ክፍል 1
ሰኔ 11 ቀን 2012 በተደረገው የደቡብ ክልል ም/ቤት ጉባኤ የሲዳማ ዞን ክልል እንዲሆን የተጀመረው ሽግግር መጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው ከብዙ አመታት ትግልና ከአንድ ህዝበ_ዉሳኔ በኋላ መሆኑ ይታወሳል፡፡ መግለጫው ለሲዳማ ነዋሪዎች ሁሉ መልካም ዜና ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የአስተዳደር ደረጃ ለሲዳማ ህዝብ የክፍታ ጫፍ ሆኖ ሳይሆን፣ ግዛቱ ከሶስት አስርት አመታት በፊት ወደ ነበረበት ደረጃ በመመለሱ ነው፡፡ የኢህአዴግ ጎጠኛ መንግስት ከመቋቋሙ በፊት፣ ሲዳማ አንዴም ክፍለ አገር፤ በፊትም ጠቅላይ ግዛት በመባል ከ14ቱ የኢትዮጵያ ዋና ዋና ግዛቶች አንዱ ሆኖ እንደቆየ የትናንት ትዉስታ ነው፡፡
ቢሆንም ቅሉ በትግል የተገኘ ድል ሁሉ ጣፋጭ ነውና አሁን ያገኘነውን የአስተዳደር መሻሻል በጸጋ ተቀብለን፤ ክልላችንን እንዴት እንገንባ፤ እንዴት ፍትሃዊ አስተዳደር እንፍጠር፤ የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሳን ለመወያየት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ይህቺም አጨር መጣጥፍ የቀረበችው ለዚህ ዓላማ አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው፡፡ የሲዳማ ተወላጆች በአሁኑ ሰአት በሌላም መንገድ እድለኞች ነን፤ አስተዳደራችን ከፍ ወዳለ ደረጃ በሚሸጋገርበት ጊዜ፤ አገራችን ኢትዮጵያም በከፍተኛ የለውጥ ጉዞ ላይ ነች፡፡ የለውጡ አቅጣጫ ከመበተን ወደ አንድነት፤ ከመጨቆን ወደ ፍትሃዊ ሥርአት፤ ከአፈና ወደ ዴሞክራሲ፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት ወደ መልካም አስተዳደር እያሸጋገረን እንደሆነ እነሆ በዓይናችን እያየን ነው፡፡ የሲዳማ ተወላጆችና የፖለቲካ ልሂቃን የትልቋ አገራችን አንድ ክፍል በመሆናችን፤ በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ መሳተፍ የግድ ነው፡፡
ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ወስጥ ሲዳማ ዝቅ ባለ የአስተዳደር ደረጃ መመደቡ ብቻ ሳይሆን፤ እኛንም ሆነ አገራችንን በከፍተኛ ደረጃ የሚበክል መርዛማ የፖለትካ ፍልስፍና በመተግበሩ እርስ በርሳችን የሚያናክስ፣ በቀጠናው ውስጥ ብጥብጥና ሁከት የሚቀሰቅስ ድባብ ተፈጥሮ እንደሰነበተ እናስታውሳለን፡፡ ትህነግ/ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመኑን ለማስረዘም ሲል ሆን ብሎ ጠንስሶ በስራ ላይ ያዋለው የፖለቲካ፤ ኢኮኖሚና ማህበራዊ የአገዛዝ ቀመር፣ አንዱን ማህበረሰብ ከሌላው የሚያናክስ፣ አንዱን ጠቅሞ ሌላውን የሚበድል፣ አንዱን ወዳጅ ሌላውን ጠላት የሚያደርግ ነበር፤ ስለሆነም