በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
አማራ ሆይ! ብአዴን የሚባል የምሳር እጀታ ህወሀት በሚባለው ምዕራባውያንና አረቦች በቀጠቀጡት ምሳር ገብቶ ከሰላሳ ዓመታት በላይ አስጨፍጭፎኻል፡፡ ብአዴን በሰማእታት መሰዋእትነት ህወሀት ተሚባለው ምሳር በግድ ሲላቀቅ ደሞ ወነግ ተሚባለው ምሳር እንደ አመንዝራ ተሰክቷል፡፡ ትናንት በህወሀት የምሳር ቀለበት ሰተት ብሎ ገብቶ አንተን ሲያስገድል፣ ሲያሳር፣ ሲያስገርፍ፣ ሲያሰልብ፣ ሲያሰድድ፣ ሲያደኸይ፣ ሲያሳምምና አንገት ሲያስደፋ ኖሯል፡፡እንደ አለመታደል ዛሬ ደግም ያለወላጅ ፈቃድና ያለሰርግ ራሱን ለወነግ ምሳር ድሮና በቀለበቱ እንደ ቅርቃር ተቸክሎ ከሌላው ቀርቶ ከቤጌምድር፣ ከወሎ፣ ከሸዋና ከጎጃምም አማራን ሲያስጨፈጭፍና እንደ ዘፀዐቱ ዘመን ሲያሰድድ ይውላል፡፡ እንግዲህ ይኸንን እንደ ደን የሚያስጨፈጭፍህን እጀታ እስከመቼ በትከሻህ ትሸከማለህ?
በአምስቱ ዘመን የአማራ ተጋድሎ በባንዳነት ያገለገሉ እርጉሞች ከነፃነት በኋላ ተሸማቀው አካካባቢያቸውን እየለቀቁ ከማይታወቁበት አገር ጅራታቸውን እንደ ውሻ ወትፈው ይኖሩ ነበር፡፡ ዓይን አውጣ ብአዴናዊ ባንዳዎች ግን የሰማእታትን ድል ቀምተው የባርነት ወንበራቸውን ለመጠበቅ ለነፃነት የሚታገሉትን ወጣቶች ህወሀት ባሰለጠናቸው መንገድ ሲያሳድዱ ይውላሉ፡፡ በአዴፓነት እንደታደሱና ብአዴን ከድሮ ገራፊ አለቃቸው በረከት ጋር ወህኒ የገባ አስመስለው ያታልሉኻል፡፡ አንዳንዱ ዘልዛላ አማራና እየደሰኮሩ አማራን በማስፈጀት ላይ ያሉ ድስኩራም ምሁራንም አዴፓ ኮርቻና ጋላቢ የተቀየረለት ብአዴን መሆኑን ዘንግተዋል፡፡
አዴፓ የሚለው ሥም የብአዴንን መልክና ምንነት አይቀይረውም፡፡ አዴፓ የሚለው ስም ብአዴን ለሰላሳ አመታት በአማራ ሕዝብ የፈጠመውን ወንጀልና ክህደት እንደ እንዶድ አያፀዳውም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን የህወሀት አጋሰስ ሆኖ እየተጫነ ያዘረፈውን ሐብት አያስመልሰውም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን የአማራን ዓይን ጨፍኖ ለህወሀት ያስረከባቸውን ራያን፣ ሁመራና ወልቃይትን አይመልስም፡፡
አዴፓ የሚለው ማታለያ ብአዴን ከቢሮው ጣራ አልሞ ተኳሽ አንጠልጥሎ ባህርዳር ያሰዋቸውን ወጣቶች ነፍስ አይመልስም፡፡ አዴፓ የሚለው ጅል ስም ብአዴን በህወሀት አሽከርነት በድብቅ ስፍራዎች ያስቀበራቸውን፣ ያሰለባቸውን፣ ያስገረፋቸውን፣ ያስጠለፋቸውና አካለ ጎደሎ ያስደረጋቸውን ዜጎች አይታደግም፡፡ አዴፓ የሚለው ሥም ብአዴን በአምባ ጊዮርጊስ፣ በጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ዳንግላ፣ ቡሬ፣ ወልዲያ፣ ማጀቴና ሌሎችም ቦታዎች ያስፈጃቸውን ዜጎች አያስረሳንም፡፡
ብአዴን “አያገባኝም” እያለ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በሻሸምኔ’ በዝዋይ፣ በአዳሜ ቱሉ፣ በባሌ፣ በጉራፈርዳ፣ በጎሬ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ በደራ’ በሀረር፣ በድሬዳዋና ሌሎችም ሥፍራዎች በዘራቸው ለተፈጁት አማሮች ታሪክ ሲከሰው የሚኖር የእንዴህ ልጅ ነው፡፡
ብአዴን ዛሬም የድሮ ጌታው ህወሀት ያወጣለትን የእጅታ ስም የቀየረው የዛሬውን ጌታውን ወነግ ቁጥር 2 ተከትሎ ነው፡፡ ወነግ ቁጥር-2ን እንደ ዓይነ-ሥውር እየተከተለ የብአዴን ሥራ ግን ዛሬም አማራን እንደ አልተፈለገ ጫካ ማስጨፍጨፍ ነው፡፡ ይህ የማያቋርጥ የብአዴን የሎሌነት ባህሪ የሚያመለክተው የብአዴን “መሪዎች” የባርነት ጅን ተሸካሚዎች መሆናቸውን ነው፡፡ የምርምር ሥነ-ምግባር ቢፈቅድና እነዚህ እጀታዎች የዘር ሰንሰለታቸው (ክሮሞዞማቸው) ቢጠና እንደ ጠማማው እንጨት የሎሌነት ጂን ተሸካሚዎች ሆነው እንደሚገኙ እሙን ነው፡፡
አማራ ሆይ! ብአዴን ሞልቶ ለማይመርገው ሆዱና ነገ ለሚበሰብሰው ሥጋው ሳስቶ በመላ አገሪቱ እያስፈጀህ ነው፡፡ አንተ አገር እንጅ እንደ ጋማ ከብት ታስረህ የምትውልበት ክልል ኖሮህ አያውቅም፡፡ በክልል እግር ብረት አስሮ ዘርህን እያስጨፈጨፈ ያለው ተድንጋይ ዘመን ምሳር ጋብቻ የፈጠመ ብአዴን የተባለ እጀታ ነው፡፡
አማራ ሆይ! አያት ቅድመ አያቶችህ ነፃነቷን አስከብረዋት በኖሩት አገር በሰላምና በክብር መኖር የምትችለው ብአዴን የተባለውን እጀታ ተጫንቃህ ስታወርድ ነው፡፡ የሎሌት ጅን ተሸካሚ በሆነው እርጉሙ ብአዴን እጀታነት ባለቤት እንደሌለው ጫካ የምትጨፈጨው እስክ መቼ ነው?
እባክህ አማራ የሚያጨፈጭፍህን የምሳር እጀታ ከተከሻህ አሁኑኑ አውርደው!
ጥቅምት ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ.ም.