ፖለቲካችን  ከዜሮ ድምር (zero sum politics ) እንዲላቀቅ ምሁራን ሳትታክቱ  ሃሳብ አዋጡ። (መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ)

ሃሳብ ከማዋጣት አንፃር፣የዛሬው ፅሑፊ  ፣ በሥርዓተ መንግሥታችን አወቃቀር ና ጎልቶ በሚታየው እንከን ላይ ያነጣጠረ ይሆናል።  የፅሑፉ ቃታ ተሥቦ መልዕክቱ ለመንግሥት ሲደርሰው፣ፅሑፉ ሃሳብ እንጂ ጥይት ዓለመሆኑንን እንደሚገነዘብ አምናለሁ።  ይህን ለማለት ያሥገደደኝ መንግሥት የተባለው አካል እንዲሁ በቀለሉ የሚታ፣እንደ ጦጣ ዘፍ ላይ ተቀምጠው የማይዘልፉት  እንደሆነ በቅጡ ሥለተረዳሁ ነው።

መንግሥት ሲባል ለአፍ ይቅለል እንጂ ፣በተግባር ሲመዘን ግዙፍ ና ግርማ ሞገሥ ያለው ፣ተፈሪም ተከባሪም ተቋም ነው።  እንደው  በዋዛ በመመልከት  የመንግሥትን ኃላፊነት በአንድ ሰው ላይ  ብቻ ጥለን እንደአሻን የምናብጠለጥለው ከሆነ ተሣሥተናል።ወይም አገዛዙን “እንደሞናርኪ” ቆጥረነዋል ማለት ነው።  …

በዚህ  በ21 ኛው ክ/ዘ  መንግሥት በቀጥታ፣ በንጉሥ ፈላጭ ቆራጭነት የሚገዛበት  አገር የለም።እናም  የመንግሥት ሥልጣን በአንድ ሰው ተጠቃሎ የሚያዝበት ፣አንድ ሰው ብቻውን ፈላጭ ቆራጭ የሚሆንበት አገዛዝ የለም።እርግጥ ነው፣በቡድን የተደራጁ፣ራሳቸውን ፓርቲ ያሰኙ በምርጫ ና በምርጫ ሥም የመንግሥትን ሥልጣን የሚጨብጡበት የተለያዩ መንገዶች አሉ። ይህንን እውነት መረዳት በጣም አሥፈላጊ ነው።ይህንን እውነትም ከእኛው መንግሥት አንፃር በመገምገም ፣በለውጥ ሂደት ላይ ያለ መንግሥትን እንቅፋቶች በቅጡ መመልከት ና እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ እንቅፋቶቹን ከመንገዱ ለማንሳትና ለውጡ እሥከነአካቴው እንዳይደናቀፍ  ታላቅ ራእይ የሰነቁ ቅን ዜጎች የሚያደርጉትን   ያላሰለሰ ሁሉአቀፍ ትግል  መደገፍና በተቻለ አቅምም መርዳት ያሥፈልጋል።

እንደሚታወቀው፣የአንድ አገር መንግሥት  የአንድ ሉአላዊ አገር ምሰሶ ነው። ብዙ  ተቋማትን አቀናጅቶ በመያዝ የሚመራ ፣በአንድ ሉአላዊ አገር ውሥጥ ፣ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት በማዋቅሩ ውሥጥ ያቀፈ አካል ነው። በመንግሥት ማዋቅር ውሥጥ ያሉ ተቋማት እሥካልጠነከሩ ጊዜ ድረሥ በአንድ አገር የተሞላ ሠላም፣እድገት፣ ና ብልፅግና እውን ሊሆን አይችልም።

