February 15, 2021
35 mins read

የሞራል ዝቅጠት እና የአድርባይነት ልክፍት ፡ ጣምራ ደዌዎቻችን! – ጠገናው ጐሹ

February 15, 2021
ጠገናው ጐሹ

ስለ ሞራል (moral) መሠረታዊ ምንነት ስንነጋገር በመልካም (ጥሩ) ነገር እና በመጥፎ (በጎጅ) ነገር   መካከል የሚኖረውን ወይም ያለውን ልዩነት ተገንዝቦ ወይም ተረድቶ ከመልካሙ ነገር ጋር በፅዕናት በመቆም መጥፎውን (ጎጅውን) ስለ መፀየፍና ስለ መዋጋት ፣ ወይም ተቃራኒውን ሆኖና አድርጎ ስለመገኘት ሰብእና ነው የምነጋገረው።

ስለ አድርባይነት (opportumism) ስንነጋገር ደግሞ በአገር ወይም በማህበረሰብ ወይም በቡድን ወይም በግለሰብ ደረጃ ባሉ መስተጋብሮቻችን ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ አንዳንድ አጋጣሚዎችን ወይም ሁኔታዎችን ከግል ወይም ከቡድን ፍላጎት አንፃር ብቻ ያላቸውን ፋይዳ እያሰሉ የመጠቀምን እና በተቃራኒው ትክክለኛ መርህንና አቋምን ለርካሽ መስዋእትነት አሳልፎ ስለሚሰጥ ሰብእና ነው የምንነጋገረው።

የሞራላዊ እሴቶች ንቅዘት እና  የክፉ አድርባይነት ልክፍት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን ለመረዳት የተለየ እውቀት ጨርሶ አይጠይቅም።  የአድርባይነት ልክፍት ባለበት የሞራል ጉስቁልና ይኖራል። የሞራል ጉስቁልና ባለበትም አድርባይነት ይኖራል። እነዚህ አስቀያሚ ባህሪያት ከግለሰብና ከተወሰነ ቡድን አልፈው በአገር ደረጃ ሲስፋፉና ሥር ሲሰዱ  የሚያስከትሉት  አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የደህንነት ቀውስ  በእጅጉ አስከፊ ይሆናል ።  በሌላ አገላለፅ እነዚህ ባህሪያት የአንድ አገር የፖለቲካ ሥርዓት እጅግ አስነዋሪ መገለጫዎች  መሆናቸው ቀርቶ ጨርሶ የማያስገርሙ ፣ የማያስደነግጡና  የተለመዱ  እየሁኑ ሲመጡ የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ሳይሆን አጠቃላይ ትውልድን የመግደል አቅማቸው በእጅጉ የበረታ ነው።  የአገሬ ህዝብ የመከራና የውርደት ዶፍ ምክንያት የሆነው የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች አገዛዝ ፍፃሜ አግኝቶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ያደረጋቸው ቀደምት  ተጋድሎዎች በሚያሳዝን አኳኋን  የመኮላሸታቸውን  (ጭንጋፍ የመሆናቸውን) እውነት አስከፊ ካደረጉብን አይነተኛ ምክንያቶች መካከል የሞራል ንቅዘትና የአደርባይነት ልክፍት  ዋነኞቹ  መሆናቸውን የሚጠራጠር ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። ለምን? ቢባል በእነዚህ ደዌዎች የተበከለ ማህበረሰብ  እንኳን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እና ዘላቂና  አስተማማኝ  የጋራ እድገትን  እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ የአንድ አገር ህዝብ ከነችግሩም ቢሆን ለመቀጠል ዋስትና አይኖረውም ።የፖለቲካ ንግዳቸውን ወይም ቁማራቸውን በየጎሳቸው /በየመንደራቸው/ በየቋንቋቸው ማንነት ላይ መሠረት ያደረጉ ገዥ ቡድኖች በተጭበረበረ ምርጫም ይሆን ፖለቲከኛው ጀዋር መሃመድ እንደነገረን በሜንጫ (በገዳይ መሣሪያ) መንበረ ሥልጣን ላይ እስከቆዩ ድረስ የሞራል ንቅዘቱና የአድርባይነት ደዌው ይበልጥ አስከፊ እየሆነ እንደሚሄድ መጠራጠር የማይቀረውን አደጋ ቁጭ ብሎ እንደ መጠበቅ ነው የሚሆነው። እኩያን ገዥ ቡድኖች በይፋ የሚደረገውን ግድያ ለእራሳቸውም ሲሉ በአንፃራዊነት ለማስቆም ወይም ለመቆጣጠር ሊሞክሩ ቢችሉም ጊዜያዊና የውሸት እንጅ ዘላቂና የእውነት ሊሆን አይችልም። የህሊናንና የመንፈስ ሽፍትነትን ከእውነተኛና ቅን ህሊና እና መንስ በሚመነጭ  የተግባር ውሎ እንጅ የአጭር ጊዜ የማስታወስ ችግር አለበት የሚሉትን መከረኛ ህዝብ የጊዜያዊ ማስታገሻ ጥገኛ (ሱሰኛ) በማድረግ ከቶ ሊሆን አይችልም። ሊሆንም አይገባውም። ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የሆነውና አሁንም በተረኛ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች  እጅግ በባሰ አኳኋን  እየቀጠለ ያለው መሪር እውነት ግን  ይኸው ነው።

