ፖለቲካዊነት (Politisization)

ለፈረጅኛው ቃል ተመጣጣኝ ትርጉም ስላላገኘሁለት ለርዕስነቱ ያህል ፖለቲካዊነት ስለው ክዚህ ቀጥሎ ግን ራሱን የእንግሊዘኛውን ቃል አንድጠቀም ይፈቀድለኝ። ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ ስርዓት ውስጥ ሁሉም ነገር ፖሊቲካዊ ይዘት አንዲኖረው ሲደረግ ይታያል። በኔ አስተያየት ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክኒያት የፖለቲካ ተጠቃሚነት ለማግኘት አንደሆነ ለመረዳት ቀላል ይመስለኛል። ሆኖም ፖለቲካዊ መሆን የማይገባውን ጉዳይ ሁሉ ፖለቲካዊ ማድረግ ውጤቱ ውድቀት ነው ብዬ አምናለሁ። ቢያንስ ይህንን ከህውሃት ውድቀት ልንረዳው የምንችል ይመስለኛል።

ፖለቲሳይዜሽን በተለያዩ አውዶች ላይ የተለያየና ፍልስፍና የሚመስል ትርጉም ሲሰጠው ይታያል። ለዚህ አጭር ጽሁፍ ይስማማል ብዬ የወሰድኩት ቀላልትርጉም ግን “ፖሊቲሳይዜሽን’  ማለት አንድን ነገር ወስዶ የፖለቲካ ጉዳይ ማድረግና ጉዳዩን ፖለቲካዊ ይዘት መስጠት ነው.’ የሚለውን ነው።። አንድን ነገር ፖሊቲሳይዝ ስታደርገው የፖለቲካ ጉዳይ ቢሆንም ባይሆንም ለፖለቲካው እስከጠቀመ ድረስ በዚያ አውድ ውስጥ ታመጣዋልህ ማለት ነው። ለምሳሌ የትምህርት ቤቶች ወይም የተማሪዎች ስራ አፈጻጸም ባንድ አጋጣሚ ቢቀንስ ፖለቲከኞች ‘አይ ይሄ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሰሩት ሥራ ነው።’ ሊሉት ይችላሉ።

 

በኔ ግንዛቤ ፖለታይዜሽን በአገራችን ፖለቲከኞች እጅግ እየተለመደ የመጣው ባለፉት አርባ አመታት አካባቢ እንደሆነ እረዳለሁ። የተለያዩ ጉዳዮችን ለምሳሌ አንደ ማህበራዊ ግንኙነት፣ ጤና፣ ንግድ፣ ኪነት/ሥነጥበብ፣ ባህል፣ እምነት፣ ወዘተ ለምን ፖሊቲካዊ ይደረጋሉ? ሁሉም አንደፖለቲካ የየራሳቸው ፍልስፍና፣ ጽንሰሃሳብ፣ ህግጋት፣ ተሞክሮ፣ ሃላፊነት ወዘተ አላቸው። ለኔ ከፖለቲካ ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ፖለቲካዊ የሚደረጉት ፖለቲከኞች በያዙት ሥልጣን ላይ ለመቆየት በቂ ምክኒያት ሳይኖራቸው ወይም ፍጹም ምክንያት ሳይኖራቸው ሲቀር ነው ብዬ አምናለሁ።

 

