ምንድን ነው ሰው ማለት?? (ዘ-ጌርሣም)

ሰውን ሰው ያሰኘው
ከእንስሳት የለየው
ማሰብ መናገሩ
አዕምሮን በመግራት በዕውቀት መዳበሩ

ለምን ሰው ተባለ
ከአውሬ ካልተሻለ
ወንድም እያደነ
እህት እያፈነ

አህያው እንስሳው
እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለው
ነግ ለሚተኛበት ለማይቀርው አፈር
እንደ ዱር አራዊት ሲያሳድድ የሚያድር

ሌሎች አፈናቅሎ
ከኖሩበት ቦታ ከቀያቸው ነቅሎ
ከሆነ ለወገን አንገትን ማስደፊያ
ለታሪክ ጠባሳ ለጠላት መሳቂያ

በአዕምሮ ዳኛና በዓይን ምስክርነት
አንጥሮ ሲነገር ስለ ሰው ምንነት
ለህሊናው አድሮ እራሱን ሲሞግት
ሰው ማለት ያኔ ነው ሲመለስ ከጥፋት
ሰው ማለት ያኔ ነው ትንሽ ሰው ሰው ሲሸት

አዙሮ ለማየት ተስጥቶታል አንገት
ለማሰብ እንዲችል ታድሏል ጭንቅላት
ልብን ለአዘኔታ
እንዲያደርግ ይቅርታ
ሁሉም ተሟልቶለት
አንድም ሳይጎልበት
አልጋ በአልጋ ሆኖ ቢፈቀድለትም
በፍቅር መኖርን አላውቀበትም

ሰው ማለት ግብዝ ነው
ጊዜ የማይመክረው
እንደ ግዑዝ ድንጋይ እንደማይናገር
እንደ ወጀብ ነፋስ እንደማይበገር
ጥፋት በጥፋት ላይ እየጨመረበት
የሰውነት ክብርን ሚዛኗን አጠፋት

ሰው ማለት ያኔ ነው እራሱን ሲሞግት
ሰው ማለት ያኔ ነው ሲመለስ ከጥፋት
ሰው ማለት ያኔ ነው ትንሽ ሰው ሰው ሲሸት
ካለፈው ተምሮ በራስ ሞጋችነት ራሱን ሲዳኛት

አለበለዚያማ ማስተዋል አቅቶት
የሰውነት ዋጋን (value) መቀበል ተስኖት
መጨመር ካማረው በጥፋት ላይ ትፋት
መመደብ ይከብዳል ሰውን በሰውነት

ሰው ማለት ምንድን ነው
እስኪ የገባችሁ ንገሩኝ ልወቀው
ሊሆን ስለሚችል ለኔ ያልተረዳኝ
ጥያቄየን ላቅርብ ካለ የሚነግረኝ

ምንድን ነው ሰው ማለት ??
እኔ ያላወቅሁት !!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share