መስፋፋት እንደኛ አገር የመሳሰሉ ኢኮኖሚዎችንና ማህበረሰቦችን ሊያዘበራርቅ ችሏል ብል የምሳሳት አይመስለኝም። ምክንያቱም ቀላል ነው። ከካፒታሊዝም የተወሳሰበ ዕድገት ጋር የሚጓዝ፣ እንዲሁም ውስጣዊ ይዘቱን ለመረዳት ያሚያስችለን ምሁራዊ ኃይልና ጭንቅላት ለማዳበር ባለመቻላችን ነው። ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ የዘመናዊነት አስተሳሰብን አፈላለቅና ዕድገትንና ትርጉሙን ለመረዳት አንዳንድ ነገሮችን ማንሳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን የዘመናዊነት አስተሳሰብ ያፈለቁ የግሪክ ፈላስፎች እንደነበሩ ይታወቃል። በጊዜው የግሪኮች የዘመናዊነት አስተሳሰብ መነሻው ፍልስፍና እንደነበር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በዘመኑ የነበረው ኋላ-ቀር ሁኔታ ስላስገደዳቸውና በትራዲሽናል ኖርምስ ብቻ ተደስተው መኖርን ስላልፈለጉ የግዴታ የተፈጥሮንና የኮስሞስን ምስጢር መመራመር  ተገደዱ። ከዕምነታዊ አስተሳሰብ በመላቀቅ አርቆ-አሳቢነትን ማዳበር ቻሉ። ለሰው ልጅ ኋላ-ቀርነትና ዕድገት፣ ወይም ደግሞ ለጦርነትና ለሰላም መኖር ዋናው ምክንያት አርቆ-አለማሰብና አርቆ ማሰብ መሆኑን በመረዳት ለጭንቅላት ከፍተኛ ቦታ ሰጡት።  በዚህም አማካይነት በተፈጥሮ ውስጥ የሚገኙ ነገሮችንና፣ የተለያዩ ነገሮችንም ምን ምን ነገሮች እንዳሚያይዟቸው ለማወቅ ቻሉ። ቀስ በቀስም የተፈጥሮን ህግ በመረዳትና ጭንቅላታቸውን በማዳበር ለዘመናዊነት የሚሆነውን መሰረት መጣል ቻሉ። ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስና ማቲማቲክስ፣ እንዲሁም ሌሎች ዕውቀቶች ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆኑ የጭንቅላት ስራ ውጤቶች ናቸው። ለዚህ ይነቱ ዕውቀት መዳበርና በአዲስ መልክ መቀረጽ ጥቁር አፍርካ፣ ሶርያና ኢራክ እንደተሳተፉበት ሰፋ ያሉ ማረጋገጫዎች አሉ።

ይሁንና በሌላ ወገን ደግሞ በራሳቸው በግሪክ ፈላስፋዎች መሀከል ዕድገትን ወይም ዘመናዊትን በሚመለከት የተለያዩ አስተሳሰቦች እንደነበሩ መገንዘብ ይቻላል። አንደኛው የመንፈስን ተሃድሶ የሚያስቀድምና በመንፈሳዊና በማቴሪያላዊ ዕድገት መሀከል ሚዛናዊነት መኖር አለበት ብሎ የሚያስብ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የማቴሪያል ዕድገትን የሚያስቀድምና የሰው ልጅ ፍላጎት የማያቋርጥ ነው ብሎ የሚያምን ነበር። እንዲሁም አንደኛው የፍልስፍና ዘርፍ የሰው ልጅ ማህበራዊ ነው፣ ስለሆነም በጋራ ነው መስራት ያለበት ሲል፣ ሌላው ደግሞ የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ግለሰብአዊና የራሱን ጥቅም አሳዳጅ ነው፤ ስለሆነም በጋርዮሽ ሊሰራ አይችልም በማለት ይከራከሩ ነበር። የኋላ ኋላ የማቴሪያል ዕድገትን ብቻ ያሰቀደመው አስተሳሰብ አይሎ በመውጣቱ ለግሪክና ለሮማውያን ስልጣኔ መፈረካከስ ዋናው ምክንያት እንደሆነ ይታወቃል። በተለይም የሶፊስቶች ፍልስፍና በመባል የሚታወቀው በክስተት ላይ የተመሰረተው አስተሳሰብ ተቀባይነት በማግኘቱ አገዛዞች ይህን ዐይነቱን የበላይነትንና የስግብግብነትን መንፈስ(Power and Greed) ሊያዳብሩ በመቻላቸው ስልጣኔያቸው ሊወድም ቻለ። ዓላማቸውም ከውስጥ ሰላምና ስምምነትን ማስፈን ሳይሆን በሌላው ህዝብ ላይ የበላይነታቸውን ማሳየት በመሆኑ ውድቀታቸው ተፋጠነ። ወደ ውጭ ደግሞ ጦርነትን ማስቀደምና ወረራ በማካሄድ የሌሎች አገሮችን ህልውና መድፈርና አገርን ማፈራረስ ነበር። በዚህ መልክ የዳበረው የተበላሸ አስተሳሰብ የኋላ ኋላ ካፒታሊዝምን ባዳበሩ አገሮች በመወሰዱ ከኢኮኖሚ ዕድገትና ከቴክኖሎጂ ምጥቀት ባሻገር የእነዚህ አገሮች አገዛዞች ባህርይ ጦርነትና ወረራ ለመሆን በቅቷል። የባርያ ንግድና የቅኝ ግዛት ፖሊሲዎች የዚህ ዐይነቱ የአገዛዝ ፈሊጥ ባህርዮች ናቸው። የመጀመሪያውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች የዚህ ዐይነቱ የበላይነት ስሜትና የስግብግብነት መግለጫ ባህርዮች ናቸው። በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮችና በአገራችንም ተግባራዊ የሆነው በተለይም በኢኮኖሚ የሚገለጸው የዘመናዊነት ፖሊሲ የዚህ ዐይነቱ የስግብግብነት ፖሊሲ አንድ አካል ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም በአገራችንም ሆነ በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮች በዘመናዊነት ስም ሰተት ብሎ የገባው ትምህርት ከፍልስፍና የተነጠለና፣ የተፈጥሮንና የኮስሞስን ውስጣዊ ህጎች እንድናውቅ የሚረዳን ባለመሆኑ ሁለ-ገብና የተስተካከለ ዕድገት ለማምጣት አላስቻለንም። ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት አስተሳሰብና ተግባራዊነቱ የግዴታ ጥራዝ-ነጠቅነትን እንድናዳብር ነው የረዳን ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ በተወሳሰበ መልክ እንድናስብ፣ ጠለቅ ብለን እንድንመራመር፣ የህብረተሰባችንን ሁኔታና ለዕድገት ማነቆ የሆኑ ነገሮችን ደረጃ በደረጃ ለማጥናትና ለመረዳት አላስቻለንም። ከፍስልፍናና ከተፈጥሮ ሳይንስ ተነጥሎ የገባው የትምህርት አስተጣጥ የግዴታ አመጸኛና የሽወዳ መነፈስን እንድናዳብር መንገዱን አዘጋጀልን። ግልጽነትና ሀቀኝነት እንዲኖረን አላስቻለንም፤ በተሟላ መልክም የአገራችንን ታሪክና ለዕድገት ማነቆ የሆኑ ነገሮችን እንድንረዳ የሚያስችል ዕውቀት አላጎናጸፈንም። ጭንቅላታችንም በተበላሸ መልክ መዋቀር ወይም ፕሮግራምድ መሆን በመጀመሩ ከጠለቀ ውይይትና ክርክር፣ እንዲሁም ከመደማመጥ ይልቅ ኩርፊያንና ግብዝነትን አዋሃደን። ስለሆነም በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አገሮች ውስጥ የሚታየው ትርምስና የአገዛዞች አምባገነንነትና ሀብትን አውዳሚነት፣ ጦርነትም ዋናው ባህርያቸው ለመሆን የበቃው መንፈሳቸው በተበላሸ የዘመናዊነት አስተሳሰብ ስለተበከለ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድ አገርና ህዝብ ተከታታይነት እንዲኖራቸው የሚያስፈልጉ ሞራላዊና ስነ-ምግባራዊ ብቃትነት፣ ኃላፊነት መሰማት(Awarenesss)፣ በተፈጥሮና በሰው ልጅ መሀከል ስለሚኖረው ግኑኝነትና፣ የሰው ልጅም ለመኖር ሲል የግዴታ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ ስለመሆኑ ጉዳይና፣ ሌሎች አያሌ እሴቶች ለመዳበር ባለመቻላቸው አገዛዞችም ሆነ ህዝቦች በዘፈቀደ እንዲኖሩ ለመገደድ በቁ። ድህነትና ጦርነትም መለዮአቸው ሆኑ። ይህ ጉዳይ ደግሞ በጎሳና በሃይማኖት ስም ተሳበው ለሚካሄዱ ግጭቶችና ሀብት አውዳሚ ግብግቦች መንገድ ማመቻት ቻለ። በጥራዝ-ነጠቅነት መንፈስ የተወጠሩ ኤሊት ነን ባዮች ጦርነትን በመቀስቀስና ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር በየአገሮችና በአገራችንም ጭምር ታሪክ እንዳይሰራ ለማድረግ በቁ።

