ሕወኃት – ጨዋታው እያበቃ ነው!!! Game Over!!  የሕወኃት መፍረክረክ የቅርብ ጊዜ ምልክቶች፣ መንስኤዎችና አንደምታዎች

አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ – ግንቦት 18/2012

መንደርደሪያ

አንባቢ ይህን ርዕሥ ብቻ አይቶ ለድምዳሜና ለመሳሳት አላግባብ የደፈርኩና የቸኮልኩ ባይመስለው ደስ ይለኛል፡፡ “ጌም ኦቨር” በሚለው እይታና ድምዳሜዬ ላይ ለመድረስ “ትንሽ አልቸኮልክም ወይ” በሚል ገና ከወዲሁ በመፍረድ (Judge) አንባቢ ራሱ የቸኮለ እንዳይመስልበት ይጠንቀቅ፡፡ የሕወኃትን መፍረክረክና የህልውናዋ ጉዳይ የመጨረሻው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ ምልክቶች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም ጎልተው መታየት ጀምረዋል፡፡ የነዚህን ምልክቶች የአሁን መንስኤዎችና አንደምታቸውንም የሚጠቁሙ ዓለማቀፋዊ፣ ቀጠናዊ፣ ብሔራዊና ክልላዊ መልክ ያላቸው በርካታ ኩነቶች አሉ፡፡ አንባቢ ከወዲሁ ፍርድ ከመስጠቱ በፊት በዚህ ጽሁፍ የዘረዘርኳቸውን ጠቋሚ ነጥቦች በሙሉ እንዲያያቸው በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

 • በርዕሱ ላይ እንደተመለከተው “የቅርብ” (ምልክቶችና መንስኤዎች) የሚለው የጊዜ ማዕቀፍ የሚሸፍነው ያለፈውን አንድ-ሁለት ወር ጊዜ ነው፡፡ (ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ግንቦት አጋማሽ / 2012 ዓ.ም ያለውን ማለት ነው)፡፡
 • በዚህ መጣጥፍ ሕወኃትን “አንቺ” የምለው ለሌላ ሣይሆን የተጋሩ ወገኖቼን አጠቃቀም ኮርጄ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕወኃት የመጨረሻው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንድትገኝ አስተዋጽኦ ያደረጉ የምላቸውን የሩቅና የቅርብ ሁነቶች፤ ዕውነትም መጨረሻዋ ደርሷል ያስባሉኝን ጠቋሚ ምልክቶችና አንደምታቸውንም በጂኦግራፊ ተዋረዳቸው እንደሚከተለው ነካ – ነካ አደርጋለሁ፡፡

ዓለም አቀፍ፡

 • ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር በስልክ መወያየታቸውና ከጥቂት ቀናት በኋላም ዋና ጸሐፊው የተቋረጠው የአባይ ግድብ ድርድር እንደገና በሦስቱ ሐገሮች መካከል እንዲጀመር (ግብጽን) መምከራቸው፤
 • የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ኢትዮጵያ የአባይን ውኃ በአግባቡ ለመጠቀም ተፈጥሮአዊና ሕጋዊ መብት እንዳላት ዕውቅና መስጠቱና ተመሣሣይ መልእክት ማስተላለፉ፤
 • ዓለም ባንክ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዕርዳታና ብድር ለኢትዮጵያ መፍቀዱ፤
 • የኢትዮጵያና የአሜሪካ መንግሥታት የ230 ሚሊዮን ዶላር የልማት ትብብር ስምምነት መፈራረማቸው …
 • የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ሪቨረንድ ጄስ ጃክሰን፣ ግብጽ የኢትዮጵያን በውኃዋ የመጠቀም የተፈጥሮ መብቷን መጋፋቷንና የቅኝ ግዛት ውሎቿን ለመጫን መሞከሯን እንድታቆም የአሜሪካ ጥቁር የምክርቤት አባላት ክንፍ ግፊት እንዲያደርግ መጎትጎታቸው፤
 • ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይና ከፍተኛ የአመራር ቡድናቸው ከቱርክ ከፍተኛ መሪዎች ጋር የ”ምክክር” መድረክ፣ ከሱዳን መሪዎችም ጋር መሰል ስትራቴጂያዊ ውይይት ማድረጋቸው …
 • መሐመድ አል-አሩሲን የመሰሉ ትንታግ ኢትዮጵያውያን በተለይ በአረቡ ዓለም የኢትዮጵያን ጥቅም ወክለው ሲያደርጉት የቆዩት ሙግትና እየፈጸሙት ያለው ገድል በመንግሥት፣ በባለሙያዎችና በህዝብም ዕውቅናና ድጋፍ እያገኘ መምጣቱ፤