“የበላይነት ተረኝነት ይገባናል በሚሉ እና የለም የበላይነት ዙፋናችን ጨርሶ አይደፈርም”  በሚሉ  የአንድ አስከፊ ሥርዓት (ኢህአዴግ)  ውላጆች  መካከል በተደረገ ፍትጊያ (ፍልሚያ) አሸንፈው በተረኝነት  ዙፋኑ ላይ የተሰየሙ ኢህአዴጋዊያን /ብልፅግናዊያን ለዘመናት ከመጡበትና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት ውስጥ ተዘፍቀው የዴሞክራሲ ሥርዓት አሸጋጋሪ  ሐዋርያትና የአገር ደህንነት ዋስትናዎች እንደሆኑ ሊያሳምኑን ሲቃጣቸው “እናንተ እነማን ናችሁ ? ለምንና እንዴት? ከየት ወደ የት? በመሬት ላይ ተዘርግቶ በሚነበበው የግፍ ሥራችሁና በርካሽ የፖለቲካ ዲስኩራችሁ መካከል ያለውን የልዩነት ስፋትና ጥልቅት ለማየት ለምንና እንዴት ጨርሶ ተሳናችሁ ?” ብለን ሳንጠይቅ  በግልብ  የስሜታዊነት ፈረስ መጋለባችን ያስከፈለንና እያስከፈለን ያለውን ከባድ ዋጋ ተረድተን ለምን ወደ ትክክለኛው ፍኖተ ለውጥ ለመግባት እንደተሳነን የየእራሳችንን ህሊና መጠየቅ ይኖርብናል።

ስለ ገጠመንና እየገጠመን ስላለው ግዙፍና መሪር ፈተና  ተገቢውን ጊዜ ወስደን ሂሳዊ በሆነ አቀራረብና ይዘት ለመረዳትና  መፍትሄ ለመፈለግ  ባለመቻላችን የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ ማንነት ፖለቲካ  ቁማርተኞች እግሮች ሥር እየወደቅን የመንደፋደፋችን  ውርደት የሞራል ዝቅጠትና የአድርባይነት ደዌ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?  ይህንን አስከፊ ዝቅጠትና ደዌ አሸንፎ  ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ ለመገስገስ ይቻል ዘንድ የየራስን ውስጠ ህሊና ታግሎ ከማሸነና የሚበጀውን ከማድረግ ይልቅ የትንታኔ ድሪቶ መደረት ከቶ ምን ይፈይዳል ? የኢትዮጵያ ሁኔታ (ጉዳይ) እንኳን ፊደል ለቆጠረው ፊደል ለመቁጠር እድሉን ላላገኘው ምሥኪን የአገሬ ሰውም  ግልፅና ግልፅ አይደለም እንዴእጅግ ከባዱ ፈተና የቅን ልቦና እጦት፣የሞራል ልእልና ንቅዘት፣ ልክ ከሌለው አድርባይነት  መላቀቅ ያለመቻል፣ ለአገር (ለወገን)  ከምር  ታማኝ ያለመሆን፣ ልኩን ያለፈ ፍርሃትን (የቁም ሞትን) ለማሸነፍ ያለመቻል ፣ ወዘተ ፈተና እንጅ የረቀቀ ንድፈ ሃሳብ ችግር ከቶ እንዴት ሊሆን ይችላል ?

