ትውልድ ገዳዩ የጎሳ/የቋንቋ  ፖለቲካ ማንነት እንደ ሥርዓት በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ የመከራ እንባ ማቆሚያ የለውም! – ጠገናው ጎሹ

July 26, 2020
ጠገናው ጎሹ

ከሰሞኑ የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች የሚያውል የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞችን እብደት  ከምር ላስተዋለና ለሚያስተውል የአገሬ ሰው ይህ ትውልድ በእጅጉ ፈታኝ የሆኑ ጣምራ እንቆቅልሾቹን ለመፍታት የሚያስችለውን የፖለቲካና የሞራል ልዕልና  ለመጎናፀፍ ገና ብዙ እንደሚቀረው ለመረዳት አይቸገርም ። ከእነዚህ ጣምራ እንቆቅልሾች መካከል አንዱ “የእኛና  የእናንተ ወይም የእኛና የእነርሱ”  የሚል የአጥፊና ጠፊ ማንነት ፖለቲካ ልክፍተኞች  የሰነዘሩትና የሚሰነዝሩት ሰይፍ ሰለባ የሆኑ ንፁሃን ወገኖችን ብዛትና አይነት እየቆጠሩ በሃዘን መብከንከንን የመላመድ አደጋ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ  ሎሌነት በማይሰለቻቸው ብአዴናዊያን አጃቢነት እየታገዘ  በተረኛ ኦህዴዳዊያን /ኦነጋዊያን የበላይነት የሚዘወረውን የሸፍጥ ብልፅግና ፖለቲካ እና  ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ  መዘውር ዘዋሪነት ሳይወድ በግድ ተግዶ መቀሌ ላይ ያዙኝና ልቀቁኝ የሚለውን ህወሃት በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት አግባብ አስወግዶ ለህዝብ የሚበጀውን ሥርዓት እውን ለማድረግ አለመቻል የሚያስከትለው አስከፊ የፖለቲካና የሞራል ቀውስና ሃፍረት  ነው።   ለዘመናት ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ችቦ እየተቀባበለና በያለበት እያቀጣጠለ የእራሱ አንፀባራቂ  ታሪክ  ባለቤት ሆኖ ከመገኘት ይልቅ የበሰበሰና የከረፉ ሥርዓታቸውን እንደ ሥርዓት አስቀጥለውና የህወሃትን የበላይነት በኦህዴድ ተረኝነት በመተካት “ተደመር” ሲሉት ለምንና እንዴት ሳይል የተደመረ ወይም ግራ የተጋባ ትውልድ የእነዚህ ጣምራ እንቆቅልሾች ሰለባ ቢሆን የሚያሳዝን እንጅ የሚገርም አይደለም።

ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ  ሶስት አሥርተ ዓመታትን እያስቆጠረ ያለው የኢህአዴጋዊያን (የብልፅግናዊያን) የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት ሥርዓት እና ለግማሽ ምእተ ዓመት ያህል ከተለከፉበት ተመሳሳይ የፖለቲካ በሽታ መላቀቅ ያቃታቸው ኦነጋዊያን ክፉ ልክፍት  ያስስከተለው  የፖለቲካ አስተሰሰብና አካሄድ  ሰለባ ከሆኑት እጅግ አያሌ ቁጥር ካላቸው ወገኖች አንዱ ሆኖ አልፏል ።  ከነዚህ አያሌ ቁጥር ካላቸው ወገኖች መካከል “የፖለቲካችን ትልቁ ውድቀት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ አለመቻልና እንደማነኛውም አገር በታሪክ ሂደት የተፈፀሙ አሉታዊ ሁኔታዎችን በትምህርት  ሰጭነታቸው ከመጠቀም ይልቅ ትውልድን  የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ  መርዝ  እየጋቱ የመግደልና የማጋደል  ወንጀል ነው” በሚል ፅዕኑ እምነታቸው  ምክንያት የጓሰኞችና ዘረኞች ሰይፍ ሰላባ የሆኑ  ቁጥራቸው ብዙ ነው።  ሌሎቹ  (ሀጫሉን ጨምሮ) ደግሞ  በእጅጉ  ስሜታዊ ለሆነው የጎሳና የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ  በእድሜም ሆነ የተሳሳተ የታሪክና የፖለቲካ ትርክት እየሰሙ ብቻ ሳይሆን  በሃውልትና በሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ እየተማሩ/እየተጋቱ በማደግ ረገድ በጣም  ቅርብ የነበሩ በርካታ ወገኖች ደግሞ  በሥልትና ስትራቴጅ እንጅ በኦሮሙማ (oromization) የቅዠት ፖለቲካ መሠረታዊ ልዩነት በሌላቸው ቡድኖች መካከል በሚፈጠር ግጭትና ሽብር ውስጥ ሰለባ የሆኑ ናቸው።

ሁለቱም ወገኖች (ሰለባዎች) በጤናማና ከዘመን ሥልጣኔ ጋር ወደ ፊት በሚራመድ የፖለቲካ አውድ (condusive and progressive political environment) ውስጥ ለመኖር እድል ቢሰጣቸው ኖሮ በየተሠማሩበት የሙያ መስክ ለሁለንተናዊ የአገር እድገትና ብልፅግና ሊያበረክቱት ይችሉ የነበረውን አስተዋፅኦ በጤናማ ህሊና ለሚያስብ ሰው የሚሰማውን መሪር የሃዘን ስሜት መገመት አያስቸግርም።

የአገሬ ህዝብ  የተቸገረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት ባለመሆኑ እንጅ  በአብሮነቱ (በኢትዮጵያዊነቱ) ምክንያት ይመስል  በጎሳ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት በየመንደሩና በየቋንቋው ጠርንፈው ለዘመናት  ሲገዙት የኖሩት ኢህአዴጋዊያን  አሁንም ብልፅግና በሚል የሸፍጥ ስያሜ ያንኑ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓታቸውን ባስቀጠሉበት እውነታ ውስጥ “የዴሞክራሲና የትውልድ ጠበቃዎች ነን “ ሲሉን ጨርሶ ህሊናቸውን አይጎረብጠውም።

በለየለት የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ  አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ እብደት የተለከፉ ነፃ አውጭዎች ነን ባዮችም እንደ ሀጫሉ አይነት ጥሩ ተሰጥኦ የነበራቸውና ያላቸው ድምፃዊያን  ስለ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያና  ስለ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀን የኦሮሞን ህዝብ መክዳት መስሎ እስኪሰማቸው ድረስ በትውልድ ላይ ከባድ  የማንነት ሥነ ልቦና ቀውስ  በመፍጠር  ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ፈፅመዋል። ዛሬም በአስከፊ ሁኔታ ቀጥለውበታል ። ከዚህ አልፈው እርስ በእራሳቸው በሚፈጥሩት ሽኩቻ  ህይወት እስከ ማጥፋት የመድረሳቸውን እብደት ቆም ብሎ የሚጠይቅ ህሊና ጨርሶ አልፈጠረባቸውም። ወይ ከእብደታቸው እንዲመለሱና የጋራ የሆነች ዴሞክራሲያዊት አገር የመፍጠር እና  የእኩልነትና የጋራ ብልፅግና የማረጋገጥ እልህ አስጨራሽ ትግል አካል እንዲሆኑ ፣ ያለዚያ ግን ለዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ትግልና ግብ እንዲንበረከኩ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ በእነርሱ እብደት ምክንያት የሚፈሰው የደም እንባ ማቆሚያ ይኖረውም።

የጎሳ ማንነታችን መብት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር በሚፈጠር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲከበር  ማድረግ  እየቻልን በየጎሳችንና በየቋንቋችን ከረጢት  ውስጥ  ተጠርንፈን እራሳችንን በእራሳችን እየገደልንና እያጋደልን ወይም እየተገዳደልን ከመቀጠል የከፋ የትውልድ ማንነት ውድቀትና የቁም ሞት የለምና ቆም ብለን ከምር ማሰብን ግድ ይለናል።

የብዝሃነት መስተጋብሩ ሰፊና ውብ የሆነውን ኢትዮጵያዊነት ላለንበት ዘመን በሚመጥን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይበልጥ አድምቀን ለዘመናት ከኖርንበት ሁለንተናዊ ድህነት ለመውጣት የሚያስችለንን ሁኔታ መፍጠር እስካልቻልን ድረስ የመቃብር ሬሳዎች ብቻ ሳይሆን መቃብር ያልገባን የቁም ሙቶች እየሆን እንቀጥላለን። መቸም የእራሳችንን ልክ የሌለው ድንቁርና እና ውድቀት አምነንና ተቀብለን አስፈላጊውን እርምት ከማድረግ ይልቅ የሚቀለን ሰበብ መደርደርና መካድ (clumsy execuese and denial) ሆኖ ነው እንጅ እፊታችን ቆሞ የሚሞግተን መሪር ሃቅ ይኸው ነው።