ይህ መንግሥት  የተባለ ሥያሜ የተሠጠው  ይህ ወደ እድገት ና ወደብልፅግ ና ወሳጅ ፣የህዝቡን ሠላም አረጋጋጭ ኃይል  ደግሞ፣ የሰው ሥብሥብ እንጂ የመለአክት ሥብሥብ አይደለም። የሰው ሥብሥብ በመሆኑም፣መንግሥታዊ ሥራን የሚሠሩ ሰዎች፣  እንደማንኛውም ሰው፣ሊሳሳቱ፣ሊያጠፉ፣ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደማንኛችን፣ዓይነቱ ብዙ ከሆነው የፈጣሪ ጥሪ ወይም ከሞት አያመልጡም። ሟች፣በስባሽ ና አፈር የሚሆኑ ናቸው።

ሟች የሆነው የሰው ሥብሥቡ መንግሥት ፣ የአንድ አገርን ዕጣ ፈንታ፣ በምርጫ ይሁን በጡንቻ ፣የመንግሥትን ሥልጣን ለጥቂት ወይም ለተራዘመ  ጊዜ ይዞ የሚቆይ ነው። በአንዳንድ ሀገሮችም ፣ ለተወሰነ ጊዜ ሥልጣንን ይዞ የሚቆይ ተቆጪ ና ቀጪ እንዲሆን የአብላጫውን  ዜጋ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት እንዳለ ይታወቃል።

ይህ መንግሥት  የተሰኘ  ፣ግዙፍ የሥልጣን መዋቅሮች ያሉት አካል፣ የአብላጫውን ወይም የጥቂቱን ዜጋ ይሁንታ አግኝቶ ሥልጣን ቢይዝም፣በአብዛኛው ዓለም በህጎች ሁሉ የበላይ በሆነ ህገ መንግሥት የሚመራ ፣በህግ የበላይነትም የሚያምን እንደሆነ ይታወቃል።

መንግሥት ፣የህግ የበላይነትን ለማሥከበር የሚችሉ ተቋማትም አሉት።   የሀገርን ሠላም እና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ፣እንዲሁም ፀጥታን ለማሥከበር  ሲባል፣ ከቀላላ እሥከ  ከባድ መሣሪያ  የታጠቀ ፣  ጦር ሠራዊትም  አለው።  ፍርድ ቤቶች ፣ዳኞች፣ጠበቆች፣ፖሊሦች በቅንጅት የሚሰሩበት ህጋዊ ተቋማት  ፤  እንዲሁም ጥፋተኞችን ማረሚያ እሥር ቤቶችም አሉት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የግል ወይም የቡድን   የፖለቲካ ትርፍን እያሰሉ አዋጅ ማወጅ የእውነተኛ ለውጥ ባህሪ አይደለም! - ጠገናው ጎሹ

የአንድ አገር መንግሥት ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ሳይሆኑ፣  መንግሥታዊ ሥራ የሚከውኑ በሚኒሥቴር ደረጃ  ልዩ፣ልዩ ተቋማት አሉት።

እነዚህ ልዩ፣ልዩ ተቋማትንም በየጊዜው የሚገመግማቸው ፣ በመንግሥት ደረጃ የሚንቀሳቀሰው የሚኒሥትሮች ምክር ቤት ነው።እናም ይህ የሚኒሥትሮች ምክር ቤት ህግ አሥፈፃሚው የመንግሥት አካል ነው።

እንደምታውቁት መንግሥት ሥራውን የሚያሣልጥበት ሦሥት አደረጃጀቶች አሉት።እነሱም ህግ አውጪ፣ህግ ተርጓሚና ህግ አሥፈፃሚ በመባል ይታወቃሉ።የተወካዮች ምክር ቤት ህግ አውጪ ሲሆን፣የፊደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ህግ ተርጓሚ ነው።የሚኒሥትሮች ምክር ቤት ደግሞ የወጡትን ህጎች የሚያሥፈፅም የመንግሥት አካል ነው።