ስለሆነም ዘመናዊ የሚባለውን አስተሳሰብ እንዲያው በጭፍኑ ከመጥላታችን በፊት የነገሩን ሂደትና መበከል በደንብ ጠጋ ብለን መመርመር አለብን። በተለያዩ ፈላስፋዎችና የኢኮኖሚ ምሁሮች መሀከል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና የአገርን ግንባታን  በሚመለከት የተለያዩ አስተሳሰቦች እንዳሉ መረዳት አለብን። ይህ ከመሆኑ በፊት የሚተገበሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችም ሆነ በጭፍኑ ዘመናዊነትን መጥላት ወደባሰ ትርምስ ውስጥ ነው የሚከቱን። ማንኛውም ምሁር ነኝ ባይ መረዳት ያለበት ጉዳይ እሱ ከሞተ በኋላ ሌላ ተተኪ ትውልድ እንዳለና እንደሚፈጠርም ነው። በመሆኑም ለተከታታዩ ትውልድ መጥፎ ነገር ሳይሆን ጥሩ ነገር ጥሎ ለማለፍ ሞራላዊና ታሪካዊ ግዴታ እንዳለበት ማወቅ አለበት። በዚህም አማካይነት ብቻ ነው የአገር ወዳድነት ስሜት ሊለካ የሚችለው።

እንደገና ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ ከአፄ ምኒልክ የዘመናዊነት ፖሊሲ በኋላ ዘመናዊነት ስተት ብሎ መግባት የቻለው አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ከተመለሱና የተበላሸ የትምህርትና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ ነው። ይህ የተደረገበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ሆን ተብሎ ሳይሆን በተለያዩ ዕውቀቶች ወይም ለዕድገት በሚጠቅሙና በማይጠቅሙ በተለያዩ አስተሳሰቦች መሀከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት የሚችል ህብረተሰባዊ ወይም ምሁራዊ ኃይል ባለመኖሩ ብቻ ነው። ስለሆነም በጊዜው ተግባራዊ የሆኑት የትምህርትና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ስንመለከት ውስጠ-ኃይሉ የዳበረ፣ የማሰበ ኃይሉ የሾለ፣ በተለያዩ አቅጣዎች ለመመራመር የሚችልና የሚያመዛዝን ምሁራዊ ኃይል ብቅ እንዲልና ልዩ ዐይነት ሚናን እንዲጫወት የሚያስችል አልነበረም። ይህ ጉዳይ የግዴታ የአገር ወዳድነት ስሜት እንዳይዳብርና በጋራ አገርን ለመገንባት እንዳንችል አድርጎናል። የአገር ወዳድነት ስሜት ለመዳበር አልቻለም። በአንፃሩ ወደ ውጭ የሚመለከትና ለውጭ ኃይሎች የአገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥና ብሄራዊ ስሜትን የሚያኮላሽና ብሄራዊ ነፃነትን የሚያስደፍር ኃይል ብቅ ሊል ችሏል ማለት ነው።

