አድዋ ይመስክር (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

የጦር እምቢልታ ባድዋ ሲነፋ

በለው! ስትባል ወደ ፊት ግፋ!

ዳማው ፈረስህ እየደነፋ

ለዓለም ሊያውጅ ያፍሪካን ተስፋ

አንጸባረቀ የጋሻህ ጣፋ።

የጋሻህ ጣፋ ቢያጥበረብረው

ጠላት ወደቀ ራሱን አዞረው

ከፈረስ ወርደህ ገብተህ ጨበጣ

ጠላትክን ገድለህ ማርከህ ስትመጣ

የዳኘው አሽከር! ብለህ ስትፎክር

ያድዋ ተራራ ነበር ምስክር

ያድዋ ተራራ የሰሜኑ በር

የተኮፈሰው ርቆ ከድንበር

ታሪክ መዝግቧል ጠላት ሲሰበር

ጠላት ሲሰበር ሲበለሻሽ

እግሬ አውጭኝ ብሎ ነቅሎ ሲሸሽ

ማልዶ የወጣው ገና ሳይነጋ

ሽቅብ ቁልቁል ሲል ውሎ ሲዋጋ

ወገን ድል ቀንቶት ምርኮ ሲያንጋጋ

ሲሸልልና ደግሞም ሲፎክር

ያየው ተራራ አድዋ ይመስክር።

አድዋ ይመስክር ከየጠረፉ

የተጠሩና የተሰለፉ

የኢትዮጵያ ልጆች ልሳነ ብዙ

ጉንዳኖች መስለው እየተጓዙ

ባንድ ላይ ወድቀው እየተነሱ

የጠላትን ጦር እንደመለሱ።

ቅኝ ተገዝቶ እየማቀቀ

ባርነት ገብቶ ለተጨነቀ

የተስፋ ጮራ የፈነጠቀ

አድዋ ይመስክር ጀግናው ተራራ

የኢትዮጵያ አንድነት ምን እንደሠራ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሬ ሆይ! - በላይነህ አባተ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share