የወያኔን የማያባራ ጥፋት በማስቆም ሂደት መሟላት ያለባቸው ወሣኝ ቅድመ ሁኔታዎች! – አንድነት ይበልጣል -ሐዋሳ

የለውጥ ኃይሎች ሙሉ ትብብር፣ የረቀቀ የቀዶ ሕክምና ሥራ (surgical precision“)

እና እጅግ ያነሰ የሕዝብ ጉዳት (collateral damage“)

አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ – ጥቅምት 22 / 2013

የዚህ ትንሽ ጽሁፍ ርዕሥ፣ ሀሳቡ የተገኘው ከ”ከድር ሰተቴ” ነው፡፡ ከቀናት በፊት “ከሁሉም ጥፋትና ክፋት ጀርባ ሕወሐት አለ!” በሚል ርዕስ ትንሽ አስተዋጽኦ ለማድረግ ሞክሬ ነበር፡፡ ለዚህ አስተዋጽዖ ከድር በሰጠው ጠቃሚ አስተያየት ላይ፡ “ተንታኝ” የተባለው ሁሉ “እርምጃ ይወሰድ” ይላል እንጂ “ምን ዓይነት እርምጃ?” ስትለው መልስ የለውም” ሲል ትዝብቱን በቁጭት ገልጧል፡፡ ዕውነቱን ነው፤ ከድር በማከልም “በአጭር ጊዜ (swiftly!) መልስ የሚሰጥ እርምጃም አለ ብዬ አላስብም” ብሏል፡፡ አሁንም ዕውነቱን  ነው፤ በተጨማሪም የወያኔን ጥፋት በማስቆም ሂደት ውስጥ “surgical precision” እና “we have a hostage situation here” የሚሉት ቁምነገሮች ሊጤኑ እንደሚገባ ከድር በአስተያየቱ አጽንዖት ሰጥቶ ጠቁሟል፡፡ በኔ እምነት፣ እነዚህም በጣም ዕውነት ናቸው! ለዚህ ጽሁፍ ርዕሥም ሆነ ለይዘቱ መነሻ የሆኑት እነዚህ የከድር ቁልፍ ነጥቦችና ጥያቄዎች መሆናቸውን አለመግለጽ አይቻለኝም፡፡ ይህን ትንሽ ጽሁፍ እንድሞክር ያደፋፈረኝ፣ የከድር ትዝብትና ሥጋት፣ ዕውነትም የእኔም ምናልባትም የብዙዎችም ሥጋት ስለሆነ ነው፡፡

ለነዚህና መሰል ከባድ ሚዛን ትዝብቶች፣ ጥያቄዎችና ችግሮች፣ በትንሽ ማስታወሻና በአንድ ግለሰብ ዜጋ ብቻ መልስ ማቅረብ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የዚህ ትንሽ ማስታወሻ ቀዳሚና ዋና ዓላማ፣ በዚህ አቅጣጫ ማሰላሰል፣ መወያየት፣ ሀሳብን ማጥራትና ማጋራት እናም አጠናክሮና አቀናጅቶ ጠቃሚና የሚሠራ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ እንዲጀመር ማስታወስና መጎትጎት ብቻ ነው፡፡

የወያኔን አላባራ ያለ ጥፋት ለማስቆም የሚጠብቁን ዋና ዋና ተግዳሮቶች

የወያኔን አላባራ ያለ ጥፋት በተግባር ማስቆም፣ ተወግዶ ለማየት የመፈለግንና የመመኘትን፣ የማውገዝን፣ ውሳኔ ሰጪዎችን የመጎትጎትንና አልፎም የመኮነንን ያህል ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የመፍትሔ አካል መሆን እያለበት ነገር ግን ሳያውቅ የችግሩ አካል የሆነ፣ ወቅትን ባላገናዘቡና ባልጠበቁ ልዩ ልዩ አጀንዳዎች የተወጠረ፣ የሚጓተትና የሚገፋፋ፣ መኮነን እንጂ የሌሎችን ችግርና ሁኔታ መረዳት፣ መታገሥና መደገፍ የማይቀናውን የልሂቃንን ስብስብና ተከታዮቻቸውን ይዘን ለውስብስብ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፤ ገና ተጨማሪ ጊዜ፣ ልፋት፣ ጥበብና ትዕግሥት ይጠይቃል፡፡ ወያኔን መገላገል በነጻ አይገኝም፤ ዋጋ የማይጠይቅ  (risk free) ነገር የለም፡፡