 

ቀጠናዊ፡

 • የግብጽ ባልተጠበቀ ሰዓትና ሁኔታ ወደ ድርድሩ ለመመለስ መፈለግ፣
 • ከተደጋጋሚ ውይይት በኋላ ሱዳንም ነበራት የተባሉትን ጥያቄዎችና ብዥታዎች በማጥራት ወደቀልቧ ለመመለስ መቻሏ፤ ሱዳን በርካታ ጫናዎችና ማባበያዎችን መቋቋም መቻሏን መገመት ይቻላል፤
 • ሕወኃት 22 ሚሊዮን ዶላር ቁማር ተበላችበት የተባለለትና የከሸፈው ፕሬዚዳንት ኢሣያስን የመግደል ሙከራዋ፤
 • የኤርትራ የመከላከያ ሠራዊት ዋና ኃላፊ የመጀመሪያውን የውጭ ሐገር የሥራ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ማድረጋቸውና ኤርትራና ኢትዮጵያ ይፋዊ በሆነም ባልሆነም መልኩ በከፍተኛ ቅርበትና ትብብር እየሠሩ መገኘታቸው፤
 • ስለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዕውነታ ለመላው የአፍሪካ (ለእስያም) አምባሳደሮችና ለተፋሰሱ ሐገራት ዝርዝር ማብራሪያ መሰጠቱና የኢትዮጵያን ቁርጠኛ አቋም ለወዳጅም ለጠላትም ግልጽ መደረጉ፤

 