አፄ ኃይለስላሴ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ከተገደዱ በኋላና የወታደሩ አገዛዝ ስልጣንን ከተረከበ በኋላ የተወሰነ የአገር ወዳድነት ስሜት ሊዳብር ቢችልም ይህ ስሜት ከውስጥ ባሉና ለስልጣን በሚስገበገቡ ኃይሎች ሊሸረሸርና ደብዛው ሊጠፋ ቻለ። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያን እንደዋና ጠላት አድርገው የተነሱት እንደነ ህወሃትና ሻቢያ፣ በኋላም ደግሞ ኦነግ የሚባሉት ጽንፈኛ ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበርና በራሳቸው አገር ላይ ጦርነት በመክፈት ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በቁ። እነዚህ ትናንሽ ጭንቅላት ያላቸው ኃይሎች ለውጭ ኃይሎች ተገዢና መሳሪያ በመሆንና በመታለል በጥቁሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጦርነት በመክፈትና ተንኮል በመተብተብ ለዕድገትና ለስልጣኔ የሚሆን ኃይል እንዳይዳብር ለማድረግ ችለዋል።

ህወሃት የሚባለው የውጭ ቅምጥ አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ደግሞ ተግባራዊ ያደረገው የክልልና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የባሰውን የብሄራዊ ስሜት እንዲሸረሸር  ለማድረግ በቅቷል። በክስተት ላይ የተመሰረተው ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚባለውና ህወሃት ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማውም ሀብትን ከማውደምና ጥቂቶችን ከማደለብ ባሻገር የሰፊውን ህዝብ ስነ-ልቦና ማዳከም ነው። የባህል ጦርነት በማካሄድ በአገርና በባህል ላይ ዘመቻ የሚያደርግ የህብረተሰብ ኃይል መኮትኮት ነው። የዚህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ኃይል ዋናው የኑሮው ፍልስፍና ደግሞ ስግብግብነትና አመጽ ነው። ሰርቶ ሳይሆን ዘርፎ ሀብታም በመሆን የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር የአገር እሴት እንዲወድምና አገራዊ ስሜት እንዳይዳብር ማድረግ ነው። የህወሃት መሪዎችና ካድሬዎቻቸው የውጭ ኃይሎች ተላላኪ በመሆን ኢትዮጵያን፣ በተለይም የኦርቶዶክስን ሃይማኖትና አማራን ነው እንደዋና ጠላት በማየት አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የስነ-ልቦናና የባህል ጦርነት ማካሄድ የጀመሩት። በዚህም አማካይነት ነው ብሄራዊ ወይም የአገር ወዳድነት ስሜት ሊወድምና የውጭ ኃይሎችም አገራችንን ሊያጠቁና በቀላሉ ሊያዳክሙን የቻሉትና ለወረራ የተጋለጥነው። ይህ ዐይነቱ በህወሃትና በውጭ ኃይሎች፣ ማለትም በአሜሪካንና በእንግሊዝ፣ እንዲሁም በተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች እንደኛ የመሳሰሉት የጥንት ታሪክና ባህል ያላቸውን አገሮች ማፈራረስ ዋናው ስትራቴጂ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የአገር ወዳድነት ስሜት እንዲጠፋ ለማድረግና ለማንበርከክ ነው። በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም በነፃ ንግድና በነፃ ገበያ ስም የሚካሄዱት ዘመቻዎችና ወረራዎች የጥሬ-ሀብትን በቁጥጥር ስር ከማዋል አልፎ የዓለምን ህዝብ አመጋገብ አንድ ወጥ ማድረግ ነው። ሃይማኖትና አስፈላጊ የሆኑ ባህሎችን በመደምሰስ ጦርነትና ስግብግብነትን ማለማመድ ነው። በዚህ መልክ  የአገር ወዳድነት ስሜት ደብዛው በጠፋበት አገር ደግሞ በተለይም ወጣቱና የዋሁ ህዝብ ወዴት እንደሚጓዙና ለምንስ እንደሚኖሩ ማወቅ አይችሉም። የህወሃት የጥፋት ፖሊሲ በራሱና በካድሬዎቹ ዙሪያ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ለሆዳቸው ያደሩ፣ የታሪክንና የባህልን ምንነት ያልተገነዘቡ፣ ከዚህም ከዚያም የተውጣጡ የየብሄረሰቡ ኤሊቶች፣ ይሁንና ደግሞ በሃሳባቸው የቀጨጩ ኃይሎች  ዙሪያም የሚታይ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ህወሃት ተግባራዊ ያደረገው ሳይንሰ-አልባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ ምሁራን ነን ባዮችን ሊበክልና አገርንም ለማውደም በቅቷል ማለት ይቻላል። በተለይም በየክልሉ አስተዳዳሪዎች የሚታየው የመንፈስ መበላሸትና ሌላውን መጤ እያሉ ማሳደድና መግደል ከዚህ ዐይነቱ ከዝቀተኛ ዕውቀትና መንፈስ የመነጨ ባህርይ ነው። የውጭ ኃይሎችም እንደነዚህ የቀጨጨና ስግብግብ ባህርይ ያላቸውን የውስጥ ኃይሎችን በመጠቀም ነው በቀላሉ አገር እንድትፈራረስ ለማድረግ የሚችሉት። ስለሆነም ብሄራዊ ስሜትን በማናገት፣ የአገር ወዳድነት ስሜት እንዲኮላሽ ማድረግና ለውጭ ኃይሎች እጅን ወደላይ አንስቶ የመሸነፍን ምልክት ማሳየት  በውስጥና በውጭ ኃይሎች በተቀነባበረ ሴራ የሚካሄድ ነው ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነት የተበላሸ ሞራል ባለበትና የአገር ወዳድነት ስሜት በወደመበት አገር ደግሞ ጠንካራ ኢኮኖሚና ህብረተሰብ መገንባት አይቻልም፤ ባህልንና ልዩ ልዩ እሴቶችን ማዳበር በፍጹም አይቻልም። ፍቅርንና ስላምንም ማስፈን አይቻልም።

 

ለአገር ወዳድነት ስሜት ጠንቅ የሆኑ ነገሮች!

