“ማየት መብላት አይደለም “ Seeing is not eating – ከመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ጥያቄ አለኝ

ዛፍን ዛፍ ብሎ በወል ሥሙ፣ ዘረኛው ሲጠራ
የራሱን የሰው ሥም ግን ለምን፣በጎሳው ተጠራ?
የአፍሪካ ሀገር ሁሉ ፣ሲቋቋም መንግሥቱ
ተብሎ እኮ አይደለም፣ ኩኩዩ ፣ሲኋሊ፣ቱትሲ ፣ ሁቱ…
ለምን ተሰረዘ፣የኢትዮጵያዊው ፣ኢትዮጵያዊነቱ ?
ለምንድነው የሚጠራው በነገድ ጥቂቱ?
ተክዶ አይደለም ወይ ኢትዮጵያዊነቱ?
አማራ፣ኦሮሞ፣ትግሬ፣ሲዳማ… ክልል ነህ መባሉ
ኢትዮጵያን አሶጥቶ ፣ ዘርን በልቡ ለምንድነው መትከሉ???
ለምንድነው አልኩኝ በምን ምክንያት
የሰው ልጅ በዘሩ የሚጠራበት?
ለምንድነው አልኩኝ በምን ምክንያት?
ኢትዮጵያዊው በኢትዮጵያዊነቱ የማይኮራበት።
ለምንድነው አልኩኝ በምን ምክንያት?
ሀገሬ የዋለችው፣ለቤተ ሙከራ፣ላብራቶሪነት።…
ለምንድነው አልኩኝ በምን ምክንያት?
ጥቂቶች በቋንቋ የሚነግዱት።
አማራ፣ኦሮሞ፣ትግሬ ና …ብቻ በማለት።
ለምንድነው 70 የሰው ቋንቋን…መብት ማሳጣት???
ለምንድነው አልኩኝ በምን ምክንያት ?
ጥቂቶች በቋንቋ ተናጋሪ ብዛት የሚነግሱበት ?
ከቶ ለምንድ ነው ፣ የትላንቱ ታሪክ ዛሬ መረሳቱ ?
ተቀምቶ አልነበር ወይ የዜጋው፣ሀብትና ህይወቱ።
እንዴት ከቶ ይረሳል የትላንትናው፤
ጥቂቶች በህዝብ ሥም ለአመታት ነግደው
ዞር እንዳላሉ ብዙ ዶላር አፍሰው።
ከቶ እንዴት ይረሳል ፣ያ የሰሩት ግፍ
ጎሣን መትከላቸው፣ ከጫፍ እሥከ ጫፍ።
ያ የነገድ ተክል ነው አድጎ ጥላቻን ያፈራ
ያንንም ሳያጣጥም በልቶ ነው …
ክልል ካልሆንኩ ያለው ሁሉም በየተራ።
ታዲያ ለምንድነው ዛሬ ያ ሁሉ ግፍ መረሳቱ
አመድ ላይ ጭቃላይ ዳግም፣ መጣሉ የሰው ሰውነቱ?
ትላንት በቋንቋ ነጋሹ፣ ሰውን ባለማክበሩ
ቋንቋ በመሆኑ የ27 ዓመት የቡድን መዝሙሩ
ሆኖ እንደነበር ለህሊና ቢሶች የብዝበዛ መሣሪያ
ደሃውን ህዝብ ግን የበለጠ መድኸያ።
ዛሬሥ ለምንድ ነው በለውጥ ሰዓት
በቋንቋ፣በነገድ፣በጎሣ የሚሸቅጡት።
ሰው አይዶለም ወይ፣የአዳም ምንነት
ህይዋን አይደለች ወይ የሁላችን እናት?!

