የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብና የፖሊቲካ ድርጅቶች (የግል አስተያየት) – ባይሳ ዋቅ-ወያ

የሕወሓት ባልታሰበ ቀንና አኳኋን መንበረ ሥልጣኑን ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባንም መልቀቁ ቅጽበታዊ እንጂ ዘላቂ እፎይታ ሊያጎናጽፈን አልቻለም። አዲሱ አመራር ቃል የገባልንና በተግባር የተረጎመውን አንጻራዊ ነጻነትና ሰላም በደንብ ሳናጣጥም “ጥያቄያችን አልተመለሰልንም” የሚል የተቃውሞ ድምጽ ከያቅጣጫው ተሰማ። በሌላ ቡድን መተካታቸው ያናደዳቸው የሕወሓት ኤሊቶች “የዓቢይ መንግሥት ሆን ብሎ የትግራይን ሕዝብ እያጠቃ ነው” ብለው ስሞታ ማቅረብ ጀመሩ። ታምቆ የነበረው “የማንነት” እና “የክልል ምሥረታ ጥያቄ” በየቀኑ ዓቢይ ጉዳይ እየሆነ መጣ። እስከ ዛሬም “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያልን በየዋህነት አገራችንን የምንታደጋት መስሎን ለኢትዮጵያ ኅልውና ስንታገል መኖራችን ሕዝባችንን ከመፈናቀል ከመገደልና ከመገለል ስላላዳነ እኛም እንደ ሌሎቹ ብሔሮች በመጀመርያ ደረጃ ለብሔራችን መታገል አለብን” ብለው አዳዲስ የአማራ ብሔር “ተወካይ” ነን ባይ ድርጅቶች ብቅ ብቅ አሉ። ይህ ሁሉ አበቃ ብሎ፣ እነቅማንትና አገውን የመሳሰሉ ሕዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶች ደግሞ “ድሮም አማራው በግድ አማሮች ናችሁ ብሎን ነው እንጂ እኛ የራሳችን ቋንቋና ባሕል ያለን የኩሽ ሕዝቦች ነንና የተለየ ማንነታችን ይታወቅልን” ብለው የሌሎች ብሔርተኛ ድርጅቶችን ካምፕ ተቀላቀሉ።

እነዚህን ሁሉ የብሔር ድርጅቶችና አክቲቪስቶችን የሚያገናኛቸው የአሰተሳሰብ ድልድይ፣ ያሁኑን መንግሥት በጅምላ፣ ዓቢይን ደግሞ በግል መጥላት ይመስለኛል። ሁላቸውም ዓቢይን የሚጠሉበት የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። የአማራው አክቲቪስት “ዓቢይ በስውር ከኦነግ ጋር ይሠራል፣ የሚያስቀድመውም የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ብቻ ነው፣ ኦሮሞውንም ባለተራ አደረገ” ብሎ ሲከሠው፣ ኦሮሞዎች ደግሞ “ዓቢይ የነፍጠኛውን ሥርዓት መልሶ ሊያመጣብን እየሞከረ ነው” ይሉታል። የትግራይ ፖሊቲከኞች ደግሞ “ዓቢይ ሆን ብሎ በትግራይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በክልሉ ሕዝብ ላይ የማግለል እርምጃ እየወሰደ ነው” የሚል ስሞታ ያቀርባሉ። በአጭሩ፣ በዶ/ር ዓቢይ የሚመራው መንግሥት የሶስቱም ትላልቅ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጥቅም አይጠብቅም / አያስጠብቅም የሚል ነው ስሞታቸው። ዓቢይን መጥላት የግለሰቦች ወይም የቡድኖች ህጋዊም ሰብዓዊም መብት ቢሆንም፣ በዚህ ጥላቻ ላይ ተመሥርቶ ማንም ሳይወክላቸው በሕዝቡ ስም “የየራሳቸውን ጥያቄ” እያነሱ ለምሳሌ ሰሞኑን አንድ ግለሰብ በአይጋ ፎረም ላይ እንደ ጻፈው፣ “ያገር አንድነት ለዘላለም የሚታሠር ጌጥ ወይም ክታብ አይደለም፣ ለሁላችን ከጠቀምን እንይዘዋለን፣ ላንድ ወገን ብቻ የሚያገለግል ከሆነ ደግሞ አውልቀን እንወረውረዋለን፣ በስመ አንድነት ከእንግዲህ የሚታለል ወገን የለም” ብሎ በመወትወት የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ብሎም የወደፊት የአብሮነት ዕድላቸውን ጥያቄ ውስጥ ለመክተት መሞከር ግን ትክክለኛ አካሄድ አይመስለኝም።

በመሠረቱ ማንኛውም ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ በ1966 ዓ/ም በጸደቁት የተመድ የዓለም ዓቀፍ ቃል ኪዳን (Covenants) እና በፌዴራል ኢትዮጵያም ሕገ መንግሥት ስለተደነገገ፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ አንስተው ተግባራዊ እንዲሆንላቸው መወትወታቸው መብታቸው ነው። የሚገርመው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለ በሩብ ምዕተ ዓመት ውስጥ አንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቀጽ 39ን ጠቅሶ ከኢትዮጵያ ተገንጥዬ የራሴን ነጻ አገር ልመሥርት ያለ አልነበረም። ይህ ዝም ብሎ በአጋጣሚ የሆነ አይመስለኝም። ያለፉት መቶ ዓመታት፣ በሌሎች አገራት እንደ ተከሰተው አንዱ ብሔር በሌላው ውስጥ ቀልጦ ለምሳሌ እንደ ጣሊያንና ፈረንሳይ አንድ ሕዝብ መፍጠር ባንችልም፣ ሕዝቡ የራሱን ቋንቋና ባሕል እንደ ጠበቀ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ግን በተቻለ መጠን ለመመሳጠር፣ ካልሆነም ደግሞ ተከባብሮ በሰላም እንደ ጥሩ ጎረቤት አብሮ መኖር መቻሉን የሚያሳይ ነው። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአማርኛ ተናጋሪዎች ሁኔታ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው።