አክራሪ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞችን ፣ በዚሁ ልክፍት ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉ የኢህአዴግ/የብልፅግና ገዥ ቡድኖችን እና ቤተ መንግሥትን ደጅ የሚጠኑ እጅግ ወራዳ (አሳፋሪ) ተፎካካሪ ተብየ ፖለቲከኞችን በቅጡ የሚያደርግ ሥራ ባለመሥራታችን  እያየነው ያለነውን የመከራና የውርደት መጠንና አይነት በቃላት ለመግለፅ በእጅጉ ስንቸገር እንታያለን ።  በግፍ ከገደሉ በኋላ አስከሬንን እጅግ እኩይ ለሆነ የፖለቲካ ፍላጎት ማርኪያነት ማንግላታት እና  የጎሳንና ሃይማኖታዊ እምነት ማንነትን እየለዩ   የበርካታ ንፁሃን ዜጎችን  ህይወት ለማጥፋት በምክንያትነት መጠቀም በጎ ህሊና እንዳለው ግለሰብ ዜጋም ሆነ እንደ አገር በእጅጉ ያሸማቅቃል ወይም አንገት ያስደፋል። ከዚህ የከፋ የትውልድ በቁም ሞት የለም (አይኖርም) ።

በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የጨቀየ ሥርዓታቸውን በሸፍጥ ተሃድሶ ስም ያስቀጠሉት ገዥ ቡድኖች (ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን) እና ኢትዮጵያ ስለምትባል አገር መስማትም ሆነ ማየት የሚፀየፉና በእነርሱ የእብደት ፖለቲካ አምሳል እንደገና ካልሠሯት  ጨርሶ ትፍረስ የሚሉ እኩያን ወገኖች  ይህን ትውልድ በእውንና በቁም ሲገድሉትና ሲያጋድሉት ይኸውና ሥስት አሥርተ ዓመታትን አስቆጠረ። እናም ስለ ነፃነትና ስለ ፍትህ እየጮሁ ወደ መቃብር ለወረዱት ንፁሃን ወገኖች  ከንፈር እየመጠጠና የደም እንባ እያነባ  ወይም ርቀት በማይጓዝ የስሜታዊነት ትኩሳት እየነደደ ዴሞክራሲን የሚናፍቅ ትውልድ ቆም ብሎ እራሱን ከምር በመመርመር  ይኖርበታል።  ይህን ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ሸፍጠኛ የጎሳ/የመንደር ፖለቲካ ማንነት  ገዥ ቡድኖችና ቢጤዎቻቸው  ካስለከፉት አስከፊ የፖለቲካ ልክፍት በመውጣት ከእጁ ላይ የተነጠቀውን  የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ትግል መልሶ እጁ ውስጥ በማስገባት ለዘመናት የዘለቀውን የመከራና የሰቆቃ እንባ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የሚችለው። ይህን ማድረግ ከተሳነው ግን እየተፈራረቁ የሚገዙት ገዥ ቡድኖች የመከራ ቀንበር አላላውሰው ባለ ቁጥር  የደም እንባውን እያነባና የቁም ሞቱን እየሞተ ይቀጥላል ።

እራሱን ጠቅሞ ለአገርም ብዙ ማበርከት የሚችልን ትውልድ  የወጣትነት እድሜውን እና የአእምሮና የአካል አቅሙን /ብቃቱን ለርካሽ ፖለቲካቸው ማስፈፀሚያ እንዲሆን መርዝ እየጋቱ ያሳደጉት እራሳቸው ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) እና መሰል የጎሳ ፖለቲካ ማንነት ልክፍተኞች  እንጅ ከሌላ ፕላኔት ተመርዞ  የመጣ ትውልድ የለም ። ፍፁም ንፁሃን ዜጎችን በጎሳ ማንነታቸውና  በሃይማኖታዊ እምነታቸው እየለየ እንኳን ለማየት ለመስማትም እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ በመግደል በአስከሬናቸው የሚሳለቅ ትውልድ ከዚህ እጅግ አስከፊ ልክፍት በእውን መዳን ካለበት የልክፍቱ ምንጭ የሆነውን መርዘኛ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎ ማስወገድን የግድ ይለዋል ። የነፃነት ፣የፍትህ፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና  ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ ከመጠየቅና ከመታገል በስተቀር ሌላ ዓላማና ተልእኮ በሌላቸውና በማይኖራቸው ንፁሃን ዜጎች ላይ የሚያርፈው  የግፍ ፖለቲካ  ሰይፍ ከነሰገባው ወደ ታሪክ ማስተማሪያ ሙዜየም  መግባት ካለበት መሠረታዊ   ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን  እውን  ማድረግ የግድ ነው።

ማቆሚያ ካጣው  አስከፊ የውድቀት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት መንፈስንና ቁመናን በመላበስ የተግባር ሃይሎች ሆነን እስካልተገኘን ድረስ የምናነባው እንባ ወደ ሰማይ ቢረጭ ወይም ወደ ምድር ቢፈስ ብዙም የሚፈይደው ፋይዳ አይኖረውም ።

“እንዴ! አምላክ ወደ ሰማይ የሚረጨውን የተበዳይ እንባ ለምን አይሰማም?” የሚል ቁጣና ድንጋጤ አዘል ጥያቄ የሚጠይቁ  ወገኖች እንደሚኖሩ  አውቃለሁ። እያልኩ ያለሁት ፈጣሪ የተበዳይን እንባ  አይመለከትም ወይም አይቀበልም አይደለም።እያልኩ ያለሁት ፈጣሪ ከረቂቅ አእምሮና ከብቁ አካል ጋር የፈጠረን  እገዛውን ከልብ እየጠየቅን የሚበጀንን ሁሉ በጥሞና አስበንና አቅደን ወደ ተግባር በመለወጥ የጋራ አገራችንን (ኢትዮጵያን)  የነፃነት፣ የፍትህ ፣ የሰላም ፣ የፍቅር እና የጋራ ብልፅግና ምድር ለማድረግ የየእራሳችንን ሃላፊነት ሳንወጣ የምናነባው እንባና የምናሰማው እግዚኦታ የትም አያደርሰንም ነው። ለዚህ ተግባር አልባ እግዚኦታችን ደግሞ  ለውጥ መጣ እያልን እልልታውን አቅልጠን ሳንጨርስ ከሆነውና እየሆነ ካለው በእጅጉ አሰቃቂና አሳፋሪ የፖለቲካ ቀውስ በላይ ማስረጃ የለም።

መሆን ያለብንን ሆነንና ማድረግ ያለብንን አድርገን ባለመገኘታችን መከራና ውርደቱ ይበልጥ እየከፋ በሄደ ቁጥር “የእርሱ ቁጣ ነውና ሁሉን ነገር ለእርሱ ትተን  እግዚኦ እንበል” ማለት ፈጣሪ ሰውን ከእንስሳት ለይቶ የፈጠረበትን ምክንያትና ዓላማ ዝቅ ማድረግ ወይም ዋጋ ማሳጣት  ነው የሚሆነው ። በእራሳችን ልክ የሌለው ስንፍና ወይም ድንቁርና ወይም ፍርሃት ወይም አድርባይነት (እራስ ወዳድነት) ወይም ሸፍጠኝነት እና በአጠቃላይ ልክ የሌለው ሁለንተናዊ  ውድቀት ምክንያት በገንዛ አገራችን ላይ ከሰብአዊ ፍጡር በታች ያዋለንን  የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችን የግፍ ሥርዓት በቃ ማለት ሲያቅተን “እርሱ ባይለው ነውና እርሱ ባለው ጊዜ ነፃ እንወጣለን”  በሚል የመከራና የውርደት ዘመንን  ማራዘምና መቁጠር ፈጣሪ ሰውን ከፈጠረበት የተቀደሰ ዓላማ ጋር ጨርሶ የሚሄድ አይደለም። ይህን  ለማወቅ የሃይማኖታዊ ትምህርት ሊቅ መሆንን ጨርሶ  አይጠይቅም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የባራክ ኦባማና የወይዘሮ አዜብ መስፍን ታሪካዊ ግንኙነት

ልክ በሌለው ስንፍናችንና ፍቅርና ሰላም አልባ በሆነው ህይወታችን እራሳችንን በእራሳችን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣን  “እርሱ ሊቀጣን ፈልጎ ነው” እያልን  እግዚኦ ማለት የእውነትን  አምላክ ትቶ ጨካኝ አምላክን የመፈለግ ድንቁርና ነው ። እንዲህ አይነት ጨካኝ  አምላክ ደግሞ  እራሳችን ያሰነፍነው አእምሯችን የሚፈጥረው ካልሆነ በስተቀር ጨርሶ የለም። የነበረው፣ ያለውና የሚኖረው አምላክ ሃላፊነታችን እየተወጣን እገዛህውን ስንጠይቅ መይም ስንለምን  ፈጥኖ የሚደርስ  የእውነት አምላክ እንጅ ልክ ለሌለው የገንዛ እራሳችን ውድቀት የምንደረድረውን የሰበብ ዝባዝኬን እየተቀበለ የፍርድ ብይን የሚያካፋፍል አይደለም።  የተፈጠሩልንን መልካም እድሎች (አጋጣሚዎች) ደጋግመን እያበላሸንና ለዘመናት በመጣንበት የውድቀት መንገድ ላይ እየተተራመስን   “የፈጣሪ ቅጣት  ነው” ማለት ጨርሶ  ትርጉም የለውም።