 

በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግስታት ታሪክ እስከዛሬ የተፈረመ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ የሚሆን የህግ ድጋፍ ያለው ውል በወረቀት ሰፍሮ አይገኝም፡፡ወንዙን በጋራ ለመጠቀም የሚስችል ሥምምነቶች ግን ተደርገዋል፡፡እነዚህ ስምምንቶች ግን አስገዳጅ ህግ በመሆኑ ተፈፃሚ እንዳልሆኑ ይታወቃል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢሕአዴግ የሚወገድ እንጂ የሚጠገን ስርዓት አይደለም! - አገሬ አዲስ

የአባይ ወንዝ ውሃን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ጠንካራ ሥምምነት እንኳን በግብፅ፣በሱዳን፤በውሃ ሰጪዋ በኢትዮጵያ መካከል  የማድረግ እንቅሥቃሴ የተጀመረው ከህዳሴ ግድብ በኋላ ነው፡፡ሥምምነት እንደአስገዳጅ ህግ የሚታየው ዓለም አቀፍ ህጎችን አገናዝቦ የተፃፈ ከሆነ ና በዚህ ውል ላይ ኢትዮጵያ ከፈረመች ብቻ ነው፡፡

ይኽም ማለት፣ውሃውን በጋራ ለመጠቀም፣ሁሉንም ተደራዳሪ ወጎኖች የማያስቀይም እና ተጠቃሚ የሚያደርግ ድርድር ሲሆን ብቻ ነው፡፡አንድ ውል ተቀባይነት የሚያገኘው። ውሉ ” እንደውጫሌ ውል” በሸፍጥ የተሞላ አንድ አንቀፅ ወይም ሐረግ ወየም ቃል ከለበት ግን ተቀባይነት አያገኝም።እንዲህ አይነቱ  ሸፍጥ እንዳይኖር እያንዳንዷ አንቀፅ፣ሐረግና ቃላት ልትፈተሽ ይገባታል።ዛሬ እየተደራደርን ያለነው  የዓፄ ሚኒልክ ዓይነት ውል አይደለም እና!!

ዓፄ ምኒልክ “የአባይን ተፈጥሯዊ ፍስት የሚያስተጓጉል ተግባር አልፈፅምም ባለው የሥምምነት ፊርማቸውን በዛ ኋላ ቀሩ ዘመን ያደረጉት ሥምምነቱ ከአለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ህግ አንፃር ፍትሃዊ እና አሥገዳጅነት እንደሌለው አውቀው እንደሆነ ባናውቅም፣ሌሎች የልማት ሥራዎች ለመትጋት ሠላም በእጅጉ አሥፈላጊ በመሆኑ እና በህዝብ ቁጥራችንም አነሥተኛ በመሆናችን ምናልባትም ከ17 ሚሊዮን የልዘለለን ነበርን እና ቅድሚያ ለሚሠጠው ቅድሚያ በመሥጠት በሥራ በመጠመዳቸው እንጂ፣እውቀቱ፣ሀብቱና የሰው ኃይሉ ቢኖራቸው ኖሮ እንደዛሬው ዓይነት ግዝፉ የኃይል ማመንጫ ሊገነቡ አይችሉም ማለት የዋህነት ነው።

ምኒልክ ” በአባይና በባሮ ወንዝ ላይ ከእንግሊዝዋ ንግስት ጋር በ1902 እኤአ ያደረጉት ስምምነት ከቅኝ ገዢዋ ከታላቋ ብሪትን ጋራ ያደረጉት ውል በመሆኑ ለዛሬ የግብፅ መከራከሪያ ከቶም ለመሆኑ አይችልም።(አንዳንዶች  ያልተገባ ና ከቶም የማይመጥናቸው ሥም ሊሠጣቸው ባልደፈሩ ነበር።)

ሥምምነቱ በዋነኛ ባለቤቷ በግብፅ መንግሥት እና በኢትዮጵያ መንግስት የለመፈረሙ እየታወቀ ይህንን ሥምምነት እንደመከራከሪያ ግብፆች ያቀርቡ እነደነበርም ይታወቃል፡፡ሥምምነቱን ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ፤ከኩሩና ጀግና ህዝብ ባለቤቷ ከኢትዮጵያ ጋር ማድረጓ እየታወቀ ይህንን እንደመደራደሪያ ሁሌም መቁጠራቸው ና ማንሳታቸው ያስገርማል፡፡እንደሚታወቀው ግብፅ ከ1882 እስከ 1952 እኤአ ለ70 ዓመት በእንግሊዝ ቅኝ የምትገዛ ሀገር ነበረች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኩሬአውያን - ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ታላቋ ብሪትን ፣ታላቁን የኢትዮጵያን መሪ ንጉስ ምኒልክ ፣ለልማት ያላቸውን ተነሳሽነት በማሥተዋል፣ በግብፅ ምድር በኢትዮጵያ አፈር እና ውሃ የጀመሩት እጅግ ሰፊ የመስኖ ልማት እዳይስተጓጎልባቸው፣ አሥበው ያደረጉት ስምምነት ፣ዛሬ” የእኛ ሉአላዊ ሀገር ፣የግብፅ ስምምነት ነው።” ለማለት  መድፈር በራሱ ሥህተት ነው፡፡

ዛሬ ግብፆች በአባይ ላይ ለምንሠራው ልማት እውቅና ለመሥጠት እየተስማማች ነው ፡፡በቴክኒካል ጉዳይም ተስማምተናል እየተባለ ነው፡፡በበኩሌ ግብፆች ያሰቡት አንድ ድብቅ አጀንዳ እንዳላቸው አስባለሁ፡፡ድብቁ አጀንዳቸውን የሚመዙበት ሰዓት ጊዜና ቦታ እንዳለም ሥድሥተኛው ህዋሴ ይነግረኛል።ለማንኛውም በሀገር ፍቅሩ የሚያኮራን እና በቋንቋ ለታመሠችው ኢትዮጵያችን ተሥፋ የሆናትን መከላከያ ሠራዊታችንን ዕድሜና ጤና እንዲሠጠው የእናት ሀገራችሁ አፍቃሪዎች ፀልዩ።”እናት ሀገር ኢትዮጵያ ፣የእኛ መመኪያ እያላችሁ ዘምሩ።በቋንቋ ጉያ መሽጋችሁ፣ለብዝበዛ ያለመሠለፋችሁንም በተግባር አሳዩ።

እውነት፣እውነት እላችኋለሁ  ውስጥ አዋቂዎቻቸው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ፍፁም የሆነ ውሥጣዊ አንድነት እና ለማመን የሚከብድ  ሀገራዊ  ፍቅር  እንዳለው ለግብፆች ሹክ ባይሏቸው ኖሮ ፣እንዲህ ለመደራደር አይጣደፉም ነበር።

በልማት ፣ በትምህርት፣በቴክኖሎጂ ፣በንቃተ ህሊና ኋላ በቀረቸው አፍሪካ ፣የእያንዳንዱ ሀገር መንግስት ጥንካሬ ና ዘላቂነት  የሚረጋገጠው ፣በጠንካራ ዲሲፒሊን በተገነባ ፣የሀገር ፍቅር ሥሜት በሚያንገበግበው ወታደሩ እንደሆነ አሥባችኋል?

ግብፅን ጨምራችሁ “የአፍሪካ ጠንካራ መንግሥት የቱነው?” ብትባሉ መልሱ “በሚለቴሪ ሳይንስ የዳበረ እወቀትና ክህሎት ያለው፣ሀገራዊ ፍቅሩ እጅግ ብርቱ የሆነ፣ጠንካራ ዲሲፕሊን እና አመዛዛኝ ህሊና ያለው፣ሠራዊቱን እንደራሱ ቤተሠብ የሚያይ በህዝብ ተወዳጅ የሆነ ፣መከላከያ ሰራዊት የገነባ ነው።” መልሳችሁ፡፡ኢትዮጵያ ዛሬ ከቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ትልቅ ትምህርት የወሰደ ሣራዊት እንዳላት መታወቅ ይኖርባታል፡፡የመሪው የዶክተር አብይ ትህትና ከአሥተዳደጋቸው በዘለለ ከወታደራዊ ሥነስርዓት የመነጨ እነደሆነም አሥባለሁ።

በሚሊተሪ ሳይንሥ፣በሥልጣን ተዋረድ፣ መከባበርና የተሰጠን ግዳጅ ያለአንዳች ማመንታት መፈፀም ግዴታ ነው፡፡ይኽ የወታደራዊ ሣይንሥ ሀሁ በሚገባ በሠራዊታችን ውሥጥ በመሥረፁ ፣ይኽቺ ሀገር ልትበታተን ከቶም   እንደማትችል  የግብፅ መንግሥት የተገነዘበ ይመሥለኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የወልቃይትና ያለውደታቸው ወደ ትግራይ የተጠቃለሉ ወረዳዎች ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ህወሃት ከሥልጣን ሲወገድ ብቻ ነው!" - አርበኞች ግንቦት 7