ብሔራዊ፡

 • ስለቀድሞው የብሔራዊ ደህንነት ሹም በዚህ ሰሞን ከየአቅጣጫው እየሰማን ያለነው ዜና ምንድነው? “የማይታየው ሰው (The Invisible Man) በምስጢራዊ የስለላና የመረጃ ቅብብል መረብ እጅ ሊወድቅ እንደሚችል እንዴት አልገመቱም” ነው ያለው? ይህ ዕውነት ከሆነ ትርጉምና አንደምታው እጅግ ሰፊና ሩቅ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሣይሆን ዛሬ ከሕወኃትና ከትግራይ ክልል ጋር በተገናኘ የምናያቸው በርካታ የማይገናኙና ድንገቴ የሚመስሉ ክስተቶች ባጋጣሚ የተከሰቱ ነገሮች እንዳልሆኑ መገመት ከባድ አይሆንም፡፡
 • የሕወኃት ልዩ ልዩ ቀጠናዊ፣ ብሔራዊና ክልላዊ ሤራዎችና የማተራመስ ዕቅዶች አስቀድመው በተደጋጋሚ መጋለጣቸውና የተሞከሩትም በአብዛኛው እየከሸፉ መሆናቸው፤ የሶማሌ ክልልን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፤
 • ብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፉን ተቀባይነት፣ አቅምና የማያወላውል አቋም (Integrity) ባላቸው የትግራይ ልጆች (በአብዛኛው ወጣቶች) አደራጅቶ በጥሩ ቁመና ወደሥራ መግባቱ፤
 • ሕወኃት የምትመካበትና የምታጭበረብርበት የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት (ታዬ ደንደዓ “የተደጋፊ ደጋፊዎች” ይላቸዋል) ከነመሪዎቹ ሕወኃትን ከድቶ አዲስ አበባ መግባቱ፣ ሕወኃትን ማጋለጥ መጀመሩ፤
 • ኦነግ፣ ኦብነግና ሲአንን የመሰሉ የብሔር ድርጅቶች ከሕወኃት ጋር አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸው፤
 • ኦፌኮ አባል የሆነበትና በአሁኑ ወቅትም የሚመራው “መድረክ” ራሱን ሊያጠራ ወይም ሊለይለት ስለመሆኑ ከመሪዎቹ ፍንጭ እየተሰማ ነው፡፡ ኦፌኮን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እጅግ ያስጨነቀው ነገር አለ? ምንድነው? የኦፌኮን ጭንቀት የሕወኃት ህልውና የመጨረሻው መጨረሻ ላይ ከመድረሱ ጋር የሚያያይዘው ነገር አለ እንዴ? ይህንን አረና በውስጥ መሥመር እንዲያጣራልን እጠይቃለሁ፤ ይህ ቀልድም ቀላል ነገርም አይደለም!!
 • ልደቱ/ክህደቱ እያቀረበው ያለው የሽግግር መንግሥት ጥያቄና የማቋቋሚያ ሠነድ በአጠቃላይ ሰውየው እየሆነው ያለው ነገር ሁሉ የግሉን አቋም እንጂ ፓርቲውን እንደማይወክል የኢዴፓ መሪ በይፋ አስታውቋል፤ ልደቱ ቀድሞም ቢሆን ከወያኔ ጋር ምሥጢራዊ የሥራ ግንኙነት ነበረው ሲል ሐብታሙ አያሌው የሰጠውን ምስክርነት ከተቀበልን፣ ወያኔን ከማይቀረው የፖለቲካ ሞቱ ለመታደግ ዛሬ ተልእኮ ወስዶ ይሆን እንዴ ብለን ብንጠረጥር አይፈረድብንም፡፡ የተልእኮው ጉዳይ ዕውነት ሆነም አልሆነ፣ ልደቱ በአሁኑ ጊዜ እየደረሰበት ካለው የፖለቲካ ኪሣራ አንጻር እንኳን ወያኔን ራሱንም ለመታደግ የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም የሚገኘው፡፡ ልደቱ እንኳን ከዛሬው በ1997 ዓ.ም. ከደረሰበት የፖለቲካ ደዌ የማገገም ዕድሉም አነስተኛ ነው፡፡
 • የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ በያዘው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት፣ በምርጫው መራዘም ምክንያት የተፈጠረውንና እንዳይፈጠር የተሰጋውን የሕገመንግሥትና የሥልጣን ክፍተት የሚሞላ የሕገመንግሥት ትርጓሜ በቅርቡ ይዞ የሚመጣ መሆኑ፤ ይህም -ሂደቱም ሆነ ውጤቱ በግልጽ ለወያኔ ተጨማሪ መርዶ የሚሆን ይመስለኛል፤
ተጨማሪ ያንብቡ:  ለልጅ የሳቁለት፣ ለውሻ የሮጡለት፣ ለፖለቲከኛ ያጨበጨቡለት - ይገረም አለሙ

በነገራችን ላይ ባለፈው ሰሞን ለሦስት ቀናት፣ በቅርብ ጊዜው የኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ፣ የባለሙያዎችን ሀሳብና ግብዓት የመስማት ሂደት (ሂሪንግ) በሼራተን ሆቴል መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ለዘመናት ቸል ተብሎ እንዲያውም በጥርጣሬና ጥላቻ ሲገፋ የኖረውን የልጇቿን ሰብዓዊና ሙያዊ ወረት መንዝራ መጠቀም ጀመረች!! ያውም በትህትና፡፡ ጎበዝ ልጇቿም “በ50 ዓመት የአሜሪካ ቆይታዬ ዛሬ ገና ክብር አገኘሁ” እስኪሉ ድረስ የተፈላጊነትና የጠቃሚነት ጥሩ ስሜት ተሰማቸው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን!! ይህ በዴሞክራሲ ግንባታና በሕገመንግሥት እድገት ሂደት የማይናቅ እርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ለኛ ለተራ ዜጎችም አይን ገላጭ ክስተት ብቻ ሣይሆን ማዕከላዊ መስፈሪያና ማጣቀሻ (ቤንች ማርክ) ነበር፤ ይህን ካየን በኋላ፣ በመሰል ጉዳዮች ከዚህ ያነሰ አሠራር ለመቀበል ፈቃደኞች አንሆንም፡፡ ይህም ሁነትና ስኬት ለወያኔ ከባድ መርዶ እንደነበር ከዲጂታሎቻቸው ከፍተኛ ጫጫታ መረዳት አያስቸግርም፡፡