ይህ ትውልድ አብሮት የኖረውንና አሁንም እየባሰ እንጅ እየተሻለ ያልሄደውን የእራሱን መሪር እውነት ልቡ እያወቀው በግልፅና በቀጥታ መናገሩን አጥብቆ እየፈራ ሰንካላ ሰበብና ምክንያት በመደርደር ክፉ ልማድ የተጠመደ እለት ነው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥን ለሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ/የብልፅግና ፖለቲከኞች እና ለአክራሪ ጎሰኞች አሳልፎ ያስረከበው። ለሩብ ምእተ ዓመት የመቃብርና የቁም ሙት ያደረገውን ሥርዓት ከመሠረቱ ለመለወጥና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት የከፈለውን ውድ ዋጋ እና መልካም አጋጣሚ መልሶ በተሃድሶ ስም ያንኑ ሥርዓት ላስቀጠሉት ሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን የሚያስረክብ ተደጋጋሚ የትውልድ ውድቀት በቀጠለበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ የመከረኛ ህዝብ የሰቆቃ እንባ ማቆሚያ ከቶ ሊኖረው አይችልም።

በእውነተኛው አምላክ ስም ስለ እውነት ከተነጋገርን የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች እኩያን ፖለቲከኞች እየተፈራረቁ የመቃብርና የቁም ሙት እየሞተ እንዲቀጥል ያደረጉትንና እያደረጉት ያሉትን ትውልድ ለመታደግ የሚደረገውን ተጋድሎ ከማገዝ ይልቅ የሸፍጠኛ ፖለቲከኞችን ስሜትና አካሄድ እየተከተሉ ፋይዳ ቢስ የያሳስበናል መግለጫ ከማስነበብና ከማሰማት (የሚያነብና የሚያዳምጥ ከተገኘ) እና  ድርጊት አልባ ስብከት ከማዥጎድጎድ ክፉ ልማድ ፈቀቅ አላሉም።   የአገራችን ልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት በንፁሃን ዜጎች  ላይ የሚፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ግፍ ከምር መፀየፍ ብቻ ሳይሆን ዋጋ የሚከፍሉ አርበኛ መሪዎችንና አስተማሪዎችን ለማፍራትና ለማብቃት ቢችሉ ኖሮ ይህ ትውልድ በእውንና በቁም እየሞተ ሥስት አሥርተ ዓመታትን ባላስቆጠረ ነበር። ለውጥ መጣ የሚል እጅግ ግልብ የሆነ የምሥራች ተለዋውጠን ሳናበቃ የመከራና የሰቆቃ እንባ ባላነባንም ነበር።

ጠንክረን እየሠራን፣ ሃላፊነታችንን እየተወጣን ፣ በአብሮነትና በፍቅር እየተሳሰብን፧ በሰላምና በጋራ ብልፅግና እየኖርን፣ ለግፍና ለመከራ ሥርዓት እምቢ እያልን፣ ለነገው ትውልድ እያሰብን ፣ ወዘተ ከዚህ ተፃራሪ የሆነ ፈተና ጠልፎ እየጣለን ብንቸገርና ፈጣሪን ምነው ምን አጠፋን? ብለን ብንጠይቅና ብንለምን ትክክል በሆነ ነበር ። እኛ እኮ ለረዥም ዘመናት ከመጣንባቸው የመከራና የውርደት ሥርዓቶች መማር አቅቶን አሁንም የሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን እና አክራሪ የጎሳ ፖለቲካ ማንነት ፖለቲከኞች ክፉ በትር ባረፈብን ቁጥር የደም እንባ እያነባን ፈጣሪን የምናስቸግር ፍጡሮች ሆነናል። ታዲያ ይህ ክፉ  ልማድ  የዚህን ትውልድ የቁም ሞት መንገድ ካላሳየን ሌላ ምን ሊያሳየን ይችላል?  በእራሳችን ሁለንተናዊ ውድቀት ምክንያት ለዘመናት ያነባነውና አሁንም እያነባነው ያለው የሰቆቃ እንባስ እንዴት ማቆሚያ ይኖረዋል? የኢህአዴጋዊያን (የብልፅግናዊያን) ሥርዓት ካድሬነትን የኑሮው ዋስትና ካደረገና በሚሊዮኖች ከሚቆጠር የካድሬ ሠራዊቱ ጋር በቀጠለበት መሪር  እውነታ ውስጥ የመከራ እንባ እንዴት ፍፃሜ ይኖረዋል?  ሰውን (እኛን) ከደመ ነፍስ እንስሳት ለይቶ ከረቂቅ አእምሮና ብቁ አካል ጋር የፈጠረበትን ምክንያት እየሸሸንና እራሳችንን ለባለጌና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖች የባርነት ቀንበር እያመቻቸን የእግዚኦታ ጮኸታችንና እንባችን እንዴት ፋይዳ ይኖረዋል?

የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኛ  ገዥ ቡድኖች በሚያሸክሙት የሰቆቃ ቀንበርና ፍፁም ድህነት እየተቆራመደም ቢሆን “አምላክ ይመስገን!” የሚለውን የአገሬ ህዝብ በጅምላ የሚቀጣ ጨካኝ አምላክ  ፈፅሞ  ሊኖር አይችልም።  በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ለዘመናት የተሸከምነውን የመከራ ቀንበር ከላያችን ላይ እዲወርድ የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን (መልካም እድሎችን) በተደጋጋሚ  ለሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው አሳልፈን እየሰጠን ፈጣሪን “ያንተ ፈቃድ ባይሆን ነው” ማለት ጨርሶ ትርጉም የሚሰጥ ነገር አይደለም።   እኛን የፈጠረበት ምክንያት በሥራ በልፅገን፧ በነፃነትና በፍትህ ተመክተን፣ በፍቅርና በሰላም አጊጠን፧ በእኩልነትና በመከባበር ፀንተን ፣ ወዘተ የምኖርበትን ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን በማድረግ ለዚህ እንድንበቃ  ያገዝከን አምላክ  ምሥጋና ይገባሃል እያልን የማያቋርጠውን የትውልድ ቅብብሎሽ ጤናማና የተሳካ የምናደርግ ፍጡሮቹ እንድንሆን ነው።  ከዚህ ይልቅ በእራሳችን ስንፍና እና የጋራ ራእይና ውጤት አልባነት ምክንያት የገዥዎች ብልግና እና ግፍ ከሰአብዊ ፍጡር በታች ባዋለን ቁጥር ያንኑ ተግባር አልባ እግዚኦታችን ካልሰማኸን እያልን የምናደርሰው ድርሳን፣ የምንቀድሰው ቅዳሴ፣ የምንቀኘው ቅኔ፣ የምንዘምረው ዝማሬ፣ የምንፀልየው ፀሎት ፣ የምናደርሰው ምህላ፣ የምንጠቀሰው ቅዱስ መፅሀፍ ለምድራዊም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው ሰማያዊ ህይወት የሚፈይደው ፋይዳ አይኖርም።

የተገፉና የተከፉ ሰዎች  ይኖሩበት  ወደ ነበረው ሥፍራ ሁሉ ተዘዋውሮ በማስተማሩና በመጨረሻም “የሰቆቃ ሰይፋችሁን ከህዝቤ ላይ አንሱ” በማለቱ ወሰንና ገደብ ላልነበረው ሥልጣናቸው ሥጋት የሆነባቸው የዘመኑ ገዥዎች ከሚሰቀልበት ቦታ እስከሚደርስ አላስችላቸው ብሎ መስቀሉን አሸክመው እያዳፉ በመውሰድ ሲሰቅሉት በፀጋ የተቀበለው መሰቀሉን አምነን ስለመሰቀሉና ስለ መነሳቱ እየተረክን (እየሰበክን) ብቻ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ አልነበረም። አይደለምም። ይልቁንም  የምድራዊም ሆነ የሰማያዊው (የመንፈሳዊው) ህይወት የተሳካ ይሆን ዘንድ ለነፃነት፣ለፍትህ፣ ለፍቅር፣ ለሰላም እና በአጠቃላይ ሰውን የተሟላ ሰው ለሚያደርጉ እሴቶች የምናደርገው ትግል እራስን አሳልፎ እስከመስጠት የሚጠይቅ መሆኑን አውቀን የእርሱን ያህል ባይሆነም እንደ የሰው ልጅነታችን (እንደ ሰብአዊ ፍጡርነታችን) የምንችለውን ሆነንና አድርገን እንገኝ ዘንድ ያስተማረበት በዋጋ የማይተመን ተግባራዊ ሥራ ነው።

ንፁሃን ወገኖቹ  (ዜጎች) በገንዛ አገራቸውና ቀያቸው የመቃብርና የቁም ሞት እየሞቱ ዘመናትን ሲቆጥሩ ግፈኛ ገዥዎችንና የጎሳና የሃይማኖት ማንነትን ለእኩይ ዓላማቸው ፍጆታ የሚጠቀሙ የፖለቲካ ነጋዴዎችን ገንቢ በሆነ አቀራረብ መተቸት (መገሰፅ) የተሳነው የሃይማኖት መሪ ወይም አስተማሪ  ስለ መስቀሉና ስለ ትንሳኤው ሃያ አራት ሰዓት ቢያነበንብ ምን ይፈይዳል?