ለመሆኑ የትኛው ተቋም ነው እነዚህን ጣምራ ፈተናዎች (የሞራል ድቀትና የአድርባይነት ደዌ) ትርጉም ባለው ሁኔታ እየተወጣ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው? መቸም እውነቱን መጋፈጥ ሲሳነን ሰንካላ ሰበብ የመደርደር ክፉ ደዌ ሆኖብን ካልተቸገርን በስተቀር የዚህ ጥያቄ መልስ አሉታዊ እንጅ ከቶ አወንታዊ ሊሆን አይችልም።  አዎ! ለዘመናት እጅግ አስከፊ በሆነ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውና የከረፋው ኢህአዴጋዊ ሥርዓት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ከማድረግ አንፃር ምንም አይነት ትርጉም ያለው የለውጥ እርምጃ ሳይወሰድበት በተረኛ ነን ባዮች በቀጠለበት መሪር እውነታ ውስጥ በሞራል ዝቅጠትና በአድርባይነት ደዌ ያልተበከለና በመልካም አርአያነት የሚጠቀስ ተቋም ይኖራል ብሎ ማመን ወይ የእራሱ የደዌው ሰለባ ከመሆን የሚነሳ ወይንም የለየለት ድንቁርና ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ከገዥው ፖለቲካ ቡድንና ከሚቆጣጠረው የሥራ አስፈፃሚ አካል (the ruling party and the executive branch of government it controls) የሚቀርብላቸውን ጉዳይ የይስሙላ ዲስኩር በመደስኮር እጃቸውን እያወጡ ከማፅደቅና ማህተም ከማሳረፍ ያለፈ ሃላፊነትና ተጠያቂነት ጨርሶ በማይሰማቸው ከፍተኛ ካድሬዎች ከተሞላ ህግ አውጭ አካል (parliament/legislative branch of government) እጅግ አስከፊ የሞራል ዝቅጠትና የአድርባይነት ደዌ እንጅ ሌላ ምን ልንጠብቅ እንችላለን?  አዎ! በተረኛ ፖለቲከኞችና ካድሬዎች አነሳሽነትና ተሳታፊነት እናት ምድር ኢትዮጵያ አያሌ ንፁሃን ልጆቿ በጎሳ ማንነታቸውና በሃይማኖታዊ እምነታቸው ምንነት ከሁለት ዓመታት በላይ እንኳን ለማየት ለመስማትም በሚከብድ ሁኔታ የቁምና የመቃብር ሙቶች ሲሆኑ ለካሜራ (ለሚዲያ ፍጆታ) የሚሆን የአዞ እንባ ጋር የተቀላቀለ ዲስኩር ከመደስኮር ያለፈ ፋይዳ ሳይፈይዱ  መከረኛው  ግብር ከፋይ ህዝብ የሚከፍላትንና በስሙ የምትገኘዋን የእርዳታ ወይም የብድር ገንዘብ  እየተቀራመቱ መኖር ጨርሶ የማይቀፋቸው ከፍተኛ ካድሬዎች ከታደሙበት ፓርላማ  እጅግ አስከፊ የሞራል ንቅዘትና  ክፉ የአድርባይነት ደዌ እንጅ ሌላ ምን ሊጠበቅ ይችላል