 

ክልላዊ፡

 • የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት በኦሮሚያ የክልሉንና የሐገሪቱን ሰላምና ደህንነት እየበጠበጡ ያሉ የኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ላይ ከብዙ ፈተናና ትዕግሥት በኋላ እርምጃ መውሰድ መጀመሩና ለጊዜው ወደ ጫካና ወደ ኬንያ ድንበር እንዲሸሹ ማድረጉ፣

በተለይ አንጻራዊ ሰላም በተገኘባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች የክልሉ መስተዳድር አርሶ አደሩንና በተለይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የጀመሩ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን “ድምጹን አጥፍቶ” እና ወጥሮ እየሠራና እያስፋፋ መገኘቱ፤ ይህም ለጽንፈኛ ወያኔና ለነጃዋር መርዶ ነው፤ እንደውም ወያኔና እነጃዋር የያዘ ይዟቸው እንጂ ይህ ጥረት ሥር እንዳይሰድ የበዛ አሻጥር በፈጸሙ ነበር፤

 • የአማራ ክልል መስተዳድር በክልሉ ካሉ ታጣቂዎች በተለይ ከፋኖ አባላት ጋር የደረሰው የሰላም ስምምነት፤ ታጣቂዎቹ መሣሪያቸውን አስረክበው ወደ ሰላማዊ ትግልና ኑሮ እንዲመለሱ መደረጉ፤ ለወያኔ ሌላ እጅግ ከባድ መርዶ!!
 • በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከአታካች ልፋትና ተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ የሕግ የበላይነት፣ ሰላምና ጸጥታን የማስፈን ሥራ ውጤት እያሳየ መምጣቱ፤ አሁን ለወያኔ “ሳይጠሩት አቤት ሳይልኩት ወዴት” የሚለው ማን ይሆን?
 • በሶማሌ ክልል አብዛኞቹ የቀልባሾች የትርምስ ፕሮጀክቶች መክሸፋቸው፣ የመልሶ ማቋቋም፣ የተቋም ግንባታና ሕዝብ-ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች መስፋፋት መጀመራቸው፤ የተበላሸውን የሕዝብ-ለሕዝብና የሕዝብ-ከመንግሥት ግንኙነት ለማከምና መተማመንን ለማጎልበት አበረታች ሥራዎች መጀመራቸው፤ በክልሉ ውስጥ ያሉ መልከ-ብዙ ክፉዎች በመጨረሻ ትንፋሻቸው የሚያደርጉት የለውጥ ጥረቱን የማደናቀፍ ሻጥር በቅርቡ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
 • በአፋር በልዩ ልዩ ምክንያት መሣሪያቸውን ሳያስቀምጡ የቆዩና በኃይል እርምጃ ተሰማርተው የክልሉንና የሐገሪቱን ፀጥታና አንድነት ሲያናጉ የቆዩ ኃይሎች፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ መከላከያ፣ የአፋር የሐገር ሽማግሌዎችና መስተዳድሩ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ዕርቅ ተቀብለው መሣሪያቸውን ማስቀመጣቸውና ወደሰላማዊ ኑሮ መመለሳቸው፤
ተጨማሪ ያንብቡ:  የዘመቻ ጥሪ! - ከአበበ ገላው

 