ወያኔ የፊታውራሪነት ቦታውን እስከ ለቀቀበት ቀን ድረስ ማለትም ለኸያ ሰባት ዓመታት በወረቀት ደረጃ ነው እንጂ ዘጠኙንም ክልሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተግባር ደረጃ ሲያስተዳድሩ የነበሩት የሕወሓት አባላት ወይም ደጋፊዎች ስለሆኑ “ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው” ተጠብቆላቸው ነበር ማለት አይቻልም። ያሁኑ ቡድን ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ግን ክልሎቹን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተዳድሩ የነበሩ የሕወት አባላት ስለተወገዱ፣ ክልሎቹ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ጀምረዋል ቢባል ቢያንስ ቢያንስ በመሪህ ደረጃ ትክክለኛ ግምት ነው። ችግሩ ያለው፣ ዛሬም ክልሎቹን የሚያስተዳድሩ ግለሰቦች የትናንትናዎቹ ብአዴኖች፣ ኦፒዲኦዎች እና ሕወሓት አባላት ስለሆኑ “ሕዝቡ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው” ማለት አይቻልም። ሆኖም ግን ህዝቡ የራሱን ዕድል በራሱ እንዳይወስን እያደረጉ ያሉት በሕዝብ ያልተመረጡ የዚያው ብሔር ተወላጆች ናቸው እንጂ ከሌላ ክልል የመጡ የሌላ ብሔር ተወላጆች አይደሉም። ራስን በራስ የማስተዳደር ዋነኛው ምልክቱ፣ ሕዝቡ በቀጥታ ነጻና ግልጽ በሆነ መንገድ በመረጣቸው ተወካዮቹ ሲተዳደር እስከ ሆነ ድረስ ማለቴ ነው።

1 | P a g e

ብሔርተኞች በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ አሉ። የታሪክ አጋጣሚን ተጠቅመው ሊበረቱ ወይም ሊዳከሙ ይችላሉ። በዩጎዝላቪያ ስድስቱም ሬፑብሊኮች የነበሩ ብሔርተኛ ቡድኖች የዓለም አቀፉ ሁኔታ ያመቻቸላቸውን አጋጣሚ ተጠቅመው

በ 1992 ዓ/ም “የየራሳቸውን ሕዝብ መብት ለማስጠበቅ” ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ የርስ በርስ ጦርነት ጀመሩ። አንዴ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ግን ትናንት ተስማምቶ በሰላም ይኖር የነበረው ሰፊው ሕዝብ “የየብሔሮቻቸውን መብት ለማስጠበቅ” ሲባል ግለሰብ ብሔርተኞች በቀደዱላቸው ቦይ መፍሰስ ጀመሩ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ተገዳደሉ። ለማስረዳት እንኳ በሚከብድ ዓይነት የአንድ የዘር ግንድና አንድ ቋንቋ የነበራቸው ሕዝቦች ተከፋፍለው ሰባት ጎረቤት አገራት ሆነው አረፉ። መፋታት ካልቀረ ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ተፋትተው አብሮ በሰላም መኖር ሲቻል የዚያ ሁሉ ሰፊ ሕዝብ ነፍስ በከንቱ መጥፋቱ አሳዛኝ ነበር። ከአሰቃቂው የርስ በርስ ጦርነት በኋላ የተለወጠ ነገር ቢኖር፣ በአንድ ፕሪዚዴንት ፋንታ ሰባት ፕሬዚዴንቶች መፈጠራቸው እንጂ በሕዝቡ የኑሮ ደረጃ ላይ የጎላ ለውጥ አልታየም። የአገሪቷ ሃብትም (ካፒታል) ያው እንደ ተለመደው በጥቂቶች እጅ ገብቶ ሰፊው ሕዝብ ግን እንደ ድሮው ለፍቶ ጥሮ ግሮ ከሚያገኘው እየገበረ በጥቂቶች መበዝበዙን ቀጥሎበታል። የኔ እንደሆን “ያው በገሌ” እንዳለችው ድመት ማለት ነው።