ወያኔ በአንድ በኩል የሕዝባችንንና የሐገራችንን ህልውና በቀን በቀን እየተፈታተነ – ዋና ፈተናችን ሆኖ – ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ፈጣን እርምጃ እንዳትወስድበት ጥፋቱን ሁሉ የሚፈጽመው በትግራይ ሕዝብ ውስጥ ተሸጉጦና ሕዝቡን ሰብዓዊ ጋሻ አድርጎ ተከልሎበት ነው፡፡ አሁንም በሌላ በኩል ከወያኔ ጥፋት ከገፈቱ ዋና ቀማሾችም በባሰ መልኩ፣ በአንድ ሩቅ ማዕዘንና ጫፍ ላይ ብቻ ቆመው ችግሩን በገዳዳው የሚመለከቱና የሚታዘቡ ወገኖች የሚሰጡት ፍርድ፣ የሚፈጥሩት ተገቢ ያልሆነ ውጥረትና ጫናም አለ፤ የለውጡን ቡድን ¨ፈጥነህ እርምጃ አልወሰድክም¨ ብለው ይከሳሉ፣ የለውጡ ቡድንም ተገቢና ተገቢ ያልሆኑ ተቃዋውሞዎችን በማስተናገድ መንፈሱም ሞራሉም ሊዝል ይችላል፡፡ ትኩረቱ ይበተናል፤ ኃይሉም የመበተን ዕድል አለ፡፡ በአጥፊዎች ላይ የተቻለውን ያህል እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ደግሞ (የውስጥ ሻጥሩን ሳናነሳ) ወያኔ፣ ፈረሶቹና ሁሉም ዓይነት ጽንፈኞች የዋህ ተከታዮቻቸውን አሳስተውና አነሳስተው፣ በዓለም አቀፍ አጋሮቻቸውም ታጅበው ውግዘቱን ያወርዱበታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሂትለርና ሙሶሊኒ መጨረሻ ለአቢይና ሸመልስም አይቀርላቸውም!!

እኔ እንደሚመስለኝ ግን ከወያኔ መራሹ ተግዳሮት የማይተናነሰውና ለለውጡ ቡድን ትልቅ የሚባለው ፈተና የሚመጣው ከራሱ ከውስጡ ነው፡፡ በመንግሥት ውስጥ ያሉት ቀልባሾችና ተረኛ ገዢ ለመሆን የሚሠሩት ኃይሎች የዋዛ ሤረኞች አይደሉም፤ ተባብረው መንግሥት መውሰድ የሚገባውን የማስተካከያ እርምጃ ሆን ብለው ያዘገያሉ፤ ወይም ትክክለኛውን እርምጃ ወደጎን ብለው መንግሥት መውሰድ የማይገባውን ቀልባሽና ነገር ፈላጊ እርምጃ እንዲወስድ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ለተጀመረው ለውጥ እጅግ አደገኛውና ሙሉ ትኩረት የሚሻው ተግዳሮት በመንግሥት ውስጥ ያሉ ቀልባሾችና አዲስ እያቆጠቆጡ ያሉት ተረኛ ገዢዎች የሚፈጥሩት ነው፡፡ ይህ የውስጥ ተግዳሮት የለውጡን መንግሥት አመኔታ ይቀንሳል፤ ወያኔ ከመንግሥት ውጭ ሆኖ እየፈጠረ ካለው ጥፋት ጋር ሲቀናጅ እና ወይም ሲገጣጠም ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡

ይህን የውስጥ ሻጥር ችግር በጣም የሚያባብሰው ሌላ ተያያዥ ነገርም አለ፤ ይኸውም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ልሂቃንና ተከታዮቻቸውን የሚመለከት ነው፤ እነዚህ ወገኖች ¨የተረኛ ገዢዎች ችግር ባይኖር የወያኔ ችግር ዕዳው ገብስ ነው¨ በማለት ወያኔ የጋረጠብንን ፈተና ያቃልላሉ፤ ብዙ ሰውንም ያዘናጋሉ፡፡ እናም የክፋትና የጥፋት ፋብሪካ የሆነውን ወያኔን መታገል ላይ ዳተኛነት ያሳያሉ፡፡ ትኩረታቸውን በመንግሥትና በገዢው ፓርቲ ውስጥ ባደፈጡ ቀልባሽና ተረኞች ላይ ብቻ ቢያደርጉ እንኳን “የአባት/የእናት“ ነበር! እነዚህ ልሂቃንና ተከታዮቻቸው ግን በመንግሥት እና በገዢው ፓርቲ ውስጥ የለውጥና ጸረ ለውጥ ኃይሎች መኖራቸውን ለመቀበል እንኳን ዝግጁ አይደሉም/ ፍላጎት የላቸውም፡፡ የወያኔን አላባራ ያለ ጥፋት ለማስቆም ከሚጠብቁን ዋና ዋና ተግዳሮቶች መካከል የባሰው ተግዳሮት ይህ ነው፡፡ እነዚህ አካላት ትግላቸውን በአንደኛው እጃቸው ከወያኔ በሌላኛው እጃቸው በመንግሥት ውስጥ ካሉ ጸረ ለውጥ ኃይሎች ጋር ማድረግ ሲኖርባቸው በተገላቢጦሽ እያደረጉት ይገኛሉ፤ መንግሥትን እንዳለ እንደ አንድ ውሁድ ጸረ ለውጥ ኃይል በመፈረጅ ትኩረት፣ ጊዜ፣ ጥረትና ኃብታቸውን ሁሉ በዶ/ር ዓቢይ የሚመራውን የለውጥ ቡድን በጅምላ በመኮነንና በመታገል ላይ ያውላሉ፡፡ ይህ ሁሉ በሌላ በኩል የሚያሳየው የኃይል አሰላለፉ እጅግ መዘበራረቁን ነው፡፡ ይህም የለውጡ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ በ50 – 60 ብሔር ብሔረሰብ ተቧድኖ ¨ድንበር ዘለል¨ መላፋቱ ተባብሶ ቀጥሏል፤ ዞን፣ ክልል እንሁን (አዲስ አበባም ተጀምሯል) የሚለው መጓተትና መገፋፋት እንደቀጠለ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ብሔርተኞችም መሐል ብሔራዊ መግባባት የሚባል ጠፍቶ በረባ ባልረባው እርስ በርስና በመንግሥት ውስጥ ካለው የለውጥ ቡድን ጋር መጓተትና መገፋፋቱ ብሶ ይታያል፡፡ የነባልደራስ፣ መኢአድ እና ኢዜማን ወዘተ የቅርብ ጊዜ ልፊያ ያስታውሷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አስማተኛው የኢኮኖሚ እድገት! (በ ገብርኤሉ ተስፋዬ)

የወያኔን ጉዳይ ይበልጥ አደገኛ የሚያደርጉብን ዋና ዋና ተግዳሮቶች

ወደ ወያኔ ጉዳይ እንመለስ፤ የወያኔን ጉዳይ አደገኛ ከሚያደርጉብንና ወያኔን በልዩ ጥንቃቄም እንድንይዘው ከሚያስገድዱን በርካታ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ እነዚህ ይመስሉኛል፡፡ ፡

ሀ) ወያኔ የሚፈጽመውን ሁሉ ግፍ የሚፈጽመው ራሱ ለአሰርታት የዘራውን የዘረኝነት መርዛማ ፍሬና ውጤቱን እያጣጣመና እየተጠቀመ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

ለ) ወያኔ አላባራ ያለውን ጥፋቱን በመላ ሕዝብና በሐገር ላይ የሚፈጽመው በትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ ተሸጉጦና ሕዝቡን በሰብዓዊ ጋሻነት ተከልሎበትም ነው፡፡

ሐ) ወያኔ ከትናንት ዛሬ በጣም መዳከሙ ግልጽ ነው፡፡  ነገር ግን እንደው ለማጥላላት ብለን እንደምንጠራው ተራ ሽፍታም አይደለም፡፡ ወያኔ ቀድሞም ያካበተው፣ አሁንም ጨርሶ ያልተቋረጠ ሕጋዊና ሕገወጥ ሐብትና ምንጭ አለው፡፡ ዓለም አቀፍ የተደራጀ ወንጀልን የሚያስታውሰን ኔት ዎርኩና ልምዱ፣ የሰው ኃይሉና የሎጂስቲክ ቁመናውም የሚናቅ አይደለም ወዘተ፡፡ የወያኔ ቀሪ አቅም መናቅ የለበትም የምለው ከኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አቅም ጋር በማነጻጸር አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ጥያቄው ትከሻ የመለካካት አይደለም፡፡ ወያኔ አነሰም በዛም አደጋ የማድረስ አቅሙ ገና እንዳለ ለማሣየት ብቻ ነው፡፡