ትግራይ

 • ታስረው ከተፈቱ በኋላ በውጭ ሐገር (በጥናት፣ በአማካሪነት?) ለብዙ ጊዜ የቆዩት ስዬ አብርሃ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተከስተዋል፤ ከትግራይ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም (እኔ ያነበብኩት ትርጉምና የነአብርሃና የነአምዶም ምሥጋናም ትክክል ከሆነ) ለጽንፈኛ ወያኔ “ጌም ኦቮር” ማለታቸው፣ “ብርቱካንን ተዋት፣ ከአቢይና ከኢሳያስ ጋር መሳፈጣችሁን አቁሙ” ማለታቸው ብዙ-ብዙ ትርጉም ሊኖረው ይችላል፤
 • በትግራይ ብዙ ወረዳዎች ጸረ ወያኔ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መፈንዳቱና መስፋፋቱ (ፈንቅል)፤ ይህ ለትህነግ በጣም “የቸገረ ነገር” እየሆነባት ነው፡፡ አሁን የሚበዛውን ኃብቷን (ሰው፣ ገንዘብ፣ ቁሳቁስ፣ ጊዜ) ለማጥፋት የምትገደደው፣ ደጇ የደረሰውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለመጨፍለቅ ነው፡፡ በዚህ መጠመዷ ግድ ነው፡፡ በየክልሉ ያደራጀቻቸውንና አጀንዳ፣ ተልእኮ፣ ገንዘብና መሣሪያ እያስታጠቀች ለረብሻ የምታሰማራቸውን ተከፋዮች አሁን እንዳለፈው ከጎናቸው ሆና “አለሁላችሁ” ልትላቸው ይከብዳታል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መታየት የጀመረው አንጻራዊ የፀጥታ መረጋጋት ከሕወኃት አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ጋርስ የሚያገናኘው ነገር ይኖር ይሆን? እንደው በኖረ አያስብልም? መቼም በኮሮና ፍርሐት ብቻ ነው ግጭቶቹ የቀነሱት ሊባል አይችልም፡፡
 • በትግራይ ለፈነዳው ሕዝባዊ እምቢተኝነት የመንግሥት ሜዲያዎች ሰፊ ሽፋን መስጠታቸው፤
 • የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደምሒት)፣ ትግራይን ለመገንጠልና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከወያኔ የቀረበለትን የተባበሩኝ ጥሪና ሤራ በመቃወም የተወውን ትጥቅ ትግል ለመቀጠል ተመልሶ ወደ ኤርትራ በረሐ መግባቱን ሰምተናል፡፡
 • የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር የሆነው አቶ አብርሃ ደስታ ከሰዓታት በፊት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ የሚከተለውን መረጃ ለተከታታዮቹ አቀብሏል፡ ህወሓት አሁን ትግራይ ክልል ውስጥ ባለው መነሳሳት ስለደነገጠች በደሕንነት ክፍሏ በኩል ዋና ዋና የሚባሉ የተቃዋሚ መሪዎችን የመግደል ሐሳብ ላይ ተወያይታለች …”። ይህ የማይጠበቅ ነገር አይደለም፡፡ ሕወኃት የለየላት አምባገነን ነች፡፡ መግደል፣ ማፈን፣ መሰወር፣ ማሠር፣ ማግለል፣ ማሳደድና ማደህየት …፤ ወደ ስልጣን መውጫ፣ ሥልጣን ላይ መቆያ፣ እንደአሁኑ በመጨረሻው ሰዓትም ላይ ደግሞ የተጠያቂነትን ጊዜ ማስረዘሚያ ዋና መሣሪያዎቿ ሲሆኑ እየታየ ነው፡፡

 

በነገራችን ላይ የትግራይ ሕዝብ አሁን የጀመረውን የነጻነትና የአንድነት ትግል ኢትዮጵያውያን ስንናፍቀው የቆየ ብቻ ሣይሆን ባለን አቅም ሁሉ የምንደግፈው ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ የትግራይ ሕዝብ መነሳሳት የሚያስደነግጣቸውና የሚያስጨንቃቸው ወገኖች አሉ፡፡ እነዚህም ራሳቸው ጽንፈኛ ወያኔዎችና ተከፋዮቻቸው (ዲጂታል ወያኔ..)፣ ጀዋር-ልደቱና መንጋዎቻቸው፣ በየክልሉ የሕወኃትን ፊት እያዩና እጇንና ፊሽካዋን እየጠበቁ በብሔር-ብሔር ጨዋታ የሚረብሹ፣   እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰትራቴጂክ ጠላቶች ናቸው፡፡ እኔ ኢትዮጵያ ከነችግሩ በለውጥ ጅማሮ ላይ ትገኛለች ለማለት አልሽኮረመምም፡፡ የትግራይም ሕዝብም እንደሌሎቻችን የነጻነትና የአንድነት ጮራን ማየት አለበት፤ ይገባዋል፡፡ ለዚህም ትግሉን አስፍቶና አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ከጎኑ ነን፤ ይህ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህ ደረጃ ሁለት አጣዳፊ ሥራዎች ይታዩኛል፡፡