የብሔር ወይም የማንነት ጥያቄን ከሁሉ አስቀድሞ የሚያነሳው ኤሊቱ (በማርክሲዝም ደግሞ የከበርቴውና የንዑስ ከበርቴው) ነው። የማንኛውም ብሔር ሰፊ ሕዝብ ማሕበረሰቡ ውስጥ ባለው ቦታ ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ራሱን ከሌላ ብሔር ለይቶ አያይም። ለምሳሌ ያገራችንን ሰማኒያ አምስት ብሔሮች ብንወስድ፣ የያንዳንዳቸውን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት እኩል የሚጥስ የጋራ ጠላትና ድህነት የሚባል የጋራ “ይዞታ” ስላላቸው በምንም ተዓምር በርስ በርሳቸው ላይ ክፉ አያስቡም። ወገራ ያለው አማራ በወረዳው ያሉ “የብአዴን” ሹማምንቶች የሚያደርሱበትን ግፍ እንዴት አድርጎ እንደሚወጣው ያስብ እንደሆን እንጂ፣ ግምቢ ያለውን ኦሮሞ “ራሴን በራሴ እንዳላስተዳድር አድርጎኛል” ብሎ በክፉ አያስበውም። አጋሮ ያለው ኦሮሞም ባካባቢው በሚገኙ “የኦሕዴድ” ባላሥልጣናት ሲገፋ፣ እንዴት አድርጎ ከነዚህ ራሳቸውን በራሳቸው ከሾሙ ደም መጣጮች ነጻ ወጥቶ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን ዘዴ ይቀይስ እንደው እንጂ ስለ አፋር ብሔር ክፉ የሚያስብበት አንዳችም ምክንያት አይኖረውም። ለማለት የፈለግሁት ያገራችን ትልቁ ችግር ያለው ከሁሉም ብሄር በተወጣጡ ጥቂት ኤሊት ቡድኖች መካከል ነው እንጂ በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል አይደለም የሚለውን ነው። የግለሰቦች እንጂ የሕዝብ ብሄርተኛ የለምና!

እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የታዩት የአገዛዝ ሥርዓቶች፣ የባለተራው ብሔር ኤሊት እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑትን የሚቀርቧቸውን የብሔራቸውን ግፈኛ ጠቀሙ እንጂ ለብሔራቸው ሰፊ ሕዝብ አንዳችም የፈየዱት ነገር የለም። አማርኛ ተናጋሪው የሰሜን ሸዋ ኤሊት በሰፈረበት የደቡብ አገር ያካባቢውን ሕዝብ ካፈናቀለው መሬት ላይ ያገኘውን ጥቅም እዚያው ለራሱ አዋለው እንጂ ጎጃምና ጎንደር ላሉ የአማርኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ወይም ለትግራይ ሰፊው ሕዝብ አንዳችም ያካፈለው ነገር አልነበረም። ባሕር ዳርና ጎንደር፣ መቀሌና ደሴም ከነዚህ የደቡብ ግዛቶች ከተዘረፉ ሃብቶች እንደ ብሩሴልስና ፓሪስ፣ ወይም ሎንዶንና ማድሪድ ተጠቃሚ አልሆኑም። የሕወሓት ኤሊቶችም እንደዚሁ በአዲስ አበባና በሌሎች ደቡብ ክልሎች ካካበቱት ኃብት ወደ ትግራይ ልከው የትግራይን ሰፊ ሕዝብ ተጠቃሚ አላደረጉም። ድህነት ሰፊውን የኢትዮጵያን ሰፊ ሕዝብ ያቆራኘውን ያሕል፣ ሰፊውን ሕዝብ መጨቆን፣ መበደልና መዝረፍ ደግሞ የየብሔሮችን ኤሊት ባለተራዎችን አንድ አድርጓቸዋል። በንጉሡ ዘመን በደቡብ ሕዝቦች ላይ ይፈጸም ለነበረው ጭቆናና ብዝበዛ ፊታውራሪዎቹ የአማርኛ ተናጋሪ ኤሊቶች ይሁኑ እንጂ የሌሎች ብሔሮችም ኤሊቶች በተወሰነ ደረጃ ተካፋዮች ነበሩ። በሕወሓት ዘመን የብዝበዛው የዘረፋውና የጭቆናው ተግባር በትግራይ ኤሊቶች ይመራ እንጂ የሌሎች ብሔሮች ኤሊቶችም ሰፊውን ሕዝብ በመዝረፉና በመበደሉ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ ነበራቸው። ዛሬ ኢትዮጵያን እየገዟት ያሉት እነዚህ ከሁሉም ብሔር የተወጣጡ ሌቦች (ይቅርታ ካፒታሊስቶቹ) ያገሪቷን የፖሊቲካ ሥልጣንና ኤኮኖሚውን በጋራ ተቆጣጥረውታል። ለካፒታል ደግሞ ዋናው ግቡ ትርፍ እንጂ የሰው ልጅ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ስላልሆነ፣ የተሻለ ጥቅም እስካገኙበት ድረስ ሌቦቹ እንኳን የሌላውንና ያሳደጋቸውን ሕዝብ (ብሔር) ሳይቀር ከመጉዳት ወደ ኋላ አይሉም። ለማለት የፈለግሁት፣ ዛሬ ባገራችን ተንሰራፍቶ ያለው ጭቆናና አጠቃላይ የሕዝቦች መብት ጥሰት እየተከሰተ ያለው በነዚህ የፖሊቲካና ኤኮኖሚ ሥልጣንን በጃቸው ባደረጉ ከሁሉም ብሔር የተውጣጡ ቡድኖች እንጂ፣ አንዱን ብሔር ጨቁኖ እየተጠቀመ ያለ ሌላ ብሔር የለም ለማለት ነው። ስለዚህም ትግሉ መሆን ያለበት በብሔሮች መካከል ሳይሆን፣ በሕዝቡና በነዚህ ጸረ ሕዝብ በሆኑ ሌባ ቡድኖች መካከል ነው ለማለት ነው።

