ሰማይ ተቀደደ ቢሉት ሽማግሌ ይሰፋዋል ይላሉ አበው – አማኑኤል ታደሰ (ከድሬዳዋ)

በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ይዘን የቆየነው ማህበራዊ መሠረታችን አንዱ ለሀገር ሽማግሌዎች የምንሰጠው ስፍራ ነው።የሀገሬው ህዝብ ከትንሹ የግለሰብ እና የቤተሰብ ግጭት ጀምሮ እስከ ትላልቅ ህብተረሰባዊ ጉዳዮች ድረስ በሽምግልና የመፍታት ባህልን ያዳበረ ትልቅ ህዝብ ነው። የተለያየ ባህል፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖትና የአኗኗር ዘይቤዎች ልዩነት ቢኖረውም እንኳን ይህ ህዝብ በመሀከሉ ለሚፈጠሩ ችግሮችና ግጭቶች ሽምግልናን እሴቱ አድርጎ ለዘመናት ኖሯል ዛሬም እየኖረ ነው። የሀገር ሽማግሌዎች የተጣላን ያስታርቃሉ፣ የተጣመመን በጥበበብ ያቃናሉ፣ የጎደለን አለስስት ይሞላሉ:: በሰዎች እና በህዝቦች መሀከል የተፈጠረን ቅራኔ ለመፍታትና ለማጥበብ ከሚደረግ ጥረት ባሻገር ሽምግልናን በአንድ ሀገር ውስጥ በሚኖሩ የአካባቢ ነገስታት መሀከል የተፈጠረን የጥቅምና የስልጣን ሽኩቻን ለማርገብ የምንጠቀምበት መሳሪያም ሆኖ አገልግሏል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገር ሽማግሌዎች ያለው ቦታ በመንግስታትና በዘመን መቀያየር ገፅ ውስጥ የማይቀየር ዘመን ተሻጋሪ ሀብት ነው ምንም እንኳን ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ የሽምግልናን እሴት በውል የሸረሸረ ስርዓት ቢኖረንም፡፡ ለዚህ ማሳያ የ97 ምርጫን ተከትሎ የቅንጅት አመራሮችን ምርጫ ካጭበረበረው መንግስት ጋር አሳታርቃለው ብሎ ትያቲር የሰራብንን የህወሓት-ኢህአዴግን የሽምግልና ድርሰት ወደኃላ መለስ ብሎ መታዘብ ብቻ በቂ ነው።

መንግስት የሀገራችንን የሽምግልና እሴት በውል ቢጠቀም ኖሮ አሁን በየአካባቢው የምናያቸው ስርዓት አልበኝነትና መረን የለቀቁ ግድያዎች እና ግጭቶች ባልተመለከትን ነበር። ዳሩ ግን ሽምግልናን ለዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን በዘላቂነት የመጠቀም ባህላችንን ቁልቁል እያወረድን የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር በኃላፊነት ሰምቶ ግብረገብነትን በቅጡ ተምሮ ሀገርን የሚያድን ዘመነኛ ትውልድ የመፍጠር አቅማችን ውስን እየሆነ መጥቷል፡፡
ለመንደርደሪያ ይህን ያህል ከለፈፍን ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመጣ ህወሓት ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር (ከብልፅግና) ቅጥ ያጣ ገመድ ጉተታው ውስጥ ናት። በዚህ የገመድ ጉተታ ውስጥ ትልቁ ገፈት ቀማሽ የሚሆነው ሀገርና ህዝቧ ነው በተለይ ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ። የህወሓት ጡረተኞች ከፕላኔት ሆቴል ሆነው ማዕከላዊ መንግስቱ ደግሞ ከ4-ኪሎም እንበለው ከሸገር የቀራቸው ጦር መሳሳብ እንጂ የቃላትና የፕሮፖጋንዳ ቃታቸውን መሳብ ከጀመሩ ድፍን ሁለት ዓመት አለፋቸው፡፡ ሁለቱም በመሀከላቸው ያለችውን ሀገር አስበው የሚገዙትን የህዝብ ልብ ትርታንም እንዲሁ አድምጠው ወደ መሀል መንገድ ለመምጣት ሲሳናቸው እየታዘብን ነው።

ይህን የተረዱት የሀገር ሽማግሌዎች ከፖለቲካዊ ሽኩቻ የህዝብ አብሮነት፣ ከስልጣን የሀገር ህልውና ይቀድማል ብለው በራስ ተነሳሽነት ትግራይ ክልል ድረስ ሄደው የሰላምና የእርቅ ሂደት እንዲከናወን ተማፅኖ ማቅረባቸውን ሰምተናል። እዚህ-ጋ 52 ልዑካንን የያዘው የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን በራስ ተነሳሽነት ወደ ትግራይ እንደሄዱ ነው በውል የሰማነው፡፡ ነገር ግን ማዕከላዊ መንግስቱ ወደማይሆን ነገር ውስጥ ከክልሉ መንግስት ማለትም ከህወሓት ጋር ከመግባታቸው በፊት የሀገሬው ህዝብ ቦታ በሚሰጠው የሽምግልና ሂደት ዘላቂ መፍትሔ ቢመጣ ብሎ አስቦ ወደ መቀሌ የላኩ እንጂ ታዬ ደንዳዓ እና አዲሱ አረጋ እንደነገሩን ብልፅግና ሽምግልና አላከም የሚል ዲስኩር ብዙም ምቾት አልሰጠኝም። በእርግጥ መሰረታዊው ጉዳይ ማንም ይላከው ማን የሀገር ሽማግሌዎቹ ሀገርንና ህዝብን የማዳን ሚናን ለመጫወት ወደ መቀሌ መሄዳቸው በትልቁ ያውም በደማቁ የወርቅ ብዕር የሚፃፍላቸው ሀገራዊ ጥረት ነው፡፡ ጥረታቸውም ፍሬ እንዲያፈራላቸው ምኞቴ ነው፡፡