በዚህ ዓመት በዚህ ወር የአደዋን 125ኛ ዓመት እናከብራለን።  የአደዋ ድል የቱን ያህል እንደ አገርና እንደማህበረሰብ እንድንኖር፣ እንዲያም ሲል እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ በዘመናዊነት ፖሊሲ አማካይነት አንድ ህብረ-ብሄር(Nation-State) ለመመስረት እንዳበቃን የቱን ያህል ግንዛቤ እንዳለን መገንዘብ ያስቸግራል። ይሁንና ግን በአደዋ ላይ የተጎናጸፍነው ድል ለአብዛኛዎቻችን የመንፈስ እርካታ እንደሰጠንና እንድንኮራንም አስችሎናል። በሌላ ወገን ደግሞ የአደዋን ድልና አፄ ምኒልክ አንድ ታላቅ አገር ለመመስረት ያደረጉትን ጥረት እንደሞራላዊና ታሪካዊ ግዴታ ከመቁጠር ይልቅ እንደወራሪ ኃይል በማየት ከግንዛቤና ከዕውቀት ማነስ የተነሳ በውስጥ ኃይሎች አደገኛ አገርን የማፈራረስ እርምጃ እየተወሰደ ነው። አንዳንዶች በቁጭት በመነሳት ያልነበራቸውን ወይም ደግሞ ለዕድግትና ለባህላዊ ዕምርታ የማያመቹ የሀሰት ትረካቸውን በማውራትና እየቆፈሩ በማውጣት የማይሆን ግብግብ ይዘዋል። ሳያውቁት በራሳቸው ብሄረሰብም ላይ ዘመቻ እያካሄዱ ነው። በተለይም ከትግራይና ከኦሮሞ የተውጣጡ ኤሊቶች የኢትዮጵያን ታሪክ እያጣመሙ በማንበብና የሀሰት ትረካ በማውራት ጠቅላላው የጥቁር ህዝብ በሚኮራበት የአደዋ ድልና በአፄ ምኒልክ ላይ ከፍተኛ የሀሰት ዘመቻ እያወሩና ወጣቱንም እየበከሉትና የአገር ወዳድነት ስሜት እንዳይዳብር እያደረጉ ነው። እነዚህ የትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶች በመሰረቱ የሚሰሩት ለነጩ የኦሊጋርኪ መደብ ነው። ጣሊያን አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ አርበኞች እልክ አስጨራሽ ተዋጊነት በመሸነፉ ለጣሊያን ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የነጭ ህዝብ በተለይም ለኦሊጋርኪው መደብ ይህ ሽንፈት እንደትልቅ ውርደት የሚቆጠረው። ስለሆነም ኢትዮጵያን የሚያጠቃውና አገራችንም እንደ ሃይቲ የመሰለ ዕጣ ሊደርስባትት የሚችለው እንደነዚህ የመሳሰሉሉ በዝቅተኛ መንፈስ የሚሰቃዩና ትናንሽ ጭንቅላቶች ያላቸውን እንደ ትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶችን በመጠቀም ነው።  ስለሆነም ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ሲገዛትና ሲያደማት በነበረበት ዘመን የፈረንጅ ኦሊጋርኪው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ፣ እንደ ኢኮኖሚያዊ ድቀት፣ ያልተስተካከለ ዕድገት፣ የስነ-ልቦናና የባህል ውድመት…ወዘተ. ተግባራዊ አድርጓል። አገሪቱንም በቋንቋ በመከፋፈል ልዩ ዐይነት አርቲፊሻል የማንነት ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ የአንድነት ስሜት እንዳይኖርና ችግራችንንም በጋር እንዳንቀርፍ ለማድረግ በቅቷል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ከሶስት ዐመታት ወዲህ አግጦ አፍጦ በመምጣት በተለይም ዘርና ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ በማካሄድ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ቀስ በቀስ ደብዛው እንዲጠፋ በረቀቀ መልክ እየተሰራ ነው። በተለይም በመተከልና በወለጋ ውስጥ በአንዳንድ ቦታዎች በአማራዎች ላይ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ እንዳናወራ እየተደረገ ነው። ይህ ዐይነቱ አወራር „ኢትዮጵያዊነትን አይመጥንም፣ ከዚህም በላይ የከፋ ነገር ሊደርስ ይችላል“ እያሉ አዲስ የመዘናጋት ባህል እያሰተማሩን ነው። የኢትዮጵያዊ ጨዋነት አንገትን በመድፋትና እሺ በማለት ነው የሚገለጽ ነው በማለት አዲስ ነገር ያስተምሩናል። ሰብአዊነትና ለሌላው ማዘን ከመንፈሳችንና ከልባችን ተሟጠው እንዲወጡ እያሸማቀቁን ነው። ሰው ሲገደል ዝምብላችሁ ተመልከቱ ይሉናል። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ከእኛ በዕድሜ ከአስረና ከሃያ ዓመት የሚያንሱ ናቸው። እነዚህ ወጣቶችና ጎልማሳዎች የካድሬ ባህርይን በማዳበር አዲስና ዕምርታዊ ለውጥ እንደመጣ በማስመሰል በዐይናችን የምናየውን፣ የምንሰማውንና በእጃችን የምንዳስሰውን ሃቅ መናገር እንደ ወንጀል እየቆጠሩብን ነው።

ወያኔ የሚባለው ፋሺሽታዊና ዘራፊ ቡድን ከስልጣን ላይ ከተወገደ በኋላ ደግሞ የቀሩት ካድሬዎችና ፕሮፊሰር ነን ባዮችና የዓለምን ታሪክና ፖለቲካ „እንገነዘባለን“ የሚሉ አንዳንድ የትግራይ ኤሊቶች ከነጮች ጁንታ ጋር በማበር በአገራችንና በህዝባችን ላይ አደገኛ ቅስቀሳ እያካሄዱ ናቸው። በተለይም ሰሞኑን ከፕሮፌሰር ገላውዴዎስ አራያ፣ የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር፣ እንዲሁም ስለ ዕድገት ኢኮኖሚ አውቃለሁ ከሚለው አፍ ተቀማጭነቱ አሜሪካን አገር በሆነው የትግራይ ሚዲያ ጋር ያደረገውን የጥያቄ ምልልስ ሳዳምጥ በጣም አሳዛኝና አሳፋሪ  ሆኖ ነው ያገኘሁት። ፕሮፌሰር ገላውዴዎስ አራያ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በፍልስፍና ሙያ ስለጠን የሚሉት የትግራይ ብሄረሰብ ኤሊቶች የሚያወሩት የተሳሳተ ትረካ የሚያረጋግጠው እነዚህ ምሁራን ነን ባዮች የተማሩትን የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የሶስዮሎጂና የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት እንደዘነጉ ነው የሚያረጋግጠው። አሊያም ደግሞ ዕውቀቱ በጭንቅላታቸው ውስጥ በደንብ አለተቀርጸም ማለት ነው። አንድ ሰው ተማረ የሚያሰኘውም የጠለቀ ቲዎሬቲካልና ኢምፐሪካል ጥናት በማካሄድ ተጨባጭ ወይም የሚጠጋጋ መረጃና ዕውቀት ለአንባቢው ሲያስተላልፍ ብቻ ነው። ካለበሊዚያ ትምህርት ቤት በመሄድ ጊዜ ማባከን ባላስፈለገ ነበር። ለማንኛውም እንደነዚህ ዐይነት የመሳሰሉት ሰዎች የሚያረጋግጡት በፍልስፍናም ሆነ በሶስዮሎጂ ጭንቅታቸው ሊሾልና በተሻለ መልክ በማገናዘብ ማሰብ እንደማይችሉ ነው። የሃሰት ትረካን በማውራትና ከውጭ የኦሊጋርኪው ኃይል ጋር በማበርና በመታገዝ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ማጠናከር ነው ዋናው ዓላማቸው።፡