የወያኔን የማያባራ ጥፋት ለማስቆም በቅድሚያ ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮች፡

1ኛ) በወያኔ ላይ መወሰድ ያለበት እርምጃ አሁን ተጀምሮ አሁን የሚያበቃ የአንድ ጊዜ እርምጃ ተደርጎ መታየት የለበትም፤

2ኛ) ወያኔን ለማስወገድ በሁሉም መስክ ማለትም በፖለቲካ፣ በመረጃና ደህንነት፣ በወታደራዊ፣ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣ በውጭ ግንኙነት፣ በባህል  በስነልቦና፣ በሜዲያና በመሳሰሉት ተደጋጋፊ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፤

3ኛ) የወያኔን አላባራ ያለ ጥፋት ለማስቆም እንደተባለውም በየዘርፉ የረቀቀ የቀዶ ሕክምና ሥራ (“surgical precision”) የሚጠይቅ መሆኑ፤

4ኛ) ወያኔን የመገላገሉ ተልእኮና ሥራ የትግራይን ሲቪል ማኅበረሰብ ዒላማ ማድረግ እንደሌለበት በለውጡ ቡድን (በመንግሥትም) ይታመናል፡፡ (ዕውነቱን በግልጽ ለመናገር)፣ የሚወሰዱ አንዳንድ እርምጃዎች ሕዝቡን መንካታቸው ፈጽሞ የማያመልጡት ነገር ከሆነም ጉዳቱ (“collateral damage”) እጅግ አነስተኛና አጭር ዕድሜ ያለው ሊሆን ይገባል፤ ራሱም ለ29 – 45 ዓመታት የወያኔ ሰለባ ሆኖ የቆየው የትግራይ ሕዝብ በመፍትሔው ሂደት አላስፈላጊ ዋጋ እንዳይከፍል የሚቻለው ሁሉ መደረግ አለበት፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማራና ኢትዮጵያዊነት፤ በጠላትም በወገንም እስከ ሞት

5ኛ) የላቀ ልምድ ባላቸውና ኃላፊነት በሚሰማቸው ከየሙያ ዘርፉ በተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ ጥልቅና ዝርዝር ጥናትና ዝግጅት ማድረግ ይገባል፤

6ኛ) በእቅድ ዝግጅትም ሆነ በአፈጻጸም ወቅት ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ጥበብ፣ ጥንቃቄ፣ ትኩረት፣ ጽናትና ቁርጠኝነት ወሣኝ መሆናቸውም ይታመናል፤

7ኛ) በተለይ በመፍትሔው አካላት ዘንድ አንድ ልብ መሆንና መናበብ፣ በበቂ የተጠና፣ በዋናዎቹ ቀዶ ጠጋኞች በኩል በሚገባ የታወቀና ስምምነት የተደረሰበት የመፍትሔ ስልት፣ ቅደም ተከተል የጠበቀና በከፍተኛ ምሥጢር የሚመራ ፈጣን እርምጃም ይጠይቃል፡፡

8ኛ) ለውጡ መሥመሩን ሳይስት ወደፊት እንዲገፋ በጽኑ የሚሹ ኃይሎች (ከመንግሥት ውጭና በመንግሥት ውስጥ ያሉ) ቢያንስ በሁለት – ሦስት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርብ ሆነው ተጋግዘው ለመሥራት ቁርጠኝነት ማሣየት አለባቸው፡

ሀ) ወያኔን አደብ በማስገዛት፡ ወያኔ ከእንግዲህ የሕዝብ ሰላም፣ የሐገር አንድነትና የሉዓላዊነት ስጋት መሆኑ እንዲቀር በማድረግ ረገድ፤

