ኦሞ የኢትዬጵያ አንድነትና ፍትሕ ማዕከል

June 16, 2020

እናት አገራችን ኢትዮጵያ የጥንታዊ ታሪክ መዘክር የሰው ዘር መገኛ ስትሆን ፤ በመላ ህዝቦችዋ ጀግንነትና አንድነት በቅኝ ገዥዎች እጅ ሳትወድቅ ነፃነትዋን ጠብቃ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ተምሳሌት በመሆን ታፍራና ተከብራ የቆየች ታሪካዊና ጥንታዊ ሀገር ነች።

ሆኖም ላለፉት 27 ዓመታት በህወሀት/ኢህአደግ የአገዛዝ ዘመን ሀገሪቱን በቋንቋና በዘር ብቻ በማካለል ፌዴራሊዝም ሸንሽኖ በህዝብ መሀል ጥርጣሬ እንድነግስና የሰው ልጅ ሰው መሆኑን ረስቶ ለዘሩና ለጎሳው ብቻ እንዲያስብ አድርጎታል።

አሁን በአራቱ የአገሪቱ ማዕዘናት ከኢትዬጵያዊነት ብሔረተኝነት ወጥቶ የማንነትና የግለኝነት ጥያቄዎች በእጅጉ ገነው እንዲወጡ ተደርገዋል! በመሆኑም ባለፉት 27 ዓመታት ተወልደውና ተኮትኩተው ያደጉ ለእናት አገራቸው ብዙም ኃላፊነት የማይሰማቸውና ይህንኑ የአካባቢ ብሔረተኝነት የሚያስተጋቡናት ይህንንም ተከትሎ  ፅንፈኝነት የተፀናወታቸው ቡድኖች እንደ አሸን እንዲፈሉና እንዲጠናከሩ በመደረጉ ኢትዬጵያዊነት ከቶውንም እንዲዳከም የሕወኃት/ኢህአደግ አገዛዙ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ፤ በዚህም መንስኤነት ከዚህ በፊት ለዘመናት በኢትዬጵያዊነት አንድ ሌላው አካባቢ አብሮ ይኖር የነበረው ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ሰላም ርቆት በግጭትና አለመረጋጋት ለዘመናት ከኖረበት ቀዬው መፈናቀል የዚህ ውጤትም መሆኑን ማጤን ይገባል፤

የደቡብ ኢትዮጵያ ብሄረሰቦችም የህወሀት/ኢህአደግ ፓለቲካ ሰለባ በመሆን እርስ በእርስ እንዲጋጩና እንዲገዳደሉም ተደርገዋል!

በተለይ በጅምሩ ወጋጎዳ የተሰኘ የቋንቋ ማዳቀል የህወሀት/ኢሕአደግ ፕሮጀክት ሳቢያ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ጋሞንና ወላይታን አጋድሏል አፈናቅሏል ፤ በሲዳማ የክልል ጥያቄ በሎቄ በሕወኃት/ኢሕአደግ ህዝብ ተጨፍጭፋል! ይህን ሁሉ እዳ የተሸከመው የደቡብ ህዝብ አሁን በሚታየው የለውጥ ጭላንጭል አንፃራዊ የዲሞክራሲያዊ መብቱን እንዳይጠቀም እየታወከ ነው፤

በሰሜን አሜሪካ የጋሞን ፣ ወላይታንና ዳውሮ ነዋሪዎች በማካተት የተመሠረተው ( የኦሞ ኢትዬጵያ አንድነትና ፍትህ ማዕከል ) በሕጋዊነት ተመዝግቦ የኦሞ ተፋሰስ አካባቢዎች በባሕልና ቋንቋ ትስስር አብረው እንደኖሩ ሁሉ ይህ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዓላማና ራዕይ ቀርፆ የበኩሉን ሚና ለመጫወትና ለአገራችን ኢትዬጵያ ሰላም ድርሻውን ለመወጣት የበኩሉን ጥረት የሚያደርግ ሲብክ ድርጅት ነው!