ያገራችንን መንግስታት ብንመለከት፣ ደርግ የንጉሳዊውን መንግስት ገልብጦ ስልጣን ለመያዝ፣ ወይም በዚያ ዘመን የነበረው ወጣትና አብዮታዊ ትውልድ በተለይ መሪዎቹ በንጉሱ ዘመን የነበረውን አስተዳደር አስወግዶ ወደ ስልጥን ለመምጣት ቢያንስ የመንግስት ልውጥ ያስፈልጋል ለማለት ምክኒያት ያስፈልጋቸው ነበር። ለአንድ መንግስት አመራር ህዝብ ሊያነሳ የሚችለው ጥያቄ የመሰረታዊ ፍላጎቶች፣ የነጻነት፣ የመብት፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ነው። የህዝብን እንቅስቃሴ የሚመሩ ፖለቲከኞች ግን ያለው ስርዓት የህዝብን ጥያቄዎች እንዲመለስ በመታገል ፋንታ ጉዳዩን ፖለቲሳይዝ በማድረግ ስርዓቱ የርዕዮተዓለም ልውጥ የሚያስፈልገው ስለሆነ  በሶሻሊዝም መተካት አለበት ወደሚለው ጥያቄ በመውሰድ የመንግስት ለውጥ ፖለቲካዊ ይዘት ተሰጠው። አጋጣሚውን ያገኘው ደርግ ደግሞ ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ወደተጠየቀው ስርዓት አሸጋግራለሁ በማለት ረፎርም የሚጠይቀውን ስርዓት ወደ ፍጹም አብዮት አራመደው ስልጣኑንም ጠቅልሎ  ያዘ። ውጤቱም ከተለወጠው ስርዓት በባሰ መልክ የሺዎችን ህይወት ቀጠፈ፣ አገርም በተፈለገው መጠን አልተራመደችም።

 

ህውሃትን ስንመለከት ደግሞ አባላቱ፣ የተማሪው የተራዘመና ለለውጥ የተደረገው ትግል በወታደሩ ተጠልፎ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ግራ የተጋቡ ወጣቶች ወደፖለቲካ መድረክ ለመንጠላጠል አንድ ነገር ይዘው ካልመጡ  አንደማይሳካ ስለተገነዘቡ አንዲሁም ሁሉም አጀንዳ የሶሻሊዝም፣ የመሬት ላራሹ፣ ወዘተ ጥያቄ ደርግ መልሻለሁ ስላለ፣ አንዲሁም የህዝባዊ መንግስት ጥያቄ በኢህ አፓ ይቀነቀን ስለነበር በኋላ ያገኙት፣ ነፍሱ ይማረውና የዋለልኝ ሃይሉን የብሄር ብሄረሰቦች መብት ጉዳይ የምትመለከት መንደርደሪያ የምትሆን አጭር ጽሁፍ ነበር ብዬ አስባለሁ።  በመንሆኑም በህወሃት ፖሊቲሲዘ የተደረገና ሥልጣን ላይ ለመንጠልጠያነት የተጠቀመችበት ምክንያት የብሄር ብሄረሰብና በኋላም በግልጽ እርቃኑን የቀረው የዘር ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ዘርን ፖሊቲሳይዝ  በማድረግ ከተያዘ ሥልጣን ያተረፉት ፖለቲከኞቹ ናቸው። ቀድሞም ዓላማቸው ዝርፊያና የግል ብልጽና መሆኑን የተናገሩት ሳይሆን ያደረጉት አሳይቶናል።  አሳዛኙ ጉዳይ ግን ፖለቲከኞች የራሳቸውን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ይዘው የሚመጡት አጀንዳ ለህዝብ መከራና ሥቃይ ሲሆን መመልከታችን ነው።

 

በብዙ አገሮች አገራዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ፖሊቲሳይዘ ይደረጋሉ ሆኖም በተለይ ባደጉትና የዜጎቻቸውን መብት የሚያስጠብቅ ሥርዓት በተዘረጋባቸው ሃገሮች ይህ የሚሆነው የዜጎቻቸውን መብት አስካልነካና ህግን እስካልጣሰ ድረስ ነው። ህዝቡም ለመብቱ ቀናኢ ስለሆነና ስርዓቱም ስለሚደግፈው አንደልባቸው በይፋ የሚሮጡበት ሜዳ የላቸውም።

 

አገራችንን ጨምሮ በሶስተኛው ዓለም የምናየው ፖሊቲሳይዜሽን ግን  ሠፊ የመብት ጥሰትንና ሰዎችን አስከማስጨፍጨፍ ድረስ የሚያደርስ መሆኑ ግን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ስንናፍቀው የኖርነውን ዴሞክራሲያዊ ስራዓት ካይናችን እያራቀው መሆኑን አየተመለከትን ነው።

 