ለማንኛውም የእነዚህ ሰዎች የጥላቻ ቅሰቀሳ መነሾው 27 ዓመት ያህል ተቀዳጅተው የነበረውን የብዝበዛና አገራችንና ህዝባችንን የማደኽየት መብታችንን አጣን በማለት ነው። ይሁንና ደግሞ እዚያው በዚያው ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብና በታሪኳ ላይ ያደረሰውን ጉዳትና የባህል ውድመት ለመቀበል አይፈልጉም። በእነሱ ዕምነት ህወሃት የሚባለው ዘራፊና ፈሺሽታዊ ቡድን ኢትዮጵያን አሰልጥኗል፤ የብሄረሰቦችንንም መብት አስከብሯል ብለው አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ። በተለይም ባለፉት አርባ ዓመታት በጠባብ ስሜት ተኮትኩተው ያደጉትና የግዴታ እኛ ብቻ ነን የኢትዮጵያን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል ለመወሰን የምንችለው ብለው አሁንም የሚንቀሳቀሱት አንዳንድ የትግራይ ወጣቶችና ኤሊቶች አገራዊና ብሄራዊ ስሜት ለማዳበር የሚችሉ አይደሉም። ከራሳቸው ጠባብ ዓላማ ውጭ ብሄራዊ አጀንዳ የላቸውም። ታሪክንም በተጣመመ መልክ ስለሚያቀርቡና ትዕቢትንም በመንፈሳቸው ውስጥ ያዳበሩ በመሆናቸው እነዚህን የመሳሰሉትን የትግራይ ኤሊቶች መንፈስ ለማነፅና ለጋራ ዓላማ እንዲነሱ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደነዚህ ዐይነት በጣም በተበላሸ ዕውቀት መንፈሳቸው የታነፁ ኤሊት ነን ባዮች የአገራችንን ችግር ከሶስዮሎጂ፣ ከፍልስፍና፣ ከስነ-ልቦናና ከባህለ-ታሪክ፣ ከኢኮኖሚ ኋላ-ቀርነት አንፃር ለማስረዳትና ለመከራከር በፍጹም አይቻልም። የህብረተሰባችንንም ታሪክ በሶስዮሎጂና በፍልስፍና መነፅር ለማስረዳትና አዲስ ለሁላችንም የሚያመች ሁለ-ገብ ዕቅድ ለማውጣት በፍጹም አይቻልም። ታዲያ መግባባትና ግንዛቤ በሌለበት፣ እንዲሁም ደግሞ እኛ ብቻ ነን መግዛት ያለብን በማለት ለተሻለ አስተሳሰብ ለመወያየት ዝግጁነት ከሌላቸው ሰዎች ጋር እንዴት በአንድ መቀመጫ ዙሪያ ተቀምጦ መወያየት ይቻላል? እንዴትስ አድርጎ ለእንደነዚህ  ዐይነት ኤሊት ነን ባዮች የኃላፊነት ቦታ መስጠት ይቻላል?