በኔ ግምት፣ የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ኤሊቶች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ይህንን መሬት ላይ ያለውን ዕውኔታ የሚያንጸባርቁ አይመስለኝም። አዎ! ዛሬ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክልሎች እያስተዳደሩ ያሉ የክልል መንግሥታት በሙሉ ባለፈው “ምርጫ” ሕዝቡን አስገድደው የተመረጡ ናቸው እንጂ ሕዝብ ራሱ በፈቃዱ የመረጣቸው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ አይደለም ብሎ እስካልሆነ ድረስ፣ ቅራኔው መሆን ያለበት ከመብት ጣሽ ቡድኑ ጋር እንጂ ከሆነ ግምታዊ ብሔር ጋር መሆን የለበትም ማለት ነው። ሥልጣን ላይ ያለው የዶ/ር ዓቢይ ቡድን የኢትዮጵያን ሕዝቦች መብት እየጣሰ ነው ከተባለ ደግሞ መፍትሔው ይህንን ቡድን በሰላማዊ መንገድ (በምርጫ) ከሥልጣን አውርዶ

2 | P a g e

በዕውነተኛ የሕዝብ ተወካዮች መተካት ነው እንጂ፣ በቡድኑ ላይ ካለን ኩርፍያ ብቻ ተነሥተን የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ መክተት አንድም የፖሊቲካን ሀሁ አለማወቅ ነው አለያም ደግሞ ሆን ብሎ ድሮም በተጠባባቂነት ያስቀመጡትን የትግል ዓላማ ዛሬ አጋጣሚን ተጠቅሞ ሥራ ላይ ለማዋል የሚደረግ ቅንነት የጎደለው አካሄድ ነው።

ከመቶ አምሳ ዓመት በፊት እንደኛው ዘመነ መሳፍንት፣ አገራቸው በጎጠኛ መሳፍንቶች ሲገዙ የነበሩ ኢጣልያን፣ ፈረንሳይና ጀርመን ከኛ በኋላ ተነስተው ዛሬ የአገረ-ብሔር ምሥረታው ተሳክቶላቸው አንድ አገር አንድ ሕዝብ ሲሆኑ እኛ ግን ጌታ እንደፈጠረን፣ ቋንቋና ባሕላችንን ይዘን ሰማኒያ አምስት የተለያዩ ብሔሮች መሆናችንን ሳስተውል፣ የአገር ምሥረታውን በተመለከተ ተከታታይ መሪዎቻችን ወይ አንዳችም ፍኖተ ካርታ አልነበራቸውም፣ ወይም ደግሞ የነበራቸው ፍኖተ ካርታ በግድፈት የተሞላ ነበር። ያ ባይሆን ኖሮ፣ ከዚህ ሁሉ የነጻነት ዘመን በኋላ ዛሬ መታገል የነበረብን ስለ ማንነት ጥያቄ ሳይሆን ስለ አገር ግንባታ ብቻ ይሆን ነበር። አንድ አገረ-ብሄር መፍጠር ባንችልም ግን፣ የተለያዩ ብሔሮችን ያቀፈችን ኢትዮጵያን በጋራ እናታችን ናት ብለን ተቀብለናታል። ይህንን ስንቀበል ግን የዚችን እናታችንን ቤት ቅርጽና ይዘት ሕዝቦቿ ተስማምተውበት የፈጠሯት እንዳልነበር በልባችን እያወቅን ነው። ስለዚህ ዛሬ ካንዳንድ ብሔር ኤሊቶች የእናታችንን ቤት ቅርጽና ይዘት አብረን በአዲስ መልክ እናስተካክላት ብለው ሃሳብ ቢያቀርቡ ፍጹም ትክክል ነው ማለት ነው። ስሕተቱ እነዚህ ኤሊቶች ሳይወከሉ ሕዝቡን እንወክላለን ብለው በሕዝብ ስም የአገሪቷን ቅርጽና ይዘት ራሳቸው ለመቀየር እርምጃ ለመውሰድ መሞከራቸው ነው። ሃሳባቸው ትክክል ሆኖ፣ ሃሳባቸውን በተግባር ለመተርጎም የሚወስዱት እርምጃ ግን ትክክል አይደለም። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ የራሱን ተወካዮች መርጦ እንደማያውቅ እያወቅን፣ ዛሬ እነዚህ ራሳቸውን የሾሙ ኤሊቶች በሕዝብ ስም ሆነው ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ለመወሰን ሲቋምጡ እያየን ዝም ማለቱ እኛንም በወንጀሉ ተባባሪነት ሊያስጠይቀን ይችላልና በጊዜ ብናስብበት የሚሻል ይመስለኛል። ስለዚህ ሁላችንም ማድረግ ያለብንና መጫወት ያለብንን ሚናችንን ካሁን ለይተን በውል እንወቅ!