ማንኛውንም እኩይ ዘዴ ተጠቅመው በመንበረ ሥልጣን ላይ በሚሰየሙ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ቀጥተኛ በሆነና ቀጥተኛ ባልሆነ ጎጅ ተፅዕኖ (ቁጥጥር) ሥር ከወደቀ የፍትህ አካል (the judiciary branch of government) አስከፊ የሞራል ንቅዘትና ክፉ የአድርባይነት ደዌ እንጅ ከቶ ሌላ ምን ልንጠብቅ እንችላለን? አዎ! በዋስ ወይም ያለዋስ  ወይም በነፃ ከማጎሪያ ቤት እንዲወጣ የወሰነለት/ላት ግለሰብ  በፖለቲከኞች ትዕዛዝ መንገድ ላይ ፖለስ እንደ አዲስ ተጠርጣሪ ተቀፍድዶ/ዳ ወደ ማጎሪያ ቤት ሲወረወር/ስትወረወር “እኔ ምን ላድርግ ፣ ከዚህ በላይ አቅም የለኝም ፤ ከዚህ በላይ መሄድ ደግሞ የኑሮ ማሸነፊያ የሆነውን  የሥራ ዋስትና ያሳጣኛል” በሚል ዳኛ (የህግ ባለሙያ) ከተሞላ የፍትህ ሥርዓት ተብየ እጅግ አስቀያሚ የሞራል ጉስቁልና እና  ክፉ የአድርባይነት ደዌ እንጅ ሌላ ምን መጠበቅ ይቻላል? እስክንድር ነጋንና የነፃነትና የፍትህ ትግል ባልደረቦቹን ጨምሮ በርካታ ንፁሃን ወገኖችን እጅግ በለየለት የፈጠራ ክስና ይህንኑ የፈጠራ ክስ ድርሰት አጥንተው ይመሰክሩ ዘንድ ሥልጠና በሚሰጣቸው እጅግ አሳዛኝ ወገኖች አማካኝነት የሚተወነው ተውኔት አልበቃ ብሎ ዳኛ ተብየውም እንዲህ አይነት ግልፅ የሆነ ፍትህን ያህል ነገር ለርካሽ ፖለቲካ ፍጆታ የማዋል አስከፊ ጨዋታ አካል በሆነበት መሪር እውነት ውስጥ እጅግ አሳፋሪ የሆነ የሞራል ውድቀትና የአድርባይነት ደዌ ካልሆነ በስተቀር  ሌላ ምን መጠበቅ ይቻላል?

ታላቁ የሰላም ምነነትና እንዴትነት በሰላም ሚኒስቴርነትና ሚኒስትርነት  ስም የርካሽ ፖለቲካ ጨዋታ መጫወቻ ካርድ  የመሆኑ መሪር እውነት በግልፅና በግልፅ እየታየበት ያለው ሁኔታ አስከፊ የሞራል መበስበስንና የአድርባይነት ደዌ ሥር መስደድን ካልሆነ ሌላ ምን ሊነግረንና ሊያሳየን ይችላል?

በግል ዝና እና ልክ በሌለው የሥልጣን ፍቅር (narcissism) ፣ በሸፍጠኛ የፖለቲካ ዲስኩር (hypocritical political rhetoric) ፣ ፖለቲካን ከትንቢት መሳይ ሃይማኖታዊ ትርክት ጋር የማቀላቀል (mixing politics with religious belief prophesy) ፣ በግፍ ለተጨፈጨፉና የቁም ስቃይ ላይ ለወደቁ ንፁሃን ደንግጦ ሃዘኑን ከመግለፅ ይልቅ የእራስን ውድቀት የመከላከል (self-defense at any cost; but not expressing a real sense of sympathy to victims of horrifying killings and sufferings) ፣  ወዘተ አስቀያሚ የፖለቲካ ባህሪያት  የተጠናወቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚመራው አስተዳደር (ሥራ አስፈፃሚ የመንግሥት አካል) የሞራል ልእልናንና የአድርባይነት ተፀያፊነትን መጠበቅ ወይ የደዌው ሰለባ መሆነ ወይም የለየለት ድንቁርና ወይም ደግሞ የለየለት የሚዛናዊ ህሊና ድህነት ነው።

 

ሰሞኑን የምርጫ ቦርድ  ተብየው ሹማምንት  “በምርጫ ብቻ!” በሚል  መሪ መፈክር ሥር የሥስት ቀናት “የጠይቁን እንመልሳለን”  ዘመቻ  ማካሄዳቸውን ታዝበናል።  በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን ይህ ቦርድ  የመጠሪያ ስያሜንና የአደረጃጀት ቅርፅን ከመለወጥ አልፎ ያልተራመደውን እና ከእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር አንፃር ምንም አይነት ትርጉም ያለው ለውጥ ሳይደረግበት በተረኛ ነን ባዮች  እንዲቀጥል የተደረገው የበሰበሰና የከረፋ ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ውስጥ ከሌሎች የመንግሥት ተቋማት ተለይቶ የሞራል ውድቀትና የአድርባይነት ደዌ   ሰለባ ላይሆን የሚችልበት ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት የለም። በሌላ አገላለፅ ይህ ቦርድ  የተረኛ ነን ባይ ገዥ ቡድኖች ርካሽ የፖለቲካ መጫወቻ ካርዶች  በመሆን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከመጡበት አስከፊ የሞራል ዝቅጠትና የአድርባይነት ደዌ ጋር እንዲቀጥሉ ከተደረጉ ተቋማት መካከል አንዱ  መሆኑን ማስተባበል መሬት ላይ እየሆነ ካለው መሪር እውነት ጋር በቀጥታ መላተም ነው የሚሆነው።