በኢትዮጵያ የመንግሥት አደረጃጀት አንፃር ፣ለክልል መንግሥታት ተብሎ በህገ መንግሥቱ የተሠጠ ሥልጣን ደግሞ አለ።ከተሠጡት ሥልጣኖች አንዳንዶቹ   አሥተዳደራዊ ጉዳዮችን በቅርብ ከመፍታት አንፃር ታልሞ የተሠጠ  ነው። ብለን ብንወሥድም፣ከቋንቋ ጀምሮ በቀበሌ  ፣በወረዳ የሚቋቋሙት ሸንጓዎች ኗሪውን ወይም ዜጋውን አሳታፊ ሳይሆኑ አግላይ ናቸው።ይህ ሰውን በቋንቋው ብቻ አግልሎ ፣በአንድ የኢትዮጵያ ግዛት የአፓርታይድ ሥርአት ይመሥል ለአንዱ ቋንቋውን በመቻሉ የተሻለ መብት ሌላው ቋንቋ ባለመቻሉ የይሥሙላ መብት የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን።በግልፅ እንነጋገር ከተባለ ሰዎች ቋንቋቸውን እንጂ በቀና ልብ የማያገላግላቸውን ችሎታ ያለውን ተወካያቸውን አይመርጡም።  ይህ የምርጫ ሥርዓት ፣አሳታፊ በሆነ ፣ ዜጎችን ያለአድሎ ተሳታፊ በሚያደርግ የምርጫ ሥርዓት መተካት አለበት።በትግራይም ሆነ በኦሮሚያ  የሚኖር ማንኛውም ዜጋ፣ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ቋንቋ እንደ ዋና መሥፈርት ተቆጥሮ መብቱ ሊገፈፍ አይገባም።(በአማራ በተባለው ክልል አማርኛ የሚችል ሰባት ቤቱ የኦሮሞ ጎሣ የሆነ ፣ እንዲሁም የትግሬ ጎሣ የሆነ በአማራ ፓርቲ ውሥጥ ገብቶ ከፍተኛ አመራር ቢሆን የሚከለክለው የለም።ከዚህ አንፃር ሥርዓቱ ምን ያህል መሠረታዊ ችግር እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል።)  አሁን እና ዛሬ ያለው የወያኔ ኢህአዴግ ፓለቲካዊ ሥርዓት ፣የቱንም ያህል ህገመንግሥታዊ ነው ቢባልም ፣ ዜጎችን በዜግነታቸው እና በአካባቢው ነዋሪነታቸው  ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ የሚያግድ    መምረጥም መመረጥም የማያሥችል ሥርዓተ ምርጫ ያለው ሥለሆነ አግላይ እና ከፋፋይ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በ27  ዓመት ሲገለገልበት የቆየውን የአፓርታይድ ሥርዓት ዛሬም አላፈረሰውም።በመሬት ላይ ያለው እውነት የሚነግረን ኢህአዴግ በሥም እንደጠፋና በግብር ግን እንዳለ ነው።

አዎ ፣እውነት ነው፣ ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውሥጥ ናት።ከጅምሩ ክቡር ጠ/ሚ አብይ አህመድ ጋር ለውጥ ላመጡት ድፍን አገር ድጋፍ ሠጥቷል።አብይንም በተለየ ሁኔታ በመደገፍ ለታላቅ ለውጥ ማለትም የህን የዘር አገዛዝ እሥከወዲያኛው ለሚያረግፍለት የልተጨበጠ አዲስ መንግሥት ድጋፉን ሠጥቷል።በኢትዮጵያ ውሥጥ ለሃያአንደኛው ክ/ዘ የሚመጥን የፖለቲካ ሥርዓት የሚጣል ብሎ በማሰብ “አብይ!አብይ!አብይ!…” ብሎ መሪውን እንደንጉሥ ተቀብሏል።  የዘረኛና የከፋፋይ ሥርዓት በላያችን ላይ የጫነብንን ህውሃት  ህወሓት /ኢህአዴግን እሥከነግሳንግሱ ያሶግድልኛል ብሎ ኢትዮጵያዊው ተሥፋ አድርጎ ነበር ።