የመንግሥት ድርሻ፣ መንግሥትን በብዙ መልክ መግለጽ ይቻላል። የቤተሰብ መሪ/አባት ነው የሚሉ አሉ፣ ስለሆነም፣ የቤተሰቡን አባላት በሙሉ በእኩልነት የሚያይ፣ የቤተሰቡን የቀን ተቀን ፍላጎት የሚያሟላ መሆን አለበት ማለት ነው። መንግሥት ማለት ሕዝብ ነው። ሕዝቡ በገዛ ፈቃዱ ከመሃሉ ጥሩ ጥሩውን እየመረጠ የራሱን ጥቅም ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እንዲጠብቁለት ወደ ሥልጣን መድረክ የሚያወጣቸው የማህበረሰቡ ምርጥ ግለሰቦች ጥርቃሞ ነው። ስለሆነም፣ የተልዕኳቸው/ የግዴታቸው አልፋና ኦሜጋ የወከላቸውን ሕዝብ መብት መጠበቅ ማክበርና ማስከበር ብቻ ነው። የመንግሥት መብት ብሎ ነገር የለም ግዴታ እንጂ! አዎ የኢሕአዴግን መንግሥት የዶ/ር ዓቢይንም ጨምሮ፣ ግልጽና ፍትሓዊ በሆነ መንገድ አልመረጥናቸውም። ግን ደግሞ እንወክልሃለን ስላሉን ቃል ደግሞ ዕዳ ነውና “በአግባቡ ወክሉንና ግዴታችሁን ተወጡ” ብለን የመጠየቅ ሙሉ መብት አለን። መንግሥት ደግሞ የፈለገው ዓይነት ጥያቄ ይሁን ከጠያቂዎቹ ማለትም ከሕዝብ ጋር ቁጭ ብሎ መወያየትና ለጥያቄው መፍትሔ መፈለግ እንጂ “ጥያቄው ትክክል አይደለም” ብሎ መዝጋት ጠያቂዎቹን ያስኮርፋል፣ ለግጭት ይጋብዛል። ማንኛውም ዓይነት ማህበረሰባዊ ጥያቄ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የማይፈታበት ምክንያት የለም። አለበለዚያ ግን መንግሥት ጉልበት አለኝ ብሎ ወታደርን አስዘምቶ ሕዝብን መግደል ማሰር ማሰቃየት ኃላፊነትን በትክክል ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። ማን አለብኝነት ደግሞ ወያኔ መራሹ መንግሥት፣ ባዶ እጃቸውን ጎዳና ላይ ወጥተው በታገሉት ወጣቶች እንዴት ተሽቀንጥሮ እንደተጣለ በዓይናችን በብረቱ አይተናል። ጠብመንጃም የችግሮቻችን መፍቻ አድርጎ መጠቀሙ ላንዴና ለመጨረሻ ያብቃ! አለመግባባትን መፍታት ያለብን በውይይት ብቻ መሆን አለበት ለማለት ነው። ይህ ደግሞ መንግሥት ከሁሉም አስቀድሞ በተግባር ማዋል ያለበት ግዴታው ነው።

የትግራይ ክልል መንግሥት ሚና፣ እንደሚገባኝ ከሆነ ከዶ/ር ዓቢይ መንግሥት ጋር ያላችሁ አለመግባባት ለኸያ ሰባት ዓመት በኢሕአዴግ ውስጥ ከነበራችሁ ቁልፍ የአመራር ቦታ መነሳታችሁ ብቻ ይመስለኛል። ማንም የሰው ልጅ የሚያደርገው ስለሆነ አይገርምም። ይህ ዓይነቱ ክስተት ደግሞ በሰው ልጆች የፖሊቲካ ሥልጣን መተካካት ታሪክ ውስጥ የተለመደና እናንተም ሥልጣን ላይ የወጣችሁት በተመሳሳይ መንገድ ስለሆነ ያን ያህል ሊያናድዳችሁ ባልተገባ ነበር። በኔ ግምት፣ የዓቢይ መንግሥት በተለየ መልኩ የትግራይን ሕዝብ ብቻ ለይቶ የሚጎዳ እርምጃ የወሰደ አይመስለኝም። እንዲያውም የሌሎች ክልል መንግሥታት የማያደርጉትን፣ በናንተ ክልል ውስጥ ተመሽጎ ያለውን ከፍተኛ የሕወሃት አመራር አባል በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮአል ተብሎ ሲከሰስ “አሳልፈን ለፌዴራሉ መንግሥት አንሠጥም” ብላችሁ በተግባር የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የአገሪቷ የበላይ ሕግ መሆኑን አንቀበልም እያላችሁ ነው። የተጠረጠረው አንድ ግለሰብ እንጂ የትግራይ ሕዝብ አይደለም። የተከሰሰን ዜጋ ደግሞ ወንጀሉን መርምሮ፣ ግራና ቀኙና አይቶና ሰምቶ የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው ፍ/ቤት ነው እንጂ የክልል መንግሥት አይደለም። እናንተም በሕግ የበላይነት እንደምታምኑ ደጋግማችሁ እያስታወቃችሁ ነው። ሕገ መንግሥቱ ደግሞ ራሳችሁ እንደሚጥማችሁ አድርጋችሁ ያረቀቃችሁና ያጸደቃችሁ ስለሆነ ዛሬ ስለሚስተዋለው ጉድለቱ እንኳ ራሳችሁን እንጂ ሌላ ማንንም መኮነን የለባችሁም። አዎ! ያኔ ይህ ይደርሳል ብላችሁ ስላላሰባችሁ፣ የክልል ሕዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በዝርዝር ስታስቀምጡ፣ “የክልሉ መንግሥት ክልላዊ ምርጫን ያካሄዳል” የምትል አንዲት ንዑስ አንቀጽ እንኳ በአንቀጽ 54 ሥር