ታዲያ እንደ ወ/ት ብርቱካን መዴቅሳ ያሉና የነፃነትና የፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ሁሉ ድጋፉንና አድናቆቱን ችሯቸው የነበሩ እህቶች አስቦ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ጊዜ ሳይወስዱ በሸፍጠሻና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን የፖለቲካ ጨዋታ ተጠልፈው ሲወድቁና የማስመሰሉን ተውኔት ለመተውን ሲቸገሩ መስማትና ማየት ባያስገርምም ምነው ከዚህ አይነት አስከፊ አዙሪት መውጣት አቃተን? የሚል እጅግ ፀፀት አዘል ጥያቄን ያጭራል።

ነገረ ሥራችን ሁሉ የተበለሻሸው ለዘመናት ግዙፍና መሪር ዋጋ የተከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ተልእኮና ግብ የህወሃት ህልውና እንዲያበቃለት ወደ ማድረግ ደረጃ  ያወረድነው እለት ነው። የህወሃት መወገድ የመሠረታዊ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ የግድ ከሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ እንጅ በእራሱ ግብ አልነበረም ። አሁንም ሊሆን አይችልም ። የህወሃትን ተልእኮና ግብ በአሽከርነት ሲተገብሩና ሲያስተገብሩ የነበሩ ኢህአዴጋዊያን ስምና የአደረጃጀት ቅርፅ በመቀይር እና ህወሃት/ኢህአዴግን በኦህዴድ/ኦሮሙማ/ብልፅግና በመተካት በዚያው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት መቀጠላቸውን ተቀብሎ የእነሱው ሹመኛ መሆን ያስከተለውና የሚያስከትለው የሞራል ንቅዘትና የአድርባይነት ክፉ ደዌ ከእራስ አልፎ ለዚህ ትውልድ የሚያስተላልፈው መልእክት በእጅጉ አደገኛ ነው።

እንደ ወ/ት ብርቱካን አይነት መልካም የፖለቲካ ሰብእና እና ተሞክሮ ያላቸው (የነበራቸው) ወገኖች የዚህ አይነት እጅግ ግልብ ስሜታዊነት የተጫነው፣ ከአፍንጫ ሥር እርቆ ያልሄደ እና ጨርሶ መልካም አርአያነት የሌለው የፖለቲካ ሰብእና ሰለባዎች መሆናቸውን “መብታቸው ነው” በሚል ደምሳሳ (አጠቃላይ) እውነታ ሸፋፍኖ ለማለፍ መሞከር እራስን ከመሸንገል አልፎ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ በመጠን ሊለካ የማይችል (priceless) ዋጋ የከፈሉትንና በመክፈል ላይ ያሉትን ወገኖች በተንሸዋረረ የፖለቲካ አይን ማየት ነው የሚሆነው።  በነገራችን ላይ  የትክክለኛ መብት እርካታ የሚመነጨው  መከረኛው የአገሬ ህዝብ ከዘመናት የመከራና የውርደት ሥርዓት አዙሪት ሰብሮ በመውጣት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን  ለማድረግ ይቻለው ዘንድ በፅዕናት ቆመው የሚታገሉትን ወገኖች በማገዝ እንጅ የሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞችን በግርግር አስመርጦ የድል ሰርትፊኬት (ማረጋገጫ ወረቀት) ከመስጠት በፍፁም አይደለም።

በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን እነዚህ የምርጫ ቦርድ ተብየ ሹማምንት  እጅግ አያሌ ንፁሃን ዜጎች  ከሁለት ዓመታት በላይ  የግፍ ጭፍጨፋ ሰለባ በሆኑበት መከረኛው ህዝብ በእነዚህ ንፁሃን ወገኖቹ ሃዘን የሚያነባው እንባ ገና ባልቆመበት  ዛሬም እጅግ አያሌ ንፁሃን ዜጎች ከቁም ሰቆቃ ወይም የቁም ሞት ጋር እንደተፋጠጡ በሚገኙበት፣ የነገውና የተነገ ወዲያው እጣ ፈንታቸው ምን እንደሚሆን ፈፅሞ ለማወቅ በማይችሉበት በአንድ ሥርዓት ውላጆች መካከልና በሻእቢያ ተጋባዥነት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የትግራይ ህዝብ የአጠቃላይ ቀውስ ሰለባ በመሆኑ ከእኛ አልፎ ዓለምን በእጅጉ እያሳሰበ ባለበት ፣ የኦሮሙማ ፖለቲከኞች አዲስ አበባን ለመሰልቀት ከፍተኛ ግልፅና ስውር ዘመቻ በከፈቱበት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ በጀምላ  ሲገደሉና አፈር ሲለብሱ ቆመው የተመለከቱ ወይም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያነሳሱና የተሳተፉ የቤንሻንጉል- ጉሙዝ ብልፅግናዎች ለሌላ ጉዳይ በተሰበሰቡበት አጋጣሚ “በሆነው ነገር አዝነናልና ይቅርታ እንጠይቃለን” በሚል በሚሳለቁበት ፣ እንኳን ለፖለቲካ ሥራና ለምረጫ ዘመቻ እንደ ተራ ዜጋ ከቦታ ቦታ ወይም ከአንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ ሌላው ያለ ሥጋት መዘዋወር እጅግ አስጨናቂ በሆነበት ኢትዮጵያ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ሥርዓት አገር ትሆን ዘንድ ከመታገልና መስዋእትነት ከመክፈል ሌላ ምንም አይነት ወንጀል የሌለባቸው የቁርጥ ቀን ወገኖች በየማጎሪያ ቤቱ በሚንገላቱበት፣  እና ከዚህ  ሁሉ በላይ ደግሞ የኢህአዴግን ሥርዓት በኦህዴድ/ኦሮሙማ የበላይነት ለመተካት ከባድና አደገኛ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ግዙፍና መሪር እውነታ  ውስጥ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቱን እያሳለጥነው ነው በሚል ሊያሳምኑን ሲሞክሩ “ምነው ነውር አይደል እንዴ?”ብሎ የሚጠይቃቸው እንጥፍጣፊ ህሊና እንዴት እንደሌላቸው በእጅጉ ያስደነግጣል።  ታዲያ ይህ አስከፊ የሞራል ንቅዘትና የአድርባይነት ደዌ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ብልፅግና በሚል ስያሜ የሰየሙት ኦህዴድ/ኦሮሙማ መራሹ ገዥ ቡድን በመርጫ ቦርድ ተብየው ህግና ደንብ መሠረት ማድረግ ያለበትን ሳያደርግ “ብልፅግና ሆኛለሁና እንዲታወቅልኝ” ሲባል “እሽ እንደ ትእዛዙ ይፈፀማል” ብሎ የተቀበለ እና በሌላ በኩል ግን ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችን “ያንን ወይም ይህንን አላሟላችሁም” በሚል ህልውናቸው እንዲያከትም ያደረገ ምርጫ ቦርድ በምን አይነት  የፖለቲካ ሰብእና፣ የሙያ ብቃት፣የሥነ ምግባር ሰብእና  እና የሞራል ልእልና ነው ስለ ነፃ ፣ ፍትሃዊ፣ዴሞክራሲያዊ ፣ሰላማዊና ባለ እራይ ምርጫ ሊነግረን የሚቻለው ይህን አስተያየቴን ግልፅና ቀጥተኛ ሂሳዊ ትችትን እንደ ነውር ወይም ክብረ ነክ ለሚቆጥሩ ወገኖች በሚመች አገላለፅ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነው። ከዘመናት የመከራና የውርደት ሥርዓት አዙሪት ሰብረን እንዳንወጣ ካደረጉን ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይህ አይነት የመሽኮርመምና ነውር ያልሆነውን ሁሉ እንደ ነውር የመቁጠር ክፉ ልማድ ነውና አላደረግሁትም ፤አላደርገውምም።