ትልቁን የአገርና የህዝብ ጥቅም ወደጎን አስቀምጠን፣ በትናንሽ የጎጥና የድንበር ጉዳዮች ስንናከስ ሰንብተናል፤ ጠላት ነው ተብሎ በተነገረን ማህበረሰብ ላይ ጥርስ ስንነክስ፤ ሲያመች በህግ ካላመቸም በጉልበት በማንነት ላይ ያተኮሩ በደሎች ሲፈጽሙ ቆይተዋል፤ ከሁሉ ይበልጥ የሚጎዳው ግን በብሄራዊ አንድነታችን ላይ የተሰነዘረው ሥነ_ልቦናዊ ጥቃት ነው፤ በመላው አገራችን የተዘረጋው የአስተዳደር ሥርኣት በጎጥና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አንዳችን ካንዳችን ጋር ያለን መተሳሰርና መጋመድ እየተፋቀ “እኔ፣ እኔ፣ የኔ፣ የኔ” በሚል አመለካከት ተተካ፡፡ ይህም አመለካከት ከኢኮኖሚ ጥቅመኛነት ጋር የተጣመረ በመሆኑ፤ የኛን ቋንቋ ከማይጋራ ወገናችን ጋር አብሮ መኖር አዳጋች እየሆነ መጣ፡፡ ገፍታሪነት፣ አግላይነትና አሳዳጅነት የዘመኑ መገለጫችን ሆነ። ይህም በመሆኑ የአብሮነትና የብሄራዊ አንድነት ስሜታችን እየደበዘዘና የጎጥ፣ የመንደር ማንነታችን እየጎለበተ መምጣቱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡
ቀደም ሲል እንደተጠቆመው መላው አገራችን እሰይ በሚያሰኝ የለውጥ ጉዞ ላይ ነች፡፡ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ሲዳማ ክልል እንዲሆን ዝግጅት ላይ መድረሳችን በአንድ በኩል ትልቅ አስደሳች ክስተት ሲሆን በሌላ በኩል ከባድና ሰፋፊ እድሎችና ተግዳሮቶች ይዞልን መምጣቱን እናስተውላለን፡፡ ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ የተለያዩ ተግዳሮት ቢኖሩትም፣ በዚህ መጣጥፍ ላይ ትኩረት ሰጥቼ የምዳስሰው ጎላ ጎላ ብለው የሚታዩኝን እድሎች ነው፤
በጅምላ ሲታይ፣ ዋናው እድል ካሳለፍነው ጊዜ ሁሉ በተሻለ ደረጃ ቅራኔዎችን አስወግደን የአብሮነትና የጋራ እድገት ላይ እንድናተኩር በር የሚከፍት ጊዜ መምጣቱ ነው፡፡ ሌላው ጎልቶ የሚታየኝ እድል የሲዳማ ህዝብ በአገር ግንባታና በአገራዊ አንድነት ጉዳዮች ላይ፣ ከሌሎች ትልልቅ ማህበረሰቦች እኩል፣ የፊት ወንበር ላይ ተቀምጦ ውሳኔ የመስጠት እድሉ ከፍ ማለቱ ነው፡፡ ይህ እድል ሲዳማ ብለን ከምናውቀው ወሰን የላቀና የመጠቀ በመሆኑ ጮቤ የሚያስረግጥ ቢሆንም፣ ከባድ፣ ከባድ የሆኑ ሃላፊነቶችንም ጨምሮ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ ሃላፊነት ከማንም ይበልጥ በሲዳማ ልሂቃንና የፖለቲካ ቡድኖች ጫንቃ ላይ የሚወድቅ ነው፡፡ አዲሱ ክልል የሲዳማ ዞን ሲሰራበት የቆየውን ፈር ተከትሎ የሚጓዝ ከሆነ ካለፉት የአስተዳደር ውድቀቶች ምንም አልተማርንም ማለት ስለሚሆን በአዲሲቱ ኢትዮጵያ ያገኘናቸውን ድሎች ሳንጠቀምባቸው ይባክናሉ፡፡