ተጨማሪ ያንብቡ:  እኛ እና እናንተ በምንም አንገናኝም| ኮ/ል ደመቀ ስለወልቃይት | COLONELL DEMEKE ZEWDU | WELKAYIT AMHARA | ETHIOPIA

በመሆኑም አካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ ጥያቄዎቹም ምላሽ እንዲያገኙ ዜጎች ፓለቲካዊ አጀንጃ ያላቸውን ካድሬዎች ግፊትና ቅስቀሳ ሳይዋከብ ኃላፊነት ባልጎደለው መንፈስ ለጋራ ዕድገትና ብልፅግና በሚመች መልኩ የጋራ ትስስር ካለቸው የጋሞና ዳውሮ ሕዝቦች ጋር በመምከር መፍትሔ እንዲኖረው ማድረግና ድር ብያብር እንዳሉት የአባቶቻችን ቢሂል ያሉንን ሃብቶች እውቀትና የሰው ኃይል በጋራ በማድረግ አንድ አካባቢ ያጣውን ሃብት ከኩታ ገጠሙ በሟሟላት የጋራ ዕድገትን ዕውን በማድረግ ለትውልድ ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ለአገራችንም የጋራ ዕድገት አሻራችንን ማሳረፍ ይቻላል። የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አስተዳደር ከ 56 የአካባቢው ብሔረሰብ የተውጣጡ 87 የሰላም አምባሳደሮች ጥናትና የውሳኔ ሃሳብ መነሻነት ከጋሞ ወላይታና ዳውሮን የፓለቲካ ተወካዬችን ጭምር በጋራ ዕልባት ለማግኘት ማወያየታቸውን ተከታትለናል።

በታሪክና በባሕል አብሮ ተስማምቶ በመኖር የሚታወቀውን የኦሞ አካባቢን ሕዝብ የበለጠ ለጋራ እድገት ጥረት መደረግ ባለበት በዚህ ወቅት ጭራሹኑ አብሮነትን የሚሸረሽር ሐሳብ ይዘው ብቅ ያሉ አንዳንድ የወላይታ ተወላጆች እንዳሉ ተረድተናል::

እነዚህ ቡድኖች አካባቢው በአንድ አስተዳደር ስር እንዲሰባሰብ ቀደም ሲል በደርግ ዘመንና በአሁን ወቅትም ባለው አገዛዝ በጥናት ተደግፎ የቀረበውን የኦሞ አካባቢ ማሕበረሰብ አንድነት ክልል በመቃወም ለልዩነት የተበጀውን የሕወኃት/ኢሕአደግ ሕገመንግሥት የሙጥኝ በማለት ወላይታ ብቻውን አንድ ክልል እንዲሆን አጥብቀው እየጠየቁ ነው::

የወላይታ አርቆ አስተዋይ ሕዝብ ለሕዝቦች አብሮ መኖር ፋይዳ የማይሰጠው የሕወኃት/ኢሕአደግ ሕገመንግሥት መንፈስ በመከተል ለብቻችን ክልል እንሁን ጥያቄ ሥፍራ ባለመስጠት ኃላፊነት በተሞላው ስሜት ለዚህ ሕዝብና መጪው አዲሱ ትውልድ ከአጎራባች ወገኖቹ ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ መኖር ያለውን ከፍተኛ ታሪካዊ ትስስርና ፋይዳ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለመሆኑ እኛ ዐማሮች ምን እስከምንሆን እየጠበቅን ይሆን? - ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

በወላይታ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ጥበት እንዳለና በዚህም ሳቢያ አካባቢው የሚመካበት ሌላ አጥጋቢ የምጣኔ ሃብት ባለመኖሩ እጅግ ከፍተኛ ሥራ አጥነት እንዳለ ይታወቃል ፤

በዚህም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት 106 ሺህ የሚገመቱ ከከፍተኛ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተመርቀው በአካባቢው በቂ ሥራ በማጣት እንደሚኖሩ ስንገነዘብ ጥቂቶች ደግሞ በማህበር ተደራጅተው ከሙያቸው ውጪ በኮብል ድንጋይ ንጣፍ ስራ መሰማራታቸውን ይታወቃል! ይህ እያንዳንዷ ቤት የዚህ ሥራ አጥ ማህበራዊ ችግር ሰለባ መሆኑ እንደ አባቶቻችን ቢሂል ለቀባሪ እንደማርዳት ነው። ገበሬው በካድሬዎች የመሬት ቅርምት ጭምር በእርሻ መሬት ጥበት እየተፈናቀለ ወደ ከተሞች በመፍለስ በወላይታ አካባቢ ሥራ በማጣት በአዲስ አበባ ፣ ሻሸመኔና ፣ አዋሳ ወዘተ ከተማዎችን በመቶ ሺዎች በማጣበብ በጎልበት ሥራና በሊስትሮነት ለመተዳደር መገደድ የአደባባይ ምስጥር ነው።

በአሁኑ ወቅት ለብቻችን ክልል እንሁን ጥያቄ ለሕዝቡ ማሕበራዊ ችግሮች እንዳችም መፍትሄ ማቅረብ የማይችል ባዶ ተስፋ መሆኑን ሕዝባችን በጥንቃቄ እንዲገነዘብ እንሻለን!

