በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተገደለችው የወጣት ሃይማኖት በዳዳ ተጠርጣሪ ገዳይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡

፡የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ደግነት ወርቁ የተባለ ወጣት ነው የ27 ዓመቷን ሃይማኖት በዳዳ ሕይወት በማጥፋት የተጠረጠረው ብሏል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፡፡
ትናንት ምሽት 1 ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ባካሄደው ክትትል ነው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡
ቀን ከሌሊት በተካሄደው በዚህ ክትትል የተያዘው ወጣቱ ደግነት ወርቁ ከሟች ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ እንዳልነበራቸው ትናንት እስከ እኩለ ሌሊት በተደረገ ምርመራ የወንጀሉን ዝርዝር ለፖሊስ አስረድቷል፡፡
ግለሰቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርና የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ስለሆንኩ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች ይረዱኝ በማለት ወደ ግቢው በተለያዩ ጊዜያት ይመላለስ እንደነበር ዘርዝሯል፡፡
ከዚያም በግንቦት 17 ቀን 2012 እንደልማዱ ለዚሁ ጉዳይ እንደመጣ ገንዘብ እንደተቸገረና ቢላዋ ይዞ በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎች በአንዱ ላፕቶፕ ወይም ሞባይል ካገኘ ሰርቆ ሽጦ ለመጠቀም ሲዟዟር የሟች ክፍል ክፍት በመሆኑ መግባቱን አስረድቷል፡፡
ሟች ሞባይሏን እንድትሰጠው ጠይቋት እምቢ ስትለው መታገላቸውንና ከዚያም በያዘው ስለት ወግቷት ንብረቱን ይዞ መውጣቱን ተናግሯል፡፡
ፖሊስ ከሟች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው 12 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ተጨማሪ ምርመራ ማድረጉን የግድያ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለኢቲቪ ገልጿል፡፡
ለፖሊስ ምርመራ ትልቅ አቅም የሆነው የሟች ወላጅ አባት ከሳምንት በፊት ለልጃቸው የሰጧት የ5 ሺ ብር ቼክ ነው፡፡
ገዳዩ በወቅቱ የሟችን ላፕቶፕና ሞባይል ፓስፖርት መታወቂያና ይህንን ቼክ ወስዶ ስለነበር ቼኩን የካ አካባቢ በአንድ ባጃጅ ተሳፍሮ አሽከርካሪውን መታወቂያ ስላልያዝኩ በአንተ መታወቂያ ይህንን ብር አውጣልኝ ብሎት የባጃጅ ሹፌርም መልኩን አስተውሎ ስለነበር ምርመራው ከዚህ እንደጀመረ ፖሊስ ገልጿል፡ ኮሚሽኑ በወቅቱ የሆስፒታሉ ሴኩሪቲ ካሜራ አፕዴት ሳይደረግ ከአገልግሎት ውጪ መሆኑንና የጥበቃ ሰራተኞችም ቢላዋ ተይዞ እስከሚገባ ፍተሻቸው አጋላጭ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
EBC
ተጨማሪ ያንብቡ:  የጠለምትና የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የጎንደሬዎች . . .(አንዱዓለም ተፈራ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share