ቀዳሚ ሆኖ የሚታየኝ ሃላፊነት በሲዳማ ልሂቃን ዘንድ መተግበር ያለበት ጥልቅ የሆነ የአመልካከት ለውጥ ነው፡፡ እራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር ተዛምደው የመጡ በጣም የተሳሳቱና አግላይ የሆኑ ፖሊሲዎች በዚህ ዞንና በመላ አገራችን ሲተገበሩ ቆይተዋል፡፡ ለምሳሌ በአንድ አገር ውስጥ እንደምንኖርና በአንድ ሰንደቅ አላማ ስር እንደምንተዳደር የተዘነጋ በሚመስል ደረጃ፣ በነጻ አውጭ ግንባር ስም የተደራጁ ፓርቲዎች እስከ አሁን ድረስ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በሲቪል ሰርቪሱም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የብሄረሰብ ስብጥር በፍጹም አይታይም፤ ሰራተኛ ሲመለመል “ምን ችሎታ አለህ” ተብሎ ሳይሆን “ከማን ተወልድክ” በሚል ፖሊሲ ላይ ተመስርቶ የተፈጸመ በሚመስል መልኩ፤ በዞኑ ውስጥ በርካታ ማህበረሰቦች መኖራቸው ባይካድም፤ ሁሉም የሃላፊነት ወንበሮች በአንድ ማህበረሰብ አባላት መሞላታቸው በግልጽ ይታያል። ይህ አግላይና ጎጂ ፖሊሲ በሲዳማ ብሄረሰብ በራሱ ውስጥም ይከሰታል፤ ዜጎች ከተወሰነ አካባቢ ወይም ወረዳ በመምጣታቸው ብቻ አድሎ እንደሚፈጸምባቸው ስንታዘብ ቆይተናል፡፡ ሁላችንም የዚህ ክልል ተወላጆች፤ የዚች አገር ዜጎች በመሆናችን እኩል መብት ሊኖረን ይገባል፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት ሲፈጽሙ ነበር ብለን የወቀስናቸውንና የጠላናቸውን የአግላይነትና የመበላለጥ ስህተቶች መደጋገም ለአገራዊ ግንባታ አይጠቅምም፤ ስለሆነም ሁሉንም ተወላጆች በእኩልነትና ፍትሃዊነት የሚመለከት ሥርዐት መገንባት የአዲሱ ክልላችን ተልእኮ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
በአዲሱ ክልል ውስጥ ፍትሃዊ አስተዳደርን መስርቶ ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ መሆን የሚያስችሉ በርካታ የፖሊሲ ለውጦችን መተግበር አስፈላግ ቢሆንም፤ ለጊዜው አንገብጋቢ የመሰሉኝን ብቻ ልጥቀስ፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ፤ የፖሊሱን ክፍል ጨምሮ ከላይ እስክታች መበወዝ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ባሮጌ አቁማዳ አዲስ ጠጅ አይቀመጥም እንዲሉ፤ አዲሱ ክልል በህዝብ ብብት ስር ተንጠልጥለው፤ ለሙስናና ለድህነትም ምክንያት የሆኑ ሹሞችን ይዞ ለህዝባችን ፋይዳ ሊሰራ አይችልም፡፡ እኒህን በጡረታ አሰናብቶ ሲቪል ሰርቪሱን አዲስ አመለካከትና ትኩስ ሃይል ባለው ወጣት ትውልድ መተካት ግድ ይላል፡፡ ሰው አጣን እንዳይባል፤ የክልላችንም ሆነ የአገራችን ወጣት ዲግሪ ተሸክሞ ስንቱ ነው ለችሎታውና ለብቃቱ በማይመጥን ስራ ላይ የተሰማራ፤ ስንቱ ነው አገር ጥሎ የሚሰደድ፤ ስንቱ ነው የመስራት እድል ተነፍጎት ከቤቱ የተቀመጠ ፡፡ አስተዳደሩን ከማዘመንና