3 | P a g e

ብታካትቱ ኖሮ ዛሬ በምርጫው ጉዳይ ላይ ከፌዴራል መንግሥቱና ከምርጫ ቦርዱ ጋር አታካራ ውስጥ አትገቡም ነበር። ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተመለከተ ደግሞ የትግራይን ክልል ያላንዳች ጣልቃ ገብነትና ጫና እያስተዳደረ ያለው ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጣው ሕወሓት ስለሆነ ኩርፊያችሁ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ስለዚህ እባካችሁ፣ ይህንን የጥቂት ሕወሓት አባላት እንጂ የትግራይ ሕዝብ ችግር ያልሆነውን ጥያቄ እያነሳችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ አብሮነት አትገዳደሩ። የትግራይ ሕዝብ መብት ከሌሎች በበለጠ እንጂ ባነሰ መልኩ የተከበረ ስላልሆነ፣ እስቲ ረገብ በሉና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር “በመሪነት” ሳይሆን “በእኩልነት” አብሮ ለመኖር ትጉ።

የኦሮሞ ሽምቅ ተዋጊዎች፣ የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት ይደርስበት ከነበረው ጭቆና ነጻ ለመውጣት ዘመናትን ያስቆጠረ ትግል እያካሄደ ነበር። በዚህ ሂደቱም ብዙ መስዋዕት ከፍሎ ብዙ ድሎችን ተቀዳጅቷል። ኦሮሚያ የምትባል በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሷን በራሷ የምታስተዳድር ክልል ፈጥሯል። ሕዝቡ በፈቃዱ ነጻ ሆኖ በመረጣቸው ተወካዮቹ ባይሆንም በራሱ የኦሮሞ ልጆች እየተዳደረ ነው። በክልሉ ውስጥ ልጆቻቸው በራሳቸው ቋንቋ የመማርና የማስተማር ድል ተጎናጽፈዋል። አዎ! ማህበረሰቡ ገና ያልተመለሰለት ጥያቄ ቢኖረውም እስካሁን ሕዝቡ ከተጎናጸፈው ድል አንጻር ሲታይ የሚቀረው የቤት ሥራ ቀላል ነው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር የትጥቅ ትግልን የሚጋብዝ አይደለም ማለቴ ነው። በኔ ግምት በውይይት የሚፈታ ነው። ያ ሳይሆን ቀርቶ ግን፣ ዛሬ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልሎች እየታየ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ስዎች ይገደላሉ፣ ገዳዩም ኦሮሞ፣ ሟቹም ኦሮሞ፣ የሚገዳደሉትም በኦሮሚያ ላይ ነው። የንግድ እንቅስቃሴ ቆሞአል። በኮማንድ ፖስት ዓዋጁ ምክንያት ላለፉት ሁለት ዓመታት የሰዎች በነጻ የመሰብሰብና የመንቀሳቀስ መብት ተጥሶአል። በጸጥታ ምክንያት አርሶ አደሩ ማረስ ስላልቻለ በዚህ ዓመት በአካባቢው ይህ ነው የማይባል ረሃብ ገብቷል። ከላይ እንዳልኩትም ዛሬ እየቀረበ ያለው “ራስን በራስ የማስተዳደር” ጥያቄ ከጠረጴዛ ዙርያ ውይይት አልፎ ለመገዳደል የሚያደርስ አይደለም። ስለዚህ እባካችሁ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመቅረብ ተዘጋጁ።

የክልል ጥያቄ ለሚያነሱ የደቡብ ሕዝቦች፣ ጥያቄያችሁ ትክክለኛ ነው። ከመጀመርያው ጀምሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከማንኛውም ሕዝብ በላይ በደል ሲደርስበት የነበረውን ከአምሳ በላይ ሕዝብ አንድ ላይ ጨፍልቆ “የደቡብ ሕዝብ” ብሎ መሰየሙ የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች በናንተ ላይ ያላቸውን የንቀት ደረጃ የሚያሳይ ነው። ሌሎች “ብሔር” ተብለው እናንተ ግን “ሕዝብ” የተባላችሁበት መስፈርት አለመኖሩም ዛሬም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እኩል አይደላችሁም ማለትን ያመላክታል። ይህ በሚቀጥለው የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ሂደት ውስጥ ቅድሚያ ሊሠጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። እስካሁን ያቀረባችሁት የተለያዩ ክልሎች የመሆን የመብት ጥያቄያችሁን እያቀረባችሁ ያለው ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስለሆነም ሊያስመሰግናችሁ ይገባል። ቀጥሉበት። መንግሥት ደግሞ በበኩሉ ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መብታችሁን ለማክበርና ለማስከበር ግዴታውን አውቆ በአስቸኳይ ለጥያቄያችሁ መልስ መስጠት አለበት። የዘገየ ፍትሕ፣ የተነፈገ ፍትሕ ነውና! – justice delayed – justice denied!