አያሌ ዘመናትን ያስቆጠረው የመከራና የሰቆቃ እንባ መቆም ካለበት ክርስቶስ በማይናወጥ መርህና በተግባር ቁርኝት ላይ የተመሠረተ እምነት፣ ፍቅር ፣ሰላም፣ እኩልነትና መተሳሰብ፣ ወዘተ  ከፍተኛውን ዋጋ የከፈለበት  ወርቃማ ተልእኮ መሆኑን ከልብ በማወቅና በመቀበል  የእራስን ድርሻ  ተወጥቶ  መገኘትን ግድ ይላል። ለሩብ ምእተ ዓመት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቆ የኖረውንና አሁንም እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንደተዘፈቀ የቀጠለውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ብልፅግና   “አድህነነ በእንተ ተሃድሶህ !”  እያሉ ከመማፀን የከፋ ፖለቲካዊ ፣ ሞራላዊና መንፈሳዊ ውድቀት የለም።

ከዚህ ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) ካስለከፉን ክፉ የፖለቲካ ደዌ ለመላቀቅ ተጨማሪ ብዙ ዓመታት ሊወስድበን አይገባም።  ይህን አድርገን የተገኘን እለት ነው ለዘመናት ያነባነውና የተራጨነው የመከራና የሰቆቃ እንባ በእውን የሚቆመው።  መቸም እውነትን በአርበኝነት ስሜት ከመጋፈጥና ትክክለኛውን የጋራ መውጫ መንገድ ከማበጀት ይልቅ የሚቀለን የመካድና ተልካሻ ሰብብ የመደርደር ክፉ ልማድ ሆኖብን ነው እንጅ በእውናችንም ሆነ በህልማችን  እየሞገተ እረፍት የሚነሳን መሪር እውነታ ይኸው  ነው።

ሸፍጠኛና ሴረኛ የገዥው ቡድን ባለሥልጣናት እና የእኩይ ፖለቲካ ጨዋታ ልክፍተኞች ይህኑ ክፉ ልማድ ይበልጥ እያለማመዱን በሄዱ ቁጥር ከፖለቲካ ጨዋታው እየወጣን ለእነርሱ ልክ የሌለው የሥልጣን ብልግና መቀጠል አመች ሁኔታ እንደምንፈጥርላቸው አሳምረው ያውቁታል ። የዚህ አስቀያሚ የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ ሆኖ ላለመቀጠል ነገ ሳይሆን ዛሬ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ የግድ መሆን ያለበትም ለዚህ ነው።

እንኳን በጎሳና በሃይማኖታዊ እምነት ማንነቱ በግፍ ለተገደለ ወገን በተፈጥሮ ወይም በሌላ ምክንያት ለሞተና ለሚሞት ወገንም  ሃዘንን በእንባ መግለፅ የጤናማ ሰብአዊነት ባህሪ ነው። የመከራ ህይወትና የግፍ  አሟሟት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን ሥርዓት አስወግዶ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመተካት የአያሌ ንፁሃን ወገኖችን ህይወት ከመታደግ ይልቅ ማቆሚያ በሌለው የደም እንባ እየታጠቡና እየተራጩ ወደ መቃብር አውርዶ በየቤቱ የመቆዘውምን ክፉ ልማድ በቃን ማለት የግድ ነው። የምንነጋገረው ነፃነት፣ፍትህ፣ የዜግነትና የሰብአዊ መብት፣ ሰላም፣ ፍቅርና የጋራ ብልፅግና ስለሚረጋገጥባት ዴሞክራሲያዊት አገር ከሆነ ከዚህ አስከፊ የቁም ሞት ለመውጣት እልህ አስጨራሹ ትግል መቀጠል ይኖርበታል።

አዎ! የሶስት አሥርተ ዓመታት የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ካስከተለው ለመግለፅ የሚያስቸግር መከራና ውርደት ከምር በመማር የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግ /ብልፅግና በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት የሚገዳደር ህሊናዊና ድርጅታዊ አቅም መፍጠር የተሳነው ትውልድ አሁንም መንፈሳዊና አካላዊ አቅሙን የሚያጎሳቁል የመከራና የውርደት እንባ  ከማንባት አስከፊ አዙሪት ለመላቀቅ አልተቻለውምና በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል። ቅጥ ላጣው ሃዘኑና ልክ ለሌለው  የሞራል ጉስቁልናው ዋነኛ ተጠያቂ የሆኑት  ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) “አሸጋጋሪ ዴሞክራቶች እኛ ነን” የሚሉትን እጅግ ሃፍረተ ቢስ የፖለቲካ ጨዋታ ትተው ወደ አገራዊ የጋራ መፍትሄ ፍለጋ መድረክ እንዲመጡ ከማስገደድ  ይልቅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሸፍጥ ተሃድሶ  ተደማሪ በመሆን ”የለውጥ ሃይሉን መጋፋት አገር ያፈርሳል” የሚል እጅግ የዘቀጠ አስተሳሰብ የተጠናወተው ፖለቲከኛ ባለበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ  የመከረኛው ህዝብ የደም እንባ እንዴት ሊቆም ይችላል?  በፍፁም ሊቆም አይችልም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለመለስ ሙት አመት ማስታወሻ (ከፋሲል የኔአለም) ጋዜጠኛ

እኩያን ገዥ ቡድኖችና ቢጤዎቻቸው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን፣ የዜግነት እኩልነትን ፣የአብሮነት እሴትን፣ አገራዊ ኩራትንና ክብርን በአፍ ጢማቸው የደፋው ህገ መንግሥታቸው “ከተነካ አገር አለቀላት” ሲሉት “የእናንተና ለዚሁ የረከሰ ዓላማችሁ ተባባሪ የሆኑ እኩያን የፖለቲካ ሥልጣን ህልውና ያበቃለታል እንጅ ከየትኛውም ጎሳ ወይም ማህበረሰብ በተገኙ ኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት የተሠራችን አገር ማፍረስ ጨርሶ አይደረግም” ከማለትና አስፈላጊውን ትግል ከማስቀጠል ይልቅ ስለምትፈርስ አገር በህልሙና በቁም የሚቃዥ ፖለቲከኛና አገር ወዳድ ነኝ ባይ ቁጥር ከመቀነስ ይልቅ እየበዛ በሚሄድበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ የመከራና የሰቆቃ እንባ ከቶ ሊቆም አይችልም።

ሥርዓተ ኢህአዴግን ሥርዓተ ብልፅግና ብሎ በሰየመ ተራ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ በምንገኝበት በዚህ ወቅት “በእውነተኛው (በትክክለኛው) ፍኖተ ዴሞክራሲ ላይ ነን ” በሚል ቅዠት የቤተ መንግሥትን (the palace poitics) ደጅ የሚጠና ተቀዋሚ  ነኝ ባይ ፖለቲከኛ በሚተራመስባት አገር ውስጥ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ እያየነውና እየሰማነው ያለው እጅግ አደገኛ እብደት የማይጠበቅ አልነበረም፤ አይደለምም ።

ልክ የሌለው የፖለቲካ ድንቁርና እና የሞራል ውድቀት ሰለባ ያደረጉትን ወጣት ትውልድ በስሜት ትኩሳት በማነሳሳት የገንዛ ወገኑን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለ በኋላ በአስከሬን ላይ ተጨማሪ አረመኔያዊ ወንጅል ሲፈፅም ቆመው መመልከት ብቻ ሳይሆን ተባባሪ የነበሩና የሆኑ  የብልፅግና እና  መሰል ፖለቲከኞች  የሃዘን መግለጫ ሲያዥጎደጉዱና የአዞ እንባ ሲያነቡ ማየትና መስማት በእጅጉ ህሊናን ያቆስላል።

 

ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች በአንድ በኩል ከመከራና ከሰቆቃ አስከፊነት ፈንቅሎ የሚወጣው የእንባ ጎርፍ እነርሱንም እንደሚጠራርግ ሲያውቁ የስሜት ማብረጃ እርምጃዎችን በማሳየት ፣ በሌላ በኩል ደግሞ  ማዘናጋቱ የሠራላቸው ሲመስላቸው  የተለከፉበትን የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ በተረኝነት ለማስቀጠል የማይፈነቅሉት ድንጋይና የማይፈበርኩት የፈጠራ ትርክት የለም ።ለሩብ ምዕተ ዓመት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከበከተውና ከከረፋው ኢህአዴጋዊ ሥርዓት “የለውጥ ሃዋርያት ተገኙ” ከሚል የፖለቲካ ቂልነት ወይም እንጭጭነት የመነጨ  የምሥራች  ተለዋውጠን ሳንጨርስ አይተነውና ሰምተነው በማናውቀው አኳኋን ንፁሃን ዜጎች በገንዛ አገራቸውና ቀያቸው በአስቀቃቂ ሁኔታ ከመገደል አልፎ አስከሬናቸው በስለት ሲቆራረጥ፣ በየአደባባዩና በየጎዳናው ሲጎተት፣ በእሳት ሲቃጠል እና መቀበሪያ ሲከለከል  መስማትና ማየት ሳንሞት በቁማችን የመሞታችን መሪር እውነት ካልሆነ ሌላ ምን ሊነግረን ይችላል?

