ማላገጫው የመንግስት በጀት! – ዘብሔረ ባህር ዳር

የመንግስት ሰራተኛውና ማላገጫው በጀት/ከአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ውጭ ይመለከታል

42 ዓመቴ ነው፡፡ በመንግስት ሰራተኛነት ለ22 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ አገልግሎት ሰጭ ተቋም ላይ ሳለሁ ለ8 ዓመታት ፋታ የማይሰጥ ስራ ሰርቻለሁ፡፡ 14 ዓመታት ደግሞ በማላገጥ ያለቀ ዘመኔ ነው፡፡ ከገቢ አንፃር ሳየው ለ8 ዓመቱ የልጅነት ዘመኔ ከባድ ስራ ማካካሻ ነው፡፡

መንግስት የሲቪል ሰርቪሱን መለስ ብሎ ማየት አለበት፡፡ በመንግስት ሰራተኛው ላይ አዲስ ሪፎርም መስራት አለበት፡፡ ለመንግስት ሰራተኛው የሚመደብ የመንግስት በጀት ማላገጫ ከመሆን መዳን አለበት፡፡ ለዚህም ዋና ዋና ሶስት ምክንያቶች ተንተን አድርገን ስንመለከት፡-

ያልተመቻችሁ የመንግስት ሰራተኞች ቻሉት እውነታው ይህ ነው፡፡

  1. በአንድ ተቋም ላይ ስራው ከሚፈልገው ሰው በላይ መታጨቁ፤

ሲቪል ሰርቪሱ በእያንዳንዱ ሙያ በተናጠል የስራ ዝርዝርና እቅድ አዘጋጅቶ ለሰራተኛው ያቀርባል፡፡ ችግሩ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፡፡ ሲጀምር በዝርዝር የተቀመጡትን ስራዎች ለመስራት የሰራተኛው አቅም ምን ያክል ነው? በማይረባ የትምህርት ስርዓት ተጋፎ ድግሪ የያዘውና ስማቸውን እንኳን በውል ከማናውቃቸው የርቀት ዩኒቨርስቲዎች በተማሩት ሳይሆን በገዙት የድግሪ ወረቀት የሚመደቡ ሰራተኞች እንዴት ነው በዘርፉ በጣም የሰለጠኑ ፕሮፌሽናሎች የሚሰሩትን ስራ መስጠት ቀልድ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ዝርዝር ተግባራት ይዘለሉና አቅማቸው ብቻ የሚፈቅደውን የተወሰኑ ስራዎች ብቻ ተለምደው እነዚያ ብቻ እንደስራ ተቆጥረው በዚያው ይቀጥላል፡፡

ለምሳሌ፡- እኔ ባለሁበት ቢሮ በአንድ ቡድን ውስጥ 7 ባለሙያዎች/ሰራተኞች አለን፡፡ ጊዜ ደጉ የኮሮና ወረርሽኝ በሽታ መጣና ብዙው ሰው ቤት እንዲቀመጥና /ስራውን እንዲሰራ/ ተባለ፡፡ “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” ይላል ያገሬ ሰው፤ ከቤት ሆነው መስራቱ ይቅርና ሲደብራቸው እየመጡ ከመረበሽና ከተማዋን ሲያካልሉ ከመዋል ቢቆጠቡ ጥሩ ነው፡፡ ድሮም ለቡድኑ2 ሰው እንደሚበቃ ይሰማኝ ነበር፡፡ አንድም ስራ ሳናጎድል ግን 8 ሰዓት ሳንሰራ የክፍሉን ስራ በፍቅር በሰላም ሸፍነነው ሰንብተናል፡፡ ከተማው ለሚዞሩት ያው እኛ በሰራነው ደሞዝ እየተከፈላቸው፡፡ የነሱ መኖር በሌለና ባልተሰራ ስራ ሰውን ሲያጋጩ፣ ሲገመግሙና ለመሾም ሲሯሯጡ፣ በሰራተኛው እና ወደቢሮ ለጉዳይ በሚመጣ ሰው ላይ ብሮክራሲ ሲያበዙበት መዋል ነው፡፡