ይህንን ከውሥጥ ምንጩ ተረድቶም  ወደ ድርድር የተመለሠ ይመሥላል። ብዬም አስባለሁ፡፡ይሁን እንጂ በቀጣይ በሀገር ውስጥ በህቡ በዶላር ያሥታጠቃቸው ግለሰቧች ለጥፋት የተቀበሉትን ብር ፣መበተን መጀመራቸው እንደማይቀር ጠርጥሩ።

የግብፆች የመጨረሻው ካርድ በሀገር ውሥጥ የሚያሠማሯቸው  ህቡ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ኃይሎች እንደሆኑም ገምቱ። ይህንን ግምትና ጥርጣሬያችሁን በመረጃና በማሥረጃ ሣይረፍድ በሣይንሳዋ የሥለለ መንገድ አረጋግጦ መንግሥት በጊዜ   ካልተቆጣጠረው ፣ እነዚህ ሆዳቸው አምላካቸው የሆነ፣ ኢትዮጵያን ባያፈርሷትም ሰላሞን ማናጋታቸው ግን እርግጥ ይሆናል።

ዛሬና አሁን እንደልብ እንዳይቀሳቀሱ ያገዳቸውም  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ እንደሆነ ይታወቃል።ዛሬ በየክልሉ  ኢትዮጵያ ሀገሬ፣መመኪያ ክብሬ…የሚል ለሀገሩ ደስ እያለው ለመሰዋትነት ቆርጦ የተነሳ ሠራዊት አለ።ቋንቋ ሳይሆን ዜጋ መሆን የሚያኳራው እና ሁሉም እናቶች የእርሱም እናት እንደሆኑ የሚቆጥር፣አባቶችም እንዲሁ የሁሉም አባት እንደሆኑ የሚገነዘብ ፣ቆዳ ማዋደድን የሚፀየፍ ሠራዊት በእያንዳንዱ ከተማና ገጠር በይኖር ኖሮ ፣ ዛሬም በኢትዮጵያ ውሥጥ ከኮሮና የባሠ ዘረኝነት ይሥተዋል ነበር።

በህቡ የሚቀሳቀሱት ህሊና ቢሥ ቅጥረኞቹ በዚህ ወቅት የተሳጣቸውን ዶላር ሊጠቀሙበት ይችሉ ነበር።ሊጠቀሙ ባለመቻላቸው ጭንቅ ይዟቸዋል።ይሁን እንጂ በትንሽ ፣በትንሹ ሚሊዮን ብሮችን ለሥራ አጡ በመበተን በቋንቋ ሥም ሀገር ለመበጥበጥ የህቡ እንቅስቃሴ እንደሚጀምሩ  የሚደርጉት የሾርኒ ቅስቀሳ ይመሰክራል፡፡ መቼም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ጡት የሚጠባ ህፃን ጭምር “በሌለ፣ሁሉን አቀፍ ጭቆና”ህዝቡ ለመሥዋትነት ተዘጋጅቷል ብሎ  ህዝብን በመናቅ ፣በህዝብ ሥም “ቡከን ጦር አውርድ”(እንደ ዓፄ ልብነድንግል) ማለት ከጥጋብ  የዘለለ ትርጉም አይሰጠውም።

ደግሞም ከዚህ ቅጥፈት ተነሥተን፣ ሥለ ሃምሳ ሚሊዮን ህዝብ ሲያወሩ፣ሥለ 50 ሚሊዮን ዶላር የጥፋት በጀት የሚያወሩ ይመሥለናል። ይህ ጥርጣሪያችን እውነት ቢሆን እንኳን  መመኪያችን የሆነው ፣የነፃነታችን ዋሥትና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ነውና ኢትዮጵያን ለማፍረሥ የሚዶልቱና የሚያሴሩ ይፈራርሳሉ እንጂ ኢትዮጵያ ከቶም አትፈርሥም ።

“ኢትዮጵያ  በውድ ልጆቿ መሥዋዕትነት ለዘለአለም  ታፍራና ተከብራ ትኖራለች።”

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.