ይሁን እንጂ ፣ህወሃት /ኢህአዴግ ዛሬ ከሥልጣን ቢገለልም ፣ሮጦ ከመሸገበት ሆኖ ፣ ባለው የገንዘብ አቅም ሀገር ና ህዝብን ሠላም እያሳጣ በመሆኑ የለውጥ ኃይሉ ጉዞ እንደታሰበው አልሆነም ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአብይ አህመድና የቲያትሩ ውድቀት

ህወሃት / ኢህአዴግ ፣በዐውደ ውጊያ ላይ የሞተ ዳግመኛ የመዋጋት እድል የለውም።ሸሽቶ ያመለጠ ግን ዳግመኛ የመዋጋት እድል አለው። ( He who fights and runs away will  live to fight another day.But he who is in battle skin will never rise to fight again.) የተባለውን ጥቅሥ በሚገባ ተረድቶ መቀሌ በመመሸግ ወደ ቀድሞ የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣኑ ለመመለሥ በታወቀው ህዝብ አደናጋሪ ፕሮፖጋንዳውና በእቅድ እና በሥልት የመልሶ ማጥቃት ጠርነቱን ቀጥሏል።በመቶሺ የሚቆጠር ፣ገደል ግባልኝ ብለው የሚገባልኝ ጦር አለኝ በማለትም  ተመልሶ ወደሥልጣን ባይመጣም ሥልጣንን በጠመንጃ አፈሙዝ ለመጋራት በብርቱ ሲጥር ይሥተዋላል።

ይህ ሁኔታ የሚያሳብቀው ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዘው፣  በጠመንጃ አፈሙዝ እንጂ ፣ በዜጎች ይሁንታ ያለመሆኑን ነው።

የብልፅግና ፓርቲም ቢሆን፣ከዚህ አዙሪት የማይወጣበት ነባራዊ እውነት እና ኢህአዲጋዊ አደረጃጀት እንዳለው እሙን ነው።ብልፅግና ከሌላ ዓለም የመጡ ሰዎችን እንዳላሰበሰበ ይታወቃል።አደረጃጀቱ ያው ና ያው ነው።  ህዝብ  ከአደረጃጀቱ ጀምሮ መሠረታዊ ለውጥ ቢፈልግምየተሐወጠ ነገር የለም።ዛሬም በብልፅግና ውሥጥ  እንደ ጋሪ ፈረሥ በአንድ አቅጣጫ የሚመለከቱ፣የሰውን ሰው መሆን የማይቀበሉ፣ለአሥገኘላቸው ጥቅም ሲሉ ለቋንቋ የሚሰግዱ ፣በከተማ ኑሯቸው ግን በሚያግባባቸው አማርኛ የሚዘምሩ፣የሚደንሱ ና የማጨፍሩ አባላትን ያሰባሠበ ፓርቲ ነው።

ብልፅግና ህዝብ የውቃል ሳይሆን እኔ አውቃለሁ ባዮች የበዙበት እንደሆነም ይተቻል።ይህም ብቻ አይደለም።ትክክለኛ ሒስ የሚያቀርቡበትን አግላይ እና ዛሬም የኢህአዴግን ቋንቋ አምሌኪነት የሙጥኝ ያለ ፣ከመሆኑም በላይ፣ዛሬም እንደትላንቱ አሳሪ ና ጨቋኝ መሆኑን በተግባር እያሰመሠከረ የመጣ ፀረ-ዴሞክራሲ ሥርዓት ነው ።እየተባለ በምሁራን የሠላ ትችት ይሰነዘርበታል።

ትችታቸው የፓርቲውን እድሜ ና መሬት ላይ ያለ፣ ነባራዊ ችግርን ያላገናዘበ ቢሆንም፣ የቅድማያ ምልከታቸውና ግምገማቸው ፓርቲው ልብና አይምሮ እንዲገዛ የሚያደርግ ነው።

አንድ ፓርቲ መገምገም ያለበት በሚያራምደው ፓለቲካ ተቀባይነት፣ በደጋፊው ሥፋት ና ብዛት ሰበብ ባገኘው ውጤት ና ቅቡልነት ፣እንዲሁምበፕሮግራሙ ጥራት ና ለሀገር ጥቅም ባለው ፋይዳ እንደሆነ ይታወቃል።

ከዚህ አንፃር የብልፅግና ፓርቲ ሲገመገም የሚሥተዋሉበት ድክመቶች እንዲህ በቀላሉ የሚሥተካከሉ አይደሉም።የብልፅግና ፓርቲ ለውጡ ካመጣው እድል ማንም የሚካፈለው እንዲኖር ካልፈለገ እና አግላይ በመሆን ከፋፋይ ከሆነው የቋንቋ ፖለቲካ ላይ ከተንጠለጠለ የሚያራምደው ፓለቲካ ሲሰላ ቢውል ውጤቱ  ዜሮ ድምር (zero sum politics ) ፖለቲካ ሆኖ ያርፈዋል እንጂ ተጨባጭ ለውጥ አያመጣም።

ይህቺ አገር አንድ የምትኮራበት ብሔራዊ ቋንቋ ትላንት ነበራት ።አማራ ፣ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ሱማሌ፣ ቢንሻጉል ፣ሐረሪ ፣ደቡቡብ  ህዝቦች በአጠቃላይ፣ጋምቤላ፣አፋር፣ተግራይ፣አዲስ አበባ እና ድሬደዋ ውሥጥ የሚኖሩ ያለማጋነን ከ60 ፐርሰንት በላይ  ዜጎቿ የሚናገሩት።የሚግባቡበት ። …በዚህ እንደ ብሔራዊ  ቋንቋ ባገለገለ የዜጎች መግባቢያ ቋንቋ የኢትዮጵያ መሪዎች  በዓለም መድረክ ሃሳባቸውን ሲገልፁበት ነበር። ክብርት ፕሬዝዳንታችንም በዓለም መድረክ የኢትዮጵያን ቅን እና የመተሣሠብ ሃሳብ ሲገልፁበት አዳምጠናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትግራይ ማለት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለት ትግራይ ናት፡ - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ይህ የሚያሥረዳን ኢትዮጵያን ወደከፍታ ለማውጣት የሚፈልጉ መሪዎች እንዳሉ ሲሆን፣ከፍታን ሳይሆን ዝቅታንና የውጪ ኃይሎች ዘመናዊ ባርነትን ና አሸከርነትን የሚሹ ፖለቲከኞች ግን በቋንቋው እጅግ በሚገርም ችሎታ እየተግባቡበት፣ የተውሶ ያልሆነውን የገዛ አገራቸውንያልተዋስነው አንጡራ ሀብታችንን ፣ የአማርኛ  ቋንቋን ሲያጥላሉ እና እንዲጠላም ሲያሻጥሩ ይሥተዋላሉ። ይህ እኩይ ድርጊታቸውም በአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲደገፍ ይሥተዋላል።

በእውነቱ፣ይህ የአንዳንድ የጥቅም ተገዢ የመንግሥት ባለሥልጣናት  ድርጊት ወደ ሠላም፣ወደ እድገት፣ወደብልፅግና ዜጎችን የሚወሥድ አይደለም።ይልቁንም ተጋብተው ፣ተዋልደው ፣በጋብቻ በተዛመዱ እና ደማቸው በተቀላቀለ  ዜጎች መካከል ያልተገባ ልዩነትን በመፍጠር፣ ሰዎች ሰውነታቸውን በመርሳት ፣በቋንቋ ልዩነት ብቻ፣ ፊትና ጀርባ እንዲሆኑ   በማደርግ መናቆራቸው ዘላቂ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ አገሪቱን  ለታሪካዊ ጠላቶቿ የሚያጋልጥ  ፣ የአገሪቱን የከርሰ ምድር ሀብትም ያለሃይ ባይ ለመዝረፍ ለቋመጡም መንገዳቸውን ጨርቅ የሚያደርግላቸው ይሆናል።