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር፣ ምሥረታ ፣ ግንባታና የማያቋርጥ ቀጣይነት እጅግ ወሳኝ ሚና ወይም ድርሻ ያላቸው ተቋማት የሞራል ንቅዘትና የአድርባይነት  ደዌ ተጠቂዎች  በሆኑበት ግዙፍና መሪር የኢትዮጵያ ፖለቲካ  እውነታ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይወለዳል ብሎ እንኳን ለማመን ለማሰብም ይከብዳል። ተረኞቹ ገዥዎቻችን  ለዘመናት በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሠበሰውና የከረፋው ሥርዓተ ህወሃት/ኢህአዴግ  እንደ ሥርዓት የቆመባቸው አደገኛ መዋቅራዊ ምሰሶዎቹ ፣ ህገ መንግሥት ተብየው ፣ አስተሳሰቦቹ ፣ወዘተ ጨርሶ ባልተነኩበትና እንዲያውም ይባስ ብሎ መከረኛ ንፁሃን ዜጎች ከሁለት አመታት በላይ  ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ  የመከራና የውርደት ዶፍ ሰለባዎች መሆናቸው መረጃ ጥቀሱ በማያሰኝ ሁኔታ ግልፅና ግልፅ ሆኖ እያለ “ከህወሃት/ኢህአዴግነት ወደ ኦህዴድ/ኢህአዴግ/ብልፅናነት ተሸጋገረናልና ምርጫዎቻችሁ እኛና እኛ ብቻ እንሁን ፤ ለዚህ ደግሞ ሥርዓትና ደንብ ሳንከተል የምሥራች ብለው የተቀበሉን (ለነገሩ ወደው አይደለም የሚቀበሉን)  የምርጫ ቦርድ ሹማምንቶቻችን ምሥክሮቻችን ናቸው” የሚል አይነት እጅግ የለየለት ስላቅ ሊሳለቁ ሲቃጣቸው መታዘብ በእውን የነፃነትና የፍትህ አርን ለሚናፍቅ የአገሬ ህሊናን ያቆስላል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሬት ላይ ተዘርግቶ ከሚነበበው ግዙፍና መሪር ሃቅ በተቃራኒ  ከግልብ ምናቡ (ስሜቱ) እየመዘዘ እና እጅግ አሳሳች በሆነ የሰላ አንደበቱ የዲስኩር ድሪቶ እየደረተ “የተዋጣልኝ ዴሞክራት አሸጋጋሪ ነኝና እመኑኝ!” እንደለው (እንደሚለው) ሁሉ የምርጫ ቦርድ ተብየው ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን  ሜዴቅሳም ምርጫ ተብየው የሚካሄደው መረጋጋት፣ ሰላምና ደህንነት ባለባት አገር ውስጥ ይመስል በሰሞኑ “ጠይቁን እንመልሳለን” ዘመቻ “በእኛ ላይ እምነት ልታሳድሩ ይገባል” የሚልና መሠረታዊ የህዝብን ግንዛቤ በእጅጉ የሚያጎሳቁል ዲስኩር ውስጥ ግብታ ስትቸገር ማየትና መስማት ቢያንስ ህሊናን በእጅጉ ይጎረብጣል።

ታዲያ ይህን አይነቱን አስተሳሰብ፣አቋምና አካሄድ “የሞራል ዝቅጠትና የአድርባይነት ደዌ ሳይሆን ታሪካዊውን የዳግማዊ ኢህአዴግ ለውጥ ማገዝ ነው” የሚል እጅግ ስንኩል የመከራከሪያ ድሪቶ ከመደረት በግልፅ፣በቀጥታና ገንቢነት ባለው አኳኋን መሪሩን እውነት መጋፈጥና መላልሰን ከምንዘፈቅበት አዙሪት ወጥተን ወደ እውነተኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደንን  ፍኖተ ፈልጎ ማገኘት ነው የሚሻለው።

 ስምና የበላይ አለቃ ቀይሮ የቀጠለውን ኢህአዴጋዊ ሥርዓት እንደገና ሌላ ሦስት ዓሥርተ ዓመታት ይገዛ ዘንድ ለመምረጥ ( በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተበከለ ሥርዓት ምኑ እንደሚመረጥ አላውቅም) ዝግጁ ሆኖ መገኘት ጨርሶ መድሃኒት የሌለው አባዜ ልክፍት ካልሆነ በስተቀር እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊነት ከቶ ሊሆን አይችልም!

ክፉው ሳይሆን በጎው ይሆን ዘንድ እየተመኘሁ አበቃሁ!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop