ከአንተ በፊት አባ ገዳ ነግሮኛል! – ዮሐንስ መኮንን

አባቴ እና ወንድሙ በኦሮሞ ምድር ሀብት አፍርተው ትዳር መሥርተው ወልደው ከብደው ይኖሩ ነበር:: ከእለታት በአንዱ ቀን የኦሮሞ አባ ገዳዎች እባቴን እና አጎቴን ጠርተው እንዲህ ሲሉ ጠየቋቸው:: “ሀገራችን ሀገራችሁ ልጆቻችን ልጆቻችሁ ናቸው:: እስካሁን እንደ እንግዶች ሆናችሁ አብረን ኖረናል:: ከአሁን ብኇላ ግን እንግድነታችሁ አብቅቷልና ኦሮሞ ሆናችኇል:: ከፈለጋችሁ ጎሳ መርጣችሁ ስም ሰይመንላችሁ አብረን እንኖራለን:: ይቅርብን ካላችሁ ደግሞ ጎሳም ሳትመርጡ ስማችሁም ሳይለወጥ የኦሮሞ ቤተሰብ ሆናችሁ ኑሩ” አሏቸው:: አጎቴ ስሙ ሽፈራው ደለለኝ መሆኑ ቀርቶ “ባልቻ ሄርጳ” ተብሎ የጎሳ አባል ሆነ:: ልጆቹንም ኦሮሞ ብቻ አድርጎ አሳደገ:: አባቴ ግን ስሙንም ሳይቀይር ጎሳም ሳይመርጥ መኮንን ደለለኝ እንደተባለ አማራ የሆነ የኦሮሞ ቤተሰብ ሆኖ ኖረ:: ልጆቹንም አማራ እና ኦሮሞ አድርጎ አሳደገን:: እኛም በአማርኛ እና በኦሮምኛ አፋችንን ፈተን አደግን::
አንደኛው አጎቴ ከሦስት ወር በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ቤተሰብ ለቀብር ሄደን የአየሁት ትንግርት ነበር:: እንደ አንድ የኦሮሞ አባገዳ በፈረስ ጉግስ የታጀበ ከፍ ያለ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመለት:: ከቀብር በኇላም የኦሮሞ አባገዳዎች ቤተሰቡን “የአጎታችሁን መሬት እያረሰ ሀብት ንብረቱን ወርሶ ኦሮሞ ሆኖ አብሮን የሚኖር ሰው ወክሉ” አሉን:: አንደኛው የአጎታችን ልጅ ጎሳውንም ሀብቱንም ስሙንም ወርሶ ኑሮውን ቀጥሏል::
አንተ አውሮፖ አሜሪካ እና አውስትራሊያ ተቀምጠህ “ውጣ እና ግባ ወይንም ነባር ነህ ሠፋሪ” እያልክ የምትሰድበኝን ዘገምተኛና ዘረኛ “አክቲቪስት” ነኝ ባይ አልሰማህም:: ምክንያቱም ስለ ኦሮሞ አቃፊነት (ሞጋሳ) ከአንተ በፊት አባቴ አስጠንቶኛል:: አንተ ሳትወለድ (ሳትጨነግፍ ላለማለት ያህል) ወዶና ፈቅዶ ኦሮሞ የሆነው አጎቴ መንዜው ባልቻ ሄርጳ መርቆኛል:: ከአንተ በፊት አባ ገዳ ነግሮኛል:: ከአንተ ይልቅ አባገዳን ስለማምን ስድብህን አልሰማህም!!! (ይህን እየጻፍኩልህ የአጎቴ የኦሮምኛ ምርቃቱ በጆሮዬ እያቃጨለ እንባዬ መውረዱን ዘግይቼ ነው ያወቅሁት)
በኦሮሞ ምድር የኦሮሞ ቤተሰብ ሆኖ ስለኖረው ስለ መንዜው አባቴ እና ባልቻ ሄርጳ ስለተባለው ኦሮማራ ይኼን ካልኩ ስለእናቴ ደግሞ የምጽፈውን ተከተለኝ
ቢቂላ ጉደታ ኦዶ (Biqilaa Guddataa Oddoo) የተባለ ጦረኛ የቦረና ኦሮሞ የወራሪውን የጣልያንን ጦር ለመውጋት ከአጼ ምኒልክ ጦር ጋር አድዋ ዘምቶ የሀገርን ዳር ድንበር አስከብሮ ሲመለስ ከነጦሩ ምእራብ ሸዋ ላይ የአሪሮ ጎሳ ባላባት ሆኖ ኑሮውን ይመሠርታል:: ቢቂላም አያቴን ቶሎሳን ይወልዳል:: ቶሎሳ ልበብርሃን እና ትምህርት ወዳጅ ስለነበር ጎጃም እና ጎንደር ተዟዙሮ የቤተክህነቱን ትምህርት ተምሯል:: ታዲያ የቦረናው ሰው ቶሎሳ ቢቂላ ከአማሮች ምድር ፊደል ብቻ ሳይሆን ወለዬዋን ፋንታዬንም አብሮ ቀጽሎ (ተምሮ) ኖሮ የእኔን እናት ጆርጌን ወለዱ:: አናቴ ጆርጌ አያቷ በጦርነት ላይ አገጩን በጥይት ተመትቶ እንደነበረ ሳይቀር እያስታወሰች ስለ ጀግንነቱ እና ሀገር ወዳድነቱ አውግታኛለች::
እናቴ ጆርጌ ከኦሮሞዎቹ ወላጆቿ ጋር ብዙም አልኖረችም:: ይልቁኑም ነፍጠኛው አማራ ፊታውራሪ መልሴ አጥናፉ አያቴን ኦቦ ቶሎሳን ለምነው በማደጎ እናቴ ጆርጌን ይወስዳሉ:: ኦሮሞዋ እናቴም ስሟ ጆርጌ ቶሎሳ መሆኑ ቀርቶ አሳዳጊዋ ባወጡላት ስም “ፀሐይ መልሴ አጥናፉ” ተብላ ነፍጠኛ አማራ ሆና አደገች:: አማራው አሳዳጊዋም ከልጆቹ እኩል ሀብት ሲያወርሳት ምእራብ ሸዋ ላይ አራት ጋሻ የእርሻ መሬት እና አዲስ አበባ ጉለሌ ላይ ደግሞ ግማሽ ጋሻ መሬት ይሰጣታል::
ይሄውልህ እንግዲህ አኔ የኦሮሞ ባህል ውስጥ ኖሮ በፈቃዱ ኦሮሞ ከሆነው አማራው አባቴ እና በአማራ ቤተሰብ ውስጥ አድጋ በፈቃድዋ አማራ ከሆነችው ኦሮሞ እናቴ ተገኘሁ:: መንዜው አባቴ ኦሮሚፋ አቀላጥፎ ሲናገር አማራነቱን ትጠራጠረዋለህ:: ኦሮሞዋ እናቴ ደግሞ አማርኛዋ ጎጃሜውን ያስንቃል:: ማንነቴን ብታውቅ ኖሮ እንኳንስ “ሠፋሪ” ብለህ ልትሰድበኝ ቀና ብለህ አታየኝም ነበር:: ምክንያቱም እኔ ጣልያንን አባርሮ ድንበር ያስከበረ የቦረና ኦሮሞ ባላባት ልጅ ነኛ ! ሀገርና ወገንን መውደድን ለኢትዮጵያ ድንበር መውደቅን ኦሮሞው ቅድመ አያቴ በወሬ ሳይሆን በተግባር አስተምሮ ኢትዮጵያን በአደራ አስረክቦኛል:: ይብላኝ ላንተ! አደራህን በልተህ ቅድመ አያቴ አዋርዶ ካባረራቸው ባእዳኖች ለቁራሽ ጉርሻ ደጅ መጥናትህ ሳያስ ለጎሳ ፖለቲካህ እንዲመችህ እኔን እና ወንድሞቼን ታባላናለህ::