መታወቅ ያለበት ጉዳይ ዕውነተኛ የአገር ወዳድነት ስሜት ከቡድናዊ ወይም ከብሄረሰብ አስተሳሰብ የፀዳ መሆን አለበት። በአንድ አገር የሚኖርን ህዝብ፣ ከየትኛውም ብሄረሰብ ይምጣ በእኩልነት፣ በወንድማዊነትና በእህትነት መንፈስ ማየት የአገር ወዳድነት ባህርይ መሆን አለበት። ዕውነተኛ የአገር ወዳድነት ስሜት በአድሎአዊነት ሳይሆን፣ በሰብአዊነትና በአንድ አገር ለሚኖር ህዝብ ተቆርቋሪ በመሆን የሚገለጽ ነው። ስለሆነም የአገር ወዳድነት ስሜት የሚለካው የራሱን ብሄረሰብ ጥቅም በማስቀደም ሳይሆን የጠቅላላውን ህዝብ ጥቅም በማስጠበቅና ለሁላችንም የሚስማማ የተከበረችና ጠንካራ አገር መገንባት ሲቻል ብቻ ነው። በዚህ መንፈስ የሚታነፅ ግለሰብም የአገሩን ጥቅም ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ አይሰጥም። ወገናዊነቱ ለአገሩና ታሪክን በአዲስ መንፈስ መገንባት ነው። አገሩን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ ለተከታታዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው። ሳስበው ዛሬ ከፍተኛ ዘመቻ የከፈቱት የትግራይ ወጣቶችና ኤሊቶች ለዚህ ዐይነቱ ታሪካዊና ፍትሃዊነት ለተሞላበት ስራ የተፈጠሩና ጭንቅላታቸውም የተዋቀረ አይደለም። ይህ ዐይነቱ በሽታ ወደ ኦሮሞ ኤሊቶችም ዘንድ በመሸጋገር „ኢትዮጵያ ትፍረስ፣ ትውደም“ እያሉ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሁሉ ሲያስተጋቡ ይደመጣሉ። ያልገባቸው ነገር ኢትዮጵያ ስትፈርስ በውስጧ ያቀፈቻቸውን የትግራይና የኦሮሚያ ክልሎችንም ይዛ እንደምትጠፋ ወይም እንደምትፈራርስ ነው። በዚያው ህዝባቸው መሄጃና መድረሻም እንደሚያጣ አይገባቸውም። ተምሮ መደንቆር ማለት እንደዚህ ነው።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ብሄረሰቤን እወክላለሁ፣ ለጥቅሙም እታገላለሁ የሚሉትን ኤሊቶች የምሁራዊ ሁኔታ ስንመረምር አስተሳሰባቸው በሳይንስና በተገለጸለት አስተሳሰብ የተዋቀረ አይደለም። በአንድ አገር ውስጥ ዕውነተኛና በሳይንስ ላይ የተመሰረተ የተስተካከለ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው የአንድን አገር ታሪክና ተጨባጩን ሁኔታ በብሄረሰብ መነጽር በመመልከት ሳይሆን በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በሶስዮሎጂ መነጽር እንጂ በሃሰት ትረካ መነፅር አይደለም። ስለሆነም ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌላቸው ኤሊቶች ደግሞ የዓለምን የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና፣ የኢኮኖሚ አወቃቀር ሁኔታ በደንብ የመመርመር ኃይልና ችሎታ የላቸውም። ያለው የሌለውን ኃይላቸውን ሲጨቁነኝ ነበር በሚለው ብሄረሰብ ላይ ብቻ በማንሳት የውጭ ኃይሎች በአገራችን ውስጥ ገብተው እንዲፈተፍቱና የአገራችንም ሁኔታ እንዲበላሽና መፍትሄም እንዳያገኝ ያደርጋሉ። ስለሆነም ቆሜለታለሁ የሚሉት ብሄረሰብም በውዠንብር ዓለም ውስጥ እንዲኖር በማድረግ የድህነትና የድንቁርና ሰለባ እንዲሆን ያደርጉታል። በተጨባጭ ሲታይም ለብሄረሰባቸው መብትና ጥቅም ሳይሆን የሚታገሉት ለራሳቸው ጥቅምና የበላይነት ብቻ ነው። ድሮ አማራ ነበር፣ ቀጥሎ ደግሞ ትግሬ፣ ዛሬ ደግሞ እኛ በተራችን የበላይነትን በመቀዳጀትና የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖር በውጭ ኃይሎች በመመራትና በመታገዝ የኢትዮጵያን ውድቀት ማፋጠን አለብን ብለው ነው የሚነግሩን። ታሪኳን እንዳለ መበወዝና በአዲስ መልክ መጻፍ አለበት ብለው ነው የሚንቀሳቀሱት። የህውሃቱን የ27 ዓመታት የስልጣን ዘመን ስንመለከት ይህንን ነው የሚያረጋግጠው።

ስለሆነም መደረግ ያለበት ትግል ከብሄረሰብ ጥቅም ባሻገር፣ አይ በአንድ ርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ ካለበለዚያ ደግሞ የሰብአዊነትን መርሆ በማስተጋባት ለነፃነት፣ ለሰላምና ለዲሞክራሲ መታገል ነው። የአንድ አገር ችግር በብሄረሰብ መነፅር ሊታይና መፍትሄም ሊያገኝ በፍጹም አይችልም። እያንዳንዱ ለስልጣን የሚታገል ግለሰብም ሆነ ድርጅት እራሱን እንደ ሰው ማየት አለበት። ብሄረሰብ የሳይንስ ክፍል ስላለሆነ ክቡሩ የሰው ልጅም ወደ ብሄረሰብነት ዝቅ ተብሎ የሚታይ አይደለም። የሰው ልጅ ተንቀሳቃሽና ፈጣሪ ኃይል ስለሆነ ከብሄረሰብ በላይ ነው። ስለሆነም በዛሬው ዓለም ብሄረሰብ የሚባል ነገር በአገራችን ምድር የለም። በአገራችን ምድር ያሉት የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩና ባህል የሚሉት ነገሮች ያላቸው ሰዎች ወይም አንድ ህዝብ፣ ይሁንና ደግሞ በመጋባትና በመወላለድ የተሳሰሩ ናቸው። ፍላጎታቸውም በሰላም መኖር ነው። በሰላም ውሎ በሰላም ማደር ነው። ለአንድ ሰው ለመኖር የሚያስፈልጉትን መሰረታዊ ነገሮች ማግኘት ነው ዋናው ፍላጎታቸው። ፍላጎታቸው ጦርነት አይደለም።