1ኛ) ለትግሉ በፍጥነት የተቀናጀ አመራር መስጠትና የሰከነ እንዲሆንና ሕዝባዊ መሠረት እንዲይዝ ማድረግ፤ ትግሉ በፍጥነት እንዲሳካና ታጋዮችና ሕዝቡ ከሚገባው በላይ ዋጋ እንዳይከፍሉ ማለት ነው፡፡ ተስፋ የቆረጠችው ጽንፈኛ ወያኔ የመጨረሻ ምሽጓ ላይ ሲከሰቱባት ምንም ከማድረግ እንደማትመለስ መታወቅ አለበት፡፡ እደግመዋለሁ፣ ምንም ከማድረግ አትመለስም፡፡ ስለዚህ እነ አረና፣ ትዴት፣ ብልጽግና፣ አሲምባ ዴፓ እና የትግራይ የነጻነትና የአንድነት ትግል አራማጅ አንጋፋና ታዋቂ ግለሰቦችና አክቲቪስቶች ሁሉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ግቦችን ያገናዘበ የፖለቲካና የጸጥታ ዕቅድ ነድፈው ይህንንም በጥሩ ጥምረትና ቅንጅት መፈጸም ይኖርባቸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም እንደ መንግሥት ተገቢ የድጋፍ ድርሻውን በጥንቃቄና በብልኃት ሊወጣ ይገባል፡፡ በተለይም የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ራሱ ከማክበርም (Respect) አልፎ በሌሎች ጉልበተኞች እንዳይጣሱ ጥበቃ (Protection) ማድረግ አለበት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦ! - ከሥርጉተ ሥላሴ

2ኛ) ለሕዝብ ደህንነትና ጤና የማይጠቅም የአምባገነኖች ራስ-አድን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታጋዮች ሲጣስ ትናንትና (3 ዓመት ሆነው?) በአይናችን አይተናል፡፡ የአሁኑ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግን (የአፈጻጸም ማነስ ቢታይበትም) ሕዝብና ሐገርን ለማዳን የወጣ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በተያዘው የሕዝባዊ እምቢተኛነት ትግል ሂደት በዋነኛነት ታጋዮችና በኋላም የትግራይ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ አስጊ እየሆነ በመጣው የኮሮና ቫይረስ እንዳይቀሰፉ መከላከልን ግምት ውስጥ ያስገባ የአደረጃጀትና የትግል ሥልት በፍጥነት ተቀርጾ ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ የተለመዱት ሰላማዊ ሰልፍ-ተኮር የእምቢተኝነት ትግል ሥልቶች በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በዝተውና ተደጋግመው ቢታዩ የጎን ጉዳታቸው እንዳይከፋ እሰጋለሁ፡፡ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥል፣ ነገር ግን ወቅቱን (የኮሮናን) ያገናዘበ የትግል ሥልት መጠቀም ይገባል፡፡ በጥልቅ አስበው ሲመክሩ በሁሉም ዘንድ ስምምነት የተደረገባቸውና የታወቁ ሥልቶችን ማግኘት አይከብድምና እዚህ ላይ እንበርታ፡፡ አክቲቪስት መለስ ብሥራት እንዳለው “በቀላሉ በውስጥ ፈርፍሮ/ቦርቡሮ የመጣል” አማራጭም መታየት አለበት፡፡ የመንግሥት ሜዲያዎች መስጠት የጀመሩት ሽፋን በጣም ጥሩ መሆኑንም መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡

 

መደምደሚያ

የሕወኃትን የመውደቅ ምልክቶች፣ መንስኤዎችና አንደምታዎች የሚያሳዩ በአጠቃላይ ህልውናዋ ከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቁን የሚያሳብቁ “የሚሊዮን ዶላር” ጥያቄዎቼ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነዚህ በፍሬ ነገር ደረጃ ከታዩ የማረጋገጫ ዓረፍተነገሮች (Statement) ሊሆኑም ይችላሉ፤

