አባይ ጉዱ ፈላ አባይ ፈላ ጉዱ
ሲወርድ ሲዋረድ የሰራው ጉድጓዱ
ያ የቦረቦረው ያረሰው ሁዳዱ
ታጠረ መሄጃው ማለፊያ መንገዱ
እጁን ተሸበበ እግሮቹን ታሰረ
ጉዞውን አቆመ ረጋ! ተከተረ፤
ዝንት እድሜ ዘመኑን እንዲያ እንዳልተጓዘ
አፈር ግሳንግሱን እንዳላጓጓዘ
ጊዜ ከዳውና ጉዱ ተዝረጥርጦ
ሁሌ እንደለመደው ላይጓዝ አምልጦ
አገሩን ቀዬው ሰፈሩን ሊያበራ
ከንቱነቱ ሊቀር መሆኑ ኪሳራ
በስሚንቶ ምርጊት በደንጊያ ድርድሮሽ
እንዳይሮጥ እንዳይሄድ ወደ ግብጥ እንዳይሸሽ
ወገቡን ተያዘ እግሮቹን ታሰረ
ጉዞው ጨነገፈ ረጋ! ተገተረ፤
ጥንቱን ድሮስ ቢሆን ነው ጠፍቶ እንጅ ጎበዝ
እርካቡን የሚረግጥ ልጓሙን የሚይዝ
ተረግዞ ተወልዶ እትብቱ ካለበት
ውሎ ላይሰነብት እግሩ ወዶ ሽሽት
እንዲያ መጣደፉ ቁልቁል መሽኮልኮሉ
ጎርምሶ ሸፍቶ ካገር መኮብለሉ፤
እንግዲህ አባይ ሆይ ይቆረጥ ተስፋህ
አጉዘህ ተጉዘህ ቅብጥ* ማደርህ
መሄጃ መንገድህ ማለፊያህ ይዘጋ
እጅ እግርህም ይረፍ መንፈስህም ይርጋ።
*ጥንታዊ የግብፅ ስም ነው፡፡
ምስጋና ይሁን ለዐባይ ሳተኖች!!
በላቸው ገላሁን ሚያዝያ ፯ ፳፻፬
ፒትስበርግ