 

ለዚህ ሁሉ አስከፊ ቀውስ የመጀመሪያውን ሃላፊነትና ተጠያቂነት መውሰድ ያለበት ከአገር መሪነቱ መንበር ላይ የተቀመጠው  ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሚመራው ገዥ ፓርቲና መንግሥት ካልሆኑ ማን ሊሆን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ በኩል  በጎሳ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ  ማንነት በተለከፉ ልክፍተኞች እና በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር በሚመሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአብሮነት አምሮብን መኖር እንችላለን በሚሉ ወገኖች መካከል ያለውን የሃይል ሚዛን እያየ ሚዛኑ አይሎ  ከሚታይበት ወገን ጋር  በመገለባበጥ  የፖለቲካ ጨዋታ የተጠመደ በመሆኑ በሁለት ዓመታት ውስጥ የደረሰው የትውልድ ሁለንተናዊ ቀውስ ለማመን የሚያስቸግር ነው። የማይጠበቅ ግን አልነበረም ።

በፅዕኑና በዘላቂ አገራዊ መርህ ላይ ሳይሆን ለመንበረ ሥልጣንና ልክ ለሌለው የግል ዝና የተመቸ ወይም የሚመች  መስሎ ከሚታይ የሃይል ሚዛን ጋር የሚደረግ የዥዋዥዌ ፖለቲካ  ጨዋታ በጠንካራ ህሊናዊና ድርጅታዊ ትግል  ወይ ካልተስተካከለ ወይም ካልተሸነፈ በስተቀር የግፍና የመከራ እንባ ጨርሶ ፍፃሜ አይኖረውም ።

በሌላ አገላለፅ፦

  • ለርካሽ የፖለቲካ ፍጀታ የተዥጎደጎደውና የሚዥጎደጎደው የይቅር በሉንና የጊዜ ስጡን ዲስኩር መሬት ላይ ሲፈለግ ድራሹ በጠፋበት
  • የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠያቂነት የምር ከሆነ የሰለምና እርቅ እና የማንነትና የወሰን ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት አጥንቶ ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ መስጠት የግድ ነው የሚለው ጥያቄ ግፊቱ እየበረታ ሲመጣ  በእራሳቸው ውስጥም ሆነ በመካከላቸው ሰላም የሌላቸው ግለሰቦችና  የችግሩ አካል የሆኑ ፖለቲከኞች የተካተቱባቸውን ኮሚሽኖች  ተብየዎችን  አቋቋምኩ የሚል  የፖለቲካ ተውኔት በሚተወንበት
  • ለዴሞክራሲ እውን መሆንና መጠናከር እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ተቋማት መካከል ማለትም ለምርጫ ቦርድና ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከኢህአዴግ ጋር ንክኪ ያልነበራቸውንና በአገር ቤትም ሆነ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አንፃራዊ እውቅና ያላቸውን ግለሰቦች በመሾም ከአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀሉ ጋር የቀጠለውን ሥርዓተ ኦህዴድ/ኢህአዴግ/ብልፅግናን የማታለያ ገፅታ ለማላበስ የሚደረገው እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ  በደራበት፣

 

  • ሥልጣን በተረከበበት ንግግሩ ጥርሱን ነቅሎ ያደገበትን ሥርዓት ወንጀለኛና አሸባሪ ነበር (ነበርን) በሚል ይቅርታ በጠየቀበት አንደበቱ ያለፈውን ግንቦት ሃያ አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት “በአገሪቱ ለዘመናዊ ፖለቲካ በር የከፈተ ነው” የሚል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ እራሱን ግልፅ ባደረገበት
  • ተረኛ የጎሳ/የቋንቋ/የመንደር ፖለቲካ ማንነትን መሠረት ያደረገ ሹመትና ሽልማት እየሰጡ ዴሞክራሲያዊ ተሃድሶውን (democratic reform) እያጧጧፍነው ነው የሚል የለየለት የቅጥፈት ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ  በሚነዛበት
  • ለበርካታ ዓመታት በዘለቀው ወንጀለኛ ወይም አሸባሪ ሥርዓት ውስጥ እጁ በንፁሃን መከራና ደም የጨቀየውን የኢህአዴግ ባለሥልጣንና ፖለቲከኛ በሹመትና በሽልማት እያንበሸበሸ የህወሃት ወንጀለኛ ፖለቲከኞችንና ካድሬዎችን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ የፍትህን መሠረታዊ ትርጉምና ልእልና የሚያረክስ የፖለቲካ ጨዋታ በሰፈነበት
  • የፖሊስ ፣የፀጥታና የደህንነት አካላት አስከፊ ችግር ከህዝብና ከአገር ይልቅ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቆ ዘመናት ያስቆጠረውንና አሁንም የቀጠለውን ሥርዓት የማገልገል እንጅ የስያሚ ችግር ይመስል የሰላም ሚኒስቴር የሚል ርካሽ የፖለቲካ ተውኔት በሚተወንበት
  • ለአዲስ አበባ ከንቲባነት የሚበቃ አዲስ አበቤ ተፈልጎ የጠፋ ይመስል በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀነባባሪነት ተዘጋጅቶ በቀረበ የፖለቲካ ሸፍጥ አካሄድ እና ፋታ በማይሰጥ ፍጥነት ለገጠር ቀመስ ከተማ ይሠራ የነበረውን የኦህዴድ ካድሬ በምክትል ከንቲባነት ስም ወሰን/ገደብ በሌለው መንበረ ሥልጣን ላይ እንዲቀመጥ የተደረገበት ርካሽ የፖለቲካ ሴራ በተጎነጎነበትና ሥራ ላይ በዋለበት  
  • ለህዝብ ግልፅ ባልተደረገ የሸፍጥና የሴራ ስምምነት ኦነግን ሁለት ክፉ አማራጮችን ማለትም  ወይ በኢትዮጵያ ላይ ወሰን የሌለው የበላይነትን ማረጋገጥ፣ያ ካልሆነ ግን የነፃ ኦሮሚያ መንግሥትን ማወጅ የሚሉ አካሄዶችን ይዞ  እንዲገባና ብዙም ሳይቆይ ይህንኑ ዓላማውን ለማስፈፀም ሲል በንፁሃን ዜጎች ላይ የመከራ ናዳ ሲያወርድ ፋይዳ ያለው እርምጃ ያለመውሰድ ክፉ የፖለቲካ ሸፍጥ ደመና ባጠላበት
  • ቄሮ በሚል የጅምላ ስም ከሚጠራው  እንቅስቃሴ መካከል በአደገኛ አክራሪነቱ የቀጠለው  ቡድን ጃዋር መሃመድና መሰሎቹ እንደ ተናካሹ ደመ ነፍስ እንስሳ “ያዘውና በለው” ባሉት ቁጥር ታይቶ የማይታወቅ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት  ሲፈፅም ለእራስ ሥልጣን ሥጋት እስከልፈጠረ ድረስ በሚል  ሁለት ዓመታት ሙሉ  በትእግሥት ስም የዘለቀው የፖለቲካ ሸፍጥ አገርን ለፍተኛ አደጋ በዳረገበት
  • ከነችሮቹም ቢሆን ለአያሌ ዘመናት አብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን በመጋባትና በመዋለድ፣ ለአንዲት የጋራ አገሩ የጋራ ደምና አጥንት ዋጋ በመክፈል እና በኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ክሮች  ( economic and cultural fabrics) ተሳስሮ የኖረ ህዝብ በእጅጉ የተቸገረው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ የሚያግዘው ሃይል አለማግኘቱ  ሆኖ ሳለ ፊደል የመቁጠራቸውን መሠረታዊ ትርጉም ወይም እሴት ጨርሶ ዋጋ ያሳጡ እንደ በቀለ ገርባ አይነት ፖለቲከኞች ቋንቋን ፣የገበያ ግብይትን፣ ጋብቻን፣ እና ልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮችን ኢላማ ያደረገ የጥላቻና የመለያየት ዘመቻ በአደባባይ ሲያካሂዱ ሊያስከትለው የሚችለውን አስከፊ አደጋ ተገንዝቦ ቢያንስ ኧረ ነውር ነው በማለት ፖለቲካዊና ሞራላዊ ግዴታውን የሚወጣ ባለሥልጣን የውሃ ሽታ በሆነበት
  • የሁሉም ዜጎች መሠረታዊ መብቶች የሚረጋገጥባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ በየንግግሮቹና ፅሁፎቹ ያስተጋባ የነበረው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በሚመራው የፖለቲካ ድርጅት መድረክ ላይ ሰውን በሰውነቱ እኩል አድርጎ የፈጠረ የእግዚአብሔርን ቃል (አስተምህሮት) ተሸክሜያለሁ የሚል ግለሰብ “ከእናንተ ያልሆኑትን መነኮሳትና ሌሎች አገልጋዮችን ከደብረ ሊባኖስ አባሩና ተቆጣጠሩት” የሚል እጅግ ዘግናኝና አደገኛ ዘመቻ ሲያካሂድ ትክክል አይደለምና ይታረም ከማለት ይልቅ ከፍተኛ የአድናቆትና የድጋፍ ጭብጨባ የሚቸርበት
  • የህወሃት ፖለቲከኞች በበላይነት ሲመሩት በነበረው ወንጀለኛ ሥርዓት ውስጥ ለፈፀሙት ወንጀል ተመጣጣኝ ሃላፊነትና ተጠያቂነት መውሰድ እንዳለባቸው ግልፅ ቢሆንም አገልጋይነቱን ተቀብሎ ወንጀል የፈፀመ የኢህአዴግ/የብልፅግና ባለሥልጣንና ካድሬም ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንዲወስድ በማድረግ ለአገር ሲባል በእውነተኛ ኑዛዜና በፍትህ አግባብ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ትግራይን እየተሻገሩ  ከሻእቢያ ጋር የሚደረግ አስቀያሚ የፖለቲካ  መተሻሸት  በደራበት
  • የሚጓጉለትን እውቀትና ክህሎት ተጎናፅፈው የነገን ኢትዮጵያ በመረከብ የተሻለ ህይወት ለመኖር የሚያልሙ ሚሊዮኖች ህፃናትና ታዳጊ ወጣቶች በፖለቲካ ሥርዓት ብልሹነት ምክንያት ህልውናቸው በሁለንተናዊ የቀውስ ማእበል ከሥሩ የመነቀል አደጋ በተጋረጠበት መሪር ሁኔታ ውስጥ የችግኝ ተከላ ዘመቻን እኔ ካልመራሁት በሚል ለነፍስ አድን ይውል የነበረውን ወርቃማ ጊዜና እውቀት ከቅድሚያ ትኩረት ውጭ ለሆነ የፖለቲካ ትርፍ የማዋል ዘመቻ ገኖ በሚታይበት  
  • ሥልጣኑን ሲረከብ ሴቶች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ህብረተሰብ ስላላቸው መተኪያ የማይገኝለት ሚና የእራሱን ቤተሰቦች በምሳሌነት በመጥቀስ የአድማጭንና የተመልካችን ቀልብ መግዛት የቻለ ጠቅላይ ሚኒስትር አገር አለን ብለው ለትምህርት በሄዱበት ደንቢዶሎ በጨካኝ አክራሪ ጎሰኞች ታግተው ሁኔታቸው አለመታወቁ አልበቃ ብሎ ወላጀቻቸውን ቤተ መንሥት ድረስ አስጠርቶ የርካሽ ፖለቲካ ጨዋታ አጃቢ ካደረገ በኋላ  አሁን በቅርቡ ሲጠየቅ ደግሞ የግብር ይውጣ ምላሽ የሰጠበት እጅግ ህሊናን የሚያደማ የፖለቲካ ሸፍጥ ግልፅ በሆነበት፣
  • እንደ አዳነች አቤቤ የመሰሉ የጎሳ/የቋንቋ/የመንደር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት ወገንተኝነታቸውን የስሜት ትኩሳት ለመቆጣጠር ተስኗቸው በአደባባይ እንደ ህግ ባለሙያ ሳይሆን እንደ ተራና ደንቆሮ ካድሬ የሚተውኑ ወገኖች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆንና በዘላቂነት መቀጠል ቁልፍ ሚና ያለውን የፍትህ ሥርዓት እንዲመሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሆነው በተሾሙበት
  • የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የከፈለው በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀውን ሥርዓተ ኢህአዴግ በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አስወግዶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ለመሸጋገር እንጅ የህወሃትን የበላይነት በኦህዴድ/ኦዴፓ ተክቶ ብልፅግና በሚል የማጭበርበሪያ ስም እንዲቀጥል ለማድረግ  አይደለምና ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል በሚል የሚችሉትን ከማድረግ ውጭ ሌላ ክፋት ያልነበራቸውንና የሌላቸውን ዜጎች ግልፅ የሆነና በጎሳ/በቋንቋ/በሃይማኖት ማንነት ላይ የተመሠረተ የጥላቻና የጥቃት ዘመቻ ላይ ተሠማርተው ከነበሩት እኩያን ጋር ቀላቅሎ በማሠርና ሰብአዊ መብታቸውን በመደፍጠጥ  ታሪክ እራሱን እየደገመ  ባለበት እና
  • እጅግ አደገኛ በሆነ አክራሪ የጎሳና የሃይማኖት ማንነት ትኩሳት የተለከፉ ወገኖች የጎሳና የሃይማኖት ማንነትን ዒላማ ያደረገ እልቂት (genocide) መፈፀማቸው የአደባባይ ሚስጢር ሆኖ ሳለ የዚህ ወንጀል ተባባሪ አንሆንም ያሉ ወይም ዒላማ ከተደረጉ ወገኖቻቸው ጋር የቆሙ ወይም ገዳዮች በጠላትነት ፈርጀው  የሚያጠቁት ሃይማኖት ተከታይች በመሆናቸው የእልቂቱ ሰለባ የሆኑ ኦሮሞ ወገኖችን ቁጥር በመጥቀስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አቀነባባሪነትና አስተባባሪነት  እልቂቱ ዘር ተኮር እንዳልሆነ ለማሳመን የሚደረግ  እጅግ ርካሽ የሆነ  የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በሚካሄድበት  መሪር እውነታ ውስጥ የመከረኛው ህዝብ የደም እንባ ፈፅሞ ማቆሚያ አይኖረውም ።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ዶክቶር ብርሃኑ ነጋ ና አውራምባ ታይምስ - ከግርማ ካሣ