 • ይህን ሁሉ የሤራና የዕቅድ ክሽፈት፣ የጥንት ኔት ወርክና የአዲስ ተከፋይ/ጥምረት ክህደት ሕወኃት በየትኛው ትከሻዋ ትሸከመዋለች? ከበቀለ ገርባና ከልደቱ/ክህደቱ ሌላ ያልከዳት ማን አለ?
 • የምሽግን መፍረስ፣ የውስጥ ስንጥቃቱን መስፋት (ትግራይ ብልጽግና)፣ “የድጋፍ መሠረቷን” መደርመስና “የልጆቿን” የእምቢተኛነት ናዳ (ፈንቅል) እንኳን ቀፎዋን የቀረችው ትሀነግ/ሕወኃት ሌላ ማን ባለ ፈርጣማ ጡንቻ ሊቋቋመው ይችላል?
 • ሌላ-ሌላውን ተከፋይ ለጊዜው ብናቆየው፣ ለ30 ሺህ ዲጂታል ወያኔ፣ ቁጥራቸው ከዚህም ለሚልቀው ለየክልሉና ዞኑ የብሔር-ብሔር ጨዋታ ተከፋዮችስ ከዚህ በላይ ከየት ከሚመጣ ገቢና ገንዘብ ክፍያቸው ሊቀጥል ይችላል? እነ መሶበ፣ መሥፍን ኢንዱስትሪያልና በአጠቃላይ የኤፈርት ኩባንያዎች ደግሞ እንደ ድሮው ፕሮጀክት ማግበስበስ፣ የገበያ ሞኖፖሊ፣ ስንጥቅ ትርፍ፣ የብድር ቅድሚያ፣ የዕዳ እፎይታ፣ ቀረጥ ነጻና ግብር ስወራ ወዘተ አሁን የማይታሰብ ሆኖባቸዋል፡፡
 • ሕወኃት የተማመነችባት እመቤት (ግብጽ ..) እንኳን ለእርሷ ልትተርፍና ደጀን ልትሆናት፣ ለራሷም መሆን አቅቷት አንገቷን ስትደፋና ሰታዞርስ ወዴት፣ ወደማን ይጠጓል?
 • በዚህ ሁሉ ድቆሳና እንዲሁም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ድካም ላይ ጽንፈኛ ወያኔዎች የእርጅናውን፣ የበሽታውን፣ የመጠጡን፣ የሌላ-ሌላውን፣ የብልግናውን ሱስና የተስፋና ራዕይ አልባነቱን ድካም እንደምን ይችሉታል? አይችሉትም!!! ሕወኃት በጣር ላይ ሆናና እነርሱም ሞተው የወለደቻቸው ጭንጋፎችም (ባይቶና፣ ሳልሳዊ ወያኔ … ) የትም አይደርሱም፡፡ በቅርቡ ሲፍረከረኩ የምናያቸው ይመስለኛል፡፡ ባለቀ ሰዓት ለከሸፈ ዓላማ የተጠፈጠፉ ናቸው፤ ዕጣ ፈንታቸው ከሕወኃት ዕጣ ፈንታ ሊለይ ከቶ አይችልም፡፡

ታዲያ ሕወኃት የምትገኝበት ይህ ሁኔታና ጊዜ፣ “ጌም ኦቨር” (ጨዋታው አበቃ) አያስብልምን? የሕወኃት ጀምበር በደንብ እየጠለቀች ነው፡፡ የፖለቲካ ሞት ይባላል፡፡

 

መውጫ

በዚህ የነካ-ነካ ዳሰሳ ውስጥ ለራሴ በጣም የገረመኝን አንድ ጉዳይ አምኜ ልቋጭ፤ “መስከረም 30 እንገናኝ” ከሚለው የ”አለሁ-አልሞትኩም” ማቃሰቱ ውጭ፣ በነዚህ ኩነቶች ውስጥ የጃዋርን (ኮቪድ-87) ሚና/ቦታ ምናልባትም ከጥላው ውጪ ለማየት አለመቻሌ ነው፡፡ እንደው ልጁ ዛሬም በትናንት የጋንግስተር ቁመናው ላይ የሚገኝ የሚመስላቸው ሰዎች ሚናው እዚህ አለመጠቀሱ ግር ብሏቸው ጥያቄ ካነሱ ብዩ ነው፡፡ በኔ ግምገማ ጃዋርም በፖለቲካ አንጻር አሁን አለ የሚባል ነገር አይደለም፡፡ አሁን አንባቢ መፍረድ ይችላል፡፡ ሀሳቤን አስጨርሶኛላ! በነዚህ እይታዎቼ ተሳስቼ ብገኝም ብዙም አልደነግጥም፤ (እኔ ማን ነኝ ላለመሳሳት – መሳሳት ብርቅ ነው እንዴ?!) ይልቁንስ ተሰውረውብኝ ሳላያቸው የቀሩ ልዩ ሁኔታዎችን እንደገና ለማየትና ለመመርመር ዕድል ይሰጠኝ ይሆናል፤ እናም ከስህቴ ለመማር ወደኋላ አልልም፡፡