በግሌ ሽምግልናው ለህወሓት ተጨማሪ ዕድልን ይዞ የመምጣት ሀይል አለው በስርዓቱ ከተጠቀመችበት። በውል ሳትጠቀም የሽማግሌዎቹን ሚና እንደ እርባና ቢስ ቆጥራ የምትዘልቅ ከሆነ ዕዳው ለራሷ ነው። የጠ/ሚኔስቴር አብይ አህመድ ለሽምግልና ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ለማመን አቀበት መውጣት አይጠይቅም፡፡ እንደውም የሳቸው ለሽምግልና ያላቸው አተያይ አንድ ሀገርኛ አባባል ያስታውሰኛል፡፡ አበውና እመው “አማካሪ የሌው ንጉስ ያለ አንድ ዓመት አይንገስ” ይላሉ ይህ ማለት ሽማግሌ ሳይዙ ሀገር ማስተዳደር አይቻልም እንደማለት ነው፡፡ በሽምግልና የማይፈታ ህፀፅ የለም ማለትም “ሰማይ ተቀደደ ቢሉት ሽማግሌ ይሰፋዋል” እንደሚባለው ነባራዊ ሁነት ማለት ነው፡፡ ጠ/ሚው በዚህ ሀገርኛ ብሂል መሰለኝ ከቃላት ልመና ተሻግረው የሀገሬው ህዝብ በሚያከብረው ሽምግልና ከትህነግ-ህወሓት ጋር ያላቸውን ልዩነት ለመፍታት ያሰቡት፡፡ እዚህጋ መታሰብ ያለበት ሁነት ሽምግልናው በፍቅርና ይቅርታ ማዕከላዊ መንግስቱን ከህወሓት ሰዎች የማስታረቅ ትልምን የያዘ ነው በመሠረታዊነት ደግሞ ህዝቡን ከተጋረጠበት አደጋ ለመጠበቅ ያለመ ነው፡፡ የዚህ የዕርቅ ሂደት በ4 ኪሎ ሰዎች በህወሓት ላይ የተሳበች የመጨረሻዋ የሰላም አማራጭ ካርድ ተደርጋ መወሰድ ይቻላል፡፡ ይህን አማራጭ በእርግጥ የህወሓት ጡረተኞች ብሎም ዲጂታል ወያኔዎች ደጅ እንደተጠኑ እንደተለመኑ አድርገው እንደሚያዩት እና ለእርቅም አላስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች እንደሚያስቀምጡ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህም የህወሓት ሰዎችን በእርቁ ጉዳይ የሰጡትን ምላሽ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ህወሓት ይህን የሽምግልና ሂደት አጣጥሎና ውድቅ አድርጎ በለመደው የራሱ ጎዳና መጓዝን ከመረጠ ማዕከላዊ መንግስቱ ተመጣጣኝ ሀይል የመጠቀም መብቱን secure ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ለጥቆም ህወሓት ለምሳ ያሰቡትን ሀገር የመመስረት ትልማቸውን ተነጥቀው ቁርስ ላይ በማዕከላዊ መንግስቱ ተበልተው ከክልሉ መንግስት መንበሩን ይለቃሉ፡፡ ሲሰልስም ግብዓተ-መሬታቸው አለቀባሪ ለትግል ወጣንበት ባሉት የደደቢት በረሀ ይፈጠማል ማለት ነው፡፡

በነገራችን ላይ የሽምግልና ሂደቱ ለድርድር ማቅረብ የሌለበት መሠረታዊ ነገር ቢኖር የፍትህና የተጠያቂነት ጉዳዮችን ነው፡፡ በተለይ አሰቃቂ የሰብዓዊ የመብት ጥሰትን በዜጎች ላይ ባለፉት 28 ዓመታት ያደረሱ የህወሓት ሰዎችን በይቅርታ ማለፍ ለብሔራዊ አንድነታችንና ለአብሮነታችን የሚኖረው ሚና እጅጉን ያነሰ ነው፡፡ ህወሓት ደግሞ አንዱ መደራደሪያው የሚሆነው በማዕከላዊ መንግስቱ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ስር ያልዋሉ የቀድሞ የደህንነት ሰዎች እንደ ጌታቸው አሰፋ ያሉ ሰዎችን ከተጠያቂነት ማዳን አንዱ ነው፡፡ ይህን በመደራደሪያነት ለእርቅ መቀበል በሰብዓዊ የመብት ጥሰት የተጎዱትን ዜጎች ቁስል ላይ እሳት እንደመስደድ ነው የሚቆጠረው፡፡ ስለሆነም ፌዴራል መንግስቱ በእነዚህ ጉዳች ላይ ከህወሓት ጋር ለድርድር መቅረብ ማለት ከሰይጣን ጋር በገሀነም ለመጫወት ትኬት እንደመቁረጥ ነው ሊወሰደው የሚገባው፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.