የአማራ ሕዝብ ሆይ! ለዘመናት አብራችሁ እንደ አንድ ሕዝብ የኖራችሁ የቅማንትና የአገው ሕዝብ ዛሬ የማንነትን ጥያቄ ቢያነሳ መናደድና ብሎም ጠብመንጃ አንስቶ እነሱን ለመውጋት አትፍጠኑ። እነዚህ ሕዝቦች እየጠየቁ ያሉት እኮ ከኢትዮጵያ እንገንጠል ሳይሆን፣ አማራ አይደለንም፣ ስለሆነም ልክ እንደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር ነው። ይህ ማለት ደግም በምንም መልኩ የአማራን ሕዝብ ፖሊቲካዊ ኤኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ጥቅም አይነካም። አልፎ አልፎ ባንዳንድ ክልሎች ጸረ ሰላም ኃይሎች አማርኛ ተናጋሪውን ሕዝብ አሳዛኝ በሆነ መልክ ማፈናቀላቸው ሁላችንንም ያስከፋን ጉዳይ ነው። እንደዚህ ዓይነት መፈናቀል ደግሞ በአማርኛ ተናጋሪው ብቻ ሳይሆን በሶማሌና በኦሮሞ፣ በጉሙዝና በጌዴኦ እንዲሁም በቅማንት ሕዝቦችም ላይ የተፈጸመ ስለሆነ አማርኛ ተናጋሪው ብቻ ተለይቶ የተጠቃ አድርጋችሁ አትውሰዱት። ይህ ማለት ግን የመፈናቀል ወንጀልን ተቃውማችሁ መብታቸው ለተጣሰባቸው ዜጎች ያላችሁን ድጋፍ አትስጡ ሳይሆን፣ ክስተቱን በብሄር መነጽር ብቻ አትዩት ማለቴ ነው። ምንም እንኳ የክልል መንግሥታችሁ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመረጣችኋቸው ባይሆንም፣ በክልላችሁ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ራሳችሁን በራሳችሁ እንዳታስተዳድሩ የሚጫናቸው ብሔር የለም። በመሆኑም ዋናው ቅራኔያችሁ ከክልል መንግሥታችሁ ጋር እንጂ ከሌላ ብሔር ጋር መሆን የለበትም። እነሱን ደግሞ በሚቀጥለው ምርጫ ልትገላገሏቸው ትችላላችሁ። አስታውሱ! ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች (ብሔሮች) ጋር የሚያገናኛችሁ የአንድ አገር ሕዝብነት ብቻ ሳይሆን ሁላችሁንም እኩል እየደቆሰ ያለው ድህነት የሚባል ጠላት አለና እሱን በጋራ ተዋግቶ ድል ለመቀዳጀት ተዘጋጁ።

ኤሊቶችችሁ ግን እያነሱ ያሉት “የሕዝባችን ተበድሏል” ዋይታ፣ ከላይ ካልኩት የሌሎችም ብሔር ኤሊቶች ከሚያነሱት የተለየ አይደለምና፣ እስቲ ሰከን ብላችሁ “የትኛው ብሔር ነው እየበደለን ያለው” “ራሳችንን በራሳችን እንዳስተዳድር እያደረገን ያለውስ ማነው?” በሉና ራሳችሁን ጠይቁ! መልሱን እዚያው ሰፈራችሁ ታገኙታላችሁ። አዎ! ኢትዮጵያን ለመፍጠርም ሆነ ኅልውናዋን ዘላለማዊ ለማድረግ ሁላችሁም ያበረከታችሁት አስተዋፅዖ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ካበረከቱት እኩል ነውና ይህንን አባቶቻችሁና አያቶቻችሁ የደሙለትን አገር ኅልውና አትፈታተኑ። ቅንነት ካለ በውይይት የማይፈታ የፖሊቲካ ጥያቄ የለም።

4 | P a g e

የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ ከሁላችንም አስቀድማችሁ በመንቃት የሕዝባችንን ችግርና የዲሞክራሲን አስፈላጊነት ላገራችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝቦች ለማሳወቅ የወሰዳችሁትና እየወሰዳችሁ ያለው እርምጃ እጅግ በጣም የሚያኮራ ነው። በርቱበት እንላለን። ሁለት ነገሮች ግን አጥብቃችሁ እንድታስቡበት እንፈልጋለን። የመጀመርያው፣ የነቃችሁ የሕረተሰቡ ክፍል በመሆናችሁ የትግሉ ፊታውራሪ ናችሁ ማለት በሕዝብ ስም የራሳችሁን የፖሊቲካ ዓላማ ከግብ ለማድረስ መሞከር ትክክል አይደለም። በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው። አዎ! መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ በአንድ ላይ አራት ኪሎ መጥቶ የሥልጣን ወንበር ላይ መቆናጠጥ ስለማይችል፣ የግድ ከመካከሉ ተዓማኒነት ያላቸውን የማህበረሰቡን አባላት መርጦ መላክ አለበት። የናንተ ተቀዳሚው ድርሻ መሆን ያለበት እነዚህን ባብዛኛው ለዘመናዊ ዕውቀት ያልተጋለጠውን ሕዝባችንን አንቅታችሁ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ማለትም ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ማህበረሰባዊና ፖሊቲካዊ ዕውቀቱን ከፍ ማድረግ ነው። ዞሮ ዞሮ በመጨረሻ ላይ የፖሊቲካ ሥልጣን ላይ የምትወጡት እናንተ ብትሆኑም፣ ሕዝቡ እንናተኑ መልሶ በራሱ ፈቃድ እንዲመርጣችሁና ለሥልጣን እንዲያበቃችሁ አስተምሩት። በነጻ ሃሳቡን የሚገልጽበት ዕድል ቢሰጠውና ሁኔታው ቢመቻችለት፣ ሕዝቡ ምን እንደሚያስፈልገው ጠንቅቆ ያውቃል። ምክሬ እንቅስቃሴያችሁን እንድታቆሙ ሳይሆን፣ የትግላችሁ ዓላማ፣ ሰፊው ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እንዲችል (empowerment) የሚነገረውንና የሚሰማውን በደንብ አላምጦ የሚመቸውን መርጦ የሚወስድበት በቂ ዕውቀት እንዲኖረው (informed decision) ለማድረግ መሆነ አለበት ማለቴ ነው።