ለ) በምርጫ፡ በመጪው ግንቦት/ሰኔ (2013) ሊካሄድ የታቀደው ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ እንዲሆንና ሕዝባችንና ሐገራችን ወደ ዲሞክራሲ የሚያደርጉት ሽግግር አሁንም እንዳይከሽፍ በማድረግ ረገድ፤ በተለይ የተቻለውን ያህል ከተሣካ ምርጫ በኋላ በሚቋቋመው የሕዝብ መንግሥት አነሳሽነትና አመቻችነት፣ እጅግ እያወዛገበ የሚገኘውና ለብዙ ሐገራዊ ችግሮቻችን ሥርዓታዊና ተቋማዊ መንስኤ የሆነው ሕገመንግሥት የሚሻሻልበት ሁኔታ ላይ መሥራት፤

ሐ) ብሔራዊ መግባባት፡ ከመንግሥት ውጭ ያሉ የብሔርም ሆነ የዜግነት (ሲቪል) ፖለቲካ የሚያራምዱ የለውጥ ኃይሎች እና በመንግሥት ውስጥ ያለው የለውጥ ኃይል እንዲሁም ሌሎች አግባብ ያላቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ በተመረጡ አንኳር ሐገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በሰፊውና በተከታታይ ተወያይተው ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስና በዚያው መንፈስና ልክ ደግሞ ወደ ተግባራዊ የትብብር ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡

ወያኔን የማስተካከያ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ የሚጠበቁ ተከታታይ እርምጃዎች

  • ነገሮች ሁሉ በፍጥነት ተረጋግተው ወዲያውኑ ሥራ እንደ ወትሮው መቀጠል አለበት፤
  • የአስተዳደር ክፍተት እንዳይፈጠር ተተኪ ጊዜያዊ አመራር (የትግራይ ብልጽግናና የለውጥ ኃይሎችን ያካተተ) ከላይ እሰከታች አስቀድሞ ማዘጋጀትና ወዲያውኑ ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል፤
  • የትግራይን ሕዝብ በፍጥነት ለማረጋጋትና ዕምነቱንም ለማግኘት፣ ተጨባጭ የፖለቲካ፣

የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ፣ ማሕበራዊ፣ ባህላዊና ልዩ ልዩ የሜዲያ ሥራዎች አስቀድሞ ታቅደው መሠራት ይኖርባቸዋል፤

እዚህ እንደዓቅሜ ለማቅረብ የሞከርኩት ጥቅል የሆነ የመፍትሔ መርሆዎች፣ ሥርዓቶችና አቅጣጣዎችን ነው፤ ሌላ ምን አላችሁ? ዕውነት ለመናገር እኔ ለራሴ ዝርዝር መፍትሔ ሰጪ አካል ብሆን ብዬ ገና ሳሳብ ይደክመኛል! … ይቻላል፣ ነገር ግን ቀላል አይደለም! ፈጣሪ ይርዳን!!

 

2 Comments

  1. የለውጥ ኃይል ተብዬው ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ወደ ስልጣን ሲመጣ ይናገር ከነበረው በተቃራኒ ሄዶ የነበረዉን የህዝብ ድጋፍ አጥቷል።የትግራይንም ጉዳይ አወሳስቧል።ይህ የሆነው እንደ አገር ከማሰብ ይልቅ ከአሳዳጊዉ ጌቶቹ የባሰ ጎጠኛ በመሆኑ ነዉ ።ለዚህ ደግሞ ስትራቴጂውን ሽመልስ ነግሮናል።መንግስትም ሳይዛነፍ በተግባር አሳይቶናል።እንደሚባለዉ አቢይ የTPLF ን ጉዳይ ይበልጡኑ ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀመበት እንጂ ለመፍትሄ አይደለም። ጠተቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ የሚንቀሳቀስበት ባህርይ የለዉም።