ከማጽዳት ጎን ለጎን፣ ሲቪል ሰርቪሱ ሁሉንም ማህበረሰቦች የሚያገለግል እንደመሆኑ መጠን፣ በይዘቱም የክልሉን ህዝብ የሚመስል ሆኖ ቢዋቀር አግላይነትንና፤ ሙስናንና ለመከላከል ምቹ መደላድል ይፈጥራል፡፡ የፍትሃዊ አስተዳደርም ተምሳሌት ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር ማንኛውም በዚህ ክልል ውስጥ ነዋሪ የሆነ ዜጋ፤ ሙያዊ ብቃት እስካለው ድረስ በማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት፣ በማንኛውም የስልጣን እርከን የማገልገል እድል ሊከፈትለት ይገባል፡፡ ማንኛውም የክልሉ ተወላጅ ሕጋዊ መስፈርቱን እስካሟላ ድረስ ለፌዴራል፣ ለክልልና ለከተማ ምክር ቤቶች የመወዳደር መብቱ እንዲጠበቅ በህግ ሊደነገግ ይገባል፡፡ እንዲሁም ማንኛውም የሲዳማ ተወላጅ በማንኛውም የሲዳማ ክልል ወስጥ በሚንቀሳቅስ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ሲቪክ ማህበር ወስጥ ገብቶ የማገልገል መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች በሚለው መርህ መሰረት፤ ከየትኛውም የአገራችን ክፍል የሚመጣ ዜጋ መኖሪያውን በኛ ክልል ለማድረግ ከመረጠ እጃችንና ልባችን ከፍተን ልንቀበለው ይገባል፡፡ ልክ በርካታ የሲዳማ ተወልጆች አዲስ አበባ፣ ደብረዘይት፣ አዳማ ቤቴ ብለው ያለ ስጋት እንደሚኖሩት፡፡
ይህ አሠራር እራስን በራስ ከማስተዳደር መርህ ጋር ይጋጫል የሚሉ ልሂቃን አሉ፡፡ በበኩሌ ምንም ግጭት አይታየኝም፤ በአንድ መንገድ ወይም በሌላ አንድ ኢትዮጵያዊ ግለስብ ውይም ማህበርሰብ መኖሪያውን በዚህ ክልል ውስጥ ካደረገ፤ ያለጥርጥር የዚህ ክልል ነዋሪ ነው፡፡ ስለሆነም ሌሎች ነዋሪዎች ያላቸው መብትና ግዴታ እሱም በእኩል ተመዝኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ መምረጥ፣ መመረጥ፣ ሰርቶ፣ ሃብት ማፍራት፤ እስከከፍተኛው የስልጣን እርከኖች ላይ ሃላፊነት ላይ መቀመጥ፣ ደስ ባለው ስፍራ ላይ ቤት ሰርቶ፣ ልጆች ወልዶ የመኖር መብት አለው፡፡ በአንጻሩ ታክስ መክፈል፣ ክልሉ ወይም አገሩ ለግዳጅ ሲጠሩት ተሳታፊ መሆን የሁሉም ዜጋ ግዳጅ ነው፡፡ ለማጠቃለል አንድ አካባቢ ወይም ግዛት ወይም ክልል እራሱን የማስተዳደር ስልጣን አለው ሲባል፣ ሁሉም በዚያ ግዛት ውስጥ የሚኖር ህዝብ፣ ቋንቋና ጎጥ ሳይለይ፣ በሚመርጠው መንግስት ይተዳደራል ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ የተልያዩ ማህበረሰቦች እኩልነትን ያጎናጽፋል እንጂ፣ አንዱን ከሌላው የሚያስበልጥ መብትና ስልጣን የሚሰጥበት አንዳችም እድል አይኖርም ማለት ነው፡፡