እኔ እንዳለሁበት ክፍል በቀን ከበዛ 2 ሰዓት ካለያ 30 ደቂቃ ነው ስራው የሚፈልገው፡፡ ቀሪ ሰዓቱን እንደቋሚ እስረኛ ታጉረህሲሰለችህ  ለሻይ ወጣ ስትል የሹመኞች የት ወጣህ የት ገባህ፣ ሹመኞችራሳቸው የማይሰሩትን በሰራኸው ስራ ላይ ህፀፅ ፈልገው ቁም ስቅልህን ሲያሳዩህበደንቆሮ ጨለማ ግምገማቸው ስትማረር፣ስትጣላ፣ ነገር ከወዲያ ወዲህ ሲመላለስ ስታይ ወይም ስታመላልስ፣ የነገር ቡድን ስትፈጥር ትውልና ከዛ የተረፈው ሰፊ ጊዜ ደግሞ ሶሻል ሚዲያው ላይ መጣድ ነው፡፡ ነገር ያማረው የብሔርናየጎሳ ነገር እንቅልፍ ያሳጣው ደግሞ መከረኛው ፌስ ቡክ ላይ ግደለው ቁረጠው ሲል ይውላል፡፡ አንድ ጉረቤቴና የስራ ባልደረባየ ወደስራ ለመሄድ ስንጠራራ እሱ እንደሚለው “ወደ ማንቦዛረጥ እንሂድ” ይላል፡፡ ሴቶቹ ደግሞ “ከቤት ስንውል የቤቱ ስራ ጭንቅ ነው የምናርፈው ከዚህ ነው” ይላሉ፡፡ ብዙዎቻችን የሰራነው ስራ ተሰራ አልተሰራ በሀገር ደረጃ የምናመጣው ጠብ የሚል ውጤት የለም፡፡ እንግዲህ ቀኑን ሙሉ ካለምንም ስራ ስናላግጥ ውድ ጊዜን ስንገድል እንውላለን፡፡ ደግነቱ የመንግስት ሰራተኛ ክፍያ ደስ አይልም እንጅ ከምር የዚችን ድሀ ሀገር በጀት መንግስት ላላገጠበት ጊዜአችን ይከፍለናል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦህዴድ አመራር በአዲስ አበባ ጉዳይ ሚስጥራዊ ስብሰባ አድርጎ ውሳኔ ማስተላለፉ ተሰማ!!

መንግስት ሆይ፡-

እባክህ በሰለጠኑ ሰዎች ጥናት አጥና፡፡ 8 ሰዓት የሚያሰራ ስራ መሆኑን አረጋግጥ፡፡ ለሙያው 8 ሰዓት ሙሉ የሚሰሩ በቂ ክፍያ ያላቸው በጣም ምርጥ የምትላቸውን ጥቂት ሰዎች ብቻ ቅጠር፡፡ የስራ ፈተና አንፃራዊ በሆነ በሚጠናና በሚረሳ ነገር ላይ አታድርግ፤ በዘመድ አዝማድ እንዳይሰራ ጥብቅ ቁጥጥር አድርግ፡፡ እኔን ጨምረህ ከ10 ዓመት በላይ ያገለገልን ሰዎች በጡረታ አባረን፡፡

  1. የፋይል እድሜቸው ጎልማሳ ሰዎቹና አስተሳሰባቸው ግን በጣም ያረጁ በበቂ እውቀት ያልተገነቡ መሆኑ፤

ሰው እድሜው ሲጨምር ሰውነቱ እየዛለ አህምሮው እየበሰለ ይሄዳል፡፡ ይህ የሚሆነው መጃጀት ላይ ከመድረሱ በፊት ነው፡፡ በደንብ የተማሩ ከሆኑና በጥብቅ ዲሲኘሊን ያደጉ ከሆነ ትልልቅ ሰዎች ከሀገር አልፎ የአለም ዋልታ ይሆናሉ፡፡ በእድሜ ትልቅ ስለሆኑ ብቻ ትልቅ ቦታ ማስቀመጥ ደግሞ ትልቅ ጥፋት ያደርሳል፡፡ ያው የሳጥናኤል ቦታም ትልቅ ነበር፡፡