ሁለተኛው ምክሬ የፖሊቲካ ባሕላችንን በተመለከተ ነው። እባካችሁን ሰዎችን ወደ ውይይትና ድርድር ጠረጴዛ እንጂ ወደ ግጭት መድረክ አትጋብዙ። ውይይት ነፍስ ያድናል፣ ግጭት ግን ነፍስ ይገድላል። የሰው ልጆች እንደ መሆናችን ደግሞ ሁላችንም መኖር እንጂ መሞት አንፈልግም። አዎ! በታሪካችን ውስጥ ከታቃራኒ ወገን ጋር አብሮ ለመኖር ሰጥቶ የመቀበል ባሕል አልነበረንም። ያንን ኋላ ቀር ባሕል ቀይረን፣ ተወያይተን ለመስማማት፣ ስምምነት ላይ መድረስ ሲያቅተን ደግሞ በሚያስማምው ላይ ብቻ ተስማማተን በማንስማማበት ጉዳይ ላይ ደግሞ ላለመግባባት ተስማምተን አብሮ መኖር እንደሚቻል ራሳችን ተምረን ሌሎችንም እናስተምር። የኔ ብቻ ትክክል ነው፣ በመሆኑም የኔን አስተሳሰብ ካልተቀበልክ አብሬህ አልኖርም ማለት ለዘመናት ተጣብቆን የኖረ የፊውዳል አስተሳሰብን እርግፍ አርገን እንጣለው። ግትርነት የትም አያደርስም። ይህ መንግሥትንም ይመለከታል።

ለማጠቃለል ያህል፣

መንግሥትም ሆናችሁ የፖሊቲካ ድርጅቶች በድርጊታችሁም ሆነ ባላማድረጋችሁ፣ ሕዝቦቻችንን አሸናፊ ለማይኖረው የርስ በርስ ግጭት አትጋብዙ። የርስ በርስ ግጭት ከማንኛውም ጦርነት ዓይነት ሁሉ የከፋ አጥፊ ነው። የሚዋጉት ጎረቤት ለጎረቤት ዘመድ ከዘመድ ጋር ስለሆነ፣ ከውጪ ወራሪ ኃይል ድርጊት በላይ የማሕበረሰቡን ድርና ማግ ይበጣጥሳል። ውጊያው የሚካሄደው የርስ በርስን ጓዳ በሚያውቁ ያንድ ሰፈር ሰዎች መካከል ስለሆነ በሰው ልጆች ነፍስና በኤኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጥፋት እጅግ በጣም አስከፊ ነው። ስለዚህ በቀልል ውይይት መፍታት ለሚቻል ማህበራዊና ፖሊቲካዊ ችግር፣ ተተኪ የማይገኝለትን ክቡር የሰውን ልጅ ነፍስ በከንቱ አንሰዋ! ለዚያውም ለሞት እንጂ ለመኖር ያልታደለ ለፍስ!

ወገኖቼ፣ በጣም ብዙ ብዙ የሚለያዩን ወይም ሊለያዩን የሚችሉ ማህበረሰባዊ፣ ባሕላዊ ታሪካዊና ፖሊቲካዊ ጉዳዮች ያሉትን ያሕል የሚያገናኙን በጣም እጅግ በጣም ብዙ ነገሮችም አሉ። በጎ በጎዎን ልተውና አንድ አሉታዊ የሆነ ግን ደግሞ ሰፊውን ሕዝባችንን ለዘመናት ብሔርን ከብሔር ሳይለይ አንድ ላይ አቆራኝቶ ያቆየውን ድህነታችንን ለመጥቀስ እሻለሁ። ድህነት ዳርቻ ወይም ድንበር አያውቅም። ብሔርን ከብሔር አይለይም፣ ሁሉንም እኩል ያጠቃል። በዘጠኙም ክልሎች የሚኖሩ ወገኖቻችን ዛሬ ሁሉም በእኩልነት የሚጋሩት “የጋራ ጠላት” ድህነትን ነው። ይህንን የጋራ ጠላት ደግሞ አሸንፎ ወደ ተሻለ ነገ ለማለፍ የሁሉም ክልል ብሔሮች ትብብር ያስፈልጋል። ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከሁሉም መቅደም ያለበት የዲሞክራሲ ጥያቄ ቢሆንም፣ ከዚያው እኩል መታየት ያለበት ደግሞ ይህንን መብት ለመቀዳጀት ጉልበትን መጠቀም አላስፈላጊ መሆኑን ነው። የሰው ልጅ ስለ አስተዳደር ከማውራቱ በፊት በሕይወት የመኖር ዋስትናው መጠበቅ አለበት። በግጭት ውስጥ ደግሞ ሞት ስላለ፣ ከግጭቱ ማግሥት የሚያስተዳድርም የሚተዳደርም ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ቅድሚያ እንስጥ። የሕዝባችን በሕይወት የመኖር ዋስትና መከበር አለበት። ሌላው ሁሉ በሕይወት ከመኖር በኋላ የሚመጣ ነው።

******

ጂኔቫ፣ ሰኔ 15 ቀን 2020 ዓ/ም
[email protected]

5 | P a g e

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.