ከዚሁ ጋር ተዳብሎ በሚገባ መፈተሽ ያለበት የፍርድ አሰጣጡ ተቋም ብቃትና ተቋሙን የሚመሩት ሙያተኞች ብቃት ነው፡፡ ከህግ ሙያተኞች አካባቢ በህግ አፈጻጸምና በዳኞች ብቃት ላይ በርካታ ቅሬታዎች ሲነሱ ይሰማል፡፡ በተለይም በዳኞች ሙያዊ ብቃት፣ ስነ ምግባር እጦትና በሙስና መዘፈቅ ጉዳዮች ብዙ ብዙ ቅሬታዎች ይሰነዘራሉ፡፡ ለምሳሌ ብዙ ዳኞችና አቃቤ ህግ አባላት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ፣ ለብ ለብ የሆነ ኮርስ ጨርሰው የተመለሱ በመሆናቸው፣ ብርቱ ጥንቃቄ ለሚጠይቀው የዳኝነት ሥራ ብቃት የላቸውም የሚል ክስ በአንድ በኩል ሲሰማ፤ በሌላ በኩል የፍርድ አሰጣጡም በሙስና የተጨማለቀው በዚሁ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ማንም ተሟጋች ትክክለኛ ፍርድ አገኛለሁ የሚል እምነት እንደሌለው በስፋት ይነገራል፡፡ ፍትህ በደራው ገበያ ላይ የምትሸጥና የምትለወጥ ሸቀጥ እንዳትሆን አጥብቀው ይፈራሉ፡፡ ከብቃት ማነስ ባሻገር የሙያተኞቹም የብሄር ስብጥር አንድ አስጊ ጉዳይ መሆኑ ይነገራል፡፡ አሁን በአገልግሎት ላይ ያሉት ዳኞችና አቃቤ ሕግ ሠራተኞች በሙሉ ወይም በአብላጫ እጅ ከአንድ ማህበረሰብ የመጡ ናቸው፤ ይህ አሰራር ለሌሎች ማህበረሰብ አባላት እድል ከመንፈጉም በላይ፣ አፓርታይድ መሰል ባህሪ አለው፡፡ መፍትሄው ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም፤ ልክ እንደሲቪል ሰርቪሱ ይህንንም ተቋም ከላይ እስከታች መበውዝ ነው፡፡ የሲቪክ ሰርቪስ ኮሌጅ ምሩቃኑ ለሰጡት አገልግሎት በሚልዮን እጥፍ የተከፈሉ በመሆናቸው እነሱን አሳርፎ፤ እሳት የበሉ፣ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁና ብቃት ያላቸው የህግ ባልሙያዎችን በስራው ላይ መመደብ፡፡
ሁለተኛው እድል ኢኮኖሚአዊ ፍትህ መገንባትን የሚመለከት ነው፡፡ ትልልቅ የልማት ፕሮጀችቶችን በሚመለከት ክልሉ ካለፈው ጊዜ የተሻለ የገንዘብ አቅም ይኖረዋል ብዬ ገምታለሁ፡፡ ይሁን እንጂ እንዳለፈው ጊዜ ሹሞች ተቀራምተው የሚበሉት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሲቪክ ማህበራት ተደራጅተው የዚህ አይነት የብክነትና የስልጣን መባለግ አዝማሚዎችን እንዲታገሉ መንግስት ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የፖለቲካ ሹመት፣ ለሹሞች የሚጎመዝዝ እንጂ የሚጣፍጥ እንዳይሆን፣ ታክስ ሰብሳቢነትና ሙስና በክልላችን እንዳያንሰራራ የሲቪክ ማህበራት ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ክልሉም ከምድራችን የሚገኘውን የውሃ፤ የማእድን፣ የመሬትና የሰው ሃይል አስተባብሮ በትልልቅ የልማት ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ህዝቡን ከድህንት አዙሪት ወስጥ ማውጣት ተቀዳሚ ተግባሩ መሆን አለበት፡፡ ለገጠር ልማት ቅድሚያ በመስጠት የጎዳና ተዳዳሪነትን ምንጭ ማምከንና