የእድሜ ነገር ሲነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን አይሆንልንም፡፡ ብዙዎቻችን ህፃን መሆን ያምረናል፡፡ ምን ማማር ብቻ ህፃን ነንም እንላለን እንጅ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም የሚያሳፍሩ ገጠመኞች አሉኝ፡፡ የሆነ ጊዜ ቢሮው ኘሮፋይላችንን ለጠፈ፡፡ ሰዎች ምድር ተሰንጥቃ እንድትውጣቸው የፈለጉበት ጊዜ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- የሰትየዋ እድሜ 30 የአገልግሎት ዘመን 31፣ አስቡት ይች ሴትዮ ከመወለዷ 1 ዓመት በፊት ስራ ይዛለች፡፡ የሰውየው እድሜ 35 የአገልግሎት ዘመን 32፣ ይህ ሰውየ በ3 ዓመቱ ስራ ይዟል፡፡ ሌላው ሰውየው እድሜ 38 የአገልግሎት ዘመን 33፣ በአምስት ዓመቱ ስራ ይዟል፡፡ ይህ እንግዲህ በጣም ግርምትን ከፈጠሩና ሰውን ካስደነገጡት ውስጥ ነው የጠቀስኩላችሁ፡፡ ብዙው ሰው ግን ከ12-16 እድሜ ክልል ውስጥ እያለ የተቀጠረ መሆኑን አየን፡፡

 

የችግሩን ምንጭ በተቻለኝ ለማወቅ ሞክሬ ያገኘሁት ምላሽ የመጀመሪያ ፍላጎታቸው ተሎ ጥሮታ ላለመውጣት ነው፡፡ አሁን ላይ እነዚህ ሰዎች እንዲህ አርጅተው የፋይል እድሜቸው 55 አልሞላ ብሎአቸው በጣም እየተቸገሩ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት እንቢ አናረጅም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በጣም ያስቁኛል፡፡ ለባጅና በር ላይ ለሚለጠፍ የሚጠቀሙት ፎቶ በ70ዎቹ ዓ.ም ውስጥ የተነሱትን ነው፡፡ ከምር አይደለም ባለጉዳይ አብሬ የምሰራው እኔ እንኳን ይህ ሰው ማን ነው ብየ ጠይቄ አውቃለሁ፡፡ ማርጀታቸውን በተዓምር አይቀበሉም፡፡ ፀጉራቸው ላይ ነጩ እንዳይታይ ያለባቸው ድካም ለስራ ቢውል እንዴት ጥሩ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቅስቀሳው ተጠናክሮ ቀጥሏል -ፖሊስ እውቅና የተሰጠውን የሰላማዊ ሰልፍ የበራሪ ወረቀት ቅስቀሳ ለማስተጓጎል እየሞከረ ነው::