አዎ! የፖለቲካ ልዩነታችንን እንደ ኮቪድ -19 የመሰለ ወረርሽኝን ለመዋጋትና የአገርን አንድነትና ልኡላዊነት ለማስከበር በአስገዳጅ ቅድመ ሁኔታነት ማቅረብ ጨርሶ ትክክል ሊሆን አይችልም ።ለእንደዚህ አይነት አገራዊ ጉዳዮች በጋራ የመቆማችን አስፈላጊነት  የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፖለቲካ ሰብእና ከመውደድ ወይም ካለመውደድ ጋር የሚጣበቅ ከቶ ሊሆን አይገባውም። ለዚህ ነው እኮ ህወሃትና ሻዕቢያ ሲሰርቁ  ተስማምተው ሲካፈሉ ግን በመጣላታቸው ሻዕቢያ  የኢትዮጵያን ልኡላዊነት ሲደፍር አያሌ ወገኖች የህይወት ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆኑት።ይህን ደግሞ ከለየላቸው ባንዳዎችና የጎሳ ንጉሦች ወይም ንግሥቶች የመሆን ቅዠት ውስጥ ገብተው የጋራ አገር የሚለውን ታላቅ ጉዳይ ጨርሰው የዘነጉ ወገኖች ካልሆኑ በስተቀር እጅግ ብዙሃኑ የአገሬ ህዝብ በሚገባ ይገነዘበዋል። ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ  በጋራ  ቆሞ መተኪያ የማይገኝለትን ዋጋ የመክፈል  ታሪክ ለእርሱ አዲስ አይደለምና።

ከሻእቢያ ሽንፈት በኋላ   “አንድነቷንና ልኡላዊነቷን በደምና አጥንት ያስከበርነው በነፃነት ፣ በፍትህ ፣በእኩልነት፣ በሰላምና በጋራ ብልፅግና የምንኖርባት አገር  እንድትሆን  ስለሆነ ከእንግዴህ  ህዝብን በጎሳና በቋንቋ ከፋፍሎ መከራና ውርደት ውስጥ እንዲኖር የማደረጉ  የፖለቲካ ጨዋታ መቆም አለበት” ብሎ የህወሃት/ኢህአዴግን ሥርዓት  በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት የሚታገልና ውጤታማ የሚሆን ሃይል ባለመገኘቱ መከራውና ውርደቱ ለውጥ መጣ እስከተባለበት ድረስ ቀጥሎ ቆይቷል።  አለመታደል ሆኖ ሳይሆን በከፍተኛ መስዋእትነት የተገኘን እጅግ ከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ በአግባቡ መርቶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግር ሃይል ባለመገኘቱ ኢህአዴግ የሸፍጥ ተሃድሶውን እንዲቀጥል እድል በተሰጠው ማግሥት ጀምሮ አስከ አሁን ድረስ ያየነውንና የሰማነውን እጅግ አስከፊ ሁኔታ ቃላት አይገልፁትም።

ህዝብን ለኢኮኖሚዊ፣ማህበራዊ፣ሞራላዊና መንፈሳዊ ውድቀት በመዳረግ እንደ ኮቪድ -19 የመሰሉ የተፈጥሮ ፈተናዎች በተከሰቱ እና  የውስጥ ቅጥረኞችን በመጠቀም ልኡላዊነትን የሚጋፉ እንደ ግብፅ አይነት መንግሥታት የዲፕሎማሲንና የጦርነት ፕሮፓጋንዳን እያቀላቀሉ ያዙንና ልቀቁን ባሉ ቁጥር በከፍተኛ ሥጋትና ጭንቀት ውስጥ እንዲኖር ያደረውና አሁንም እያደረገው ያለው በጎሳ/በዘር/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት ላይ የተመሠረተው፣ በህወሃት የበላይነት ሲመራ የነበረውና አሁን ደግሞ እራሱን ብልፅግና ብሎ በመሰየም በኦህዴድ የሚመራው ገዥ ፓርቲና መንግሥትበአስተሳሰቡም ሆነ በመንግሥታዊና የፓርቲ መሠረታዊ ምንነቱና ማንነቱ  ያው ኢህአዴግ ነው።

አዎ!  የታላቅና ረጅም ታሪክ ባለቤቶች እንደ መሆናችን እና በተፈጥሮ ሃብትም እንደ መታደላችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ መንግሥትና ህብረተሰብ እውን ለማድረግ ባለመቻላችን በብርቱ ድህነት ውስጥ መማቀቃችን ሳያንስ ይኸውና በጎሳ ፖለቲካ ማንነት ላይ የተመሠረተ ግድያ እየፈፀምን በአስከሬን/በሬሳ የምንሳለቅ ጉዶች ሆነናል።

ታዲያ ግብፅና መሰሎቿ ይህንን የቤታችን አስከፊ ሁኔታ ተጠቅመው ከእኛው መንጭቶ ወደ እነርሱ የሚፈሰውን የዓባይ ውሃ ከመሠረታዊና ከኤሌትሪክ ኅይል ፍጆታ አልፈው ለቅንጦት/ለመዝናኛነት እየተጠቀሙበት እኛ በመሠረታዊ ፍጆታ እጥረትና በጨለማ ኑሮ እንደተጎሳቆልን እንድንቀጥል ልኡላዊነታችንን ከመዳፈር አልፎ በእኩያን ወገኖች መሣሪያነት አገራችንን ለማፈራረስ እንቅልፍ ቢያጡ ለምን ይገርመናል ? ኀያልን መንግሥታትስ ቢሆን በሜድትራኒያንና በመካከለኛው ምሥራቅ ብሄራዊ ጥቅማቸውን በማስጠበቅና ይበልጥ በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና አላት ከሚሏት ግብፅ ይልቅ ተመፅዋቻቸው መሆናችን ሳያንስ በሥርዓት ብልሹነት ምክንያት በጎሳ/በቋንቋ የተገደቡ ትንንሽ መንግሥታትን በመፈልፈል  ከተጠመድን  ደካሞችጋር እንዲቆም እንዴት እንጠብቃለን?  በአንፃራዊነት የበለፀጉ አገሮችን ክፉኛ የፈተናቸውና እየፈተናቸው ያለው የኮቪድ-19 ህይወት አጥፊና ኢኮኖሚ ደፋቂ የሆነውን ማእበልስ እንዴት በቀላሉ ልንወጣው እንችላለን?

የዓለም አቀፍ ግንኙነት በዋናነት የሚዘወረው የእየራስ ፍላጎትንና ጥቅምን ከፍ ለማድረግና ለማስከበር በሚደረግ ፍትጊያና አንዳንዴም ሊታይ ከሚችለው ጦርነት ባላነሰ በሚካሄድ የጥቅም ግጭት ውስጥ እንጅ በሞራል ፣ በርህራሄ ፣ በቅንነት፣ በግልፅነት፣ በታማኝነት፣ ወዘተ አይደለም። ይህ ማለት እነዚህ በጎ እሴቶች ለፖለቲካ አያስፈልጉም ማለት አይደለም ። እነዚህ እሴቶች ወደ ገሃዱ ዓለማችን አስቸጋሪና ውስብስብ ባህሪና መስተጋብር ሲወርዱ ጉልህ  ሚና የመጫወታቸው እድልም እየተዳከመ የመሄዱ ነገር የዓለማችን መሪር እውነት መሆኑን ከቶ ልንስተው አይገባም ለማለት ነው።

ለዚህ ነው በዚህ አስቸጋሪና ውስብስብ የዓለም መንግሥታት ግንኙነት ሂደት ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ አግኝቶ ተገቢውን ሚና ለመጫወትና በግንኙነቱ የሃይል ሚዛን ላይ በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በሚጨበጥ ተግባር ጉልህ የሆነ ተፅዕኖ ማሳደር መቻል እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ። ይህን ሆኖና አድርጎ ለመገኘት ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ የተመሠረተና ለዜጎች ሁለንተኑዊ መብቶችና ጥቅሞች ከምር የሚጨነቅና የሚሠራ ሥርዓተ መንግሥት መኖርን የግድ ይላል። የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካን በተረኛ ጉልቻነት እየፈራረቁ እና ስምና ድርጅታዊ ቅርፅ እየቀየሩ የእራሳቸውን ዜጎች ልክ በሌለው የድህነት አረንቋ ውስጥ ዘፍቀውና በግፍ ቀንበር ሰንገው የያዙ (የሚይዙ) ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች በሚገዙት አገር ውስጥ የአገርን አንድነትና ልኡላዊነት በአስተማማኝና በዘላቂነት መጠበቅና ማስጠበቅ  ማስከበር እችላለሁ ማለት ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት አያልፍም።

የአገር ደህንነት በሚል ሰበብ ወይም ምክንያት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄንና ትግልን  እርግፍ አድርገን እንተወው የምንል ከሆነ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ መደስኮሩን ትተን እንደ ደመ ነፍስ እንስሳ የሸፍጥና የሴራ ተሃድሶ ፍርፋሪ በመልቀም ሆዳችን እየሞላን ለመኖር ፈቃደኞች መሆኖችን ግልፅ ማድረግ ይሻለናል። ይህን አይነት አስቀያሚ  ውድቀት በእውን የምንፀየፍ ከሆነ  ገንቢና ሰላማዊ የሆነው የእውነተኛ ዴሞክራሲ ሥርዓት ለውጥ  ትግል ጨርሶ ሊገታ አይገባውም ብለን መሟገትና ትግሉንም በተጠናከረና በተቀናጀ ሁኔታ ማስቀጠል  ይኖርብናል። ዘመናትን ካስቆጠረው መሪር የህይወት ገጠመኝ እና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ  ከቀጠለው  ኢሰብአዊ የፖለቲካ ባህሪና ተግባር ለመማር ካልቻልን ወይም ፈቃደኞች ካልሆን የመከረኛው ህዝብ የሰቆቃ እንባ አሁን ከምናየው በላይ በእጅጉ የከፋ እንደሚሆን ለመናገር ነብይ መሆንን አይጠይቅም።

ኢህአዴጋዊያንና/ብልፅግናዊያንና ቢጤዎቻቸው ለሩብ ምእተ ዓመት በንፁሃን ደም የጨቀየው ማንነታቸውና ምንነታቸው በይቅርታ ሃያልነት መታደስ ካለበት በበሰበሰውና በከረፋው ሥርዓተ ፖለቲካና ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ ተዘፈቀው ጉልቻ ከመለዋወጥና ከማለዋወጥ ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ በመውጣት ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ወደ ሚበጀው አገራዊ የምክክር መድረክ በመታደም እውነተኛና በጋራ ሊተገበር የሚችል ስትራቴጅና ሥልት መንደፍና ይበልጥ  ሳይመሽ  ወደ ተግባር  መግባት ይኖርባቸዋል።

ከላይ እስከ ታች ችሎታንና ቅን ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነትን ተጠቅሞ ቢችል እጅግ ወፍራም እንጀራ ካልሆነም ወፍራም እንጀራውን እያበሰለ ሩብ ምእተ ዓመትን ያስቆጠረና አሁንም በዚያው ለመቀጠል የወሰነ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የካድሬ ሠራዊት የሚተራመስበት ሥርዓት  ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ይችላል ማለት በህዝብ መከራና ሰቆቃ ማሳለቅ ነው የሚሆነው። ።

እናም የመከረኛው ህዝብ የመከራና የሰቆቃ እንባ መቆም ካለበት መውጫ መንገዱ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንጅ በፍፁም የኢህአዴጎች/የብልፅግናዎች የሸፍጥና የሴራ ተሃድሶ ሊሆን እንደማይችል አውቆ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ትግሉን ከተዳከመበት አንስቶና አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ነው።

ይህ እንደሚሆን ያለኝን ተስፋ እየገለፀሁ አበቃሁ!

 

 

3 Comments

  1. Empty rhetoric. Anyone can talk like this non stop. Finding the working solution for the problems we are in is however difgicult. There is no an easy solution for the problems we sre facing …such empty rhetoric does not help in any way to resolve the challenges. Try to be pragmatost.

  2. “የእልቂቱ ሰለባ የሆኑ ኦሮሞ ወገኖችን ቁጥር በመጥቀስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አቀነባባሪነትና አስተባባሪነት እልቂቱ ዘር ተኮር እንዳልሆነ ለማሳመን የሚደረግ እጅግ ርካሽ የሆነ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በሚካሄድበት መሪር እውነታ ውስጥ የመከረኛው ህዝብ የደም እንባ ፈፅሞ ማቆሚያ አይኖረውም ።”

    ምንድን ነው የምታወራው? በአርሲ የተገደሉት አማሮች ጎን ኦሮሞዎችም እንዳሉ የአርሲ ሊቀጳጳስ ግድያው የብሄር ሳይሆን የሀይማኖት እንደሆነ እሳቸውም የተረፉት በሀገር ሽማግሌዎች ልመና እንደሆነ መሰከሩ:: የዐቢይ ተቃዋሚዎች ዛሬ የወያኔ ሀገር ማፍረስ አራጋቢዎች መሆናቸው ያሳዝናል:: የዝዋይ አርሲ ባሌና ሻሸመኔ እስላሚክ ኦሮሞ የጃዋር ክንፍ የሸዋን ክርስቲያን ኦሮሞ ከአማራ ነጥሎ አያይም:: ይህ መሬት ላይ ያለ ያፈጠጠ ሀቅ ነው:: አማራ የሚሸነፈው ኢትዮጵያም የምትበተነው ሁሉን ኦሮሞ ወያኔ እንደሚፈልገው አማራ እንዲጠላለት ሲሳካለት ነው:: አምና በአማራ ክልል ዐቢይ እነ አምብቸውን አስገደለ እሱ ኦነግ ነው:: ይህን የደደበ ፕሮፓጋንዳ ዘፋኙ ሳይቀር ነገደበት:: ዘንድሮ ደግሞ ሀጬ ሁንዴሳን ዐቢይ ነፍጠኛ ስለሆነ አስገደለው በማለት ፅንፈኛና ደደቡ ኦሮሞ ይነግድበታል::
    ወያኔ ሀገር ለማፍረስ ጦርነት ጀምሯል:: ዛሬ ፖለቲካ የሚነገድበት ወቅት አይደለም:: ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከዐቢይ ጋር ተሰልፎ የሀገሩን አንድነት ያስጠብቃል!!

  3. እሰይ የልቤን ነው የጻፍከው። አሁን እዘጭ እዘጭ እያሉ የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮዎች) በአክራሪዎች ሃይል ተጠልፈዋል የሚሉን ወስላቶች ናቸው። ገና ከጅምሩ እይታቸው ኦሮሞን ለኦሮሚያ ነው። ለዛ ነው በትምህርት ተቋማት ሰው በጩቤ ወግተው ሲገድሉ (በጅማ፤ በወለጋ፤ እና በሌሎችን የትምህርት ተቋማት) መንግሥት ዝም ብሎ ስለተመለከተ የልብ ልብ ተሰማቸው። በአዲስ አበባ ጸብ የለሽ በዳቦ ዓይነት እየዞሩ ትንኮሳ በማደረግ የሰው ቤት የያፈረሱት፤ ቤት ያቃጠሉት፤ በነሲብ ሳይሆን ተደራጅተውና አስበው ነው። ይህን ሁሉ ለማቀናበር ሶሻል ሚዲያ፤ የጃዋር የውስጥ የግንኙነት መረብና የ OMN ሚዲያ ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ ሃጫሉን ለግድያ ሲያመቻቹት ይጠይቁት የነበረው ጥያቄ ሁሉ ከአማራ ህዝብ ጋር ጥላቻን የሚፈጥርና ሆን ተብሎ የተተበተበ ገመድ እንደሆነ ተቆርጦ የቀረው የከያኔው ቃለ መጠይቅ ያሳያል። ታዲያ የጃዋርና የጀሌዎቹ ብልሃት ራሳቸው አስገድለው አማራ ገደለው በማለት ህዝብ ለማጫረስ ነበር። ያው ቀደም ብለው ባስተላለፉት መመሪያ መሰረት ከኦሮሚያ ፓሊስ እስከ እልፍ ጀሌዎቹ ነዳጅ በጣሳ፤ ቋንጭራና ገጀራ በእጃቸው ይዘው ነው የሰውን ህይወትና ሃብት ያወደሙት። ስለዚህ አላማቸው በአክራሪ ሃይሎች እንደተጠለፈ አድርገው የሚያወሩ ለዘብተኛ ፓለቲከኞች ሁሉ ነገር አማቺዎች እንጂ እውነትን እየነገሩን አይደለም። እነ ዶ/ር መራራ ሳይቀሩ ነው በዚህ መርዝ ሰንበቴ የገቡት። ከጃዋር ጋር ዶ/ር መራራ አብሮ መዋል ከጀመረ ወዲህ የተናገራቸውን መዝኖ መፍረድ ይቻላል።
    የኦሮሞ ፓለቲከኞች አብደዋል። በአፍሪቃ፤ በእስያ፤ በአውሮፓ፤ በሰሜን አሜሪካ በየምክንያቱ ገብተው በዚያው ተወሽቀው እየኖሩ ኦሮሚያን ለኦሮሚያ የሚሉ ግብዞችና እውር እይታ ያላቸው የዘር ጥማተኞች ናቸው። አሁን ኦሮሚያ ለብቻዋ ብትገነጠልና ሃገር ብትሆን እርስ በርሳቸው መላተማቸው አይቀሬ ነው። ችግሩ የጭንቅላት እንጂ የመሬት አይደለም። ዘረኞች ከየትኛውም ወገን ይሁኑ ሰካራሞች ናቸው። እይታቸው ሙሉ ያልሆነ እርምጃቸው ሸፋፋ ነው። ለዛም ነው ዝንተ ዓለም ስንገዳደል የምንኖረው። ለአረቡ፤ ለነጩ ስናጎበድድ ስንታዘዝ ወገናችን ግን ስንገድልና ስናጣጥል ጊዜው ነጎደ። አረቡ፤ ቻይናው፤ ህንድ ወይም ነጩ ለጥቁር ህዝብ ገዶት አያውቅም። እንድንፋጅ ግን ይሻሉ። ለዛም ነው ግብጽ በገንዘብ፤ በሃሳብ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አፈንጋጭ የሆኑ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ሁሉ ሲረድ የኖሩት። አሁንም እየረድ ያሉት። የቀድሞው የግብጽ መሪ ናሰር እንዲህ ብሎ ነበር ” የአባይን ጥቅም ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን ማተራመስ አማራጭ የሌለው ብልሃት ነው” ማን ያስታውስ ይሆን? የታህሳሱ ግርግር እየተባለ በሚጠራው የእነ መንግስቱ ንዋይ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ላይ ግብጽ ወታደራዊ ሃይል አዲስ አበባ አስገብታ እንደነበር? ዛሬ በአልጀዚራና በሌሎችም የአረብ ሃገሮች ሚዲያ የኢትዮጵያ ስምና ህዝብ የሚያጣጥሉት ራሳችን ካስተማርናቸው ክፋት ተነስተው ነው። ሻቢያ፤ ወያኔ፤ የኦሮሞ አክራሪዎች አንዴ እስላም ሌላ ግዜ ክርስቲያን እየሆኑ የሃገሪቱን ገጸ ባህሪ አፍረክረውታል። ለዚህም ነው የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች ዶ/ር አብይ የተሸለመውን የሰላም ሽልማት እንዲቀማ በህበረት ለኖቬል ኮሚተው ደብዳቤ የጻፉት። ጥላቸው የኢትዪጵያ ሰንደቅ ዓለማ ክፍ ብሎ መታየትና የሃገራችን ህዝቦች አንድነት ላይ ነው። ትግሬ እገነጠላለሁ ይላል፡ አማራው ከቅማንት ጋር ይፋለማል፤ ኦሮሞው ጉራጌውንና መጤ ነው ብሎ ያመነውን አንገት ይቀላል እንዲህ ባለ ሃገር ኦሮሞው ሰላም ተኝቶ ማደር ይችላል? ጭራሽ። በክልል ፓለቲካ ሰበብ ሁሌም አነሰብኝ፤ ተቀማሁ፤ አምጣ፤ ውሰድ በሚል ውዝግብ መተራረድን እያየን ነው ይቀጥላል። ለዚህም ነው አሁን ኦሮሞዎቹ በሚበትኑት ወረቀት ላይ የአማራን፤ የመጤን፤ የጉራጌን ወዘተ ንብረት የሚገዛ እንገላለን የሚሉት። ያለህን ሁሉ ጥለህ ውጣ ነው። ይህ ደግሞ በተደራጀ መልኩ የሚፈጸም ወንጀል እንጂ በግብታዊ የፓለቲካ ትኩሳት የሚሰራ ተግባር አይደለም። መኪና ሲያቃጥሉ ታርጋ እያዪ እንደነበር በአይኑ የተመለከተ ሰው ነግሮኛል። ቤት ሲያቃጥሉ አንድ ቀደም ብሎ ቀለም እየቀባ ሌላው እየተከተለ ቀለም የተቀባውን ቤትና ንብረት ነበር የሚያጋዪት። ይህ ቀደም ሲል በሰበታ የተፈጸመ ወንጀልም ነው። ግን የጠ/ሚሩ ዝምታ ገና ሃገሪቷን የእሳት ቋያ ያደርጋታል። እንዴት የገደለ አይገደልም። በደቦ የገደለ አስልፎ መግደል ነው እነርሱንም። ያለዚያ ልንወጣው የማይቻለን ማጥ ውስጥ እንገባለን። እየገባንም ነው። ኦሮሞ ይሁን አማራ ወይም ትግሬ ወይም ሌላ ከገደለ መግደል ነው። የመኖር መብት የለውም። የሚያሳዝነው ተምረናል የሚሉ የዘር ፓለቲከኞችም ቀበሮና ተኩላ ሆነው በበጎች መካከል መሰለፋቸው ነው። የተማረ ይግደለኝ ይል የለ የሃገሬ ሰው። ይኽው የተማረውና ያልተማረው አንድ ግንባር ፈጥረው አንገት ቆራጭና ቤት አቃጣይ ሆነውልሻል። እስይ እንዲህም ብሎ የነጻነት ትግል የለም። ሰው እንደ ሰንጋ በሬ የሚያርድ አረመኔዎች! በቃኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share