ፈጣሪ የሐገራችንን ደህንነትና የሕዝባችንን ጤና ይጠብቅልን!!

3 Comments

 1. አንድነት ይበልጣል በጣም ውብ ትንታኔ አስነበብከኝ። ደሥም አለኝ። እንደቃልህ ይሁን! ችግሩ ሟች ይዞ ይሞትልና አንተም እንዳልከው ወያኔን ከነሰንኮፏ ነቅሎ ለመጣል ንጹሓንም እንዳይጎዱ ለመታደግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በርታልኝ ወንድማለም፤ ከዋሻው ጫፍ ጭላንጭሉ ላይ ነን!

 2. General AbaDulla Gemeda and Worqneh Gebeyehu are still till this day in control of not only Oromo’s politics but they are also in control of all of Ethiopia’s politics , Abiy Ahmed is just General Abadulla Gemeda’s errand boy who does as ordered by General Abadulla Gemeda no questions asked.

  Abiy Ahmed and Lemma Megerssa are just spies for General Abadulla Gemeda as they were spies for Worqneh Gebeyehu , as they were spies for Getachew Assefa , as they were spies directly reporting to Meles Zenawi (Hailemariam Desalegn)….

  That is because initially Worqneh Gebeyehu was the man who first hired Lemma Megerssa in his first job as a spy decades ago . Lemma Megerssa had been associating with Oromos talking about the hardships Oromos face just to get Oromos trust ever since his first job as a spy , once Lemma Megerssa gets our Oromos trust he sells informations to the General Abadulla Gemeda as always. The trust we gave Abiy Ahmed in the last two years is costing us with our lives dearly now . The sad thing is they are the Prime Minister and the Defense Minister of Ethiopia and OLF foolishly returned from Eritrea to Ethiopia trusting the psychopath Abiy Ahmed will adhere to the promises he made to OLF in Eritrea two years ago, the promises never materialized yet till this day, actually Abiy Ahmed is keeping the promise he made to General Abadulla Gemeda only, he is not planning to keep the promise he made to nooneelse.

  Fenkel Tigraian youth are the only ones saying nice things about Abiy Ahmed now because they don’t know him as we do, they are getting fooled by Abiy Ahmed now as we were fooled by Abiy Ahmed two years ago.

 3. አይ ጊዜ ፣ አይ ዘመን፣ስንቱን አየነው፣ ስንቱንስ ሰማነው። ፈንቅል ብለው መጡ የትግራይ ልጆች? ለፈጣሪ ምን ይሳነዋል። አውራዎቹ በውሪዎቻቸው አማካኝነት ስለ መስከረም ሰላሳ ሲዶልቱ ከውስጥ ሊፈነቅልባቸው ሆነና ሊያርፈው? ኢትዮጵያ የራሷ አምላክ የላትም የሚሉ ምን ሊሉ ይሆን? አንድ መምህር የማነ የሚባል በዩቱብ ዘርግፎላቸዋል። እኔስ የጨነቀኝ የቱባዎቹ ባለስልጣናት ጉዳይ አይደለም እነሱን ተማምነው ላቶቻቸውን ውጭ ሲያሰጡ የነበሩትን እንጅ። ህሊናው ያላቸው ፌዴራሌዎች አምልጠዋል። መለዮ ብለናል ለነሱና ለፈንቅል ልጆች። ትእግስትና ምልጃ ትእቢትን ከወለደ ሌላ ምን ሊሆን ኖሯል ፈንቅል እንጂ? ፈጣሪ መላው ህዝባችንን ከኮረና መአትና ካላስፈላጊ እርስ በርስ ጦርነት ይጠብቅልን። አሜን።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.