አለባበሳቸው ሁሉ ያሳፍረኛል፡፡ከ60-75 ዓመት የሚገመቱ ሲሆን ለስራ ጅንስ በስኒከር ጫማ ቢለብሱም ወንዶቹ ይሻላሉ፡፡ ሴቶቹ እንደልጅ ልጆቻቸው ይለብሳሉ፤ በዛ ግድንግድ ቦርጫቸው ላይ ታይት ሱሪ በቦዲ ይለብሳሉ፡፡ በጣም ነው የሚያሳቅቁት፤ የሚያሳፍሩትም፡፡ እንደዛ ሁነው ከነሱ በላይ ዘናጭ በአለም ላይ የለም እንደዚህ ነው የሚያስቡት፡፡ ማርጀትን አለመፈለግ፣ ተፈጥሮን አለመቀበል በራሱ መታመም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የኋላ ታሪካቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ የልጅነት እድሜአቸውን ተቆልፈው በድህነት ያሳለፉና በመካከለኛ የወጣትነት እድሜ ላይ ት/ቤት የገቡ ናቸው፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ ገጠመኝ ሁለት ጎልማሶችን አንዱ ሽማግሌ በነገር እየነካካ አጣላቸውና ሊደባደቡ ሲጋበዙ የሰውየውን ጠባይ እያወቁ ፀባቸው በመክረሩ ሲጨንቀኝ እየፈራሁ “ኧረ ትልቅ ሰው አይደለህ ተው በላቸው” ማለት እንደዛ ቀን ቀልቤ ተገፎ አያውቅም፡፡ “ትልቅ ትልቅ አትበይኝ ማን ነው ትልቅ”ብሎ ጠረንጴዛውን በቡጢ ሲነርተው በድንጋጤ ፀበኞች ጋብ ቢሉም የኔ ድንጋጤ ግን የተለየ ነው አልረሳውም፡፡እንግዲህ ቢሮዎች የተሞሉ በእነዚህ ሰዎች ነው፡፡ ስራ ከማጣትና ከማርጀት የማጣ ውጤት ነው፡፡ ጥቂቶች የጡረታ ዓመት እንዲደርስ በጉጉትና በድካም ውስጥ በመጠበቅ ዝም ብለው የሚኖሩ ሲሆን ብዙ ሽማግሌና አሮጊቶች ግን የቢሮውን ፀጥታና ሰላም ሲያደፈርሱ፣ ከነዛችው ጥቂት ስራ ሲያውኩ የሚውሉ ናቸው፡፡

መንግስት ሆይ፡-

እባክህ ባለጉዳይ ከመጉላላት ይድን ዘንድ፣ የመንግስት በጀትም ለሌላ ስራ ይውል ዘንድና ሽማግሌዎችም ከድካማቸው ያርፉ ዘንድጡረታ አስወጣቸው፡፡

  1. ወጣት በሚባለው እድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ደግሞ የሙያ ዲሲኘሊን የጎደላቸውና ግልብ በሆነ እውቀት የሚፎክሩ መሆናቸው፤

ወጣት ትኩስ ያልደከመ ሀይል አለው፡፡ ይህ ሀይል ስራ ላይ ሲውል ከፍተኛ ውጤት ማስማዝገብ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵይ በጣም ጥቂት ምርጥ ወጣቶች አሏት፡፡ በነሱ ከፍተኛ ትጋት ሀገር ውላ እያደረች ነው፡፡እንዳለመታደል የነዚህን ድንቅ ወጣቶችን ስራ በመጎተት የተሰሩትን በማፍረስ የሀገር ኢኮኖሚ እንዳያድግ የሚያደርጉ ወጣቶች ደግሞ አሉከእውቀት ይልቅ ፀብና ግርግር የሚወዱጠበንጃ፣ ቦንብ፣ ሜንጫና ገጀራ መያዝ የሚቀላቸውነው፡፡ ከነዚህ የተረፉት ደግሞ መንግስት የዜግነት እየከፈለ የሚያኖራቸው ወጣት የመንግስት ሰራተኞች ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሁመራ አቅራቢያ “ማይካድራ” በተባለ አካባቢ የህወሓት ልዩ ኃይል ባልታጠቁ ዜጎች ላይ አሰቃቂ እልቂት ፈፀመ

ሲቭል ሰርቪሱ ላይ ከምንም በላይ ከፍቶ የሚታየው የስነ ምግባር ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ነው ከታች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ሙስና የተስፋፋው፡፡ ምስኪኑን ሰራተኛ የስነ ምግባር መርሆችን ቢሮህ ውስጥ አለጠፍክም ብሎ ቁም ስቅሉን የሚያሳየው አለቃው የመንግስትን መሬት ሲቸበችብ የሚውል፣ የስንት ደሀ እንባን የሚያፈስ፣ ፍትህ የሚያጓድል ሳይሆን ፍትሀዊነትንየሚያጠፋ ህግ ጠላቱ የሆነበት ወጣት ነው፡፡ የቀበሌ/የነዋሪነት መታወቂያ፣ የሱካርና ከዘይት እደላ፣ቀበሌ መኖሪያ ቤት ወረፋ፣የወል መሬትን መሸንሸን፣ ካርታና ኘላን መስጠት፣ ኢንቨስትመን ቦታ ማፅደቅና ሌሎች ህገወጥ ስራዎች በብዛት የሚሰሩት በወጣት የመንግስት ሰራተኞች ነው፡፡ ይህ ዘረፋ አይደለም፤ ሀገር መግደል እንጅ፡፡