ድህነትን ማጥፋት ይቻላል፡፡ የዛሬ አስር ዓመት ልጆቻችን የጎዳና ተዳዳሪዎች ሳይሆን፤ የአገራችን ፈርጥ ሆነው የምናጌጥባቸውና የምንኮራባቸው እንዲሆኑ ሁላችንም በርትተን መስራት ይኖርብናል፡፡ ህዝባችንን ከድህነት የማውጣቱ ተልእኮ በተቀዳሚ የክልሉ ሃላፊነት ነው ቢባልም፤ ህብረሰቡም ዓይንና ጆሮውን ከፍቶ በንቃት ሊከታተል ይገባል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ብዙ የልማት ፕሮጀችቶች ተዘርፈዋል፤ ከእንግዲህ አናሰርቅም ብለን ዘብ መቆም አለብን፡፡
ከዚሁ ከኢኮኖሚው ሳንወጣ አንድ ቀረብ ብለን ልናየው የሚገባ ዘርፍ አለ፤ ይከውም በተልምዶ የትናንሽና መካከለኛ ኢንዱስትሪ የሚባለው የንግድ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ የንግድ ዘርፍ በክልላችን ዋነኛው የግል ባለሃብቶች የተሰማሩበት የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ ከትናንሽ ሱቆችና ወፍጮ ቤቶች እስከ ትልልቅ ሆቴሎች በዚሁ ዘርፍ ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከእርሻና ከግንባታ በመለስ የክልሉ መንግስት ዋነኛው የገቢ ምንጭም ይኸው ሴክተር ነው፡፡
ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓምታት ወዲህ ይህ ሴክተር ከባድ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ከዚያ በፊት በዘመነ ወያኔ በሙሰኛ ታክስ ሰብሳቢዎች ሲዘረፉና የንግድ ተቋማቸው ሲዘጋ ሲከፈት ኖረዋል፡፡ አሁን ደግሞ የንግዱ ማህበረስብ ከሁለት አቅጣጫ በተወነጨፉ መቅሰፍቶች ክፉኛ እየተጎዳ ነው፡፡ አንደኛው በተለይም ሃዋሳ ከተማንና አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎችን ያጠቃው፤ በማህበርሰቦች መካከል የተከሰተው ግጭት ሲሆን፤ ሁለተኛው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር አቀፍ ደረጃ ተከስቶ እንቅስቃሴን እስከማቆም የደረሰው የኮሮና ወረርሽኝ ነው፡ በዚህም የተነሳ የንግድ ቤቶች በብዛት እየተዘጉ ናቸው፡፡ ሃዋሳ በተለይ ትልልቅ የንግድ ተቋሞች ሥራ ስለሌለ ለቤት ኪራይና ለሠራተኛ የሚከፍሉት ስላጠራቸው የንግድ ተቋማቸውን በመዝጋት አፋፍ ላይ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ ከግል ባለሃብቶች አልፎ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቤተሰቦችንና የመንግስትንም ገቢ በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ የሚጥል ውጤት ይኖረዋል፡፡