የአሃዳዊነትን ስሜትን ወደሚያስተጋቡት ጋ ስንመጣም ተመሳሳይ ችግር ይታያል። እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ ዘመናዊ የመንግስት አወቃቀር ታሪክ፣ የዕድገትንና ለዕድገት ማነቆ የሆኑ ነገሮችን በሚመለከት ጉዳይ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለአንድ አገር ዕድገትና ለህዝብ ኑሮ መሻሻል ስላላቸው ሚና፣ ስለፍልስፍናና ሶስዮሎጂ፣ ባጭሩ ጠቅላላውን ህብረተሰብ በሚመለከቱ ነገሮች ላይ ውይይትና ምርምር፣ እንዲሁም ክርክር ተካሂዶ አያውቅም። የፖለቲካ ትግል የሚባለው ወደ አርባ ዓመታት ያህል ያስቆጠረው ዕድሜ የምሁራዊ እንቅስቃሴ ዘመን ሳይሆን በስሜት ላይ ያተኮረ ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። በረቀቀ መልክ ለማሰብ ያልረዳንና፣ ምርምርና ጥናት በማድረግ የተሻለ አመራር ለመስጠት ያላስቻለን እልክ አስጨራሽ አካሄድ ነበር። አንዳንዱ እራሱን ከደሙ ንጹህ ለማድረግ ቢጥርም ከዚህም ሆነ ከዚያኛው የተውጣጣው፣ በተለይም ደግሞ ከአማራው ብሄረሰብ ተወለድኩ የሚለው ምሁር ነኝ ባይ ይህንንም ያህል በተወሳሰበ መልክ የሚያስብ አይደለም። ላይ እንዳልኩት የአንድ አገር የህብረተሰብ ታሪክ ቆሞ የሚቀር አይደለም። የሰው ልጅና በአጠቃላይ ሲታይ ህብረተሰብ ውስጣዊ ኃይል እንዳላቸው መረዳት ያስፈልጋል። ስለሆነም ከውስጥም ሆነ ከውጭ በሚመጣ አስተሳሰብና ልዩ ልዩ ባህላዊና የአመራረት ዘዴዎች የኃይል አሰላለፍና የአስተሳሰብ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችልም መገንዘብ  ያስፈልጋል። ስለሆነም በየጊዜው በተለይም በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነትና ተግባራዊነት ሊለወጡ የሚችሉና የሚለወጡ የህብረተሰብ አወቃቀሮችን በደንብ ለመመርመር መቃጣት ተገቢ ነው። በዚህ ረገድ ለአህዳዊነት እታገላለው የሚለው በተለይም የአማራው ኤሊት ከላይ የዘረዘርኳቸውን መሰረተ-ሃሳቦች ለመረዳት አይፈልግም። ለምሳሌ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በሶሻሊዝም ስም ተግባራዊ ለመሆን የተደረገውን እንደ መሬት ለአራሹ የመሳሰሉትን የጥገና ለውጦች የኮሙኒስቶች ስራ ነው በማለት እንዳለ ይወነጅላል። ስለሆነም አንድ ህዝብ በቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ የተሻለ የአመራረት ዘዴ ማስገባት እንዳለበት፣ ከጎጆ ቤት መላቀቅ እንዳለበት፣ ንጹህ ውሃና የተሟላ ዴዬት ማግኘት እንዳለበት፣ አቡጊዳን በማስተማር አስተሳስቡ መሾልና እንደማህበረሰብ መኖር እንዳለበት በፍጹም አይገነዘብም። በመሆኑም አንድን ህዝብ የሚጠቅሙ የኢኮኖሚና ሌሎች የጥገና ለውጦች ሲካሄዱ ልክ እንደ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ይህ ዐይነቱ ድርጊት የኮሙኒስቶች ነው በማለት ዘመቻ ማካሄድ ይጀምራል።  የአህዳዊነት ስሜት አለኝ ቢልም የአገራችንን ሁኔታ በልዩ መነጽር በመመልከት ነገሩን ለመረዳት አይፈልግም። የአንድ ህብረተሰብ የተወሳሰበና የጠለቀ ችግር በተወሳሰበና በጋራ ጥናት መፈታት እንዳለበትም በፍጹም አያምንም። ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ ለአድሃዊነት እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። ከስሜታዊ አስተሳሰብ በመላቀቅ የአገራችንን የተወሳሰበ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ችግር በሳይንሳዊ ዘዴ ማጥናት ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያን እንደ አንድ አገርና ማህበረሰብ ለመገንባት ያለው ትልቁ ችግር በሁላችንም ዘንድ ያለው የአገራችንንም ሆነ የዓለም አቀፍ ሁኔታን በደንብ ለመገንዘብ አለመቻል ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያችን ዘመናዊ ከሚባለው ነገር ጋር ከተዋወቀች ጀምሮ ተነጥላ የምትኖር ሳትሆን ከውጭው ዓለም ጋር በተለይም ከካፒታሊስት አገሮች ጋር በብዙ ድሮች ተያይዛለች። እነዚህም ግኑኝነቶች በንግድ፣ በመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ፣ በዕዳ ወይም በብድር፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት፣ በሚሊታሪና በስለላ ግኑኝነቶች የሚገለጹና በአገር ወዳድነት ስሜታችን ላይ የራሳቸውን በይበልጥ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደሩ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ በእኛ መሀከል ባለው የግንዛቤ እጦት የተነሳ የካፒታሊስት  አገሮች አገራችንና ህዝባችንን የባሰውኑ እንዲዘበራረቁና የዝንተ-ዓለማችንን በድህነት ዓለም ውስጥ ዘፍቀን እንድንኖር ለማድረግ በቅተዋል። የሚያደርጉብንን ጫናና ፖሊሲ ነክ ነገሮች ለመረዳት ባለመቻላቻን አንድነታችን ሊላላና ብሄራዊ ነፃነታችንም እንዲደፈር ለማድረግ በቅተናል። ከሃምሳ ዓመታት በላይ በሚያስቆጥር ዘመን እገራችን እንደ ነፃ አገር የምትታይ ሳትሆን ወደድህነት ዓለም እንድትገፈተር በማድረግ በካፒታሊስት አገሮች አሁን ደግሞ በቻይና ላይ ጥገኛ ለመሆን በቅተናል። ለእርሻ የሚሆን ፍሬያማ መሬት ቢኖረንምና የተለያዩ ሰብሎችን፣ ቅጠላቅጠሎችንና ፍራፍሬዎችን ለማብቀልና ራሳችንን ለመመገብ ብንችልም በተለይም በቢሮክራሲው ዘንድ በሚሰራው አሻጥርና የዕውቀት ማነስ የተነሳ ሌላው ቢቀር እንኳ በምግብ ራሳችንን እንዳንችል ለመደረግ በቅተናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም በተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መሀከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ባለመቻላችንና ህብረተሰብአዊ ሀብትን ሊፈጥር የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እየደጋገምን ተግባራዊ በማድረጋችን ወደ ውስጥ ያተኮረና ድሀነትን የሚቀርፍ ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ መገንባት አልቻልንም። ይህንን በሚመለከት በሁላችንም ዘንድ ሃሳብ ለሃሳብ ሳንለዋወጥ አንድ ዐይነት ስምምነት ያለ ይመስላል። ኢትዮጵያና ህዝባችን ማደግና መሻሻል የለባቸውም፤ የሳይንስና የቴክኖሎጂም ባለቤት መሆን የለባቸውም የሚል ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ በኢምፔሪያሊስት አገሮች ላይ ጥገኛ ሆና መቆየቷና መኖርም ያለባት ተፈጥሮአዊ ህግ ነው የሚል ስምምነት ነው በሁላችንም ዘንድ የሰፈነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በካፒታሊስት አገሮች ላይ፣ በተለይም በአሜሪካን ካፒታሊዝም ላይ ትልቅ ዕምነት አለን። በአሜሪካን፣ በእስራኤልና በኢትዮጵያችን መሀከል ያለው ግኑኝነት በፍቅር ወይም በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ይፈላለጋሉ የሚል አስተሳሰብ ሲንሸራሸር ይሰማል። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስንና የአገዛዝ አወቃቀርን ሁኔታ የሚጥስ ነው። በአገሮች መሀከል የፍቅር ወይም የወዳጅነት ግኑኝነት ሳይሆን ሊኖር የሚችለው፣ የጥቅም ግኑኝነት ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ የየዋህነት አስተሳሰብ እስካለ ድረስና አሜሪካንና እስራኤልን እንደ ተፈጥሮአዊ አጋር አገሮች አድርገን እስከቆጠርን ድረስ እገራችን በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዳታድግ፣ እንዲሁም ጤናማና ውስጠ-ኃይል ያለው አገር እንዳይመሰረት ነው የምናደርገው። ስለሆነም በአንድ ጊዜ ሁለት ነገሮችን መውደድ የማይቻለውን ያህል፣ አይ ለኢትዮጵያና ለህዝባችን ጠበቃ መሆን፣ አሊያም ደግሞ አሜሪካንና እስራኤልን  ነው የምናፈቅረው ብሎ ለእነሱ ጠበቃ መቆም። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ፣ ከሁለቱ አገሮች ጋር ምንም ዐይነት ግኑኝነት አይኑረን ማለቴ አይደለም። በተለያየ መልክ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነት ይኖረናል። ይሁንና ያለንን ምሁራዊ ድክመት በመረዳታቸው እንደፈለጋቸው እንዲጫወቱብን ለማድረግ በቅተናል። ለምሳሌ ዛሬ በኢኮኖሚያቸው ጠንካራ ከሆኑ አገሮች ከጃፓንና ከቻይና ለመማር የምንችላቸው ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ቢኖሩም ለመማር ዝግጁ አይደለንም።