የብሄር ጥያቄ ብለው የተነሱት ወያኔዎች በልተው ሲጠግቡ፣ አንደገና ያንድን ዘር ጉዳይ ብቻ ፖለቲካዊ ይዘት ሰጥተው ተስፋፊነትንና የህዝብ ጥያቄ ያልሆኑ ጉዳዮችን ፖለቲሳይዝ በማድረግ ወደሥልጣን ለመንጠላጠል አገርን የሚያምሱ ሌሎች ፖለቲከኞች ተፈጥረዋል። አነዚህም የህውሃትን ጉዞ ተጉዘው፣ ገለው አጥፍተውና ዘርፈው የሚጠፉ ናቸው። ከሁሉ በላይ የሚያዛነውና መሸከም የምይቻለው ግን በዚህ ምክኛት የሚሰቃየው፣ ህይወቱ የሚመሳቀለና የሚሞተው ህዝብ ነው።

 

የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ይህን ጉዳይ ዝም ተብሎ የሚታይ አይደለም። ሁላችን በተቻለን አቅም ልንታገለው የሚገባ ነው። ቢያንስ ድምጻችንን ማሰማት ይገባናል። መጠየቅ አለብን። መተቸት አለብን፣ መቃወም አለብን። ሰላማዊ የትግል ስልቶችን ተጠቅመን መለውጥ አለብን። ህዝብም ምርጫን ጨምሮ ያገኛቸውን ዕድሎች ሁሉ የተሻለ ሁኔታ እንዲመጣ የየራሱን አስትዋጽዎ ማድረግ ይኖርበታል። ይህ ከሆነ በጊዜ ሂደት ትክክለኛው መስመር ላይ ለመውጣ አንችላለን የሚል ተስፋ አለኝ።

 

አሁን ካለው የለውጥ ሥርዓት ያገራችን ህዝብ ብዙ የጠበቀ፣ ተስፋም ያደረገ ይመስለኛል። የለውጡ ሃይል ውይ የዓላማ ውይም የስልት ስህተትና ችግር ላይ በመውደቁ፣  የተጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ይችላል የሚለው እምነት አየተሸረሸረ ይመስለኛል። ፍልስፍናውም ሆነ የለውጡ ሥልት ከተገዳዳሪዎቹ ተፈጥሮና አቅም ጋር የተመጣነ አይመስልም። በዝምታ የሚታለፉ በለውጡ ምክንያት እየገነኑ የመጡ የመብትና የህግ ጥሰቶች የህዝብን ብልጽግና ቀርቶ በሰላምና በህይወት የመኖር መብትን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ካስገባው ውሎ አድሯል። ይህ ደግሞ መንግስት የነበረውን ከፍተኛ ድጋፍ እየሸረሸረበት መጥቶ ማዝመም ሳይጀምር ራሱን ማስተካከል ይገባዋል።

 

አሁንም ብዙ ፖሊቲሳይዝ የሚደረጉ ጉዳዮች እየተበራከቱ ነው። ሃይማኖት፣ ፓርክ ግንባታ፣ የፖሊስ ሥልጠና፣ የታዋቂዎች ግድያ፣ የኢሬቻ በዓል፣ ወዘተ የዘመነ ፖሊቲሳይዜሽን ማቀንቀኛዎች ሆነዋል። ሌሎችም እንደሚቀጥሉ መገመት ይቻላል። ፓርክ መገንባት ያለበት ለከተሞች አድገት ስለሆነ የኢኮኖሚ ፕሮግራም አካል ተደርጎ መታየት ያለበት ይምስለኛል። ፖሊሶይ በሥልጠና ክህሎታቸውን ማሳደጋቸው ያለባቸው ህዝብን የመጠበቅና ህግን የማስከበር ሥራ በተዋጣና በሃላፊነት አንዲወጡ አንጂ ለፖሊቲካ ፍጆታና ለታይታ መሆን አይገባውም። የታዋቂዎች ሞት መዘከር ያለበት፣ በገዳዮቹ ወንጀለኝነት፣ በህገወጥ ሥራና በሰላምና በህይወት የመኖር መብቱ በመጣሱ ምክን ያት ተገቢው ፍትህ አንዲያገኝ በማድረግ አንጂ፣ የሌሎች በርካታ ዜጎች ሞት በቅጡ የዜና ሽፋን ባልተሰጠበትና ተጎጂዎች ማደሪያ ባጡበት ሁኔታ ለአንድ ታዋቂ የሚደረገው ከልክ ያለፈ ትዕይንት አሁንም ዜጎች ነግ በኔ አንዲሉና በለውጡ ያላቸው በዕኩል የመታየት ተስፋና እምነት እየተሸረሸረ ከመሄድ ባለፈ የሚያመጣው ጥቅም አናሳ ነው። ስለዚህ ነው ፖሊቲሳኢዜሽን ውድቀትን አንጂ እድገትን አያመጣም ለማለት የሚቻለው። ለዚህ ዋናው ምክን ያት ደግሞ የሚደረጉ ድርጊቶች ሁሉ በእውነት በትክክለኛ አሰራር ላይ የተመሰረቱ ሳይሆን በፖሊታይዜሽን ጊዚያዊ ጥቅም  ላይ  ያተኮረ ስለሆነ በህዝብ ሚዛን ቀሎ መገኘትን ያመጣል።