ስለሆነም አሁን መላው ህብረሰብ፣ ማለት መንግስትና ህዝቡም አፋጣኝ መፍትሄዎችን በመፈለግ ላይ መረባረብ አለብን፡፡ የኮሮናን ወረርሽኝ ለመከላከል ከምናደርገው ጥረት ጎን ለጎን ለኢኮኖሚውም ትኩረት ሰጥተን በክልላችን ኢንቨስተሮች ላይ ካንዣበበው አደጋ መታደግ ይጠበቅብናል፡፡ በበኩሌ የንግዱን ማህበረሰብ ከኪሳራ ለማዳን ይጠቅማሉ ያልኳቸውን መፍትሄዎች እነሆ፤
1ኛ፡ የክልሉ ወይም የከተማው አስተዳደር( ወይም ሁሉም በጥምረት) የንግዱን ማህበረሰብ ተግዳሮት የሚያዳምጥና መፍትሄዎች የሚያቀርብ ኮሚሽን ማቋቋም
2ኛ፡ የክልልና የከተማ መስተዳደሮች ውዝፍ ያልተከፈሉ ታክሶችን ሙሉ በሙሉ መሻር
3ኛ፡ ትልልቅ አከፋፍዮች ለትንንሽ ነጋዴዎች በዱቤ ያቀርቡትን የእቃ ዋጋ በረዥም ጊዜ እንዲከፈል አዲስ ውል መፈራረም
4ኛ፡ በክልልና በከተማ ደረጃ ያሉ የመንግስት አካላት የሚያስከፍሉትን ታክስ መጠን በጣም መቀነስ ወይም ሁኔታው እስኪሻሻል በእንጥልጥል ማቆየት
5ኛ፡ በመጨረሻም የግል ባንኮች እስከዛሬ በነጋዴውና በተራው ህዝብ ጫንቃ ላይ ፋፍተዋል፣ በቅርንጫፍ ላይ ሌላ ቅርንጫፍ ገንብተዋል፤ እግዜር ይመስገን በብዙ ሚሊዮኖች አትርፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ እሰይ የሚባል የመልካም ስራ ውጤት ነው፡፡ ከዚያም በዘለለ ልብን በደስታ የሚሞላው እንዲህ እንደ አሸን የፈሉት ባንኮች የኢትዮጵያ ዜጎች ንብረት መሆናቸው ነው፡፡ ታዲያስ ጎበዝ እንረዳዳ እንጂ ብለን እጃችንን ወደነሱ መዘርጋት በእንዲህ ያለው ክፉ ቀን የሚያስከፋ አይደለም፡፡ በመሆኑም አንድ ትልቅ ጥሪ ለሁሉም የግል ባንኮች እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፤ እኔ በምኖርባት በውቢቱ ሃዋሳ ከተማ በርካታ የንግድ ተቋማት፣ ከላይ እንደጠቀስኩት በአዳጋ ላይ ናቸው፤ መንግስት ሃላፊነት ስላለበት የንግዱን ማህበረሰብ ለመደገፍ ብርቱ ጥርት ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ባንኮች በበኩላቸው ሊያደርጉ የሚችሉት ብዙ፣ብዙ በጎ ነገር እንዳለ ቢታወቅም፤ ቀጥሎ የተጥቀሱት ሁለት ሃሳቦች ደግሞ በቀላሉ ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡ ሀ/ ብዙ ነጋዴዎች ወለድ የሚያስቆጥር የባንክ እዳ እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ባንኮቹ እዳውን ሙሉ በሙሉ መሰረዝ ቢችሉ መልካም ነው፡፡ ይህ አማራጭ የማይቻል ሆኖ ከተገኘ፣ እዳው ከወለድ ነጻ ሆኖ በረዢም ጊዜ እንዲከፈል ማድረግ ይቻላል፡፡
ለ/ ብዙ ሆቴሎችና የንግድ ተቋማት ገቢያቸው ስለተቋረጠ ለኪራይና ለሠራተኛ የሚከፍሉት ገንዘብ እየቸገራቸው ነው፡፡ ለሚፈልጉ ነጋዴዎች ባንኮች የረዥም ጊዜ ብድር ቢያቀርቡላቸው ለብዙ ቤተስቦች የመኖር ዋስትና እንደመስጠት ይቆጠራል፡፡ ለእንዲህ ያለው ብድር ወለዱ መጀመሪያ ዜሮ ቢሆንና ሁኔታው እየተገመገመ ቀስ እያለ ወለዱ ቢጨምር ተመራጭ ይሆናል፡፡
(ክፍል 2 ይቀጥላል)