በመግባቢያ ቋንቋ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ መዝሙር በዚች አገር መዘመር እሥካላቆመና ቋንቋ መግባቢያነቱ ተውቆ ለሁሉም ቋንቋ ክብር እሥካልተሠጠው ድረሥ ፣አገራችን ወደትክክለኛው የሠላም መንገድ ልትመጣ አትችልም።

አገሪቱ ወደትክክለኛው መሥመር ልትመጣ የምትችለው አንድ ብሔራዊ ቋንቋ እና እንደ አካባቢው ኗሪ ብዛት በእዛው አካባቢ የሚያገለግል የሥራ ቋንቋ ሲኖራት ነው።

ከሰው የተወለደ ሰው እንደመሆኑ መጠን በሚኖርበት አካባቢ መግባቢያው አማርኛ እሥከሆነ ድረሥ ያ ቋንቋ የሁሉም ሰው የሥራ ቋንቋ ሊሆን ይገባል እንጂ ፣በማያውቀው ቋንቋ በግድ መዳኘት የለበትም።

አገሬን የሚያጠፋት ፣በራሥ ያለመተማመናችን እና እንደ ጋሪ ፈረስ ወደአንድ አቅጣጫ ብቻ ማየታችን ነው።ምናልባትም ሰሩን እያየ ገደል እንደገባው በሬ ፖለቲከኞቻችን ሥለሚያሥቡ ይመሥለኛል።

ፖለቲከኞቻችን ሥለዛሬው ጮማ ፣ውሥኪ፣ጫትና ጨብሲ ብቻ የሚያሥቡ ከሆነ ይህቺን አገር እንደሚያጠፏት የታወቀ ነው።ይህ አይምሮ የጎደለው ሰው አሥተሳሰብ ነው።ታላቅ አገሮች ታላቅ የሆኑት መሪዎቻቸው ለልጅ ልጆቻቸው አሥቀድመው ሥለሚየሥቡ እና ለእነሱ ምቾት በብርቱ ሥለሚሰሩ ነው።በእኛ አገር ግን የሚታየው ፖለቲካዊ እውነት ከጎረቤት አገሮች እንኳን ዝቅ ያለ እጅግ የጠበበ የፓለቲካ አሥተሣሠብ ነው።

የፖለቲካ አሥተሳሰባችን  ፣  ሰው በገዛ አገሩ ላይ በእኩል የማይሥተናገድበት፣በቋንቋ ሥም ወጣቱ እንዲገለል እና ፍቅርና መተሣሠብ እንዲያጣ የሚደረግበት፣ አዳሜ ሞችነቱን የዘነጋበት ፣ ሰው ሰውን ለማረድ ቢላዋ እና ገጀራ ሲያነሳ ጥቂት እንኳን የማይፀፀትበትን እኩይ ባህል ፈጥሯል። ይህ ደግሞ አገራችንን ሲመኞት ለኖሩት ፣በጥሬ ሀብቶ ለመክበር  ብርቱ ፍላጎት ላላቸው የከበርቴ አገር ቱጃሮች የሚያመቻምቸን ካልሆነ በሥተቀር ሐማናችንም አይጠቅምም። እናም የዛሬው የፖለቲካ ጫዎታችን የዜሮ ደምር መሆኑንን ተገንዝበን ከምንምነት በመውጣት እንደታላላቀ አገር መንግሥታት የሀገራችንን ፖለቲካ፣ከቋንቋ ፖለቲካ በማላቀቅ ፣በፍትህ፣በእኩልነት፣በወንድማማችነት፣በዴሞክራሲ..መሥመር ላይ ብናራምደው መልካም ይመሥለኛል ።አሁን እየተጎዝንበት ያለው የፖለቲካ መንገድ ግን ፣ ዘላቂ ሠላምን የማያመጣ እንደውም ጊዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ እዛና እዚህ የሚቀብር መሆኑንን እንገንዘብ።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share