ለማንኛውም በመሀከላችን ያለው እርስ በርሱ የሚጋጭ አስተሳሰብና ምሁራዊ ብስለት አለመኖር የአገር ወዳድነት ስሜት እንዳይዳብር አድርጎናል። ትክክለኛ ዕውቀት ባልተስፋፋበት አገር ውስጥ ጭንቅላት ሀቀኛ ከመሆን ይልቅ መዋለል ይጀምራል። ሀቀኛ ከመሆን ይልቅ መዋሽት ይጀምራል። ነገሮችን በግልጽ ከማየትና ሳይንሳዊ ግምጋሜ ከመስጠት ይልቅ ወደ ተራ አነጋገር ይገባል። የመጨረሻ መጨረሻም ወደ መካካድና ወደ መዋሽት ማምራት ይጀመራል። በገሃድና የሚረጋገጥ ወንጀል እየሰሩና እየታየም የለም እኔ አለሰራሁም፣ በቦታውም አልነበርኩም እየተባለ መማል ይጀመራል። ይህ ዐይነቱ ውሽት ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ አንድ ሰው ወይም የሰው ልጅ ሊኖረው የሚገባውን ባህርዮች፣ ማለትም ሀቀኝነት፣ ሰብአዊነት፣ ሞራላዊነትና ስነ-ምግባራዊነት፣ መጸጸት… ወዘተ. የሚባሉ እጅግ አስፈላጊ ነገሮችን የሚጥስ ነው። ኢኮኖሚክስም ስንማር በመጀመሪያው የቡክ ኪፒንግ ኮርስ ላይ አራት መሰረታዊ ነገሮች በጭንቅላታችን ውስጥ እንዲቀረጹ ነው የተማርነው። እነዚህም፣ ግልጽነት፣ አንድን ነገር በተሟላ መልክ ማቅረብ፣ ሀቀኝነትና በስነ-ስርዓት  ማዘጋጀት  የሚሉ ናቸው። የመጨረሻ መጨረሻም ማንኛውም ነገር በሰነድ ወይም በማስረጃ መረጋገጥ አለበት ይላል። ስለሆነም አንድ አገርና ማህበረሰብ በውሸትና በመካካድ እንዲሁም በተበላሸ ዕውቀት ሊያድጉ በፍጹም አይችሉም። ተከታታይነት ያለው ማህበረሰብም መገንባት በፍጹም አይቻልም።

ባጭሩ በዚህም ሆነ በዚያ አልነው እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን መሰረተ-ሃሳቦች ያላካተተ የኢትዮጵያዊነት ጩኸትና የባንዲራ ማውለብለብ ወደፊት አያራምዱንም። እዚያው በዚያው እየተንደፋደፍን ከመቅረት በሰተቀር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት አያደርጉንም። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ያልተመሰረተ፣ በስራ-ክፍፍል የማይገለጽ ኢኮኖሚ፣ በከተማዎችና በመንደሮች ግንባታና በተለያዩ የመገናኛና የመመላለሽ ነገሮች የማይያያዝ አገር ደግሞ እንደ አገርና እንደ ማህበረሰብ ሊቆይ አይችልም። እንደዚህ ዐይነት አገር ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ውድቀት ወይም ወደ መፈራረስ ነው የሚያመራው። ይህንን ደግሞ ሁላችንም የምንመኝ አይደለንም። ስለሆነም አገራችንን አሁን ካለችበት የተመሰቃቀለና አገር አፍራሽ ሁኔታ ለማላቀቅ ሁኔታውን በአዲስ መነጽር ማየትና መመርመር መቻል አለብን። ነገሮችን በአዲስ መልክ ማየት የእኛ ትውልድ ጉዳይ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ዕድሜያችንም ስለገፋና በጭንቅላታችን ውስጥ የተቀረጸ ወይም ፕሮግራምድ የሆነ ነገር ስላለ አሁን ባለንበት ዕድሜያችን ከዚህ አስተሳሰብ መላቀቅ በጣም ያስቸግራል። ስለሆነም እራስን ወደ ውስጥ መመልከትና በዛሬው ሁኔታ ሳይደሰቱ የአገራችንን ሁኔታ በአዲስ ዕውቀት መመርመርና ለተወሳሰበው ችግርም መፍትሄ መፈለግ የታዳጊው ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነትና ሞራላዊ ግዴታ ነው። መልካም ግንዛቤ !!

 

[email protected]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop