ፍትሕ! ሕገወጥ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለወንጀለኞች – በገ/ክርስቶስ ዓባይ         

/

በገ/ክርስቶስ ዓባይ
ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ/ም

አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በአረመኔዎች የተወሰደበትን የግፍ ግድያ ተከትሎ በቀጣዩ ቀን ማለትም ማከሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ/ም እነዚሁ የጥፋት ኃይሎች በአነሳሱት የመንጋ ዘመቻ፤ በንፁሐን ዜጎች ንብረት እና በመንግሥት ተቋማት ላይ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፤ ያውም በኢትዮጵያ ምድር ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ከፍተኛ የሆነ የንጹሐን ሕይወትና የንብረት ውድመት ደርሷል።

እንዲህ ያለውን ሕገወጥ ዘመቻ መንግሥት በወቅቱ መቆጣጠር በተገባው ነበር፤ ነገር ግን የዲሞክራሲን ጭላንጭል ሳያይ ለረጅም ዓመታት ታፍኖ ለቆየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስተዋወቅ፤ በልበ ሠፊነት እየሠራ ያለውን  የዶ/ር ዓቢይ አስተዳደር ታላቅ ፈተና ላይ ጥሎታል። ይህን መሰል ሕገወጥ ድርጊት የጠነሰሱት፤ ያቀነባበሩት እና የመሩት በውጭ ኃይል እየተደገፉ ያሉት ባንዳዎች ለመሆናቸው ምንም ማስረጃ አያስፈልገውም። ሐቀኛ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ንብረት አያወድሙምና!

የሰይጣን እንደራሴዎች፤ ቀደም ሲል የነበራቸውን ሥልጣን መከታ በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ መቶ በመቶ በመቆጣጠር፤ የሠፊውን ሕዝብ አንጡራ ሀብት በመመዝበርና በመዝረፍ ሲያጋብሱ እንደነበር የማይታበል ሐቅ ነው። ከልዩ ልዩ አገራት የሚገኘውንም ብድር ሳይቀር በውጭ አካውንታቸው እንዲገባ በማድረግ ለግላቸው እንዳዋሉት የሚካድ አይደለም። ይህ ሁሉ ሆኖ ሰላም ለማስፈን ሲባል በለውጡ ሂደት  የተጠየቁት አንዳችም ነገር የለም። ነገር ግን እነዚህ ወንጀለኞች ከፍተኛ ገንዘብ በጆንያዎች አጭቀው በመያዝ፤ ተሰባስበው በመኮብለል እራሳቸውን አግልለው ተቀምጠዋል።

ይሁን እንጂ ሰላም ለሰይጣን አይዋጥለትምና ለእነሱም ፍርሃትና ስጋት ስለሆነባቸው ሤራ ማውጠንጠኑን አላቆሙም። ጉዳያቸውንም የሚያስፈጽምላቸው አገሩንና ወገኑን በገንዘብ የሚሸጥ ከሀዲ አላጡም። ስለሆነም ከሰበሰቡት ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ገንዘብ ላይ እጃቸው አንዳነሳ እየዘገኑ ለተላላኪዎቻቸው ያዘንባሉ።

እነዚህ ተላላኪ ባንዳዎችም የፖለቲካ ሀሁ የማያውቁትን የዋህ የኦሮሞ ወጣቶች በመጠቀም ዘግናኝ የሆነ የነፍስ ማጥፋት ወንጀልና የንብረት ውድመት አስፈጽመዋል። እነዚህ ወንጀለኞች በስማቸው የተመዘገበ ታላላቅ  ሕንፃ በአዲስ አበባ ከተማ እንዳላቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ስማቸውን እገሌና እገሌ ብሎ መጥቀስም አስፈላጊ አይደለም በግልጽ ይታወቃሉና። ዝርዝሩን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ባለሥልጣናት እንተዋለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቀጣዩ መንግሥታችን ሸክም (ይሄይስ አእምሮ)

በአንፃሩም፤ የመንግሥትን ከለላና ጥበቃ በመተማመን ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ብሎም አገራቸውን ለማሳደግ ሰላማዊ የየዕለት ተግባራቸውን በመሥራት ላይ ባሉ ንጹሐን ዜጎች፤ ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለፍትሕ ቁሜአለሁ የሚለው የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት ችላ ሊለው እንደማይገባ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚስማማበት ጉዳይ እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም።

እንዲህ ያለውን ኪሣራ መንግሥት በምን አቅሙ ሊሸፍነው እንደሚችል ግራው ሊገባው እንደሚችል ይታመናል። ምክንያቱም መንግሥት የሚንቀሳቀሰው በየዓመቱ በተተመነ በጀት ስለሆነ እንዲህ ያለውን ድንገተኛ አጋጣሚ ለመሸፈን የፋይናንስ አቅም ሊያጥረው እንደሚችል አጠያያቂ አይሆንም። ነገር ግን ከጉዳዩ ጋር የተያያዙትን እና በቀጥታ ግንኙነት ያላቸውን አካላት፤ ተጠያቂ ማድረግ ፍትሐዊ እንደሆን አሻሚ ሊሆን አይችልም።

እንዲህ ዓይነቱን የንጹሐን ዜጋ ሕይወት፤ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የመቅጠፍና ይህንንም እንደ ምክንያት  አድርጎ አስቀድሞ በተጠና እና በተቀነባበረ መንገድ፤በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዘርን መሠረት ያደረገ፤ በግል ድርጅቶችና በመንግሥት ተቋማት ላይ የመንጋ ውድመት ዘመቻ ያካሄዱት ቡድኖች፤ በግልጽ የሚታወቁ ስለሆነ በእነርሱ ላይ የማያወላውል እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።

መንግሥት ሴራውን በጠነሰሱትና በመሩት ላይ፤ የጠ/ዐቃቢ ሕግ ሕጋዊ የሆነ ክስ መሥርቶ የፍርዱ ሂደት ለትምህርት እንዲሆን በቀጥታ ሥርጭት ለሕዝብ እንዲታይ መደረግ ይኖርበታል ። ይህ ሁኔታ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል፤ ለወደመው ንብረት ግን በቡድኖቹ (ፓርቲዎቹ) ስም የተመዘገበ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ሀብት በሀራጅ ተሸጦ፤ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት በካሣ መልክ እንዲከፈል ያስፈልጋል። ይህ ብቻም አይደለም፤ በዚህ እኩይ ተግባር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉት የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች ስለሆኑ ለወደፊቱ ለትምህርትና ለመቀጣጫም እንዲሆን ከ2013 ዓ/ም የኦሮሚያ በጀት ላይ ተቀንሦ ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት እንዲከፈል በማድረግ ፍትህን ማስፈን ተገቢ ይሆናል።

እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት ለመወሰን እንደሚቸገር ግልጽ ነው። ምክንያቱም አጥፊዎች ሁልጊዜም ጥቂት ሰዎች ናቸውና፤ አብዛኛው ሕዝብ በእነዚህ እኩይ ሰዎች ምክንያት አብሮ መበደል እንደሌለበት እሙን ነው። ነገር ግን ከሕዝብና ከፈጣሪ አምላክ የሚሰወር አንዳችም ነገር የለምና አባት፤ አናት፤ ወንድም፤ እህት፤ ወይም ጓደኛ የሆነ ሁሉ በመምከርና በመገሰጽ ማስቆም ሲገባቸው፤ ይህንን ስላላደረጉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አባሪና ተባባሪ መሆናቸው የሚካድ አይሆንም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አዜብ መስፍንና የቼኮሌቱ ታሪከ

ስለሆነም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዘመቻው ተባባሪ ስለሆኑ ችግሩንም እንዲያውቁና እንዲረዱ ማድረግ ፍትሐዊ ከመሆኑም በላይ፤ ለወደፊቱም ተመሳሳይ መጥፎ ተግባር እንዳይከሰት ታላቅ ትምህርት የሚሰጥ በመሆኑ በዚሁ መልክ ሊወሰን ይገባዋል።

በኦሮሚያ ክልል ቦታና ቤት ገዝተው የሚኖሩ የሌላ ብሔር ማኅበረሰቦች በየክፍለ ከተማ ማዘጋጃ ቤቶች የሚደርስባቸው ግፍና መጉላላት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይ ተማሩ ተብለው በመሐንዲስነት ተመድበው የሚሠሩ ኃላፊዎች፤ እራሳቸውን በማኅበር አደራጅተው የሕዝብ ጉዳይን ጠፍንገው በመያዝ ከአእምሮ በላይ የሆነ ሕገወጥ ክፍያ፤ በሕጋዊ መንገድ እያስከፈሉ መሆኑና የክልሉ አስተዳደርም የሕዝብን በደልና ዕንግልት ለማስቆም የወሰደው እርምጃ አለመኖሩን በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የአቶ ሺመልስ አብዲሳ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ የኢንጂኔር ታከለ ኡማ አስተዳደር፤ እና የጠ/ ሚንስትር የዶ/ር ዓቢይ አህመድ አስተዳደር ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል። በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ ፍትሐዊነት የሚመዘንበት ሁኔታ ላይ ይገኛል። ይኸውም ከዘርና ከጎሣ አስተሳሰብ ነፃ በሆነ መልኩ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ቆርጠው መነሳታቸውን በቅድሚያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከዚያም ባለፈ ለዓለም ሕዝብ የሚያረጋግጡበት ወቅት አሁን ነው።

ምክንያቱም ግብር ከፋይ ሰላማዊ ሕዝቦች፤ ሳያስቡት በድንገት በደረሰባቸው የመንጋ ጥቃት፤ ያጋጠማቸውን ኪሣራ መንግሥት በጥልቀት መርምሮ ተገቢውን ካሣ ሊከፍላቸው ይገባል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ‘አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ’ እንደሚባለው ይሆንና ውጤቱ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ለማንም የተሰወረ አይሆንም።

ነገሩ ‘ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ!’ ከሆነ በአገራችን እንደ ሩዋንዳ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ የከፋ ዕልቂት ሊከሰት እንደሚችል ይታመናል። ምክንያቱም ሕግንና መንግሥትን መከታ በማድረግ፤ ዕለታዊ ተግባራቸውን እያከናወኑ የነበሩት ንጹሐን ዜጎች፤ ዕድሜ ልካቸውን የለፉበት ሀብትና ንብረት፤በማንነታቸው እየተመዘኑ በመንጋ ዘመቻ ሲወድምባቸው መንግሥት እያየ ፍትሕ የማያስከብር ከሆነ፤ ሁሉም በራሱና በመሰለው መንገድ ሁሉ መብቱን ለማስከበር ይጣጣራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አቤ ጆቤና ሥጋቱ - ይሄይስ አእምሮ

በዚህ ጊዜ የዘር ጥላቻው እየከረረ በመሄድ፤ እርስ በእርስ መገዳደል ሊከሰት ይችላል። እንዲህ ያለውን አስፈሪ ሁኔታ ለመግታትና የቀድሞዋን የኢትዮጵያውያንን እሴት ለማምጣት የግድ የሕግ የበላይነትና የፍትሕ መረጋገጥ ይኖርበታል። የመንግሥት ተቋማትም ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ህልውና ሲሉ የሕግ የበላይነትን በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በብልጽግና ፓርቲ ያለው እምነት ከፍተኛ እንደሆነ ቢታወቅም፤ ይህንን እምነትና የጸና ድጋፍ ለመሸርሸር ሲሉ ተስፋ የቆረጡ ሴረኞችና ቅጥረኛ ባንዳዎች፤ የሕዝብ አመኔታን እንዲያጣ የተቀነባበረ ተንኮል መሥራታቸው ይፋ ወጥቷል። እንዲህ ያለውን ፈተና በድል ለመወጣት ሲባል ጀግንነትና ጥበብ  የተሞላበት የማያሻማና ድርድር የሌለው ውሳኔ መወሰን ግድ ይላል።

በአዲስ አበባ በቦሌ፤ በጃክሮስ፤በጀሞ፤ በባሌ፤ በአርሲ፤ በሐረር፤በባሌ ሮቤ፤ ብርዶዶላ በጅማ፤በሻሸመኔና በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸመውን ቃጠሎ ዘረፋና ቤት የማውደም ተግባር፤ ከሠለጠነ ሕዝብ ሳይሆን ከእንስሳነት ባህርይ ባልወጡ፤ የአስተሳሰብ አድማሳቸው እጅግ በጣም ውስን በሆኑ፤ የዋሃን ወጣት ዜጎች የተካሄደ ለመሆኑ መስካሪ የሚያሻ አይመስለንም። የወደመው ንብረት ከመቶ ሚሊዮን ብር ባላይ ሊደርስ እንደሚችል ቢገመትም ትክክለኛው ማስረጃ ግን ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በቅንጅት ተጣርቶ መቅረብ ይኖርበታል።

የጥፋት መልዕክተኞች የአላቸውን የሚዲያ ተቋም በመጠቀም ሕዝብ ቀስቅሰዋል በመባል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች፤ፍትሐዊ ምርመራ እንዲደረግባቸው፤ በተለይ ደግሞ የፓርቲ ዓባላት ያሉበት ከሆነ በሰላም ሳይሆን ሕዝብን ለአመጽ በማነሳሳት ሕገወጥ ተግባር እንዲፈጸም ተባባሪ በመሆናቸው፤ ለአገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ሰላም ሲባል፤ የፓርቲያቸው ሕጋዊነት እንዲሠረዝና መጭው ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስም በቁጥጥር ሥር እንዲቆዩ ማድረግ ብልህነት ነው።

የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲሥራ በብዙ ሊቃውንትና የፖለቲካ ጠበብት ቢመከርም ሕዝብ በራሱ ጊዜ እየተሻሻለ ይሄዳል በሚል ችላ በማለቱ ያስከተለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የከፋ ጥፋት ከመከተሉ በፊት ተገቢውን የማያወላውል የማረሚያ እርምጃ በአፋጣኝ ሊወስድ ይገባል እንላላን።

-//-

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share