በሌላ አንፃር ይህ በሂደትም ምንም ሃብት ምንጭ በሌለበት ማህበራዊ ችግርችንን ካለመፍታቱም ለአካባቢው ሰላምና ማሕበራዊ ዕድገትና ትስስር ፋይዳ የማይሰጠውን ” ክልል ወይም ሞት ” እኩይ አላማ የሚያጦዙት ወገኖች መቀሌ የከተሙት እንደመሆናቸው የእነርሱንም ተልዕኮ የሚያስፈፅሙት ደግሞ ከአንተው አብራክ የወጡ ይህንን የክልል ጥያቄ አርቆ አስተዋይነት በጎደለው ሁኔታ ( መናን ከሰማይ እንደሚወርድ ) አድርገው የሚያዋክቡህ ምናልባትም በዚህ ሂደት ስኬት ለአካባቢው ዕድገትና ሰላም ቦታ ሳይሰጡ የግል ጥቅማቸውንና በተለይም ስልጣንን ግባቸው ያደረጉ ጥቂት ወገኖች መሆናቸውን የወላይታ ሕዝብ በጥልቀት ሊገነዘብ ይገባል ።

በአሁኑ ወቅት መንግሥትና ሕዝብ በሕዳሴው ግድብ ዕውን ለማድረግ ጥረት በሚያደርግበትና ባላንጣችን ግብፅ ውኃችንን እንዳንጠቀም በምትፎክርበት እንደዚሁም ዓለማችንን ያወከው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሕዝባችን ላይ ብዙ ሞትና ጉዳት ሳያስከትል ለመመቋቋምና ለመከላከል ከባድ የሞትና የሽረት ትግል ትኩረት በማድረግ በሚሠራበት ወቅት ሕዝብን የሚከፋፍል አጀንዳ ሥራ ላይ ካልዋለ ብሎ ተጽእኖ ለማሳደር መሞከር የአካባቢውን ሰላምና ወደሚያውክ ቀውስ መግፋት በታሪክ ትዝብት ላይ የሚጥል መሆኑን መገንዘብ ይገባናል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠት ዕውቀት መር ትውልድ ለመፍጠር ይሰራል

ስለዚህ ወላይታ ለብቻ ክልል ይሁን የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው ለሕዝቦች ሰላምና የጋራ ትስስር ደንታ በሌላቸው የተፀነሰና የተዘራ እንክርዳድ መሆኑን ተገንዝቦ መንግሥት በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር በአባቢያችን ካሉት የጋሞና የዳውሮ እንዲሁም አጎራባች ወገኖቻችን ለዘመናት አብረው የኖሩበትን ትስስር ከግምት በማስገባት ለወደፊት ለሰላማችን ፣ ለጋራ ዕድገትና ብልፅግና ትልቅ ስፍራ በመስጠት አስተዋይነት ያለው ውሳኔና ድምዳሜ እንዲደረስ ሕዝባችንን እናሳስባለን ።

በዚህ አጋጣሚ ከላይ በመግቢያችን እንደጠቆምነው የኦሞ አንድነትና ፍትህ ማዕከል በወላይታ በጋሞና የዳውሮ ተወላጆች የጋራ ጥረት በሰሜን አሜሪካ የተመሠረተ ከማናቸውም ፓለቲካ ድርጅትና ፍላጎት ነፃ በመሆን የተቋቋመና በዚሁ መንፈስ በሕጋዊነት የተመዘገበ ድርጅት እንደሞሆኑ

ይህ አካባቢ ማሕበረሰብ ለዘመናት አብሮ የነበራቸውን ትስስር በማጠናከር በሰላምና አብሮነት ለጋራ ብልፅግናና ማሕበራዊ ትስስር እንዲሰሩ ግቡና ዓላማው በማድረግ የተመሰረተ ይህም ሰላም ለእናት አገራችንም አስተዋፅኦ እንዲኖረው  ይህ ዓላማው መሬት ወርዶ እነዚህ ኩታ ገጠም ሕዝቦች በቀደሙት 27 ዓመት የተካሄደውን ልዩነት በመስበር በጋራ እንዲኖሩ መጭው ትውልድም ይህ መሠረት ስር ሰዶ እንዲመቻችለት የበኩላችንን ድርሻ የምናበርከት መሆኑን እናረጋግጣለን።

 

ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር

ኦሞ ኢትዮጵያ አንድነትና ፍትህ ማዕከል

ሰሜን አሜሪካ

 

OMO Ethiopia Unity and Justice Center.

4017 Harvest Run Clarkston, GA 30021 USA,

Phone 1+571- 470-2353, Email info@omoethiopia.org OR terotemamo@gmail.com,

Website OMOEthiopia.org

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share