  2. አንድነት፤
    What a difference a day makes! ወለጋ የሆነው ነገር የለውጡን ህይል ለመከላከል እማይቻልበት ከፍታ ላይ እየወሰደው ነው (indefensible የሚባለው ኣይነት!)፡፡ “ሽኔ ተደመስስ” ተብለን መከላከያ እግሩ በወጣ 24 ሰአት ሳይሞላ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ጭፍጨፋ እንዴት ይካሄዳል? ክምናስበው በላይ በጣም የተቀናጀ ጥፋት የተደገስ ይመስላል፡፡
    የተሳካ ኢትዮጵያን የማፍረስ ፕሮጀክት አማራን ክማፍረስ ይጀምራል፤ ወይም አማራን ከሌሎች ጋር እንዲተናነቅ ማድረግ፤ ቅኝ ገዢዎችም፤ ጠላቶችም፤ ወያኔም ለዘመናት ይህንኑ ነው ያራመዱት፤ ምንም አዲስ ነገር የለውም፤፤ ስለሆነም አማራን በተከታታይ ጥቃት ገፍቶ ራሱ (በአብዛኛው እንወክለዋለን በሚሉት አማካይነት) ኢትዮጳያን የማፍረሱ ፕሮጀክት ተባባሪ እንዲሆን ማድረግ፡፤
    እንዴት? አማራን መጨፍጨፍና ማስጨፍጨፍ፤ (በነገራችን ላይ ይህ የተጀመረው ዛሬ አይደለም፤ ወያኔና ሻቢያ ደርግ ከመውደቁ በፊት ደምቢ ዶሎ ላይ ይሁን አሦሣ ላይ በኦነግ በኩል ፈጽመውታል)፤ አማራን የተጠቂነት፤ የቁጭትና የእልህ ሥነልቦና ላይ በማድረስ፤ ብልጽግና እና አቢይ ላይ እንዲነሳሳ ማድረግ፡፤
    ማስረጃ የሚሆኑ ምልክቶች፤
    1። ሥዩም መስፍን ጦርነት ካለ በሁሉም አቅጣጫ ነው አለን፡፡ አቢይ እምቢ ሲለው እሱው ጀመረው፤፤
    2። ዓይጋፎረም ሥዩም ያለውን ደገመና “ጦርነቱ ትግራይ ውስጥ ብቻ አይሆንም፤ ሁሉም ቦታ ነው” አለን፤፤ ከልምድ እንደሚታወቀው አይጋፎረም የሚለውን ወያኔ ይፈጽማል።
    3። የወለጋው ጥቃት ተፈጸመ፤፤
    አሁን ምን ይደረግ?
    1። እንዳልከው “surgical precision” አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል (unattainable)፤፤ የቀነሰ “ኮላተራል ዳሜጅ” ሊሆን ይችላል፤፤ አሁንም ጥያቄው ለ”ትግራይ ህዝብ” ተብሎ ወያኔን “እሹሩሩ” በማለት ኢትዮጲያን ከትርምስ መታደግ ይቻላል ወይ? ነው፤፤ አይመስለኝም! አቢይም ግልጽ ስትራቴጂ ያለው አይመስልም፤
    ስለዚህ
    2። ዶ/ር አቢይ ሁሌ “ሽኔ” እና “ወያኔ” ናቸው እያለ መቀጠሉም አደጋ አለው፤፤ ወይ ችግሩን በግልጽ ለህዝቡ ያስጣው፡፡ ያዘጋጀው ፕላን ካለ ዝርዝር ዉስጥ ሳይገባ ጠቆም ያድርግ፡፤ “አዝኛለሁ” ብቻ አይበቃም፤፤
    3፤፤ ቢያንስ “ሽብርተኛ” ድርጅት መሆናቸውን ፓርላማው ይወያይበት፤፤ ሸኔ is acting like the Ugandan Lord Resistance Army or the Nigerian Boko Haram.
    4፡፤ ፕሮፓጋንዳ ቢቀር ወቅታዊ መረጃ መስጠት፤፤ ወያኔ እኮ የትግራይን ህዝብ ነጥላ በድምጺ ወያኔ እና በትግራይ ሚዲያ ከሁዋላዋ አሰልፋለች፤ “አይ የትግራይ ህዝብ እውነቱን በኋላ ይረዳዋል” ከሆነ – big mistake!
    ይህም ያልፋል እንበል፤፤ የመጨረሻው ለመሆኑስ ምን ዋስትና አለ? ያው እንደምታየው “ይሄ ይደረግ” ብሎ ሃሳብ የሚወረውር እየጠፋ ነው፡፤ ክላይ “ናኒ” የተባለችው ኮሜንት ያደረግችውን ተመልከት፡፡ ሃሳቧ “ልክ ነው” ቢባል እንኳ “እሺ ምን ይደረግ ታዲያ?” ለሚለው አንዲት ሃባ እንኳ ጠቋሚ ዐረፍተ ነገር የላትም፤፤
    ሌላው እንግዲህ የቀረን ወያኔ እንደምትለው ወታደራዊ አገዛዝ ነው፤፤ ይሰውረነ!
    ፈታኝ ነው፤ ፈጣሪ ይርዳን!
    Ethiopia shall prevail!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share