ይህ ሌብነት ትልቅ የአስተዳደግ የስነ ምግባር ችግር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በዚህ ውስጥ የሚገኙት የልጅነት ጊዜአቸውን በእረኝነትና ቤተሰብ እያላቸው በጎዳና ያሳለፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ የልጅነት ጊዜዎች ከቤተሰብ አይን ርቀህ ስትልው የምትሰራዉን መገመት አያቅትም፡፡ ስልጣኔን ፈፅሞ አያውቁትም፡፡ ይህን ስል ሁሉንም እረኞችና ጎዳና ላይ የሚውሉ ልጆች ማለቴ እንዳልሆነ ይመዝገብልኝ፡፡ እነዚህ ወጣቶች የትምህርት ዝግጅታቸው ስሙ ድግሪ ቢሆንም የብዙዎች የተገዛ ሲሆን የሌሎች ደግሞ ዩኒቨሪስቲዎች ጋፈው የሚያስመርቋቸው ናቸው፡፡ አይደለም እንግሊዝኛ አማረኛን በትክክል በትክክል ማንበብ የሚቸገሩ ናቸው፡፡ እንዴት እንደተመረቁ ሳስበው አይገባኝም፡፡ ከእውቀት የፀዱ እንዳይባሉ ለማሳመን የሚሆን ግልብ እውቀት አላቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በኔ እይታ የተስረከረከ ያልጠራ እውቀት ነው ያላቸው፡፡ ለምሳሌ ሌብነታቸውን ብቻ አነሳሁ እንጅ ሁሉንም የስነ ምግባር መርሆች ድፍጥጥ አድርገው የረገጡ ናቸው፡፡ ሌብነት በራሱ ሁሉንም ስነ ምግባር ያጠፋል፡፡ ሌባ የሆነ ሰው ሀላፊነት አይወጣም፣ ለህዝም አይቆረቆርም፤ ስልጣኑን ለግሉ መጠቀሚያ ያደርጋል እንደዚህ እያለ 12ቱን መርህ አፈር ደሜ ያስግጣቸዋል፡፡

ሌላው የመንግስት ሰራተኞች የስነ ምግባር ችግር አለባበሳቸው ነው፡፡ ገበያ ይሁን ወፍጮ ቤት፤ ስፖርት ቤት ይሁን መኖሪያ ቤት፤ ሰርግ ቤት ይሁን ሀዘን ቤት፣ ፀሎት ቤት ይሁን ዳንስ ቤት ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ ሁሉም ደስ ያለውን የተመቸውን ይለብሳል፡፡ ከኛ ቢሮ አንድ ሴት ብቻ አለች ሁሌም በዲሲኘሊን ሽክ ብላ በቢሮ አልባሳት የምትመጣ፡፡ ቢሮ ሀላፊዎችን ጨምሮ ሌሎቻችን እናሳፍራለን፡፡

መንግስት ሆይ፡-

እባክህ የድግሪ ወረቀት ሳይሆን ችሎታን መዝን፡፡ እንደባንክና ትልልቅ ካንፖኒዎች የቁጥጥር ስርዓት ዘርጋ፡፡የመንግስት ሰራተኞች አነጋገርና አለባበስ የቢሮ እንዲሆን አድርግ፡፡ለሌባ ለሚሰርቅ ሰው አትክፈል፡፡ ሰው በሰራው ልክ ብቻ ይከፈለው፡፡ አበቃሁ፡፡

 

ዘብሔረ ባህር ዳር

ከባህር ዳር

1 Comment

  1. You are stupid. There is no salary in Ethiopia. It is slavery and food for work. If you were laid salary you should be Woyane

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share