ዛሬ ሀገሬ ቀን ጥሏት አንተን የመሰለ እሾህ አበቀለችና ታሪክ ተገልብጦ በፈረንጅ ሀገር የምትንከራተተው ስደተኛው እንተ “ባለሀገር” ሆንክ:: ሀገር ጠባቂው እኔ ደግሞ “ሠፋሪ” ተባልኩ:: አዲስ አበባ ላይ የግማሽ ጋሻ መሬት ወራሽ የሆንኩት እኔ ዛሬ በኪራይ ቤት ኑሮዬን መግፋቴ ሳያንሰኝ አንተ በሀበሻነትህ አፍረህ ከፈረንጅ ዜግነት የተቀበልከው የባህር ማዶ ሰው “መጤ” እያልክ በሀገሬ ከወገኔ ጋር የምኖረውን እኔን ትሰድበኛለህ:: አንተ ምንታደርግ! ድንጋይ እንዲሰብሩ ጊዚ የሰጣቸው ቅሎች ሕገመንግስት ብለው መዝገብ ሲያበጁ የእኔ ቢጤ ሠርገኛ ጤፍ ኢትዮጵያዊን የዜግነት ክብር እንኳን አልሰጡንም:: እነርሱ በሰፉት የጎሳ ከረጢት መግባት ሳይቻለኝ ስለቀረ ሀገሬ እንደዜጋም ረስታኛለች:: በዘር ሀረጉ ደሙ “ንጹህ” ለሆነው ባለጊዜ እንጂ የእኔ ቢጤ ቅይጡ ኦሮማራ በአያት ቅድመአያቶቹ ምድር መጻተኛ እና ባይተዋር ነው::
ወዲህ አንደኛው እብድ አለህ ደግሞ:: አንተኛው “ኦሮሞ ጠል” ነኝ (Oromofobic) ነኝ ባዩ ጎረምሳ! አንተን ደግሞ ነፍጠኛው አያቴ እድሜ ሰጥቶት ከዚህ ዘመን ደርሶ አውቆህ ቢሆን ኖሮ “ጥቁር ውሻ ውለድ” ብሎ ይረግምህ ነበር:: ኦሮሞዋን እናቴን ፍጹም ልጁ አድርጎ አሳድጏልና::
ቅድመአያቶቻችን በሞጋሳ እና በማደጎ ተፋቅረው አብረው ኖረው, ጋሻ መሬት ተካፍለው, ጠላት ሲመጣባቸው አብረው ዘምተው, ሀገር እቅንተው አብረው ሲኖሩ “ኦሮማራዎቹ” እኔና አንተ በአሥር አመት ወረፋ በተገኘ በኪራይ ቤት እየኖርን ድንጋይ መወራወራችን መቼም ድንቅ ስላቅ ነው::
“ይህቺም ቡናቁርስ ሆና ሚጥሚጣ በዛባት” እንዲሉ !

አርክቴክት

ዮሐንስ መኮንን
ተጨማሪ ያንብቡ:  ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ውርደት ጥቁር ቀን (ሮበሌ አባቢያ)

1 Comment

  1. በኦሮሞ ታሪክ ብዙ ጎበናዎች ለሚኒሊክ አብረዋል። የምኒልክ አሽከር ሙሉ ኦሮሞው ፤ ራስ ጎበና ዳጬ ነፍጠኛ ነበር።

    ራስ ጎበና ከእነመሰሎቹ ጎበናዎች የኦሮሞ ጡት በአኖሌ አስቆርጠዋል። ብሔር ብሔረሰቦችን ለነፍጥኛ በባርያነት እየሸጡ ቅኝ ግዛት አስገዝተዋል በአቢሲኒያ የዘውድ ሥርዓት ነገሥታት እየተጣለላቸው ፍርፋሪ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share