የኢትዮጵያ ዓመታዊ የቢሊዬን የዛፍ ችግኞች ተከላና ውጤቱ – ሰርፀ ደስታ

በኢትዮጵያ ላለፉት 10 ዓመታት በላይ በርካታ የዛፍ ችግኞች እየተተከሉ እንደሆነ ሲዘገብ ቆይቷል በዚህም ዓመት 5ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዟል፡፡ የዛፍ ችግኞች መተከሉ ተነሳሽነት ከመልካም ጎን የሚቆጠር ሆኖ ተተከል እየተባለ የሚገለጸው ቁጥር አሳማኝነቱ አጠያያቂ ብቻም ሳይሆን ውጤቱ የማይታይ መሆኑ ግልጽ በሆነ የቁጥር ጫወታ የተባለውም ልማት ሳይሰራ ብዙ ንብረትም ዓላግባብ እየባከነ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ቁጥርን አጋኖ ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ በግብርናው ብዙ ዓመረትን ወደ ውጭ ሳይቀር እናስወጣለን ተብሎ በተነገረበት በዛው ዓመት ብዙ ሕዝብ ሲራብ አይተናል፡፡ ቢያንስ ላለፉት 5 ዓመታት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሁለት ቢሊየን ያላነሰ የዛፍ ጭግኞች እየተተከሉ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ዓመታዊ ተከላው ሁለት ቢሊየን ነው ብንል እንኳን ባለፉት 5ዓመታት ብቻ ቢያንስ ከአራት ሚሊየን ሄክታር የማያንስ ተከላ ተካሂዷል፡፡ ዘንድሮ የታሰበው የአምስት ቢሊየን የዛፍ ችግኝ ተከላ ብቻውን ሁለት ሚሊየን ሄክታር መሬት የሚሸፍን ነው፡፡ ሆኖም ባለሙያዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ በዓመት ወደ 70ሺ ሄክታር የተጣራ የደን ውድመት የሚደርስባት ዓገር ስትሆን በአጠቃላይ የገበሬውን ጨምሮ በሰው ሰራሽ ተከላ ያለው የደን ይዞታ ከ1 ሚሊየን ሄክታር የሚበልጥ አደለም፡፡

እንግዲህ በቢሊየን ቁጥር ችግኝ እንተክላለን ማለቱ ውጤቱ የማይታይ ለሪፖረት የቀረበ ቁጥር መሆኑ ብቻም ሳይሆን እንዲህ ባለ የተሳሳተ ሪፖረት በማቅረብ ብቻ ብዙዎች የሚወደሱና የተሻለ ቦታ በመንግስት መዋቅሩ እያገኙ መምጣታቸው እንደ አገር ሲታሰብ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡ በውሸት መረጃ ተጠያቂነት ባለመኖሩም ዓመቱን ሙሉ ባልተሠሩ ሥራዎች የአገር ሀብት ሲባክን ቆይቶ በመጨረሻ በወረቀት ላይ ትልልቅ ቁጥር ማቅረብ እንደልዩ ባሕል እያደገ የመጣ ችግር ነው፡፡ ይሄ ዓይነቱ ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት ሥር የሰደደ ስለሆነ አሁን ሁሉም የለመደው ይመስላል፡፡ ውጤቱ ግን ለአገር ውድቀት ነው፡፡ ይሄ አይነት ሪፖረት በችግኝ ተከላው ብቻ ሳይሆን በሁሉም በሚባል ደረጃ የመንግስት መዋቅሮችን የተጠናወተ ችግር ነው፡፡ ቢያንስ ከአሁን ጀምሮ ቢታሰብበትና ሰዎች በመዋሸታቸው ሊጠየቁ የሚችሉበት ሁኔታ ቢኖር ይላሉ ባለሙያዎች፡፡ሁሉም ተጠያቂ መሆን ቢችል ቢያንስ ላልሰራው ሥራ የሐሰት ሪፖረት ማቅረብን ባልደፈረ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የእኔና ቤተሰቦቼ ህይወት አደጋ ላይ ነዉ - ፖለቲከኛ ዳንዔል ሺበሺ

ደንን አስመልክቶ በየዓመቱ በቢሊየን ችግኝ የሚተክል አገር በዓለም የለም፡፡ የብዙ አገራት የቢሊየን ይቅርና የሚሊየን የዛፍ ችግኝ ተከላዎች የብዙ ዓመታት እቅድ ነው፡፡ በእኛው አገር ግን ዛሬ እንኳን አገራት ሁሉ ታላላቅ እቅዶቻቸውን ሳይቀር በዓለም ዓቀፉ ወረርሽኝ  ምክነያት እያጠፉ ባለበት ሁኔታ ከአምናውም ከፍ አድርገን የ5ቢሊየን ችግኝ ተከላን እንደሚተገበር በሰፊው እያወራን ነው፡፡ እንዲህ ነው የሆነው! ያለ እቅድ የሚመራ አገር ይፈርሳል የሚለው የኢዝራኤሉ የስለላና ደህንነት ድርጅት ሞሳድ ልዩ ቃል (ሞቶ)ን ያስተውሉ፡፡

አመሰግናለሁ!

ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን! ኢትዮጵያን ይጠብቅ! አሜን

 ሰርፀ ደስታ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share