 

በተለይ አንደአገራችን ላሉ በዝናብ ላይ በተመሰረተ እርሻ ለዘመናት በዘለቀ ኢኮኖሚ 85% የሚሆነው ህዝብ ለሚተዳደርባት አገር የመስኖ እርሻ ምን ያህል ጠቃሚ ኢንደሆነ የሚካድ አይደለም። ካንድ አስር ዓመታት በፊት ህውሃት ይህንን ዘዴ ወሃ ማቆር በሚል ፕሮግራም ለማስፋፋት ሞክራ ነበር። ይህ ስራ ግን፣ ገበሬውም ሳያምንበት አንደ ሸክም ተጭኖበት፣ ካድሬዎችም አንደ ተልኮና ኮታ ይዘው ውዲያና ወዲህ ሲሉት ብዙ ጉልበትና ሃብት ፍሶበት ሳለ ምናልባት ከጥቂቶች በስተቀር ያልተሳክ የሆነውና መና የቀረው በዚሁ በፖሊቲሲዛይዜሽን ምክንያት ነው።

 

በኔ እይታ ፖሊቲሳይዜሽን የደካማነት ምልክት ነው። አንድ መንግስት ዴሞክራሲያዊ አስከሆነ ደርስ የህዝብንና የያንዳንዱን ዜጋ መብት ለማስጠበቅ፣ አገርን ባስተማማኝ መሰረት ላይ ለማቆም፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ ወጣቱ መልካም ዜጋ አድርጎ ለመቅረጽና ለወጣቱ ትውልድ የትምህርትና የሥራ ዐድል ለመፍጠርና አገርን ከፍ ካለ ማማ ላይ ሊያወጡ የሚችሉ ሃቀኛና ትክክለኛ ሥራዎች ሠርቶ ከፍ ያለ ተቀባይነትን ማግኘት በሚቻልበትና ፍትህና አድገት የጠማው ህዝብ በሞላበት አገር የሆነ ያልሆነውን ሁሉ ፖሊቲሳይዝ ማድረግ በራስ መተማመንንና ሃቀኝነትን አያሳይም። በዚህ ያመራር ስህተትም ብዙ ዜግች ጉዳት ላይ ይወድቃሉ የመነግስትም ዕጣ ፋንታ ውድቀትይሆናል። ስለዚሁ መሪዎቻችን በጊዜ ወደልቡናቸው ቢመለሱና ህዝቡን በእኩልነት አይተው መብቱንና ሰላሙን ቢያስከብሩለትና በጠራ ህቀኛ ሥርዓት ቢመሩት ተዓምር የሚሰራና አገሩን በዓለም ያስጠራና ሊያስጠራ የሚችል በሃይማኖትና በአብሮነት ሥርዓት የታነጸ እርሾ ያልተለየው ታላቅ ህዝብ መሆኑን መረዳት አዋቂነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል አላለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ያድን!

ስም-አልባ

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.